በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከታሪክ ማኅደራችን

“የኮልፖርተርነት ሥራዬን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየወደድኩት ሄጃለሁ”

“የኮልፖርተርነት ሥራዬን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየወደድኩት ሄጃለሁ”

በ1886፣ አንድ መቶ የሚሆኑ ሚሌኒያል ዶውን፣ ጥራዝ 1 የተባለው መጽሐፍ ቅጂዎች ወደ ቺካጎ እንዲላኩ አሌጌኒ፣ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ይገኝ ከነበረው የድርጅቱ ቢሮ ተጭነው ወጡ። ቻርልስ ቴዝ ራስል ይህን አዲስ ጥራዝ በመጻሕፍት መሸጫ መደብሮች አማካኝነት ለማሰራጨት ተስፋ አድርጎ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ ሃይማኖታዊ መጻሕፍትን ከሚያሰራጩ ትላልቅ ድርጅቶች መካከል አንዱ ጭነቱን ለመረከብ ተስማማ። ከሁለት ሳምንት በኋላ ግን ሙሉው ጭነት ወደ ድርጅቱ ቢሮ ተመላሽ ሆነ።

በወቅቱ አንድ እውቅ የሆነ ወንጌላዊ ሚሌኒያል ዶውን ከእሱ መጻሕፍት ጎን ተደርድሮ በማየቱ በጣም ተበሳጭቶ ነበር። መጽሐፉ ከመደርደሪያው ላይ ካልተነሳ እሱም ሆነ ዝነኛ የኢቫንጀሊካን ተከታይ የሆኑ ጓደኞቹ በሙሉ መጽሐፎቻቸውን በመውሰድ ንግዳቸውን ወደሌላ ቦታ እንደሚያዘዋውሩ ዛተ። አከፋፋዩ ቅር እያለው ሚሌኒያል ዶውን የተባለውን መጽሐፍ መለሰ። በተጨማሪም ሰዎች መጽሐፉን እንዲያነቡ ጋዜጦች ላይ ማስታወቂያዎች ወጥተው ነበር። ይሁንና ተቃዋሚዎች የማስታወቂያው ኮንትራት እንዲሰረዝ አደረጉ። ታዲያ ይህ አዲስ መጽሐፍ ለእውነት ፈላጊዎች የሚደርሰው እንዴት ነው?

ይህን ለማድረግ ኮልፖርተሮችን መጠቀም ቁልፍ ሆኖ ተገኘ። * በ1881 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ ማኅበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የሚያሰራጩ 1,000 የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች እንደሚያስፈልጉ ጥሪ አስተላለፈ። ኮልፖርተሮቹ ከጥቂት መቶዎች የማይበልጡ ቢሆኑም የእውነትን ዘር በጽሑፎች አማካኝነት በስፋት አሰራጭተዋል። በ1897 ወደ አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚሆን ሚሌኒያል ዶውን በሰዎች እጅ የገባ ሲሆን አብዛኛውን ያሰራጩት ኮልፖርተሮች ናቸው። ብዙዎቹ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩት የመጠበቂያ ግንብ ኮንትራት በማስገባትና መጽሐፍትን በማበርከት በሚያገኙት አነስተኛ የወጪ መተኪያ ነበር።

ኮልፖርተር ሆነው የሚያገለግሉት ምን ዓይነት ሰዎች ነበሩ? ከእነዚህ ደፋር ሰባኪዎች መካከል አንዳንዶቹ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ አዋቂዎች ነበሩ። ብዙዎቹ ኮልፖርተሮች ያላገቡ ወይም ልጆች ያልነበሯቸው ባለትዳሮች ሲሆኑ ጥቂት የማይባሉ ቤተሰቦችም በዚህ ሥራ ተካፍለዋል። መደበኛ ኮልፖርተሮች ረዘም ያለ ሰዓት ሲሠሩ ጊዜያዊ ኮልፖርተሮች ደግሞ በየቀኑ አንድ ወይም ሁለት ሰዓት ያገለግሉ ነበር። ሆኖም ኮልፖርተር ለመሆን ሁኔታውና ጤንነቱ የሚፈቅድለት ሁሉም ሰው አልነበረም። ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው ግን ኮልፖርተር ለመሆን “በጣም የተማሩና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው መሆን ወይም በመላእክት ልሳን መናገር” እንደማይጠበቅባቸው በ1906 በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተነገረ።

በሁሉም አህጉራት ማለት ይቻላል ተራ የሆኑ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ሥራ ማከናወን ችለዋል። አንድ ወንድም በሰባት ዓመት ውስጥ ወደ 15,000 ገደማ የሚሆኑ መጻሕፍትን እንዳበረከተ ተናግሯል። ቢሆንም ይህ ወንድም “ኮልፖርተር የሆንኩት መጽሐፍ ለመሸጥ ሳይሆን ስለ ይሖዋና ስለ እውነት ለመመሥከር ነው” ብሏል። ኮልፖርተሮች በሄዱበት ሁሉ የሚዘሩት የእውነት ዘር ሥር ይሰድ ስለነበር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድን እየበዛ መጣ።

ቀሳውስት ኮልፖርተሮቹን መጽሐፍ አዟሪዎች በማለት በንቀት ይጠሯቸው ነበር። በ1892 የታተመ መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ወጥቶ ነበር፦ “[ኮልፖርተሮች] እውነተኛ የጌታ ወኪሎች መሆናቸውን የሚያውቁት ወይም ጌታ ትሕትናቸውንና የሚከፍሉትን መሥዋዕትነት በማየት እንዳከበራቸው የሚገነዘቡት ብዙ ሰዎች አይደሉም።” አንድ ኮልፖርተር እንደተናገረው የእነዚህ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሕይወት አልጋ ባልጋ አልነበረም። በአብዛኛው በእግራቸው ስለሚጓዙ ጠንካራ ጫማ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ብስክሌትም ይጠቀሙ ነበር። ገንዘብ በማይኖራቸው ጊዜ መጻሕፍትን በምግብ ይለውጡ ነበር። ቀኑን ሙሉ ሲያገለግሉ ከዋሉ በኋላ የድካም ስሜት ቢኖራቸውም ደስተኞች ሆነው ወደ ድንኳኖቻቸውና ወደ ተከራይዋቸው ቤቶች ይመለሳሉ። ከጊዜ በኋላ ግን እንደ ቤት ሆነው እንዲያገለግሉ አድርገው በቀየሯቸው ሠረገላዎች መጠቀም በመጀመራቸው ጊዜያቸውንም ሆነ ገንዘባቸውን ማዳን ችለዋል። *

በ1893 በቺካጎ ከተካሄደው የአውራጃ ስብሰባ ጀምሮ ለኮልፖርተሮች ተብለው የሚዘጋጁ ልዩ ፕሮግራሞች እንዲህ ባሉ ስብሰባዎች ላይ መቅረብ ጀመሩ። በእነዚህ ፕሮግራሞች ላይ የተሞክሮዎች ልውውጥ ይደረግ እንዲሁም የተለያዩ የስብከት ዘዴዎችና ተግባራዊ የሆኑ ምክሮች ይቀርቡ ነበር። በአንድ ወቅት ወንድም ራስል እነዚህ ትጉህ ሰባኪዎች ጥሩ ቁርስ እንዲበሉ እንዲሁም ረፋድ ላይ አንድ ብርጭቆ ወተት፣ ሞቃት በሆነ ቀን ደግሞ ቀዝቃዛ ነገር እንዲጠጡ መክሯቸው ነበር።

የአገልግሎት ጓደኛ የሚፈልጉ ኮልፖርተሮች በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ቢጫ ሪባን ያደርጉ ነበር። አዳዲስ ኮልፖርተሮች ልምድ ካላቸው ጋር ይቀናጁ ነበር። አዳዲሶች በዚህ መልክ ሥልጠና ማግኘታቸው አስፈላጊ ነበር። አንዲት አዲስ ኮልፖርተር ያደረገችው ነገር የዚህን እውነተኝነት ይጠቁማል፤ ይህች እህት ከመደንገጧ የተነሳ የያዘቻቸውን ጽሑፎች ለቤቱ ባለቤት ስታስተዋውቅ “እነዚህን መጻሕፍት አትፈልጊያቸውም አይደል?” ብላ ነበር። ደስ የሚለው ግን የቤቱ ባለቤት መጽሐፎቹን መውሰድ ፈለገች፤ ከጊዜ በኋላም ይህች ሴት እህታችን ሆናለች።

አንድ ወንድም ‘አሁን ያለኝን ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ሳላቆም በየዓመቱ ለስብከቱ ሥራ 1,000 የአሜሪካ ዶላር መዋጮ ባደርግ ይሻላል ወይስ ኮልፖርተር ብሆን?’ የሚለው ነገር አሳስቦት ነበር። ጌታ ሁለቱንም በአድናቆት ቢቀበልም ጊዜውን ቢሰጥ ግን የበለጠ በረከት እንደሚያገኝ ለዚህ ወንድም ተነገረው። በሌላ በኩል ሜሪ ሂንድስ ኮልፖርተር መሆን “ለበርካታ ሰዎች መልካም ነገር ለማድረግ የሚያስችላት ከሁሉ የተሻለ መንገድ” እንደሆነ ተገንዝባ ነበር። አልበርተ ክሮስቢ የተባለች አንዲት ዓይናፋር እህት ደግሞ “የኮልፖርተርነት ሥራዬን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየወደድኩት ሄጃለሁ” ብላለች።

ዛሬም የእነዚህ ቀናተኛ ኮልፖርተሮች ሥጋዊና መንፈሳዊ ልጆች ብሎም የልጅ ልጆቻቸው መንፈሳዊ ውርሻቸውን እንደጠበቁ ናቸው። በቤተሰብህ የዘር ሐረግ ውስጥ ኮልፖርተር ወይም አቅኚ የሆነ ሰው ከሌለ አቅኚ በመሆን በቤተሰብህ ውስጥ አዲስ ታሪክ ለመጀመር ለምን ጥረት አታደርግም? አንተም የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን እያደር መውደድህ አይቀርም።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 በወቅቱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ይጠሩበት የነበረው “ኮልፖርተር” የሚለው ቃል ከ1931 ጀምሮ “አቅኚ” በሚለው ተተክቷል።

^ አን.8 ኮልፖርተሮች ይጠቀሙባቸው ስለነበሩት እንደ ቤት ሆነው የሚያገለግሉ ሠረገላዎች ዝርዝር ሐሳብ ወደፊት በሚወጣ እትም ላይ ይቀርባል።

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በጣም የተማሩና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው መሆን ወይም በመላእክት ልሳን መናገር” አይጠበቅባቸውም

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኮልፖርተር አልፍሬድ ዊንፍሬድ ኦሴ በጋና፣ በ1930 አካባቢ

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከላይ፦ ኮልፖርተር ኤዲት ኪን እና ገርትሩድ ሞሪስ በእንግሊዝ በ1918 አካባቢ፤ ከታች፦ ስታንሊ ኮሳቡም እና ሄንሪ ኖንክስ፣ ያበረከቷቸውን መጻሕፍት ይዘውባቸው ከነበሩ ባዶ ካርቶኖች ጋር በዩናይትድ ስቴትስ