በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎች ‘ከእንቅልፋቸው እንዲነቁ’ እርዷቸው

ሰዎች ‘ከእንቅልፋቸው እንዲነቁ’ እርዷቸው

ሰዎች ‘ከእንቅልፋቸው እንዲነቁ’ እርዷቸው

“ዘመኑን ስለምታውቁም ይህን አድርጉ፤ . . . ከእንቅልፍ የምትነቁበት ሰዓት አሁን ነው።”​—ሮም 13:11

ልታብራራ ትችላለህ?

ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ንቁ ሆነው መኖር የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

ንቁ የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ጥሩ አዳማጭና አስተዋይ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?

ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ እንዲሁም ቀስ አድርጎ ሰዎችን መቀስቀስ ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ ምን ሚና ይጫወታል?

1, 2. ብዙ ሰዎች መንቃት የሚያስፈልጋቸው ከየትኛው እንቅልፍ ነው?

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንቅልፍ እየተጫጫናቸው እንዲያውም ተኝተው በማሽከርከራቸው ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጣሉ። ሌሎች ደግሞ ተኝተው በማርፈዳቸው ወይም በሥራ ገበታቸው ላይ እያሉ ተኝተው በመገኘታቸው ከሥራ ይባረራሉ። መንፈሳዊ ድብታ ግን ከዚህ ለከፋ ጉዳት ይዳርጋል። መጽሐፍ ቅዱስም “ነቅቶ የሚኖር . . . ሰው ደስተኛ ነው” በማለት ሲናገር ስለዚህ ዓይነቱ እንቅልፍ መጥቀሱ ነው።​—ራእይ 16:14-16

2 ታላቁ የይሖዋ ቀን እየቀረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የሰው ዘር በመንፈሳዊ ሁኔታ አንቀላፍቷል። አንዳንድ የሕዝበ ክርስትና መሪዎችም እንኳ መንጎቻቸው “እንቅልፍ” እንደያዛቸው ሲናገሩ ይደመጣል። ለመሆኑ መንፈሳዊ እንቅልፍ ሲባል ምን ማለት ነው? እውነተኛ ክርስቲያኖች ምንጊዜም ንቁ መሆናቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሌሎች ከመንፈሳዊ እንቅልፍ እንዲነቁ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

መንፈሳዊ እንቅልፍ ሲባል ምን ማለት ነው?

3. በመንፈሳዊ ንቁ ያልሆነን ሰው እንዴት አድርገህ ትገልጸዋለህ?

3 እንቅልፍ የጣላቸው ሰዎች በአብዛኛው ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አያደርጉም። ከዚህ በተቃራኒ ግን መንፈሳዊ እንቅልፍ የያዛቸው ሰዎች መንፈሳዊ ነገሮችን በማከናወን አይሁን እንጂ በሌሎች ሥራዎች የተጠመዱ ሊሆኑ ይችላሉ። በዕለታዊ ኑሯቸው ከልክ በላይ እየተጨነቁ አሊያም ደስታ ለማግኘት፣ ዝና ለማትረፍ ወይም ሀብት ለማካበት እየተሯሯጡ ይሆናል። ይሁንና መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ምንም ጥረት አያደርጉም ማለት ይቻላል። በመንፈሳዊ ንቁ የሆኑ ሰዎች ግን “በመጨረሻው ዘመን” ውስጥ እንደምንገኝ ይገነዘባሉ፤ በመሆኑም የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ረገድ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ንቁዎች ናቸው።​—2 ጴጥ. 3:3, 4፤ ሉቃስ 21:34-36

4. “እንደ ሌሎቹ አናንቀላፋ” የሚለው ምክር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

4 አንደኛ ተሰሎንቄ 5:4-8ን አንብብ። ከዚህ ጥቅስ ማየት እንደምንችለው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የእምነት ባልንጀሮቹ ‘እንደ ሌሎቹ እንዳያንቀላፉ’ አሳስቧቸዋል። ጳውሎስ ይህን ማሳሰቢያ ሲሰጥ ምን ማለቱ ነበር? ‘እንዳንቀላፋን’ ተደርገን እንድንቆጠር ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ችላ ማለት ነው። ሌላው ደግሞ ይሖዋ፣ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸውን ሰዎች የሚያጠፋበት ጊዜ መቅረቡን አምነን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን ነው። በመሆኑም ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች የሚከተሉት ጎዳናም ሆነ የሚያሳዩት ዝንባሌ ተጽዕኖ እንዳያደርግብን መጠንቀቅ ይኖርብናል።

5. በመንፈሳዊ ያንቀላፉ ሰዎች ተለይተው የሚታወቁት በየትኛው አመለካከታቸው ነው?

5 አንዳንድ ሰዎች፣ ለሥራቸው ተጠያቂ የሚያደርጋቸው አምላክ እንደሌለ አድርገው ያስባሉ። (መዝ. 53:1) ሌሎች ደግሞ አምላክ ለሰው ልጆች ምንም ደንታ ስለሌለው እነሱም በሕይወታቸው ውስጥ ለእሱ ቦታ መስጠት እንደማያስፈልጋቸው ይሰማቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል መሆናቸው ብቻ የአምላክ ወዳጅ እንደሚያደርጋቸው ይሰማቸዋል። ሁሉም ቢሆኑ በመንፈሳዊ አንቀላፍተዋል፤ በመሆኑም እነዚህ ሰዎች መንቃት ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?

እኛ ራሳችን ንቁዎች መሆን ይኖርብናል

6. ክርስቲያኖች ምንጊዜም በመንፈሳዊ ንቁ ሆነው ለመገኘት መጣር ያለባቸው ለምንድን ነው?

6 ሌሎችን መቀስቀስ እንድንችል እኛ ራሳችን ንቁዎች መሆን ይኖርብናል። ይህ ምን ይጠይቃል? የአምላክ ቃል ምሳሌያዊ እንቅልፍን የሚያይዘው ‘ከጨለማ ሥራ’ ጋር ማለትም መረን ከለቀቀ ፈንጠዝያ፣ ከስካር፣ ልቅ ከሆነ የፆታ ግንኙነት፣ ከብልግና፣ ከጠብ እንዲሁም ከቅናት ጋር ነው። (ሮም 13:11-14ን አንብብ።) እንዲህ ካሉ ድርጊቶች መራቅ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ንቁ መሆን የግድ አስፈላጊ ነው። አንድ ሾፌር፣ እያሽከረከሩ መተኛት ያለውን አደጋ አቅልሎ የሚመለከት ከሆነ ሕይወቱን ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል። ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ማንቀላፋት ሕይወትን ሊያሳጣ እንደሚችል መገንዘባቸው በጣም አስፈላጊ ነው!

7. ሰዎች ለምሥራቹ ያላቸው አመለካከት በእኛ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው?

7 ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በአገልግሎት ክልሉ ውስጥ ያሉ ሰዎች ለምሥራቹ ፈጽሞ ጥሩ ምላሽ ሊሰጡ አይችሉም የሚል አመለካከት ይኖረው ይሆናል። (ምሳሌ 6:10, 11) ምናልባትም ይህ ግለሰብ ‘ለምሥራቹ ምላሽ የሚሰጥ አንድም ሰው ከሌለ ሰዎችን አግኝቶ ለማነጋገርና ለመርዳት ይህን ያህል መድከም ምን ያስፈልጋል?’ የሚል ሐሳብ ሊመጣበት ይችላል። እርግጥ ነው፣ በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች መንፈሳዊ እንቅልፍ ላይ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይሁንና ያሉበት ሁኔታም ሆነ አመለካከታቸው በጊዜ ሂደት ሊለወጥ ይችላል። በመሆኑም አንዳንዶች ከእንቅልፋቸው በመንቃት ጥሩ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ። እኛ ራሳችን ንቁ በመሆን ለምሳሌ፣ የመንግሥቱን መልእክት በሚስብ መንገድ ለማቅረብ የተለያዩ አዳዲስ ዘዴዎችን በመጠቀም እነዚህን ሰዎች ልንረዳቸው እንችላለን። ምንጊዜም ነቅተን እንደምንጠብቅ የምናሳይበት ሌላው መንገድ ደግሞ አገልግሎታችን አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት መረዳት ነው።

አገልግሎታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

8. ክርስቲያናዊ አገልግሎታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

8 በአሁኑ ጊዜ ሰዎች የሚሰጡት ምላሽ ምንም ይሁን ምን የስብከቱ ሥራችን ይሖዋን እንደሚያስከብርና ዓላማውን በማስፈጸም ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ማስታወስ ይኖርብናል። ለምሥራቹ የማይታዘዙ ሰዎች በቅርቡ የፍርድ እርምጃ ይወሰድባቸዋል። ሰዎች ለስብከቱ ሥራችን የሚሰጡት ምላሽ ለፍርድ መሠረት ይሆናል። (2 ተሰ. 1:8, 9) ከዚህም በተጨማሪ አንድ ክርስቲያን ‘ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት መነሳታቸው’ አይቀርም በሚል ሰበብ አገልግሎቱን በቅንዓት ማከናወን አስፈላጊ እንዳልሆነ ቢሰማው ተገቢ አይሆንም። (ሥራ 24:15) ከአምላክ ቃል እንደተረዳነው እንደ ‘ፍየል’ ተቆጥረው የተፈረደባቸው ሰዎች “ወደ ዘላለም ጥፋት” ይሄዳሉ። የስብከቱ ሥራችን ሰዎች እንዲለወጡና ‘የዘላለም ሕይወት’ እንዲያገኙ በር ስለሚከፍት የአምላክ ምሕረት መገለጫ ነው። (ማቴ. 25:32, 41, 46፤ ሮም 10:13-15) ታዲያ እኛ ካልሰበክን ሰዎች ሕይወት ሰጪ የሆነውን መልእክት እንዴት መስማት ይችላሉ?

9. በስብከቱ ሥራ መካፈልህ አንተንም ሆነ ሌሎችን የጠቀማችሁ እንዴት ነው?

9 ምሥራቹን መስበካችን ለእኛም ቢሆን ጥቅም አለው። (1 ጢሞቴዎስ 4:16ን አንብብ።) ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ ተስፋዎች ለሰዎች መናገርህ እምነትህንና ለአምላክ ያለህን ፍቅር እንዳጠናከረ አልተሰማህም? ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንድታፈራስ አልረዳህም? በአገልግሎት በመካፈል ለአምላክ ያለህን ቅንዓት ማሳየትህ ለደስታህ አስተዋጽኦ እንዳደረገ አይሰማህም? እውነትን ለሌሎች የማስተማር መብት ያገኙ ብዙ ክርስቲያኖች የአምላክ መንፈስ የሰዎችን ሕይወት ሲለውጥ መመልከታቸው ደስታ አስገኝቶላቸዋል።

አስተዋዮች ሁኑ

10, 11. (ሀ) ኢየሱስና ጳውሎስ ንቁዎችና አስተዋዮች መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) ንቁዎችና አስተዋዮች መሆናችን በአገልግሎታችን ውጤታማ ለመሆን የሚረዳን እንዴት እንደሆነ አብራራ።

10 ሰዎች ለምሥራቹ ያላቸው ፍላጎት እንዲቀሰቀስ ለማድረግ የተለያዩ መንገዶችን መጠቀም ይቻላል። በመሆኑም ክርስቲያኖች በአገልግሎት ላይ ነገሮችን ለማስተዋል ንቁ መሆን አለባቸው። በዚህ ረገድ ዋነኛ ምሳሌያችን ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ፍጹም ቢሆንም በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውን ነገር ለማስተዋል ይጥር ነበር። ለምሳሌ አንድ ፈሪሳዊ በውስጡ መናደዱን፣ አንዲት ኃጢአተኛ ሴት ልባዊ ንስሐ መግባቷን እንዲሁም አንዲት መበለት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማንጸባረቋን ማስተዋል ችሎ ነበር። (ሉቃስ 7:37-50፤ 21:1-4) ኢየሱስ የእያንዳንዱን ሰው መንፈሳዊ ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት ተገቢውን ምላሽ ይሰጥ ነበር። እርግጥ ነው፣ የአምላክ አገልጋዮች አስተዋዮች ለመሆን ፍጹም መሆን አይጠበቅባቸውም። በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ጳውሎስ ምሥራቹን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ብሎም የተለያየ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ሊማርክ በሚችል መንገድ ያቀርብ ነበር።​—ሥራ 17:22, 23, 34፤ 1 ቆሮ. 9:19-23

11 ልክ እንደ ኢየሱስና እንደ ጳውሎስ እኛም ንቁዎችና አስተዋዮች መሆናችን የምናገኛቸውን ሰዎች ፍላጎት መቀስቀስ የምንችልበትን ከሁሉ የተሻለውን መንገድ ለመገንዘብ ያስችለናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድን ሰው ልታነጋግሩ ስትሉ ባሕሉን፣ ፍላጎቱንና የቤተሰቡን ሁኔታ የሚጠቁሙ ነገሮችን ለማስተዋል ጥረት አድርጉ። ምናልባትም ግለሰቡ በወቅቱ እያደረገ ያለውን ነገር በማስተዋልና ስለዚያ ጉዳይ በጎ አስተያየት በመስጠት ውይይታችንን መጀመር እንችላለን።

12. በአገልግሎት ላይ ስንሆን ከምናደርገው ጭውውት ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

12 ሁኔታዎችን በንቃት የሚከታተል ሰው ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን ያስወግዳል። በአገልግሎት ላይ ሳለን አብሮን ካለን ሰው ጋር የሚያንጽ ጭውውት ማድረግ እንችል ይሆናል። ያም ሆኖ በመስክ አገልግሎት የምንካፈልበት ዋነኛ ዓላማ ለሰዎች መስበክ መሆኑን ማስታወስ ይገባናል። (መክ. 3:1, 7) በመሆኑም ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ስንሄድ የምንጨዋወተው ነገር አገልግሎታችንን እንዳያስተጓጉልብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። በዚህ ወቅት ትኩረታችንን በሥራችን ላይ ለማድረግ ከሚረዱን ግሩም መንገዶች አንዱ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች እንዴት በተሻለ መንገድ ማናገር እንደምንችል መወያየት ነው። ሞባይል ስልክ አገልግሎታችንን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን ሊረዳን ቢችልም የቤቱን ባለቤት በምናነጋግርበት ወቅት እንዳይረብሸን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን።

ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት አሳዩ

13, 14. (ሀ) የአንድን ሰው ፍላጎት ለማወቅ ምን ማድረግ እንችላለን? (ለ) የሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት እንዲቀሰቀስ የሚያደርጉት የትኞቹ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ?

13 ንቁና አስተዋይ የሆኑ የምሥራቹ ሰባኪዎች በአገልግሎት ላይ የሚያገኟቸውን ሰዎች በጥንቃቄ ያዳምጣሉ። በክልላችሁ ውስጥ የምታገኟቸው ሰዎች ስሜታቸውን አውጥተው እንዲገልጹ ለማድረግ የትኞቹን ጥያቄዎች ማንሳት ትችላላችሁ? ምናልባት የሃይማኖት መብዛት፣ በአካባቢያቸው ዓመፅ እየተስፋፋ መሄዱ ወይም መንግሥታት በተሳካ መንገድ ማስተዳደር አለመቻላቸው ያሳስባቸው ይሆን? ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ የሚታየውን አስደናቂ ንድፍ በማንሳት ወይም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ በመጥቀስ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን መቀስቀስ ትችሉ ይሆን? በየትኛውም ባሕል ውስጥ ያሉ ሰዎች ማለት ይቻላል ስለ ጸሎት አንስቶ መነጋገር ያስደስታቸዋል፤ ሌላው ቀርቶ አንዳንድ አምላክ የለሽ የሆኑ ሰዎች እንኳ ይህ ርዕሰ ጉዳይ ትኩረታቸውን ይስባል። ብዙዎች ጸሎታቸውን የሚሰማ አምላክ መኖሩን ይጠራጠራሉ። ሌሎች ደግሞ ‘አምላክ ሁሉንም ዓይነት ጸሎት ይሰማል? ካልሆነ ጸሎታችንን አምላክ እንዲሰማ ምን ማድረግ ይኖርብናል?’ የሚሉት ጥያቄዎች ያስጨንቋቸው ይሆናል።

14 ተሞክሮ ያላቸው አስፋፊዎችን ልብ ብሎ ማየት ውይይት የመጀመር ችሎታችንን ለማሻሻል እንደሚረዳን ምንም ጥርጥር የለውም። ሰዎችን በሚያናግሩበት ጊዜ ሰዎቹን በጥያቄ እንደማያፋጥጧቸው ወይም በግል ጉዳያቸው ጣልቃ እንደማይገቡ ልብ በሉ። የድምፃቸው ቃና ወይም ፊታቸው ላይ የሚነበበው ነገር የቤቱን ባለቤት አመለካከት ለመረዳት ጥረት እንደሚያደርጉ የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ ተመልከቱ።​—ምሳሌ 15:13

ደግና ዘዴኛ መሆን

15. በስብከት ሥራችን ደግነት ማሳየት የሚገባን ለምንድን ነው?

15 ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ይዞህ እያለ ብትቀሰቀስ ደስ ይልሃል? ብዙ ሰዎች ከእንቅልፋቸው ድንገት ሲቀሰቀሱ ደስ አይላቸውም። በመሆኑም እንዳይደነግጡ ቀስ አድርጎ መቀስቀሱ በአብዛኛው የተሻለ ነው። ሰዎችን ከመንፈሳዊ እንቅልፋቸው ከመቀስቀስ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ቤቱ በመሄዳችን ቢናደድ የተሻለው ምላሽ ምንድን ነው? ስሜቱን ተረዳለት፤ የተሰማውን በግልጽ ስለተናገረ አመስግነው እንዲሁም በሰላም ተሰናብተህ ሂድ። (ምሳሌ 15:1፤ 17:14፤ 2 ጢሞ. 2:24) እንዲህ ዓይነት ደግነት ማሳየትህ ግለሰቡ ወደፊት ሌላ የይሖዋ ምሥክር ሲያነጋግረው ጥሩ ምላሽ እንዲሰጥ ሊያነሳሳው ይችላል።

16, 17. በአገልግሎት ላይ አስተዋዮች መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሰዎች ለሚሰነዝሩት የተቃውሞ ሐሳብ ምላሽ መስጠት ይጠበቅብህ ይሆናል። ሰዎች እንዲህ ሊሉን ይችላሉ፦ “አይ፣ እኛ የራሳችን ሃይማኖት አለን” ወይም “ስለ ሃይማኖት መነጋገር አልፈልግም።” ምናልባት ይህ፣ ከእኛ ለመለየት ሲሉ የሚያቀርቡት ሰበብ እንጂ እውነተኛ ስሜታቸው ላይሆን ይችላል። ይሁንና የቤቱ ባለቤት ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለው ፍላጎት እንዲቀሰቀስ የሚያደርጉ ትኩረት የሚስቡ ጥያቄዎችን ደግነት በሚንጸባረቅበትና በዘዴ በማንሳት ውይይቱን መቀጠል ትችል ይሆናል።​—ቆላስይስ 4:6ን አንብብ።

17 አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሥራ በመያዛቸው ከእኛ ጋር መነጋገር እንደማይችሉ በሚናገሩበት ጊዜ ያሉበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ተሰናብተን መሄዳችን የተሻለ ነው። ይሁን እንጂ አጠር ያለና የቤቱን ባለቤት ልብ ሊነካ የሚችል ሐሳብ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማህ ጊዜ ይኖር ይሆናል። አንዳንድ ወንድሞች ከመሰናበታቸው በፊት አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የቤቱን ባለቤት ስሜት የሚኮረኩር ጥቅስ ካነበቡ በኋላ በዚያ ላይ እንዲያስብ የሚያደርገውን አንድ ጥያቄ ይጠይቃሉ። እንዲህ ያለ ዘዴ መጠቀማቸው የቤቱን ባለቤት ፍላጎት ሊቀሰቅሰውና ጊዜ የለኝም ያለው ሰው ከእነሱ ጋር አጠር ያለ ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛ እስከመሆን ሊያደርሰው ይችላል። አንተስ ሁኔታዎች የሚፈቅዱልህ ከሆነ እንዲህ ለማድረግ ለምን አትሞክርም?

18. መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት በመስጠት ረገድ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ምን ማድረግ እንችላለን?

18 መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት ምንጊዜም ዝግጁ ከሆንን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምናገኛቸው ሰዎች ለምሥራቹ ያላቸው ፍላጎት እንዲቀሰቀስ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎችን ማግኘታችን አይቀርም። ብዙ ወንድሞችና እህቶች ጥቂት ጽሑፎችን በኪሳቸው ወይም በቦርሳቸው ይይዛሉ። በተጨማሪም አጋጣሚውን ሲያገኙ ሊጠቀሙበት የሚችሉ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በአእምሯቸው ይይዛሉ። አንተም መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ከፈለግክ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹን ወይም በጉባኤህ ውስጥ ያሉ አቅኚዎችን ማነጋገር ትችላለህ።

ዘመዶቻችንን ቀስ አድርገን እንቀስቅሳቸው

19. ዘመዶቻችንን ለመርዳት የምናደርገውን ጥረት ማቆም የሌለብን ለምንድን ነው?

19 ሁላችንም ዘመዶቻችን ምሥራቹን ቢቀበሉ ደስ እንደሚለን የታወቀ ነው። (ኢያሱ 2:13፤ ሥራ 10:24, 48፤ 16:31, 32) ያም ሆኖ መጀመሪያ ላይ ጥሩ ምላሽ ካልሰጡን እንደገና ለመሞከር ያለን ፍላጎት ሊጠፋ ይችላል። ‘ምንም ባደርግላቸው ወይም ብናገራቸው አይለወጡም’ ብለን እናስብ ይሆናል። ሆኖም የዘመዶችህ ሕይወት ወይም አመለካከት እንዲለወጥ የሚያደርጉ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። ምናልባትም አሁን እውነትን በተሻለ መንገድ ማብራራት በመቻልህ የተለየ ውጤት ልታገኝ ትችላለህ።

20. ዘመዶቻችንን ስናነጋግር ዘዴኛ መሆናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

20 ለዘመዶቻችን ስሜት ግድ የለሽ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል። (ሮም 2:4) በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች እንደምናደርገው ሁሉ ዘመዶቻችንን በደግነት ማነጋገር አይገባንም? በእርግጥም በገርነትና በአክብሮት ለማነጋገር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እየተሰበኩ እንደሆነ እንዲሰማቸው ሳታደርጉ እውነት ሕይወታችሁን ያሻሻለው እንዴት እንደሆነ እንዲገነዘቡ እርዷቸው። (ኤፌ. 4:23, 24) ይሖዋ ‘የሚበጃችሁን ነገር በማስተማር’ ትርጉም ያለው ሕይወት እንድትመሩ የረዳችሁ እንዴት እንደሆነ በግልጽ እንዲታያቸው አድርጉ። (ኢሳ. 48:17) የክርስቲያኖች አኗኗር ምን እንደሚመስል በአንተ ሕይወት እንዲመለከቱ አድርግ።

21, 22. ዘመዶቻችንን በመንፈሳዊ ለመርዳት በምናደርገው ጥረት መጽናታችን ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ የሚያሳይ አንድ ተሞክሮ ተናገር።

21 በቅርቡ አንዲት እህት እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ለ13 ወንድሞቼና እህቶቼ በቃልም ሆነ በምግባር ለመመሥከር ምንጊዜም ጥረት አደርጋለሁ። ለእያንዳንዳቸው ደብዳቤ ሳልጽፍ ዓመቱ ያለፈበት ጊዜ የለም። ያም ሆኖ ለ30 ዓመታት ከቤተሰባችን ውስጥ የይሖዋ ምሥክር የሆንኩት እኔ ብቻ ነበርኩ።”

22 እህት እንዲህ ስትል አክላ ተናግራለች፦ “አንድ ቀን፣ እኔ ካለሁበት በመቶዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ርቃ ለምትኖረው እህቴ ስልክ ደወልኩላት። በዚህ ጊዜ እህቴ የቤተ ክርስቲያኗ ሰባኪ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠናት ብትጠይቀውም እሱ ግን ያን ማድረግ እንዳልቻለ ነገረችኝ። በዚህ ረገድ እኔ ልረዳት ፈቃደኛ እንደሆንኩ ስነግራት ‘እሺ፣ ሆኖም አንድ ነገር እንድታውቂ እፈልጋለሁ። እኔ እንደሆነ ፈጽሞ የይሖዋ ምሥክር አልሆንም’ አለችኝ። ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ በፖስታ ከላኩላት በኋላ በየተወሰነ ጊዜ እደውልላት ነበር። እሷ ግን መጽሐፉን አንድም ቀን ገልጣው አታውቅም ነበር። በመጨረሻም አንድ ቀን ስልክ ደውዬ መጽሐፉን እንድትይዘው ከጠየቅኳት በኋላ ለ15 ደቂቃ ያህል መጽሐፉ ላይ ያሉትን አንዳንድ ጥቅሶች እያነበብን ተወያየንባቸው። በዚህ መልክ ለጥቂት ጊዜ በስልክ ከተነጋገርን በኋላ ከ15 ደቂቃ በላይ ማጥናት እንደምትፈልግ ገለጸች። ከዚያም ለማጥናት ራሷ መደወል የጀመረች ከመሆኑም በላይ በጠዋት ከአልጋዬ ሳልነሳ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በቀን ውስጥ ሁለት ጊዜ ትደውልልኝ ነበር። እህቴ በቀጣዩ ዓመት ተጠመቀች፤ ከዚያ በኋላ ባለው ዓመት ደግሞ አቅኚ ሆነች።”

23. ሰዎችን ከመንፈሳዊ እንቅልፋቸው ለማንቃት መታከት የሌለብን ለምንድን ነው?

23 ሰዎችን ከመንፈሳዊ እንቅልፍ መቀስቀስ ዘዴኛ መሆንና ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ትሑት የሆኑ ሰዎች፣ እነሱን ከእንቅልፋቸው ለማንቃት ለምናደርገው ጥረት አሁንም ድረስ በጎ ምላሽ እየሰጡ ነው። በየወሩ በአማካይ ከ20,000 የሚበልጡ ሰዎች ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክር ይሆናሉ። እንግዲያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለሚኖረው አርክጳ ለተባለ ወንድም የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ልብ ማለታችን ተገቢ ነው፦ “በጌታ የተቀበልከውን አገልግሎት ከፍጻሜ እንድታደርስ ለአገልግሎቱ ትኩረት መስጠትህን ቀጥል።” (ቆላ. 4:17) የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ በጥድፊያ ስሜት መስበክ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ጥሩ ግንዛቤ ይሰጠናል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አንተ ራስህ ንቁ መሆን የምትችልባቸው መንገዶች

▪ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ተጠመድ

▪ ከጨለማ ሥራዎች ራቅ

▪ በመንፈሳዊ ማንቀላፋት ያለውን አደጋ አስተውል

▪ በክልልህ ስላሉ ሰዎች ምንጊዜም አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ

▪ ለሌሎች ለመስበክ አዳዲስ ዘዴዎችን ሞክር

▪ አገልግሎትህ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አስታውስ