የአምላክን ቃል በድፍረት አውጀዋል!
የአምላክን ቃል በድፍረት አውጀዋል!
ተቃውሞ በሚያጋጥምበት ወቅት ያለምንም ፍርሃት በድፍረት መመሥከር ያስፈልጋል። ስለ አምላክ መንግሥት ‘የተሟላ ምሥክርነት መስጠት’ እንዲሁም የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (በአማርኛ አይገኙም) በተባሉትና በሌሎች ጽሑፎች ላይ እንደተገለጸው እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ባሕርይ እንዳላቸው አሳይተዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የእምነት ባልንጀሮቻችን ሁሉ እኛም ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠንና ቃሉን ያለምንም ፍርሃት በድፍረት ለመናገር እንዲረዳን በጸሎት እንለምነዋለን።—ሥራ 4:23-31
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የነበረውን የስብከት እንቅስቃሴያችንን አስመልክቶ አንድ ወንድም የሚከተለውን ጽፎ ነበር፦ “የአምላክ አገልጋዮች የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት በሚል ርዕስ በተከታታይ ከወጡት ጥራዞች ሰባተኛ የሆነውን ያለቀለት ሚስጥር (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ በከፍተኛ ቅንዓት ያሰራጩ ነበር። ይህ መጽሐፍ በወቅቱ ይዘጋጁ ከነበሩት መጻሕፍት ሁሉ በስርጭቱ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ሆኖ ነበር። በ1918 የመንግሥት ዜና ቁጥር 1 ወጣ። ቀጥሎም፣ ያለቀለት ሚስጥር የተባለው መጽሐፍ እንዳይሰራጭ ባለሥልጣናቱ ያገዱት ለምን እንደሆነ የሚያብራራው የመንግሥት ዜና ቁጥር 2 ተዘጋጀ። ከዚያ በኋላ የመንግሥት ዜና ቁጥር 3 ወጣ። ታማኝ የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች እነዚህን ጽሑፎች በስፋት አሰራጭተዋል። በእርግጥም የመንግሥት ዜናዎቹን ለማሰራጨት እምነትና ድፍረት ጠይቆባቸዋል።”
በአሁኑ ጊዜ፣ አዳዲስ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በአብዛኛው የአገልግሎት ሥልጠና ይሰጣቸዋል፤ በድሮ ጊዜ ግን እንደዚህ ያለው ሥልጠና አልነበረም ማለት ይቻላል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ ፖላንዳዊ ወንድም በ1922 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መስክ አገልግሎት ሲወጣ ያጋጠመውን ሁኔታ እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፦ “የያዝኩትን ጽሑፍ ምን ብዬ ማበርከት እንዳለብኝ የማላውቅ ከመሆኑም በላይ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታዬ በጣም ውስን ነበር፤ ያም ቢሆን ብቻዬን ወደ አንድ ዶክተር ቢሮ በመሄድ በሩን አንኳኳሁ። በዚህ ጊዜ አንዲት ነርስ በሩን ከፈተች። በወቅቱ ደስታና ፍርሃት የተቀላቀለበት ስሜት ተሰምቶኝ ስለነበር ያንን ጊዜ ፈጽሞ አልረሳውም። ቦርሳዬን ስከፍት መጽሐፎቹ በሙሉ ከነርሷ እግር ሥር ተዘረገፉ። ምን ብዬ እንደተናገርኩ ባላውቅም አንድ መጽሐፍ አበረከትኩላት። ልክ ተሰናብቻት ስሄድ ድፍረት እንዳገኘሁና ይሖዋም እንደባረከኝ ተሰማኝ። ያን ቀን በዚያ የንግድ አካባቢ ብዙ ቡክሌቶችን አበረከትኩ።”
“በ1933 ብዙ ወንድሞች የመንግሥቱን መልእክት ለሰዎች ለማድረስ የድምፅ ማጉያ መሣሪያ የተገጠመላቸውን መኪኖች ይጠቀሙ ነበር” በማለት አንዲት እህት ተናግራለች። በአንድ ወቅት እሷና የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አንድ ባልና ሚስት በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኝ ተራራማ አካባቢ እየሰበኩ ነበር። እህት በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ በማለት አስታውሳ ተናግራለች፦ “ወንድም መኪናውን ወደ ተራሮቹ አናት ሲወስደው እኛ ደግሞ ከተማው ውስጥ ቆየን። በሸክላ የተቀዳውን መልእክት ማጫወት ሲጀምር ድምፁ ከሰማይ የመጣ ይመስል ነበር። የከተማዋ ሰዎች ወንድም የሚገኝበትን ቦታ ለማወቅ ብዙ ቢለፉም ሊደርሱበት አልቻሉም። የተቀዳው መልእክት ተሰምቶ ካበቃ በኋላ ሰዎችን ቀርበን በማናገር መሠከርንላቸው። የድምፅ ማጉያ መሣሪያ በተገጠመባቸው ሌሎች ሁለት መኪኖች ላይም ሠርቻለሁ፤ አብዛኞቹ ሰዎች መልእክቱን ለመስማት ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ ከመኪኖቹ የሚወጣው ድምፅ እያንዳንዱን ቤት ይገባ ስለነበር ሰዎቹ መልእክቱን
ከመስማት ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም። ይሖዋ ምንጊዜም በትክክለኛው ጊዜ ላይ ትክክለኛውን ዘዴ እንድንጠቀም ያደርግ እንደነበር ማስተዋል ችያለሁ። ይህ የስብከት ዘዴ ከፍተኛ ድፍረት ማሳየት ጠይቆብናል። ያም ቢሆን ዘዴው የታለመለትን ግብ መትቷል፤ እንዲሁም የይሖዋ ስም በስፋት እንዲታወቅ አድርጓል።”የአምላክ አገልጋዮች በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በአገልግሎት ላይ የሸክላ ማጫዎቻዎችን በመጠቀም የተቀዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን ለሰዎች ያሰሙ ነበር። አንዲት እህት እንደሚከተለው በማለት ታስታውሳለች፦ “አንዲት ወጣት እህት ከቤት ወደ ቤት እየሄደች የሸክላ ማጫወቻውን ከፍታ ታሰማ ነበር። አንድ ቤት ደርሳ የተቀዳውን ንግግር ማሰማት ስትጀምር የቤቱ ባለቤት በጣም ስለተናደደ የሸክላ ማጫወቻውን በእርግጫ ብሎ አሽቀነጠረው። ደግነቱ አንድም ሸክላ አልተሰበረም። በአንድ የቆመ የጭነት መኪና ውስጥ ምሳቸውን እየበሉ የነበሩ ሦስት ሰዎች ሁኔታውን ይመለከቱ ነበር፤ እናም እህትን ጠርተው የተቀዳውን ንግግር እንድታሰማቸው ጠየቋት እንዲሁም ጽሑፍ ወሰዱ። ይህም አገልግሎቷን እንድትቀጥል ብርታት ሆኗታል።” እንዲህ ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ለማለፍ ከፍተኛ ድፍረት ይጠይቃል።
ይህችው እህት አክላ እንዲህ ብላለች፦ “በ1940 መጽሔቶችን መንገድ ላይ ማበርከት ስንጀምር የነበረው ሁኔታ ትዝ ይለኛል። ቀደም ሲል አንዳንድ መፈክሮችን በመያዝ ሰልፍ እንወጣ ነበር። ወንድሞችና እህቶች በአንድ መስመር በመሰለፍ ‘ሃይማኖት ወጥመድና ማጭበርበሪያ ነው’ እንዲሁም ‘አምላክንና ንጉሡ ክርስቶስን አገልግሉ’ የሚሉ መፈክሮችን አንግበው በእግረኛ መንገድ ላይ ይሄዱ ነበር። እግረ መንገዳቸውን ትራክቶችን በነፃ ለሰዎች ያድላሉ። እንዲህ ያሉ የስብከት ዘዴዎች ድፍረት የሚጠይቁ ቢሆንም በሕዝብ ሁሉ ፊት የይሖዋን ስምና የእሱን ሕዝቦች በማሳወቅ ረገድ ዒላማቸውን መትተዋል።”
አንዲት ሌላ እህት ደግሞ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አስታውሳ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በትንንሽ ከተሞች መጽሔቶችን ማሰራጨት በጣም ከባድ ነበር። ምክንያቱም በጊዜው በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ኃይለኛ ተቃውሞ ይደርስ ነበር። . . . አንድ ጥግ ላይ መጽሔቶችን ይዞ በመቆም፣ እንድንጠቀምባቸው የተነገሩንን መፈክሮች ጮክ ባለ ድምፅ ማሰማት በእርግጥም ድፍረት ይጠይቅ ነበር። ሆኖም አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር ቅዳሜ ቅዳሜ ከአገልግሎት አንቀርም ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ወዳጃዊ በሆነ መንፈስ ያነጋግሩናል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ለጠብ የተዘጋጁ በርከት ያሉ ሰዎች ይከቡናል፤ በዚህ ወቅት ረብሻ ከመፈጠሩ በፊት ከአካባቢው ዘወር እንላለን።”
የይሖዋ ምሥክሮች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ስደት ቢያጋጥማቸውም አገልግሎታቸውን በድፍረት አከናውነዋል። “ድፍረት”ተብሎ በተጠራው የምሥክርነት ወቅት ማለትም ከታኅሣሥ 1, 1940 እስከ ጥር 12, 1941 ድረስ በተካሄደው የ43 ቀናት ዘመቻ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ 50,000 የሚያህሉ አስፋፊዎች ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ቡክሌቶችን አሰራጭተዋል።
በአምላክ ድርጅት ውስጥ ያሉ ብዙ አረጋውያን ቀደም ባሉት ጊዜያት ከፍተኛ ድፍረት የሚጠይቁ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸው እንደነበር መቼም አይረሱም። አንዳንዶች ‘እስከ መጨረሻው ድረስ በቅንዓት መስበካችንን እንቀጥል!’ የሚለውን አባባል ለዓመታት ይጠቀሙ እንደነበር ያስታውሳሉ፤ ይህም በወቅቱ የነበራቸውን ድፍረት የሚያንጸባርቅ ነው። ይህ ሥርዓት ከማለቁ በፊት ከአምላክ የተቀበልነውን መልእክት ለሰዎች ለማድረስ ወደፊት ምን ዓይነት ዘዴዎችን እንደምንጠቀም ጊዜ የሚያሳየን ነገር ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ይሖዋ በሚሰጠን እርዳታ እየታገዝን ቃሉን በእምነትና በድፍረት ማወጃችንን እንቀጥላለን።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በመንግሥቱ የስብከት ሥራ መካፈል ምንጊዜም ድፍረት ይጠይቃል