በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋን ክብር እያንጸባረቃችሁ ነው?

የይሖዋን ክብር እያንጸባረቃችሁ ነው?

የይሖዋን ክብር እያንጸባረቃችሁ ነው?

“የይሖዋን ክብር እንደ መስተዋት [እናንጸባርቃለን]።”​—2 ቆሮ. 3:18

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ የይሖዋን ክብር ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?

መጸለይና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የይሖዋን ክብር ለማንጸባረቅ የሚረዱን እንዴት ነው?

የይሖዋን ክብር ማንጸባረቃችንን ለመቀጠል ምን ሊረዳን ይችላል?

1, 2. የይሖዋን ባሕርያት ማንጸባረቅ እንችላለን ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?

ሁላችንም ወላጆቻችንን የምንመስልበት አንድ ነገር አይጠፋም። ከዚህ አንጻር ሰዎች አንድን ልጅ ‘ቁርጥ አባትህን ትመስላለህ’ ወይም አንዲትን ልጅ ‘በእናቷ ነው የወጣችው’ ቢሉ የሚገርም አይደለም። ብዙ ጊዜ ልጆች ወላጆቻቸው ላይ የሚያዩትን ነገር ማድረግ ይቀናቸዋል። እኛስ፣ የሰማዩን አባታችንን ይሖዋን መምሰል እንችላለን? ይሖዋን አይተነው ባናውቅም እንኳ የአምላክን ቃል ማጥናት፣ ፍጥረታቱን መመልከት፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በተለይ ደግሞ የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገራቸውና ባደረጋቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን የይሖዋን ግሩም ባሕርያት ለመገንዘብ ይረዳናል። (ዮሐ. 1:18፤ ሮም 1:20) በመሆኑም የይሖዋን ክብር ማንጸባረቅ እንችላለን።

2 አምላክ አዳምንና ሔዋንን ከመፍጠሩ በፊትም እንኳ የሰው ልጆች ፈቃዱን ማድረግ፣ ባሕርያቱን ማንጸባረቅ እንዲሁም ለእሱ ክብር ማምጣት እንደሚችሉ ያውቅ ነበር። (ዘፍጥረት 1:26, 27ን አንብብ።) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የፈጣሪያችንን ባሕርያት ማንጸባረቅ ይኖርብናል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ባሕላችን፣ የትምህርት ደረጃችን እንዲሁም ዘራችን ምንም ይሁን ምን የአምላክን ክብር የማንጸባረቅ መብት ይኖረናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አምላክ አያዳላም፤ “ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”​—ሥራ 10:34, 35

3. ይሖዋን ማገልገል ምን ስሜት ይፈጥርብናል?

3 ቅቡዓን ክርስቲያኖች የይሖዋን ክብር ያንጸባርቃሉ። በመንፈስ የተወለደው ሐዋርያው ጳውሎስ “እኛ ሁላችንም ባልተሸፈነ ፊት የይሖዋን ክብር እንደ መስተዋት ስናንጸባርቅ ያንኑ መልክ ለመምሰል ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን” በማለት የጻፈው ለዚህ ነው። (2 ቆሮ. 3:18) ነቢዩ ሙሴ አሥርቱ ትእዛዛት የተጻፈባቸውን ጽላቶች ይዞ ከሲና ተራራ ሲወርድ ከይሖዋ ጋር ተነጋግሮ ስለነበር ፊቱ አብርቷል። (ዘፀ. 34:29, 30) ምንም እንኳ ክርስቲያኖች እንደ ሙሴ ዓይነት ሁኔታ ባያጋጥማቸውም ስለ ይሖዋ፣ ስለ ባሕርያቱና ለሰው ልጆች ስላለው አስደናቂ ዓላማ ለሌሎች በመናገር ፊታቸው በደስታ ሊያበራ ይችላል። በጥንት ዘመን፣ በደንብ እንዲያንጸባርቁ ተደርገው እንደሚሠሩ የብረት መስተዋቶች ቅቡዓኑና ምድራዊ ተስፋ ያላቸው አጋሮቻቸው በአኗኗራቸውና በአገልግሎታቸው የይሖዋን ክብር ያንጸባርቃሉ። (2 ቆሮ. 4:1) አንተስ፣ አምላክ የሚደሰትበትን ምግባር በማሳየትና አዘውታሪ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ በመሆን የይሖዋን ክብር እያንጸባረቅክ ነው?

የይሖዋን ክብር ማንጸባረቅ እንፈልጋለን

4, 5. (ሀ) እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛስ ምን ትግል አለብን? (ለ) ኃጢአት በእኛ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?

4 የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በምናደርገው ነገር ሁሉ የፈጣሪያችንን ክብር ማንጸባረቅ እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። ያም ቢሆን ብዙ ጊዜ እንደምንፈልገው አንሆንም። ጳውሎስ በዚህ ረገድ ትግል ማድረግ አስፈልጎት ነበር። (ሮም 7:21-25ን አንብብ።) ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ትግል ማድረግ ያስፈለገን ለምን እንደሆነ ሲገልጽ “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል” ብሏል። (ሮም 3:23) አዎን፣ የሰው ልጆች ከአዳም በወረሱት ኃጢአት የተነሳ ጨካኝ ለሆነው ‘ንጉሥ’ ማለትም ለኃጢአት እየተገዙ ነው።​—ሮም 5:12፤ 6:12

5 ለመሆኑ ኃጢአት ምንድን ነው? ከይሖዋ ባሕርይ፣ መንገድ፣ መሥፈርት እንዲሁም ፈቃድ ጋር የሚቃረን ማንኛውም ነገር ኃጢአት ነው። ስለዚህ ኃጢአት ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ያበላሽብናል። ዒላማውን እንዲስት የሚያደርገው ነገር እንዳጋጠመው አንድ ቀስተኛ እኛም ኃጢአት አምላክ ያወጣውን የአቋም ደረጃ እንዳናሟላ በማድረግ ዒላማችንን እንድንስት ያደርገናል። ሁላችንም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ኃጢአት እንሠራለን። (ዘኍ. 15:27-31) የሰው ልጆች ኃጢአት ከሚያሳድረው ተጽዕኖ መላቀቅ ስለማይችሉ ከፈጣሪያቸው ጋር ተቆራርጠዋል። (መዝ. 51:5፤ ኢሳ. 59:2፤ ቆላ. 1:21) በመሆኑም አብዛኛው የሰው ዘር ከይሖዋ የራቀ አኗኗር ስለሚከተል የእሱን ክብር የማንጸባረቅ ውድ መብቱን አጥቷል። የኃጢአትን ያህል በሰው ልጆች ላይ መጥፎ ውጤት ያስከተለ ነገር እንደሌለ ምንም ጥያቄ የለውም።

6. ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?

6 ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ ይሖዋ ‘ተስፋ ሰጥቶናል።’ (ሮም 15:13) ከኃጢአት ነፃ እንድንሆን የኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት አዘጋጅቶልናል። በዚህ መሥዋዕት እንደምናምን በተግባር በማሳየታችን “የኃጢአት ባሪያዎች” ከመሆን ተላቀናል፤ ይህ ደግሞ የይሖዋን ክብር ማንጸባረቅ እንድንችል አድርጎናል። (ሮም 5:19፤ 6:6፤ ዮሐ. 3:16) ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ይህን ዝምድና ጠብቀን መመላለሳችን በአሁኑ ጊዜ የይሖዋን በረከት ለማግኘት ዋስትና ይሆነናል፤ ወደፊት ደግሞ ፍጽምናን እንድንላበስና የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ያስችለናል። እኛ የሰው ልጆች ከኃጢአት ባርነት ገና ነፃ ያልወጣን ቢሆንም እንኳ አምላክ የእሱን ክብር ማንጸባረቅ እንደምንችል አድርጎ የሚመለከተን መሆኑ በእርግጥም ትልቅ በረከት ነው!

የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ

7. የአምላክን ክብር ለማንጸባረቅ ከፈለግን የትኛውን ሐቅ አምነን መቀበል ይኖርብናል?

7 የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ እንድንችል በመጀመሪያ ኃጢአተኞች እንደሆንን አምነን መቀበል ይኖርብናል። (2 ዜና 6:36) በመሆኑም የአምላክን ክብር በደንብ ማንጸባረቅ የምንችለው የኃጢአት ዝንባሌ እንዳለብን የምንገነዘብና ይህን ዝንባሌ ለመቆጣጠር ጥረት የምናደርግ ከሆነ ብቻ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የብልግና ምስሎችን የመመልከት አስጸያፊ ልማድ ካለን መንፈሳዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገን አምነን መቀበልና ይህን እርዳታ ለማግኘት መጣር ይኖርብናል። (ያዕ. 5:14, 15) ለአምላክ ክብር በሚያመጣ መንገድ ለመመላለስ ከፈለግን ልንወስደው የሚገባው የመጀመሪያ እርምጃ ይህ ነው። የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የእሱን የጽድቅ መሥፈርቶች እያሟላን እንደሆነ ለማወቅ በየጊዜው ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል። (ምሳሌ 28:18፤ 1 ቆሮ. 10:12) የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ ከፈለግን በውስጣችን ያለውን ማንኛውንም ዓይነት የኃጢአት ዝንባሌ ከመዋጋት ወደኋላ ማለት የለብንም።

8. ፍጹማን ባንሆንም እንኳ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

8 በዚህች ምድር ላይ ሙሉ በሙሉ አምላክን ያስደሰተውና የእሱን ክብር ያንጸባረቀው ኢየሱስ ብቻ ነው። እኛ ግን እንደ ኢየሱስ ፍጹማን አይደለንም። ያም ሆኖ የእሱን አርዓያ ለመከተል ጥረት ማድረግ እንችላለን፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 2:21) ይሖዋ የእሱን ክብር ከማንጸባረቅ ጋር በተያያዘ ምን ያህል እንደተሻሻልን ብቻ ሳይሆን በዚህ ረገድ የምናደርገውን ማንኛውንም ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከታል፤ ደግሞም ለእሱ ክብር ለማምጣት የምናደርገውን ልባዊ ጥረት መባረኩ አይቀርም።

9. መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተው ለመኖር የሚፈልጉ ክርስቲያኖችን የሚረዳቸው እንዴት ነው?

9 የይሖዋ ቃል የአምላክን ክብር በተሻለ ሁኔታ ማንጸባረቅ የምንችልባቸውን መንገዶች ይጠቁመናል። በመሆኑም ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥልቀት ማጥናትና ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል ወሳኝ ነገር ነው። (መዝ. 1:1-3) መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ አንዳንድ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ይረዳናል። (ያዕቆብ 1:22-25ን አንብብ።) የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ለእምነታችን መሠረት ከመሆኑም ባሻገር ከባድ ኃጢአቶችን ከመሥራት ለመቆጠብና ይሖዋን ለማስደሰት ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል።​—መዝ. 119:11, 47, 48

10. ጸሎት ይሖዋን በተሻለ መንገድ ለማገልገል የሚረዳን እንዴት ነው?

10 የአምላክን ክብር ለማንጸባረቅ የሚረዳን ሌላው ነገር ደግሞ ‘በጽናት መጸለይ’ ነው። (ሮም 12:12) ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ ለማገልገል የእሱን እርዳታ በጸሎት መጠየቅ እንችላለን፤ ይህን ማድረግም ይኖርብናል። በመሆኑም ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን፣ እምነታችንን እንዲያሳድግልን፣ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ እንዲሰጠን እንዲሁም “የእውነትን ቃል በአግባቡ [የመጠቀም]” ችሎታ እንዲኖረን እሱን በጸሎት መጠየቃችን ተገቢ ነው። (2 ጢሞ. 2:15፤ ማቴ. 6:13፤ ሉቃስ 11:13፤ 17:5) አንድ ልጅ በአባቱ እንደሚመካ ሁሉ እኛም በሰማይ በሚገኘው አባታችን በይሖዋ መተማመን ይኖርብናል። አምላክ፣ እሱን በተሻለ መንገድ ለማገልገል እንዲረዳን ብንጠይቀው ፈጽሞ እንደማያሳፍረን እርግጠኞች ነን። ይሖዋን እንዳስቸገርነው ሆኖ በፍጹም ሊሰማን አይገባም! ከዚህ ይልቅ በጸሎት አማካኝነት እሱን ማወደስና ማመስገን ይኖርብናል። እንዲሁም በማንኛውም ጊዜ በተለይ ደግሞ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የአምላክን አመራር እንፈልግ፤ በተጨማሪም ለቅዱስ ስሙ ክብር በሚያመጣ መንገድ እንድናገለግለው ይረዳን ዘንድ እንለምነው።​—መዝ. 86:12፤ ያዕ. 1:5-7

11. የጉባኤ ስብሰባዎች የአምላክን ክብር ለማንጸባረቅ የሚረዱን እንዴት ነው?

11 አምላክ ውድ የሆኑ በጎቹን እንዲንከባከብ ‘ለታማኝና ልባም ባሪያ’ አደራ ሰጥቶታል። (ማቴ. 24:45-47፤ መዝ. 100:3) የባሪያው ክፍል የእምነት ባልንጀሮቹ የይሖዋን ክብር የማንጸባረቃቸው ጉዳይ ያሳስበዋል። አንድ ልብስ ሰፊ፣ ይበልጥ አምረን እንድንታይ ልብሳችንን እንደሚያስተካክልልን ሁሉ ስብሰባዎችም ከክርስቲያናዊ ማንነታችን ጋር በተያያዘ ማስተካከያዎችን እንድናደርግ ይረዱናል። (ዕብ. 10:24, 25) እንግዲያው በስብሰባዎች ላይ በጊዜ ለመገኘት ጥረት እናድርግ፤ ምክንያቱም የማርፈድ ልማድ ካለን የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንን ለይቶ የሚያሳውቀውን ማንነታችንን ‘ለማስተካከል’ ከሚረዱን ስብሰባዎች የምናገኘው ጥቅም ይቀንሳል።

አምላክን እንምሰል

12. አምላክን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

12 የይሖዋን ክብር ለማንጸባረቅ ‘አምላክን መኮረጅ ይገባናል።’ (ኤፌ. 5:1) ይሖዋን ከምንመስልበት መንገድ አንዱ አመለካከታችንን ከእሱ አመለካከት ጋር ማስማማት ነው። እሱ ከሚፈልገው ውጪ ነገሮችን ማከናወን ለእሱ ክብር የማያመጣ ከመሆኑ በላይ እኛንም ይጎዳናል። በዙሪያችን ያለው ዓለም በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ስለሆነ ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች ለመጥላትና እሱ ለሚወዳቸው ነገሮች ጥልቅ ፍቅር ለማዳበር ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (መዝ. 97:10፤ 1 ዮሐ. 5:19) አምላክን ማገልገል የምንችልበት ብቸኛውና ትክክለኛው መንገድ ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር ማድረግ መሆኑን ከልባችን አምነን መቀበል ይኖርብናል።​—1 ቆሮንቶስ 10:31ን አንብብ።

13. ኃጢአትን መጥላት የሚኖርብን ለምንድን ነው? ይህስ ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

13 ይሖዋ ኃጢአትን ስለሚጠላ እኛም መጥላት ይኖርብናል። በእርግጥም፣ በተቻለ መጠን ከኃጢአት ለመራቅ መጣር ይገባናል፤ በኃጢአት ሳንሸነፍ እስከምን ድረስ መሄድ እንደምችል ለማየት በኃጢአት ዙሪያ ዳር ዳር ማለት የለብንም። ለምሳሌ፣ በክህደት እንዳንሸነፍ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው አካሄድ የአምላክን ክብር እንዳናንጸባርቅ ያደርገናል። (ዘዳ. 13:6-9) በመሆኑም ከከሃዲዎች ወይም ወንድም ነኝ እያለ የአምላክን ስም የሚያስነቅፍ አኗኗር ከሚከተል ማንኛውም ሰው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሊኖረን አይገባም። ይህን የሚያደርገው የቤተሰባችን አባል ቢሆንም እንኳ እንዲህ ካለው ሰው መራቅ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 5:11) ከሃዲዎችን ወይም የይሖዋን ድርጅት የሚተቹ ሰዎችን ተከራክረን ለመርታት መሞከሩ ምንም ፋይዳ የለውም። እንዲያውም በኢንተርኔትም ሆነ በጽሑፍ የሚያወጡትን ሐሳብ ማንበቡ መንፈሳዊ አደጋ የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ ተገቢ አይደለም።​—ኢሳይያስ 5:20ን እና ማቴዎስ 7:6ን አንብብ።

14. የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ምንድን ነው? ለምንስ?

14 በሰማይ ያለውን አባታችንን የምንመስልበት ዋነኛው መንገድ ፍቅር ማሳየት ነው። አዎን፣ እኛም እንደ እሱ አፍቃሪዎች መሆን ይገባናል። (1 ዮሐ. 4:16-19) እንዲያውም በመካከላችን ያለው ፍቅር የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትና የይሖዋ አገልጋዮች መሆናችንን ለይቶ ያሳውቃል። (ዮሐ. 13:34, 35) እርግጥ ነው፣ ከአዳም የወረስነው ኃጢአት ይህን እንዳናደርግ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ምንም ነገር ሳይበግረን በማንኛውም ጊዜ ፍቅርን ለማሳየት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ፍቅርን ጨምሮ ሌሎች አምላካዊ ባሕርያትን ማዳበራችን ደግነት የጎደላቸውን ነገሮች ከማድረግና ኃጢአት ከመፈጸም እንድንቆጠብ ይረዳናል።​—2 ጴጥ. 1:5-7

15. ፍቅር ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት የሚነካው እንዴት ነው?

15 ፍቅር ለሌሎች ሰዎች መልካም እንድናደርግ ይገፋፋናል። (ሮም 13:8-10) ለምሳሌ ለትዳር ጓደኛችን ያለን ፍቅር የጋብቻ መኝታ ከርኩሰት የጸዳ እንዲሆን ለማድረግ ማለትም አንዳችን ሌላው ታማኞች ለመሆን ያነሳሳናል። ለሽማግሌዎች ያለን ፍቅርና ለሥራቸው ያለን አክብሮት የሚሰጡንን መመሪያ ለመታዘዝና ለእነሱ ለመገዛት እንድንነሳሳ ያደርገናል። ልጆች፣ ለወላጆቻቸው ፍቅር ካላቸው እነሱን የሚታዘዟቸውና የሚያከብሯቸው ከመሆኑም ሌላ ስለ ወላጆቻቸው መጥፎ ነገር አይናገሩም። ለሰዎች ፍቅር ካለን ዝቅ አድርገን አንመለከታቸውም፤ ወይም አክብሮት በጎደለው መንገድ አናናግራቸውም። (ያዕ. 3:9) የአምላክን መንጋ የሚወዱ ሽማግሌዎች በጎቹን በርኅራኄ ይይዟቸዋል።​—ሥራ 20:28, 29

16. ፍቅር ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ የሚረዳን እንዴት ነው?

16 ፍቅር ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘም ጎልቶ መታየት የሚገባው ባሕርይ ነው። ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ካለን በአገልግሎት ላይ የሚያጋጥሙን ሰዎች በሚያሳዩት ግድ የለሽነት ወይም በሚሰጡት አሉታዊ ምላሽ ተስፋ አንቆርጥም። ከዚህ ይልቅ ምሥራቹን መስበካችንን እንቀጥላለን። ፍቅር ለአገልግሎታችን እንድንዘጋጅና ውጤታማ ለመሆን ጥረት እንድናደርግ ያነሳሳናል። አምላክንና ሰዎችን ከልብ የምንወድ ከሆነ የስብከቱ ሥራችንን እንደ ግዴታ አናየውም። እንዲያውም ይህን ኃላፊነታችንን እንደ ታላቅ መብት በመቁጠር በደስታ እናከናውነዋለን።​—ማቴ. 10:7

የይሖዋን ክብር ማንጸባረቃችሁን ቀጥሉ

17. የአምላክ ክብር እንደጎደለን መገንዘባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

17 አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ኃጢአትን የሚመለከተው አቅልሎ ነው፤ እኛ ግን እንደዚያ አናደርግም። ይህ ደግሞ የኃጢአት ዝንባሌያችንን መዋጋት እንዳለብን እንድንገነዘብ ያደርገናል። ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ እንዳለን መገንዘባችን ሕሊናችንን ለማሠልጠን ይረዳናል፤ ይህም በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ ኃጢአት እንድንሠራ የሚገፋፋ ስሜት ማቆጥቆጥ ሲጀምር ተገቢ እርምጃ እንድንወስድ ያነሳሳናል። (ሮም 7:22, 23) እርግጥ ደካሞች መሆናችን የታወቀ ነው፤ ሆኖም አምላክ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ትክክል የሆነውን ነገር እንድናደርግ ሊያጠነክረን ይችላል።​—2 ቆሮ. 12:10

18, 19. (ሀ) ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር የምናደርገውን ትግል በድል ለመወጣት ምን ሊረዳን ይችላል? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?

18 የይሖዋን ክብር ለማንጸባረቅ ከፈለግን ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር መዋጋትም ይኖርብናል። አምላክ የሰጠን መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ ይህን በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ያስችለናል። (ኤፌ. 6:11-13) ሰይጣን ለይሖዋ ብቻ የሚገባውን ክብር ለመውሰድ ያልተቋረጠ ጥረት ያደርጋል። በተጨማሪም ዲያብሎስ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማበላሸት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ይሁንና በሚሊዮን ከሚቆጠሩ የእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አብረን ሆነን ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችንና የይሖዋን ክብር ማንጸባረቃችን ለሰይጣን ትልቅ ሽንፈት ነው። እንግዲያው በሰማይ እንዳሉ መንፈሳዊ ፍጥረታት እኛም “ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ እንዲሁም ያሉትም ሆነ የተፈጠሩት በአንተ ፈቃድ ስለሆነ ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል” እያልን ይሖዋን ማወደሳችንን እንቀጥል።​—ራእይ 4:11

19 ምንም ይምጣ ምን የይሖዋን ክብር ማንጸባረቃችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ይሖዋ በርካታ ታማኝ አገልጋዮቹ፣ እሱን ለመምሰልና ክብሩን ለማንጸባረቅ የቻሉትን ያህል እንደሚጥሩ ሲመለከት እንደሚደሰት ምንም ጥርጥር የለውም። (ምሳሌ 27:11) “ጌታ አምላኬ ሆይ፤ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፤ ስምህንም ለዘላለም አከብራለሁ” በማለት እንደዘመረው እንደ ዳዊት ሊሰማን ይገባል። (መዝ. 86:12) የይሖዋን ክብር ፍጹም በሆነ መንገድ የምናንጸባርቅበትንና እሱን ለዘላለም የምናወድስበትን ቀን በታላቅ ጉጉት እንጠባበቃለን! በእርግጥም ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ይህን በረከት ማጨዳቸው የማይቀር ነው። ታዲያ በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ አምላክን ክብር እያንጸባረቅክ ነው? ለዘላለምስ ይህን ማድረግ ትፈልጋለህ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በእነዚህ መንገዶች የይሖዋን ክብር እያንጸባረቅክ ነው?