በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወንዶች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ እርዷቸው

ወንዶች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ እርዷቸው

ወንዶች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ እርዷቸው

“ከአሁን ጀምሮ ሰውን በሕይወት እንዳለ የምታጠምድ ትሆናለህ።”​—ሉቃስ 5:10

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ በሚሰብክበት ወቅት ወንዶች ምን ዓይነት ምላሽ ሰጥተው ነበር? (ለ) በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ የትኞቹን ነጥቦች እንመለከታለን?

ኢየሱስ በመላው ገሊላ እየተዘዋወረ ሲሰብክ ከቆየ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በጀልባ ተሳፍሮ ገለል ወዳለ ስፍራ ሄደ። ይሁንና ሕዝቡ በእግር ተከተሉት። በዚያ ዕለት የተሰበሰቡት “ሴቶችንና ልጆችን ሳይጨምር አምስት ሺህ ወንዶች ነበሩ።” (ማቴ. 14:21) በሌላ ወቅት ደግሞ ፈውስ ለማግኘትና የሚናገረውን ለመስማት በርካታ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መጥተው ነበር። በዚያ የተገኙት “ሴቶችንና ልጆችን ሳይጨምር አራት ሺህ ወንዶች” ነበሩ። (ማቴ. 15:38) ከእነዚህ ዘገባዎች መረዳት እንደምንችለው ወደ ኢየሱስ ከመጡትና ከእሱ ለመማር ፍላጎት ካሳዩት ሰዎች መካከል በርካታ ወንዶች ይገኙበት ነበር። እንዲያውም ደቀ መዛሙርቱ በተአምር ዓሣ ካጠመዱ በኋላ ለስምዖን “ከአሁን ጀምሮ ሰውን በሕይወት እንዳለ የምታጠምድ ትሆናለህ” በማለት መናገሩ ሌሎች ብዙ ወንዶች ለመልእክቱ ምላሽ ሊሰጡ እንደሚችሉ ይጠብቅ እንደነበር ያሳያል። (ሉቃስ 5:10) በሌላ አባባል ደቀ መዛሙርቱ በሰው ዘር ባሕር ላይ መረባቸውን እንዲጥሉ እያሳሰባቸው ነበር፤ መረባቸው ከሚይዘው መካከል ደግሞ ብዙ ወንዶች እንደሚገኙበት ምንም ጥርጥር የለውም።

2 በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ በርካታ ወንዶች ለምንሰብከው ቅዱስ ጽሑፋዊ መልእክት ፍላጎት የሚያሳዩ ከመሆኑም ሌላ ውይይት ለመጀመር ፈቃደኞች ናቸው። (ማቴ. 5:3) ይሁንና ብዙዎቹ ወንዶች መንፈሳዊ እድገት ከማድረግ ወደኋላ ይላሉ። ታዲያ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን? ኢየሱስ ለወንዶች ለመመሥከር ለየት ያለ የስብከት ዘዴ ባይከተልም በዘመኑ የነበሩ ወንዶችን የሚያሳስቧቸውን ጉዳዮች በማንሳት ያወያያቸው እንደነበር እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እኛም የእሱን ምሳሌ በመከተል በዛሬው ጊዜ ያሉ ወንዶች በአብዛኛው ለሚያሳስቧቸው ሦስት ነገሮች መፍትሔ እንዲያገኙ መርዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት፦ (1) የመተዳደሪያ ጉዳይ (2) የሰው ፍርሃት እና (3) ብቃት የለኝም የሚል ስሜት።

የመተዳደሪያ ጉዳይ

3, 4. (ሀ) ብዙ ወንዶች በዋነኝነት የሚያሳስባቸው ነገር ምንድን ነው? (ለ) አንዳንድ ወንዶች ከመንፈሳዊ ነገሮች ይልቅ ለመተዳደሪያቸው ቅድሚያ የሚሰጡት ለምንድን ነው?

3 ከጸሐፍት መካከል አንዱ ኢየሱስን “መምህር፣ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው። ይሁንና ኢየሱስ “የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ቦታ የለውም” በማለት መለሰለት፤ በዚህ ጊዜ ሰውየው ኢየሱስን ለመከተል ያደረገውን ውሳኔ መጠራጠር ጀመረ። የዕለት ጉርስ ወይም ማረፊያ ከየት ማግኘት እንደሚችል በእርግጠኝነት አለማወቁ ኢየሱስን መከተል ከባድ እንዲሆንበት ሳያደርግ አልቀረም፤ ምክንያቱም ይህ ሰው የክርስቶስ ተከታይ ስለመሆኑ ምንም የተገለጸ ነገር የለም።​—ማቴ. 8:19, 20

4 ብዙውን ጊዜ ወንዶች ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ በቁሳዊ ረገድ አስተማማኝ የሆነ ነገር መያዝ ይመርጣሉ። ብዙዎቹ ከፍተኛ ትምህርት መከታተልና ዳጎስ ያለ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ መያዝ ቅድሚያ የሚሰጡት ነገር ነው። እንደ እነሱ አስተሳሰብ ከሆነ፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናት ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ከመመሥረት ይልቅ አንገብጋቢው ነገር ገንዘብ ለማግኘት መሯሯጥ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጥሩ እንደሆነ ቢሰማቸውም “የዚህ ሥርዓት ጭንቀት” እና “ሀብት ያለው የማታለል ኃይል” በውስጣቸው ያለው ፍላጎት እንዳያድግ አንቀው ይይዙታል። (ማር. 4:18, 19) ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ቅድሚያ በሚሰጡት ነገር ላይ ማስተካከያ እንዲያደርጉ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

5, 6. እንድርያስ፣ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ቅድሚያ በሚሰጡት ነገር ላይ ማስተካከያ እንዲያደርጉ የረዳቸው ምንድን ነው?

5 እንድርያስና ወንድሙ ስምዖን ጴጥሮስ በጋራ ሆነው ዓሣ የማጥመድ ሥራ ይሠሩ ነበር። ዮሐንስ፣ ወንድሙ ያዕቆብና አባታቸው ዘብዴዎስም የተሠማሩት በዚህ ሥራ ነበር። ይህ ቤተሰብ ቀጥሮ የሚያሠራቸው ሰዎች መኖራቸው የቤተሰቡ ንግድ ጥሩ እንደነበር ይጠቁማል። (ማር. 1:16-20) እንድርያስና ዮሐንስ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ኢየሱስ ከአጥማቂው ዮሐንስ ሲሰሙ መሲሑን እንዳገኙ እርግጠኞች ነበሩ። እንድርያስ ምሥራቹን ለወንድሙ ለስምዖን ጴጥሮስ ነገረው፤ ዮሐንስም በበኩሉ ዜናውን፣ ለወንድሙ ለያዕቆብ ሳያበስረው አልቀረም። (ዮሐ. 1:29, 35-41) በቀጣዮቹ ወራት አራቱም ኢየሱስ በገሊላ፣ በይሁዳና በሰማርያ በሚሰብክበት ወቅት አብረውት ነበሩ። ከዚያ በኋላ እነዚህ ደቀ መዛሙርት ዓሣ ወደ ማጥመድ ተግባራቸው ተመለሱ። ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት ቢኖራቸውም በሕይወታቸው ውስጥ አንደኛ ቦታ የሰጡት ለአገልግሎት አልነበረም።

6 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኢየሱስ የእሱ ተከታዮች በመሆን ‘ሰዎችን እንዲያጠምዱ’ ጴጥሮስንና እንድርያስን ጋበዛቸው። ታዲያ እነዚህ ደቀ መዛሙርት ምን ምላሽ ሰጡ? “ወዲያውኑም መረባቸውን ትተው ተከተሉት።” ያዕቆብና ዮሐንስም ቢሆኑ ወዲያውኑ “ጀልባዋንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።” (ማቴ. 4:18-22) ለመሆኑ እነዚህ አራት ደቀ መዛሙርት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲሰማሩ የረዳቸው ነገር አለ? ወይስ ይህን ውሳኔ ያደረጉት ድንገት በስሜት ተገፋፍተው ነው? በስሜት ተገፍተው እንዳልሆነ ምንም ጥርጥር የለውም! እነዚህ ደቀ መዛሙርት ቀደም ባሉት ወራት፣ ኢየሱስ ሲሰብክ አዳምጠው የነበረ ከመሆኑም በላይ ተአምራትን ሲፈጽም፣ ለጽድቅ ያለውን ቅንዓት ሲያሳይና በርካታ ሰዎች ለምሥራቹ በጎ ምላሽ ሲሰጡ ተመልክተዋል። ይህም ይበልጥ በይሖዋ እንዲታመኑ አድርጓቸዋል።

7. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ይሖዋ ለሕዝቡ የሚያስፈልጋቸውን የመስጠት ችሎታ እንዳለው እምነት እንዲኖራቸው መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

7 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን በይሖዋ ላይ እምነት እንዲጥሉ በመርዳት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (ምሳሌ 3:5, 6) የምናስተምርበት መንገድ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል። በምናስተምርበት ወቅት፣ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የምናስቀድም ከሆነ አምላክ አትረፍርፎ እንደሚባርከን ቃል መግባቱን ጎላ አድርገን መጥቀስ እንችላለን። (ሚልክያስ 3:10ን እና ማቴዎስ 6:33ን አንብብ።) ይሖዋ ለሕዝቡ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚሰጣቸው ለማሳየት የተለያዩ ጥቅሶችን መጠቀም ብንችልም ራሳችን ምሳሌ ሆነን መገኘታችን የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አቅልለን ማየት የለብንም። የራሳችንን የሕይወት ተሞክሮ ለጥናቶቻችን መናገራችን በይሖዋ ላይ ያላቸው እምነት እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በተጨማሪም ከጽሑፎቻችን ላይ ያነበብናቸውን አበረታች ተሞክሮዎች ልናካፍላቸው እንችላለን። *

8. (ሀ) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ‘ቀምሶ ማየቱ’ ምን ጥቅም አለው? (ለ) ተማሪያችን የይሖዋን ጥሩነት በራሱ ሕይወት እንዲመለከት መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

8 ሌሎች የይሖዋን በረከት እንዴት እንዳገኙ በማንበብና በመስማት ብቻ ጠንካራ እምነት መገንባት አይቻልም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የይሖዋን ጥሩነት በራሱ ሕይወት ማየት ይኖርበታል። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ቸር [“ጥሩ፣” NW] መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ፤ እርሱን መጠጊያ የሚያደርግ ምንኛ ቡሩክ ነው!” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 34:8) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን የይሖዋን ጥሩነት እንዲቀምስ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን የገንዘብ ችግር አለበት እንበል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ማጨስ፣ ቁማር እንደ መጫወትና ከልክ በላይ እንደ መጠጣት ያሉ መጥፎ ልማዶችን ለመተው እየታገለ ይሆናል። (ምሳሌ 23:20, 21፤ 2 ቆሮ. 7:1፤ 1 ጢሞ. 6:10) እነዚህን መጥፎ ልማዶቹን ለማሸነፍ እንዲረዳው አምላክን በጸሎት መጠየቁ አስፈላጊ መሆኑን ማስገንዘባችን ተማሪው የይሖዋን ጥሩነት እንዲቀምስ ሊረዳው እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም ተማሪያችን ለሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ጊዜ በመመደብ፣ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በመዘጋጀትና በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ እንዲሰጥ ማበረታታታችን ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው መገንዘብ ይኖርብናል። እነዚህን ነገሮች ሲያደርግ የይሖዋን በረከት በራሱ ሕይወት ስለሚመለከት እምነቱ እያደገ ይሄዳል!

የሰው ፍርሃት

9, 10. (ሀ) ኒቆዲሞስና የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስ ተከታይ መሆናቸውን ሰዎች እንዳያውቁ ለማድረግ የሞከሩት ለምንድን ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ወንዶች ክርስቶስን ከመከተል ወደኋላ የሚሉት ለምንድን ነው?

9 አንዳንድ ወንዶች በሰዎች ተጽዕኖ የተነሳ ክርስቶስን ሙሉ በሙሉ ከመከተል ወደኋላ ይሉ ይሆናል። ኒቆዲሞስና የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስ ተከታይ መሆናቸውን ሰዎች እንዳያውቁ ለማድረግ ሞክረዋል፤ ምክንያቱም ሌሎች አይሁዳውያን ይህን ቢያውቁ ምን ሊሏቸው ወይም ምን እርምጃ ሊወስዱባቸው እንደሚችሉ በማሰብ ፍርሃት አድሮባቸው ነበር። (ዮሐ. 3:1, 2፤ 19:38) ይህ ፍርሃታቸው መሠረተ ቢስ አልነበረም። የሃይማኖት መሪዎቹ ለኢየሱስ ያላቸው ጥላቻ እየጨመረ በመምጣቱ በእሱ እንደሚያምን የተናገረ ማንኛውም ሰው ከምኩራብ እንዲገለል ያደርጉ ነበር።​—ዮሐ. 9:22

10 ዛሬም በአንዳንድ ቦታዎች አንድ ወንድ ለአምላክ ወይም ለመጽሐፍ ቅዱስ አሊያም ለሃይማኖት ከፍተኛ ፍላጎት ካሳየ ከሥራ ባልደረቦቹ፣ ከጓደኞቹ ወይም ከዘመዶቹ ትችት ይሰነዘርበት ወይም ተቃውሞ ይደርስበት ይሆናል። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ሃይማኖትን ስለ መቀየር ማውራት እንኳ አደገኛ ሊሆን ይችላል። በተለይ ደግሞ አንድ ሰው በጦር ሠራዊት ውስጥ እያገለገለ አሊያም በፖለቲካ ወይም ባለበት ማኅበረሰብ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ከሆነ የሚያጋጥመው ተጽዕኖ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። በጀርመን የሚኖር አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የምትሰብኩት ነገር እውነት መሆኑን አውቃለሁ። ነገር ግን፣ ዛሬ የይሖዋ ምሥክር ብሆን ነገ ሁሉም ሰው ማወቁ አይቀርም። የሥራ ባልደረቦቼ፣ ጎረቤቶቼ እንዲሁም እኔና ቤተሰቤን የሚያውቁ ሰዎች ምን ይሉኛል? ይህን መቋቋም አልችልም።”

11. ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ የሰው ፍርሃትን እንዲያሸንፉ የረዳቸው እንዴት ነው?

11 የኢየሱስ ሐዋርያት ደፋሮች ቢሆኑም እንኳ የሰው ፍርሃትን ለማሸነፍ ትግል ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር። (ማር. 14:50, 66-72) ሐዋርያቱ ሌሎች የሚያደርሱባቸውን ከፍተኛ ተጽዕኖ ተቋቁመው መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ኢየሱስ የረዳቸው እንዴት ነው? ኢየሱስ ወደፊት ለሚያጋጥማቸው ተቃውሞ ደቀ መዛሙርቱን አዘጋጅቷቸዋል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ሰዎች፣ በሰው ልጅ ምክንያት በሚጠሏችሁ፣ በሚያገሏችሁ፣ በሚነቅፏችሁና ክፉ እንደሆናችሁ አድርገው ያለ ስማችሁ ስም በሚሰጧችሁ ጊዜ ሁሉ ደስተኞች ናችሁ።” (ሉቃስ 6:22) ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ነቀፋ ሊደርስባቸው እንደሚችል መጠበቅ እንዳለባቸው አስጠንቅቋቸዋል። የሚደርስባቸው ማንኛውም ነቀፋ “በሰው ልጅ ምክንያት” እንደሆነ ገልጾላቸዋል። በተጨማሪም ይሖዋ እንደሚረዳቸውና እንደሚደግፋቸው እስከተማመኑ ድረስ አምላክ ከጎናቸው እንደሚሆን ኢየሱስ አረጋግጦላቸዋል። (ሉቃስ 12:4-12) ከዚህም በላይ አዳዲስ ሰዎች፣ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነፃነት እንዲቀራረቡና ከእነሱ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ያደርግ ነበር።​—ማር. 10:29, 30

12. አዲሶች የሰው ፍርሃትን እንዲያሸንፉ መርዳት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

12 እኛም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን የሰው ፍርሃትን ማሸነፍ እንዲችሉ መርዳት ይኖርብናል። ምን ፈታኝ ሁኔታ እንደሚያጋጥማቸው አስቀድመው ካወቁ ለመቋቋም ቀላል ይሆንላቸዋል። (ዮሐ. 15:19) ለምሳሌ ተማሪያችሁ፣ የሥራ ባልደረቦቹም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ለሚያነሱት ጥያቄ ወይም የተቃውሞ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቀላልና አሳማኝ የሆነ መልስ እንዴት መስጠት እንደሚችል ለምን አታሠለጥኑትም? እኛ ራሳችን ከተማሪያችን ጋር የተቀራረበ ወዳጅነት ለመመሥረት ጥረት ከማድረግ ባሻገር ከእሱ ጋር የሚመሳሰል ዝንባሌ ወይም ተሞክሮ ካላቸው የጉባኤው አባላት ጋር ማስተዋወቃችን ጥሩ ነው። ከሁሉም በላይ አዘውትሮ ልባዊ ጸሎት እንዲያቀርብ ማስተማር ይኖርብናል። ይህ ደግሞ ወደ አምላክ እንዲቀርብ እንዲሁም ይሖዋን ምሽጉና ዐለቱ እንዲያደርግ ይረዳዋል።​—መዝሙር 94:21-23ን እና ያዕቆብ 4:8ን አንብብ።

ብቃት የለኝም የሚል ስሜት

13. ብቃት የለኝም የሚለው ስሜት አንዳንዶች በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ከመካፈል ወደኋላ እንዲሉ የሚያደርጋቸው እንዴት ነው?

13 አንዳንድ ወንዶች በደንብ ማንበብ ወይም ሐሳባቸውን በትክክል መግለጽ ባለመቻላቸው አሊያም ዓይን አፋር በመሆናቸው ብቻ በአንዳንድ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ከመካፈል ወደኋላ ይላሉ። አንዳንዶቹ ብዙ ሰው ባለበት አመለካከታቸውንና ስሜታቸውን መግለጽ ይከብዳቸዋል። ማጥናት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ወይም እምነታቸውን ለሌሎች ማካፈል የሚለው ነገር ሲያስቡት እንኳ በጣም ያስፈራቸዋል። አንድ ወንድም ከቤት ወደ ቤት ስለ መሄድ ምን ይሰማው እንደነበር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ልጅ ሳለሁ በፍጥነት ወደ በሩ እሄድና የበሩን ደወል የደወልኩ አስመስል ነበር፤ ከዚያም ማንም እንዳልሰማኝ ወይም እንዳላየኝ ተስፋ በማድረግ ቀስ ብዬ እሄዳለሁ። . . . ከቤት ወደ ቤት ስለመሄድ ሳስብ ሕመም ይሰማኝ ነበር።”

14. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጋኔን ያደረበትን ልጅ መፈወስ ያልቻሉት ለምንድን ነው?

14 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት፣ ጋኔን ያደረበትን ልጅ መፈወስ ሳይችሉ በቀሩበት ወቅት ብቃት የለኝም የሚል ስሜት ተሰምቷቸው ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። የልጁ አባት ወደ ኢየሱስ በመምጣት “[ልጄ] የሚጥል በሽታ ስላለበት በጠና ታሟል፤ አንዴ እሳት ውስጥ አንዴ ደግሞ ውኃ ውስጥ ይወድቃል፤ ወደ ደቀ መዛሙርትህ አምጥቼው ነበር፤ እነሱ ግን ሊፈውሱት አልቻሉም” አለው። ኢየሱስ ጋኔኑን በማስወጣት ልጁን ፈወሰው። ከዚያ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እምነታችሁ ስላነሰ ነው። እውነት እላችኋለሁ፣ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያክል እምነት ካላችሁ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም።” (ማቴ. 17:14-20) እንደ ተራራ ያሉ መሰናክሎችን ለመወጣት በይሖዋ ላይ እምነት ማሳደር አስፈላጊ ነው። አንድ ሰው ይህን እውነታ ማስተዋል ተስኖት ባሉት ችሎታዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ቢጀምር ምን የሚከሰት ይመስልሃል? ይህ ግለሰብ የሚያደርገው ነገር ሳይሳካለት ይቀራል፤ ይህ ደግሞ ብቃት የለኝም የሚል ስሜት እንዲያድርበት ያደርጋል።

15, 16. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ብቃት የለኝም የሚለውን ስሜት እንዲያሸንፍ ልንረዳው የምንችለው እንዴት ነው?

15 ብቃት የለኝም ከሚል ስሜት ጋር የሚታገልን ሰው ልንረዳው ከምንችልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ ከራሱ ይልቅ በይሖዋ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ማበረታታት ነው። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በተገቢው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ።” (1 ጴጥ. 5:6, 7) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን ይህን ሐሳብ ተግባራዊ እንዲያደርግ ከተፈለገ መንፈሳዊ ሰው እንዲሆን ልንረዳው ይገባል። መንፈሳዊ ዝንባሌ ያለው ሰው ለመንፈሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ ይሰጣል። ለአምላክ ቃል ፍቅር ይኖረዋል፤ እንዲሁም “የመንፈስ ፍሬ” ገጽታዎችን በሕይወቱ ለማንጸባረቅ ጥረት ያደርጋል። (ገላ. 5:22, 23) የጸሎት ሰው ይሆናል። (ፊልጵ. 4:6, 7) በተጨማሪም የሚያጋጥመውን ማንኛውንም ሁኔታ ለመቋቋም ወይም የሚሰጠውን ማንኛውንም ኃላፊነት በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስችለውን ድፍረትና ጥንካሬ ለማግኘት ፊቱን ወደ አምላክ ያዞራል።​—2 ጢሞቴዎስ 1:7, 8ን አንብብ።

16 አንዳንድ ተማሪዎች የማንበብ፣ ሐሳባቸውን የመግለጽ ወይም የመናገር ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ በተግባር የተደገፈ እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ይሖዋን ከማወቃቸው በፊት በፈጸሟቸው መጥፎ ድርጊቶች የተነሳ አምላክን ለማገልገል ብቁ እንዳልሆኑ ሊሰማቸው ይችላል። በሁለቱም ሁኔታዎች ቢሆን የሚያስፈልገው እነዚህን ሰዎች በፍቅርና በትዕግሥት መርዳት ብቻ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም” ብሏል።​—ማቴ. 9:12

ብዙ ወንዶችን ‘ለማጥመድ’ ጥረት አድርጉ

17, 18. (ሀ) በአገልግሎታችን ላይ ለብዙ ወንዶች መስበክ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በቀጣዩ የጥናት ርዕስ ላይ የምናጠናው ስለ ምን ጉዳይ ነው?

17 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ለሚገኘውና ጥልቅ እርካታ ለሚሰጠው መልእክት ወደፊት ሌሎች በርካታ ወንዶች ምላሽ እንደሚሰጡ ተስፋ እናደርጋለን። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ታዲያ በአገልግሎታችን ላይ ለብዙ ወንዶች መስበክ የምንችለው እንዴት ነው? በአብዛኛው ወንዶች በቤታቸው በሚገኙበት ጊዜያት ማለትም ምሽት ላይ፣ ቅዳሜና እሁድ ከሰዓት በኋላ ወይም በበዓል ቀናት ለመስበክ ሰፋ ያለ ጊዜ በመመደብ ይህን ማድረግ እንችላለን። ከተቻለ በሩን ለሚከፍትልን ሰው የቤቱን አባወራ ማነጋገር እንደምንፈልግ መግለጽ እንችላለን። አመቺ በሚሆንበት ጊዜ አብረውን ለሚሠሩ ወንዶች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር እንሞክር፤ እንዲሁም በክልላችን ውስጥ ለሚገኝ ባለቤቱ የይሖዋ ምሥክር ለሆነች የማያምን ባል ለመስበክ ጥረት እናድርግ።

18 ለምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ ለመስበክ ጥረት ስናደርግ ለእውነት አድናቆት ያላቸው ሰዎች በጎ ምላሽ እንደሚሰጡ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ለእውነት ልባዊ ፍላጎት የሚያሳዩ ሰዎችን ሁሉ በትዕግሥት እንርዳ። በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ የተጠመቁ ወንዶች በአምላክ ድርጅት ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ላይ ለመድረስ እንዲጣጣሩና ለዚያ የሚያስፈልገውን ብቃት እንዲያሟሉ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጻሕፍትን እንዲሁም በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ የሚወጡትን የሕይወት ተሞክሮዎች ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ቅድሚያ እንዲሰጡ ወንዶችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

• አዳዲስ ሰዎች የሌሎችን ተጽዕኖ እንዲቋቋሙ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

• አንዳንዶች ብቃት የለኝም የሚለውን ስሜት ማሸነፍ እንዲችሉ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለወንዶች ለመመሥከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ትጠቀምባቸዋለህ?

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ ፈተናዎችን መቋቋም እንዲችል ልታዘጋጀው የምትችለው እንዴት ነው?