በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢዩ ንጹሑን አምልኮ ደግፏል

ኢዩ ንጹሑን አምልኮ ደግፏል

ኢዩ ንጹሑን አምልኮ ደግፏል

ኢዩ ንጹሑን አምልኮ ደግፏል። የተሰጠውን ኃላፊነት በሚወጣበት ወቅት ደከመኝ የማይል፣ የጥድፊያ ስሜት የሚታይበት፣ ቆራጥ፣ ቀናተኛና ደፋር ሰው መሆኑን አሳይቷል። ኢዩ እኛም ልናንጸባርቃቸው የሚገቡ ግሩም ባሕርያት ነበሩት።

የእስራኤል ብሔር በመጥፎ ሁኔታ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ኢዩ አንድ ተልእኮ ተሰጠው። የሟቹ የአክዓብ ሚስት የሆነችውና በወቅቱ ንጉሥ የነበረው የኢዮራም እናት ኤልዛቤል በአገሪቱ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ታሳድር ነበር። ኤልዛቤል ሕዝቡ ከይሖዋ ይልቅ በኣልን እንዲያመልክ አድርጋ የነበረ ከመሆኑም ሌላ የአምላክን ነቢያት ገድላለች፤ በተጨማሪም ሕዝቡን ‘በግልሙትናዋና በመተትዋ’ በክላው ነበር። (2 ነገ. 9:22 የ1954 ትርጉም፤ 1 ነገ. 18:4, 13) በመሆኑም ይሖዋ ኢዮራምንና ኤልዛቤልን ጨምሮ የአክዓብ ቤት በሙሉ እንዲጠፋ ወስኖ ነበር። ይህን እርምጃ የማስፈጸም ተልእኮ የተሰጠው ደግሞ ለኢዩ ነበር።

ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ ኢዩ መተረክ የሚጀምሩት እስራኤላውያን በሬማት ዘገለዓድ ከሶርያውያን ጋር ውጊያ ላይ በነበሩበት ወቅት ከሠራዊቱ ጦር መኰንኖች ጋር ተቀምጦ እንደነበር በመግለጽ ነው። ኢዩ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው የጦር መኮንን ምናልባትም የእስራኤል ጦር አዛዥ ሊሆን ይችላል። ነቢዩ ኤልሳዕ፣ ከነቢያት ልጆች አንዱን ከጠራው በኋላ ወደ ኢዩ እንዲሄድና ንጉሥ አድርጎ እንዲቀባው ነገረው፤ በተጨማሪም በከሃዲው በአክዓብ ቤት ያለውን ወንድ ሁሉ እንዲገድል ለኢዩ መመሪያ እንዲሰጠው አዘዘው።​—2 ነገ. 8:28፤ 9:1-10

ኢዩ፣ የጦር መኮንኖቹ ነቢዩ የመጣበትን ዓላማ ሲጠይቁት ለመናገር አቅማምቶ ነበር። ሆኖም አጥብቀው ሲጠይቁት እውነቱን ተናገረ፤ ከዚያም እሱና ጓደኞቹ በኢዮራም ላይ እርምጃ ለመውሰድ አሴሩ። (2 ነገ. 9:11-14) እነዚህ ሰዎች፣ በጊዜው በነበረው አገዛዝና በኤልዛቤል ድርጊት ቁጭትና ቅሬታ የነበራቸው ይመስላል። ያም ሆነ ይህ፣ ኢዩ ተልእኮውን በተሻለ መንገድ መወጣት የሚችለው እንዴት እንደሆነ በጥንቃቄ ማሰብ ጀመረ።

ንጉሥ ኢዮራም በጦርነት ላይ በመቁሰሉ ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል ሄዶ ነበር። ኢዩ፣ ዓላማው ግቡን እንዲመታ በኢዝራኤል የሚገኝ አንድም ሰው ስለዚህ ጉዳይ መስማት እንደሌለበት ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም “ይህን ነገር ወደ ኢይዝራኤል ሄዶ እንዳይናገር፣ ማንም ሰው ከዚህች ከተማ ሾልኮ እንዳይወጣ ጠብቁ” በማለት ትእዛዝ ሰጠ። (2 ነገ. 9:14, 15) ምናልባትም ለኢዮራም ታማኝ ከሆኑ ወታደሮች የተወሰነ ተቃውሞ ሊገጥመው እንደሚችል ሳይጠብቅ አልቀረም። በመሆኑም እንዲህ ያለ ተቃውሞ ሊነሳ የሚችልበት አጋጣሚ እንዳይፈጠር ለማድረግ ፈልጎ ነበር።

አነዳዱ እንደ እብድ ነበር!

ኢዩ ድንገተኛ ጥቃት ለመሰንዘር በሠረገላው ላይ ሆኖ ከሬማት ዘገለዓድ ወደ ኢይዝራኤል በፍጥነት መገስገስ ጀመረ። ኢዩ 72 ኪሎ ሜትር የሚፈጀውን ይህን መንገድ አገባዶ ወደ ኢይዝራኤል ሲቃረብ በማማው ላይ የቆመው ጠባቂ ‘የኢዩን ወታደሮች’ ተመለከተ። (2 ነገ. 9:17) ኢዩ ዓላማውን ለማሳካት ብዛት ያለው የጦር ኃይል ይዞ እንደመጣ ምንም ጥርጥር የለውም።

ጠባቂው በአንደኛው ሠረገላ ላይ ደፋሩን ኢዩ ሲመለከት ‘አነዳዱ እንደ እብድ ነው’ በማለት ለኢዩራም ተናገረ። (2 ነገ. 9:20) ኢዩ ለወትሮውም አነዳዱ እንዲሁ የነበረ ይመስላል፤ ይህን የተለየ ተልእኮ ለመወጣት ያለው ጉጉት ደግሞ እንደ እብድ እንዲነዳ ወይም በከፍተኛ ፍጥነት እንዲገሰግስ አድርጎት ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።

ኢዩ ወደ እሱ ለተላኩት ሁለት መልእክተኞች ምንም ነገር ለመናገር ፈቃደኛ ባለመሆኑ ንጉሥ ኢዮራምና የእሱ አጋር የሆነው የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ በየሠረገሎቻቸው ላይ ሆነው ሊገናኙት መጡ። “ኢዩ፣ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ሲል ኢዮራም ጠየቀው። ኢዩም በቁጣ “የእናትህ የኤልዛቤል የጣዖት አምልኮና [“ግልሙትናዋና፣” የ1954 ትርጉም] መተት እንዲህ በዝቶ እያለ ምን ሰላም አለ!” ብሎ መለሰለት። ይህ ምላሽ ያስደነገጠው ኢዮራምም ሠረገላውን አዙሮ መሸሽ ጀመረ። ይሁንና ኢዩ ከእሱ ይልቅ ፈጣን ስለነበር ቀስቱን አነጣጥሮ በማስፈንጠር ልቡ ላይ ወጋው፤ ንጉሡም በሠረገላው ላይ እንዳለ ሞተ። እንዲሁም አካዝያስ ለማምለጥ ቢሞክርም ኢዩ ተከታትሎ በመድረስ እሱንም ገደለው።​—2 ነገ. 9:22-24, 27

ቀጥሎ መጥፋት ያለባት የአክዓብ ቤተሰብ ደግሞ ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል ነበረች። ኢዩ ኤልዛቤልን ‘ይህች የተረገመች ሴት’ ብሎ መጥራቱ ተገቢ ነበር። ኢዩ ኢዝራኤል ሲደርስ ኤልዛቤል ከቤተ መንግሥቱ ሆና ቁልቁል በመስኮት ስትመለከት አያት። ኢዩ ምንም ሐተታ ሳያበዛ ለቤተ መንግሥቱ ጃንደረቦች ኤልዛቤልን ወደ ታች እንዲወረውሯት ትእዛዝ ሰጠ። ከዚያም መላው እስራኤልን ያሳተችውን ይህችን ሴት በፈረሶቹ ረጋገጣት። በተጨማሪም ኢዩ ክፉ ከነበረው ከአክዓብ ቤት የቀሩትን በርካታ ሰዎች ለማጥፋት እርምጃ መውሰዱን ቀጠለ።​—2 ነገ. 9:30-34፤ 10:1-14

የጭካኔ ድርጊት መፈጸም የሚያስደስት ነገር ባይሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይሖዋ ፍርዱን ለማስፈጸም በአገልጋዮቹ ይጠቀም እንደነበረ መዘንጋት አይኖርብንም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አካዝያስ ኢዮራምን ለመጠየቅ መሄዱን፣ እግዚአብሔር ለአካዝያስ መውደቅ ምክንያት አደረገው፤ አካዝያስ እንደ ደረሰም የናሜሲን ልጅ ኢዩን ለመቀበል ከኢዮራም ጋር ወጣ፤ ኢዩም የአክዓብን ቤት እንዲያጠፋ እግዚአብሔር የቀባው ሰው ነበር።” (2 ዜና 22:7) ኢዩ፣ የኢዮራምን ሬሳ ከሠረገላው ወደ ናቡቴ እርሻ እንዲጣል ባደረገ ጊዜ አክዓብ ናቡቴን በመግደሉ የቅጣት ፍርድ እንደሚጠብቀው ይሖዋ የተናገረው ቃል መፈጸሙን ተገነዘበ። በተጨማሪም “የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ደም ሁሉ ከኤልዛቤል እጅ” እንዲበቀል ታዝዞ ነበር።​—2 ነገ. 9:7, 25, 26፤ 1 ነገ. 21:17-19

በዛሬው ጊዜ ማንኛውም የይሖዋ አገልጋይ ንጹሑን አምልኮ በሚቃወሙ ሰዎች ላይ የኃይል እርምጃ አይወስድም። ምክንያቱም አምላክ “በቀል የእኔ ነው” በማለት ተናግሯል። (ዕብ. 10:30) ሆኖም ክርስቲያን ሽማግሌዎች ጉባኤውን ከበካይ ተጽዕኖ ለመከላከል የኢዩን ዓይነት ድፍረት የተሞላበት እርምጃ መውሰድ አለባቸው። (1 ቆሮ. 5:9-13) በሌላ በኩል ደግሞ የጉባኤው አባላት በሙሉ ከተወገዱ ግለሰቦች ጋር ወዳጅነት ላለመፍጠር መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።​—2 ዮሐ. 9-11

ኢዩ ለይሖዋ እንደሚቀና አሳይቷል

ኢዩ ተልእኮውን ለመፈጸም የተነሳሳበት ምክንያት ምን እንደሆነ ታማኝ ለነበረው ለኢዮናዳብ “በል አብረን እንሂድና ለእግዚአብሔር ያለኝን ቅናት እይልኝ” በማለት ከተናገረው ቃል መረዳት እንችላለን። ኢዮናዳብ የቀረበለትን ግብዣ ተቀብሎ የኢዩ ሠረገላ ላይ በመውጣት ወደ ሰማርያ አብሮት ሄደ። ኢዩ እዚያ እንደደረሰ “የበኣልን አገልጋዮች ለማጥፋት ተንኰል” ጠነሰሰ።​—2 ነገ. 10:15-17, 19

ኢዩ “ለባኣል ትልቅ መሥዋዕት” ለማቅረብ እንዳሰበ ለሕዝቡ ተናገረ። (2 ነገ. 10:18, 19) አንድ ምሑር “ይህ የኢዩ አባባል ውስጠ ወይራ የሆነ የብልሃት አነጋገር ነበር” በማለት ገልጸዋል። ኢዩ እዚህ ላይ የተጠቀመበት የዕብራይስጥ ቃል “በጥቅሉ የሚያመለክተው ‘መሥዋዕትን’ ሲሆን ከሃዲዎችን ‘ማረድን’ ለማመልከትም ሊያገለግል ይችላል።” ኢዩ በዚህ ዝግጅት ላይ አንድም የበኣል አምላኪ እንዲቀር ስላልፈለገ ሁሉን በበኣል ቤተ ጣዖት እንዲሰበሰቡና የተለየ ልብስ እንዲለብሱ አደረገ። “ኢዩ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርቦ እንዳበቃ” ያዘጋጃቸው 80 የታጠቁ ሰዎች የበኣል አምላኪዎችን እንዲገድሉ ትእዛዝ ሰጠ። ከዚያም የበኣልን ቤተ ጣዖት በማፈራረስ አካባቢውን መጸዳጃ ቦታ ስላደረገው ስፍራው የአምልኮ ቦታ መሆኑ ቀረ።​—2 ነገ. 10:20-27

ኢዩ ብዙ ደም እንዳፈሰሰ ግልጽ ነው። ያም ሆኖ ቅዱሳን መጻሕፍት ኢዩን የሚገልጹት፣ የእስራኤልን ብሔር ኤልዛቤልና ቤተሰቧ ከሚያሳድሩት ጭቆና ነፃ እንዳወጣ ደፋር ሰው አድርገው ነው። ማንኛውም የእስራኤል መሪ እንዲህ የመሰለውን እርምጃ ለመውሰድ ደፋር፣ ቆራጥና ቀናተኛ መሆን ነበረበት። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰጥቷል፦ “ይህ ኃላፊነት ከባድ ስለሆነ ቆራጥ መሆንንና ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግን ይጠይቅ ነበር። እርምጃው ለዘብ ያለ ቢሆን ኖሮ የበኣል አምልኮን ከእስራኤል ለማጥፋት የተወሰደው እርምጃ አይሳካም ነበር።”

በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ኢዩ የነበሩትን አንዳንድ ባሕርያት እንዲያንጸባርቁ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ በሚያወግዛቸው ድርጊቶች ላይ ለመካፈል ብንፈተን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ከዚህ ድርጊት ለመራቅ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ብሎም ደፋርና ቀናተኛ መሆን አለብን። ለአምላክ ታማኝ ከመሆን ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ለይሖዋ እንደምንቀና ማሳየት ይኖርብናል።

የይሖዋን ሕግ ለመጠበቅ ጥንቃቄ አድርጉ

የዚህ ታሪክ የመጨረሻ ክፍል ለእኛ ጥሩ ማስጠንቀቂያ ይዟል። ኢዩ ‘በቤቴልና በዳን የሚገኙ የወርቅ ጥጃዎችን ከማምለክ እንዳልራቀ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ነገ. 10:29) ለንጹሕ አምልኮ ከፍተኛ ቅንዓት የነበረው እንዲህ ያለ ሰው ከጣዖት አምልኮ መራቅ ያልቻለው ለምንድን ነው?

ኢዩ የእስራኤል መንግሥት ከይሁዳ መንግሥት እንደተገነጠለ እንዲቀጥል ከተፈለገ በሃይማኖትም መለየት እንዳለበት ሳይሰማው አልቀረም። በመሆኑም ከእሱ በፊት እንደነበሩት የእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ኢዩም የጥጃ አምልኮን እንዲቀጥል በማድረግ እስራኤልን ከይሁዳ ለመለየት ሞክሯል። ይሁንና ይህ ድርጊት ንጉሥ እንዲሆን በሾመው በይሖዋ ላይ የነበረው እምነት እንደጠፋ የሚያሳይ ነው።

ኢዩ ‘በአምላክ ፊት መልካም የሆነውን ነገር ስላደረገ’ ይሖዋ አመስግኖታል። ያም ሆኖ “ኢዩ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ሕግ በፍጹም ልቡ ለመጠበቅ ጥንቃቄ አላደረገም።” (2 ነገ. 10:30, 31) ኢዩ ከዚህ ቀደም ካደረጋቸው ነገሮች አንጻር እንዲህ ማድረጉ ያስገርመን አልፎ ተርፎም ያሳዝነን ይሆናል። ሆኖም ለእኛ ግሩም የሆነ ትምህርት ይሰጠናል። ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና በፍጹም አቅልለን መመልከት የለብንም። የአምላክን ቃል በማጥናት፣ ባነበብነው ነገር ላይ በማሰላሰልና በሰማይ ለሚገኘው አባታችን ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ ሆነን መኖር እንችላለን። እንግዲያው የይሖዋን ሕግ በፍጹም ልባችን ለመጠበቅ የተቻለንን ያህል ጥንቃቄ እናድርግ።​—1 ቆሮ. 10:12

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የዓለም ታሪክ ስለ ኢዩ ምን ይላል?

አንዳንድ ተቺዎች በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱት ግለሰቦች በእርግጥ በሕይወት ስለመኖራቸው ብዙውን ጊዜ ጥያቄ ያነሳሉ። ታዲያ ኢዩን በተመለከተ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ማስረጃ ማግኘት ይቻላል?

በጥንቷ አሦር ከተገኙ መረጃዎች መካከል ቢያንስ ሦስቱ ይህን የእስራኤል ንጉሥ በስም ጠቅሰውታል። ከእነዚህ መካከል በአንደኛው ላይ ለአሦር ንጉሥ ለሳልሳዊ ሰልምናሶር ሲሰግድና ግብር ሲሰጥ የሚታየው ኢዩ ወይም ከእሱ መልእክተኞች አንዱ እንደሆነ ይታመናል። በምስሉ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “የኡምሪ (ሁኡምራይ) ልጅ ኢዩ (ላኡአ) በግብር መልክ ያመጣውን ብር፣ ወርቅ፣ በወርቅ የተሠራ የሳፕሉ ሳህን፣ ከታቹ ሾጣጣ ቅርጽ ያለው ከወርቅ የተሠራ የአበባ ማስቀመጫ፣ የወርቅ ዋንጫዎች፣ የወርቅ ባልዲዎች፣ ቆርቆሮ፣ የንጉሥ በትር፣ (እና) የእንጨት ፑሩሁቱ [የዚህ ቃል ትርጉም አይታወቅም] ተቀብያለሁ።” ኢዩ ቃል በቃል “የኡምሪ ልጅ” አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ይህ አባባል በእስራኤል በተከታታይ የገዙትን ነገሥታት የሚያመለክት ነው። ይህን አባባል ሊጠቀሙ የቻሉት ኡምሪ ታዋቂ በመሆኑና የእስራኤል ዋና ከተማ የነበረችውን ሰማርያን በመገንባቱ ሊሆን ይችላል።

የአሦር ንጉሥ ከኢዩ ግብር እንደተቀበለ ቢናገርም ይህን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማግኘት አልተቻለም። ያም ሆኖ አንድ ሐውልት፣ በሰልምናሶር ምስል እና በአሦራውያን የነገሥታት ታሪክ ላይ የአሦር ንጉሥ ኢዩን ሦስት ጊዜ ጠቅሶታል። እነዚህ ማስረጃዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ኢዩ በእርግጥ በሕይወት የነበረ ሰው ስለመሆኑ ቅንጣት ታክል እንዳንጠራጠር ያደርጉናል።