በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

በዕድሜ ከሚበልጡኝ ጋር እቀራረብ ነበር

በዕድሜ ከሚበልጡኝ ጋር እቀራረብ ነበር

ኤልቨ ጄርዲ እንደተናገሩት

ከ70 ዓመታት በፊት ቤታችን መጥቶ የነበረ አንድ እንግዳ ለአባቴ ያቀረበለት ሐሳብ የሕይወቴን አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ለወጠው። ትልቅ ቦታ ከምሰጠው ከዚያ ቀን ወዲህ ሌሎች በርካታ ሰዎችም በሕይወቴ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ይህ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ ከፍ አድርጌ የምመለከተው አንድ ልዩ ወዳጅነት እንድመሠርት አጋጣሚ ከፍቶልኛል። እስቲ እንዲህ ያልኩበትን ምክንያት ላጫውታችሁ።

የተወለድኩት በ1932 በሲድኒ አውስትራሊያ ነው። ወላጆቼ በአምላክ የሚያምኑ ቢሆኑም ወደ ቤተ ክርስቲያን አይሄዱም ነበር። እናቴ፣ አምላክ ምንጊዜም እንደሚመለከተኝና አስቸጋሪ ልጅ ከሆንኩ እንደሚቀጣኝ ትነግረኝ ነበር። ይህም አምላክን እንድፈራው አደረገኝ። ያም ሆኖ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ይማርከኝ ነበር። አክስቴ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ልትጠይቀን ስትመጣ አስደሳች የሆኑ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ትነግረኝ ነበር። በዚህም የተነሳ እሷ የምትመጣበትን ቀን የምጠብቀው በጉጉት ነበር።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለሁ አባቴ፣ አንዲት አረጋዊት የይሖዋ ምሥክር ለእናቴ የሰጠቻቸውን መጻሕፍት ያነብ ነበር። አባቴ በእነዚያ መንፈሳዊ ጽሑፎች ውስጥ ያነበበውን ነገር በጣም ስለወደደው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ። አንድ ቀን ምሽት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን እያጠና ሳለ ተደብቄ ሳዳምጥ አየኝ። ወደ መኝታ ቤቴ ሄጄ እንድተኛ ሊያደርግ ሲል የሚያስጠናው ሰው “አብራን ቁጭ ብላ ብታዳምጥስ?” አለው። አስጠኚው ያቀረበው ይህ ሐሳብ በሕይወቴ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተልኝ ከመሆኑም በላይ ከእውነተኛው አምላክ ከይሖዋ ጋር ለመሠረትኩት ወዳጅነትም ፈር ቀዳጅ ሆኖልኛል።

ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እኔና አባቴ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርን። አባቴ የተማረው ነገር በሕይወቱ ላይ ለውጥ እንዲያደርግ አነሳሳው። ሌላው ቀርቶ የግልፍተኝነት ባሕርዩን መቆጣጠር ጀመረ። ይህም እናቴና ታላቅ ወንድሜ ፍራንክ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲጀምሩ አነሳሳቸው። * አራታችንም እድገት በማድረግ ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን። ከዚያ ጊዜ አንስቶ፣ በዕድሜ የሚበልጡኝ በርካታ ሰዎች በተለያዩ ወቅቶች በሕይወቴ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ አሳድረዋል።

የሥራ መስክ ስመርጥ

በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለሁ በዕድሜ ከሚበልጡኝ የጉባኤያችን አባላት ጋር እቀራረብ ነበር። ከእነሱ መካከል አንዷ ለመጀመሪያ ጊዜ ምሥራቹን ለቤተሰባችን የነገረችው አለስ ፕሌስ የምትባል አረጋዊት እህት ናት። እሷን የማያት ልክ እንደ አያቴ ነበር። አለስ በአገልግሎት ላይ ጥሩ ሥልጠና የሰጠችኝ ሲሆን ለመጠመቅ ያወጣሁት ግቤ ላይ እንድደርስም አበረታታኛለች። በመሆኑም በ15 ዓመቴ ተጠመቅኩ።

በተጨማሪም ፐርሲ እና ማጅ [ማርጋሬት] ደነም ከሚባሉ አረጋዊ ባልና ሚስት ጋር እቀራረብ ነበር። ከእነሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረቴ ለቀጣይ ሕይወቴ በእጅጉ ጠቅሞኛል። ሒሳብ ስለምወድ ወደፊት የሒሳብ አስተማሪ የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ። ፐርሲ እና ማጅ በ1930ዎቹ ውስጥ በላቲቪያ ሚስዮናውያን ሆነው ያገለግሉ ነበር። ይሁንና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓ ሲፈነዳ ሲድኒ ከተማ በሚገኘው የአውስትራሊያ ቤቴል እንዲያገለግሉ ተመደቡ። ፐርሲ እና ማጅ ለእኔ ልዩ ትኩረት ይሰጡኝ ነበር። ሚስዮናዊ ሆነው ሲያገለግሉ ያጋጠሟቸውን ብዙ አስደሳች ተሞክሮዎች ሲናገሩ አዳምጥ ነበር። እኔም የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ መሆን የሒሳብ አስተማሪ ከመሆን እጅግ የላቀ እርካታ እንደሚያስገኝ በደንብ መገንዘብ ቻልኩ። ስለዚህ የሒሳብ አስተማሪ የመሆን ግቤን ቀይሬ ሚስዮናዊ ለመሆን ወሰንኩ።

እነዚህ ባልና ሚስት አቅኚ መሆኔ ለሚስዮናዊነት አገልግሎት እንደሚረዳኝ በመግለጽ እዚህ ግብ ላይ እንድደርስ አበረታቱኝ። በመሆኑም በ1948 ማለትም በ16 ዓመቴ አቅኚ ሆንኩ፤ በወቅቱ ሲድኒ ውስጥ ኸርትስቪሌ በሚባል አካባቢ በሚገኘው ጉባኤያችን ውስጥ በአቅኚነት በደስታ የሚያገለግሉ አሥር ወጣቶች ነበሩ።

በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ኒው ሳውዝ ዌልስ እና ኩዊንስላንድ በሚባሉ ግዛቶች ባሉ አራት ከተሞች ውስጥ በአቅኚነት አገለገልኩ። ከመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቼ መካከል አንዷ ቤቲ ሎ ነች (አሁን ቤቲ ሬምነንት ትባላለች)። ቤቲ አሳቢ ልጅ ስትሆን እኔን በሁለት ዓመት ትበልጠኛለች። ከጊዜ በኋላ ከሲድኒ በስተምዕራብ 230 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ካውረ በተባለች ከተማ ከእኔ ጋር በአቅኚነት ማገልገል ጀመረች። ከቤቲ ጋር በአቅኚነት አብረን ያገለገልነው ለአጭር ጊዜ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ወዳጅነታችን ቀጥሏል።

ልዩ አቅኚ ስሆን ከካውረ በስተደቡብ ምዕራብ 220 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በነራንድረ እንዳገለግል ተመደብኩ። አዲሷ የአገልግሎት ጓደኛዬ ጆይ ሌኖክስ የምትባል ቀናተኛ አቅኚ ስትሆን (አሁን ጆይ ሀንተር ትባላለች) እሷም ብትሆን በሁለት ዓመት ትበልጠኝ ነበር። በከተማዋ የነበርነው የይሖዋ ምሥክሮች ሁለታችን ብቻ ነበርን። እኔና ጆይ የምንኖረው ሬይ እና ኤስተር አይረን የተባሉ ጥሩ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ያላቸው ባልና ሚስት ባከራዩን ቤት ውስጥ ነበር። እነሱን ጨምሮ አንድ ወንድና ሦስት ሴቶች ልጆቻቸው ለእውነት ፍላጎት አሳዩ። ሬይ እና ወንድ ልጁ በሳምንቱ መካከል ያሉትን ቀናት የሚያሳልፉት ከከተማ ውጭ በጎችን በመንከባከብና በስንዴ ማሳ ላይ በመሥራት ሲሆን ኤስተርና ሴት ልጆቿ ደግሞ በቤታቸው ለእንግዶች የምግብና የመኝታ አገልግሎት ይሰጡ ነበር። እሁድ እሁድ እኔና ጆይ ለቤተሰቡና በዚያ ተከራይተው ለሚኖሩ በርከት ያሉ የባቡር መንገድ ሠራተኞች የሚበቃ ራት እናዘጋጅ ነበር። እነዚህ ሠራተኞች የሚመጡት ርቧቸው ስለሆነ ብዙ ምግብ መሥራት ነበረብን። ይህም የቤት ኪራያችንን በከፊል ይሸፍንልን ነበር። ከራት በኋላ ዕቃዎቹን አነሳስተን ስንጨርስ ለዚህ ቤተሰብ ጣፋጭ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ እናቀርብላቸው ነበር፤ ማለትም ሳምንታዊውን የመጠበቂያ ግንብ ጥናት አብረናቸው እናደርግ ነበር። ሬይና ኤስተር እንዲሁም አራቱም ልጆቻቸው ወደ እውነት የመጡ ሲሆን የነራንድረ ጉባኤ መሥራች አባላት ለመሆን ችለዋል።

በ1951 ሲድኒ ውስጥ በተካሄደው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ነበር። እዚያም ሚስዮናዊ ለመሆን ከሚፈልጉ አቅኚዎች ጋር በተደረገ አንድ ልዩ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። በአንድ ትልቅ ድንኳን ውስጥ በተካሄደው በዚያ ስብሰባ ላይ ከ300 በላይ አቅኚዎች ተገኝተን ነበር። ንግግሩን ያቀረበው ከብሩክሊን ቤቴል የመጣው ወንድም ናታን ኖር ሲሆን ምሥራቹን በመላው ዓለም ማዳረስ ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ገለጸ። ንግግሩን ሲያቀርብ እያንዳንዱን ቃል የተከታተልነው በጥሞና ነበር። በዚያ ከተገኙት አቅኚዎች መካከል አብዛኞቹ ከጊዜ በኋላ በደቡብ ፓስፊክና በሌሎችም አካባቢዎች የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ ረገድ ፈር ቀዳጅ ሆነዋል። በ1952 በጊልያድ ትምህርት ቤት 19ኛ ክፍል ገብተው እንዲሠለጥኑ ከተጠሩት 17 አውስትራሊያውያን መካከል አንዷ በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ። በሚስዮናዊነት ለማገልገል የነበረኝ ሕልም ገና በ20 ዓመቴ እውን ሆነ!

ባሕርዬን ማሻሻል ሲያስፈልገኝ

በጊልያድ የቀሰምኩት ትምህርትና የመሠረትኩት ወዳጅነት የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቴን ማሳደግና እምነቴን ማጠናከር ብቻ ሳይሆን በባሕርዬም ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። በወቅቱ ገና ወጣት ስለነበርኩና ከእውነታው የራቀ አስተሳሰብ ስለነበረኝ ከራሴም ሆነ ከሌሎች ፍጽምና እጠብቅ ነበር። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከመጠን ያለፈ ጥብቅ ነበርኩ። ለምሳሌ ያህል፣ ወንድም ኖር ከወጣት ቤቴላውያን ጋር ኳስ ሲጫወት ሳየው በጣም ደንግጬ ነበር።

አስተዋይና የረጅም ዓመት ተሞክሮ ያላቸው የጊልያድ አስተማሪዎች ችግሬ ሳይገባቸው አልቀረም። ለእኔ ትኩረት በመስጠት አስተሳሰቤን እንዳስተካክል ረዱኝ። ይሖዋ ከልክ በላይ ጥብቅ እንዲሁም ከሌሎች ብዙ የሚጠብቅ ሳይሆን አፍቃሪና አድናቂ አምላክ እንደሆነ ቀስ በቀስ መገንዘብ ጀመርኩ። አብረውኝ የሚማሩ አንዳንድ ተማሪዎችም ረድተውኛል። ከእነዚህ መካከል አንዷ “ኤልቨ፣ ይሖዋ እኮ ለመቅጣት አለንጋ ይዞ የሚጠብቅ አምላክ አይደለም። በራስሽ ላይ ይህን ያህል ጥብቅ አትሁኚ!” ያለችኝን አስታውሳለሁ። ይህች እህት የሰጠችኝ ግልጽ ምክር ልቤን ነካው።

ከጊልያድ ስንመረቅ እኔና አብረውኝ የተማሩ አራት ሚስዮናውያን በናሚቢያ እንድናገለግል ተመደብን። ብዙም ሳይቆይ በድምሩ 80 ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመርን። አገሩንም ሆነ የሚስዮናዊነት ሕይወቴን ወድጄው ነበር። ይሁን እንጂ በጊልያድ አብሮኝ ከተማረና ስዊዘርላንድ ከተመደበ አንድ ሰው ጋር ፍቅር ይዞኝ ስለነበር በናሚቢያ አንድ ዓመት ካሳለፍኩ በኋላ እጮኛዬ ወደሚገኝበት ወደ ስዊዘርላንድ ሄድኩ። እጮኛዬ ቀድሞውኑም የወረዳ የበላይ ተመልካች ስለነበር ከተጋባን በኋላ ከእሱ ጋር አብሬ ማገልገል ጀመርኩ።

እጅግ አስደንጋጭ ሁኔታ ሲያጋጥመኝ

በወረዳ ሥራ አም⁠ስት አስደሳች ዓመታትን ካሳለፍን በኋላ በስዊዘርላንድ ቤቴል እንድናገለግል ተጠራን። በቤቴል ውስጥ በዕድሜ ከእኔ በሚበልጡና በመንፈሳዊ በጎለመሱ ወንድሞችና እህቶች ተከብቤ መኖሬ በጣም የሚያስደስት ነበር።

ብዙም ሳይቆይ አንድ በጣም አስደንጋጭ ሁኔታ አጋጠመኝ። ባለቤቴ ለእኔም ሆነ ለይሖዋ ታማኝ እንዳልሆነ ደረስኩበት። ከዚያም ጥሎኝ ሄደ። በሁኔታው በጣም ተበሳጭቼና አዝኜ ነበር! በቤቴል ያሉ በዕድሜ የሚበልጡኝ ወዳጆቼ ፍቅራቸውን ባያሳዩኝና ድጋፍ ባያደርጉልኝ ኖሮ ሁኔታውን እንዴት እንደምቋቋመው አላውቅም ነበር። እነሱም፣ ማውራት ስፈልግ ያዳምጡኝ እንዲሁም ማረፍ ስፈልግ ደግሞ እንዳርፍ ይተዉኝ ነበር። በቃላት ለመግለጽ አዳጋች በሆነ ሥቃይ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት እነዚህ ወዳጆቼ ያካፈሉኝ የሚያጽናና ሐሳብና ያሳዩኝ ደግነት ያበረታታኝ ከመሆኑም በላይ ከምንጊዜውም ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድቀርብ ረድቶኛል።

በተጨማሪም ጥበበኛ የሆኑና በፈተናዎች ነጥረው የወጡ በዕድሜ ከእኔ የሚበልጡ ወዳጆቼ ከዓመታት በፊት የተናገሯቸውን ሐሳቦች አስታወስኩ። ከእነዚህም መካከል ማጅ ደነም የሰጠችኝ ሐሳብ ይገኝበታል። በአንድ ወቅት እንዲህ ብላኝ ነበር፦ “ኤልቨ፣ ይሖዋን ስታገለግዪ በሕይወትሽ ውስጥ ብዙ ፈተናዎች ያጋጥሙሻል፤ ከሁሉም የሚከብዱት ፈተናዎች የሚመጡብሽ ግን በጣም ከምትቀርቢያቸው ሰዎች ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ ፈተናዎች በሚያጋጥሙሽ ጊዜ ወደ ይሖዋ መቅረብ ይኖርብሻል። የምታገለግይው ይሖዋን እንጂ ፍጽምና የሌላቸውን ሰዎች እንዳልሆነ አስታውሺ!” ማጅ የሰጠችኝ ምክር በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት እንድወጣ ኃይል ሰጥቶኛል። ባለቤቴ የፈጸመው ስህተት ከይሖዋ እንዲነጥለኝ ፈጽሞ ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ።

ከጊዜ በኋላ ወደ አውስትራሊያ በመመለስ ቤተሰቦቼ በሚኖሩበት አቅራቢያ በአቅኚነት ለማገልገል ወሰንኩ። ወደ ቤተሰቦቼ ለመሄድ በመርከብ እየተጓዝኩ ሳለ አብረውኝ ከሚጓዙ ሰዎች ጋር ደስ የሚል የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት አደርግ ነበር። ከእነሱ መካከል የኖርዌይ ተወላጅ የሆነው አርነ ጄርዲ የተባለ ሰው ይገኝበታል። ይህ ሰው ረጋ ያለ ሲሆን የነገርኩትን ነገር ወደደው። አርነ ከጊዜ በኋላ ወደ ሲድኒ መጥቶ ቤተሰቤንና እኔን ጠየቀን። አርነ ፈጣን መንፈሳዊ እድገት አድርጎ ተጠመቀ። በ1963 እኔና አርነ የተጋባን ሲሆን ከሁለት ዓመት በኋላ ወንድ ልጃችንን ጌሪን ወለድን።

ሌላ አሳዛኝ ሁኔታ ሲያጋጥመኝ

እኔ፣ አርነና ጌሪ አስደሳች የሆነ የቤተሰብ ሕይወት ነበረን። ብዙም ሳይቆይ አርነ በዕድሜ የገፉት ወላጆቼ ከእኛ ጋር እንዲኖሩ ቤታችንን አሰፋው። ይሁንና በትዳር ሕይወት ስድስት ዓመት ካሳለፍን በኋላ አንድ ሌላ አስደንጋጭ ሁኔታ አጋጠመን። አርነ የጭንቅላት ካንሰር እንዳለበት በምርመራ ታወቀ። ረዘም ላለ ጊዜ የጨረር ሕክምና የተደረገለት ሲሆን እኔም እሱን ለማስታመም በየቀኑ ሆስፒታል እመላለስ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ጤንነቱ ተሻሽሎ ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን ሕመሙ እየተባባሰ ከመምጣቱም በላይ አእምሮው ላይ እክል አጋጠመው። በሕይወት የሚቆየው ለጥቂት ሳምንታት ብቻ እንደሆነ ተነገረኝ። ይሁን እንጂ አርነ ከሞት ተረፈ። ውሎ አድሮም ወደ ቤቱ የተመለሰ ሲሆን ጤንነቱ እስኪመለስለት ድረስ አስታመምኩት። ከጊዜ በኋላ እንደገና በእግሩ መሄድ የጀመረ ከመሆኑም ሌላ የጉባኤ ሽማግሌ እንደ መሆኑ መጠን ኃላፊነቶቹን እንደ ቀድሞው መወጣት ቻለ። ደስተኛና ተጫዋች መሆኑ ለጤንነቱ መሻሻል አስተዋጽኦ ያደረገለት ሲሆን ለእኔም እሱን መንከባከብ ቀላል እንዲሆንልኝ አድርጓል።

ከዓመታት በኋላ ማለትም በ1986 የአርነ ጤንነት እንደገና ማሽቆልቆል ጀመረ። በዚህ ጊዜ ወላጆቼ በሕይወት ስላልነበሩ ከሲድኒ ወጣ ብሎ ወደሚገኘው ብሉ ማውንቴይን የተባለ ውብ አካባቢ ተዛውረን መኖር ጀመርን፤ ይህ ቦታ ለወዳጆቻችን ቅርብ ነበር። በኋላም ጌሪ፣ ካረን የምትባል ደስ የምትል መንፈሳዊ እህት ያገባ ሲሆን እነሱም አብረናቸው እንድንኖር ሐሳብ አቀረቡልን። በመሆኑም ከተወሰኑ ወራት በኋላ ሁላችንም፣ እኔና አርነ እንኖርበት ከነበረው ቦታ ጥቂት ርቆ ወደሚገኝ አንድ ቤት ተዛውረን መኖር ጀመርን።

አርነ የመጨረሻዎቹን 18 ወራት የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ያሳለፈ ሲሆን የማያቋርጥ እንክብካቤም ያስፈልገው ነበር። በአብዛኛው ቤት ስለምውል በየቀኑ፣ መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማጥናት ሁለት ሰዓት ያህል አሳልፍ ነበር። በዚህ ወቅት ያለሁበትን ሁኔታ መቋቋም የምችልበትን መንገድ የሚጠቁሙ በርካታ ጥበብ ያዘሉ ምክሮችን አግኝቻለሁ። በተጨማሪም በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ አረጋውያን ቤት ድረስ መጥተው በመጠየቅ ፍቅራቸውን አሳይተውኛል፤ አንዳንዶቹ ተመሳሳይ መከራ ያሳለፉ ናቸው። በእርግጥም ሊጠይቁን መምጣታቸው መንፈሴ እንዲታደስ አድርጓል! አርነ በትንሣኤ ላይ ያለውን ጠንካራ እምነት እንደያዘ ሚያዝያ 2003 በሞት አንቀላፋ።

ከሁሉ የሚበልጠው የድጋፍ ምንጭ

ወጣት ሳለሁ ከእውነታው የራቀ አስተሳሰብ ነበረኝ። ይሁን እንጂ አንዳንዴ የሕይወት አቅጣጫችን እኛ ካሰብነው ውጪ ሊሆን እንደሚችል ተገነዘብኩ። በአንድ በኩል ዘርዝሬ የማልጨርሳቸው በረከቶችን ባገኝም በሌላ በኩል ደግሞ ሁለት ከባድ መከራዎች ደርሰውብኛል፤ አንደኛውን የትዳር ጓደኛዬ ታማኝነቱን በማጓደሉ ሌላኛውን ደግሞ በበሽታ ምክንያት አጥቻለሁ። በዚህ ሁሉ ጊዜ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ምክርና መጽናኛ አግኝቻለሁ። ያም ቢሆን ከሁሉ የሚበልጥ የድጋፍ ምንጭ የሆነኝ “በዘመናት የሸመገለው” ይሖዋ አምላክ ነው። (ዳን. 7:9 የ1954 ትርጉም) ምክሩ በባሕርዬ ላይ ለውጥ እንዳደርግ የረዳኝ ሲሆን ይህም በሚስዮናዊነት ሥራ አስደሳች ተሞክሮዎችን እንዳገኝ አስችሎኛል። ችግሮች ሲያጋጥሙኝ ‘የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ደግፎ ያቆመኛል፤ እንዲሁም ማጽናናቱ ነፍሴን ደስ ያሰኛታል።’ (መዝ. 94:18, 19 NW) በተጨማሪም ከቤተሰቤ ብሎም ‘ለክፉ ቀን ከተወለዱ ወዳጆቼ’ ፍቅርና ድጋፍ አግኝቻለሁ። (ምሳሌ 17:17) ከእነዚህ ወዳጆቼ መካከል ብዙዎቹ ጥበበኛና በዕድሜ ከእኔ የሚበልጡ ነበሩ።

“ጥበብ ያለው በአረጋውያን ዘንድ አይደለምን? ማስተዋልስ ረጅም ዕድሜ ባላቸው ዘንድ አይገኝምን?” በማለት ኢዮብ ጠይቆ ነበር። (ኢዮብ 12:12) ካሳለፍኩት ሕይወት በመነሳት ለዚህ ጥያቄ ‘አዎን’ የሚል መልስ መስጠት እችላለሁ። በዕድሜ የሚበልጡኝ ጥበበኛ ሰዎች የሰጡኝ ምክር ረድቶኛል፤ የእነሱ ማጽናኛ ደግፎኛል እንዲሁም ወዳጅነታቸው የተሻለ ሕይወት እንድመራ አድርጎኛል። ከእነሱ ጋር በመቀራረቤ አመስጋኝ ነኝ።

አሁን 80 ዓመቴ ሲሆን እኔ ራሴ አረጋዊ ከሚባሉት መካከል አንዷ ሆኛለሁ። በሕይወቴ ውስጥ ያሳለፍኩት ነገር ለሌሎች አረጋውያን ለየት ያለ ትኩረት እንድሰጥ አድርጎኛል። አሁንም ቢሆን እነሱን መጠየቅና መርዳት እወዳለሁ። እርግጥ ነው ከወጣቶች ጋር መሆንም ያስደስተኛል። የእነሱ ጥንካሬ ሌሎችን ለሥራ የሚያነሳሳ ሲሆን ቅንዓታቸውም የሚጋባ ነው። ምክርና ማበረታቻ ለማግኘት ወደ እኔ የሚመጡትን ወጣቶች መርዳት በመቻሌ ትልቅ እርካታ ይሰማኛል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 የኤልቨ ወንድም ፍራንክ ላምበርት በአውስትራሊያ ገጠራማ አካባቢ ቀናተኛ አቅኚ ሆኖ አገልግሏል። የ1983 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 110-112 ላይ እሱ ካደረጋቸው ብዙ አስደናቂ የስብከት ጉዞዎች ውስጥ አንዱን ይተርካል።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በነራንድረ ከጆይ ሌኖክስ ጋር በአቅኚነት ስታገለግል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤልቨ በ1960 ከስዊዘርላንድ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ጋር

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አርነ ታሞ ሳለ ስትንከባከበው