በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በኋላችሁ ያሉትን ነገሮች’ አትመልከቱ

‘በኋላችሁ ያሉትን ነገሮች’ አትመልከቱ

‘በኋላችሁ ያሉትን ነገሮች’ አትመልከቱ

“ዕርፍ ጨብጦ በኋላው ያሉትን ነገሮች የሚመለከት ሰው ለአምላክ መንግሥት የሚገባ አይደለም።”​—ሉቃስ 9:62

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

‘የሎጥን ሚስት ማስታወስ’ ያለብን ለምንድን ነው?

ልናሰላስልባቸው የማይገቡ ሦስት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

ከይሖዋ ድርጅት እኩል መጓዝ የምንችለው እንዴት ነው?

1. ኢየሱስ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር? የትኛው ጥያቄስ ይነሳል?

“የሎጥን ሚስት አስታውሱ።” (ሉቃስ 17:32) ኢየሱስ ክርስቶስ ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት የሰጠው ይህ ከባድ ማስጠንቀቂያ ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ለመሆኑ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነው? አይሁዳዊ የነበሩት አድማጮቹ ኢየሱስ ምን ለማለት እንደፈለገ ገብቷቸው እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። የሎጥ ሚስት የደረሰባትን ነገር አሳምረው ያውቁ ነበር። እሷና ቤተሰቧ ከሰዶም እየሸሹ ሳለ የተነገራትን ማስጠንቀቂያ ባለመስማት ወደኋላ ተመለከተች፤ በዚህም የተነሳ የጨው ዓምድ ሆና ቀረች።​—ዘፍጥረት 19:17, 26ን አንብብ።

2. የሎጥ ሚስት ወደኋላ የተመለከተችው ለምንድን ነው? ታዛዥ አለመሆኗ ምን አስከተለባት?

2 ለመሆኑ የሎጥ ሚስት ወደኋላ የተመለከተችው ለምንድን ነው? ምን እየተከናወነ እንዳለ ለማወቅ ፈልጋ ይሆን? ወይም ደግሞ ከተማዋ ስለመጥፋቷ ተጠራጥራ ምናልባትም እምነት ጎድሏት ይሆን? ወይስ በሰዶም ትታው የመጣችው ነገር አሳስቷት? (ሉቃስ 17:31) ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ታዛዥ አለመሆኗ ሕይወቷን አሳጥቷታል። እስቲ አስበው! የሎጥ ሚስት የሞተችው ምግባረ ብልሹ የሆኑት የሰዶሞና የገሞራ ነዋሪዎች በጠፉበት በዚያው ዕለት ነው። በመሆኑም ኢየሱስ “የሎጥን ሚስት አስታውሱ” ማለቱ ምንም አያስገርምም!

3. ኢየሱስ በምሳሌያዊ ሁኔታ ወደኋላ መመልከት እንደሌለብን ያጎላው እንዴት ነው?

3 እኛም ቢሆን በምሳሌያዊ ሁኔታ ወደኋላ መመልከት የለብንም። ኢየሱስ የእሱ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት ቤተሰቡን ተሰናብቶ እንዲመጣ ለጠየቀው ሰው መልስ በሰጠበት ወቅት ይህን ሐሳብ ጎላ አድርጎ ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “ዕርፍ ጨብጦ በኋላው ያሉትን ነገሮች የሚመለከት ሰው ለአምላክ መንግሥት የሚገባ አይደለም።” (ሉቃስ 9:62) ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት መልስ መስጠቱ ከሚገባው በላይ ጥብቅ እንደሆነ ወይም ምክንያታዊነት እንደጎደለው የሚያሳይ ነው? በፍጹም፣ ሰውየው ጥያቄውን ያቀረበው ከኃላፊነት ለመሸሽ እንደሆነ አውቆ ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱ “ዛሬ ነገ” የማለት ዝንባሌ ‘በኋላችን ያሉትን ነገሮች ከመመልከት’ ተለይቶ እንደማይታይ ገልጿል። እያረሰ ያለ አንድ ሰው ወደኋላ ለመመልከት ሲል ለአንድ አፍታ ዞር ቢል ወይም ዕርፉን አስቀምጦ ሙሉ በሙሉ ወደኋላ ቢዞር ችግር አለው? ወደኋላ የተመለከተው እንዴትም ይሁን ሰውየው ከዋነኛው ሥራው ተዘናግቷል፤ ይህ ደግሞ በሥራው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል።

4. ትኩረት ማድረግ ያለብን በምን ላይ ነው?

4 ትኩረታችን ማረፍ ያለበት ባለፉት ነገሮች ላይ ሳይሆን ከፊታችን ባሉት ነገሮች ላይ ነው። ይህ ሁኔታ በ⁠ምሳሌ 4:25 ላይ እንዴት በግልጽ እንደተቀመጠ ልብ በል፦ “ዐይኖችህ በቀጥታ ይመልከቱ፤ ትክ ብለህም ፊት ለፊት እይ።”

5. በኋላችን ያሉትን ነገሮች እንዳንመለከት የሚያደርገን ምን ምክንያት አለን?

5 በኋላችን ያሉትን ነገሮች እንዳንመለከት የሚያደርገን በቂ ምክንያት አለን። ይህ ምክንያት ምንድን ነው? የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ በመሆኑ ነው። (2 ጢሞ. 3:1) ከፊታችን የሚመጣው ጥፋት የሚነካው ሁለት ከተሞችን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም ነው። ታዲያ በሎጥ ሚስት ላይ የደረሰው ነገር እንዳይደርስብን ምን ሊረዳን ይችላል? በቅድሚያ፣ ዞር ብለን ለመመልከት ከሚፈትኑን በኋላችን ካሉ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል። (2 ቆሮ. 2:11) እንግዲያው እነዚህ ነገሮች ምን እንደሆኑ እንዲሁም በእነሱ ላይ ከማተኮር መቆጠብ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመርምር።

ቀደም ሲል ያሳለፍነው ጊዜ የተሻለ እንደነበር ማሰብ

6. ስላለፉት ጊዜያት የምናስበው ነገር ሁልጊዜ ትክክል ላይሆን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

6 ሊያጋጥሙን ከሚችሉ አደገኛ ሁኔታዎች አንዱ ቀደም ሲል ያሳለፍነው ጊዜ የተሻለ እንደነበር ማሰብ ነው። ስላለፉት ጊዜያት የምናስበው ነገር ሁልጊዜ ትክክል ላይሆን ይችላል። ምናልባት ሳይታወቀን፣ ከዚህ በፊት የነበሩብንን ችግሮች አቃለን ልናይና በወቅቱ የነበረንን ደስታ አጋነን ልንመለከት እንችላለን፤ በዚህም የተነሳ ያለፈው ጊዜ በጣም የተሻለ እንደነበር አድርገን ልናስብ እንችላለን። እንዲህ ያለው የተዛባ አመለካከት ቀደም ሲል ያሳለፍናቸውን ጊዜያት እንድንናፍቅ ሊያደርገን ይችላል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል፦ “አንተም፣ ‘ከእነዚህ ቀናት የቀድሞዎቹ ለምን ተሻሉ?’ አትበል፤ እንዲህ ያሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ጠቢብነት አይደለምና።” (መክ. 7:10) እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

7-9. (ሀ) እስራኤላውያን በግብፅ ምድር እያሉ ምን ደረሰባቸው? (ለ) እስራኤላውያን እንዲደሰቱ የሚያደርጓቸው ምን ምክንያቶች ነበሩ? (ሐ) እስራኤላውያን መነጫነጭና ማጉረምረም የጀመሩት በምን ምክንያት ነው?

7 እስቲ በሙሴ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንመልከት። በመጀመሪያ ላይ እስራኤላውያን በግብፅ ምድር እንደ እንግዳ ታይተው ጥሩ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር፤ ሆኖም ዮሴፍ ከሞተ በኋላ ግብፃውያን እነሱን “እያስጨነቁ የግዳጅ ሥራ የሚያሠሯቸውን አሠሪ አለቆች ሾሙባቸው።” (ዘፀ. 1:11) ፈርዖን ቁጥራቸው እንዳይጨምር ለመከላከል ሲል በአምላክ ሕዝቦች ላይ ከዘር ማጣፋት ዘመቻ የማይተናነስ ድርጊት ፈጸመ። (ዘፀ. 1:15, 16, 22) በመሆኑም ይሖዋ ለሙሴ እንደሚከተለው ብሎ መናገሩ ምንም አያስገርምም፦ “በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ።”​—ዘፀ. 3:7

8 እስራኤላውያን በባርነት ይኖሩበት የነበረውን የግብፅን ምድር ለቀው ሲወጡ ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ? ይሖዋ በትዕቢተኛው ፈርዖንና በሕዝቡ ላይ አሥር መቅሰፍቶችን በማምጣት ኃይሉን በሚያስደንቅ መንገድ ሲገልጥ ለመመልከት ችለዋል። (ዘፀአት 6:1, 6, 7ን አንብብ።) እንዲያውም ግብፃውያን እስራኤላውያንን ነፃ ከመልቀቅ አልፈው አገራቸውን ለቀው እንዲወጡላቸው አቻኮሏቸው፤ እንዲሁም “የግብፃውያንን ንብረት በዝብዘው ወሰዱ” እስኪባል ድረስ እጅግ ብዙ ወርቅና ብር ሰጧቸው። (ዘፀ. 12:33-36) በተጨማሪም እስራኤላውያን፣ ፈርዖንና ሠራዊቱ በቀይ ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሲጠፉ በመመልከታቸው ደስታቸው እጥፍ ድርብ ሆነ። (ዘፀ. 14:30, 31) እንዲህ ያሉ አስደናቂ ነገሮች ሲከናወኑ መመልከት እንዴት እምነትን የሚያጠናክር ነው!

9 የሚገርመው ነገር የይሖዋን እጅ ያዩት እነዚህ ሰዎች በተአምራዊ ሁኔታ ነፃ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ መነጫነጭና ማጉረምረም ጀመሩ። በምን ምክንያት? በምግብ! ይሖዋ በሰጣቸው ነገር ስላልረኩ እንዲህ በማለት አማረሩ፦ “በግብፅ ያለምንም ዋጋ የበላነው ዓሣ እንዲሁም ዱባው፣ በጢኹ፣ ኵራቱ፣ ነጭ ሽንኩርቱ ትዝ ይለናል። አሁን ግን የምግብ ፍላጎታችን ጠፍቶአል፤ ከዚህ መና በስተቀር የምናየው የለም!” (ዘኍ. 11:5, 6) በእርግጥም፣ እስራኤላውያን አመለካከታቸው ተዛብቶ ነበር፤ በዚህም የተነሳ በባርነት ወደኖሩበት ምድር ለመመለስ እስከመመኘት ደርሰው ነበር! (ዘኍ. 14:2-4) በኋላቸው ያሉትን ነገሮች በመመልከታቸው የይሖዋን ሞገስ አጡ።​—ዘኍ. 11:10

10. ከእስራኤላውያን ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?

10 ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? ችግሮችና መከራዎች ሲያጋጥሙን፣ ቀደም ሲል ስለነበሩን ጥሩ መስለው የሚታዩ ነገሮች ማብሰልሰል ምናልባትም እውነትን ከማወቃችን በፊት ስለነበረን ሕይወት ማውጠንጠን የለብንም። ካሳለፍነው ሕይወት ስለምናገኛቸው ትምህርቶች ማሰላሰላችን ወይም ስላሉን ጥሩ ትዝታዎች ማሰባችን ስህተት ባይሆንም ስላለፈው ጊዜ ሚዛናዊና ከእውነታው ያልራቀ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። አለበለዚያ፣ አሁን ባሉን ነገሮች ያለመርካት ስሜታችን እያደገ በመሄድ ወደ ቀድሞ አኗኗራችን ለመመለስ ልንፈተን እንችላለን።​—2 ጴጥሮስ 2:20-22ን አንብብ።

ቀደም ሲል የከፈልናቸው መሥዋዕቶች

11. አንዳንዶች ከዚህ በፊት የከፈሏቸውን መሥዋዕቶች እንዴት ይመለከቷቸዋል?

11 አንዳንዶች ከዚህ በፊት የከፈሏቸውን መሥዋዕቶች ወደኋላ በመመልከት በውሳኔያቸው መቆጨታቸው የሚያሳዝን ነው። ምናልባትም ከፍተኛ ትምህርት የመከታተል፣ ትልቅ ቦታ የመድረስ ወይም የተደላደለ ሕይወት የመምራት አጋጣሚህን መሥዋዕት አድርገህ ይሆናል። በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በንግዱ፣ በመዝናኛው፣ በትምህርቱ ወይም በስፖርቱ ዓለም ትልቅ ደረጃ ላይ በመድረስ ጥሩ ገቢ ማግኘት ሲችሉ ይህን አጋጣሚ ትተዋል። ይህን እርምጃ ከወሰዱ ረዘም ያለ ጊዜ ቢያልፍም መጨረሻው እስካሁን አልመጣም። ታዲያ እነዚህን መሥዋዕቶች ባትከፍል ኖሮ ምን ዓይነት ሕይወት ልትመራ ትችል እንደነበር በማሰብ ትቆጫለህ?

12. ጳውሎስ ወደኋላ ስለተዋቸው ነገሮች ምን ተሰምቶት ነበር?

12 ሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን ሲል ብዙ ነገሮችን ትቷል። (ፊልጵ. 3:4-6) ታዲያ ወደኋላው ስለተዋቸው ነገሮች ምን ተሰምቶት ነበር? “ለእኔ ትርፍ የነበረውን ነገር ሁሉ ለክርስቶስ ስል እንደ ኪሳራ ቆጥሬዋለሁ” ብሏል። እንደዚህ የተሰማው ለምንድን ነው? ቀጥሎ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ጌታዬ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ከሚገልጸው የላቀ ዋጋ ያለው እውቀት የተነሳ ሁሉንም ነገር እንደ ኪሳራ እቆጥረዋለሁ። ለእሱ ስል ሁሉንም ነገር አጥቻለሁ፤ ያጣሁትንም ነገር ሁሉ እንደ ጉድፍ እቆጥረዋለሁ፤ ይህም ክርስቶስን አገኝ ዘንድ [ነው]።” * (ፊልጵ. 3:7, 8) አንድ ሰው ቆሻሻ ወይም ጥራጊ ከደፋ በኋላ ባልጣልኩት ብሎ እንደማያዝን ሁሉ ጳውሎስም በዓለም ውስጥ ሊያገኛቸው የሚችላቸውን አጋጣሚዎች ወደኋላ በመተዉ በፍጹም አልተጸጸተም። እነዚህን አጋጣሚዎች አንዴ ከተዋቸው በኋላ፣ ዋጋ እንዳላቸው በመቁጠር እነሱን ፍለጋ አልተመለሰም።

13, 14. የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

13 እንዳመለጡን አድርገን ስለምናስባቸው አጋጣሚዎች ማውጠንጠን ጀምረን ከሆነ ምን ሊረዳን ይችላል? የጳውሎስን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል። እንዴት? አሁን ያሉህ ነገሮች ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው አስብ። ከይሖዋ ጋር ውድ የሆነ ዝምድና መሥርተሃል፤ እንዲሁም ታማኝ በመሆን ረገድ በእሱ ዘንድ ጥሩ ስም አትርፈሃል። (ዕብ. 6:10) ይህ ዓለም፣ አሁንም ሆነ ወደፊት ከምናገኛቸው መንፈሳዊ በረከቶች ጋር ሊወዳደር ቀርቶ ጫፉ ጋ እንኳ ሊደርስ የሚችል ምን ቁሳዊ ነገር ሊሰጠን ይችላል?​—ማርቆስ 10:28-30ን አንብብ።

14 በመቀጠልም ጳውሎስ ታማኝነታችንን ጠብቀን እንድንኖር የሚረዳንን ሌላ ነገር ጠቅሷል። “ከኋላዬ ያሉትን ነገሮች እየረሳሁ ከፊቴ ወዳሉት ነገሮች እንጠራራለሁ” በማለት ተናግሯል። (ፊልጵ. 3:13) ጳውሎስ አስፈላጊ የሆኑ ሁለት እርምጃዎችን ጎላ አድርጎ እንደጠቀሰ ልብ በሉ። አንደኛ፣ ስለተውናቸው ነገሮች ከመጠን በላይ በማሰብ ጉልበታችንንና ውድ ጊዜያችንን እንዳናጠፋ እነዚህን ነገሮች መርሳት ይኖርብናል። ሁለተኛ፣ ገመዱን ለመበጠስ የተቃረበ ሯጭ እንደሚያደርገው በተዘጋጀልን ነገር ላይ በማተኮር ወደፊት መዘርጋት ይኖርብናል።

15. ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በተዉት ምሳሌ ላይ ማሰላሰላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

15 የጥንቶቹም ሆኑ ዛሬ ያሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በተዉት ምሳሌ ላይ የምናሰላስል ከሆነ በኋላችን ያሉትን ነገሮች ከመመልከት ይልቅ ወደፊት ለመግፋት የሚያስችል ተጨማሪ ኃይል እናገኛለን። ለምሳሌ፣ አብርሃምና ሣራ የዑርን ከተማ ዘወትር ያስታውሱ የነበረ ቢሆን ኖሮ “መመለስ የሚችሉበት አጋጣሚ በኖራቸው ነበር።” (ዕብ. 11:13-15) ሆኖም ወደዚያ አልተመለሱም። ሙሴም ቢሆን መጀመሪያ ላይ ግብፅን ለቆ ሲወጣ የተዋቸው ነገሮች የትኛውም እስራኤላዊ ትቶት ከወጣው ነገር እጅግ የላቁ ናቸው። ሆኖም እነዚያን ነገሮች ይናፍቅ እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ ምንም ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ይላል፦ “የሚከፈለውን ወሮታ በትኩረት በመመልከቱ ቅቡዕ ሆኖ የሚደርስበት ነቀፋ በግብፅ ከሚገኝ ውድ ሀብት የላቀ እንደሆነ አስቧል።”​—ዕብ. 11:26

መጥፎ ትዝታዎች

16. መጥፎ ትዝታዎች ምን ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ይችላሉ?

16 ሁሉም ትዝታዎች ጥሩ ናቸው ማለት አይቻልም። ምናልባት ከዚህ በፊት የሠራናቸውን ኃጢአቶች ወይም ስህተቶች ነጋ ጠባ እያሰብን እንጨነቅ ይሆናል። (መዝ. 51:3) ወይም ደግሞ የተሰጠን ጠንከር ያለ ምክር ያስከተለብን የስሜት ቁስል እስካሁን አልሻረ ይሆናል። (ዕብ. 12:11) አሊያም የተፈጸመብን ወይም እንደተፈጸመብን የተሰማን የፍትሕ መጓደል አስተሳሰባችንን ተቆጣጥሮት ይሆናል። (መዝ. 55:2) ታዲያ እንዲህ በመሰሉ በኋላችን ባሉ ነገሮች ላይ እንዳናተኩር ምን ማድረግ እንችላለን? እስቲ ሦስት ምሳሌዎችን እንመልከት።

17. (ሀ) ጳውሎስ ‘ከቅዱሳን ሁሉ እንደሚያንስ’ አድርጎ ራሱን የቆጠረው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ አፍራሽ በሆኑ አስተሳሰቦች እንዳይዋጥ የጠበቀው ምንድን ነው?

17 ቀደም ሲል የሠራናቸው ስህተቶች። ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱን የሚቆጥረው ‘ከቅዱሳን ሁሉ እንደሚያንስ’ አድርጎ ነበር። (ኤፌ. 3:8) እንደዚህ የተሰማው ለምንድን ነው? “እኔ የአምላክን ጉባኤ አሳድድ [ነበር]” በማለት ምክንያቱን ተናግሯል። (1 ቆሮ. 15:9) ከዚህ በፊት ያሳድዳቸው ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹን ሲያገኛቸው ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ይሁንና ጳውሎስ እንዲህ ያሉ አፍራሽ አስተሳሰቦች አእምሮውን እንዲቆጣጠሩት አልፈቀደም፤ ከዚህ ይልቅ ትኩረቱን ከአምላክ ባገኘው ጸጋ ላይ አድርጓል። (1 ጢሞ. 1:12-16) ይህም በውስጡ የአመስጋኝነት ስሜት እንዲያድርበት በማድረግ በአገልግሎቱ እንዲቀጥል አነሳስቶታል። ጳውሎስ ለመርሳት ጥረት ከሚያደርጋቸው ነገሮች መካከል ከዚህ በፊት የፈጸማቸው የኃጢአት ድርጊቶች ይገኙበታል። እኛም ይሖዋ ባሳየን ምሕረት ላይ ትኩረት የምናደርግ ከሆነ ከዚህ በፊት የተፈጸሙ ልንለውጣቸው የማንችላቸውን ነገሮች እያነሳን አላስፈላጊ ጭንቀት ውስጥ ከመግባትና ኃይላችንን ከሟሟጠጥ እንጠበቃለን። ከዚህ ይልቅ ጉልበታችንን አምላክ የሰጠንን ሥራ ለመሥራት ልንጠቀምበት እንችላለን።

18. (ሀ) የተሰጡንን ምክሮች አስመልክቶ አሉታዊ አስተሳሰብ መያዝ ምን አደጋ አለው? (ለ) ምክር ከመቀበል ጋር በተያያዘ ሰለሞን የሰጠውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

18 ሥቃይ ያስከተለብን ምክር። ከዚህ በፊት የተሰጡንን አንዳንድ ምክሮች እያስታወስን የምንበሳጭ ቢሆንስ? እንዲህ ማድረጋችን ሥቃይ የሚያስከትልብን ከመሆኑም በላይ ቀስ በቀስ ኃይላችንን በማዳከም ‘እንድንታክት’ ሊያደርገን ይችላል። (ዕብ. 12:5) ምክሩን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆን ‘ብናቃልለው’ አሊያም መጀመሪያ ላይ ተቀብለን በኋላ ችላ በማለት ‘ብንታክት’ ዞሮ ዞሮ ለውጥ የለውም፤ ሁለቱም ቢሆኑ ከምክሩ ጥቅም ለማግኘትም ሆነ ለመሻሻል ፈቃደኞች እንዳልሆንን የሚያሳዩ ድርጊቶች ናቸው። ሰለሞን “ምክርን አጥብቀህ ያዛት፤ አትልቀቃት፤ ጠብቃት፤ ሕይወትህ ናትና” በማለት የሰጠውን ማሳሰቢያ መከተል ምንኛ የተሻለ ነው። (ምሳሌ 4:13) የመንገድ ምልክቶችን በማክበር እንደሚጓዝ አሽከርካሪ አንተም ምክርን ተቀብለህ ተግባራዊ በማድረግ ወደፊት መጓዝህን ቀጥል።​—ምሳሌ 4:26, 27፤ ዕብራውያን 12:12, 13ን አንብብ።

19. የዕንባቆምንና የኤርምያስን ዓይነት እምነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

19 የተፈጸመብን ወይም እንደተፈጸመብን የተሰማን የፍትሕ መጓደል። ነቢዩ ዕንባቆም፣ ይሖዋ ፍትሐዊ ያልሆኑ አንዳንድ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ባለመረዳቱ ፍትሕን እንዲያሰፍን ወደ አምላክ ጮኾ ነበር፤ እኛም እንደዚህ ነቢይ የሚሰማን ጊዜ ሊኖር ይችላል። (ዕን. 1:2, 3) በዚህ ጊዜ ይህ ነቢይ የነበረው ዓይነት እምነት ማሳየታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው፤ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በድነቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።” (ዕን. 3:18) በተጨማሪም በጥንት ዘመን እንደኖረው እንደ ኤርምያስ ሁሉ እኛም የፍትሕ አምላክ በሆነው በይሖዋ ላይ እምነት በመጣል ምንጊዜም እሱን ‘በትዕግሥት የምንጠባበቅ’ (NW) ከሆነ ሁሉም ነገር በተገቢው ጊዜ እንደሚስተካከል እርግጠኞች እንሆናለን።​—ሰቆ. 3:19-24

20. ‘የሎጥን ሚስት እንደምናስታውስ’ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

20 በዚህ ዘመን በመኖራችን ደስተኞች ነን። ምክንያቱም በጊዜያችን በጣም አስገራሚ የሆኑ ነገሮች እየተከናወኑ ነው፤ በቅርቡ እንደሚፈጸሙ የምንጠብቃቸው ሌሎች ነገሮችም አሉ። በመሆኑም ሁላችንም ከይሖዋ ድርጅት እኩል መጓዛችንን እንቀጥል። በኋላችን ያሉትን ነገሮች ትተን ትኩረታችንን ከፊታችን ባሉት ነገሮች ላይ እንድናደርግ የተሰጠንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማሳሰቢያ እንከተል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ‘የሎጥን ሚስት እንደምናስታውስ’ እናሳያለን!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 “ጉድፍ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ለውሾች የሚሰጥ” ነገር፣ “አዛባ” እና “ዓይነ ምድር” የሚል ትርጉምም አለው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደተናገሩት ጳውሎስ ይህን ቃል የተጠቀመበት “ከማይረባ እንዲሁም ከሚያጸይፍ ነገር መሸሽን እንዲሁም ወደዚያ ነገር ድርሽ አለማለትን” ለማመልከት ነው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]