በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ጊዜህን ይበልጥ አስደሳችና ውጤታማ ማድረግ

የጥናት ጊዜህን ይበልጥ አስደሳችና ውጤታማ ማድረግ

የጥናት ጊዜህን ይበልጥ አስደሳችና ውጤታማ ማድረግ

መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ይበልጥ አስደሳች እንዲሆንልን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በጥናት የምናሳልፈው ጊዜ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆንስ ምን ማድረግ እንችላለን? እስቲ ከግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት የሚረዱንን ሦስት አስፈላጊ እርምጃዎች በአጭሩ እንመልከት።

1 መጸለይ፦ የመጀመሪያው እርምጃ መጸለይ ነው። (መዝ. 42:8) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የአምላክን ቃል ማጥናት የአምልኳችን ክፍል እንደሆነ አድርገን መመልከት ይኖርብናል። ስለዚህ አእምሯችንንና ልባችንን ለጥናቱ ለማዘጋጀት እንዲረዳን ብሎም ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ይሖዋን መለመን ያስፈልገናል። (ሉቃስ 11:13) በሚስዮናዊነት ለረጅም ጊዜ ያገለገለችው ባርባራ እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ወይም ማጥናት ከመጀመሬ በፊት ሁልጊዜ እጸልያለሁ። ከዚያ በኋላ ይሖዋ ከእኔ ጋር እንደሆነና በማደርገው ጥረት እንደሚደሰት ይሰማኛል።” ጥናት ከመጀመራችን በፊት መጸለያችን ከፊታችን የቀረበልንን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ሙሉ በሙሉ ለመቀበል አእምሯችንና ልባችን ክፍት እንዲሆን ይረዳናል።

2 ማሰላሰል፦ አንዳንዶች ጊዜ ስለሚያጥራቸው የአምላክን ቃል የሚያነቡት ላይ ላዩን ነው። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ሊያገኙ ይችሉ የነበረውን ጥቅም ያጣሉ። ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት ይሖዋን ሲያገለግል የቆየው ካርሎስ፣ ከጥናቱ ይበልጥ ጥቅም ለማግኘት የግድ ለማሰላሰል የሚሆን ጊዜ መመደብ እንዳለበት መገንዘብ ችሏል። እንዲህ ይላል፦ “ከበፊቱ ጋር ሲነጻጸር አሁን የማነበው ጥቂት ገጾችን ይኸውም በቀን ሁለት ገጽ ያህል ብቻ ነው። በመሆኑም ጠቃሚ ትምህርቶችን መቅሰም እችል ዘንድ ባነበብኩት ነገር ላይ ለማሰላሰል የሚያስችል ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት ችያለሁ።” (መዝ. 77:12) ጊዜ ወስደን የምናሰላስል ከሆነ ከአምላክ ፈቃድ ጋር በተያያዘ ያለን እውቀትና ግንዛቤ እያደገ ይሄዳል።​—ቆላ. 1:9-11

3 ተግባራዊ ማድረግ፦ አንድን ተግባር ማከናወን ምን ፋይዳ እንዳለው ከተገነዘብን ከዚያ ነገር የምናገኘው ጠቀሜታ ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስን ከማጥናት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ የማጥናት ልማድ ያለው ጋብሪኤል የሚባል አንድ ወጣት ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ጥናት በዕለት ተዕለት ሕይወቴ የሚያጋጥሙኝን ችግሮች እንድቋቋምና ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ እንድሆን ያደርገኛል። የምማረውን ነገር ሁሉ በሕይወቴ ተግባራዊ ለማድረግ እጥራለሁ።” (ዘዳ. 11:18፤ ኢያሱ 1:8) አዎን፣ ልንቀስመውና ተግባራዊ ልናደርገው የምንችል እጅግ ብዙ እውቀት አምላክ ሰጥቶናል።​—ምሳሌ 2:1-5

ክለሳ፦ የጥበብ ሁሉ ምንጭ ከሆነው ከይሖዋ የሚገኘውን እውቀት የመቅሰም ታላቅ መብት አግኝተናል! (ሮም 11:33) ስለዚህ ከዚህ በኋላ በምታጠናበት ጊዜ አእምሮህንና ልብህን ለማዘጋጀት እንዲረዳህ ብሎም ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጥህ በቅድሚያ ወደ ይሖዋ መጸለይህን አትርሳ። እንዲሁም በምታጠናበት ወቅት አልፎ አልፎ፣ ባነበብከው ነገር ላይ ቆም እያልክ አሰላስል። በተጨማሪም የተማርከውን ነገር ሳትረሳ በዕለታዊ ሕይወትህ ተግባራዊ አድርግ። እነዚህን አስፈላጊ እርምጃዎች ከወሰድክ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ በጣም አስደሳችና ውጤታማ ይሆንልሃል።