በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕመም ደስታህን እንዲሰርቅብህ አትፍቀድ

ሕመም ደስታህን እንዲሰርቅብህ አትፍቀድ

ሕመም ደስታህን እንዲሰርቅብህ አትፍቀድ

ጠዋት ከእንቅልፍህ እንደተነሳህ ‘አሁን ደግሞ ይህ ቀን እንዴት ያልፍ ይሆን?’ ብለህ የተጨነቅክባቸው ጊዜያት ይኖሩ ይሆናል። በእያንዳንዱ ቀን የሚያጋጥምህን አካላዊ አሊያም ስሜታዊ ሥቃይ ማሰቡ ጭንቀት ሊያስከትልብህ ይችላል። እንዲያውም “እንዲህ ሆኖ ከመኖር . . . መሞትን እመርጣለሁ” በማለት እንደተናገረው እንደ ኢዮብ ይሰማህ ይሆናል። (ኢዮብ 7:15) ያለህበት ሁኔታ ለረጅም ጊዜ እንዲያውም ለዓመታት የሚዘልቅ ቢሆንስ?

ሜምፊቦስቴ ያለበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነት ነበር። ሜምፊቦስቴ የንጉሥ ዳዊት ጓደኛ የነበረው የዮናታን ልጅ ሲሆን የአምስት ዓመት ልጅ ሳለ ‘በመውደቁ ሽባ ሆኖ’ ነበር። (2 ሳሙ. 4:4) የአካል ጉዳተኛ በመሆኑ የሚደርስበት ሥቃይ ሳያንስ በአንድ ወቅት ንጉሡን እንደከዳ ተደርጎ በሐሰት መከሰሱና ንብረቱን ማጣቱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሳይሆንበት አልቀረም። ሆኖም ሜምፊቦስቴ የአካል ጉዳት ቢኖርበትም፣ ስሙ ቢጠፋም እንዲሁም የሚያበሳጭ ነገር ቢያጋጥመውም እነዚህን ነገሮች ተቋቁሞ በመጽናቱና ደስታውን እንዲሰርቁበት ባለመፍቀዱ ለእኛ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል።​—2 ሳሙ. 9:6-10፤ 16:1-4፤ 19:24-30

ምሳሌ የሚሆነን ሌላው ሰው ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። በአንድ ወቅት፣ “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ” በማለት የጠራውን ችግር ተቋቁሞ መኖር እንደነበረበት ጽፏል። (2 ቆሮ. 12:7) እዚህ ላይ ጳውሎስ እሾህ በማለት የጠቀሰው፣ ለረጅም ጊዜ አብሮት የኖረውን አካላዊ ችግር ወይም ሐዋርያነቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎችን ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፣ ችግሩ ዘላቂ በመሆኑ ሁኔታው ያስከተለበትን አካላዊና ስሜታዊ ሥቃይ ተቋቁሞ መኖር ግድ ሆኖበት ነበር።​—2 ቆሮ. 12:9, 10

በዛሬው ጊዜም አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች በቀላሉ የማይድንና አቅም የሚያሳጣ ሕመም ሊይዛቸው ወይም የስሜት ቀውስ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ማግዳሊና በ18 ዓመቷ ሲስተሚክ ሉፐስ ኤራይቲማቶሰስ የሚባል በሽታ እንዳለባት ታወቀ፤ አንድ ሰው በዚህ ሕመም በሚያዝበት ጊዜ በሽታ ተከላካይ ሴሎቹ የራሱን የሰውነት ክፍሎች እንደ ባዕድ ቆጥረው ያጠቃሉ። “ይህ በሽታ እንዳለብኝ ሲነገረኝ በጣም ደነገጥኩ” በማለት ማግዳሊና ተናግራለች። “ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሁኔታዬ እየተባባሰ ሄደ፤ በዚያ ላይ የምግብ መፈጨት ችግር፣ የአፍ ቁስለትና የታይሮይድ ዕጢ ችግር ሁኔታዬን የከፋ እንዲሆን አደረጉት።” ኢዛቤላ ደግሞ ለሌሎች በግልጽ ከማይታይ ችግር ጋር እየታገለች መኖር ነበረባት። እንዲህ ብላለች፦ “ከልጅነቴ ጀምሮ በመንፈስ ጭንቀት እሠቃያለሁ። በዚህም የተነሳ ድንገተኛ የሆነ የመሸበር ስሜት ይሰማኛል፤ እንዲሁም የሆድ ቁርጠትና የመተንፈስ ችግር ያጋጥመኛል። በመሆኑም ብዙ ጊዜ የድካም ስሜት ይሰማኛል።”

እውነታውን አምኖ መቀበል

በሽታና የአቅም ማጣት ሕይወትህን ሊያመሰቃቅሉት ይችላሉ። በዚህ ጊዜ፣ ረጋ ብለህ ያለህበትን ሁኔታ በሐቀኝነት መርምር። እርግጥ ነው፣ የአቅም ገደብ እንዳለብህ አምኖ መቀበል ሊከብድህ ይችላል። ማግዳሊና እንዲህ ብላለች፦ “ያለብኝ ሕመም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ ነው። ብዙ ጊዜ በጣም ስለሚደክመኝ ከአልጋዬ መነሳት እንኳ ያቅተኛል። የበሽታው ባሕርይ ተለዋዋጭ መሆኑ አስቀድሜ ፕሮግራም እንዳላወጣ አድርጎኛል። ከሁሉ ይልቅ የሚያስጨንቀኝ ግን እንደ ድሮ ይሖዋን ማገልገል አለመቻሌ ነው።”

በሌላ በኩል ዝቤግኒየቭ ስላለበት ሁኔታ እንዲህ ብሏል፦ “ያለብኝ ሩማቶይድ አርትራይተስ የተባለ በሽታ መገጣጠሚያዎቼን አንድ በአንድ በመጉዳት ከዓመት ወደ ዓመት ኃይሌን እያሟጠጠው መጣ። ሕመሙ ከባድ በሚሆንበት ጊዜ ቀላል የሚባሉ ሥራዎችን እንኳ ማከናወን ያቅተኛል። ይህ ደግሞ የከንቱነት ስሜት እንዲሰማኝ ያደርጋል።”

የአንጎል ዕጢ እንዳለባት ከጥቂት ዓመት በፊት ያወቀችው ባርባራ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “በሰውነቴ ላይ ድንገተኛ የሆኑ ለውጦች መታየት ጀመሩ። ሰውነቴ የሚልፈሰፈስ ከመሆኑ በላይ በተደጋጋሚ ራሴን ያመኛል፤ እንዲሁም ትኩረቴን መሰብሰብ የሚያቅተኝ ጊዜ አለ። የአቅም ገደብ እንዳለብኝ ከተገነዘብኩ በኋላ ሁኔታዬን አንድ በአንድ መገምገም አስፈልጎኝ ነበር።”

እነዚህ ግለሰቦች በሙሉ ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች ናቸው። እነዚህ ክርስቲያኖች፣ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጡት ነገር ነው። ሙሉ በሙሉ በአምላክ ይታመናሉ እንዲሁም የሚሰጣቸውን እርዳታ ይቀበላሉ።​—ምሳሌ 3:5, 6

ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው?

አንድ ሰው መከራ የሚደርስበት የአምላክን ሞገስ ስላጣ ነው ብለን ከማሰብ መቆጠብ ይኖርብናል። (ሰቆ. 3:33) ኢዮብ ‘ነቀፋ የሌለበትና ቅን’ ሰው ቢሆንም ምን እንደደረሰበት አስታውስ። (ኢዮብ 1:8) አምላክ ክፉ ነገሮችን በማምጣት ማንንም አይፈትንም። (ያዕ. 1:13) በቀላሉ የማይድኑ በሽታዎችንና የስሜት ሥቃይን ጨምሮ ማንኛውንም ሕመም የወረስነው የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ከሆኑት ከአዳምና ከሔዋን ነው።​—ሮም 5:12

ይሁን እንጂ ይሖዋና ኢየሱስ፣ ጻድቃኖች ሲቸገሩ ዝም ብለው አያዩም። (መዝ. 34:15) በተለይ ደግሞ በሕይወታችን ውስጥ አስቸጋሪ ነገሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ አምላክ ‘መጠጊያችንና ምሽጋችን’ መሆኑን ይበልጥ እናስተውላለን። (መዝ. 91:2) ታዲያ በቀላሉ ከማንገላገለው ችግር ጋር በምንታገልበት ወቅት ደስታችንን ጠብቀን ለመኖር ምን ሊረዳን ይችላል?

ጸሎት፦ ልክ እንደ ጥንቶቹ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አንተም በጸሎት አማካኝነት ሸክምህን በሰማዩ አባትህ ላይ መጣል ትችላለህ። (መዝ. 55:22) እንዲህ ስታደርግ “ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም” ይኖርሃል። ይህ ውስጣዊ ሰላም ‘ልብህንና አእምሮህን ይጠብቅልሃል።’ (ፊልጵ. 4:6, 7) ማግዳሊና በአምላክ በመታመን ወደ እሱ መጸለይዋ ያለባትን አቅም የሚያሳጣ ሕመም እንድትቋቋም አስችሏታል። እንዲህ ብላለች፦ “የልቤን አውጥቼ ለይሖዋ መንገሬ እፎይታ አስገኝቶልኛል፤ እንዲሁም ደስታዬን መልሼ ማግኘት እንድችል አድርጎኛል። በእያንዳንዱ ዕለት በአምላክ መታመን ምን ማለት እንደሆነ አሁን በደንብ ገብቶኛል።”​—2 ቆሮ. 1:3, 4

ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ፣ በቃሉና በክርስቲያን ወንድሞቻችን አማካኝነት አስፈላጊውን ጥንካሬ እንድታገኝ በማድረግ ለጸሎትህ መልስ ሊሰጥህ ይችላል። አምላክ በተአምራዊ መንገድ ያለብህን የአቅም ገደብ እንዲያስወግድልህ መጠበቅ የለብህም። ይሁንና የሚያጋጥምህን እያንዳንዱን ፈታኝ ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብና ጥንካሬ እንደሚሰጥህ መተማመን ትችላለህ። (ምሳሌ 2:7) ከአምላክ የምታገኘው “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነው ኃይል” ብርታት ሊሰጥህ ይችላል።​—2 ቆሮ. 4:7

ቤተሰብ፦ በቤት ውስጥ ፍቅርና ርኅራኄ የሚንጸባረቅበት መንፈስ መኖሩ በሽታህን እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል። የቤተሰብህ አባላትም ቢሆኑ የአንተ ሁኔታ እንደሚያስጨንቃቸው ማስታወስ ይኖርብሃል። እነሱም ልክ እንደ አንተው ምንም ማድረግ ባለመቻላቸው በሐዘን ሊዋጡ ይችላሉ። ያም ቢሆን ምንጊዜም ሌላው ቀርቶ በአስቸጋሪ ጊዜያትም ጭምር አንተን ለመርዳት ከጎንህ ናቸው። አብራችሁ መጸለያችሁ ውስጣዊ ሰላም እንዲኖርህ ይረዳሃል።​—ምሳሌ 14:30

ባርባራ፣ ሴት ልጇንና በጉባኤዋ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ወጣት እህቶችን አስመልክታ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በአገልግሎት እንድካፈል ይረዱኛል። ቅንዓታቸውን ስመለከት ልቤ በደስታ ይሞላል።” ዝቤግኒየቭ ሚስቱ የምታደርግለት ድጋፍ በዋጋ የማይተመን እንደሆነ ይሰማዋል። እንዲህ ይላል፦ “አብዛኞቹን የቤት ውስጥ ሥራዎች የምታከናውነው እሷ ነች። ከዚህም በላይ ወደ ጉባኤ ስብሰባዎችና ወደ አገልግሎት ለመሄድ ስዘጋጅ ልብሴን እንድለብስ ትረዳኛለች፤ እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ ቦርሳዬን ትይዝልኛለች።”

የእምነት ባልንጀሮች፦ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በምንሆንበት ጊዜ እንበረታታለን እንዲሁም እንጽናናለን። ይሁንና በሕመምህ ምክንያት በስብሰባዎች ላይ መገኘት ባትችልስ? ማግዳሊና እንዲህ ብላለች፦ “ጉባኤው፣ ስብሰባው እንዳያመልጠኝ ሲል የሚተላለፉትን ትምህርቶች ይቀዳልኛል። ብዙ ጊዜ የእምነት ባልንጀሮቼ ሊያደርጉልኝ የሚችሉት ነገር ካለ እንድነግራቸው ስልክ ደውለው ይጠይቁኛል። አበረታች ደብዳቤዎችንም ይልኩልኛል። እንደሚያስቡልኝና ስለ እኔ ደኅንነት እንደሚጨነቁ ማወቄ ችግሩን እንድቋቋም ረድቶኛል።”

በመንፈስ ጭንቀት የምትሠቃየው ኢዛቤላ ደግሞ እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “በጉባኤ ውስጥ የሚያዳምጡኝና ችግሬን ለመረዳት የሚጥሩ ብዙ ‘አባቶችን’ እና ‘እናቶችን’ አግኝቻለሁ። ጉባኤውን የማየው እንደ ቤተሰቤ ነው፤ ሰላምና ደስታ የማገኘው እዚያ ስሆን ነው።”

የተለያዩ ችግሮች እየደረሱባቸው ያሉ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከሌሎች “መለየት” ወይም ማግለል አይኖርባቸውም። ከዚህ ይልቅ ከጉባኤው ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ከፍ አድርገው መመልከት አለባቸው። (ምሳሌ 18:1 የ1954 ትርጉም) እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ ለሌሎች ትልቅ የብርታት ምንጭ ይሆናሉ። የሚያስፈልግህ ነገር ምን እንደሆነ ለመንፈሳዊ ወንድሞችህና እህቶችህ ለመናገር መጀመሪያ ላይ ታቅማማ ይሆናል። ነገር ግን የእምነት ባልንጀሮችህ የምትፈልገውን ነገር በግልጽ መናገርህ ያስደስታቸዋል። ምክንያቱም “ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ” ለማሳየት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (1 ጴጥ. 1:22) በመኪናቸው ወደ ጉባኤ እንዲወስዱህ ወይም አብረሃቸው ማገልገል ትችል እንደሆነ ለምን አትጠይቃቸውም? አሊያም ከእነሱ ጋር በግል ተገናኝተህ መጫወት እንደምትፈልግ ልትነግራቸው ትችላለህ። እርግጥ ነው፣ ከእነሱ ብዙ መጠበቅ የለብንም፤ ከዚህ ይልቅ ለሚያደርጉልን ነገር አመስጋኝ መሆን ይኖርብናል።

አዎንታዊ አመለካከት፦ በቀላሉ የማይድን በሽታ እያለብህም ደስታህን ጠብቀህ መኖርህ በአብዛኛው የተመካው በአመለካከትህ ላይ ነው። በችግርህ ላይ ብቻ የምታተኩርና ይህን እያሰብክ የምትቆዝም ከሆነ በቀላሉ አፍራሽ አመለካከቶች ሊመጡብህ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “በሕመም ጊዜ፣ ሰውን መንፈሱ ትደግፈዋለች፤ የተሰበረውን መንፈስ ግን ማን ሊሸከም ይችላል?” ይላል።​—ምሳሌ 18:14

ማግዳሊና እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “በችግሮቼ ላይ ብቻ ላለማተኮር ጥረት አደርጋለሁ። ጥሩ ጤንነት እንዳለኝ በሚሰማኝ ወቅት ዕለቱን በደንብ ተደስቼ ለማሳለፍ እሞክራለሁ። በቀላሉ የማይድን በሽታ እያለባቸውም ታማኝ ሆነው ስለቀጠሉ ክርስቲያኖች የሚናገሩ የሕይወት ታሪኮችን ማንበብ ያበረታታኛል።” ኢዛቤላ ደግሞ ይሖዋ እንደሚወዳትና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታት ማወቋ ብርታት ሆኗታል። “እንደምፈለግ ይሰማኛል፤ ይሖዋ በሕይወት ለመቀጠል ምክንያት ሆኖኛል። ከፊቴ አስደናቂ የሆነ ተስፋም ይጠብቀኛል” ብላለች።

ዝቤግኒየቭ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ያለብኝ ሕመም ትሕትናን እንዳዳብርና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ጭምር ታዛዥ እንድሆን ረድቶኛል። ነገሮችን በማስተዋል እንድመለከት እንዲሁም ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንዲኖረኝና አልፎ ተርፎም ከልቤ ሰዎችን ይቅር እንድል አስተምሮኛል። ያለሁበትን ሁኔታ እያሰብኩ መቆዘምን አቁሜ ይሖዋን ማገልገሌ ደስታ አስገኝቶልኛል፤ ይሖዋን በደስታ ማገልገል ተምሬያለሁ። እንዲያውም በመንፈሳዊ እድገት ማድረጌን እንድቀጥል ገፋፍቶኛል።”

ይሖዋ፣ በጽናት ለመቀጠል የምታደርገውን ማንኛውንም ጥረት እንደሚመለከት ምንጊዜም ማስታወስ ይኖርብሃል። እሱ ሥቃይህን ይረዳል እንዲሁም ስለ አንተ ያስባል። ‘የምታከናውነውን ሥራ እንዲሁም ለስሙ የምታሳየውን ፍቅር’ አይረሳም። (ዕብ. 6:10) እሱን ለሚፈሩ ሁሉ “ፈጽሞ አልተውህም፣ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት ቃል መግባቱን ልብ በል።​—ዕብ. 13:5

አልፎ አልፎ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሲሰማህ በአዲሱ ዓለም ስለሚኖረው አስደናቂ ሕይወት አስብ። የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ የሚያመጣቸውን በረከቶች በዓይንህ የምታይበት ጊዜ በጣም እየቀረበ ነው!

[በገጽ 28 እና 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕሎች]

በቀላሉ የማይድን ሕመም እያለባቸውም መስበካቸውን ቀጥለዋል

“ብቻዬን መሄድ እያቃተኝ ስለመጣ አገልግሎት ይዘውኝ የሚወጡት ባለቤቴ ወይም አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ናቸው። አገልግሎት ላይ የምጠቀምባቸውን መግቢያዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በቃሌ ለማስታወስ እሞክራለሁ።”​—የዢ፣ የማየት ችግር ያለባቸው

“ከስልክ በተጨማሪ ደብዳቤዎችን በመጻፍ እመሠክራለሁ፤ እንዲሁም ፍላጎት ካላቸው የተወሰኑ ሰዎች ጋር አዘውትሬ እጻጻፋለሁ። ሆስፒታል ስተኛ ሁልጊዜ አልጋዬ አጠገብ መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎች ጽሑፎችን አስቀምጣለሁ። ይህም ከብዙ ሰዎች ጋር ግሩም የሆኑ ውይይቶችን ለመጀመር በር ከፍቶልኛል።”​—ማግዳሊና፣ ሲስተሚክ ሉፐስ ኤራይቲማቶሰስ የሚባል በሽታ ያለባት

“ደስ የሚለኝ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ነው፤ ነገር ግን ጥሩ ስሜት በማይሰማኝ ጊዜ በስልክ እመሠክራለሁ።”​—ኢዛቤላ፣ በከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት የምትሠቃይ

“ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያስጠኑ አብሬ መገኘት ያስደስተኛል። ደህና በምሆንበት ጊዜ ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ መመሥከር ደስ ይለኛል።”​—ባርባራ፣ የአንጎል ዕጢ ያለባት

“አገልግሎት ስወጣ ብዙ ጽሑፍ አልይዝም። በመገጣጠሚያዬ ላይ የሚሰማኝ ሕመም እስካላስቸገረኝ ድረስ እያገለገልኩ እቆያለሁ።”​—ዝቤግኒየቭ፣ ሩማቶይድ አርትራይተስ በሚባል በሽታ የተያዘ

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወጣት አዋቂ ሳይል ሁሉም የብርታት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ