በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ትክክለኛ ሰዓት ማወቅ ይቻላል?

ይህ ጥያቄ ሊነሳ የቻለው የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ማርቆስና ሐዋርያው ዮሐንስ የኢየሱስን አሟሟት አስመልክተው በመንፈስ መሪነት በጻፉት ዘገባ መካከል ልዩነት ያለ ስለሚመስል ነው። ማርቆስ፣ ወታደሮቹ ኢየሱስን ሲሰቅሉት “ጊዜው ሦስት ሰዓት ነበር” ብሏል። (ማር. 15:25) ዮሐንስ ደግሞ ጲላጦስ ኢየሱስ እንዲሰቀል ለአይሁዶች አሳልፎ በሰጠው ጊዜ ሰዓቱ “ስድስት ሰዓት ገደማ” እንደነበር ጽፏል። (ዮሐ. 19:14-16) የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች እነዚህን እርስ በርሳቸው የሚጋጩ የሚመስሉ ጥቅሶችን ለማስታረቅ የተለያዩ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። ይሁንና በሁለቱ ዘገባዎች መካከል ልዩነት የተፈጠረበትን ምክንያት ለማብራራት የሚያስችል አጥጋቢ መረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ያም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ስለ ጊዜ አቆጣጠር የነበራቸውን አመለካከት ማወቃችን ጠቃሚ ነው።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. አይሁዶች የቀኑን ክፍለ ጊዜ ፀሐይ ከምትወጣበት አንስተው በመቁጠር በ12 ሰዓታት ይከፋፍሉት ነበር። (ዮሐ. 11:9) በመሆኑም “ሦስት ሰዓት” የሚባለው ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት እስከ ሦስት ሰዓት ያለው ጊዜ ሲሆን “ስድስት ሰዓት” የሚባለው ሰዓት ደግሞ የሚያልቀው እኩለ ቀን ላይ ነበር። እርግጥ ነው፣ ፀሐይ የምትወጣበትና የምትጠልቅበት ጊዜ ከወቅት ወቅት ይለያያል። ስለሆነም የቀኑ ርዝመት እንደ ወቅቱ ሁኔታ እንደሚለያይ ግልጽ ነው። ከዚህም በላይ በቀኑ ክፍለ ጊዜ ሰዓት የሚቆጥሩት ፀሐይ የምትገኝበትን አቅጣጫ በመመልከት ነበር። በመሆኑም ሰዓቱን ሲናገሩ ትክክለኛውን ጊዜ ሳይሆን ግምቱን ነበር። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በአብዛኛው የምናገኘው በሦስት ሰዓት፣ በስድስት ሰዓት ወይም በዘጠኝ ሰዓት ስለተከናወኑ ድርጊቶች ነው፤ ይህም ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው ድርጊቱ በተጠቀሰው ጊዜ ገደማ መከናወኑን ነው። (ማቴ. 20:3, 5፤ ሥራ 10:3, 9, 30) ከእነዚህ ውጪ ለምሳሌ “ሰባት ሰዓት” እንደሚሉ ያሉ አገላለጾች መጠቀስ ያስፈለገው በሚተረከው ዘገባ ውስጥ ድርጊቱ የተከናወነበት ሰዓት መገለጹ አስፈላጊ ስለነበረ ነው።​—ዮሐ. 4:52

ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ቀን የተከናወኑት ነገሮች የተፈጸሙበትን ጊዜ አስመልክቶ በአራቱም የወንጌል ዘገባዎች ላይ የሰፈረው ሐሳብ እርስ በርሱ ይስማማል። ካህናትና ሽማግሌዎች ማለዳ ላይ እንደተሰበሰቡና ከዚያም ኢየሱስን ወደ ሮማዊው ገዥ ጳንጥዮስ ጲላጦስ እንደወሰዱት አራቱም ወንጌሎች ይናገራሉ። (ማቴ. 27:1፤ ማር. 15:1፤ ሉቃስ 22:66፤ ዮሐ. 18:28) ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ ከስድስት ሰዓት አንስቶ (በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ነበር) “እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ” አገሩ በሙሉ በጨለማ እንደተሸፈነ ዘግበዋል።​—ማቴ. 27:45, 46፤ ማር. 15:33, 34፤ ሉቃስ 23:44

ኢየሱስ የተሰቀለበትን ጊዜ በተመለከተ ልብ ሊባል የሚገባው አንድ አስፈላጊ ነጥብ አለ፦ በወቅቱ ግርፋት የስቅላቱ ሂደት አንዱ ክፍል ተደርጎ ይታይ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ግርፋቱ በጣም ከባድ ስለሚሆን ግለሰቡ ከግርፋቱ የተነሳ ሊሞት ይችላል። ኢየሱስም ቢሆን የመከራውን እንጨት መጀመሪያ ላይ ብቻውን ቢሸከመውም በኋላ ላይ ሌላ ሰው እንዲሸከም መደረጉ አሰቃቂ በሆነ መንገድ ተገርፎ እንደነበር ያሳያል።(ሉቃስ 23:26፤ ዮሐ. 19:17) ግርፋቱ የስቅላቱ ሂደት የመጀመሪያ ክፍል ተደርጎ የሚታይ ከሆነ ኢየሱስ በመከራው እንጨት ላይ ከመቸንከሩ በፊት የተወሰነ ጊዜ አልፎ መሆን አለበት። በመሆኑም የተለያዩ ግለሰቦች ኢየሱስ የተሰቀለበትን ሰዓት በተመለከተ የተለያየ ጊዜ ሊናገሩ ይችላሉ፤ ይህን የሚወስነው ግለሰቡ የተመለከተው ከስቅላቱ ሂደት የትኛውን ክፍል ነው የሚለው ነው።

ሐዋርያው ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው ሌሎቹ ወንጌሎች ከተጻፉ ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በኋላ ነው። በመሆኑም እነሱ የጻፏቸውን ዘገባዎች የማንበብ አጋጣሚ ነበረው። ዮሐንስ በዘገባው ላይ ማርቆስ ከጠቀሰው የተለየ የሚመስል ሰዓት እንዳሰፈረ ግልጽ ነው። ይሁንና ይህ ሁኔታ ዮሐንስ የማርቆስን ዘገባ እንዳለ ለመገልበጥ እንዳልሞከረ በግልጽ ያሳያል። ዮሐንስም ሆነ ማርቆስ ወንጌሎቹን የጻፉት በአምላክ መንፈስ መሪነት ነው። በሁለቱ ዘገባዎች መካከል ልዩነት የተፈጠረበትን ምክንያት ለማብራራት የሚያስችል አጥጋቢ መረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም በእነዚህ የወንጌል ዘገባዎች ላይ እምነት መጣል እንችላለን።