በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከታሪክ ማኅደራችን

ውድ የሆኑ ቅርሶቻችንን ጠብቆ ማቆየት

ውድ የሆኑ ቅርሶቻችንን ጠብቆ ማቆየት

የይሖዋ ሕዝቦች ትኩረት የሚስቡ ብዙ ታሪኮች አሏቸው። እነዚህን አስደናቂ ታሪኮች ከታተሙ ጽሑፎች ብቻ ሳይሆን ፎቶግራፎችን፣ ደብዳቤዎችንና የግል ማስታወሻዎችን በማገላበጥ ማግኘት ይቻላል፤ እንዲሁም ከአምልኮታችን፣ ከስብከት ሥራችንና ከታሪካችን ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶችን በመመልከት ብዙ ነገር ማወቅ ይቻላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ጠብቆ ማቆየትና የቀድሞ ታሪካችንን መመርመር የሚያስገኘው ጥቅም አለ? በጥንቷ እስራኤል የነበሩ የቤተሰብ ራሶች የይሖዋን ሕግጋት እንዲሁም የእሱን ድንቅ ሥራዎች ለልጆቻቸው ማሳወቅ ይጠበቅባቸው ነበር፤ ይህም ልጆቻቸው ‘በአምላክ እንዲታመኑ’ ለማድረግ ትልቅ እገዛ ያደርጋል።​—መዝ. 78:1-7

የታሪክ ማኅደርን መመርመር በጥንት ዘመንም ቢሆን ከይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ትልቅ ሚና ነበረው። ለምሳሌ ያህል፣ ተቃዋሚዎች በኢየሩሳሌም ተጀምሮ የነበረውን ቤተ መቅደስ የመገንባት ሥራ ለማስቆም በሞከሩበት ወቅት ዳርዮስ የሜዶን ዋና ከተማ በነበረችው በአሕምታ የሚገኙት የመንግሥት መዛግብት እንዲመረመሩ ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፤ ይህም ንጉሥ ቂሮስ ግንባታው እንዲካሄድ መፍቀዱን የሚያሳይ ሰነድ እንዲገኝ አስችሏል። (ዕዝራ 6:1-4, 12) በመሆኑም ቤተ መቅደሱ አምላክ ባዘዘው መሠረት እንደገና ሊገነባ ችሏል። የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስም “ሁሉንም ነገር ከመጀመሪያው አንስቶ በጥንቃቄ” መርምሮ ለማጠናቀር የታሪክ ማኅደሮችን አገላብጦ ነበር።​—ሉቃስ 1:1-4

የበላይ አካሉም ለቲኦክራሲያዊ ታሪካችን ትልቅ ትኩረት ይሰጣል። መንፈሳዊ ቅርሶቻችንን ጠብቆ የማቆየትን፣ የመመዝገብንና ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍን አስፈላጊነት በተመለከተ አንድ የበላይ አካል አባል አስተያየት ሲሰጥ “የምንሄድበትን ለማወቅ የተነሳንበትን ማወቅ ያስፈልገናል” በማለት ተናግሮ ነበር። ለዚህም ሲባል በቅርቡ፣ በጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ ሥር ሆኖ የሚንቀሳቀስ የታሪክ ማኅደር ክፍል የተባለ አዲስ ዲፓርትመንት በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ተቋቁሟል።

“የቤተሰብ አልበም” እና “የቤተሰብ ውርስ”

ጊዜ እየነጎደ ሲሄድ ያለፈው ታሪክም እየተረሳ ይሄዳል፤ በመሆኑም ብዙ ሰዎች የቤተሰባቸውን ታሪክ የሚያስታውሱ ነገሮችን አሟልተው ባለማስቀመጣቸው ይቆጫሉ። የታሪክ ማኅደር ክፍል፣ ያሉንን በርካታ ታሪኮች ጠብቆና መዝግቦ ለማቆየት በትጋት እየሠራ ይገኛል። አንዳንድ ፎቶግራፎች “የቤተሰባችን አልበም” እንደሆኑ ተቆጥረው በታሪክ ማኅደራችን ውስጥ በጥንቃቄ ተቀምጠዋል። በተጨማሪም የቀድሞ ጽሑፎቻችን፣ የተለያዩ ግለሰቦች ስለራሳቸው የጻፏቸው መሳጭ ታሪኮችና በዋጋ የማይተመኑ ውድ ማስታወሻዎች በታሪክ ማኅደራችን ውስጥ ከተካተቱት ቅርሶች መካከል የሚመደቡ ናቸው። እንዲህ ያሉ ነገሮች ስለ ቲኦክራሲያዊ ታሪካችን በደንብ እንድናውቅና የመንፈሳዊ ቤተሰባችን የወደፊት ሁኔታ አስተማማኝ እንደሆነ እንዲሰማን የሚያደርጉን ሲሆን “የቤተሰብ ውርስ” ብለን ልንጠራቸው እንችላለን።

“ከታሪክ ማኅደራችን” በሚለው አዲስ ዓምድ አማካኝነት በታሪክ ማኅደር ክፍሉ ውስጥ የሚገኙትን ነገሮች እንድትጎበኙ እንጋብዛችኋለን። ይህ ዓምድ በመጠበቂያ ግንብ የጥናት እትም ላይ በየሦስት ወሩ ይወጣል። ለምሳሌ ያህል፣ በቀጣዩ እትም ላይ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ በምስሎች የተደገፈ ዘገባ ለማቅረብ አስበናል፦ ዶውን ሞባይል የተባለው ማጓጓዣ ምንድን ነው? የሚጠቀሙበት እነማን ነበሩ? ጥቅም ላይ የዋለው መቼ ነበር? የሚጠቀሙበትስ ለምን ዓላማ ነበር?

የቤተሰብ አልበም ቤተሰቡ ያሳለፈውን ታሪክ መለስ ብሎ ለመቃኘት እንደሚረዳ ሁሉ በታሪክ ማኅደራችን ውስጥ ያሉት ስብስቦችም ስለ እኛና ስለ መንፈሳዊ አያቶቻችን ብዙ የሚነግሩን ነገር አለ፤ ለምሳሌ ከእኛ በፊት የነበሩ የይሖዋ ሕዝቦች ስላሳዩት እምነትና ድፍረት፣ በሰማይ ያለውን አፍቃሪ አባታችንን ማገልገል ስለሚያስገኘው ደስታና ስላለው ተፈታታኝ ሁኔታ እንዲሁም አምላክ ለሕዝቦቹ ስለሚሰጠው አመራርና የማያቋርጥ ድጋፍ ለማወቅ ያስችሉናል። (ዘዳ. 33:27) ይሖዋ፣ የድርጅታችንን ታሪክ ጠብቆ ለማቆየት የምናደርገውን ጥረት እንደሚባርክልን እርግጠኞች ነን፤ ይህም ከምንጊዜውም ይበልጥ አንድነት ኖሮንና ኃይል አግኝተን የእሱን ፈቃድ እንድንፈጽም ይረዳናል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዲፓርትመንቱን ሥራ መቃኘት

ክርስቲያናዊ ጽሑፎች፣ ዲቪዲዎችና ሌሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ነገሮች በሚዘጋጁበት ጊዜ ጸሐፊዎቻችን፣ ሠዓሊዎቻችን እንዲሁም የምርምር ሥራ የሚያካሂዱትን ጨምሮ ሌሎች ወንድሞቻችን ለሥራቸው የሚረዳቸውን መረጃ ለማግኘት የታሪክ ማኅደራችንን ይጠቀማሉ። ስለዚህ የታሪክ ማኅደር ክፍሉ ከቅርንጫፍ ቢሮዎች፣ ቤቴል ውስጥ ካሉ ዲፓርትመንቶች፣ ከጉባኤዎች፣ ከግለሰቦች፣ ከዓለማዊ ተቋማትና ከሌሎች ምንጮች የተለያዩ ታሪካዊ ቁሳቁሶችን ለማሰባሰብና ጠብቆ ለማቆየት ጥንቃቄ የተሞላበት አንዳንድ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው። እስቲ ይህ ዲፓርትመንት የሚያከናውነውን ሥራ በአጭሩ ለመቃኘት እንሞክር፦

ማሰባሰብና ጥናት ማካሄድ፦ በታሪክ ማኅደራችን ስብስብ ውስጥ በየጊዜው አዳዲስ ነገሮች እየተጨመሩ ነው። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በስጦታ የተገኙ ወይም ለአሥርተ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ያገለገለ ቤተሰብ ካላቸው ግለሰቦች በውሰት የመጡ ናቸው። በእነዚህ ስብስቦች ላይ ጥናት ማካሄድና ማመሳከር ስለ ታሪካችንና በወቅቱ ስለነበሩት የይሖዋ ሕዝቦች ያለን ግንዛቤ እንዲሰፋ ይረዳል።

መዝግቦ ማስቀመጥ፦ የታሪክ ማኅደር ክፍሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ነገሮችን ያሰባሰበ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ከመቶ ዓመት የሚበልጥ ዕድሜ ያላቸው ናቸው። እነዚህ ስብስቦች ዓይነታቸው የተለያየ ሲሆን ወደፊት ሲፈለጉ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በጥንቃቄ ተመዝግበው መቀመጥ አለባቸው።

ማደስና ጠብቆ ማቆየት፦ በቀላሉ የሚበላሹ መጻሕፍትና ጥንታዊ ቁሳቁሶች በባለሙያዎች አማካኝነት በጥንቃቄ ከታደሱ በኋላ የቀድሞ ይዞታቸው ተጠብቆ እንዲቀመጡ ይደረጋል። ሰነዶች፣ ፎቶግራፎች፣ ከመጽሔቶችና ከጋዜጦች ላይ ተቆርጠው የተወሰዱ ጽሑፎችና ፎቶዎች፣ ፊልሞች እንዲሁም የተቀዱ ነገሮች ወደ ዲጂታል ፋይል ይቀየራሉ። ይህም ሰነዶችን ወይም ሌሎች ታሪካዊ ጠቃሜታ ያላቸው ቁሳቁሶችን በኮምፒውተር አማካኝነት ማየት ስለሚያስችል እነዚህ ነገሮች በእጅ ተነካክተው ከመበላሸት እንዲድኑ ያደርጋል።

ጥሩ ቦታ ማስቀመጥና ሲፈለጉ ማውጣት፦ በታሪክ ማኅደራችን ውስጥ የተካተቱት ነገሮች እንዳይጠፉ ወይም ብርሃንና እርጥበት እንዳያበላሻቸው ሥርዓት ባለውና አስተማማኝ በሆነ መንገድ ይቀመጣሉ። ምርምር ለማካሄድ ወይም በተፈለጉ ጊዜ በቀላሉ ከተቀመጡበት ለማውጣት እንዲቻል እነዚህ ውድ የሆኑ ታሪካዊ ቅርሶቻችን በኮምፒዩተር አማካኝነት የመረጃ ማዕከል እየተዘጋጀላቸው ነው።

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

1. “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” ማስተዋወቂያ ፖስተር 2. የመጽሔት ኮንትራት መመዝገቢያ 3. የድምፅ ማጉያ መሣሪያ የተገጠመለት መኪና 4. የሚያዝያ 15, 1912 መጠበቂያ ግንብ ሽፋን 5. ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ እስር ቤት እያለ የጻፈው ማስታወሻ 6. የደብልዩ ቢ ቢ አር ሬዲዮ ጣቢያ ማይክሮፎን 7. የሸክላ ማጫወቻ 8. የመጻሕፍት መያዣ ቦርሳ 9. የግል ማስታወሻዎች 10. ለጄ ኤፍ ራዘርፎርድ የተላከ ቴሌግራም