በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወትንና ሰላምን እንድታገኙ እንደ መንፈስ ፈቃድ ተመላለሱ

ሕይወትንና ሰላምን እንድታገኙ እንደ መንፈስ ፈቃድ ተመላለሱ

ሕይወትንና ሰላምን እንድታገኙ እንደ መንፈስ ፈቃድ ተመላለሱ

“እንደ ሥጋ ፈቃድ ሳይሆን እንደ መንፈስ ፈቃድ [ተመላለሱ]።”​—ሮም 8:4

1, 2. (ሀ) አንድ ሰው ሲያሽከረክር ትኩረቱ የሚከፋፈል ከሆነ ምን አስከፊ አደጋ ሊደርስ ይችላል? (ለ) በመንፈሳዊ ሁኔታ ትኩረቱ የተከፋፈለ ሰው ምን አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል?

“ትኩረትን ሰብስቦ አለማሽከርከር እንደ ወረርሽኝ ተስፋፍቷል፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ከዓመት ወደ ዓመት እየተባባሰ የመጣ ይመስላል።” ይህን የተናገሩት የዩናይትድ ስቴትስ የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ናቸው። ሹፌሮች፣ ተቀዳሚ ተግባራቸው ከሆነው በትኩረት ከማሽከርከር እንዲዘናጉ ከሚያደርጓቸው ነገሮች አንዱ የሞባይል ስልክ ነው። በአንድ ወቅት ተካሄዶ በነበረ ጥናት ላይ ቃለ መጠየቅ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የሞባይል ስልክ እየተጠቀመ በሚያሽከረክር ግለሰብ እንደተገጩ አሊያም ከመገጨት ለጥቂት እንደተረፉ ተናግረዋል። እያሽከረከሩ ሌሎች ሥራዎችን ማከናወን ጊዜ የሚቆጥብ ቢመስልም ውጤቱ ግን አስከፊ ሊሆን ይችላል።

2 ከመንፈሳዊ ደኅንነታችን ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ትኩረቱ በተለያዩ ነገሮች የተሰረቀ አሽከርካሪ የአደጋ ጠቋሚ ምልክቶችን ማስተዋል እንደማይችል ሁሉ በመንፈሳዊ ሁኔታ ትኩረቱ የተከፋፈለ ሰውም በቀላሉ ለአደጋ ሊጋለጥ ይችላል። ከክርስቲያናዊ ጎዳና እንዲሁም ከቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ቀስ በቀስ እየራቅን የምንሄድ ከሆነ አደጋ ደርሶበት እንደተሰባበረ መርከብ እምነታችን ሊጠፋ ይችላል። (1 ጢሞ. 1:18, 19) ሐዋርያው ጳውሎስ “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሞት ያስከትላል፤ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ግን ሕይወትና ሰላም ያስገኛል” በማለት በሮም ለሚገኙ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ ባስጠነቀቃቸው ወቅት ስለዚህ አደጋ እየጠቆማቸው ነበር። (ሮም 8:6) ለመሆኑ ጳውሎስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? “በሥጋዊ ነገሮች ላይ” ማተኮር ትተን “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” የምንችለውስ እንዴት ነው?

“ኩነኔ የለባቸውም”

3, 4. (ሀ) ጳውሎስ በውስጡ ምን ዓይነት ትግል እንዳለበት ጽፏል? (ለ) የጳውሎስ ሁኔታ የእኛን ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው?

3 ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እሱ ራሱ በሕይወቱ ስላጋጠመው ትግል ይኸውም በአካል ክፍሎቹና በአእምሮው መካከል ስለነበረው ውጊያ ጠቅሷል። (ሮም 7:21-23ን አንብብ።) ጳውሎስ ይህን የተናገረው የኃጢአት ሸክም ከአቅሙ በላይ የሆነበት ይመስል ሰበብ አስባብ ለመደርደር አሊያም ራሱን ለመኮነን አይደለም። ጳውሎስ “የአሕዛብ ሐዋርያ” እንዲሆን የተመረጠና በመንፈስ የተቀባ ጎልማሳ ክርስቲያን ነበር። (ሮም 1:1፤ 11:13) ታዲያ ጳውሎስ በውስጡ ስለሚካሄደው ትግል የጻፈው ለምንድን ነው?

4 ጳውሎስ በራሱ ጥረት፣ የሚመኘውን ያህል የአምላክን ፈቃድ ማድረግ እንደማይችል አምኖ መቀበሉ ነበር። ይህ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል” በማለት ተናግሯል። (ሮም 3:23) ጳውሎስ የአዳም ዘር እንደመሆኑ መጠን ኃጢአት፣ ፍጽምና በጎደለው ሥጋ ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ ነፃ አልነበረም። የእኛም ሁኔታ ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም፤ ሁላችንም ፍጽምና የጎደለን በመሆኑ ልክ እንደ ጳውሎስ በየዕለቱ ትግል እናደርጋለን። በዚያ ላይ ደግሞ ትኩረታችንን በመስረቅ ‘ወደ ሕይወት ከሚወስደው ቀጭን መንገድ’ እንድንወጣ ሊያደርጉን የሚችሉ በርካታ የሚያዘናጉ ነገሮች ያጋጥሙናል። (ማቴ. 7:14) ይሁን እንጂ፣ ጳውሎስ በትግሉ ማሸነፍ እንደቻለ ሁሉ እኛም ትግሉን በድል መወጣት እንችላለን።

5. ጳውሎስ እርዳታና እፎይታ ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው?

5 ጳውሎስ “ማን ይታደገኛል?” በማለት ከጠየቀ በኋላ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን!” ሲል መልሱን ተናግሯል። (ሮም 7:24, 25) ከዚያም “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት” ስላላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች መናገር ጀመረ። (ሮም 8:1, 2ን አንብብ።) እነዚህ ክርስቲያኖች ‘ከክርስቶስ ጋር እንዲወርሱ’ ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀብሏቸዋል። (ሮም 8:14-17) የአምላክ መንፈስ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ካላቸው እምነት ጋር ተዳምሮ ጳውሎስ የገለጸውን ትግል በድል እንዲወጡ አስችሏቸዋል፤ በዚህም የተነሳ “ኩነኔ የለባቸውም።” “ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ” ወጥተዋል።

6. ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ጳውሎስ ለጻፈው ሐሳብ ትኩረት መስጠት ያለባቸው ለምንድን ነው?

6 ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ቢሆንም ስለ አምላክ መንፈስና ስለ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የተናገረው ሐሳብ ተስፋቸው የትም ይሁን የት ለሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ይጠቅማል። በመሆኑም ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ ተመርቶ የጻፈውን ይህን ምክር ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች መረዳታቸውና ከምክሩ ለመጠቀም ጥረት ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው።

አምላክ ‘የሥጋን ኃጢአት የኮነነው’ እንዴት ነው?

7, 8. (ሀ) “ሕጉ ከሥጋ ባሕርይ የተነሳ ደካማ” ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ በመንፈሱና በቤዛው አማካኝነት ምን ነገር አከናውኗል?

7 ጳውሎስ ኃጢአት ፍጹም ባልሆነው ሥጋችን ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በ⁠ሮም ምዕራፍ 7 ላይ ተናግሯል። በሮም ምዕራፍ 8 ላይ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ስላለው ኃይል ገልጿል። ሐዋርያው፣ ክርስቲያኖች ኃጢአት ከሚያሳድረው ተጽዕኖ ጋር በሚያደርጉት ትግል የአምላክ መንፈስ ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት እንደሆነ አብራርቷል፤ ይህ መንፈስ ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲኖሩና የእሱን ሞገስ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። አምላክ፣ የሙሴ ሕግ ማድረግ ያልቻለውን ነገር በመንፈሱና በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት እንደፈጸመ ጳውሎስ ተናግሯል።

8 በውስጡ ብዙ ትእዛዛትን ያቀፈው የሙሴ ሕግ ኃጢአተኞችን ይኮንናል። ከዚህም በተጨማሪ በሕጉ ሥር የሚያገለግሉት የእስራኤል ሊቀ ካህናት ፍጹማን ያልነበሩ ሲሆን የሚያቀርቡት መሥዋዕትም ኃጢአትን ለማስወገድ አይችልም ነበር። በመሆኑም “ሕጉ ከሥጋ ባሕርይ የተነሳ ደካማ” ሊሆን ችሏል። ይሁንና አምላክ “የገዛ ራሱን ልጅ በኃጢአተኛ ሥጋ አምሳል በመላክ” እና ቤዛ እንዲሆን በማድረግ “የሥጋን ኃጢአት ኮንኗል”፤ ይህም ሕጉ “ሊፈጽመው ያልቻለውን ነገር” ለማከናወን አስችሏል። በዚህም የተነሳ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባላቸው እምነት መሠረት ጻድቃን ተብለው ለመጠራት ችለዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች “እንደ ሥጋ ፈቃድ ሳይሆን እንደ መንፈስ ፈቃድ” እንዲመላለሱ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። (ሮም 8:3, 4ን አንብብ።) በእርግጥም “የሕይወትን አክሊል” ማግኘት ከፈለጉ ምድራዊ ሕይወታቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ ይህን ማሳሰቢያ በታማኝነት መከተል ይኖርባቸዋል።​—ራእይ 2:10

9. በ⁠ሮም 8:2 ላይ የተጠቀሰው “ሕግ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው?

9 ጳውሎስ ስለ ሙሴ ‘ሕግ’ ከመናገሩም በተጨማሪ “የዚያ መንፈስ ሕግ” እንዲሁም ‘የኃጢአትና የሞት ሕግ’ የሚሉ አባባሎችን ተጠቅሟል። (ሮም 8:2) እነዚህ ሕጎች ምንድን ናቸው? እዚህ ላይ የተጠቀሰው “ሕግ” የሚለው ቃል በሙሴ ሕግ ውስጥ ያሉትን ዓይነት ደንቦች አያመለክትም። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል፦ “እዚህ ላይ ሕግ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል፣ ሰዎችን እንደ ሕግ እየመራ ጥሩ ወይም መጥፎ ነገሮችን እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸውን በውስጣቸው ያለ መመሪያ የሚያመለክት ነው። ቃሉ አንድ ሰው የሕይወቱ መመሪያ አድርጎ የሚጠቀምበትን ነገር ለማመልከትም ያገለግላል።”

10. ለኃጢአትና ለሞት ሕግ የተገዛነው እንዴት ነው?

10 ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) ሁላችንም የአዳም ዘር እንደመሆናችን መጠን ለኃጢአትና ለሞት ሕግ ተገዝተናል። በመሆኑም ኃጢአተኛው ሥጋችን አምላክን የሚያሳዝኑ ነገሮችን እንድናደርግ ሁልጊዜ ይገፋፋናል፤ እነዚህ ነገሮች ደግሞ የሚመሩት ወደ ሞት ነው። ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ያሉትን ድርጊቶችና ባሕርያት “የሥጋ ሥራዎች” ሲል ጠርቷቸዋል። አክሎም “እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽሙ የአምላክን መንግሥት አይወርሱም” ብሏል። (ገላ. 5:19-21) በሌላ አባባል እነዚህ ሰዎች እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚመላለሱ ናቸው። (ሮም 8:4) ‘ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሚያንቀሳቅሳቸው’ እና ‘ሕይወታቸውን የሚመሩበት’ መመሪያ ሙሉ በሙሉ ሥጋዊ ነው። ለመሆኑ እንደ ሥጋ ፈቃድ እየተመላለሱ እንደሆኑ ተደርገው የሚቆጠሩት ዝሙት የሚፈጽሙ፣ ጣዖት የሚያመልኩ፣ በመናፍስታዊ ድርጊት የሚካፈሉ ወይም እነዚህን የመሳሰሉ ከባድ ኃጢአቶችን የሚሠሩ ሰዎች ብቻ ናቸው? አይደለም፣ አንዳንዶች ተራ የባሕርይ ችግር አድርገው የሚመለከቷቸው እንደ ቅናት፣ በቁጣ መገንፈል፣ የከረረ ጭቅጭቅና ምቀኝነት የመሳሰሉ ባሕርያትም ከሥጋ ሥራዎች የሚፈረጁ ናቸው። ታዲያ እንደ ሥጋ ፈቃድ ከመመላለስ ራሴን ሙሉ በሙሉ ነፃ አውጥቻለሁ ብሎ መናገር የሚችል ሰው ይኖራል?

11, 12. ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ እንድንሆን ይሖዋ ምን ዝግጅት አድርጎልናል? የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

11 ይሖዋ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ የምንሆንበትን መንገድ ስላመቻቸልን በጣም ደስተኞች ነን! ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” አምላክ ላሳየን ፍቅር ምላሽ በመስጠትና በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት እንዳለን በተግባር በማሳየት የወረስነው ኃጢአት ካስከተለብን ኩነኔ ነፃ መውጣት እንችላለን። (ዮሐ. 3:16-18) በመሆኑም እኛም እንደ ጳውሎስ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን!” ለማለት እንደምንገፋፋ ምንም ጥርጥር የለውም።

12 ያለንበት ሁኔታ ከከባድ በሽታ ለመዳን ከሚደረግ ጥረት ጋር ይመሳሰላል። አንድ ሰው ከበሽታው ሙሉ በሙሉ ለመዳን ከፈለገ ሐኪሙ የሚያዘውን ማድረግ ይኖርበታል። በቤዛው ላይ እምነት እንዳለን በተግባር ማሳየታችን ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ ሊያወጣን ቢችልም ዛሬም ጭምር ፍጽምና የጎደለንና ኃጢአተኞች ነን። ጥሩ መንፈሳዊ ጤንነት እንዲኖረን እንዲሁም የአምላክን ሞገስና በረከት እንድናገኝ ከዚህ የበለጠ ነገር ያስፈልገናል። ጳውሎስ ‘የሕጉን የጽድቅ መሥፈርት’ ለመፈጸም እንደ መንፈስ ፈቃድ መመላለስ እንደሚኖርብንም ጠቅሷል።

እንደ መንፈስ ፈቃድ መመላለስ የሚቻለው እንዴት ነው?

13. እንደ መንፈስ ፈቃድ መመላለስ ሲባል ምን ማለት ነው?

13 ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረው ‘መመላለስ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንድ ቦታ ወይም ግብ ላይ ለመድረስ መገስገስን ያመለክታል። በመሆኑም እንደ መንፈስ ፈቃድ ለመመላለስ ከፈለግን የማያቋርጥ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ይኖርብናል፤ እንዲህ ሲባል ግን ፍጹም እንሆናለን ማለት አይደለም። (1 ጢሞ. 4:15) በየዕለቱ መንፈሱ የሚሰጠንን አመራር ተከትለን ለመመላለስ ወይም ሕይወታችንን ለመምራት አቅማችን የፈቀደውን ያህል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ‘በመንፈስ መመላለስ’ የአምላክን ሞገስ ያስገኛል።​—ገላ. 5:16

14. “እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ ሰዎች” ምን ዓይነት ዝንባሌ አላቸው?

14 በመቀጠል ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አእምሯቸው ተቃራኒ በሆኑ ነገሮች ላይ ስላተኮረ ሁለት ዓይነት ሰዎች ተናግሯል። (ሮም 8:5ን አንብብ።) እዚህ ላይ የተጠቀሰው ሥጋ የሚለው ቃል የሰውን አካል ብቻ የሚያመለክት አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሥጋ” የሚለው ቃል ፍጹም ያልሆነውንና ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ ያለውን ሥጋችንን ለማመልከትም ይሠራበታል። ይህ ዝንባሌ፣ ጳውሎስ ቀደም ሲል ለጠቀሰው በሥጋችንና በአእምሯችን መካከል ለሚካሄደው ትግል መንስኤ ነው። ከጳውሎስ በተቃራኒ “እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ ሰዎች” ሊታገሉ ቀርቶ ውጊያውን የመጀመር ሐሳብ እንኳ የላቸውም። አምላክ ከእነሱ ምን እንደሚጠብቅ ከማሰብና እሱ የሚሰጣቸውን እርዳታ ከመቀበል ይልቅ “አእምሯቸው ሙሉ በሙሉ በሥጋዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ” እንዲሆን ያደርጋሉ። ብዙ ጊዜ ትኩረታቸው ያረፈው ምቾታቸውን በመጠበቅና የሥጋቸውን ምኞት በማርካት ላይ ነው። “እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን አእምሯቸው ሙሉ በሙሉ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ” ይኸውም በመንፈሳዊ ዝግጅቶችና እንቅስቃሴዎች ላይ ያተኮረ እንዲሆን ያደርጋሉ።

15, 16. (ሀ) አንድ ሰው አእምሮው በአንድ ነገር ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲያተኩር ማድረጉ በዝንባሌው ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች አእምሯቸው ትኩረት ስላደረገበት ነገር ምን ማለት እንችላለን?

15 ሮም 8:6ን አንብብ። አንድ ሰው ጥሩም ይሁን መጥፎ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ አእምሮው በዚያ ነገር ላይ እንዲያተኩር ማድረግ አለበት። ሁልጊዜ አእምሯቸው በሥጋዊ ነገር ላይ እንዲያተኩር የሚያደርጉ ሰዎች ውሎ አድሮ አመለካከታቸውና ዝንባሌያቸው ሙሉ በሙሉ በሥጋዊ ነገሮች ላይ ያነጣጠረ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ስሜታቸው፣ ፍላጎታቸውና ዝንባሌያቸው ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያተኮረ ይሆናል።

16 በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ትኩረታቸው ያረፈው በምን ላይ ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በዓለም ያለው ነገር ሁሉ ይኸውም የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመነጭ አይደለም።” (1 ዮሐ. 2:16) ሴሰኝነት፣ ዝና እንዲሁም ቁሳዊ ነገሮች ከእነዚህ ምኞቶች መካከል የሚፈረጁ ናቸው። መጻሕፍት፣ መጽሔቶች፣ ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እንዲሁም ኢንተርኔት እነዚህን ምኞቶች የሚያቀጣጥሉ ነገሮችን በገፍ ያቀርባሉ፤ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት የብዙ ሰው አእምሮ ያተኮረው በእነዚህ ምኞቶች ላይ ስለሆነና እነዚህን ነገሮች በጣም ስለሚፈልጓቸው ነው። ይሁንና “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሞት ያስከትላል”፤ አዎን፣ በአሁኑ ጊዜ በመንፈሳዊ በቅርቡ ደግሞ ቃል በቃል ሞት ያስከትላል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? “ምክንያቱም ሥጋ ለአምላክ ሕግ ስለማይገዛና ደግሞም ሊገዛ ስለማይችል በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር የአምላክ ጠላት ያደርጋል። ስለሆነም ከሥጋ ፈቃድ ጋር ተስማምተው የሚኖሩ አምላክን ማስደሰት አይችሉም።”​—ሮም 8:7, 8

17, 18. በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋችን ምን በረከት ያስገኝልናል?

17 በሌላ በኩል ደግሞ ‘በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሕይወትና ሰላም ያስገኛል’፤ ይኸውም ወደፊት የዘላለም ሕይወት የምናገኝ ከመሆኑም ሌላ በአሁኑ ጊዜ ውስጣዊ ሰላምና ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ይኖረናል። ታዲያ “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” የምንችለው እንዴት ነው? አእምሯችን ምንጊዜም በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ብሎም መንፈሳዊ ዝንባሌና አመለካከት በማዳበር ነው። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ አእምሯችን የሚያተኩረው ‘ለአምላክ ሕግ በመገዛት’ እና ከእሱ አስተሳሰብ ጋር ‘ተስማምቶ በመኖር’ ላይ ይሆናል። ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ምን ውሳኔ ማድረግ እንዳለብን ግራ አንጋባም። ከዚህ ይልቅ ከመንፈስ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ትክክለኛ ውሳኔ እናደርጋለን።

18 እንግዲያው አእምሯችን ሙሉ በሙሉ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረጋችን ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ ‘አእምሯችን ለሥራ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ’ ያስፈልገናል፤ በሌላ አባባል አዘውትሮ መጸለይን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማጥናትን፣ በስብሰባዎች ላይ መገኘትንና በክርስቲያናዊ አገልግሎት መካፈልን ጨምሮ ሕይወታችን በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ የሚያጠነጥን እንዲሆን ማድረግ አለብን። (1 ጴጥ. 1:13) የሥጋ ሥራዎች ትኩረታችንን እንዲሰርቁት ከመፍቀድ ይልቅ አእምሯችን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይኖርብናል። በዚህ መንገድ እንደ መንፈስ ፈቃድ እየተመላለስን እንደሆነ እናሳያለን። እንዲህ ማድረጋችን በረከት ያመጣልናል፤ ምክንያቱም በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሕይወትና ሰላም ያስገኛል።​—ገላ. 6:7, 8

ልታብራራ ትችላለህ?

• ‘ሕጉ ሊፈጽመው ያልቻለው ነገር’ ምንድን ነው? ሕጉ ማድረግ ያልቻለውን ነገር አምላክ የፈጸመው እንዴት ነው?

• ‘የኃጢአትና የሞት ሕግ’ ምንድን ነው? ከዚህስ ነፃ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

• ‘በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ የማተኮርን’ ልማድ ለማዳበር ምን ማድረግ ይኖርብናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምትመላለሰው እንደ ሥጋ ፈቃድ ነው ወይስ እንደ መንፈስ ፈቃድ?