በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

“በቀኝህም የዘላለም ፍሥሓ አለ”

“በቀኝህም የዘላለም ፍሥሓ አለ”

ሎይስ ዲደር እንደተናገሩት

በሕይወታችሁ ውስጥ ‘ምነው እንዲህ ባላደረግሁ’ ብላችሁ የተቆጫችሁበት ወቅት አለ? በይሖዋ ቀኝ ሆኜ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍኳቸውን 50 ዓመታት መለስ ብዬ ሳስታውስ አንድ ጊዜም ቢሆን እንደዚህ ተሰምቶኝ አያውቅም። ይህን ያልኩት ለምን እንደሆነ እስቲ ልንገራችሁ።

የተወለድኩት በ1939 ሲሆን ያደግሁት ካናዳ ውስጥ በሚገኝ ሳስካችዋን የሚባል ገጠራማ አካባቢ ነው፤ አራት እህቶችና አንድ ወንድም አለኝ። በዚህ ገላጣ አካባቢ በሚገኘው እርሻችን ያሳለፍኩት ሕይወት አስደሳች ነበር። አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችን መጥተው አባቴን አነጋገሩት፤ እኔም “አምላክ ስም አለው?” ብዬ ጠየቅኳቸው። እነሱም ከያዙት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ መዝሙር 83:18⁠ን አውጥተው ይሖዋ የሚለውን የአምላክን ስም አሳዩን። ይህም ስለ አምላክና ስለ ቃሉ ይበልጥ የማወቅ ጉጉት አሳደረብኝ።

በዚያ ወቅት በነበሩት የገጠር ትምህርት ቤቶች ውስጥ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ሁሉም ልጆች የሚማሩት አንድ ክፍል ውስጥ ነበር። እነዚህ የገበሬ ልጆች ትምህርት ቤት ለመድረስ በፈረስ ወይም በእግራቸው ብዙ ኪሎ ሜትሮች ይጓዙ ነበር። በአካባቢው የነበሩ ቤተሰቦች አስተማሪዎቻችን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ያሟሉላቸዋል። በአንድ ወቅት እኛም በተራችን ጆን ዲደር የተባለውን አዲስ አስተማሪ በቤታችን እንዲኖር ተቀብለነው ነበር።

በወቅቱ እኔ ባልገነዘበውም ይህ ወጣት አስተማሪም እንደ እኔ ለአምላክ ቃል ከፍተኛ ጉጉት ነበረው። አንድ ቀን አባቴ በወቅቱ ይደግፈው ስለነበረው የኮሚኒዝም እና የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም እያደነቅሁ ስናገር ጆን ስለሰማኝ እንዲህ አለኝ፦ “ማንም ሰው ሌሎች ሰዎችን የመግዛት መብት የለውም። ይህን የማድረግ መብት ያለው አምላክ ብቻ ነው።” ጆን ረጋ ብሎ የተናገረው ይህ ሐሳብ አስደሳች የሆኑ ብዙ ውይይቶች እንድናደርግ መንገድ ከፈተ።

ጆን የተወለደው በ1931 በመሆኑ ጦርነት ስላስከተላቸው መጥፎ ውጤቶች ብዙ ነገሮች ሰምቶ ነበር። በ1950 የኮሪያ ጦርነት ሲፈነዳ ጆን በጦርነት ስለመካፈል ምን አመለካከት እንዳላቸው የተለያዩ ቀሳውስትን ጠይቆ ነበር። ሁሉም፣ ክርስቲያኖች በጦርነት መካፈል እንደሚችሉ ነገሩት። ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮችን ተመሳሳይ ጥያቄ ሲጠይቃቸው የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ስለ ጦርነት የነበራቸውን አቋም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳዩት። ውሎ አድሮም በ1955 ጆን፣ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ እኔ ተጠመቅን። ሁለታችንም፣ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ይሖዋን በሙሉ ኃይላችን የማገልገል ፍላጎት ነበረን። (መዝ. 37:3, 4) ነሐሴ 1957 እኔና ጆን ተጋባን።

የጋብቻ በዓላችንን የምናከብርበት ዕለት አብዛኛውን ጊዜ የሚውለው ትላልቅ ስብሰባዎችን በምናደርግበት ቀን ላይ ነበር። ይህንን ዕለት ለጋብቻ ሥርዓት አክብሮት ካላቸው በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ማሳለፍ ያስደስተን ነበር። እኔና ጆን፣ በብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘነው በ1958 ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ ለመገኘት አምስት ሆነን በመኪና ከሳስካችዋን ወደ ኒው ዮርክ ሲቲ ጉዞ ጀመርን። ለአንድ ሳምንት ያህል ቀን ቀን ስንጓዝ እንውልና ማታ ላይ ድንኳን ውስጥ እንተኛ ነበር። ቤተልሔም፣ ፔንስልቬንያ ስንደርስ እዚያ ያገኘነው አንድ ወንድም ምሽቱን እሱ ቤት እንድናሳልፍ ሲጋብዘን ያልጠበቅነው ነገር በመሆኑ ምን ያህል እንደተገረምን አስቡት! ይህ ወንድም ያሳየን ደግነት ተጣጥበንና ንጹሕ ሆነን ኒው ዮርክ ሲቲ ለመድረስ አስችሎናል። ይህ ትልቅ ስብሰባ ይሖዋን ማገልገል ከፍተኛ ደስታ እንደሚያስገኝ እንድንገነዘብ አደረገን። በእርግጥም መዝሙራዊው እንዳለው “[በይሖዋ ቀኝ] የዘላለም ፍሥሓ አለ።”​—መዝ. 16:11

አቅኚነት

ይህ ከሆነ ከአንድ ዓመት በኋላ ማለትም በ1959 በሳስካችዋን በአንዲት አነስተኛ ተጎታች ቤት ውስጥ እየኖርን አቅኚ ሆነን ማገልገል ጀመርን። ገላጣ በሆነ ቦታ ላይ በሚገኝ ጉብታ ላይ ካለው ቤታችን ሆነን ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀው የሚገኙ ቦታዎችን ማየት እንችል የነበረ ሲሆን የተወሰነው አካባቢ የአገልግሎት ክልላችን ነበረ።

አንድ ቀን፣ ትኩረት የሚስብ ደብዳቤ ከቅርንጫፍ ቢሮው ደረሰን። ጆን ትራክተሩን እየጠገነ ስለነበር ደብዳቤውን ይዤ በፍጥነት ወደ እሱ ሄድኩ። ደብዳቤው በሬድ ሌክ፣ ኦንታሪዮ ልዩ አቅኚ ሆነን እንድናገለግል የሚጋብዝ ነበር። ከዚያም ቦታው የት እንደሚገኝ ለማወቅ ወዲያውኑ ካርታ ማገላበጥ ጀመርን።

የተመደብንበት ቦታ ስንደርስ ሰፋፊ ደኖችና በወርቅ ማዕድን ማውጫዎች አካባቢ የሚገኙ ትናንሽ ከተሞች ተመለከትን። ይህ ቦታ በፊት ከነበርንበት ገላጣ አካባቢ በጣም የተለየ ነበር! እዚያ የደረስን ቀን ማረፊያ ስለምናገኝበት መንገድ ከአንዲት ሴት ጋር ስንነጋገር የሴትየዋ ጎረቤት የሆነች አንዲት ትንሽ ልጅ ሰማችን። ይህች ልጅ እየሮጠች ወደ ቤቷ ሄዳ ጉዳዩን ለእናቷ ነገረቻት። እናትየውም እሷ ቤት እንድናድር ጋበዘችን። ያደርንበት ክፍል የሚገኘው ምድር ቤት ውስጥ ሲሆን ግድግዳው በጭቃ የተለሰነ፣ ወለሉም አፈር ነበር። በሚቀጥለው ቀን ባለ ሁለት ክፍል የእንጨት ቤት አገኘን፤ ክፍሉ ቤቱን ለማሞቅ ከሚያገለግለው ከብረት የተሠራ የእንጨት ምድጃ በቀር የቧንቧ ውኃም ሆነ የቤት ዕቃዎች አልነበሩትም። ስለዚህ ያገለገሉ ዕቃዎች ከሚሸጡበት ሱቅ የተወሰኑ ዕቃዎችን ገዛዛን፤ ቤቱ የተሟላ ዕቃ ባይኖረውም ለእኛ በቂ ነበር።

ለተመደብንበት ቦታ ቅርብ የሚባለው ጉባኤ የሚገኘው ከ200 ኪሎ ሜትር በሚበልጥ ርቀት ላይ ነበር። በወርቅ ማዕድን ማውጫ ቦታው ይሠሩ የነበሩት በርካታ ሠራተኞች የመጡት ከአውሮፓ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን በቋንቋቸው እንድናመጣላቸው ጠየቁን። በአጭር ጊዜ ውስጥ 30 የሚሆኑ ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን አገኘን። ከስድስት ወር በኋላ ደግሞ አንድ ትንሽ ጉባኤ ተቋቋመ።

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረች የአንዲት ሴት ባል፣ ሚስቱን እንዲመክርለት የቤተ ክርስቲያኑን ቄስ ደውሎ ጠራው። ቄሱ ሲመጣ ማስተማር ከሚገባን ነገሮች አንዱ የሥላሴ ትምህርት መሆን እንዳለበት ተናገረ። በዚህ ጊዜ ሴትየዋ የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ካመጣች በኋላ ለተናገራቸው ነገሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማስረጃ እንዲያቀርብ ቄሱን ጠየቀችው። ቄሱ ምንም ዓይነት ማስረጃ ማቅረብ እንደማያስፈልገው በመናገር መጽሐፍ ቅዱሱን ጠረጴዛው ላይ ወረወረው። ቄሱ ሲወጣ ከቤታቸው እንዲያባርሩንና ሁለተኛም እንዳያስገቡን በዩክሬን ቋንቋ ለባልና ሚስቱ ነገራቸው። ይህ ቄስ፣ ጆን የዩክሬን ቋንቋ ይሰማል ብሎ አልገመተም ነበር!

ብዙም ሳይቆይ፣ ጆን ለወረዳ ሥራ ሥልጠና መውሰድ ስለነበረበት ሬድ ሌክን ለቀን ሄድን። ይሁንና ከአንድ ዓመት በኋላ ጆን አውራጃ ስብሰባ ላይ የጥምቀት ንግግር ሲሰጥ ከጥምቀት እጩዎቹ መካከል የዚህችን ሴት ባል ተመለከተ! ከቄሱ ጋር ያደረግነው ውይይት ይህ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲመረምር አነሳስቶት ነበር።

በወረዳ ሥራ መጠመድ

በወረዳ ሥራ ላይ ሳለን የተለያዩ ቤተሰቦች ጋ የማረፍ ለየት ያለ አጋጣሚ ነበረን። በዚህ ወቅት በቤታቸው እንድንሰነብት ከፈቀዱልን ወንድሞች ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መሥርተናል። በአንድ ወቅት ያረፍነው ፎቅ ላይ በሚገኝ ክፍል ውስጥ ነበር፤ ክፍሉ ማሞቂያ ስላልነበረው በቅዝቃዜው ወቅት አረጋዊቷ እህት ማለዳ ላይ ቀስ ብለው ወደ ክፍላችን ይገቡና ትንሿ ምድጃ ላይ እሳት ያቀጣጥላሉ። ብዙም ሳይቆይ የምንታጠብበት ሙቅ ውኃና ማስታጠቢያ ሳህን ይዘው ይመጣሉ። እኚህ ረጋ ያሉ እህት ካሳዩን ደግነት ብዙ ተምሬያለሁ።

የወረዳ ሥራ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድቀርብ ረድቶኛል። አልበርታ ውስጥ ካሉት ወረዳዎች አንዱ፣ አንዲት እህት የምትኖርበትን በስተሰሜን ርቆ የሚገኝ የማዕድን ማውጫ ከተማ ያጠቃልል ነበር። የይሖዋ ድርጅት በገለልተኛ ክልል የምትኖረውን ይህች እህት ለመርዳት ምን ዝግጅት አደረገ? በትላልቅ ከተሞች ለሚገኙ ጉባኤዎች እንደምናደርገው ሁሉ ለአንድ ሳምንት ከእሷ ጋር ለማገልገልና ስብሰባ ለማድረግ በየስድስት ወሩ እሷ ወዳለችበት ቦታ በአውሮፕላን እንሄድ ነበር። ይህ ይሖዋ በመንጋው ውስጥ ለሚገኝ ለእያንዳንዱ በግ የሚያደርገውን ፍቅራዊ እንክብካቤ የሚያሳይ ዝግጅት ነበር።

በቤታቸው ካሳረፉን ብዙ ወንድሞች ጋር ያለን ግንኙነት አይቋረጥም ነበር። ከእነዚህ ወዳጆቻችን ጋር ደብዳቤ መጻጻፍ ያስደስተን ነበር። ለወንድሞቻችን ደብዳቤ ስጽፍ የደብዳቤ መጻፊያ ወረቀቶችን በያዘ አንድ ሣጥን እጠቀማለሁ፤ ይህ ሣጥን ጆን መጀመሪያ ከሰጠኝ ስጦታዎች አንዱ ነው። የሚያምር ቀለም ያለውን ይህን ሣጥን አሁንም ድረስ እንደ ውድ ስጦታ አድርጌ እመለከተዋለሁ።

ቶሮንቶ በሚገኝ አንድ ወረዳ እያገለገልን እያለ አንድ ወንድም ከካናዳ ቅርንጫፍ ቢሮ ደውሎ ቤቴል ገብተን ማገልገል እንችል እንደሆነ ጠየቀን። መልሱን ከቻልን በሚቀጥለው ቀን እንድናሳውቀው ነገረን። እኛም ፈቃደኞች መሆናችንን በማግስቱ ገለጽንለት።

የቤቴል አገልግሎት

በተለያዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች መካፈላችን ከይሖዋ እጅ የሚገኘውን ፍስሃ በተለያየ መንገድ ለማጣጣም አስችሎናል። በ1977 ወደ ቤቴል ስንገባም ተመሳሳይ ነገር አጋጥሞናል። ከአንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር ወዳጅነት መመሥረታችን የተለያየ ባሕርይ እንዳላቸው ለማስተዋል ያስቻለን ከመሆኑም ሌላ ለአምላክ ቃል ምን ያህል ጥልቅ አክብሮት እንዳላቸው ተገንዝበናል።

የቤቴል ሕይወትም የራሱ የሆኑ ጥሩ ነገሮች ነበሩት። ለምሳሌ ያህል፣ ልብሳችንን እንደ ድሮው በሻንጣ መያዛችን ቀርቶ የልብስ መሳቢያ ውስጥ ማስቀመጥ ችለናል፤ እንዲሁም አንድ ጉባኤ ውስጥ በቋሚነት ተመደብን እናገለግል ነበር። በቤቴል ከተሰጠኝ የሥራ ምድብ ሌላ ቤቴልን ማስጎብኘት የምወደው ሥራ ነበር። ለሚጎበኙት ወንድሞች በቤቴል የሚከናወነውን ሥራ ማብራራት፣ የእነሱን አስተያየት መስማትና ለጥያቄዎቻቸው መልስ መስጠት ሁልጊዜ ያስደስተኝ ነበር።

በዚህ ሁኔታ ዓመታቱ ሳናውቀው ነጎዱ፤ በ1997 ጆን ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት በሚሰጠው ሥልጠና እንዲካፈል ወደ ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ ተጠራ። ከዚያ በኋላ ዩክሬን ሄደን ማገልገል እንችል እንደሆነ ተጠየቅን። ጉዳዩን በጸሎት በደንብ እንድናስብበትም ተበረታትተን ነበር። ወደ ዩክሬን ለመሄድ በዚያኑ ምሽት ወሰንን።

ዩክሬን​ሌላ ለውጥ

በ1992 በሴንት ፒተርስበርግ፣ ሩሲያ እንዲሁም በ1993 በኪየቭ፣ ዩክሬን በተደረጉት ትላልቅ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተን ነበር። ይህም በምሥራቅ አውሮፓ የሚገኙ ወንድሞቻችንን የበለጠ እንድንወዳቸው አድርጎናል። በለቪፍ፣ ዩክሬን የምንኖረው በአንድ የድሮ ቤት ሁለተኛ ፎቅ ላይ ነበር። መስኮታችንን ስንከፍት ደጃችን ላይ ትንሽ የአትክልት ቦታና ዶሮዎች ስለሚታዩን በሳስካችዋን ባለው እርሻችን ላይ ያለሁ ያህል ሆኖ ይሰማኝ ነበር። እዚህ ቤት ውስጥ የምንኖረው አሥራ ሁለት ስንሆን በሥራ ገበታችን ላይ ለመገኘት በማለዳ ተነስተን ወደ ቤቴል በመኪና እንሄድ ነበር።

በዩክሬን ማገልገል ምን ይመስላል? የተለያዩ ፈተናዎችና እስራት ቢደርስባቸውም እንዲሁም እገዳ ቢጣልባቸውም ይህን ሁሉ በጽናት ካሳለፉና ጠንካራ እምነት ካሳዩ በርካታ ወንድሞች ጋር መኖራችን በትሕትና እንድንመላለስ አድርጎናል። እነዚህ ወንድሞች እንደምናደንቃቸው ስንገልጽላቸው “ይህን ያደረግነው ለይሖዋ ነው” ብለው ይመልሱልን ነበር። ይሖዋ ምንጊዜም ከእነሱ ጋር እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። እስካሁንም ድረስ አንድን ወንድም ላሳያችሁ ደግነት ስታመሰግኑት “ይሖዋን አመስግን” ብሎ ይመልስላችኋል፤ በዚህ መንገድ የጥሩ ነገሮች ሁሉ ምንጭ ይሖዋ መሆኑን ይገልጻል።

በዩክሬን የሚገኙ በርካታ ወንድሞች እርስ በርስ ለመጨዋወትና ለመተናነጽ የሚያስችል ጊዜ እንዲያገኙ ሲሉ ወደ ስብሰባ የሚሄዱት በእግራቸው ነው። አንዳንድ ጊዜ ጉዞው አንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ሊፈጅ ይችላል። ለቪፍ ውስጥ ከ50 በላይ ጉባኤዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ጉባኤዎች መካከል ሃያ አንዱ የሚሰበሰቡት በርካታ የመንግሥት አዳራሾች በሚገኙበት ሕንፃ ላይ ነው። እሁድ እሁድ የተለያዩ ጉባኤዎች ወንድሞች ወደ እነዚህ አዳራሾች ሲጎርፉ መመልከት በጣም ያስደስታል።

ወንድሞች ደጎችና ሌሎችን ለመርዳት የሚጥሩ ስለነበሩ ከእነሱ ጋር ለመቀራረብ ጊዜ አልፈጀብንም። ቋንቋውን መረዳት አሁንም ቢሆን የሚያስቸግረኝ ሲሆን በዚህ ጊዜ ወንድሞች በትዕግሥት ይረዱኛል። ፊታቸው ላይ የሚነበበው ስሜት እንኳ ብዙ ሐሳብ ያስተላልፋል።

በ2003 ኪየቭ ውስጥ በተደረገ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የገጠመኝን በወንድሞቻችን መካከል የሚታየውን እርስ በርስ የመተማመን ስሜት የሚያሳይ አንድ ተሞክሮ ልንገራችሁ። በሕዝብ በተጨናነቀ ባቡር ጣቢያ ቆመን ሳለን አንዲት ትንሽ ልጅ መጥታ “ከአያቴ ጋር ተጠፋፋን፤ ላገኛት አልቻልኩም” በማለት ነገረችን። ልጅቷ ደረታችን ላይ ያደረግነውን የስብሰባ ባጅ ስላየች የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን አውቃ ነበር። መጥፋቷን የነገረችን ብዙም ሳትሸበር ወይም ሳታለቅስ ነበር። ከእኛ ጋር የነበረች የወረዳ የበላይ ተመልካች ሚስት ጠፍተው የተገኙ ነገሮች ወደሚቀመጡበት ክፍል ልጅቷን ይዛት ሄደች። ብዙም ሳይቆይ ልጅቷ ከአያቷ ጋር ተገናኘች። ይህች ትንሽ ልጅ የጠፋችው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ቢሆንም የነበራት የመተማመን ስሜት ልቤን ነካው።

ግንቦት 2001 አዲሱ ቅርንጫፍ ቢሯችን ሲወሰን ወንድሞች ከበርካታ አገሮች ወደ ዩክሬን መጥተው ነበር። እሁድ ጠዋት በአንድ ስታዲየም ውስጥ ከቀረበው ልዩ ንግግር በኋላ አዲሱን ቤቴል ለመጎብኘት የመጡት ወንድሞች መንገዱን አጥለቅልቀውት ነበር። ይህ አጋጣሚ ፈጽሞ ከአእምሮዬ የማይጠፋ ትዝታ ጥሎብኛል! ሥርዓት በሰፈነበትና በተረጋጋ ሁኔታ ይጎበኙ የነበሩትን እነዚህ ወንድሞች ማየት ደስ የሚል ስሜት ይፈጥራል። ይህ ሁኔታ ይሖዋን ማገልገል የሚያስገኘውን ፍስሃ ይበልጥ እንድገነዘብ አድርጎኛል።

ከባድ ለውጥ

በ2004 አንድ የሚያሳዝን ነገር ገጠመን፤ ጆን ካንሰር እንዳለበት ታወቀ። በመሆኑም ለሕክምና ወደ ካናዳ ሄድን። ጆን የወሰደው የመጀመሪያው የኬሞቴራፒ ሕክምና በጣም ስላዳከመው ልዩ የሕክምና ክትትል በሚደረግበት ክፍል ውስጥ ለተወሰኑ ሳምንታት መቆየት አስፈልጎት ነበር። ደስ የሚለው ነገር ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ራሱን አወቀ። በዚህ ወቅት ጆን የመናገር ችሎታውን ያጣ ቢሆንም መጥተው ለሚጠይቁት ሰዎች የነበረውን የአመስጋኝነት ስሜት ከዓይኖቹ ማየት ይቻል ነበር።

ነገር ግን ጆን ካጋጠመው ሕመም ሙሉ በሙሉ ማገገም ስላልቻለ በዚያው ዓመት በኅዳር ወር ላይ በሞት አንቀላፋ። እኔና ጆን አብረን ይሖዋን በማገልገላችን በጣም ደስተኞች ነበርን። በመሆኑም እሱን በሞት ማጣቴ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል። ‘ታዲያ አሁን ምን ማድረግ ይሻለኛል?’ የሚል ጥያቄ ተደቀነብኝ። ወደ ዩክሬን ለመመለስ የወሰንኩ ሲሆን በዚያም የቤቴል ቤተሰብ አባላትና በዚያ ባለው ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞች ላሳዩኝ ልባዊ ፍቅር አመስጋኝ ነኝ።

በሕይወታችን ውስጥ ባደረግናቸው ምርጫዎች አንድም ቀን ተቆጭተን አናውቅም። አስደሳች ሕይወት ያሳለፍን ሲሆን ጥሩ ወዳጆችም አፍርተናል። ስለ ይሖዋ ጥሩነት ገና የምንማራቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ አውቃለሁ፤ በእርግጥም ‘በይሖዋ ቀኝ ፍሥሓ’ ስላገኘሁ እሱን ለዘላለም እያገለገልኩ እንደምቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በሕይወታችን ውስጥ ባደረግናቸው ምርጫዎች አንድም ቀን ተቆጭተን አናውቅም”

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከጆን ጋር የተጋባን ዕለት

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሬድ ሌክ፣ ኦንታሪዮ ልዩ አቅኚ ሆኜ ሳገለግል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ2002 በዩክሬን ከጆን ጋር