በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠንቀቁ’

‘ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠንቀቁ’

‘ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠንቀቁ’

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ከፈሪሳውያን እርሾ ይኸውም ከግብዝነት ተጠንቀቁ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷቸው ነበር። (ሉቃስ 12:1) ማቴዎስ ከጻፈው ተመሳሳይ ዘገባ መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ያወገዘው የፈሪሳውያንን “ትምህርት” ነው።​—ማቴ. 16:12

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “እርሾ” የሚለው ቃል አንዳንድ ጊዜ ብክለትን ለማመልከት ተሠርቶበታል። የፈሪሳውያን ትምህርትም ሆነ ዝንባሌ በብዙዎች ላይ በካይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ጥርጥር የለውም። የፈሪሳውያን ትምህርት አደገኛ የነበረው ለምንድን ነው?

1 ፈሪሳውያን ራሳቸውን እንደ ጻድቃን በመቁጠር ይኩራሩና ተራውን ሕዝብ በንቀት ይመለከቱ ነበር።

ይህ ራስን የማመጻደቅ ዝንባሌ ኢየሱስ በተናገረው አንድ ምሳሌ ላይ ተገልጿል። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ፈሪሳዊው ቆሞ በልቡ እንዲህ ሲል ይጸልይ ጀመር:- ‘አምላክ ሆይ፣ እንደ ሌሎች ሰዎች ቀማኛ፣ ዓመፀኛ፣ አመንዝራ፣ በተለይ ደግሞ እንደዚህ ቀረጥ ሰብሳቢ ስላላደረግከኝ አመሰግንሃለሁ። በሳምንት ሁለቴ እጾማለሁ፣ ከማገኘውም ነገር ሁሉ አሥራት አወጣለሁ።’ ቀረጥ ሰብሳቢው ግን ራቅ ብሎ ቆመ፤ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ለማየትም እንኳ አልደፈረም፤ ከዚህ ይልቅ ‘አምላክ ሆይ፣ እኔን ኃጢአተኛውን ምሕረት አድርግልኝ’ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።”​—ሉቃስ 18:11-13

ኢየሱስ ቀረጥ ሰብሳቢው ያሳየውን የትሕትና መንፈስ በማሞገስ እንዲህ ብሏል፦ “እላችኋለሁ፣ ከዚያኛው ሰው ይልቅ ይኼኛው ሰው ይበልጥ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ምክንያቱም ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ግን ከፍ ይደረጋል።” (ሉቃስ 18:14) ምንም እንኳ ቀረጥ ሰብሳቢዎች የሚታወቁት በማጭበርበር ተግባራቸው ቢሆንም ኢየሱስ ከእነሱ መካከል እሱን ለማዳመጥ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት ፈቃደኛ ነበር። ቢያንስ ሁለት ቀረጥ ሰብሳቢዎች ማለትም ማቴዎስና ዘኬዎስ የእሱ ተከታዮች ሆነዋል።

አምላክ በሰጠን ችሎታዎች ወይም መብቶች አሊያም ሌሎች ባላቸው ጉድለትና ድክመት የተነሳ ከእነሱ እንደምንሻል አድርገን የምናስብ ብንሆንስ? እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ቶሎ ብለን ከአእምሯችን ማውጣት ይኖርብናል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም፣ ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም፣ ተገቢ ያልሆነ ምግባር አያሳይም፣ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም፣ አይበሳጭም። ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም። ፍቅር በዓመፅ አይደሰትም፤ ከዚህ ይልቅ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል።”​—1 ቆሮ. 13:4-6

በመሆኑም የሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል። ጳውሎስ፣ “ክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም” እንደመጣ ከጠቀሰ በኋላ “ከኃጢአተኞች ደግሞ እኔ ዋነኛ ነኝ” ብሏል።​—1 ጢሞ. 1:15

ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች፦

ኃጢአተኛ እንደሆንኩና መዳኔ የተመካው በይሖዋ ጸጋ ላይ እንደሆነ እገነዘባለሁ? ወይስ ለረጅም ዓመታት በታማኝነት ማገልገሌ፣ በአምላክ ድርጅት ውስጥ መብት ማግኘቴ ወይም የተፈጥሮ ችሎታዬ ራሴን ከሌሎች የተሻልኩ እንደሆንኩ አድርጌ እንድቆጥር አድርጎኛል?

2 ፈሪሳውያን ጽድቃቸውን በሕዝብ ፊት በማሳየት ሌሎችን ለማስደመም ይጥሩ ነበር። የከበሬታ ቦታና የሚያሞካሹ የማዕረግ ስሞችን ማግኘት ይፈልጉ ነበር።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል፦ “ማንኛውንም ነገር የሚያደርጉት በሰዎች ለመታየት ብለው ስለሆነ ትልቅ ክታብ ያስራሉ፤ የልብሳቸውንም ዘርፍ ያስረዝማሉ። በራት ግብዣ ላይ የክብር ቦታ ማግኘት፣ በምኩራብ ደግሞ ከፊት መቀመጥ ይወዳሉ፤ በገበያ ቦታም ሰዎች እጅ እንዲነሷቸው ይፈልጋሉ እንዲሁም ረቢ ተብለው መጠራት ይሻሉ።” (ማቴ. 23:5-7) እስቲ ይህን የፈሪሳውያን ዝንባሌ ኢየሱስ ካሳየው ባሕርይ ጋር ለማወዳደር ሞክር። ኢየሱስ ፍጹም የሆነ የአምላክ ልጅ ቢሆንም እንኳ ትሑት ነበር። አንድ ሰው “ጥሩ” መምህር ብሎ በጠራው ጊዜ ኢየሱስ “ለምን ጥሩ ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም” ብሎታል። (ማር. 10:18) በሌላ ወቅት ደግሞ ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ትሕትና በማሳየት ረገድ ለተከታዮቹ ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል።​—ዮሐ. 13:1-15

አንድ እውነተኛ ክርስቲያን የእምነት አጋሮቹን ማገልገል ይኖርበታል። (ገላ. 5:13) በተለይ ደግሞ በጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት የሚጣጣሩ ወንድሞች ሌሎችን የሚያገለግሉ መሆን አለባቸው። “የበላይ ተመልካች ለመሆን” መጣጣራቸው ተገቢ ቢሆንም እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው ግን ሌሎችን ለመርዳት ያላቸው ፍላጎት መሆን ይገባዋል። አንድ ሰው የበላይ ተመልካች የሚሆነው ክብር ወይም ሥልጣን ለማግኘት ብሎ መሆን የለበትም። የበላይ ተመልካች በመሆን የሚያገለግሉ ወንድሞች ልክ እንደ ኢየሱስ ‘በልባቸው ትሑት’ መሆን ያስፈልጋቸዋል።​—1 ጢሞ. 3:1, 6፤ ማቴ. 11:29

ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች፦

የክብር ቦታ ወይም ተጨማሪ መብቶችን ለማግኘት በማሰብ በጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ላላቸው ወንድሞች የማድላት አዝማሚያ ይታይብኛል? ከአምልኮ ጋር በተያያዘ በዋነኝነት ለመሥራት የምመርጠው በሌሎች ዓይን ውስጥ እንድገባና ሙገሳ እንዳገኝ የሚያደርጉኝን ሥራዎች ነው? ከሌሎች ልቄ ለመታየት እሞክራለሁ?

3 የፈሪሳውያን ሕጎችና ወጎች ተራው ሕዝብ የሙሴን ሕግ በሥራ ላይ ማዋል ሸክም እንዲሆንበት አድርገው ነበር።

የሙሴ ሕግ፣ እስራኤላውያን ይሖዋን እንዴት ማምለክ እንዳለባቸው ጠቅለል ያለ ግንዛቤ የሚሰጥ ነበር። ይሁን እንጂ ለእያንዳንዱ ነገር ዝርዝር ደንቦች አልተሰጡም። ለምሳሌ ያህል፣ ሕጉ በሰንበት መሥራትን ቢከለክልም ሥራ የሚባለው ነገር ምን ነገሮችን እንደሚያጠቃልል በዝርዝር አልገለጸም። (ዘፀ. 20:10) ፈሪሳውያን ሕጉ ክፍተት እንዳለው አድርገው በማሰባቸው የራሳቸውን ትርጓሜ መስጠት እንዲሁም የተለያዩ ሕጎችንና ወጎችን ማካተት ጀመሩ። ኢየሱስ ፈሪሳውያን ያወጧቸውን ሕጎች ባይጠብቅም የሙሴን ሕጎች መፈጸም ችሏል። (ማቴ. 5:17, 18፤ 23:23) ሕጉ የተሰጠበት ምክንያት ምን እንደሆነ ገብቶት ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ከሕጉ በስተጀርባ ያለው መንፈስ ምን እንደሆነ ስለተረዳ ምሕረትና ርኅራኄ ማሳየት አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቧል። ተከታዮቹ እሱን የሚያሳዝኑ ነገሮች በሚያደርጉበት ጊዜም ጭምር ምክንያታዊ መሆኑን አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በተያዘበት ምሽት ሦስቱን ሐዋርያት እንዳያንቀላፉና ነቅተው እንዲጠብቁ ቢያሳስባቸውም በተደጋጋሚ ወደ እነሱ ሲመጣ እንቅልፍ ጥሏቸው አገኛቸው። ይሁን እንጂ ሁኔታቸውን በመረዳት “መንፈስ ዝግጁ ነው፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው” በማለት ተናገረ።​—ማር. 14:34-42

ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች፦

ምክንያታዊ ያልሆኑና የማያፈናፍኑ ደንቦችን ለማውጣት ወይም በራሴ አመለካከት ትክክል መስሎ የታየኝን ነገር እንዲያደርጉ ሌሎችን ለመጫን እሞክራለሁ? ከሌሎች በምጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ነኝ?

እስካሁን እንደተመለከትነው በኢየሱስና በፈሪሳውያን ትምህርት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። ታዲያ ማሻሻያ ልታደርግባቸው የሚገቡ ነጥቦችን አገኘህ? ከሆነ እነዚህን ማሻሻያዎች ለማድረግ ለምን ቁርጥ ውሳኔ አታደርግም?

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፈሪሳውያን በግንባራቸውና በግራ ክንዳቸው ላይ ክታብ ማለትም የሕጉን አራት ክፍሎች የያዘ ትንሽ ማኅደር ያስሩ ነበር።​—ማቴ. 23:2, 5 የግርጌ ማስታወሻ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከትዕቢተኞቹ ፈሪሳውያን በተለየ መልኩ ትሑት የሆኑ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሌሎችን ያገለግላሉ

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልክ እንደ ኢየሱስ፣ ከሌሎች በምትጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ነህ?