በአምላክ መንፈስ መመራት—በመጀመሪያው መቶ ዘመንና በዛሬው ጊዜ
በአምላክ መንፈስ መመራት—በመጀመሪያው መቶ ዘመንና በዛሬው ጊዜ
“እነዚህን ሁሉ አሠራሮች የሚያከናውነው ያው አንድ መንፈስ ነው።”—1 ቆሮ. 12:11
1. በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?
ጴንጤቆስጤ። ይህን ቃል ስትሰማ ድንቅ ነገሮች የተከናወኑበት ዕለት ወደ አእምሮህ ሳይመጣ አይቀርም። አምላክ በአገልጋዮቹ ላይ መንፈስ ቅዱስን ያፈሰሰው በዚህ ዕለት ነበር! (ሥራ 2:1-4) ይህ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በአምላክ አገልጋዮች ላይ ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መንገድ መሥራት መጀመሩን የሚጠቁም ነው። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ፣ በጥንት ጊዜ የነበሩ ታማኝ የአምላክ የአገልጋዮች የተሰጣቸውን አስቸጋሪ ተልእኮ እንዲወጡ የአምላክ መንፈስ እንዴት እንደረዳቸው ተመልክተን ነበር። ለመሆኑ የአምላክ መንፈስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይሠራ የነበረበት መንገድ በቅድመ ክርስትና ዘመን ይሠራ ከነበረበት መንገድ የሚለየው እንዴት ነው? የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በዛሬው ጊዜ እያከናወነ ካለው ነገር ክርስቲያኖች ጥቅም ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።
“እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ!”
2. ማርያም፣ መንፈስ ቅዱስ ምን ነገሮችን ሲያከናውን ተመልክታለች?
2 ኢየሩሳሌም በሚገኘው ሰፊ ደርብ ውስጥ በተሰበሰቡ ደቀ መዛሙርት ላይ በትንቢት በተነገረው መሠረት መንፈስ ቅዱስ በፈሰሰ ጊዜ ማርያም በዚያ ተገኝታ ነበር። (ሥራ 1:13, 14) ይህ ሁኔታ ከመከሰቱ በፊት ባሉት ሦስት አሥርተ ዓመታት ውስጥም ቢሆን የይሖዋ መንፈስ አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን ሲያከናውን ተመልክታለች። ይሖዋ፣ ማርያም ድንግል እያለች እንድትጸንስ በማድረግ በሰማይ የነበረው ልጁ በምድር ላይ እንዲወለድ አድርጓል። ማርያም ልትፀንስ የቻለችው “በመንፈስ ቅዱስ” ነበር።—ማቴ. 1:20
3, 4. ማርያም ምን ዓይነት ዝንባሌ አሳይታለች? እኛስ የእሷን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
3 ማርያም ይህን ልዩ መብት ልታገኝ የቻለችው እንዴት ነው? መልአኩ ከእሷ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ሲገልጽላት ማርያም “እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ! እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። (ሉቃስ 1:38) ይህ አነጋገሯ ማንነቷን በግልጽ የሚያሳይ ሲሆን ይሖዋም ይህን አስቀድሞ አስተውሎ ነበር። ማርያም እንዲህ ዓይነት ፈጣን ምላሽ መስጠቷ አምላክ በዚህ ረገድ ያለውን ፈቃድ ለመፈጸም ዝግጁ እንደሆነች የሚጠቁም ነው። በአካባቢዋ ያሉ ሰዎች ማርገዟን ሲሰሙ ምን ሊሉ እንደሚችሉ ወይም እጮኛዋ ስለ ጉዳዩ ቢያውቅ ግንኙነታቸውን ሊነካው እንደሚችል በማሰብ ለማንገራገር አልሞከረችም። ራሷን ከአገልጋዮች ሁሉ እንደምታንስ ባሪያ አድርጋ መቁጠሯ ይሖዋን እንደ ጌታዋ አድርጋ እንደተቀበለችና ሙሉ በሙሉ እንደምትተማመንበት ያሳያል።
4 ከአምላክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ያጋጠሙህ ፈታኝ ሁኔታዎች ወይም ያሉብህ ኃላፊነቶች ከአቅምህ በላይ እንደሆኑብህ የሚሰማህ ጊዜ አለ? እያንዳንዳችን ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘አምላክ ነገሮችን የሚያከናውነው ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መልኩ እንደሆነ ሙሉ እምነት አለኝ? የእሱን ፈቃድ ለማከናወንስ ልባዊ ፍላጎት አለኝ?’ አምላክ በሙሉ ልባቸው በእሱ ለሚታመኑና ሉዓላዊነቱን ለሚቀበሉ ሰዎች መንፈሱን እንደሚሰጣቸው እርግጠኛ ሁን።—ሥራ 5:32
መንፈስ ቅዱስ ጴጥሮስን ረድቶታል
5. ጴጥሮስ በ33 ዓ.ም. ከዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት በፊት መንፈስ ቅዱስ በምን መንገዶች ሲሠራ ተመልክቷል?
5 ሐዋርያው ጴጥሮስም ልክ እንደ ማርያም በ33 ዓ.ም. ከዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት በፊት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ያለውን ኃይል በሕይወቱ ተመልክቷል። ኢየሱስ ለጴጥሮስም ሆነ ለሌሎቹ ሐዋርያት አጋንንትን የማስወጣት ሥልጣን ሰጥቷቸው ነበር። (ማር. 3:14-16) በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በዝርዝር የተገለጸ ነገር ባይኖርም ጴጥሮስ ይህን ሥልጣኑን ሳይጠቀምበት አይቀርም። በሌላ ወቅት ደግሞ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ላይ እየተራመደ ወደ እሱ እንዲመጣ ለጴጥሮስ ግብዣ አቅርቦለት ነበር፤ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በባሕር ላይ በመራመድ የአምላክ መንፈስ ያለውን ኃይል የመመልከት አጋጣሚ አግኝቷል። (ማቴዎስ 14:25-29ን አንብብ።) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጴጥሮስ፣ መንፈስ ቅዱስ ታላላቅ ነገሮችን ለማከናወን የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጠው ይተማመን ነበር። ብዙም ሳይቆይ ይኸው መንፈስ ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መንገድ በጴጥሮስና በሌሎች ደቀ መዛሙርት ላይ መሥራት ጀመረ።
6. በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለትም ሆነ ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ጴጥሮስ በአምላክ መንፈስ እርዳታ ምን ነገሮችን ማከናወን ችሏል?
6 በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ዕለት ጴጥሮስና ሌሎች ደቀ መዛሙርት በእንግድነት ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሰዎችን ቋንቋ የመናገር ተአምራዊ ችሎታ ተሰጣቸው። ከዚያም ጴጥሮስ ደቀ መዛሙርቱን በመወከል ለተሰበሰበው ሕዝብ ንግግር አቀረበ። (ሥራ 2:14-36) አልፎ አልፎ የችኩልነት ባሕርይ ይታይበትና ፍርሃት ያጠቃው የነበረ ይህ ሐዋርያ ዛቻና ስደት እያለም እንኳ በድፍረት ምሥክርነት መስጠት ችሎ ነበር። (ሥራ 4:18-20, 31) በተጨማሪም አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት አንዳንድ ነገሮችን ገልጦለታል። (ሥራ 5:8, 9) ሌላው ቀርቶ ሰዎችን ከሞት የማስነሳት ሥልጣን ጭምር ተሰጥቶት ነበር።—ሥራ 9:40
7. ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ከተቀባ በኋላ ግልጽ የሆኑለት አንዳንድ የኢየሱስ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው?
7 ጴጥሮስ ከጴንጤቆስጤ ዕለት በፊትም እንኳ ኢየሱስ ያስተማራቸውን በርካታ እውነቶች መረዳት ችሎ ነበር። (ማቴ. 16:16, 17፤ ዮሐ. 6:68) ይሁንና ኢየሱስ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዳንዶቹ ግልጽ የሆኑለት ከዚያን ዕለት ጀምሮ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቶስ ከሦስት ቀን በኋላ መንፈሳዊ አካል ይዞ እንደሚነሳ እንዲሁም የአምላክ መንግሥት የሚቋቋመው በሰማይ እንደሆነ ከጴንጤቆስጤ ዕለት በፊት ማስተዋል አልቻለም ነበር። (ዮሐ. 20:6-10፤ ሥራ 1:6) ሰዎች መንፈሳዊ ፍጥረታት በመሆን በሰማይ በሚቋቋመው መንግሥት ውስጥ የመግዛት መብት ያገኛሉ የሚለው ሐሳብ ለጴጥሮስ እንግዳ ነበር። ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ከተጠመቀና ወደ ሰማይ የመሄድ መብት ካገኘ በኋላ ግን ኢየሱስ እነዚህን ጉዳዮች አስመልክቶ ያስተማራቸውን ትምህርቶች መረዳት ችሏል።
8. በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖችም ሆኑ “ሌሎች በጎች” ስለ ምን ነገሮች ማወቅ ችለዋል?
8 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስ ከፈሰሰላቸው በኋላ ከዚህ በፊት ያልተረዷቸውን ነገሮች ማስተዋል ጀመሩ። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች የይሖዋን ዓላማ ግሩም ገጽታዎች በተብራራ መንገድ እንዲጽፉ መንፈስ ቅዱስ መርቷቸዋል፤ ይህ ደግሞ ለእኛ ከፍተኛ ጥቅም አለው። (ኤፌ. 3:8-11, 18) በዛሬው ጊዜ፣ በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖችም ሆኑ “ሌሎች በጎች” እነዚህን መንፈሳዊ እውነቶች በአንድነት እየተመገቡ ነው። (ዮሐ. 10:16) አንተስ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውንና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የቀረበልህን እውቀትና ማስተዋል ከፍ አድርገህ ትመለከታለህ?
‘ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞላ’
9. ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ምን ነገሮችን ማከናወን ችሏል?
9 በ33 ዓ.ም. የዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ከተከበረ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ አንድ ሌላ ሰው የአምላክ ስጦታ የሆነውን መንፈስ ቅዱስ ተቀብሎ ነበር። ይህ ሰው በኋላ ላይ ጳውሎስ በመባል የታወቀው ሳኦል ነበር። መንፈስ ቅዱስ በእሱ ላይ መሥራቱ እኛን የሚጠቅም ነገር እንዲያከናውን አስችሎታል። ሐዋርያው ጳውሎስ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑ 14 መጻሕፍትን በመንፈስ መሪነት ጽፏል። የአምላክ መንፈስ ጴጥሮስን እንደረዳው ሁሉ በሰማይ የማይሞትና የማይበሰብስ ሕይወት ስለማግኘት የሚገልጸውን ተስፋ በግልጽ መረዳትና በጽሑፍ ማስፈር እንዲችል ጳውሎስንም ረድቶታል። ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የታመሙትን መፈወስ፣ አጋንንትን ማስወጣት ሌላው ቀርቶ የሞተ ሰው እንኳ ማስነሳት ችሏል! ሆኖም ጳውሎስ፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ያገኘው ኃይል ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር እንዲያከናውን አስችሎታል። ተአምራዊ በሆነ መንገድ ባይሆንም በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ይህን ተግባር ለማከናወን የሚያስችል ኃይል ከመንፈስ ቅዱስ ያገኛሉ።
10. መንፈስ ቅዱስ በጳውሎስ የንግግር ችሎታ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል?
10 ጳውሎስ ‘በመንፈስ ቅዱስ በመሞላቱ’ ጠንቋይ የሆነን አንድ ሰው በድፍረት መቃወም ችሏል። ይህ ሁኔታ፣ ጳውሎስ ከጠንቋዩ ጋር ሲነጋገር ያዳምጥ በነበረው የቆጵሮስ አገረ ገዥ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። “አገረ ገዥውም በይሖዋ ትምህርት ተደንቆ ስለነበር” እውነትን ተቀበለ። (ሥራ 13:8-12) ጳውሎስ፣ እውነትን በመመሥከር ረገድ የአምላክ መንፈስ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት በሚገባ እንደተገነዘበ ግልጽ ነው። (ማቴ. 10:20) በሌላ በኩል ደግሞ “የመናገር ችሎታ” ይሰጠው ዘንድ የኤፌሶን ወንድሞች ምልጃ እንዲያቀርቡለት ተማጽኗቸው ነበር።—ኤፌ. 6:18-20
11. ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ ይመራ የነበረው እንዴት ነው?
11 መንፈስ ቅዱስ ለጳውሎስ የመናገር ችሎታ መስጠት ብቻ ሳይሆን ወደ አንዳንድ አካባቢዎች እንዳይሄድ የከለከለው ጊዜም ነበር። ጳውሎስ የሚስዮናዊነት ጉዞውን በሚያደርግበት ወቅት በአምላክ መንፈስ ይመራ ነበር። (ሥራ 13:2፤ የሐዋርያት ሥራ 16:6-10ን አንብብ።) አሁንም ቢሆን ይሖዋ የስብከቱን ሥራ በመንፈሱ አማካኝነት እየመራው ነው። ታዛዥ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ እንደ ጳውሎስ እውነትን በድፍረትና በቅንዓት ለማወጅ ጥረት ያደርጋሉ። በዛሬው ጊዜ የአምላክ መንፈስ የሚሰጠው አመራር እንደ ጳውሎስ ዘመን በግልጽ የሚታይ ባይሆንም ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን ተጠቅሞ፣ ለሚገባቸው ሰዎች እውነትን የመስማት አጋጣሚ እንደሚከፍትላቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዮሐ. 6:44
“ልዩ ልዩ አሠራሮች”
12-14. መንፈስ ቅዱስ በሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ላይ የሚሠራው በተመሳሳይ መንገድ ነው? አብራራ።
12 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ እንደባረከው ከሚናገረው ዘገባ ማበረታቻ ማግኘት ይችላሉ? ምን ጥርጥር አለው! ጳውሎስ በወቅቱ የነበሩትን የመንፈስ ቅዱስ ተአምራዊ ስጦታዎች አስመልክቶ ለቆሮንቶስ ጉባኤ እንደሚከተለው በማለት በመንፈስ መሪነት መጻፉን ልብ ማለት ይገባል፦ “ልዩ ልዩ ስጦታዎች አሉ፤ መንፈስ ግን ያው አንድ መንፈስ ነው፤ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፤ ጌታ ግን ያው አንድ ጌታ ነው፤ በተጨማሪም ልዩ ልዩ አሠራሮች አሉ፤ ሆኖም የተለያዩ አሠራሮችን በመጠቀም በሁሉም ሰዎች ላይ የሚሠራው ያው አንድ አምላክ ነው።” (1 ቆሮ. 12:4-6, 11) አዎን፣ መንፈስ ቅዱስ አንድን ዓላማ ከዳር ለማድረስ በተለያዩ የአምላክ አገልጋዮች ላይ በተለያዩ መንገዶች ሊሠራ ይችላል። የክርስቶስ ንብረት የሆኑት ‘ታናሹ መንጋ’ እና “ሌሎች በጎች” መንፈስ ቅዱስን ማግኘት ይችላሉ። (ሉቃስ 12:32፤ ዮሐ. 10:16) ይሁንና የአምላክ መንፈስ በእያንዳንዱ የጉባኤ አባል ላይ ሁልጊዜ በተመሳሳይ መንገድ ይሠራል ማለት አይደለም።
13 ለምሳሌ ያህል፣ ሽማግሌዎች የሚሾሙት በመንፈስ ቅዱስ ነው። (ሥራ 20:28) ሆኖም በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በሙሉ በጉባኤ ውስጥ በበላይ ተመልካችነት ያገለግላሉ ማለት አይደለም። ታዲያ ከዚህ ሁኔታ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? የአምላክ መንፈስ በጉባኤው አባላት ላይ የሚሠራው በተለያዩ መንገዶች መሆኑን እንገነዘባለን።
14 ለቅቡዓን የተሰጣቸው “እንደ ልጅ የመቆጠር መብት የሚያስገኝ መንፈስ” ማለትም የአምላክ ልጅ እንደሆኑ እንዲሰማቸው የሚያደርገው መንፈስ ይሖዋ አንድያ ልጁን ከሞት አስነስቶ በሰማይ የማይሞት ሕይወት ለመስጠት ከተጠቀመበት መንፈስ ጋር ተመሳሳይ ነው። (ሮም 8:11, 15ን አንብብ።) ይሖዋ አጽናፈ ዓለምን ወደ ሕልውና ለማምጣት የተጠቀመውም በዚህ መንፈስ ነው። (ዘፍ. 1:1-3) በተጨማሪም ይሖዋ በዚህ መንፈስ አማካኝነት ከመገናኛው ድንኳን ጋር በተያያዘ ልዩ ችሎታ የሚያስፈልገውን ሥራ እንዲያከናውን ባስልኤልን ብቁ አድርጎታል። ልዩ ጥንካሬ የሚጠይቁ ነገሮችን እንዲፈጽም ለሳምሶን ኃይል ሰጥቶታል፤ እንዲሁም ጴጥሮስን በውኃ ላይ እንዲራመድ አስችሎታል። እንግዲያው መንፈሱን ማግኘትና በመንፈስ መቀባት አንድ እንደሆኑ አድርገን ማሰብ የለብንም፤ በመንፈስ መቀባት ከመንፈስ ቅዱስ ልዩ ልዩ አሠራሮች መካከል አንዱ ብቻ ነው። ደግሞም በመንፈስ የሚቀቡትን የሚመርጠው አምላክ ነው።
15. በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ለዘላለም የሚቀጥል ነገር ነው? አብራራ።
15 መንፈስ ቅዱስ በታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ላይ ለረጅም ዘመናት ሌላው ቀርቶ በመንፈስ መቀባት ከመጀመሩ በፊት ባሉት በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት በሕዝቦቹ ላይ በተለያዩ መንገዶች ሲሠራ ቆይቷል። በ33 ዓ.ም. ከዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት አንስቶ ግን የአምላክ መንፈስ ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መንገድ መሥራት ጀመረ፤ ሆኖም ይህ አሠራር ለዘላለም ይቀጥላል ማለት አይደለም። በመንፈስ መጠመቅ የሚያቆምበት ጊዜ አለ፤ የአምላክ ሕዝቦች ፈቃዱን ለዘላለም ማድረግ እንዲችሉ መንፈስ ቅዱስ በእነሱ ላይ መሥራቱን ግን ይቀጥላል።
16. በአሁኑ ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ምን እያደረጉ ነው?
16 የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ምን እያከናወነ ነው? ራእይ 22:17 “መንፈሱና ሙሽራይቱም ‘ና!’ እያሉ ነው። የሚሰማም ሁሉ ‘ና!’ ይበል። የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግ ሁሉ የሕይወትን ውኃ በነፃ ይውሰድ” በማለት መልሱን ይሰጠናል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች በአምላክ መንፈስ ተገፋፍተው የይሖዋን ጥሪ፣ የሕይወትን ውኃ ‘ለሚፈልግ ሁሉ’ ያቀርባሉ። ይህን ሥራ በግንባር ቀደምትነት የሚያከናውኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቢሆኑም ሌሎች በጎችም ግብዣውን ያቀርባሉ። ሁለቱም ቡድኖች፣ ሥራውን ለማከናወን የሚመሩበት የአምላክ መንፈስ አንድ ዓይነት ነው። በተጨማሪም ሁለቱም ቡድኖች “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” በመጠመቅ ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን አሳይተዋል። (ማቴ. 28:19) እንዲሁም የአምላክ መንፈስ በሕይወታቸው ውስጥ እንዲሠራ በመፍቀድ ፍሬ እንዲያፈራ ያደርጋሉ። (ገላ. 5:22, 23) እንደ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሁሉ ሌሎች በጎችም የአምላክ መንፈስ የሚሰጣቸውን እርዳታ ይቀበላሉ። በዚህ መንፈስ በመታገዝ የይሖዋን የቅድስና መሥፈርቶች ለማሟላት የተቻላቸውን ጥረት ያደርጋሉ።—2 ቆሮ. 7:1፤ ራእይ 7:9, 14
መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጣችሁ ደጋግማችሁ ለምኑ
17. የአምላክ መንፈስ እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
17 ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የምታደርገው በሰማይም ይሁን በምድር፣ ንጹሕ አቋምህን ጠብቀህ ሽልማትህን ማግኘት እንድትችል ይሖዋ “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ” ኃይል ሊሰጥህ ይችላል። (2 ቆሮ. 4:7) የመንግሥቱን ምሥራች በጽናት በመስበክህ አንዳንዶች ያፌዙብህ ይሆናል። ሆኖም የሚከተለውን ጥቅስ ማስታወስህ ጠቃሚ ነው፦ “ለክርስቶስ ስም ስትሉ ብትነቀፉ ደስተኞች ናችሁ፤ ምክንያቱም የክብር መንፈስ እንዲያውም የአምላክ መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋል።”—1 ጴጥ. 4:14
18, 19. ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት የሚረዳህ እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
18 አምላክ ከልብ ለሚፈልጉት መንፈስ ቅዱሱን በነፃ ይሰጣል። ይህ መንፈስ ችሎታህን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን በአምላክ አገልግሎት ምርጥህን ለመስጠት የሚያስችል ፍላጎት እንዲያድርብህም ያደርጋል። “እሱ ደስ ለሚሰኝበት ነገር ሲል ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ለተግባር እንድትነሳሱ በውስጣችሁ የሚሠራው አምላክ ነው።” ውድ የሆነው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ‘የሕይወትን ቃል ዘወትር አጥብቀን ለመያዝ’ ከምናደርገው ልባዊ ጥረት ጋር ተዳምሮ ‘በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችንን መዳን ለመፈጸም ተግተን እንድንሠራ’ ያነሳሳናል።—ፊልጵ. 2:12, 13, 16
19 በአምላክ መንፈስ ሙሉ በሙሉ በመተማመን የተጣለብህን ማንኛውም ኃላፊነት ለመወጣት ከልብህ ሥራ፤ የተሰጠህን ሥራ በጥራት አከናውን እንዲሁም ይሖዋን እንዲረዳህ ጠይቀው። (ያዕ. 1:5) አምላክ ቃሉን ለመረዳት፣ በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ችግሮች ለመቋቋምና ምሥራቹን ለመስበክ የሚያስፈልግህን እርዳታ ይሰጥሃል። የአምላክ ቃል “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታሰልሱ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል” በማለት ይመክረናል፤ ከምንጠይቀው ነገር አንዱ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ነው። (ሉቃስ 11:9, 13) ጥንትም ሆነ በዘመናችን እንዳሉት በመንፈስ ቅዱስ እንደተመሩት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ለመሆን ከፈለግህ አለማቋረጥ ለይሖዋ ምልጃ ማቅረብህ በእርግጥም አስፈላጊ ነው።
ልታብራራ ትችላለህ?
• ልክ እንደ ማርያም ምን ዓይነት ዝንባሌ ማሳየታችን በረከት ሊያስገኝልን ይችላል?
• ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ ይመራ እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?
• በዛሬው ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩት እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ መንፈስ፣ ጳውሎስ ክፉ መናፍስት የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ እንዲቋቋም አስችሎታል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች ተስፋቸው ምንም ይሁን ምን የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ማግኘት ይችላሉ