በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቅናት አእምሯችንን ሊመርዝ የሚችል መጥፎ ባሕርይ

ቅናት አእምሯችንን ሊመርዝ የሚችል መጥፎ ባሕርይ

ቅናት አእምሯችንን ሊመርዝ የሚችል መጥፎ ባሕርይ

ናፖሊዮን ቦናፓርት ይህ ስሜት ነበረው። ጁሊየስ ቄሳርም እንዲሁ። ታላቁ እስክንድርም ቢሆን ከዚህ ስሜት ነፃ አልነበረም። እነዚህ ሰዎች ከፍተኛ ሥልጣንና ክብር ቢኖራቸውም እንኳ ሦስቱም አእምሮን ሊመርዝ የሚችል አንድ መጥፎ ባሕርይ ነበራቸው። ሁሉም የሚቀኑበት ሰው ነበር።

“ናፖሊዮን በቄሳር ይቀና ነበር፤ ቄሳር ደግሞ [በታላቁ] እስክንድር ይቀና ነበር፤ እስክንድርም ቢሆን በሕይወት ኖሮ በማያውቀው በሄርኩለስ ይቀና ነበር ማለት እችላለሁ” ሲሉ እንግሊዛዊው ፈላስፋ በርትራንድ ራስል ጽፈዋል። አንድ ሰው የቱንም ያህል ሀብት ቢያፈራ፣ ምንም ዓይነት ጥሩ ባሕርይ ቢኖረው ወይም ደግሞ የቱንም ያህል ስኬታማ ቢሆን የቅናት ስሜት ሊያድርበት ይችላል።

ቅናት ወይም ምቀኝነት ሲባል ሌሎች ባላቸው የተመቻቸ ሁኔታ፣ ቁሳዊ ነገር፣ ብልጽግና ወዘተ ቅር መሰኘት ማለት ነው። አንድ የማመሳከሪያ መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ ምቀኝነት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት ሌላው የደረሰበት ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞትን ለማመልከት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ያላቸውን ነገር እንዲያጡ መፈለግን ለማመልከት ጭምር ነው። በመሆኑም እንዲህ ያለው ሰው ሌሎች ባላቸው ነገር ከመቅናትም አልፎ ያንን ነገር ከእነሱ መንጠቅም ይፈልጋል።

ቅናት በውስጣችን ሊያቆጠቁጥ የሚችለው እንዴት እንደሆነና መዘዞቹም ምን እንደሆኑ መመርመራችን ብልህነት ነው። በተለይ ደግሞ ቅናት ሕይወታችንን እንዳይቆጣጠረው ለማድረግ ምን እርምጃዎችን መውሰድ እንደምንችል ማወቅ ያስፈልገናል።

የቅናት ስሜትን የሚያቀጣጥል መንፈስ

ሰዎች ፍጹማን አለመሆናቸው በራሱ በውስጣቸው የመመቅኘት ወይም ‘የቅናት ዝንባሌ’ እንዲያድርባቸው ተጽዕኖ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ ይህን ዝንባሌ የሚያቀጣጥሉና የሚያባብሱ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። (ያዕ. 4:5) ሐዋርያው ጳውሎስ ከእነዚህ ምክንያቶች አንዱን ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል፦ “በመካከላችን የፉክክር መንፈስ በማነሳሳትና አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ።” (ገላ. 5:26) በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የፉክክር መንፈስ፣ በአለፍጽምና ምክንያት የወረስነውን የምቀኝነት ዝንባሌ ጭራሹን ሊያባብሰው ይችላል። ክሪስቲና እና ሆሴ * የሚባሉ ሁለት ክርስቲያኖች ይህ እውነት መሆኑን በራሳቸው ሕይወት ተመልክተዋል።

የዘወትር አቅኚ የሆነችው ክሪስቲና እንዲህ ትላለች፦ “ብዙውን ጊዜ ራሴን እንደታዘብኩት በሌሎች የመቅናት ዝንባሌ አለኝ። ራሴን ከእነሱ ጋር አወዳድርና እነሱ ባላቸው ነገር እቀናለሁ።” በአንድ ወቅት ክሪስቲና በወረዳ ሥራ የማገልገል መብት ካገኙ ባልና ሚስት ጋር አብራ እየተመገበች ነበር። እሷና ባለቤቷ ኤሪክ ከተጓዥ የበላይ ተመልካቹና ከሚስቱ ጋር በተመሳሳይ ዕድሜ ላይ እንደሚገኙና ከዚህ በፊትም አንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት እንደነበራቸው ታውቅ ስለነበር እንዲህ አለች፦ “የእኔም ባል እኮ ሽማግሌ ነው! ታዲያ እናንተ በወረዳ ሥራ ላይ እንድታገለግሉ ስትመደቡ እኛ ይህን መብት ያላገኘነው ለምንድን ነው?” ክሪስቲና በውስጧ ያደረው የፉክክር መንፈስ የቅናት ስሜቷን በማቀጣጠሉ እሷና ባሏ እየሠሩ ያሉት መልካም ነገር እንዳይታያት ጋረደባት፤ ይህ ደግሞ ባላቸው ነገር እንዳትረካ አደረጋት።

ሆሴ ደግሞ የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን ይመኝ ነበር። ሌሎች ይህን መብት አግኝተው እሱ ሳያገኝ በመቅረቱ በእነሱ ላይ የቅናት ስሜት ያደረበት ከመሆኑም በላይ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪውን በመጥፎ ዓይን መመልከት ጀመረ። “በውስጤ ያለው የቅናት መንፈስ ለዚህ ወንድም ጥላቻ እንዲያድርብኝና የሚያደርጋቸውን ነገሮች በመጥፎ እንድተረጉም አደረገኝ” በማለት ሆሴ ሳይሸሽግ ተናግሯል። አክሎም “ምቀኝነት ሕይወታችሁን ሲቆጣጠረው ራስ ወዳድ እንድትሆኑና በትክክል እንዳታስቡ ያደርጋችኋል” ብሏል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ ሰዎች ትምህርት ማግኘት

መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎችን ይዟል። (1 ቆሮ. 10:11) ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ፣ የምቀኝነት ስሜት እንዴት እንደሚያቆጠቁጥ ብቻ ሳይሆን እንዲቆጣጠራቸው የፈቀዱለትን ሰዎች እንዴት እንደሚመርዛቸው ጭምር የሚያሳዩ ናቸው።

ለምሳሌ ያህል፣ የአዳምና የሔዋን የበኩር ልጅ የሆነው ቃየን ወንድሙ አቤል ያቀረበው መሥዋዕት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ የእሱ ሳያገኝ በመቅረቱ በጣም ተናድዶ ነበር። ቃየን ስሜቱን መቆጣጠር ይችል የነበረ ቢሆንም ቅናት እንዲያሳውረው በመፍቀዱ ወንድሙን እስከ መግደል ደርሷል። (ዘፍ. 4:4-8) መጽሐፍ ቅዱስ ቃየን “ከክፉው ወገን” ማለትም ከሰይጣን ወገን እንደሆነ መናገሩ ምንም አያስገርምም።​—1 ዮሐ. 3:12

ዮሴፍ ከአባቱ ጋር ለየት ያለ ቅርርብ ያለው በመሆኑ አሥሩ ወንድሞቹ ይቀኑበት ነበር። ዮሴፍ ስላያቸው ትንቢታዊ ሕልሞች ሲነግራቸው ጥላቻቸው እየጨመረ መጣ። እንዲያውም ሊገድሉት ፈልገው ነበር። በመጨረሻ ግን ለባርነት ሸጡት፤ ከዚያም አባታቸው፣ ልጁ ዮሴፍ ሞቷል ብሎ እንዲያስብ በማድረግ የጭካኔ ተግባር ፈጸሙ። (ዘፍ. 37:4-11, 23-28, 31-33) እርግጥ ነው፣ የዮሴፍ ወንድሞች ዓመታት ካለፉ በኋላ እርስ በርሳቸው “ይኸው በወንድማችን ላይ ባደረስነው በደል ምክንያት ቅጣታችንን እየተቀበልን ነው። እርሱ እንደዚያ ተጨንቆ ስለ ሕይወቱ ሲማጠነን፣ እኛ አልሰማነውም ነበር” መባባላቸው በሠሩት በደል መጸጸታቸውን ያሳያል።​—ዘፍ. 42:21፤ 50:15-19

ቆሬ፣ ዳታንና አቤሮንም ቢሆኑ የምቀኝነት ስሜት ያደረባቸው እነሱ ያገኙትን መብት ሙሴና አሮን ካገኙት ጋር ማወዳደር ሲጀምሩ ነው። ሙሴ ‘ጌታ እንደሆነና’ ራሱን ከሌሎች በላይ ከፍ ከፍ እንዳደረገ በመናገር ከሰሱት። (ዘኍ. 16:13) ይሁንና ይህ ክስ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነበር። (ዘኍ. 11:14, 15) ሙሴን የሾመው ይሖዋ ራሱ ነበር። እነዚህ ዓመፀኞች ግን ሙሴ ሥልጣን በማግኘቱ ተመቀኙት። በመጨረሻም ምቀኝነት በይሖዋ እጅ እንዲጠፉ አደረጋቸው።​—መዝ. 106:16, 17

ንጉሥ ሰለሞንም ምቀኝነት አንድን ሰው እስከ ምን ደረጃ ሊያደርሰው እንደሚችል ተመልክቷል። አንዲት ሴት አራስ ልጇ ሲሞትባት የሞተውን ልጇን አብራት በምትኖረው ሴት እቅፍ ውስጥ ካለው ልጅ ጋር አቀያየረችው፤ ይህን ያደረገችው ሴትየዋ የሞተው ልጅ የእኔ ነው ብላ እንድታስብ ለማድረግ ነበር። እነዚህ እናቶች ለፍርድ በቀረቡበት ወቅት፣ የሌላን ሰው ልጅ ለመውሰድ የሞከረችው ሴት በሕይወት ያለው ልጅ ይገደል በሚለው ሐሳብ እስከ መስማማት ደርሳ ነበር። ይሁን እንጂ ሰለሞን ይህን ሲመለከት ሕፃኑ ለእውነተኛዋ እናት እንዲሰጥ ፈረደ።​—1 ነገ. 3:16-27

ምቀኝነት ከባድ መዘዞችን ሊያስከትል ይችላል። ከላይ የተጠቀሱት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ምቀኝነት አንድን ሰው የጥላቻ ስሜት እንዲያድርበትና ኢፍትሐዊ እንዲሆን ሊያደርገው አልፎ ተርፎም ነፍስ እስከ ማጥፋት ሊያደርሰው ይችላል። ከዚህም በላይ የጥቃት ዒላማ የሆኑት በምሳሌዎቹ ላይ የተጠቀሱት ሁሉም ግለሰቦች በደል የተፈጸመባቸው ባልሠሩት ጥፋት ነው። ታዲያ ምቀኝነት ወይም ቅናት ሕይወታችንን እንዳይቆጣጠረው ምን ብናደርግ ይሻላል? ለምቀኝነት ማርከሻ የሚሆኑ ምን እርምጃዎችንስ መውሰድ እንችላለን?

የምቀኝነት ፍቱን ማርከሻዎች!

ፍቅርንና የወንድማማች መዋደድን ማዳበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያኖችን እንዲህ በማለት መክሯቸዋል፦ “እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን ስላነጻችሁ ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ ሊኖራችሁና እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ልትዋደዱ ይገባል።” (1 ጴጥ. 1:22) ታዲያ ፍቅር የሚገለጸው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም፣ ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም፣ ተገቢ ያልሆነ ምግባር አያሳይም፣ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 13:4, 5) በልባችን ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ማዳበራችን በውስጣችን ያለውን የምቀኝነት ዝንባሌ ለመቆጠር የሚረዳን አይመስላችሁም? (1 ጴጥ. 2:1) የአምላክ ቃል እንደሚናገረው ዮናታን በዳዊት ከመመቅኘት ይልቅ “እንደራሱ አድርጎ ወደደው።”​—1 ሳሙ. 18:1

ፈሪሃ አምላክ ካላቸው ሰዎች ጋር መወዳጀት። መዝሙር 73⁠ን ያቀናበረው ግለሰብ ከችግር ነፃ የሆነ የቅንጦት ሕይወት ይመሩ በነበሩ ክፉ ሰዎች ቀንቶ ነበር። ይሁን እንጂ “ወደ አምላክ መቅደስ” መሄዱ የቅናት ስሜቱን እንዲቆጣጠር ረድቶታል። (መዝ. 73:3-5, 17) መዝሙራዊው ከእምነት ባልንጀሮቹ ጋር ኅብረት መፍጠሩ ‘ወደ አምላክ በመቅረቡ’ ያገኛቸውን በረከቶች እንዲያስተውል ረድቶታል። (መዝ. 73:28) እኛም ዘወትር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ጊዜ የምናሳልፍ ከሆነ ተመሳሳይ ጥቅም እናገኛለን።

መልካም ለማድረግ መጣር። አምላክ በቃየን ልብ ውስጥ የምቀኝነትና የጥላቻ ስሜት ማቆጥቆጡን ሲመለከት ‘መልካም እንዲያደርግ’ ነግሮት ነበር። (ዘፍ. 4:7) ታዲያ ክርስቲያኖች ‘መልካም ማድረግ’ የሚችሉት እንዴት ነው? ኢየሱስ ‘ይሖዋ አምላካችንን በሙሉ ልባችን፣ በሙሉ ነፍሳችንና በሙሉ ሐሳባችን መውደድ እንዳለብን እንዲሁም ባልንጀራችንን እንደራሳችን አድርገን መውደድ እንዳለብን’ ተናግሯል። (ማቴ. 22:37-39) ሕይወታችን፣ ይሖዋን በማገልገልና ሌሎችን በመርዳት ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ለቅናት ፍቱን ማርከሻ ነው። በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረጋችን አምላክንና ባልንጀራችንን ለማገልገል ከሚያስችሉን ግሩም መንገዶች አንዱ ከመሆኑም በላይ ለእኛም የይሖዋን “በረከት” ያስገኝልናል።​—ምሳሌ 10:22

“ደስ ከተሰኙ ሰዎች ጋር ደስ” መሰኘት። (ሮም 12:15) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ባገኙት ስኬት ተደስቶ ነበር፤ እንዲያውም በስብከቱ ሥራ እሱ ካከናወነው በላይ እንደሚሠሩም ገልጾ ነበር። (ሉቃስ 10:17, 21፤ ዮሐ. 14:12) የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን አንድነት አለን፤ በመሆኑም የአንዱ ስኬት ለሁላችንም በረከት ነው። (1 ቆሮ. 12:25, 26) ታዲያ ሌሎች ከእኛ የበለጠ ኃላፊነት ሲያገኙ ከመቅናት ይልቅ መደሰት አይገባንም?

ትግሉ ቀላል አይደለም!

ከቅናት ወይም ከምቀኝነት ጋር የሚደረገው ትግል እንዲህ በቀላሉ የሚቋጭ ላይሆን ይችላል። ክርስቲና እንደሚከተለው በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች፦ “አሁንም ቢሆን በውስጤ ኃይለኛ የቅናት ዝንባሌ አለ። ይህን ስሜት ብጠላውም አሁንም ድረስ ከውስጤ አልጠፋም፤ ስለዚህ ይህን ስሜት ለመቆጣጠር ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ ያስፈልገኛል።” ሆሴም ተመሳሳይ ትግል ማድረግ አስፈልጎት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ፣ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ያሉትን መልካም ባሕርያት ከፍ አድርጌ እንድመለከት ረድቶኛል። ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረኝ ለማድረግ መጣሬ በዚህ ረገድ ይህ ነው የማይባል ጥቅም አስገኝቶልኛል።”

ምቀኝነት “የሥጋ ሥራዎች” ከሚባሉት መካከል አንዱ በመሆኑ እያንዳንዱ ክርስቲያን ይህን ባሕርይ ለማስወገድ ከፍተኛ ትግል ማድረግ ይኖርበታል። (ገላ. 5:19-21) የቅናት ወይም የምቀኝነት ዝንባሌ እንዳይቆጣጠረን ጥረት የምናደርግ ከሆነ በሕይወታችን ይበልጥ ደስተኞች ልንሆንና በሰማይ ያለውን አባታችንን ይሖዋን ልናስደስተው እንችላለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 ስሞቹ ተቀይረዋል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ደስ ከተሰኙ ሰዎች ጋር ደስ ይበላችሁ”