በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን ማገልገል ታላቅ ደስታ አስገኝቶልኛል

ይሖዋን ማገልገል ታላቅ ደስታ አስገኝቶልኛል

ይሖዋን ማገልገል ታላቅ ደስታ አስገኝቶልኛል

ፍሬድ ራስክ እንደተናገሩት

መዝሙራዊው ዳዊት በ⁠መዝሙር 27:10 ላይ ‘አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ ይሖዋ ይቀበለኛል’ ብሎ የተናገረውን ሐሳብ እውነተኝነት የተረዳሁት ገና በልጅነቴ ነበር። ይህ ጥቅስ በሕይወቴ እንዴት እንደተፈጸመ እስቲ ላጫውታችሁ።

ያደግሁት በጆርጂያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ይኖር ከነበረው አያቴ ጋር ሲሆን እሱም የጥጥ እርሻ ነበረው። በዚያን ወቅት ማለትም በ1930ዎቹ ዓመታት በዓለም ላይ ታላቅ የኢኮኖሚ ድቀት ተከስቶ ነበር። አባቴ በእናቴና ጨቅላ በነበረው ታናሽ ወንድሜ ሞት ምክንያት ስሜቱ ክፉኛ ተጎድቶ ስለነበር ባለቤቱን በሞት ካጣው አያቴ ጋ ትቶኝ ለሥራ ራቅ ወዳለ ከተማ ሄደ። ከጊዜ በኋላ ከእሱ ጋር እንድኖር ጥረት አድርጎ የነበረ ቢሆንም ነገሮች አልተሳኩም።

የአያቴን ቤት የሚያስተዳድሩት ትላልቅ ሴቶች ልጆቹ ነበሩ። አያቴ ሃይማኖተኛ ባይሆንም እነሱ ግን አክራሪ የሳውዘርን ባፕቲስት እምነት ተከታዮች ነበሩ። አክስቶቼ እንደሚገርፉኝ ስለሚያስፈራሩኝ እሁድ እሁድ ወደ ቤተ ክርስቲያን እሄድ ነበር። በዚህም የተነሳ ከልጅነቴ ጀምሮ ለሃይማኖት ፍላጎት አልነበረኝም። ከዚህ ይልቅ መማርና በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ያስደስተኝ ነበር።

ሕይወቴን የለወጠ አጋጣሚ

በ1941 አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ አንድ አረጋዊና ባለቤቱ ወደ ቤታችን መጡ፤ ያን ጊዜ የ15 ዓመት ልጅ ነበርኩ። አረጋዊውም “አጎትህ ነኝ፤ ታልማጅ ራስክ እባላለሁ” በማለት ተዋወቀኝ። ከዚያ በፊት ስለ እሱ ሰምቼ አላውቅም፤ እሱና ባለቤቱ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። አጎቴ፣ አምላክ የሰው ልጆች በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ዓላማ እንዳለው ነገረን፤ ይህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይሰጥ ከነበረው ትምህርት ፈጽሞ የተለየ ነበር። አብዛኞቹ የቤተሰቡ አባላት እነዚህ ባልና ሚስት የተናገሩትን ነገር ያልተቀበሉት ከመሆኑም በላይ በጣም አጣጣሉት። ዳግመኛም ቤታችን ድርሽ እንዳይሉ ነገሯቸው። ሆኖም በሦስት ዓመት ብቻ የምትበልጠኝ አክስቴ ሜሪ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራሩ ጽሑፎችን ተቀበለቻቸው።

ብዙም ሳትቆይ ሜሪ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዳገኘች ተገነዘበች፤ ከዚያም በ1942 ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። ኢየሱስ “የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ” በማለት የተናገረው ነገር በሜሪ ሕይወት ውስጥ ተፈጽሟል። (ማቴ. 10:34-36) ሜሪ ከባድ የቤተሰብ ተቃውሞ አጋጥሟት ነበር። በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ ታደርግ የነበረችው የሜሪ ታላቅ እህት፣ ከከተማው ከንቲባ ጋር ተመሳጥራ አጎቴን ታልማጅን አሳሰረችው። ታልማጅ የተሰነዘረበት ክስ ‘ያለ ንግድ ፈቃድ ጽሑፎችን ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ይሸጣል’ የሚል ነበር። ከዚያም ጥፋተኛ ነህ ተብሎ ተፈረደበት።

በከተማችን የሚታተም አንድ ጋዜጣ እንደዘገበው ዳኛ የነበሩት የከተማው ከንቲባ በከተማው ፍርድ ቤት ለተሰበሰቡት ሰዎች “ይህ ሰው . . . እያሰራጨ ያለው ጽሑፍ ልክ እንደ መርዝ አደገኛ ነው” በማለት ተናግረዋል። አጎቴ ይግባኝ ጠይቆ ከሳሾቹን የረታ ቢሆንም ለአሥር ቀን ያህል እስር ቤት ቆይቷል።

አክስቴ ሜሪ ያደረገችልኝ እርዳታ

ሜሪ ስለ አዲሱ እምነቷ ለእኔ ብቻ በመናገር ሳትወሰን ለጎረቤቶቻችንም መመሥከር ጀመረች። ዘ ኒው ዎርልድ * የተባለ መጽሐፍ የተበረከተለትን አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ በምታስጠናበት ጊዜ አብሬያት እሄድ ነበር። የሰውየው ሚስት ባለቤቷ መጽሐፉን ቁጭ ብሎ ሲያነብ እንዳደረ ነገረችን። በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ ቸኩዬ መግባት ባልፈልግም የምማረው ነገር ትኩረቴን እየሳበው ነበር። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ሕዝቦች እንደሆኑ በዋነኝነት ያሳመነኝ የሚያስተምሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሳይሆን ሰዎች የሚያደርሱባቸው ተቃውሞ ነበር።

ለምሳሌ፣ አንድ ቀን እኔና ሜሪ የቲማቲም እርሻ ስንኮተኩት ቆይተን ወደ ቤት ስንመለስ የሜሪ እህቶች የሸክላ ማጫወቻዋንና የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የተቀዳባቸውን ሸክላዎች ጨምሮ ጽሑፎቿን በቆሻሻ ማቃጠያው ላይ አቃጥለውት አየን። ይህ ሁኔታ በጣም አናደደኝ፤ በዚህ ጊዜ አንደኛዋ አክስቴ በመመጻደቅ ስሜት “ላደረግነው ነገር ወደፊት ማመስገናችሁ አይቀርም” አለችን።

ሜሪ አዲሱን እምነቷን ለመተውና ለጎረቤቶቻችን መስበኳን ለማቆም ፈቃደኛ ባለመሆኗ በ1943 ከቤት ተባረረች። በዚያን ጊዜ የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ እንዲሁም አምላክ አፍቃሪና ሩኅሩኅ በመሆኑ ሰዎችን በእሳታማ ሲኦል እንደማያቃጥል ማወቄ ልቤን ነክቶት ነበር። በተጨማሪም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ተገኝቼ ባላውቅም ይሖዋ አፍቃሪ ድርጅት እንዳለው ተገንዝቤ ነበር።

አንድ ቀን ሣር እያጨድኩ እያለ አንድ መኪና በቀስታ ወደ እኔ መጣ፤ መኪናው ውስጥ ካሉት ሁለት ሰዎች መካከል አንደኛው ‘ፍሬድ ነህ?’ ብሎ ጠየቀኝ። ሰዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን በተረዳሁ ጊዜ “መኪና ውስጥ ልግባና አመቺ ወደሆነ ቦታ ሄደን እንነጋገር” አልኳቸው። እኔን እንዲያነጋግሩ የላከቻቸው ሜሪ ነበረች። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ሺልድ ቱትጂአን ሲሆን በዚያን ጊዜ ተጓዥ አገልጋይ ነበር፤ እሱም በወቅቱ የሚያስፈልገኝን ማበረታቻና መንፈሳዊ መመሪያ ሰጠኝ። የይሖዋ ምሥክሮችን ትምህርት ደግፌ መናገር በመጀመሬ የቤተሰቡ ተቃውሞ ወደ እኔ ዞረ።

ሜሪ ከምትኖርበት ከቨርጂኒያ ደብዳቤ በመጻፍ ይሖዋን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ ካደረግሁ ከእሷ ጋር መኖር እንደምችል ገለጸችልኝ። እኔም ወዲያውኑ እሷ ጋ ለመሄድ ወሰንኩ። ጥቅምት 1943 አንድ ዓርብ ምሽት፣ የሚያስፈልጉኝን አንዳንድ ነገሮች ሣጥን ውስጥ ከከተትኩ በኋላ ሣጥኑን ከቤታችን ትንሽ ራቅ ብሎ በሚገኝ አንድ ዛፍ ላይ አሰርኩት። ቅዳሜ ዕለት ሣጥኑን ካስቀመጥኩበት ወስጄ ማንም ሳያየኝ በጓሮ በኩል በጎረቤቶቻችን ግቢ በማለፍ ከሰፈሩ ከወጣሁ በኋላ ወደ ከተማ ሄድኩ። ከዚያም ወደ ሮአኖክ ከተማ በመሄድ ከሜሪ ጋር ተገናኘሁ፤ በወቅቱ ሜሪ የምትኖረው በኤድና ፋውልስ ቤት ውስጥ ነበር።

መንፈሳዊ እድገት ማድረግ፣ መጠመቅና ቤቴል መግባት

እንደ ጥንቷ ሊዲያ ሩኅሩኅ የነበረችው ኤድና ቅቡዕ ክርስቲያን ስትሆን በተከራየችው ትልቅ ቤት ውስጥ አክስቴ ሜሪ እንዲሁም የኤድና ወንድም ሚስት ከሁለት ሴት ልጆቿ ጋር ይኖራሉ። እነዚህ ሁለት ሴቶች ልጆች ማለትም ግላዲስ ግሪጎሪ እና ግሬስ ግሪጎሪ ከጊዜ በኋላ ሚስዮናዊ ሆነዋል። ግላዲስ በአሁኑ ጊዜ በ90ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ስትሆን በጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ በታማኝነት እያገለገለች ነው።

በኤድና ቤት ውስጥ ስኖር አዘውትሬ በስብሰባዎች እገኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ በአገልግሎት ሥልጠና አገኘሁ። የአምላክን ቃል ለማጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለመገኘት ነፃነት ማግኘቴ መንፈሳዊ ጥማቴን አረካልኝ። በመሆኑም ሰኔ 14, 1944 ተጠመቅኩ። ሜሪ፣ ግላዲስና ግሬስ በአቅኚነት ማገልገል የጀመሩ ሲሆን በቨርጂኒያ ሰሜናዊ ክፍል ተመደቡ። እነሱም በሊዝበርግ ጉባኤ እንዲቋቋም አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በ1946 መጀመሪያ አካባቢ እነሱ ካሉበት ብዙም በማይርቅ ስፍራ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። በዚያው ዓመት የበጋ ወቅት ላይ በክሊቭላንድ፣ ኦሃዮ ከነሐሴ 4-11 በተደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደዚያ ተጓዝን።

በዚያ ስብሰባ ላይ በድርጅቱ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ያገለግል የነበረው ወንድም ናታን ኖር በብሩክሊን የሚገኘውን ቤቴል ለማስፋፋት እንደታቀደ ተናገረ። ይህ ደግሞ አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶችን መገንባትንና ተጨማሪ የማተሚያ መሣሪያዎች መትከልን ያካትት ነበር። በመሆኑም በርካታ ወጣት ወንድሞች ያስፈልጉ ነበር። ቤቴል ገብቼ ይሖዋን ማገልገል እንዳለብኝ ወሰንኩ። ስለዚህ የቤቴል ማመልከቻ ፎርም ሞልቼ አስገባሁ፤ ከጥቂት ወራት በኋላ ማለትም ታኅሣሥ 1, 1946 ወደ ቤቴል ተጠራሁ።

የኅትመት ክፍል የበላይ ተመልካች የሆነው ማክስ ላርሰን ከአንድ ዓመት በኋላ እኔ ወደማገለግልበት የደብዳቤ ልውውጥ ክፍል መጥቶ አነጋገረኝ። እሱም ወደ አገልግሎት ዘርፍ እንደተዘዋወርኩ ነገረኝ። በዚህ ምድቤ ላይ በተለይም ደግሞ የአገልግሎት ዘርፍ የበላይ ተመልካች ከሆነው ከወንድም ቶማስ (በድ) ሱሊቫን ጋር በሠራሁባቸው ጊዜያት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ማድረግ ስለሚቻልበት መንገድና ስለ አምላክ ድርጅት አሠራር ብዙ ተምሬያለሁ።

አባቴ ብዙ ጊዜ ቤቴል መጥቶ ጠይቆኛል። የኋላ ኋላ ሃይማኖተኛ ሆኖ ነበር። በ1965 ለመጨረሻ ጊዜ መጥቶ በጠየቀኝ ጊዜ “አንተ መጥተህ ልትጠይቀኝ ትችላለህ፤ እኔ ግን ከአሁን በኋላ እዚህ መጥቼ በፍጹም አልጠይቅህም” ብሎኝ ነበር። ከመሞቱ በፊት ለተወሰኑ ጊዜያት ሄጄ ጠይቄው ነበር። አባቴ ወደ ሰማይ እንደሚሄድ እርግጠኛ ነበር። እኔ ደግሞ ይሖዋ በትንሣኤ እንደሚያስበው ተስፋ አደርጋለሁ፤ እንዲህ ከሆነ፣ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይዞ ከሞት የሚነሳው እሱ እንዳሰበው በሰማይ ሳይሆን ገነት በምትሆነው በዚህች ምድር ላይ ነው።

የማይረሱ የአውራጃ ስብሰባዎችና የግንባታ ሥራዎች

የአውራጃ ስብሰባዎች ምንጊዜም መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። በተለይ በ1950ዎቹ በኒው ዮርክ ያንኪ ስታዲየም የተደረጉት ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች በዚህ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በ1958 በያንኪ ስታዲየምና በፖሎ ግራውንድስ በተደረገው ስብሰባ ላይ ከ123 አገሮች የተውጣጡ 253,922 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። በዚያ ስብሰባ ላይ ያጋጠመኝን ነገር መቼም አልረሳውም። በአውራጃ ስብሰባው ጽሕፈት ቤት የሚያገለግሉትን ወንድሞች እየረዳሁ ሳለ ወንድም ኖር እየተጣደፈ ወደ እኔ መጣ። ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “ፍሬድ፣ በአቅራቢያችን በሚገኘው በተከራየነው አዳራሽ ውስጥ አቅኚዎቹ ሁሉ ተሰብስበው እየጠበቁን ነው፤ እኔ ደግሞ ምን እንደነካኝ እንጃ ንግግር የሚሰጥ ወንድም አልመደብኩም። እባክህ አሁኑኑ ልትሄድ ትችላለህ? በመንገድ ላይ ስትሄድ ባሰብከው አንድ ርዕስ ላይ ተመሥርተህ ጥሩ ንግግር ስጣቸው።” እኔም ወደዚያ እየሄድኩ ሳለ ደጋግሜ ጸለይኩ፤ እዚያ ስደርስ ትንፋሼ ቁርጥ ቁርጥ ይል ነበር።

በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኒው ዮርክ ሲቲ ያሉት ጉባኤዎች ቁጥር በእጅጉ ጨምሮ ስለነበር ለመንግሥት አዳራሽነት የተከራየናቸው መሰብሰቢያዎች በቂ አልነበሩም። ስለሆነም ምቹ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ለማግኘት ከሚደረገው ጥረት ጋር በተያያዘ ከ1970 እስከ 1990 ባሉት ዓመታት በማንሃተን ሦስት ሕንጻዎች ተገዝተው በአዲስ መልክ ተገነቡ። እኔም የዚህ ፕሮጀክት የግንባታ ኮሚቴዎች ሊቀመንበር የነበርኩ ሲሆን ጉባኤዎች የግንባታ ሥራውን በገንዘብ ለመደገፍና ሕንጻዎቹን ቶሎ ለማጠናቀቅ የሚያደርጉትን ጥረት ይሖዋ እንዴት አብዝቶ እንደባረከላቸው የሚያሳዩ አስደሳች ትዝታዎች አሉኝ፤ እነዚህ ሕንጻዎች ዛሬም የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

በሕይወቴ ውስጥ የተከሰቱ ለውጦች

በ1957 አንድ ቀን፣ ከቤቴል ቤት ወደ ማተሚያ ቤት እየሄድኩ ሳለ ዝናብ መጣል ጀመረ። በዚህ ጊዜ ወርቃማ ፀጉር ያላት አንዲት ቆንጆ አዲስ ቤቴላዊት ከፊቴ ስትሄድ ተመለከትሁ። ዣንጥላ ስላልያዘች አስጠለልኳት። ከማርጅሪ ጋር የተዋወቅነው በዚህ ሁኔታ ነበር፤ በ1960 ከተጋባንበት ጊዜ ጀምሮ በክፉም ሆነ በደጉ ጊዜ ይሖዋን በደስታ ስናገለግል ቆይተናል። ሃምሳኛውን የጋብቻ በዓላችንን መስከረም 2010 አክብረናል።

ከጫጉላ ሽርሽር እንደተመለስን፣ ወንድም ኖር የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ ሆኜ እንደተመደብኩ ነገረኝ። ይህ እንዴት ያለ ልዩ መብት ነበር! ከ1961 እስከ 1965 ባሉት ዓመታት በነበሩት አምስት ክፍሎች ውስጥ ሥልጠና የተሰጣቸው አብዛኞቹ ተማሪዎች የቅርንጫፍ ቢሮ አባላት ሲሆኑ ስለ ቅርንጫፍ ቢሮ አደረጃጀት ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ ሥልጠናም ተሰጥቷቸዋል። በ1965 ትምህርቱ እንደ ቀድሞው ወደ አምስት ወር እንዲያጥርና ሚስዮናውያንን በማሠልጠን ላይ እንዲያተኩር ተደረገ።

በ1972 ከጊልያድ ተቀይሬ ደብዳቤ ልውውጥ ክፍል ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። የተለያዩ ጥያቄዎችን ለመመለስና ችግሮችን ለመፍታት የማደርገው ምርምር የአምላክ ቃል የሚያስተምረውን ነገር የበለጠ እንድገነዘብ እንዲሁም ሌሎችን በምረዳበት ጊዜ ላቅ ያሉትን የአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምችል ይበልጥ እንዳስተውል ረድቶኛል።

ከዚያም በ1987 አዲስ በተቋቋመው የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት ክፍል ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ። በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግሉት ሽማግሌዎች ደምን በተመለከተ ያለንን ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋም ለሐኪሞች፣ ለዳኞችና ለማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኞች ማስረዳት ስለሚችሉበት መንገድ ሥልጠና ለመስጠት ሴሚናሮች ይዘጋጁ ነበር። በወቅቱ ያጋጥመን የነበረው ከባድ ችግር ሐኪሞች ያለ ወላጆች ፈቃድ ለይሖዋ ምሥክር ልጆች ደም መስጠታቸው ሲሆን ይህን ለማድረግም ብዙውን ጊዜ ከፍርድ ቤት ፈቃድ ያገኙ ነበር።

ብዙዎቹ ሐኪሞች በደም ምትክ ስለሚሰጡት አማራጭ ሕክምናዎች ሐሳብ ስንሰጣቸው እነዚህ አማራጭ ሕክምናዎች እንደማይገኙ ወይም ደግሞ በጣም ውድ እንደሆኑ ይገልጹልን ነበር። አንድ የቀዶ ሕክምና ዶክተር ይህን ዓይነት ሐሳብ ሲያቀርብልኝ ብዙውን ጊዜ “እስቲ እጅህን ዘርጋ” እለዋለሁ፤ ከዚያም እጁን ሲዘረጋ “በደም ምትክ ከሚሰጡት አማራጭ ሕክምናዎች ሁሉ የተሻለ ነገር ማከናወን የሚችለው እጅህ ነው” እለዋለሁ። እንዲህ ዓይነቱ የአድናቆት አስተያየት በሚገባ የሚያውቀውን ነገር ይኸውም የቀዶ ሕክምና መሣሪያዎቹን በጥንቃቄ መጠቀሙ ብዙ ደም እንዳይፈስ የሚረዳ መሆኑን እንዲያስታውስ ያደርገዋል።

ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት ሐኪሞችንና ዳኞችን ለማሠልጠን የተደረገውን ይህን ጥረት ይሖዋ በእጅጉ ባርኮታል። እነዚህ ሰዎች አቋማችንን ይበልጥ እየተረዱ ሲመጡ አመለካከታቸው የዚያኑ ያህል ተቀይሯል። በተጨማሪም በሕክምናው ዘርፍ የተደረጉ ምርምሮች በደም ምትክ የሚሰጡ አማራጭ ሕክምናዎች ውጤታማ መሆናቸውን እንዳረጋገጡ የተገነዘቡ ከመሆኑም ሌላ በርካታ ዶክተሮችና ሆስፒታሎች እንዲህ ዓይነቶቹን ሕክምናዎች ለመስጠት ፈቃደኞች ሆነዋል።

ከ1996 ጀምሮ እኔና ማርጅሪ ከብሩክሊን በስተምሥራቅ 110 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘውና በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ ባለው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ውስጥ እያገለገልን ነው። በዚያም ለተወሰነ ጊዜ በአገልግሎት ዘርፍ ስሠራ ከቆየሁ በኋላ የቅርንጫፍ ቢሮ አባላትንና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን በማስተማሩ ሥራ ለጥቂት ጊዜ ተካፍያለሁ። ባለፉት 12 ዓመታት ደግሞ በድጋሚ የደብዳቤ ልውውጥ ክፍል የበላይ ተመልካች ሆኜ እያገለገልኩ ነው፤ ይህ ክፍል ከብሩክሊን ወደ ፓተርሰን ተዛውሯል።

የዕድሜ መግፋት የሚያስከትላቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች

ዕድሜዬ ወደ 80ዎቹ አጋማሽ ስለደረሰ በቤቴል ያለኝን ኃላፊነት መወጣት እየከበደኝ መጥቷል። ከአሥር ዓመት በላይ ከካንሰር ጋር ስታገል ቆይቻለሁ። ይሖዋ ዕድሜ እንደጨመረለት እንደ ሕዝቅያስ እንደሆንኩ ይሰማኛል። (ኢሳ. 38:5) የባለቤቴ ጤንነትም ቢሆን እያሽቆለቆለ ነው፤ ያለባትን የኦልዛይመር በሽታ መቋቋም እንድትችል የተቻለንን ያህል እየጣርን ነው። ማርጅሪ ብቃት ያላት የይሖዋ አገልጋይ ከመሆኗም ሌላ ለወጣቶች መካሪ፣ ለእኔ ደግሞ ታማኝ ረዳትና ጥሩ ወዳጅ ናት። ጎበዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪና ግሩም የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ የነበረች ሲሆን ብዙዎቹ መንፈሳዊ ልጆቻችን አሁንም ድረስ ይጠይቁናል።

አክስቴ ሜሪ መጋቢት 2010 በ87 ዓመቷ አረፈች። ሜሪ የአምላክን ቃል ጥሩ አድርጋ ታስተምር የነበረ ከመሆኑም ባሻገር ሌሎች ከእውነተኛው አምልኮ ጎን እንዲቆሙ ረድታለች። ለበርካታ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተካፍላለች። የአምላክን ቃል እውነት እንዳውቅና አፍቃሪ የሆነው አምላካችንን ይሖዋን እንደ እሷ እንዳገለግል ስለረዳችኝ በእጅጉ አመስጋኝ ነኝ። ሜሪ፣ ቀደም ሲል በእስራኤል ሚስዮናዊ ሆኖ ያገለግል ከነበረው ባለቤቷ ጎን ተቀብራለች። ይሖዋ እነዚህን ባልና ሚስት በትንሣኤ እንደሚያስባቸው እርግጠኛ ነኝ።

ይሖዋን ያገለገልኩባቸውን 67 ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ ከይሖዋ ላገኘኋቸው የተትረፈረፉ በረከቶች አመስጋኝ ነኝ። ምንጊዜም የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ እጅግ ያስደስተኛል! በይሖዋ ጸጋ በመታመን ልጁ እንደሚከተለው በማለት የተናገረውን ሽልማት እንደማገኝ ሙሉ ተስፋ አለኝ፦ “ስለ ስሜ ሲል ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ ብዙ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለም ሕይወትም ይወርሳል።”​ማቴ. 19:29

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 በ1942 የተዘጋጀ ሲሆን አሁን ግን መታተም አቁሟል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጆርጂያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው በአያቴ የጥጥ እርሻ ውስጥ በ1928

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አክስቴ ሜሪና አጎቴ ታልማጅ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሜሪ፣ ግላዲስ እና ግሬስ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰኔ 14, 1944 ስጠመቅ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቤቴል ውስጥ በአገልግሎት ዘርፍ ሳገለግል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1958 በያንኪ ስታዲየም በተደረገው የብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ከሜሪ ጋር

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከማርጅሪ ጋር በሠርጋችን ቀን

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ2008 ከማርጅሪ ጋር