በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን በፍጹም ልባችሁ ማገልገላችሁን ቀጥሉ

ይሖዋን በፍጹም ልባችሁ ማገልገላችሁን ቀጥሉ

ይሖዋን በፍጹም ልባችሁ ማገልገላችሁን ቀጥሉ

“[ልጄ ሆይ፣] የአባትህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው።”​—1 ዜና 28:9

የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ሞክር፦

ምሳሌያዊው ልብ ምን ያመለክታል?

ልባችንን ለመመርመር የትኛውን ዘዴ መጠቀም እንችላለን?

ይሖዋን በፍጹም ልባችን ማገልገላችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

1, 2. (ሀ) በአምላክ ቃል ውስጥ ከሌሎች ይልቅ በብዛት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የተጠቀሰው የትኛው የአካል ክፍል ነው? (ለ) ምሳሌያዊው ልብ ምን ትርጉም እንዳለው መረዳታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

የአምላክ ቃል የሰውን የአካል ክፍሎች ብዙውን ጊዜ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ይጠቀምባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢዮብ “በእጄ ዐመፅ አይገኝም” ብሏል። ንጉሥ ሰለሞን ደግሞ “መልካም ዜናም ዐጥንትን ያለመልማል” በማለት ተናግሯል። ይሖዋም ቢሆን “ግንባርህን ከባልጩት ይልቅ እንደሚጠነክር ድንጋይ አደርገዋለሁ” በማለት ሕዝቅኤልን አበረታቶታል። በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስን “ለጆሯችን እንግዳ የሆነ ነገር እያሰማኸን ነው” ብለውት ነበር።​—ኢዮብ 16:17፤ ምሳሌ 15:30፤ ሕዝ. 3:9፤ ሥራ 17:20

2 ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ የሰውነት ክፍል ከሌሎቹ ይልቅ በብዛት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተጠቅሷል። ታማኝ የነበረችው ሐና ይህን የሰውነት ክፍል በጸሎቷ ላይ ጠቅሳው ነበር፤ ሐና “ልቤ በእግዚአብሔር ጸና” ብላለች። (1 ሳሙ. 2:1) እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “ልብ” የሚለውን ቃል አንድ ሺህ ጊዜ ያህል የጠቀሱ ሲሆን በአብዛኛው የተጠቀሙበት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ነው። ምሳሌያዊው ልብ ምን ትርጉም እንዳለው መረዳታችን በጣም ወሳኝ ነገር ነው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ልባችንን መጠበቅ እንደሚያስፈልገን ይናገራል።​—ምሳሌ 4:23ን አንብብ።

ምሳሌያዊው ልብ ምን ያመለክታል?

3. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ልብ” የሚለው ቃል ያለውን ትርጉም መረዳት የምንችለው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

3 መጽሐፍ ቅዱስ “ልብ” ለሚለው ቃል ፍቺ ባይሰጥም ቃሉ ያለውን ትርጉም እንድንረዳ የሚያስችሉ ሐሳቦችን ይዟል። በምን መልኩ? ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት የተለያየ ቀለም ያላቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ጠጠሮች በመገጣጠም ውብ በሆነ መንገድ በግድግዳ ላይ የተሠራን ምስል ወደ አእምሯችን ማምጣት እንችላለን። አንድ ሰው የምስሉን ሙሉ ገጽታ በደንብ ለማየት ከምስሉ ራቅ ማለት ይኖርበታል፤ በዚህ ጊዜ በጥንቃቄ የተቀመጡት ጠጠሮች አንድ ዓይነት ቅርጽ ወይም ምስል መፍጠራቸውን ያስተውላል። በተመሳሳይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ልብ” የሚለው ቃል የገባባቸውን በርካታ ቦታዎች ለማየት ከሞከርን እነዚህ ጥቅሶች በአንድነት አንድ ቅርጽ ወይም ምስል እንደሚፈጥሩ እናስተውላለን። ታዲያ ይህ ምስል ምንድን ነው?

4. (ሀ) “ልብ” የሚለው ቃል ምን ያመለክታል? (ለ) ኢየሱስ በ⁠ማቴዎስ 22:37 ላይ የተናገረው ሐሳብ ትርጉም ምንድን ነው?

4 የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “ልብ” የሚለውን ቃል የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት የሚገልጹ ነገሮችን በአጠቃላይ ለማመልከት ተጠቅመውበታል። ይህም ምኞቱን፣ አስተሳሰቡን፣ ዝንባሌውን፣ አመለካከቱን፣ ችሎታውን፣ ግቦቹንና አንድን ነገር ለማድረግ የሚያነሳሳውን ምክንያት ያጠቃልላል። (ዘዳግም 15:7⁠ን፤ ምሳሌ 16:9ን እና የሐዋርያት ሥራ 2:26ን አንብብ።) አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ምሳሌያዊ ልብ “የውስጣዊው ሰው መገለጫ የሆኑ ነገሮች ድምር ውጤት” ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን “ልብ” የሚለው ቃል ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ የተወሰኑትን ብቻ ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ ኢየሱስ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ” ብሏል። (ማቴ. 22:37) በዚህ አገባቡ “ልብ” የሚያመለክተው የውስጣዊውን ሰው ስሜት፣ ምኞትና ፍላጎት ብቻ ነው። ኢየሱስ ልብን፣ ነፍስንና አእምሮን ለየብቻ የጠቀሰው ለአምላክ ያለን ፍቅር በፍላጎታችን፣ በአኗኗራችንና የማሰብ ችሎታችንን በምንጠቀምበት መንገድ ላይ መንጸባረቅ እንዳለበት ለማጉላት ነው። (ዮሐ. 17:3፤ ኤፌ. 6:6) ሆኖም “ልብ” የሚለው ቃል ለብቻው ሲጠቀስ የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት የሚገልጹ ነገሮችን በአጠቃላይ ያመለክታል።

ልባችንን መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው?

5. ይሖዋን በፍጹም ልባችን ለማገልገል የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

5 ንጉሥ ዳዊት ልብን በተመለከተ ለሰለሞን እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቶት ነበር፦ “ልጄ ሰሎሞን ሆይ፤ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ስለሚመረምርና ሐሳብን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ የአባትህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው።” (1 ዜና 28:9) በእርግጥም ይሖዋ የእኛን ጨምሮ የሁሉንም ሰው ልብ ይመረምራል። (ምሳሌ 17:3፤ 21:2) ልባችንን ሲመረምር የሚያገኘው ነገር ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና በጥልቅ የሚነካ ከመሆኑም በላይ የወደፊት ሕይወታችን በዚህ ላይ የተመካ ነው። በመሆኑም ይሖዋን በፍጹም ልባችን ለማገልገል የተቻለንን ሁሉ በማድረግ ዳዊት በመንፈስ መሪነት የሰጠውን ምክር መከተላችን ተገቢ ነው።

6. ይሖዋን ለማገልገል ካደረግነው ቁርጥ ውሳኔ ጋር በተያያዘ ምን ነገር መዘንጋት የለብንም?

6 የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችንን በቅንዓት ማከናወናችን አምላክን በፍጹም ልብ የማገልገል ጥልቅ ፍላጎት እንዳለን ያሳያል። በሌላ በኩል ደግሞ የሰይጣን ክፉ ዓለም የሚያሳድርብን ተጽዕኖና በውስጣችን ያለው ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ አምላክን በሙሉ ልባችን ለማገልገል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ የማዳከም ከፍተኛ ኃይል እንዳላቸው መዘንጋት የለብንም። (ኤር. 17:9፤ ኤፌ. 2:2) እንግዲያው አምላክን ለማገልገል ያደረግነው ቁርጥ ውሳኔ አለመዳከሙን ወይም ደግሞ ጥበቃችንን አላልተን እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ልባችንን በየጊዜው መፈተሻችን አስፈላጊ ነው። ታዲያ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

7. የልባችንን ሁኔታ የሚያሳየው ምንድን ነው?

7 እርግጥ ነው፣ የአንድ ዛፍ ውስጠኛ ክፍል ወይም እምብርቱ እንደማይታይ ሁሉ ውስጣዊ ማንነታችንም ሊታይ አይችልም። ያም ሆኖ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ እንደጠቀሰው አንድ ዛፍ ያለበት ሁኔታ በፍሬው እንደሚታወቅ ሁሉ የምናደርጋቸው ነገሮችም የልባችንን እውነተኛ ሁኔታ ያሳያሉ። (ማቴ. 7:17-20) እስቲ ውስጣዊ ማንነታችንን ከሚገልጡት ከእነዚህ ድርጊቶች መካከል አንዱን እንመልከት።

ልባችንን ለመመርመር የሚረዳ ዘዴ

8. ኢየሱስ በ⁠ማቴዎስ 6:33 ላይ የተናገረው ሐሳብ በልባችን ውስጥ ያለውን ነገር ለማወቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ከላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ከመናገሩ በፊት ለአድማጮቹ፣ ይሖዋን በሙሉ ልብ ለማገልገል ያላቸውን ውስጣዊ ፍላጎት የሚያሳውቀው ነገር ምን እንደሆነ ለይቶ ነግሯቸዋል። እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ መፈለጋችሁን ቀጥሉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።” (ማቴ. 6:33) በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር በልባችን ውስጥ ያለው ፍላጎት፣ ሐሳብና እቅድ ምን እንደሆነ ያሳያል። በመሆኑም አምላክን በፍጹም ልባችን እያገለገልነው መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችለን አንዱ ዘዴ በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር ምን እንደሆነ መመርመር ነው።

9. ኢየሱስ ለአንዳንድ ሰዎች ምን ግብዣ አቅርቦላቸው ነበር? የሰጡት ምላሽስ ስለ ልባቸው ሁኔታ ምን ገልጧል?

9 ኢየሱስ ‘ከሁሉ አስቀድመው የአምላክን መንግሥት እንዲፈልጉ’ ተከታዮቹን ካሳሰባቸው ብዙም ሳይቆይ የተከሰተው ሁኔታ አንድ ሰው በሕይወቱ የሚያስቀድመው ነገር የልቡን ሁኔታ ጥሩ አድርጎ እንደሚገልጥ ያሳያል። የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ የተከሰተውን ሁኔታ መተረክ የሚጀምረው ኢየሱስ “ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቆርጦ” መነሳቱን በመግለጽ ነው፤ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ የተነሳው በቅርቡ በዚያ ምን እንደሚደርስበት እያወቀ ነው። እሱና ሐዋርያቱ “በመንገድ እየተጓዙ ሳሉ” ያገኛቸውን አንዳንድ ሰዎች ‘ተከታዬ ሁኑ’ የሚል ግብዣ አቀረበላቸው። እነዚህ ሰዎች የኢየሱስን ግብዣ ለመቀበል ፈቃደኞች ቢሆኑም አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀመጡ። አንደኛው ሰው “በመጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው። ሌላው ሰው ደግሞ “ጌታ ሆይ፣ እኔ እከተልሃለሁ፤ በመጀመሪያ ግን ቤተሰቤን እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለው። (ሉቃስ 9:51, 57-61) ኢየሱስ በሙሉ ልቡ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም በነበረው ቁርጥ አቋምና እነዚህ ሰዎች ባቀረቡት ተልካሻ ምክንያት መካከል ምን ያህል ልዩነት እንዳለ ተመልከት! ከመንግሥቱ ይልቅ የራሳቸውን ጉዳይ ማስቀደማቸው በፍጹም ልብ አምላክን ማገልገል እንደማይፈልጉ ያሳያል።

10. (ሀ) ኢየሱስ ተከታዮቹ እንድንሆን ላቀረበልን ግብዣ ምን ምላሽ ሰጥተናል? (ለ) ኢየሱስ የትኛውን ምሳሌ ተናግሯል?

10 ደቀ መዛሙርት ሳይሆኑ ከቀሩት ከእነዚህ ሰዎች በተቃራኒ እኛ ጥበበኛ በመሆን ኢየሱስ ተከታዮቹ እንድንሆን ያቀረበልንን ግብዣ ተቀብለናል፤ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን በየዕለቱ በማገልገል ላይ እንገኛለን። በዚህ መንገድ በልባችን ውስጥ ስለ ይሖዋ ምን እንደሚሰማን አሳይተናል። በሌላ በኩል በጉባኤ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እያደረግን ብንሆን እንኳ ልባችን አሁንም አደጋ እንደተጋረጠበት ማስታወስ ይኖርብናል። ይህ አደጋ ምንድን ነው? ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ሳይሆኑ ከቀሩት ሰዎች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ይህ አደጋ ምን እንደሆነ ግልጽ አድርጓል፤ እንዲህ ብሏል፦ “ዕርፍ ጨብጦ በኋላው ያሉትን ነገሮች የሚመለከት ሰው ለአምላክ መንግሥት የሚገባ አይደለም።” (ሉቃስ 9:62) ታዲያ ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

‘ጥሩ የሆነውን ነገር አጥብቀን እንይዛለን?’

11. በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ሠራተኛ ምን አጋጠመው? ለምንስ?

11 ኢየሱስ ከሰጠው ምሳሌ የምናገኘው ትምህርት ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልን እስቲ ምሳሌውን ሰፋ አድርገን እንመልከት። በእርሻው ላይ ተቀጥሮ የሚሠራው ሰው መሬቱን በማረስ ተግባር ተጠምዷል። ይሁንና ይህ ግለሰብ መሬቱን እያረሰ ሳለ ቤተሰቡ፣ ወዳጆቹ፣ ምግቡ፣ ሙዚቃውና ደስታው ወደ አእምሮው ይመጣሉ፤ እንዲሁም በፀሐይ ከመንቃቃት ጥላ ሥር አረፍ ማለት ያምረዋል። ይህ ሠራተኛ ለተወሰነ ጊዜ ካረሰ በኋላ እነዚህን ነገሮች የማግኘት ምኞቱ እያየለ በመሄዱ “በኋላው ያሉትን ነገሮች” ለማየት ይዞራል። ዘሩ እስኪዘራ ድረስ ገና ብዙ ሥራ ቢቀረውም ሐሳቡ በመከፋፈሉ ሥራው ተበድሏል። የእርሻው ባለቤት ሠራተኛው ተግባሩን በጽናት አለማከናወኑን ሲመለከት እንደሚያዝን የታወቀ ነው።

12. ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰውን ሠራተኛ በዘመናችን ከሚገኙ አንዳንድ ክርስቲያኖች ጋር እንዴት ማነጻጸር እንችላለን?

12 እስቲ አሁን ምሳሌውን በዘመናችን ከሚከሰት ሁኔታ ጋር እናነጻጽረው። ገበሬው በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ጥሩ ተሳትፎ የሚያደርግ ሆኖም መንፈሳዊ አደጋ ውስጥ የሚገኝን ማንኛውንም ክርስቲያን ሊያመለክት ይችላል። ለንጽጽር እንዲያመቸን በአገልግሎት ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግን አንድ ወንድም ወደ አእምሯችን እናምጣ። ይህ ወንድም በስብሰባዎች ላይ የሚገኝ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት የሚካፈል ቢሆንም ማራኪ መስለው ስለሚታዩት ዓለም ስለሚያቀርባቸው አንዳንድ ነገሮች ማሰቡን ማቆም አልቻለም፤ በመሆኑም በልቡ እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ይመኛል። ለተወሰኑ ዓመታት አገልግሎቱን ሲያከናውን ከቆየ በኋላ ዓለም የሚያቀርባቸውን ነገሮች የማግኘት ጉጉቱ በጣም እያየለ ስለሚሄድ “በኋላው ያሉትን ነገሮች” ለማየት ይዞራል። በአገልግሎቱ የሚያከናውነው ገና ብዙ ሥራ ቢኖርም ‘የሕይወትን ቃል አጥብቆ መያዙን’ አልቀጠለም፤ በዚህም የተነሳ ከቲኦክራሲያዊው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የሚያከናውነው ሥራ ይበደላል። (ፊልጵ. 2:16) “የመከሩ ሥራ ኃላፊ” የሆነው ይሖዋ ከሠራተኞቹ አንዱ ሥራውን በጽናት እንዳላከናወነ ሲመለከት እንደሚያዝን ምንም ጥርጥር የለውም።​—ሉቃስ 10:2

13. ይሖዋን በፍጹም ልብ ማገልገል ምን ነገር ይጠይቃል?

13 ከምሳሌው የምናገኘው ትምህርት ግልጽ ነው። በጉባኤ ስብሰባዎች እንደመገኘትና በአገልግሎት እንደመካፈል ባሉ ጠቃሚና አስደሳች እንቅስቃሴዎች አዘውትረን መካፈላችን የሚያስመሰግን ነው። ይሁንና ይሖዋን በፍጹም ልብ ማገልገል ከዚህ የበለጠ ነገር ይጠይቃል። (2 ዜና 25:1, 2, 27) አንድ ክርስቲያን በልቡ ውስጥ ‘በኋላው ላሉ ነገሮች’ ማለትም ዓለም ለሚያቀርባቸው አንዳንድ ነገሮች ፍቅር ማሳደሩን ከቀጠለ በአምላክ ፊት ያለውን ጥሩ አቋም የማጣት አደጋ ያጋጥመዋል። (ሉቃስ 17:32) ‘ለአምላክ መንግሥት የምንገባ’ ሰዎች መሆን የምንችለው “ክፉ የሆነውን ነገር” ከልባችን የምንጸየፍ እንዲሁም “ጥሩ የሆነውን ነገር” አጥብቀን የምንይዝ ከሆነ ብቻ ነው። (ሮም 12:9፤ ሉቃስ 9:62) እንግዲያው ሁላችንም፣ የሰይጣን ዓለም የሚያቀርባቸው ማንኛውም ነገሮች ምንም ያህል ጠቃሚ ወይም አስደሳች መስለው ቢታዩንም ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሙሉ ልብ ከማከናወን ወደኋላ እንዲያደርጉን መፍቀድ የለብንም።​—2 ቆሮ. 11:14፤ ፊልጵስዩስ 3:13, 14ን አንብብ።

ምንጊዜም ንቁ ሁኑ!

14, 15. (ሀ) ሰይጣን በልባችን ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚሞክረው እንዴት ነው? (ለ) ሰይጣን የሚጠቀምበት ዘዴ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

14 በፍቅር ተነሳስተን ራሳችንን ለይሖዋ ወስነናል። ብዙዎቻችን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሖዋን በፍጹም ልባችን ለማገልገል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ጠብቀን ለዓመታት ጸንተናል። ይሁን እንጂ ሰይጣን ተስፋ በመቁረጥ በእኛ ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት አላቆመም። አሁንም ቢሆን የጥቃት ዒላማ የሚያደርገው ልባችንን ነው። (ኤፌ. 6:12) በእርግጥ ሰይጣን፣ ይሖዋን በአንድ ጊዜ እርግፍ አድርገን እንደማንተው ያውቃል። በመሆኑም ለአምላክ ያለንን ከልብ የመነጨ ቅንዓት ቀስ በቀስ ለማዳከም ይህን “ሥርዓት” ስውር በሆነ መንገድ ይጠቀማል። (ማርቆስ 4:18, 19ን አንብብ።) ይህ የሰይጣን ዘዴ ውጤታማ የሆነው ለምንድን ነው?

15 የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ባለ100 ሻማ አምፖል ተጠቅመህ መጽሐፍ እያነበብክ ነው እንበል፤ በዚህ ጊዜ አምፖሉ በድንገት ይቃጠላል። ክፍልህ በአንድ ጊዜ ጨለማ ስለሚውጠው ምን እንደተከሰተ ማወቅ አያቅትህም፤ በመሆኑም የተቃጠለውን በአዲስ አምፖል ትቀይራለህ። ክፍልህም እንደገና ብርሃን ያገኛል። በሚቀጥለው ምሽት በዚያው አምፖል ተጠቅመህ ማንበብ ጀመርክ። ይሁንና አንድ ሰው ሳታውቀው ባለ100 ሻማ አምፖሉን በባለ95 ሻማ አምፖል ቀየረብህ። ታዲያ ለውጡ የሚታወቅህ ይመስልሃል? በአብዛኛው አይታወቅህም። በሚቀጥለው ቀን ደግሞ በባለ90 ሻማ አምፖል ቢቀይርብህስ? በዚህ ጊዜም ቢሆን ለውጡን እንደማታስተውል የታወቀ ነው። ለምን? የአምፖሉ ብርሃን እየቀነሰ የሚመጣው ቀስ በቀስ በመሆኑ ለውጡ አይታወቅህም። በተመሳሳይም የሰይጣን ዓለም የሚያሳድርብን ተጽዕኖ ቅንዓታችን ቀስ በቀስ እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመን ሰይጣን በይሖዋ አገልግሎት የነበረንን ባለ100 ሻማ ቅንዓት እንዲቀንስ በማድረግ ረገድ ተሳክቶለታል ማለት ነው። አንድ ክርስቲያን ንቁ ካልሆነ ቀስ በቀስ የሚከሰተውን ለውጥ ላያስተውለው እንኳ ይችላል።​—ማቴ. 24:42፤ 1 ጴጥ. 5:8

ጸሎት በጣም አስፈላጊ ነው

16. ከሰይጣን መሠሪ ዘዴዎች ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

16 እንዲህ ካሉት የሰይጣን መሠሪ ዘዴዎች ራሳችንን መጠበቅና ይሖዋን በፍጹም ልባችን ማገልገላችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? (2 ቆሮ. 2:11) ጸሎት በዚህ ረገድ በጣም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ ‘የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች እንዲቋቋሙ’ የእምነት ባልንጀሮቹን አበረታቷቸዋል። በመቀጠልም “በሁሉም ዓይነት ጸሎትና ምልጃ በማንኛውም ጊዜ . . . መጸለያችሁን ቀጥሉ” ሲል አሳስቧቸዋል።​—ኤፌ. 6:11, 18፤ 1 ጴጥ. 4:7

17. ኢየሱስ ጸሎት ካቀረበበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?

17 የሰይጣንን ጥቃት ለመቋቋም በጸሎት ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መከተላችን የጥበብ አካሄድ ነው፤ ኢየሱስ የሚያቀርባቸው ጸሎቶች ምንጊዜም ይሖዋን በፍጹም ልቡ የማገልገል ጥልቅ ፍላጎት እንዳለው ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከመሞቱ በፊት ባለው ምሽት ላይ ስለ ጸለየበት መንገድ ሉቃስ ምን ብሎ እንደዘገበ ልብ በል፦ “በከፍተኛ ጭንቀት ተውጦ ከበፊቱ ይበልጥ አጥብቆ መጸለዩን ቀጠለ።” (ሉቃስ 22:44) ኢየሱስ ከዚህ ቀደምም ቢሆን አጥብቆ ይጸልይ ነበር። በዚህ ወቅት ያጋጠመው ፈተና ግን በምድራዊ ሕይወቱ ካጋጠሙት ሁሉ እጅግ ከባድ በመሆኑ “ከበፊቱ ይበልጥ አጥብቆ” ጸልዮአል፤ ጸሎቱም ተሰምቶለታል። ከኢየሱስ ሁኔታ መረዳት እንደምንችለው ጸሎት የተለያየ የጥልቀት ደረጃ አለው። በመሆኑም የሚደርሱብን መከራዎች ይበልጥ እየከበዱ በሄዱ መጠን እንዲሁም የሰይጣን ስውር ዘዴዎች የሚያሳድሩብን ተጽዕኖዎች ይበልጥ እየጨመሩ በሄዱ ቁጥር የይሖዋን ጥበቃ ለማግኘት እኛም ‘ይበልጥ አጥብቀን’ መጸለይ ይኖርብናል።

18. (ሀ) ጸሎትን አስመልክቶ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል? ለምንስ? (ለ) በልባችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? ተጽዕኖ የሚያሳድሩትስ በምን መንገዶች ነው? ( በገጽ 16 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

18 እንዲህ ያለ ጸሎት ማቅረባችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁን . . . ይጠብቃል።” (ፊልጵ. 4:6, 7) አዎን፣ ይሖዋን በፍጹም ልብ ማገልገላችንን ለመቀጠል ከፈለግን በተደጋጋሚ አጥብቀን መጸለያችን በጣም ወሳኝ ነው። (ሉቃስ 6:12) በመሆኑም ‘በተደጋጋሚ አጥብቄ የመጸለይ ልማድ አለኝ?’ በማለት ራስህን መጠየቅህ ተገቢ ነው። (ማቴ. 7:7፤ ሮም 12:12) ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ አምላክን ለማገልገል ያለህ ፍላጎት ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ያሳያል።

19. ይሖዋን በፍጹም ልባችን ማገልገላችንን ለመቀጠል ምን ማድረግ ይኖርብናል?

19 እስካሁን እንደተመለከትነው በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጣቸው ነገሮች ስለ ልባችን ሁኔታ ብዙ ይናገራሉ። በኋላችን ያሉ ነገሮችም ሆኑ የሰይጣን መሠሪ ዘዴዎች ይሖዋን በፍጹም ልባችን ለማገልገል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ እንዳያዳክሙብን መጠንቀቅ እንደምንፈልግ ግልጽ ነው። (ሉቃስ 21:19, 34-36ን አንብብ።) እንግዲያው ልክ እንደ ዳዊት ይሖዋን “ያልተከፋፈለ ልብ ስጠኝ” ብለን መማጸናችንን መቀጠል ይኖርብናል።​—መዝ. 86:11

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በልባችን ላይ ተጽዕኖ የሚያደርጉ ሦስት ነገሮች

ለሥጋዊ ልባችን እንደምንጠነቀቀው ሁሉ የምሳሌያዊ ልባችንን ጤንነት ለመጠበቅም አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ እንችላለን። እስቲ ለልባችን ጤንነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሦስት ነገሮችን እንመልከት፦

1 ምግብ፦ የልባችን ጤንነት የተጠበቀ እንዲሆን የተመጣጠነ ምግብ በበቂ መጠን መመገብ ይኖርብናል። በተመሳሳይም አዘውትረን የግል ጥናት በማድረግ፣ በማሰላሰል እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ በመገኘት ጠቃሚ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ በበቂ መጠን መመገብ ይኖርብናል።​—መዝ. 1:1, 2፤ ምሳሌ 15:28፤ ዕብ. 10:24, 25

 2 እንቅስቃሴ፦ ጤንነታችን የተጠበቀ እንዲሆን አንዳንድ ጊዜ አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ልባችንን በደንብ ማሠራት ይኖርብናል። በተመሳሳይም በአገልግሎት ላይ በቅንዓት የምንካፈል፣ ምናልባትም ተጋድሎ በማድረግ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችንን ከፍ የምናደርግ ከሆነ የምሳሌያዊው ልባችን ጤንነት የተጠበቀ ይሆናል።​—ሉቃስ 13:24፤ ፊልጵ. 3:12

3 አካባቢ፦ የምንሠራበትም ሆነ የምንኖርበት አካባቢ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች የሞሉበት እንደመሆኑ መጠን በሥጋዊውም ሆነ በምሳሌያዊው ልባችን ላይ ከፍተኛ ውጥረት ሊያስከትል ይችላል። ይሁንና ስለ እኛ ከልብ ከሚያስቡና አምላክን በፍጹም ልባቸው ከሚያገለግሉ የእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በተቻለ መጠን ቶሎ ቶሎ የምንገናኝ ከሆነ የሚደርስብን ውጥረት ሊቀንስ ይችላል።​—መዝ. 119:63፤ ምሳሌ 13:20