በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወንድሞች ለኃላፊነት እንዲጣጣሩ አሠልጥኗቸው

ወንድሞች ለኃላፊነት እንዲጣጣሩ አሠልጥኗቸው

ወንድሞች ለኃላፊነት እንዲጣጣሩ አሠልጥኗቸው

“በሚገባ የተማረ ሁሉ ግን እንደ አስተማሪው ይሆናል።”​—ሉቃስ 6:40

1. ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት አስደናቂ ለሆነ አንድ ጉባኤ መሠረት የጣለው እንዴት ነው?

ሐዋርያው ዮሐንስ የወንጌል ዘገባውን ሲደመድም “እርግጥ ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎች ብዙ ነገሮችም አሉ፤ እነዚህ ሁሉ በዝርዝር ቢጻፉ ዓለም ራሱ የተጻፉትን ጥቅልሎች ለማስቀመጥ የሚበቃ ቦታ የሚኖረው አይመስለኝም” ብሏል። (ዮሐ. 21:25) ኢየሱስ ምድር ላይ በቆየበት አጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የአገልግሎት እንቅስቃሴ አድርጎ ነበር፤ በዚያ ወቅት ካከናወናቸው በርካታ ነገሮች አንዱ ወደ ሰማይ ሲሄድ ሥራውን በበላይነት የሚመሩ ወንዶችን መምረጥ፣ ማሠልጠንና ማደራጀት ነበር። በዚህ መልክ ኢየሱስ በ33 ዓ.ም. ወደ ሰማይ ከመመለሱ በፊት አስደናቂ ለሆነ አንድ ጉባኤ መሠረት ጣለ፤ የዚህ ጉባኤ አባላት ቁጥር በፍጥነት አድጎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያቀፈ ሆነ።​—ሥራ 2:41, 42፤ 4:4፤ 6:7

2, 3. (ሀ) የተጠመቁ ወንዶች የኃላፊነት ቦታ ላይ ለመድረስ መጣጣራቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ነገሮች እንመረምራለን?

2 በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ100,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሆኑ ቀናተኛ የመንግሥቱ ሰባኪዎች መኖራቸው መንፈሳዊ ጉዳዮችን በበላይነት የሚከታተሉ ወንዶች እንደሚያስፈልጉ ያሳያል። ለምሳሌ፣ ክርስቲያን ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ በጣም ያስፈልጋሉ። እዚህ መብት ላይ ለመድረስ የሚጣጣሩ ሁሉ ‘መልካም ሥራን እየተመኙ’ ስለሆነ ሊመሰገኑ ይገባል።​—1 ጢሞ. 3:1

3 ይሁንና ወንዶች፣ በጉባኤ ውስጥ ላሉ መብቶች ብቁ እንዲሆኑ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ዓለማዊ ትምህርት ወይም የሕይወት ተሞክሮ ብቻውን እንዲህ ላሉ መብቶች ብቁ አያደርግም። አንድ ወንድ እንዲህ ያሉ ኃላፊነቶችን ተቀብሎ በጉባኤ ውስጥ በተገቢው መንገድ ለማገልገል ከፈለገ መንፈሳዊ ብቃቶችን ማሟላት ይኖርበታል። ምክንያቱም ከችሎታው ወይም ካገኘው ስኬት ይልቅ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መንፈሳዊ ባሕርያትን ማዳበሩ ነው። ታዲያ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንዶች ብቃቱን እንዲያሟሉ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው? ኢየሱስ “በሚገባ የተማረ ሁሉ ግን እንደ አስተማሪው ይሆናል” ብሏል። (ሉቃስ 6:40) ታላቅ አስተማሪ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለበለጠ ኃላፊነት ብቁ እንዲሆኑ የረዳባቸውን አንዳንድ መንገዶች በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን፤ እንዲሁም ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እንመረምራለን።

“ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ”

4. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እውነተኛ ወዳጅ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ዝቅ አድርጎ ከማየት ይልቅ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ ይመለከታቸው ነበር። ከእነሱ ጋር ጊዜ ያሳልፍ እንዲሁም በእነሱ ላይ እምነት ይጥል የነበረ ከመሆኑ በላይ ‘ከአባቱ የሰማውን ነገር ሁሉ አሳውቋቸዋል።’ (ዮሐንስ 15:15ን አንብብ።) ደቀ መዛሙርቱ ‘የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምንድን ነው?’ በማለት ላቀረቡት ጥያቄ መልስ ሲሰጣቸው ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን መገመት ይቻላል። (ማቴ. 24:3, 4) በተጨማሪም ሐሳቡንና ስሜቱን ከእነሱ ለመደበቅ አልሞከረም። ለምሳሌ አልፎ በተሰጠበት ምሽት ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሄዶ ነበር፤ በዚያም ኢየሱስ በጭንቀት ተውጦ ከልቡ ሲጸልይ ተመልክተዋል። እርግጥ እነዚህ ሦስት ሐዋርያት ኢየሱስ ምን ብሎ እንደጸለየ አልሰሙ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በወቅቱ በምን ዓይነት ጭንቀት ውስጥ እንደነበረ አስተውለው መሆን አለበት። (ማር. 14:33-38) ቀደም ሲልም በተአምራዊ ሁኔታ ሲለወጥ ማየታቸው በሦስቱ ላይ ምን ስሜት አሳድሮባቸው ሊሆን እንደሚችል አስቡ። (ማር. 9:2-8፤ 2 ጴጥ. 1:16-18) ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የመሠረተው የተቀራረበ ዝምድና በኋላ ላይ የተቀበሉትን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት ኃይል ሰጥቷቸዋል።

5. ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሌሎችን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

5 ልክ እንደ ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም ሌሎችን ለመቅረብ ጥረት ያደርጋሉ፤ እንዲሁም እነሱን ይረዳሉ። የእምነት ባልንጀሮቻቸው በግለሰብ ደረጃ ለሚያስፈልጋቸው ነገር ትኩረት በመስጠት ከእነሱ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ለመመሥረት ጥረት ያደርጋሉ። ሽማግሌዎች ሚስጥር ጠባቂ መሆን እንዳለባቸው ቢገነዘቡም ሁሉንም ነገር በድብቅ ይይዛሉ ማለት አይደለም። የተማሯቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች ያካፍሏቸዋል እንዲሁም በወንድሞቻቸው ይተማመናሉ። ሽማግሌዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ወጣት የሆኑትን የጉባኤ አገልጋዮች በፍጹም ዝቅ አድርገው መመልከት አይገባቸውም። ከዚህ ይልቅ ጉባኤውን የሚጠቅም አስፈላጊ ሥራ ለማከናወን ብቃት እንዳላቸው መንፈሳዊ ሰዎች አድርገው ሊመለከቷቸው ይገባል።

“አርዓያ ሆኜላችኋለሁ”

6, 7. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የተወውን ምሳሌና ይህ በእነሱ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ግለጽ።

6 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለመንፈሳዊ ነገር አድናቆት ያላቸው ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ አስተዳደጋቸውና የአካባቢው ባሕል በአስተሳሰባቸው ላይ ተጽዕኖ ያሳድርባቸው ነበር። (ማቴ. 19:9, 10፤ ሉቃስ 9:46-48፤ ዮሐ. 4:27) ያም ቢሆን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን አልነቀፋቸውም ወይም በቁጣ አልተናገራቸውም። ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር እንዲያደርጉ አልጠየቃቸውም፤ ወይም ደግሞ አንድን ሥራ እንዲሠሩ አዝዞ እሱ ወደ ሌላ ተግባር አይሄድም ነበር። ከዚህ ይልቅ ምሳሌ በመሆን አስተምሯቸዋል።​—ዮሐንስ 13:15ን አንብብ።

7 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ዓይነት አርዓያ ትቶላቸዋል? (1 ጴጥ. 2:21) ሌሎችን ነፃ ሆኖ ማገልገል እንዲችል አኗኗሩን ቀላል አድርጎ ነበር። (ሉቃስ 9:58) ኢየሱስ ቦታውን የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ የሚያስተምራቸው ትምህርቶች ምንጊዜም በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ ነበሩ። (ዮሐ. 5:19፤ 17:14, 17) በቀላሉ የሚቀረብና ደግ ነበር። እንዲሁም ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ነበር። (ማቴ. 19:13-15፤ ዮሐ. 15:12) ኢየሱስ የተወው ምሳሌ በሐዋርያቱ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ለአብነት ያህል፣ ያዕቆብ ከሞት ጋር በተፋጠጠበት ወቅት በፍርሃት ከመርበድበድ ይልቅ እስኪገደል ድረስ አምላክን በታማኝነት አገልግሏል። (ሥራ 12:1, 2) ዮሐንስም ቢሆን ከ60 ለሚበልጡ ዓመታት በታማኝነት የኢየሱስን ፈለግ ተከትሏል።​—ራእይ 1:1, 2, 9

8. ሽማግሌዎች ለወጣት ወንዶችም ሆነ ለሌሎች የጉባኤው አባላት ምሳሌ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

8 ሽማግሌዎች የራሳቸውን ጥቅም በመሠዋት እንዲሁም ትሑትና አፍቃሪ በመሆን ለወጣት ወንዶች ምሳሌ መሆን ይችላሉ። (1 ጴጥ. 5:2, 3) በተጨማሪም ሽማግሌዎች በእምነታቸው፣ በክርስቲያናዊ አኗኗራቸው፣ በአገልግሎታቸውና በማስተማሩ ሥራ ምሳሌ የሚሆኑ ከሆነ ሌሎች የእነሱን አርዓያ ይከተላሉ፤ ይህን መመልከታቸው ደግሞ እርካታ ያስገኝላቸዋል።​—ዕብ. 13:7

“መመሪያ በመስጠት ላካቸው”

9. ኢየሱስ ለወንጌላዊነቱ ሥራ ደቀ መዛሙርቱን እንዳሠለጠነ እንዴት እናውቃለን?

9 ኢየሱስ ለሁለት ዓመት ያህል በቅንዓት ሲያገለግል ከቆየ በኋላ 12ቱን ሐዋርያት ለስብከት በመላክ ሥራው እንዲስፋፋ አደረገ። ይሁን እንጂ በቅድሚያ መመሪያ ሰጣቸው። (ማቴ. 10:5-14) በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር ከመመገቡ በፊት እሱ በሚፈልገው መንገድ ሕዝቡን በሥርዓት እንዲያስቀምጡና ምግቡን እንዲያከፋፍሉ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። (ሉቃስ 9:12-17) ከዚህ ለመመልከት እንደምንችለው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ግልጽና ዝርዝር የሆነ መመሪያ በመስጠት ያሠለጥናቸው ነበር። ሐዋርያቱ በዚህ መልክ ሥልጠና ማግኘታቸው መንፈስ ቅዱስ ከሰጣቸው እርዳታ ጋር ተዳምሮ በ33 ዓ.ም. እና ከዚያ በኋላ የተካሄደውን መጠነ ሰፊ የስብከት ሥራ ለማደራጀት አስችሏቸዋል።

10, 11. ለአዲሶች ደረጃ በደረጃ ሥልጠና መስጠት የሚቻለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

10 በዛሬው ጊዜ፣ አንድ ሰው መንፈሳዊ መመሪያ ማግኘት የሚጀምረው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምር ነው። ምናልባትም ይህ ሰው በደንብ ማንበብ እንዲችል መርዳት ይኖርብን ይሆናል። ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በሚያጠናበት ጊዜ ሁሉ በተለያዩ መንገዶች ተማሪውን መርዳታችንን እንቀጥላለን። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት ሲጀምር የሚያገኘው መንፈሳዊ ሥልጠና እየጨመረ ይሄዳል፤ ምክንያቱም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የመካፈል፣ ያልተጠመቀ አስፋፊ የመሆንና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች መብቶችን ሊያገኝ ይችላል። ከተጠመቀ በኋላ ደግሞ የመንግሥት አዳራሹን እንደ መጠገን ባሉ ሥራዎች እንዲካፈል በማድረግ ሥልጠና ይሰጠዋል። እንዲሁም የጉባኤ ሽማግሌዎች ይህ ወንድም የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የሚያስችለውን ብቃት ለማሟላት ከእሱ ምን እንደሚጠበቅ ሊነግሩት ይችላሉ።

11 ሽማግሌዎች ለአንድ የተጠመቀ ወንድም፣ አንድ ዓይነት ኃላፊነት በሚሰጡበት ጊዜ ድርጅታዊ አሠራሮችንና አስፈላጊ የሆኑ መመሪያዎችን ሳይሰለቹ በደስታ ሊገልጹለት ይገባል። ሥልጠና እየተሰጠው ላለው ወንድም ከእሱ የሚጠበቀውን ነገር በደንብ ሊያስረዱት ወይም ሊያብራሩለት ይገባል። አፍቃሪ የሆኑ ሽማግሌዎች፣ አንድ ወንድም የተሰጠውን ሥራ ለመሥራት ቢቸግረው ብቃት የለውም የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አይቸኩሉም። ከዚህ ይልቅ ሽማግሌዎች ስህተቱን ለይተው በመጥቀስ ማድረግ ያለበትን ነገርና አሠራሩን ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ በድጋሚ ይገልጹለታል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንዶች እንዲህ ላለው ጥረት በጎ ምላሽ ሲሰጡና ሌሎችን በማገልገል የሚገኘውን ደስታ ሲያጣጥሙ መመልከት ሽማግሌዎችን ያስደስታቸዋል።​—ሥራ 20:35

‘ጠቢብ ሰው ምክር ይሰማል’

12. ኢየሱስ የሚሰጠው ምክር ውጤታማ የነበረው ለምንድን ነው?

12 ኢየሱስ፣ ለእያንዳንዳቸው ምን እንደሚያስፈልግ ግምት ውስጥ በማስገባት ለደቀ መዛሙርቱ በግለሰብ ደረጃ ምክር ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ኢየሱስን ለመቀበል ፈቃደኛ ባልሆኑ አንዳንድ የሰማርያ ሰዎች ላይ እሳት ከሰማይ እንዲወርድ በጠየቁ ጊዜ ገሥጿቸዋል። (ሉቃስ 9:52-55) በሌላ ወቅት ደግሞ በመንግሥቱ ውስጥ ከሁሉ የላቀ ቦታ እንዲሰጣቸው በእናታቸው በኩል ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ እነዚህን ወንድማማቾች በቀጥታ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በቀኜ ወይም በግራዬ የመቀመጡ ጉዳይ ግን አባቴ ላዘጋጀላቸው የሚሰጥ እንጂ በእኔ ፈቃድ የሚሆን አይደለም።” (ማቴ. 20:20-23) ኢየሱስ የሚሰጠው ምክር ምንጊዜም ግልጽ፣ ተግባራዊ ሊሆን የሚችልና በአምላክ መሠረታዊ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ በመሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርተው አንድ መደምደሚያ ላይ መድረስ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ያስተምራቸው ነበር። (ማቴ. 17:24-27) በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ያለባቸውን የአቅም ገደብ ስለሚያውቅ ከእነሱ ፍጽምና አይጠብቅም ነበር። እንዲሁም የሚሰጠው ምክር በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነበር።​—ዮሐ. 13:1

13, 14. (ሀ) ሽማግሌዎች ለእነማን ምክር መስጠት ያስፈልጋቸዋል? (ለ) ሽማግሌዎች፣ መንፈሳዊ እድገት ለማያደርግ ወንድም በግለሰብ ደረጃ ምን ዓይነት ምክር መስጠት እንደሚችሉ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

13 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ለመቀበል የሚጣጣር ማንኛውም ወንድ በሆነ ወቅት ላይ ቅዱስ ጹሑፋዊ ምክር እንደሚያስፈልገው ግልጽ ነው። ምሳሌ 12:15 ‘ጠቢብ ሰው ምክር ይሰማል’ ይላል። አንድ ወጣት ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በሕይወቴ ውስጥ ከሁሉ በላይ ፈታኝ የሆነብኝ ነገር ካለብኝ አለፍጽምና ጋር የማደርገው ትግል ነበር። አንድ ሽማግሌ የሰጠኝ ምክር ስለ ራሴ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረኝ ረድቶኛል።”

14 ሽማግሌዎች፣ አንድ ሰው ያለው አጠያያቂ ምግባር መንፈሳዊ እድገቱን እንደገታው ሲመለከቱ ቅድሚያውን ወስደው እሱን በገርነት መንፈስ ለማስተካከል ጥረት ያደርጋሉ። (ገላ. 6:1) አንድ ወንድም አንዳንድ ባሕርያቱን እንዲያሻሽል ምክር መስጠት የሚያስፈልግበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ወንድም ራሱን የሚቆጥብ እንደሆነ የሚያሳዩ ነገሮች ካሉ አንድ ሽማግሌ ኢየሱስ ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ እንደነበረና ተከታዮቹም የእሱን ምሳሌ በመከተል ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ እንደላካቸው ቢጠቁመው ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሉቃስ 8:1) ወይም ደግሞ አንድ ወንድም ሥልጣን የመፈለግ አዝማሚያ ካለው ኢየሱስ፣ ከፍተኛ ቦታ ለማግኘት መፈለግ ያለውን አደጋ ደቀ መዛሙርቱ እንዲገነዘቡ እንዴት እንደረዳቸው ቢጠቁመው ጥሩ ነው። (ሉቃስ 22:24-27) ወንድም ይቅርታ ማድረግ የሚከብደው ቢሆንስ? ያለበት ከፍተኛ ዕዳ ቢሰረዝለትም ከእሱ አንጻር ሲታይ እጅግ አነስተኛ የሆነን ዕዳ ለመተው ፈቃደኛ ስላልሆነው ባሪያ የሚናገረውን ምሳሌ መጥቀሱ ጥሩ ውጤት ያስገኝ ይሆናል። (ማቴ. 18:21-35) ምክር መስጠት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ሽማግሌዎች ዛሬ ነገ ሳይሉ ምክር መስጠታቸው አስፈላጊ ነው።​—ምሳሌ 27:9ን አንብብ።

“ራስህን አሠልጥን”

15. አንድ ወንድም፣ ጉባኤውን እንዲያገለግል ቤተሰቡ እንዴት ሊረዳው ይችላል?

15 ሽማግሌዎች፣ ወንዶች የኃላፊነት ቦታ ላይ እንዲደርሱ ግንባር ቀደም ሆነው የሚያሠለጥኑ ቢሆንም ሌሎችም እነሱ የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ አንድ ወንድም ኃላፊነት ቦታ ላይ እንዲደርስ ቤተሰቡ ድጋፍ ሊያደርግለት ይችላል፤ ደግሞም እንዲህ ሊያደርግለት ይገባል። ይህ ወንድም የሽምግልና መብት ላይ ደርሶ ከሆነም አፍቃሪ የሆነች ሚስቱና ራስ ወዳድ ያልሆኑ ልጆቹ የሚያደርጉለት ድጋፍ ይጠቅመዋል። ኃላፊነቱን በሚገባ እንዲወጣ ከተፈለገ ጉባኤውን ለመርዳት የሚያደርገውን ጥረት ቤተሰቡ በፈቃደኝነት መደገፍ ይኖርበታል። ቤተሰቡ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየቱ ለወንድም ደስታ የሚያመጣለት ከመሆኑም በላይ ሌሎች የጉባኤው አባላትም ቤተሰቡ የሚያደርገውን ጥረት በእጅጉ ያደንቃሉ።​—ምሳሌ 15:20፤ 31:10, 23

16. (ሀ) መብት ለማግኘት ጥረት ከማድረግ ጋር በተያያዘ ኃላፊነቱ በዋነኝነት የወደቀው በማን ላይ ነው? (ለ) አንድ ወንድ ጉባኤውን ለማገልገል የሚያስችሉ መብቶች ላይ ለመድረስ መጣጣር የሚችለው እንዴት ነው?

16 አንድ ወንድም መብት ለማግኘት ጥረት ሲያደርግ ሌሎች ሊረዱት ቢችሉም ኃላፊነቱ በዋነኝነት የወደቀው በእሱ ላይ ነው። (ገላትያ 6:5ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ አንድ ወንድም ሌሎችን ለመርዳትና በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ የግድ የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ መሆን የለበትም። ይሁንና ጉባኤውን ለማገልገል የሚያስችሉ መብቶች ላይ ለመድረስ ከፈለገ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተጠቀሱትን ብቃቶች ማሟላት ይኖርበታል። (1 ጢሞ. 3:1-13፤ ቲቶ 1:5-9፤ 1 ጴጥ. 5:1-3) በመሆኑም አንድ ሰው የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ የመሆን ፍላጎት ቢኖረውም ገና እዚህ መብት ላይ ያልደረሰ ከሆነ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የሚችልባቸውን አቅጣጫዎች በቁም ነገር ሊያስብባቸው ይገባል። ከእነዚህም መካከል መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ፣ ትርጉም ያለው የግል ጥናት ማድረግ፣ በቁም ነገር ማሰላሰል፣ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ እና በክርስቲያናዊ አገልግሎት በቅንዓት መካፈል ይገኙበታል። በዚህ መንገድ “ለአምላክ ማደርን ግብ አድርገህ ራስህን አሠልጥን” በማለት ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይችላል።​—1 ጢሞ. 4:7

17, 18. አንድ የተጠመቀ ወንድም ፍላጎት ማጣት ወይም ብቃት የለኝም የሚለው ስሜት የሚፈጥርበት ጭንቀት መብት ለማግኘት እንዳይጣጣር እንቅፋት ቢሆንበት ምን ማድረግ ይችላል?

17 አንድ ወንድም ብቃት የለኝም የሚለው ስሜት የፈጠረበት ጭንቀት መብት ለማግኘት ከመጣጣር ወደኋላ እንዲል ቢያደርገውስ? ይህ ወንድም ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረጉልንን ነገር ማሰቡ ሊጠቅመው ይችላል። ይሖዋ ‘ሸክማችንን በየዕለቱ እንደሚሸከምልን’ ቃል ገብቶልናል። (መዝ. 68:19) በመሆኑም በሰማይ የሚገኘው አባታችን፣ ይህ ወንድም በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነቶችን እንዲቀበል ሊረዳው ይችላል። በተጨማሪም አንድ ወንድም የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ካልሆነ በአምላክ ድርጅት ውስጥ ኃላፊነት ተቀብለው ማገልገል የሚችሉ በርካታ የጎለመሱ ወንዶች እንደሚያስፈልጉ መገንዘቡ ለዚህ መብት እንዲጣጣር ይረዳዋል። በእነዚህ ነጥቦች ላይ ማሰላሰሉ አሉታዊ ስሜቶችን ለማሸነፍ ጥረት እንዲያደርግ ሊያነሳሳው ይችላል። ከዚህም ባሻገር የአምላክን መንፈስ ለማግኘት መጸለይ ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም ይህ መንፈስ፣ ብቃት የለኝም የሚለው ስሜት የፈጠረበትን ጭንቀት ለማስወገድ የሚረዱትንና የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ገጽታዎች የሆኑትን ሰላምንና ራስን መግዛትን እንዲያፈራ ይረዳዋል። (ሉቃስ 11:13፤ ገላ. 5:22, 23) እንዲሁም ይሖዋ፣ በትክክለኛ ዝንባሌ ተነሳስተው መብት ለማግኘት የሚጣጣሩትን ሁሉ እንደሚባርካቸው እርግጠኛ መሆን ይችላል።

18 አንድ የተጠመቀ ወንድም ኃላፊነት ቦታ ላይ ለመድረስ የማይጣጣረው ተነሳሽነቱ ስለሌለው ቢሆንስ? ሌሎችን የማገልገል ፍላጎት እንዲኖረው ምን ሊረዳው ይችላል? ሐዋርያው ጳውሎስ “እሱ ደስ ለሚሰኝበት ነገር ሲል ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ለተግባር እንድትነሳሱ በውስጣችሁ የሚሠራው አምላክ ነው” በማለት ጽፏል። (ፊልጵ. 2:13) በእርግጥም፣ ሌሎችን የማገልገል ፍላጎት እንዲኖረን የሚያደርገው አምላክ ነው፤ እንዲሁም የይሖዋ መንፈስ አንድ ሰው ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችለውን ኃይል እንዲያገኝ ይረዳዋል። (ፊልጵ. 4:13) በተጨማሪም አንድ ክርስቲያን ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ እንዲያነሳሳው አምላክን በጸሎት መጠየቅ ይችላል።​—መዝ. 25:4, 5

19. ይሖዋ “ሰባት እረኞችን፣ እንዲያውም ስምንት አለቆችን” እንደሚያስነሳ መናገሩ ምን ያረጋግጥልናል?

19 ይሖዋ፣ ሽማግሌዎች ሌሎችን ለማሠልጠን የሚያደርጉትን ጥረት ይባርካል። የተሰጣቸውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ በጉባኤ ውስጥ መብት ያገኙ ወንድሞችንም ይሖዋ ይባርካቸዋል። አምላክ በሕዝቦቹ መካከል “ሰባት እረኞችን፣ እንዲያውም ስምንት አለቆችን” በሌላ አባባል ችሎታ ያላቸውን ወንዶች በበቂ መጠን እንደሚያስነሳ ቅዱሳን መጻሕፍት ያረጋግጡልናል፤ እነዚህ ወንዶች የሚነሱት በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ለመቀበል ነው። (ሚክ. 5:5) በዛሬው ጊዜ፣ ሌሎችን የማገልገል ፍላጎት ያላቸውና በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነቶችን ለመቀበል በመሠልጠን ላይ ያሉ በርካታ ትሑት ወንዶች መኖራቸው በእርግጥም ትልቅ በረከት ነው!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ለበለጠ ኃላፊነት ብቁ እንዲሆኑ የረዳቸው እንዴት ነው?

• ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንዶች ለኃላፊነት እንዲበቁ በማሠልጠን ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

• አንድ ወንድም ለኃላፊነት እንዲጣጣር የቤተሰቡ አባላት ሊረዱት የሚችሉት እንዴት ነው?

• አንድ ወንድም የኃላፊነት ቦታ ላይ ለመድረስ በበኩሉ ምን ማድረግ ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 31 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

እድገት ለማድረግ ፍላጎት ላለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ምን ዓይነት ሥልጠና ልትሰጠው ትችላለህ?

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንዶች ኃላፊነት ለመቀበል የሚጣጣሩ መሆናቸውን ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?