ናታን—ለንጹሕ አምልኮ በታማኝነት ጥብቅና የቆመ
ናታን—ለንጹሕ አምልኮ በታማኝነት ጥብቅና የቆመ
ትልቅ ሥልጣን ባለው ሰው ፊት ቀርቦ አካሄዱ ትክክል እንዳልሆነና መታረም እንደሚያስፈልገው ማሳመን ቀላል ነገር አይደለም። ጥፋቱ እንዳይታወቅበት ሲል ሰው እንዳስገደለ የምታውቀው እንዲህ ያለ ባለሥልጣን ቢኖር ኖሮ ይህን ግለሰብ ፊት ለፊት ተጋፍጠህ ስህተቱን ትነግረው ነበር?
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የሆነው ዳዊት በአንድ ወቅት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ይፈጽማል፤ በኋላም ቤርሳቤህ ማርገዟን አወቀ። በዚህ ጊዜ ዳዊት የሠሩት ኃጢአት እንዳይታወቅ ሲል ባሏን በማስገደል ቤርሳቤህን ሚስቱ አድርጎ ወሰዳት። ሁኔታው ሳይታወቅ ወራት አለፉ፤ ዳዊትም ምንም እንዳልተፈጠረ በማስመሰል የተለመደውን ንጉሣዊ ተግባሩን ማከናወን ቀጥሎ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ ንጉሡ የሠራው ኃጢአት ተሰውሮ እንዲቀር አልፈቀደም። ስለዚህ ዳዊት የፈጸመውን ኃጢአት እንዲያጋልጥ ነቢዩ ናታንን ላከው።
ይህ ከባድ ተልእኮ ነበር። እስቲ በናታን ቦታ ሆነህ አስበው። ናታን፣ ለይሖዋ ያለው ታማኝነትና መለኮታዊ መመሪያዎችን በጥብቅ የሚከተል ሰው መሆኑ ለዳዊት ኃጢአቱን እንዲነግር እንደሚያነሳሳው ጥርጥር የለውም። ታዲያ ነቢዩ ተልእኮውን የሚወጣውና ንጉሥ ዳዊት ንስሐ መግባት የሚያስፈልገው መሆኑን አምኖ እንዲቀበል የሚያደርገው እንዴት ነው?
ዘዴኛ አስተማሪ
እስቲ ጥቂት ደቂቃዎች ወስደህ 2 ሳሙኤል 12:1-25ን ለማንበብ ሞክር። ራስህን በናታን ቦታ በማስቀመጥ ቀጥሎ ያለውን ነገር ለዳዊት እየነገርከው እንደሆነ አድርገህ አስብ፦ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ባለ ጠጋ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ድኻ ነበረ። ባለ ጠጋው እጅግ ብዙ በጎችና የቀንድ ከብቶች ነበሩት፤ ድኻው ግን ከገዛት ከአንዲት ጠቦት በግ በስተቀር ሌላ አልነበረውም። ተንከባከባት፤ አብራውም ከልጆቹ ጋር አደገች፤ አብራው ትበላ፤ ከጽዋው ትጠጣ እንዲሁም በዕቅፉ ትተኛ ነበር፤ ልክ እንደ ገዛ ልጁ ነበረች። ወደ ባለ ጠጋውም ቤት እንግዳ መጣ፤ ባለ ጠጋው ግን ከራሱ በጎች ወይም ቀንድ ከብቶች ወስዶ ለመጣበት እንግዳ ምግብ ማዘጋጀት አልፈለገም፤ ከዚህ ይልቅ የድኻውን እንስት ጠቦት በግ ወስዶ ቤቱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጀው።”—2 ሳሙ. 12:1-4
ከሁኔታው መረዳት እንደምንችለው ቀደም ሲል እረኛ የነበረው ዳዊት፣ ናታን የነገረው ነገር እውነተኛ ታሪክ ሳይመስለው አልቀረም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥተዋል፦ “ምናልባትም ናታን በደል የደረሰባቸውና ፍትሕ በማጣት የተቸገሩ ሰዎችን ጉዳይ ወደ ዳዊት የማቅረብ ልማድ ስለነበረው በዚህ ጊዜም የመጣው የዚህን ሰው ጉዳይ ሊያስፈጽም እንደሆነ ዳዊት አስቦ ሊሆን ይችላል።” ያም ሆኖ ናታን ከላይ ያለውን ታሪክ ለንጉሡ ለመናገር ድፍረት ማሳየትና ለአምላክ ታማኝ መሆን ጠይቆበታል። ዳዊት ታሪኩን ሲሰማ በጣም ተናደደ። “ሕያው እግዚአብሔርን ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል!” ሲል በቁጣ ተናገረ። ከዚያም ናታን “ያ ሰው አንተ ነህ!” በማለት ጉዳዩን ፍርጥ አድርጎ ነገረው።—2 ሳሙ. 12:5-7
ናታን ጉዳዩን በዚህ መንገድ ለማቅረብ የመረጠው ለምን ይመስልሃል? አንድ ሰው ከሌላ ሰው ጋር ፍቅር ሲይዘው ያለበትን ሁኔታ በሐቀኝነት መመርመር ሊከብደው ይችላል። ማናችንም ብንሆን የሠራነው ስህተት ሲነገረን ራሳችንን ነፃ ለማውጣት ሰበብ አስባብ መደርደር ይቀናናል። ናታን ያቀረበው ምሳሌ ግን ዳዊት ሳይታወቀው በራሱ ላይ እንዲፈርድ አድርጎታል። ንጉሡ፣ ናታን በተናገረው ታሪክ ላይ የተገለጸው ሰው የፈጸመው ድርጊት ሊወገዝ የሚገባው እንደሆነ በሚገባ ተገንዝቦ ነበር። ይሁን እንጂ ናታን፣ በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ግለሰብ የሚያመለክተው ንጉሡን እንደሆነ የገለጸው ዳዊት ይህ ድርጊት ትክክል እንዳልሆነ ከተናገረ በኋላ ነው። ዳዊት የኃጢአቱን ክብደት መገንዘብ የቻለው በዚህ ጊዜ ነበር። ይህ ደግሞ የሚሰጠውን ተግሣጽ ለመቀበል ዝግጁ እንዲሆን አድርጎታል። በእርግጥም ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር በመፈጸሙና በዚህም ምክንያት ይሖዋን ‘በማቃለሉ’ የተጸጸተ ሲሆን ለኃጢአቱ የሚገባውንም ተግሣጽ ተቀብሏል።—2 ሳሙ. 12:9-14፤ በመዝሙር 51 አናት ላይ የሚገኘውን መግለጫ ተመልከት።
ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ዓላማው አድማጮቹ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ መርዳት ነው። ናታንም ለዳዊት አክብሮት ስለነበረው ጥፋቱን የነገረው በዘዴ ነው። በተጨማሪም ዳዊት ጽድቅንና ፍትሕን ከልቡ የሚወድ ሰው እንደሆነ ያውቅ ነበር። ነቢዩ በምሳሌ ተጠቅሞ፣ በዳዊት ውስጥ ያሉት እነዚህ አምላካዊ ባሕርያት እንዲወጡ አደረገ። እኛም ቅን የሆኑ ሰዎች የይሖዋን አመለካከት እንዲያስተውሉ መርዳት እንችላለን። እንዴት? በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ ከእነሱ የላቅን እንደሆንን እንዲሰማቸው ሳናደርግ ትክክለኛውን ነገር ለመለየት የራሳቸውን የማመዛዘን ችሎታ እንዲጠቀሙ በመርዳት ይህን ማድረግ እንችላለን። ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት መመራት ያለብን በራሳችን አመለካከት ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ነው።
ናታን ታላቅ ሥልጣን ያለውን ንጉሥ ለመገሠጽ ያስቻለው ዋነኛው ነገር ለአምላክ ታማኝ መሆኑ ነው። (2 ሳሙ. 12:1) እኛም ለይሖዋ ታማኝ ከሆንን ለእሱ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥብቅና ለመቆም የሚያስችል ድፍረት እናገኛለን።
ለንጹሕ አምልኮ ጥብቅና የቆመ
ዳዊትና ናታን ጥሩ ወዳጆች ነበሩ፤ ዳዊት ለአንደኛው ልጁ ናታን የሚል ስም ማውጣቱ ይህን የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። (1 ዜና 3:1, 5) ናታን ለመጀመሪያ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የተጠቀሰው ከዳዊት ጋር ነው። ሁለቱም ለይሖዋ ፍቅር ነበራቸው። ንጉሡ ለይሖዋ ቤተ መቅደስ የመገንባት ፍላጎት እንዳለው ለነቢዩ ማማከሩ ናታን የሚሰጠውን ሐሳብ ከፍ አድርጎ ይመለከተው እንደነበር ያሳያል። ዳዊት ለናታን “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤተ መንግሥት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው። በዚህ ጊዜ ናታን “እግዚአብሔር ካንተ ጋር ስለ ሆነ፣ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” አለው።—2 ሳሙ. 7:2, 3
ናታን ታማኝ የይሖዋ አምላኪ እንደመሆኑ መጠን ዳዊት በምድር ላይ የመጀመሪያ የሆነውን ቋሚ የአምልኮ ማዕከል ለመገንባት የነበረውን ሐሳብ እንደሚደግፍ በደስታ ገለጸ። ይሁንና ናታን በዚያ ወቅት የተናገረው የግል ስሜቱን እንጂ የይሖዋን ሐሳብ እንዳልሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። አምላክ በዚያን ዕለት ሌሊት ነቢዩን ለዳዊት የተለየ መልእክት እንዲያደርስ ማለትም የይሖዋን ቤተ መቅደስ የሚሠራው እሱ አለመሆኑን እንዲነግረው አዘዘው። ቤተ መቅደሱን የሚሠራው ከዳዊት ልጆች አንዱ ነው። ሆኖም ናታን፣ አምላክ ዙፋኑን ‘ለዘላለም ለማጽናት’ ቃል ኪዳን መግባቱን ለዳዊት ነገረው።—2 ሳሙ. 7:4-16
ቤተ መቅደሱን ከመገንባት ጋር በተያያዘ፣ የአምላክ ፈቃድ ናታን ከነበረው አመለካከት የተለየ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ትሑት ነቢይ ያላንዳች ማጉረምረም ከይሖዋ ዓላማ ጋር እንደሚተባበር አሳይቷል። እኛም አምላክ በሆነ መንገድ እርማት በሚሰጠን ወቅት ልናሳየው የሚገባንን ባሕርይ በተመለከተ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! ናታን ከዚያ በኋላ በነቢይነት የተለያዩ ሥራዎችን 1 ዜና 23:1-5፤ 2 ዜና 29:25
ማከናወኑ የአምላክን ሞገስ ሳያጣ እንደኖረ ያሳያል። እንዲያውም ዳዊት ለቤተ መቅደስ አገልግሎት 4,000 ሙዚቀኞችን እንዲያደራጅ መመሪያ ለመስጠት ይሖዋ ናታንንና ባለ ራእዩ ጋድን በመንፈሱ ሳይመራቸው አልቀረም።—ለዳዊት ንጉሣዊ ሥልጣን ጥብቅና የቆመ
እርጅና የተጫጫነውን ዳዊትን ተክቶ የሚነግሠው ልጁ ሰለሞን እንደሆነ ናታን ያውቅ ነበር። በመሆኑም ዳዊት መሞቻው ተቃርቦ በነበረበት ወቅት አዶንያስ ዙፋኑን ለመንጠቅ ሲሞክር ናታን ቆራጥ እርምጃ ወስዷል። በዚህ ጊዜም ቢሆን ናታን ዘዴኛና ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። በመጀመሪያ፣ ቤርሳቤህ ወደ ዳዊት ገብታ ልጃቸው ሰለሞን ንጉሥ እንደሚሆን ቃል መግባቱን እንድታስታውሰው አሳሰባት። ከዚያም ናታን ወደ ንጉሡ በመግባት አዶንያስ ዙፋኑን እንዲወርስ መመሪያ ሰጥቶ እንደሆነ ጠየቀ። በዚህ ጊዜ አረጋዊው ንጉሥ የሁኔታውን አሳሳቢነት በመገንዘቡ ለናታንና ለሌሎች ታማኝ አገልጋዮቹ፣ ሰለሞንን ቀብተው መንገሡን እንዲያውጁ መመሪያ ሰጣቸው። በዚህ መንገድ አዶንያስ ሊያካሂደው ያሰበው መፈንቅለ መንግሥት ሳይሳካለት ቀረ።—1 ነገ. 1:5-53
ትሑት ታሪክ ጸሐፊ
በብዙዎች ዘንድ እንደሚታመነው ከ1 ሳሙኤል 25 እስከ 31 ያሉትን ምዕራፎችና 2 ሳሙኤልን በሙሉ የጻፉት ናታንና ጋድ ናቸው። በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ የተመዘገቡ በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ታሪኮችን በሚመለከት እንዲህ የሚል ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን፦ “በንጉሥ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተከናወነው ድርጊት በባለ ራእዩ በሳሙኤል የታሪክ መጽሐፍ፣ በነቢዩ በናታን የታሪክ መጽሐፍ፣ በባለ ራእዩ በጋድ የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።” (1 ዜና 29:29) በተጨማሪም ናታን፣ ‘ሰለሞን በዘመነ መንግሥቱ ስለሠራቸው’ ነገሮች እንደጻፈ ተገልጿል። (2 ዜና 9:29) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ናታን፣ ዳዊት ከሞተ በኋላም በቤተ መንግሥት ውስጥ በትጋት ማገልገሉን ቀጥሎ ነበር።
ስለ ናታን የምናውቀውን አብዛኛውን ነገር የጻፈው ራሱ ሳይሆን አይቀርም። ሆኖም ስለ አንዳንድ ነገሮች ሳይገልጽ ማለፉ ስለ እሱ ብዙ የሚነግረን ነገር አለ። ናታን ትሑት ታሪክ ጸሐፊ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። ለራሱ ክብር የማግኘት ፍላጎት አልነበረውም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደሚናገረው ናታን በመንፈስ መሪነት በተጻፈው ታሪክ ውስጥ የተጠቀሰው “ራሱን ሳያስተዋውቅና የዘር ሐረጉንም ሳይጠቅስ” ነው። በመሆኑም ስለ ናታን ቅድመ አያቶች ወይም ስለ ግል ሕይወቱ የምናውቀው ምንም ነገር የለም።
ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት ያሳየ
ስለ ናታን በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከተገለጹት ጥቂት ሐሳቦች በመነሳት ይህ ነቢይ ትሑትና መለኮታዊ አሠራሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚጥር ደፋር ሰው እንደነበረ በግልጽ መረዳት እንችላለን። ይሖዋ አምላክ ከበድ ያሉ ኃላፊነቶችን እንዲወጣ መብት ሰጥቶት ነበር። እንግዲያው ለአምላክ ታማኝ እንደመሆንና ለመለኮታዊ መመሪያዎች ጥልቅ ፍቅር እንደማሳደር በመሳሰሉት በናታን ባሕርያት ላይ አሰላስል። ከዚያም እነዚህን ባሕርያት በራስህ ሕይወት ለማንጸባረቅ ጥረት አድርግ።
እርግጥ ነው፣ ምንዝር የሚፈጽሙ ነገሥታትን እንድትገሥጽ ወይም የመንግሥት ግልበጣ ሙከራዎችን እንድታከሽፍ አትታዘዝ ይሆናል። ይሁን እንጂ በይሖዋ እርዳታ አንተም ለአምላክ ታማኝ ልትሆንና ለእሱ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥብቅና ልትቆም ትችላለህ። በተጨማሪም እውነትን በምታስተምርበትና ንጹሑን አምልኮ በምታስፋፋበት ወቅት ደፋር ሆኖም ዘዴኛ መሆን ትችላለህ።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ናታን፣ ለዳዊት ንጉሣዊ ሥልጣን ጥብቅና የቆመ እንደመሆኑ መጠን ቤርሳቤህን በዘዴ አናግሯታል