በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ፎቶ ልታነሳን ትችላለህ?”

“ፎቶ ልታነሳን ትችላለህ?”

“ፎቶ ልታነሳን ትችላለህ?”

በሜክሲኮ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግል ሆስዌ የተባለ ቤቴላዊ፣ የአንድ አውራጃ ስብሰባ ሁለተኛ ቀን ካለቀ በኋላ ከሬታሮ የምትባለውን የሜክሲኮ ከተማ እየጎበኘ ነበር። ሆስዌ ከተማዋን እየጎበኘ እያለ ሃቭዬር እና ማሩ የተባሉ ከኮሎምቢያ የመጡ ባልና ሚስት ቱሪስቶች ፎቶ እንዲያነሳቸው ጠየቁት። የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት ሆስዌና ጓደኞቹ ጥሩ አለባበስ የነበራቸው ሲሆን የስብሰባውን ባጅ ደረታቸው ላይ አድርገው ነበር፤ ይህን ያስተዋሉት ባልና ሚስት፣ ሆስዌና ጓደኞቹን ከምረቃ ሥነ ሥርዓት ወይም ከሌላ ልዩ ዝግጅት እየተመለሱ እንደሆነ ጠየቋቸው። ሆስዌ እሱም ሆነ ጓደኞቹ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ እየተካፈሉ እንደሆነ ከገለጸላቸው በኋላ ባልና ሚስቱን በእሁዱ ቀን ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ጋበዛቸው።

ሃቭዬር እና ማሩ ለዚህ ዓይነት ዝግጅት የሚሆን ተገቢ ልብስ ስለሌላቸው በስብሰባው ላይ መገኘት እንደሚያሳፍራቸው ገለጹ። ያም ቢሆን ሆስዌ ስሙንና የሚሠራበትን ቅርንጫፍ ቢሮ ስልክ ቁጥር ሰጣቸው።

የሚገርመው ነገር፣ ከአራት ወር በኋላ ሃቭዬር ለሆስዌ ደወለለት። ሃቭዬር፣ እሱና ባለቤቱ በአውራጃ ስብሰባው ላይ እንደተገኙና በወቅቱ ይኖሩ በነበረበት በሜክሲኮ ሲቲ የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው እንዲያነጋግሯቸው እንደሚፈልጉ ለሆስዌ ነገረው። ብዙም ሳይቆይ ሃቭዬርና ማሩ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። ከአሥር ወራት በኋላ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ሆኑ። ባልና ሚስቱ ከጊዜ በኋላ ወደ ቶሮንቶ፣ ካናዳ ቢሄዱም በመንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸውን ቀጥለው ስለነበር ተጠመቁ።

ከጊዜ በኋላ ሃቭዬር እውነትን እንዲቀበል ያነሳሳው ምን እንደሆነ የሚገልጽ ደብዳቤ ለሆስዌ ጻፈለት። “እኔና ባለቤቴ በስብሰባው ላይ ከመገኘታችን በፊት በሕይወታችን የአምላክን አመራር ማግኘት እንደሚያስፈልገን ተነጋግረን ነበር። አንተና ጓደኞችህ የነበራችሁን ጥሩ አለባበስ ስናይ በጣም ልዩ ከሆነ ስብሰባ መጥተው መሆን አለበት ብለን አሰብን። በስብሰባው ላይ የተገኘነው እንደ ቱሪስት ለብሰን ቢሆንም ምሥክሮቹ ወንበር እንድናገኝ በማድረግ ወዳጃዊ መንፈስ አሳዩን፤ ጥቅሶች ሲጠቀሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንድንከታተል ያሳዩን ነበር፤ እንዲሁም ግሩም ባሕርይ ነበራቸው። ይህ ሁሉ በጣም አስደነቀን።”

ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን የተናገራቸው ቃላት እውነት መሆናቸውን ሆስዌ ካጋጠመው ተሞክሮ ማየት እንችላለን። ሰለሞን “ጠዋት ላይ ዘርህን ዝራ፤ ማታም ላይ እጅህ ሥራ አይፍታ፤ ይህ ወይም ያ፣ ወይም ሁለቱ መልካም ይሁኑ፣ የቱ እንደሚያፈራ አታውቅምና” በማለት ጽፏል። (መክ. 11:6) አንተስ የተለያዩ አጋጣሚዎችን ተጠቅመህ በቅርቡ ስለምናደርገው ትልቅ ስብሰባ ወይም ስለሚቀርበው የሕዝብ ንግግር ለሌሎች በመናገር ዘሩን መዝራት ትችላለህ? ይሖዋ ልክ እንደ ሃቭዬርና ማሩ መንፈሳዊ መመሪያ ለማግኘት የተራቡና የተጠሙ ሰዎችን ወደ ራሱ ለመሳብ ሊጠቀምብህ ይችላል።​—ኢሳ. 55:1

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከግራ ወደ ቀኝ፦ አሌሃንድሮ ቮገላን፣ ማሩ ፒኛዳ፣ አሌሃንድሮ ፒኛዳ፣ ሃቭዬር ፒኛዳ እና ሆስዌ ራሚረስ በሜክሲኮ ቅርንጫፍ ቢሮ