በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከታሪክ ማኅደራችን

“በቀላሉ ዓይን ውስጥ እንድገባ አደረገኝ”

“በቀላሉ ዓይን ውስጥ እንድገባ አደረገኝ”

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሙሉ ጊዜ ሰባኪ የነበረችው ሻርሎት ዋይት ባለ ጎማ ሻንጣ እየገፋች ኬንታኪ ወደምትገኘው ሉኢቨል ከተማ ስትደርስ ብዙ ሰዎች እንደ ትንግርት ይመለከቷት ነበር።

ጊዜው 1908 ሲሆን እህት ዋይት በወቅቱ አዲስ የፈጠራ ውጤት የሆነውን ዶውን ሞባይል የተባለ ባለ ጎማ ሻንጣ ይዛ ስትመጣ የከተማውን ሕዝብ ትኩረት እንደሳበች ጥርጥር የለውም። እህት ዋይት “ሻንጣው በከተማው ውስጥ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ነበር፤ እናም በቀላሉ ዓይን ውስጥ እንድገባ አደረገኝ” በማለት ተናግራለች።

በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው የሚጠሩት የይሖዋ ምሥክሮች፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት በማጥናት ያገኟቸውን ውድ እውነቶች ለሌሎች ማካፈል አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበው ነበር። ብዙዎቹ ሚሌኒያል ዶውን * በሚል ርዕስ በተከታታይ በወጡት መጻሕፍት አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታቸው ዳብሮ ነበር። በመሆኑም ራቅ ወዳሉ የተለያዩ ከተሞች፣ መንደሮችና ገጠራማ አካባቢዎች በመጓዝ ለማገልገል ፈቃደኝነቱና አቅሙ ያላቸው ክርስቲያኖች “የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መርጃ መሣሪያ” በመባል የሚጠሩትን እነዚህን መጻሕፍት የማንበብ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ያበረክቱ ነበር።

በ1908 እህት ዋይትና ሌሎች ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ጠንካራ ሽፋን ያለውንና በስስ ጨርቅ የተለበደውን ይህን ባለ ስድስት ጥራዝ መጽሐፍ ለሕዝብ የሚያበረክቱት በ1.65 የአሜሪካ ዶላር ነበር። እነዚህ ክርስቲያኖች መጻሕፍቱን ወዲያው ከመስጠት ይልቅ መጀመሪያ ትእዛዝ ተቀብለው ይሄዳሉ፤ ከዚያም በአብዛኛው በደሞዝ ቀን ተመልሰው በመሄድ ለኅትመቱ ወጪ መሸፈኛ የሚሆን አነስተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ብቻ እየተቀበሉ መጻሕፍቱን ይሰጡ ነበር። ተቃዋሚ የሆነ አንድ ሰው መጻሕፍቱ ለሕዝብ በሚሰራጩበት ወቅት የሚጠየቀው ዋጋ አነስተኛ በመሆኑ የተሰማውን ቅሬታ ገልጾ ነበር!

ማሊንዳ ኪፈር የተባለች አንዲት እህት በአንድ ሳምንት ውስጥ ከሁለት መቶ እስከ ሦስት መቶ የሚሆኑ መጻሕፍት እንድታመጣላቸው ሰዎች ያዟት እንደነበረ ታስታውሳለች። ይሁን እንጂ መጻሕፍቱን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ አንድ ችግር አስከተለ። ስድስተኛው ጥራዝ ብቻ እንኳ 740 ገጾች ነበሩት! በዚያን ወቅት የታተመ አንድ መጠበቂያ ግንብ እንደገለጸው “ሃምሳ መጻሕፍት 18 ኪሎ ግራም ይመዝኑ” ነበር፤ በመሆኑም እነዚህን መጻሕፍት ለሰዎች ማድረስ በተለይ ለእህቶች “እጅግ አድካሚ” ነበር።

መጻሕፍቱን ለሰዎች የማድረሱን ሥራ አዳጋች እንዲሆን ያደረገውን ችግር ለመቅረፍ ወንድም ጄምስ ኮል፣ ሻንጣ ላይ በቡሎን ሊታሠር የሚችልና ታጣፊ የሆነ ሁለት ጎማ ያለው ፍሬም ፈለሰፈ። ከዚያ ወዲህ በመጻሕፍት የተሞሉ ከባባድ ካርቶኖችን መሸከም ቀረ፤ ፍሬሙን የፈለሰፈው ወንድም ራሱ “ምን በወጣኝና ነው ትከሻዬን የምገነጥለው!” በማለት በወቅቱ የተሰማውን ተናግሯል። ይህን አዲስ ዕቃ በ1908፣ በኦሃዮ ግዛት ሲንሲናቲ ከተማ ውስጥ በተደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ባስተዋወቀበት ወቅት በዚያ የተገኙ ተሰብሳቢዎች በጣም ተደስተው ነበር። ይህ ማጓጓዣ በዋነኝነት የሚያገለግለው ሚሌኒያል ዶውን የሚል ርዕስ ያላቸውን ጥራዞች ለመያዝ ስለነበር ከሻንጣው ጋር የሚያያዘው ብረት ጫፍ ላይ በሁለቱም በኩል ዶውን ሞባይል የሚል ስም ተቀርጾበት ነበር። የዚህን ሻንጣ አጠቃቀም መልመድ ያን ያህል አያስቸግርም፤ በርከት ያሉ መጻሕፍትን በዚህ ሻንጣ ውስጥ ጨምሮ በአንድ እጅ ብቻ በመግፋት በቀላሉ ከቦታ ቦታ ማጓጓዝ ይቻላል። ፍሬሙን እንደተጠቃሚው ቁመት ከፍ ወይም ዝቅ ማድረግ የሚቻል ሲሆን ጎማዎቹ ደግሞ ለጥርጊያ መንገዶችም የሚሆኑ ነበሩ። ወንድሞች አገልግሎት ላይ ዶውን ሞባይሉን ይዘው ቀኑን ሙሉ ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ በእግራቸው አሊያም ትራንስፖርት ተጠቅመው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ጎማውን በማጠፍ በእጃቸው አንጠልጥለው ይዘውት ይሄዳሉ።

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማሩ እህቶች ዶውን ሞባይል በነፃ ማግኘት ይችሉ ነበር። ሌሎች ግን በ2.50 የአሜሪካ ዶላር መግዛት ይችሉ ነበር። በፎቶግራፉ ላይ የምትታየው እህት ኪፈር ሻንጣውን በማሽከርከር ረገድ በደንብ ተክና ነበር፤ እህት ሻንጣዋን ጢቅ አድርጋ ከሞላች በኋላ በአንድ እጇ ሻንጣውን ስትገፋ በሌላኛው እጇ ደግሞ ጥቂት መጻሕፍት የያዘ ቦርሳ ታንጠለጥል ነበር። እህት ኪፈር በፔንሲልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ባለች ማዕድን በሚወጣበት አንዲት ከተማ ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች ስላገኘች በተለይ ጽሑፎቹን በምታስረክብበት ዕለት ድልድይ በማቋረጥ በቀን ውስጥ በአብዛኛው ማለት ይቻላል ሦስትና አራት ጊዜ እየተመላለሰች መጻሕፍቱን ታደርስላቸው ነበር።

በ1980ዎቹ መገባደጃ ላይ አንድ የአውሮፕላን አብራሪ፣ በአሁኑ ጊዜ በአውሮፕላን ማረፊያዎች ውስጥና በሕዝብ በተጨናነቁ የከተማ መንገዶች ላይ በብዛት የሚታየውን ባለ ጎማ ሻንጣ ፈለሰፈ። ይሁን እንጂ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ቀናተኛ ሰባኪዎች የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ውድ የሆነውን የእውነት ዘር ብዙ ቦታ ለማዳረስ ዶውን ሞባይላቸውን እየገፉ ወዲያ ወዲህ ሲሉ የሰውን ትኩረት በቀላሉ ይስቡ ነበር። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በቀላሉ ሰው ዓይን ውስጥ መግባታቸውን ይፈልጉት ነበር፤ ምክንያቱም ሰዎች በሥራቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ይረዳል።

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እህት ኪፈር ጹሑፎቹን በምታስረክብበት ዕለት ድልድይ በማቋረጥ በቀን ውስጥ በአብዛኛው ማለት ይቻላል ሦስትና አራት ጊዜ እየተመላለሰች መጻሕፍቱን ታደርስ ነበር

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ዶውን የተባለውን መጽሐፍ ለሰዎች ከማድረስ ጋር በተያያዘ ለተፈጠረው ችግር እልባት ተገኘ

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ከጊዜ በኋላ ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ (የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት) ተብሏል።