በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ለሰባ ዓመታት የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ መያዝ

ለሰባ ዓመታት የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ መያዝ

ሌነርድ ስሚዝ እንደተናገሩት

በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አካባቢ እያለሁ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ልቤን ነኩኝ። ይህ ከሆነ 70 ዓመታት ቢያልፉም በ⁠ዘካርያስ 8:23 ላይ ያለውን ጥቅስ ይኸውም “የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ አጥብቀው” ስለያዙ “ዐሥር ሰዎች” የሚናገረውን ዘገባ ትርጉም የተረዳሁበትን ጊዜ ዛሬም አስታውሳለሁ። እነዚህ ሰዎች አይሁዳዊውን እንዲህ ይሉታል፦ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ።”

በዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጸው አይሁዳዊ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን፣ ‘ዐሥሩ ሰዎች’ ደግሞ “ሌሎች በጎችን” ወይም በወቅቱ “ኢዮናዳቦች” በመባል ይታወቁ የነበሩትን ሰዎች ይወክላሉ። * (ዮሐ. 10:16) ይህን እውነት ስረዳ፣ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋዬ የተመካው እነዚህን ቅቡዓን ክርስቲያኖች በታማኝነት በመደገፌ ላይ እንደሆነ ተገነዘብኩ።

በ⁠ማቴዎስ 25:31-46 ላይ የሚገኘው ስለ “በጎች” እና ስለ “ፍየሎች” የሚናገረው የኢየሱስ ምሳሌም በጣም ነካኝ። “በጎቹ፣” በምድር ላይ ለሚገኙት ቅቡዓን ክርስቲያኖች መልካም ስላደረጉ በመጨረሻ ጊዜ ጥሩ ፍርድ የሚፈረድላቸውን ሰዎች ያመለክታሉ። እኔም ወጣት የኢዮናዳብ ክፍል አባል እንደመሆኔ መጠን ለራሴ እንዲህ አልኩ፦ ‘ሌን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ በግ አድርጎ እንዲቆጥርህ ከፈለግክ የእሱ ወንድሞች የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚሰጡህን አመራር በመቀበል እነሱን መደገፍ አለብህ፤ ምክንያቱም ይሖዋ ከእነሱ ጋር ነው።’ ይህን መረዳቴ ከሰባ ለሚበልጡ ዓመታት በሕይወቴ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል።

‘የእኔስ ቦታ ምንድን ነው?’

እናቴ የተጠመቀችው በ1925 ቤቴል በሚገኘው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ነበር። ይህ አዳራሽ ለንደን ታበርናክል (የለንደኑ ቤተ መቅደስ) ተብሎ ይጠራ የነበረ ሲሆን በአካባቢው የሚገኙ ወንድሞች ለስብሰባ ይጠቀሙበት ነበር። እኔ የተወለድኩት ጥቅምት 15, 1926 ነው። የተጠመቅኩት ደግሞ መጋቢት 1940፣ በእንግሊዝ የባሕር ጠረፍ ላይ በሚገኝ ዶቨር በተባለ ከተማ ውስጥ በተደረገ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ነው። በልጅነቴ ያገኘሁት መንፈሳዊ እውቀት ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍቅር እንዲኖረኝ አድርጓል። እናቴ ቅቡዕ ክርስቲያን ስለነበረች ለመጀመሪያ ጊዜ የያዝኩት ‘የአይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ’ የእሷን ነው ማለት እችላለሁ። በወቅቱ አባቴና ታላቅ እህቴ ይሖዋን አያመልኩም ነበር። እኔና እናቴ የምንካፈለው በደቡብ ምሥራቅ እንግሊዝ በሚገኘው ጂሊንግሃም ጉባኤ ሲሆን በዚህ ጉባኤ ውስጥ በርካታ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነበሩ። እናቴ የስብከቱን ሥራ በቅንዓት በማከናወን ረገድ ጥሩ ምሳሌ ነበረች።

መስከረም 1941፣ በሌስተር ከተማ በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ “ንጹሕ አቋም” በሚል ርዕስ የቀረበው ንግግር ከአጽናፈ ዓለማዊ አገዛዝ ጋር የተያያዘውን ጉዳይ የሚያብራራ ነበር። በይሖዋና በሰይጣን መካከል የተነሳው አከራካሪ ጉዳይ እኛንም እንደሚመለከተን ለመጀመሪያ ጊዜ የተረዳሁት ይህ ንግግር በቀረበበት ወቅት ነበር። በመሆኑም ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ እንደመሆኑ መጠን ከእሱ ጎን መቆምና ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ አለብን።

በዚህ ስብሰባ ላይ ለአቅኚነት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠ ሲሆን ወጣቶች በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል ግብ እንዲያወጡ ተበረታተው ነበር። “አቅኚዎች በድርጅቱ ውስጥ ያላቸው ቦታ” በሚል ርዕስ የቀረበው ንግግር ‘የእኔስ ቦታ ምንድን ነው?’ ብዬ እንዳስብ አደረገኝ። ይህ ስብሰባ የኢዮናዳብ ክፍል አባል እንደመሆኔ መጠን አቅሜ በሚፈቅደው ሁሉ በስብከቱ ሥራ በመካፈል የቅቡዓን ክርስቲያኖችን ቡድን የመርዳት ኃላፊነት እንዳለብኝ እንድገነዘብ አደረገኝ። በመሆኑም እዚያው ሌስተር ከተማ እያለሁ የአቅኚነት ማመልከቻ ፎርም ሞላሁ።

በጦርነቱ ወቅት በአቅኚነት ማገልገል

ታኅሣሥ 1, 1941 ማለትም የ15 ዓመት ልጅ እያለሁ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። የመጀመሪያዋ አቅኚ የአገልግሎት ጓደኛዬ እናቴ ነበረች፤ ሆኖም ከአንድ ዓመት በኋላ በጤና ምክንያት የአቅኚነት አገልግሎቷን ለማቋረጥ ተገደደች። በመሆኑም የለንደን ቅርንጫፍ ቢሮ በአሁኑ ወቅት የፖርቶ ሪኮ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሆኖ ከሚያገለግለው ራን ፓርከን ጋር አብሬ እንዳገለግል መደበኝ።

እኔና ራን በኬንት ግዛት ውስጥ በሚገኙት ብሮድስቴርዝ እና ራምስጌት በተባሉ የወደብ ከተሞች ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን፤ በዚያም አንድ ክፍል ቤት ተከራይተን መኖር ጀመርን። በዚያን ጊዜ ለልዩ አቅኚዎች ይሰጥ የነበረው የወር አበል 40 ሽልንግ (በወቅቱ 8 የአሜሪካ ዶላር አካባቢ) ነበር። በመሆኑም የቤት ኪራይ ከከፈልን በኋላ የሚቀረን ገንዘብ በጣም ትንሽ ስለሚሆን ምን በልተን እንደምናድር አናውቅም ነበር። ያም ሆኖ ይሖዋ ምንጊዜም የሚያስፈልጉንን ነገሮች ያሟላልን ነበር።

አብዛኛውን ጊዜ የምንጓዘው በብስክሌት ነበር፤ ከባድ ጭነት የተሸከሙ ብስክሌቶቻችንን በምንነዳበት ጊዜ ከሰሜን ባሕር የሚመጣውን ኃይለኛ ነፋስ ሰንጥቀን ማለፍ ይጠበቅብን ነበር። ከዚህም ሌላ የአየር ድብደባንና ለንደንን ለማጋየት የሚወነጨፉት በኬንት ግዛት ላይ ዝቅ ብለው የሚያልፉት ቪ-1 የሚባሉት የጀርመን ሚሳይሎች የሚፈጥሩትን ስጋት ችለን መኖር ነበረብን። እንዲያውም አንድ ቀን፣ አንድ ቦንብ በአናቴ ላይ አልፎ በአቅራቢያዬ ባለ መስክ ላይ በፈነዳበት ወቅት ከብስክሌቴ ዘልዬ ቦይ ውስጥ ገብቼ ነበር። ያም ሆኖ በኬንት ግዛት ውስጥ በአቅኚነት ያሳለፍናቸው ዓመታት አስደሳች ነበሩ።

“የቤቴል ልጅ” ሆንኩ

እናቴ ሁልጊዜ ስለ ቤቴል በአድናቆት ትናገር ነበር። “አንተ የቤቴል ልጅ ሆነህ ከማየት የበለጠ የምመኘው ነገር የለም” ትል ነበር። በመሆኑም ጥር 1946፣ ለንደን በሚገኘው ቤቴል ለሦስት ሳምንት እንድሠራ ግብዣ ሲቀርብልኝ ምን ያህል እንደተደሰትኩ መገመት ትችላላችሁ። ሦስት ሳምንቴን ስጨርስ በቅርንጫፍ ቢሮው የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት የሚከታተለው ፕሪስ ሂዩዝ በቤቴል በቋሚነት እንዳገለግል ጠየቀኝ። ቤቴል ውስጥ ያገኘሁት ሥልጠና በሕይወቴ ሙሉ ጠቅሞኛል።

በወቅቱ የለንደን ቤተሰብ አባላት 30 ገደማ ይሆኑ ነበር፤ አብዛኞቹ ወጣትና ነጠላ ወንድሞች ቢሆኑም በኋላ ላይ የበላይ አካል አባላት የሆኑት ፕሪስ ሂዩዝን፣ ኤድገር ክሌይን እና ጆን ባርን ጨምሮ በርካታ ቅቡዓን ወንድሞችም ነበሩ። እንደ “ዓምድ” የሚታዩት እነዚህ ወንድሞች በሚሰጡት መንፈሳዊ አመራር ሥር ሆኖ በወጣትነት ጊዜ የክርስቶስ ወንድሞችን መደገፍ መቻል እንዴት ያለ ትልቅ መብት ነው!​—ገላ. 2:9

ቤቴል በነበርኩበት ወቅት አንድ ወንድም፣ በር ላይ የቆመች አንዲት እህት እንደምትፈልገኝ ነገረኝ። የሚገርመው ነገር የፈለገችኝ እህት እናቴ ስትሆን አንድ የተጠቀለለ ነገርም ይዛ ነበር። እናቴ፣ ወደ ውስጥ መግባት ያልፈለገችው ሥራዬን ላለማስተጓጎል እንደሆነ ነገረችኝ፤ ከዚያም የያዘችውን ዕቃ ሰጥታኝ ሄደች። ያመጣችልኝ ሙቀት የሚሰጥ ካፖርት ነበር። የፍቅሯ መግለጫ የሆነው ይህ ስጦታ በማደሪያው ድንኳን ውስጥ ለሚያገለግለው ለልጇ ለሳሙኤል መደረቢያ ይዛለት ትሄድ የነበረችውን ሐናን አስታወሰኝ።​—1 ሳሙ. 2:18, 19

ጊልያድ ያሳለፍኩት ፈጽሞ የማይረሳ ጊዜ

በ1947 ከቤቴል አምስት ሰዎች ተመርጠን በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የጊልያድ ትምህርት ቤት እንድንካፈል ተጋበዝን፤ በሚቀጥለው ዓመት በ11ኛው ክፍል ገብተን ሠለጠንን። እዚያ በደረስንበት ወቅት ትምህርት ቤቱ የሚገኝበት የኒው ዮርክ ሰሜናዊ ክፍል በጣም ቀዝቃዛ ነበር። እናቴ የሰጠችኝን ሙቀት የሚሰጥ ካፖርት ይዤ መሄዴ በጣም ጠቀመኝ!

ጊልያድ ያሳለፍኳቸው ስድስት ወራት የማይረሱ ነበሩ። ከ16 አገሮች ከመጡ ሌሎች ተማሪዎች ጋር አብሬ ጊዜ ማሳለፌ የአስተሳሰብ አድማሴን አስፍቶልኛል። ከትምህርት ቤቱ ካገኘሁት ገንቢ መንፈሳዊ ትምህርት በተጨማሪ ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር የመሠረትኩት ወዳጅነትም ጠቅሞኛል። ከእነዚህም መካከል አብሮኝ በጊልያድ የተማረው ሎይድ ባሪ፣ የጊልያድ አስተማሪ የነበረው አልበርት ሽሮደር እና የይሖዋ ምሥክሮች የእርሻ ቦታ (በወቅቱ የጊልያድ ትምህርት ቤት የሚገኘው እዚህ ነበር) የበላይ ተመልካች የነበረው ጆን ቡዝ ይገኙበታል፤ ከጊዜ በኋላ ሦስቱም የበላይ አካል አባላት ሆነዋል። እነዚህ ወንድሞች የሰጡኝን ፍቅራዊ ምክር እንዲሁም ለይሖዋና ለድርጅቱ ታማኝ በመሆን ረገድ የተዉትን ግሩም ምሳሌ ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ።

የወረዳ ሥራና ወደ ቤቴል መመለስ

ከጊልያድ ከተመረቅኩ በኋላ በኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የወረዳ ሥራ እንድሠራ ተመደብኩ። በወቅቱ ገና 21 ዓመቴ ቢሆንም በትኩስ ኃይል የማከናውናቸውን ነገሮች ወንድሞች በደስታ ይቀበሉት ነበር። በዚያ ወረዳ ከነበሩትና ተሞክሮ ካካበቱት በዕድሜ የገፉ ወንድሞች ብዙ ተምሬያለሁ።

ከጥቂት ወራት በኋላ ተጨማሪ ሥልጠና ለማግኘት ወደ ብሩክሊን ቤቴል እንድመጣ ተጋበዝኩ። በዚህ ወቅት፣ እንደ ዓምድ ከሚታዩት ከሚልተን ሄንሼል፣ ከካርል ክላይን፣ ከናታን ኖር፣ ከቶማስ ሱሊቫን እና ከላይመን ስዊንግል ጋር በደንብ የመተዋወቅ አጋጣሚ አግኝቻለሁ፤ ሁሉም በአንድ ወቅት የበላይ አካል አባላት በመሆን አገልግለዋል። እነዚህ ወንድሞች ሥራቸውን ሲያከናውኑ በማየትና ክርስቲያናዊ ሕይወታቸውን በመመልከት ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ። ይህም በይሖዋ ድርጅት ላይ የነበረኝ እምነት በእጅጉ እንዲጨምር አድርጓል። ከዚህ በኋላ ተመልሼ በአውሮፓ እንዳገለግል ተመደብኩ።

እናቴ የካቲት 1950 ሞተች። ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ በኋላ ከአባቴና ከእህቴ ከዶረ ጋር በግልጽ ተወያየን። አሁን እናቴ ስለሞተች እኔም አብሬያቸው ስለማልኖር መንፈሳዊነታቸውን በተመለከተ ምን እንዳሰቡ ጠየቅኳቸው። እነሱም በጣም ከሚያከብሩት ሃሪ ብራውኒንግ ከሚባል በዕድሜ የገፋ ቅቡዕ ወንድም ጋር ይተዋወቁ ስለነበር ከእሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ለማድረግ ተስማሙ። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አባቴና ዶረ ተጠመቁ። ከጊዜ በኋላ አባቴ በጂሊንግሃም ጉባኤ ውስጥ የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ እንዲያገለግል ተሾመ። አባቴ ከሞተ በኋላ እህቴ፣ ሮይ ሞርተን የተባለ ታማኝ የጉባኤ ሽማግሌ አገባች፤ ዶረ በ2010 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግላለች።

ፈረንሳይ ሄዶ መርዳት

ትምህርት ቤት እያለሁ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛና የላቲን ቋንቋ ተምሬ ነበር፤ ነገር ግን ከሦስቱ ቋንቋዎች በጣም የሚከብደኝ ፈረንሳይኛ ነበር። በመሆኑም ወደ ፈረንሳይ ሄጄ በፓሪስ የሚገኘውን ቤቴል እንድረዳ ስጠየቅ የተደበላለቀ ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። እዚያም ኦንሪ ጋይገር ከተባለ በቅርንጫፍ ቢሮው የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት ይከታተል ከነበረ አንድ አረጋዊ ቅቡዕ ወንድም ጋር አብሬ የመሥራት መብት አገኘሁ። እዚያ የተሰጠኝ የሥራ ምድብ አንዳንዴ ከባድ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ስህተቶችን እሠራ ነበር፤ ያም ሆኖ ከሌሎች ጋር ተስማምቶ መኖር ስለሚቻልበት መንገድ ብዙ ተምሬያለሁ።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ፓሪስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ በ1951 ለማካሄድ ዝግጅት ተደረገ፤ እኔም ይህን ስብሰባ በማደራጀት ረገድ አስተዋጽኦ ማበርከት ችያለሁ። ሊዮፖልድ ዦንታ የተባለ ወጣት ተጓዥ የበላይ ተመልካች በዚህ ሥራ ሊረዳኝ ወደ ቤቴል መጣ። ከጊዜ በኋላ ሊዮፖልድ የቅርንጫፍ ቢሮው የበላይ ተመልካች እንዲሆን ተሹሟል። ብሔራት አቀፍ ስብሰባው የተካሄደው አይፍል ታወር አቅራቢያ ባለ ፓሌይ ዴ ስፖር በተባለ የመሰብሰቢያ ቦታ ነበር። ከ28 አገሮች የመጡ ልዑካን በዚህ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ነበር። በፈረንሳይ የሚገኙ 6,000 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች በስብሰባው የመጨረሻ ቀን ላይ 10,456 የሚያህሉ ሰዎች በመገኘታቸው በጣም ተደስተው ነበር።

ፈረንሳይ እንደሄድኩ አካባቢ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ችሎታዬ በጣም ውስን ነበር። ከዚህ የከፋው ግን ‘ፈረንሳይኛ የምናገረው ቋንቋውን አቀላጥፌ መናገር ስችል ብቻ ነው’ የሚል የተሳሳተ አቋም መያዜ ነው። ይሁንና ስህተት ካልሠራችሁ ማስተካከያ ማድረግ አትችሉም፤ ማስተካከያ ካላደረጋችሁ ደግሞ ችሎታችሁን ማሻሻል አትችሉም።

ይህን ችግር ለመቅረፍ ለውጭ አገር ሰዎች ፈረንሳይኛ በሚያስተምር አንድ ትምህርት ቤት ተመዘገብኩ። የጉባኤ ስብሰባ በሌለባቸው ቀናት ምሽት ላይ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ትምህርቴን መከታተል ጀመርኩ። ቋንቋውን እየወደድኩት ስለመጣሁ ፈረንሳይኛዬ ከዓመት ወደ ዓመት እየተሻሻለ መጣ። ይህ ደግሞ በፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ ለሚከናወነው የትርጉም ሥራ እገዛ ማበርከት እንድችል ረድቶኛል። ከጊዜ በኋላ እኔ ራሴም ከእንግሊዝኛ ወደ ፈረንሳይኛ መተርጎም ጀመርኩ። በመላው ዓለም ለሚገኙ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ወንድሞች በባሪያው በኩል የሚዘጋጀው መንፈሳዊ ምግብ እንዲደርሳቸው አስተዋጽኦ ማበርከት መቻል ትልቅ መብት ነው።​—ማቴ. 24:45-47

ትዳር መመሥረትና ሌሎች መብቶች

በ1956፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት የተዋወቅኳትን ኤስተር የምትባል ስዊዘርላንዳዊት አቅኚ አገባሁ። የጋብቻ ሥነ ሥርዓታችን የተፈጸመው በለንደን ቤቴል አጠገብ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ (ድሮ ለንደን ታበርናክል ይባል የነበረውና እናቴ የተጠመቀችበት ቦታ ነው) ውስጥ ነው። የጋብቻ ንግግሩን የሰጠው ወንድም ሂዩዝ ነበር። በሥነ ሥርዓቱ ላይ ሰማያዊ ተስፋ የነበራት የኤስተር እናትም ተገኝታ ነበር። ኤስተርን ማግባቴ፣ ተወዳጅና ታማኝ የትዳር አጋር ማግኘት ብቻ ሳይሆን በ2000 ምድራዊ ሕይወቷን እስክታጠናቅቅ ድረስ ጥሩ እና መንፈሳዊ ሰው ከነበረችው እናቷ ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንድመሠርትም አስችሎኛል።

እኔና ኤስተር ከተጋባን በኋላ የምንኖረው ከቤቴል ውጭ ነበር። እኔ፣ ቤቴል በትርጉም ክፍል ውስጥ ሳገለግል ኤስተር ደግሞ በፓሪስ ከተማ ዳርቻ ላይ በሚገኙ አካባቢዎች በልዩ አቅኚነት ታገለግል ነበር። ኤስተር በርካታ ሰዎች የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ መርዳት ችላለች። በ1964 በቤቴል እንድንኖር ተጋበዝን። ከዚያም በ1976 ለመጀመሪያ ጊዜ የቅርንጫፍ ኮሚቴ ሲዋቀር እኔም ከአባላቱ አንዱ ሆኜ ተሾምኩ። አብረን ባሳለፍናቸው ዓመታት ሁሉ ኤስተር ምንጊዜም ፍቅራዊ ድጋፍ አድርጋልኛለች።

‘እኔን ሁልጊዜ አታገኙኝም’

አልፎ አልፎ ኒው ዮርክ ወደሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት የመሄድ ልዩ አጋጣሚ ነበረኝ። በእነዚህ አጋጣሚዎች ከተለያዩ የበላይ አካል አባላት ጥሩ ምክር አግኝቻለሁ። ለምሳሌ በአንድ ወቅት፣ ሥራችንን በተሰጠን የጊዜ ገደብ ውስጥ የመጨረሳችን ጉዳይ በጣም እንዳስጨነቀኝ ለወንድም ኖር ነገርኩት፤ በዚህ ጊዜ ወንድም ኖር ፈገግ ብሎ “አይዞህ አትጨነቅ። አንተ ብቻ ዝም ብለህ ሥራ!” አለኝ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ፣ ሥራ ሲደራረብብኝ ከመጨነቅ ይልቅ ሥራውን አንድ በአንድ ለማከናወን እጥራለሁ፤ ደግሞም በአብዛኛው ሥራው በታሰበው ሰዓት ያልቃል።

ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ‘እኔን ሁልጊዜ አታገኙኝም’ ብሏቸው ነበር። (ማቴ. 26:11) እኛ የሌሎች በጎች ክፍል አባላትም የክርስቶስ ቅቡዕ ወንድሞች ሁልጊዜ ከእኛ ጋር እንደማይኖሩ እናውቃለን። ስለሆነም ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት ከበርካታ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር የቅርብ ወዳጅነት መመሥረት መቻሌን በሌላ አባባል የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ መያዜን እንደ ትልቅ መብት እቆጥረዋለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 “ኢዮናዳብ” ስለሚለው ስያሜ ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት ከፈለግክ የጥር 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13 አንቀጽ 5 እና 6⁠ን እንዲሁም የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 83, 165 እና 166 ተመልከት።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወንድም ኖር ፈገግ ብሎ “አይዞህ አትጨነቅ። አንተ ብቻ ዝም ብለህ ሥራ!” አለኝ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(በስተግራ) እናቴና አባቴ

(በስተቀኝ) በ1948፣ በጊልያድ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ እናቴ የሰጠችኝን ሙቀት የሚሰጥ ካፖርት ለብሼ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1997 የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ በተወሰነበት ወቅት የወንድም ሎይድ ባሪን ንግግር ሳስተረጉም

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(በስተግራ) ከኤስተር ጋር በሠርጋችን ቀን

(በስተቀኝ) ከኤስተር ጋር አብረን ስናገለግል