በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ከእውነት መሠረታዊ ገጽታዎች’ ትምህርት ማግኘት

‘ከእውነት መሠረታዊ ገጽታዎች’ ትምህርት ማግኘት

“በሕጉ ውስጥ ያለውን እውቀትና እውነት መሠረታዊ ገጽታዎች [ታውቃላችሁ]።”​—ሮም 2:20

1. የሙሴ ሕግ ምን ትርጉም እንዳለው መረዳታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የጻፋቸው ደብዳቤዎች ባይኖሩ ኖሮ የሙሴ ሕግ የተለያዩ ገጽታዎች ምን ትርጉም እንዳላቸው መረዳት አንችልም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ታማኝ ሊቀ ካህናት” የሆነው ኢየሱስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ “የማስተሰረያ መሥዋዕት” በማቅረብ፣ በቤዛው ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር ለሚያሳዩ ሰዎች “ዘላለማዊ መዳን” ያስገኘላቸው እንዴት እንደሆነ ግልጽ አድርጓል። (ዕብ. 2:17፤ 9:11, 12) ጳውሎስ የመገናኛው ድንኳን ‘ለሰማያዊ ነገሮች ጥላ’ እንደሆነ ብሎም ኢየሱስ መካከለኛ የሆነለት ቃል ኪዳን ሙሴ መካከለኛ ከሆነለት ቃል ኪዳን ጋር ሲነጻጸር ‘የተሻለ’ እንደሆነ ገልጿል። (ዕብ. 7:22፤ 8:1-5) በጳውሎስ ዘመን ሕጉን አስመልክቶ የሚሰጡ እንዲህ ያሉ ማብራሪያዎች እጅግ አስፈላጊ ነበሩ፤ በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እነዚህ ማብራሪያዎች አምላክ ያደረገልን ዝግጅት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ በተሟላ ሁኔታ ለመረዳት ያስችሉናል።

2. አይሁዳዊ የሆኑ ክርስቲያኖች ከአሕዛብ ከመጡት ይልቅ ምን የተሻለ አጋጣሚ ነበራቸው?

2 ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በላከው ደብዳቤ ላይ ያሉትን አንዳንድ ሐሳቦች በቀጥታ የጻፈው በትውልድ አይሁዳዊ ለነበሩና በሙሴ ሕግ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ለተማሩ የጉባኤው አባላት ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ከመለኮታዊው ሕግ ጋር ትውውቅ ስላላቸው ይሖዋንና የእሱን የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች በተመለከተ ‘የእውቀትንና የእውነትን መሠረታዊ ገጽታዎች’ የማወቅ አጋጣሚያቸው ሰፊ መሆኑን ጳውሎስ ተገንዝቦ ነበር። አይሁዳዊ የሆኑ ክርስቲያኖች ‘የእውነትን መሠረታዊ ገጽታዎች’ መረዳታቸውና ለእነዚህ ነገሮች ጥልቅ አክብሮት ማሳደራቸው ይሖዋ ለሕዝቡ የሰጠውን ሕግ ለማያውቁ ሰዎች ጥቅም አስገኝቷል። ምክንያቱም፣ እንደ ጥንቶቹ ታማኝ አይሁዳውያን ሁሉ እነዚህ ክርስቲያኖችም ሕጉን ለማያውቁ አሕዛብ እውነትን ማስተማርና ማስረዳት ችለዋል።​—ሮም 2:17-20ን አንብብ።

ለኢየሱስ መሥዋዕት ጥላ የሆኑ ነገሮች

3. የጥንቶቹ አይሁዳውያን ያቀርቧቸው ስለነበሩ መሥዋዕቶች ማጥናታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

3 ዛሬም ቢሆን የይሖዋን ዓላማዎች ለመረዳት ከፈለግን ጳውሎስ ስለጠቀሳቸው የእውነት መሠረታዊ ገጽታዎች ማወቃችን እጅግ አስፈላጊ ነው። ከሙሴ ሕግ በስተጀርባ ያሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ጠቃሚ ናቸው። ይህን በአእምሯችን በመያዝ የሕጉን አንድ ገጽታ ይኸውም መሥዋዕቶችን ከማቅረብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እንመለከታለን። በሌላ አባባል እነዚህ መሥዋዕቶች ትሑት የሆኑ አይሁዳውያንን ወደ ክርስቶስ የመሯቸውና አምላክ ከእነሱ ስለሚጠብቀው ነገር እንዲገነዘቡ የረዷቸው እንዴት እንደሆነ እናያለን። በተጨማሪም አምላክ መሥዋዕቶችን አስመልክቶ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግጋት ለአምላክ የምናቀርበውን ቅዱስ አገልግሎት ጥራት ለመመርመር የሚረዱን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን፤ ምክንያቱም ይሖዋ ከአገልጋዮቹ የሚጠብቀው መሠረታዊ ነገር ፈጽሞ አይለወጥም።​—ሚል. 3:6

4, 5. (ሀ) የሙሴ ሕግ የአምላክ ሕዝቦች ምን ነገር እንዲገነዘቡ አስችሏቸው ነበር? (ለ) መሥዋዕቶችን አስመልክቶ የተሰጡት የአምላክ ሕግጋት የሚያመለክቱት ምንን ነበር?

4 በሙሴ ሕግ ውስጥ የታቀፉት ትእዛዛት የጥንቶቹ አይሁዳውያን፣ ኃጢአተኞች መሆናቸውን እንዲገነዘቡ አድርገዋቸው እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል፣ የሞተን ሰው በድን የሚነካ ማንኛውም ግለሰብ የመንጻት ሥርዓት ማካሄድ ነበረበት። ይህን ሥርዓት ለመፈጸም በቅድሚያ እንከን የሌለባት አንዲት ቀይ ጊደር ታርዳ ትቃጠላለች። ከዚያም አመዱ ‘የመንጻት ውኃ’ ለማዘጋጀት ይውላል፤ በመቀጠል ግለሰቡ በረከሰ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን በዚህ ውኃ ይረጫል። (ዘኍ. 19:1-13) አንድ ሰው በሚጸነስበት ጊዜ አለፍጽምና እና ኃጢአትን እንደሚወርስ ለማስገንዘብ ደግሞ አንዲት ሴት በምትወልድበት ወቅት ለተወሰነ ጊዜ የረከሰች ትሆናለች፤ ከዚህ የምትነጻው ለስርየት የሚሆን መሥዋዕት ካቀረበች በኋላ ነበር።​—ዘሌ. 12:1-8

5 እስራኤላውያን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው በሚያጋጥሟቸው ሌሎች ጉዳዮችም ለኃጢአት ስርየት የሚሆን የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር። እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ተገነዘቡትም አልተገነዘቡት በይሖዋ ቤተ መቅደስ የሚቀርቡትን ጨምሮ በመገናኛው ድንኳን የሚቀርቡ መሥዋዕቶች ኢየሱስ ለሚያቀርበው ፍጹም መሥዋዕት “ጥላ” ነበሩ።​—ዕብ. 10:1-10

መሥዋዕቶች መቅረብ ያለባቸው በምን ዓይነት መንፈስ ነው?

6, 7. (ሀ) እስራኤላውያን ለመሥዋዕትነት የሚያቀርቡትን ነገር በሚመርጡበት ጊዜ ምን ነገሮችን ግምት ውስጥ ማስገባት ነበረባቸው? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን?

6 ለይሖዋ ከሚቀርቡ የእንስሳት መሥዋዕቶች ጋር በተያያዘ ከተሰጡ መሠረታዊ መመሪያዎች አንዱ እንስሳው ሙሉ በሙሉ “ፍጹም” ማለትም እውር ያልሆነ ወይም በተፈጥሮም ይሁን በሌላ ምክንያት ከሚመጣ የአካል ጉዳት ነፃ የሆነ አሊያም በሽታ የሌለበት እንዲሆን ያዛል። (ዘሌ. 22:20-22) እስራኤላውያን የፍራፍሬና የእህል መሥዋዕት ለይሖዋ በሚያቀርቡበት ጊዜ ከምርታቸው ‘በኩር’ ወይም “ምርጥ” የሆነውን ማቅረብ ነበረባቸው። (ዘኍ. 18:12, 29) ይሖዋ ዝቅ ያለ ጥራት ያለውን መሥዋዕት አይቀበልም ነበር። ከእንስሳ መሥዋዕት ጋር በተያያዘ የተሰጠው ይህ አስፈላጊ መሥፈርት የኢየሱስ መሥዋዕት ነውርና እንከን የሌለበት እንደሚሆን ይጠቁማል፤ በሌላ አባባል ይሖዋ የሰው ልጆችን ለመዋጀት ሲል የሚያቀርበው መሥዋዕት ለእሱ ምርጥ የሆነውንና እጅግ የተወደደውን እንደሚሆን ያመለክታል።​—1 ጴጥ. 1:18, 19

7 አንድ እስራኤላዊ ለይሖዋ ጥሩነት ልባዊ አድናቆት ካለው መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ካሉት ነገሮች እጅግ ምርጥ የሆነውን በደስታ ለመስጠት እንደሚነሳሳ ምንም ጥርጥር የለውም። እርግጥ ነው፣ መሥዋዕቱ ምን ያህል ጥራት አለው የሚለው ጉዳይ ለግለሰቡ የተተወ ነው። ይሁንና እንከን ያለበትን መሥዋዕት ቢያቀርብ አምላክ እንደማይደሰትበት ያውቃል፤ ምክንያቱም ይህ፣ ግለሰቡ መሥዋዕት ማቅረብን እንዲያው ለደንቡ ያህል የሚከናወን ሥርዓት አልፎ ተርፎም ሸክም እንደሆነ አድርጎ የሚመለከተው መሆኑን የሚጠቁም ነው። (ሚልክያስ 1:6-8, 13ን አንብብ።) እንግዲያው ለአምላክ የምናቀርበውን አገልግሎት በቁም ነገር ልናስብበት ይገባል፤ በመሆኑም እንዲህ እያልን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ይሖዋን የማገለግለው በምን ዓይነት መንፈስ ነው? የአገልግሎቴን ጥራትና እሱን ለማገልገል የተነሳሳሁበትን ዓላማ መለስ ብዬ ማጤን ያስፈልገኝ ይሆን?

8, 9. እስራኤላውያን መሥዋዕት ሲያቀርቡ ሊያሳዩ የሚችሉትን መንፈስ መመርመራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

8 አንድ እስራኤላዊ ለይሖዋ ያለውን ልባዊ ምስጋና ለመግለጽ ሲል በራሱ ተነሳስቶ መሥዋዕት የሚያቀርብበት ጊዜ አለ፤ ወይም ደግሞ የእሱን ሞገስ ለማግኘት ሲል የሚቃጠል መሥዋዕት ሊያቀርብ ይችላል። በዚህ ወቅት ተስማሚ የሆነ እንስሳ መምረጥ እንደማያስቸግረው የታወቀ ነው። ይህ የአምላክ አገልጋይ ለይሖዋ ምርጡን መስጠት መቻሉ ያስደስተዋል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች የሙሴ ሕግ እንደሚያዘው ቃል በቃል መሥዋዕት ማቅረብ አይጠበቅባቸውም፤ ያም ሆኖ ጊዜያቸውን፣ ኃይላቸውንና ሀብታቸውን ይሖዋን ለማገልገል ስለሚጠቀሙበት መሥዋዕት ያቀርባሉ ሊባል ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያናዊ ተስፋችንን ‘በይፋ ማወጅ’ እንዲሁም ‘መልካም ማድረግና ያለንን ነገር ለሌሎች ማካፈል’ ይሖዋን ደስ የሚያሰኙ መሥዋዕቶች እንደሆኑ ተናግሯል። (ዕብ. 13:15, 16) የይሖዋ ሕዝቦች እንዲህ በመሰሉ እንቅስቃሴዎች በሚካፈሉበት ወቅት የሚያሳዩት መንፈስ አምላክ ለሰጣቸው ነገሮች ምን ያህል አድናቂና አመስጋኝ እንደሆኑ ያሳያል። በመሆኑም በጥንት ዘመን የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች በፈቃደኝነት መሥዋዕቶችን በሚያቀርቡበት ወቅትም ሆነ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ይሖዋን በሚያገለግሉበት ጊዜ የሚያሳዩት ዝንባሌና ይህን ለማድረግ የሚያነሳሳቸው ውስጣዊ ግፊት ተመሳሳይ ነው።

9 ይሁንና አንድ እስራኤላዊ ስህተት ሲሠራ በሙሴ ሕግ መሠረት የኃጢአት ወይም የበደል መሥዋዕት እንዲያቀርብ የሚጠበቅበት ወቅት መኖሩስ ምን የሚያስተምረን ነገር አለ? ኃጢአት የፈጸመው ሰው ይህን መሥዋዕት የማቅረብ ግዴታ ያለበት መሆኑ በግለሰቡ የፈቃደኝነት መንፈስና በዝንባሌው ላይ የሚያመጣው ለውጥ ያለ ይመስልሃል? ምናልባትም እንዲህ ያለውን መሥዋዕት ደስ ሳይለው ሊያቀርብ ይችል ይሆን? (ዘሌ. 4:27, 28) ከይሖዋ ጋር ያለውን ወዳጅነት ላለማጣት ከልቡ የሚፈልግ ከሆነ በዚህ መንፈስ መሥዋዕቱን እንደማያቀርብ የታወቀ ነው።

10. ክርስቲያኖች ይሖዋን ጨምሮ ከሌሎች ጋር ያላቸውን የሻከረ ግንኙነት ለማደስ ምን ዓይነት “መሥዋዕቶችን” መክፈል ሊኖርባቸው ይችላል?

10 በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ሳናስበው ወይም ባለማወቅ አሊያም በግዴለሽነት ወንድማችንን ቅር የሚያሰኝ ነገር አድርገን ይሆናል። በዚህ ወቅት ሕሊናችን፣ ያደረግነው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ነግሮን ሊሆን ይችላል። ለይሖዋ የሚያቀርበውን አገልግሎት በቁም ነገር የሚመለከት ማንኛውም ሰው የሠራውን ስህተት ለማስተካከል የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለውም፤ አይመስልህም? ይህም ቅር የተሰኘውን ግለሰብ ከልብ ይቅርታ መጠየቅን፣ የተፈጸመው ኃጢአት ከባድ ከሆነ ደግሞ አፍቃሪ ከሆኑ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች እርዳታ መፈለግን ሊጨምር ይችላል። (ማቴ. 5:23, 24፤ ያዕ. 5:14, 15) በመሆኑም በባልንጀራችን ወይም በአምላክ ላይ የፈጸምነው ኃጢአት ይቅር እንዲባልልን ከፈለግን የምንከፍለው ዋጋ አለ። ያም ቢሆን እንዲህ ያሉ “መሥዋዕቶችን” የምንከፍል ከሆነ ከአምላክ እና ከወንድማችን ጋር ያለን ዝምድና ይታደሳል እንዲሁም ንጹሕ ሕሊና እናገኛለን። ይህ ደግሞ የይሖዋ መንገዶች የተሻሉ መሆናቸውን እንድንገነዘብ ያደርገናል።

11, 12. (ሀ) የኅብረት መሥዋዕትን ለየት የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው? (ለ) በዘመናችን ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በጥንት ጊዜ ይቀርብ ከነበረው የኅብረት መሥዋዕት ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

11 በሙሴ ሕግ ውስጥ ከተካተቱት መሥዋዕቶች መካከል አንዱ የኅብረት መሥዋዕት በመባል የሚታወቀው ነው። አንድ እስራኤላዊ እንዲህ ያለውን መሥዋዕት ማቅረቡ ከይሖዋ ጋር ሰላማዊ ዝምድና እንዳለው ያሳያል። በዚህ ወቅት ግለሰቡ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን የእንስሳ ሥጋ ከቤተሰቡ ጋር በመሆን ይመገባል፤ ምናልባትም ይህን የሚያደርገው በቤተ መቅደሱ ካሉት የመመገቢያ ክፍሎች በአንዱ ውስጥ ሊሆን ይችላል። መሥዋዕቱን ያቀረበው ካህን በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉት ሌሎች ካህናት እንደሚያደርጉት ከሥጋው ላይ የራሱን ድርሻ ይወስዳል። (ዘሌ. 3:1 የግርጌ ማስታወሻ፤ 7:31-33) አንድ ይሖዋን የሚያመልክ ሰው እንዲህ ያለውን መሥዋዕት የሚያቀርበው ከአምላክ ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመመሥረት ካለው ልባዊ ፍላጎት ተነሳስቶ ነው። በዚህ ወቅት ያለው ሁኔታ ግለሰቡ፣ ቤተሰቡ፣ ካህናቱ እና ይሖዋ አንድ ማዕድ ላይ ተቀምጠው በሰላም ደስ ብሏቸው እየተመገቡ እንዳሉ ሊቆጠር ይችላል።

12 በምሳሌያዊ ሁኔታ፣ ይሖዋን እንዲህ በመሰለ ማዕድ ላይ እንዲገኝ መጋበዝና ይሖዋም ግብዣውን ተቀብሎ ከእኛ ጋር ሲመገብ ማየት ትልቅ መብት አይደለም? ማንኛውም ሰው ቢሆን ለተከበረ እንግዳው ምርጡን ማቅረቡ የተለመደ ነገር ነው። ከሕጉ መሠረታዊ እውነቶች አንዱ የሆነው የኅብረት መሥዋዕት ከፈጣሪው ጋር የተቀራረበና ሰላማዊ ዝምድና ለመመሥረት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በሚበልጠው የኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ይህን ማድረግ እንደሚችል የሚጠቁም ነው። ዛሬም ሀብታችንንና ጉልበታችንን ይሖዋን ለማገልገል በፈቃደኝነት መሥዋዕት አድርገን የምናቀርብ ከሆነ ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ወዳጅነት መመሥረት እንችላለን።

መሥዋዕቶችን አስመልክቶ የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች

13, 14. ንጉሥ ሳኦል ሊያቀርብ ያሰበው መሥዋዕት በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ያላገኘው ለምንድን ነው?

13 አንድ እስራኤላዊ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለገ በሙሴ ሕግ ውስጥ የተገለጹትን መሥዋዕቶች በትክክለኛ መንፈስና የልብ ዝንባሌ ተነሳስቶ ማቅረብ እንደሚኖርበት የታወቀ ነው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ስላጡ መሥዋዕቶች የሚናገር ሲሆን እነዚህ ምሳሌዎች ለእኛ ትልቅ ማስጠንቀቂያ ይሆኑናል። ለመሆኑ ይሖዋ እነዚህን መሥዋዕቶች ያልተቀበለው ለምንድን ነው? እስቲ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት።

14 ነቢዩ ሳሙኤል፣ ይሖዋ በአማሌቃውያን ላይ ፍርዱን የሚያስፈጽምበት ጊዜ እንደደረሰ ለንጉሥ ሳኦል ነግሮት ነበር። በመሆኑም ሳኦል የእስራኤላውያን ጠላት የሆነውን ይህን ብሔር ከነከብቶቹ ማጥፋት ነበረበት። ይሁን እንጂ ንጉሥ ሳኦል ድል ከተቀዳጀ በኋላ ወታደሮቹ የአማሌቃውያን ንጉሥ የሆነውን አጋግን በሕይወት እንዲተዉት ፈቀደላቸው። ከዚህም በተጨማሪ ለይሖዋ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ በማሰብ ምርጥ ምርጡን ከብት አስቀረ። (1 ሳሙ. 15:2, 3, 21) ታዲያ ይሖዋ ምን ተሰማው? ሳኦል ባለመታዘዙ ምክንያት ይሖዋ ሞገሱን ነፈገው። (1 ሳሙኤል 15:22, 23ን አንብብ።) እኛ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንድ ሰው የሚያቀርበው መሥዋዕት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለገ የእሱን ሕግጋት መታዘዝ አለበት።

15. በኢሳይያስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ እስራኤላውያን መጥፎ ድርጊት እየፈጸሙ መሥዋዕት ማቅረባቸው ምን ውጤት አስከተለ?

15 በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያጡ መሥዋዕቶችን በተመለከተ በኢሳይያስ መጽሐፍም ላይ ሌላ ምሳሌ እናገኛለን። በኢሳይያስ ዘመን እስራኤላውያን መሥዋዕት የሚያቀርቡት ለይስሙላ ያህል ብቻ ነበር። በዚያ ላይ መጥፎ ተግባሮችን ይፈጽሙ ስለነበር የሚያቀርቡት መሥዋዕት ተቀባይነት አልነበረውም። ይሖዋ “የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምኔ ነው?” በማለት ከጠየቃቸው በኋላ እንዲህ አላቸው፦ “የሚቃጠለውን የአውራ በግና የሰቡ እንስሳትን ስብ ጠግቤአለሁ፤ በበሬ፣ በበግ ጠቦትና በፍየል ደም ደስ አልሰኝም። . . . ከንቱውን መባ አታቅርቡ፤ ዕጣናችሁን እጸየፋለሁ።” የእነዚህ እስራኤላውያን ችግር ምን ነበር? አምላክ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አብዝታችሁ ብትጸልዩም እንኳ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ በደም ተበክለዋል፤ ታጠቡ፤ ራሳችሁንም አንጹ፤ ክፉ ሥራችሁን ከፊቴ አርቁ፤ ክፉ ማድረጋችሁን ተዉ።”​—ኢሳ. 1:11-16

16. አንድ መሥዋዕት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት አለማግኘቱ የተመካው በምን ላይ ነው?

16 ይሖዋ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች በሚያቀርቡት መሥዋዕት እንደማይደሰት ከእስራኤላውያን ታሪክ መረዳት እንችላለን። ይሁንና ከአምላክ ትእዛዛት ጋር ተስማምተው ለመኖር ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች የሚያቀርቡትን ጸሎትና መሥዋዕት ይቀበል ነበር። እነዚህ ሰዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑና ምሕረት እንደሚያስፈልጋቸው ከሕጉ መሠረታዊ ገጽታዎች ተገንዝበው ነበር። (ገላ. 3:19) ይህን መገንዘባቸው የጸጸት ስሜት በልባቸው እንዲያድር አድርጎ እንደሚሆን የተረጋገጠ ነው። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ኃጢአትን የማስተሰረይ ኃይል ያለው የክርስቶስ መሥዋዕት እንደሚያስፈልገን መገንዘብ ይኖርብናል። ይህን የምንገነዘብና የምናደንቅ ከሆነ ይሖዋ እሱን በሙሉ ልባችን ስናገለግል በምናቀርበው መሥዋዕት “ደስ” ይሰኛል።​—መዝሙር 51:17, 19ን አንብብ።

በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት ማሳደር

17-19. (ሀ) ለኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ የትኛውን ጉዳይ እንመረምራለን?

17 በአሁኑ ጊዜ የምንገኝ የአምላክ አገልጋዮች በቅድመ ክርስትና ዘመን ከነበሩት በተለየ መልኩ ለአምላክ ዓላማዎች “ጥላ” ከሆኑ ነገሮች ባሻገር ያለውን ነገር የማየት አጋጣሚ አግኝተናል። (ዕብ. 10:1) ከመሥዋዕቶች ጋር በተያያዘ ለእስራኤላውያን የተሰጠው ሕግ አይሁዳውያኑ ከአምላክ ጋር ያላቸውን ጥሩ ዝምድና ጠብቀው እንዲመላለሱ የሚረዳቸውን ተገቢ አመለካከት እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል፤ ይኸውም ለአምላክ ያላቸውን ልባዊ አድናቆት እንዲገልጹ፣ ለእሱ ምርጣቸውን የመስጠት ፍላጎት እንዲያድርባቸውና የኃጢአት ስርየት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ መሥዋዕቶችን በተመለከተ በቂ ማብራሪያ በመሰጠቱ በጣም አመስጋኞች ነን፤ ምክንያቱም ይሖዋ በቤዛው አማካኝነት የኃጢአት ውጤቶችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያስወግድ እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ በእሱ ፊት ጥሩ ሕሊና ይዘን መኖር እንድንችል እንዳደረገን መረዳት ችለናል። በእርግጥም የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ግሩም ዝግጅት ነው!​—ገላ. 3:13፤ ዕብ. 9:9, 14

18 እርግጥ ነው፣ ከቤዛዊ መሥዋዕቱ ጥቅም ለማግኘት ከፈለግን ስለ ቤዛው ከመረዳት ያለፈ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በእምነት አማካኝነት ጻድቃን ተብለን መጠራት እንችል ዘንድ ሕጉ ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ሞግዚታችን ሆኗል” በማለት ጽፏል። (ገላ. 3:24) እንዲህ ዓይነት እምነት እንዳለን ደግሞ በሥራ ማሳየት ይኖርብናል። (ያዕ. 2:26) ጳውሎስ በሕጉ ውስጥ ያሉትን የእውቀት መሠረታዊ ገጽታዎች የተገነዘቡትንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች ይህን እውቀት በተግባር ላይ እንዲያውሉ ያበረታታቸው ለዚህ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ ምግባራቸውና የሚያስተምሩት መለኮታዊ ትምህርት የሚጣጣም ይሆናል።​—ሮም 2:21-23ን አንብብ።

19 በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ መጠበቅ ባያስፈልጋቸውም እንኳ አሁንም በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ይሖዋ ከአገልጋዮቹ የሚጠብቀው መሠረታዊ ነገር ፈጽሞ አይለወጥም

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንተ ብትሆን ኖሮ ለይሖዋ የምታቀርበው የትኛውን እንስሳ ነበር?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት የሚያቀርቡ ሰዎች የእሱን ሞገስ ያገኛሉ