በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የጊዜና የወቅት’ አምላክ በሆነው በይሖዋ ታመኑ

‘የጊዜና የወቅት’ አምላክ በሆነው በይሖዋ ታመኑ

‘የጊዜና የወቅት’ አምላክ በሆነው በይሖዋ ታመኑ

“ጊዜንና ወቅትን ይለውጣል፤ ነገሥታትን በዙፋን ያስቀምጣል፣ ደግሞም ያወርዳቸዋል።”​—ዳን. 2:21

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

የፍጥረት ሥራዎችና ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች ይሖዋ የቀጠረውን ጊዜ በመጠበቅ ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ መሆኑን የሚያሳዩት እንዴት ነው?

ይሖዋ ‘የጊዜና የወቅት’ አምላክ መሆኑን ማወቃችን ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

የዓለም ሁኔታና የሰዎች እቅድ በይሖዋ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አይችሉም የምንለው ለምንድን ነው?

1, 2. ይሖዋ የጊዜን ምንነት በሚገባ እንደሚረዳ እንዴት ማወቅ እንችላለን?

ይሖዋ አምላክ ሰዎችን ከመፍጠሩ ከብዙ ዘመናት በፊት ጊዜን ለመለካት የሚረዱ ነገሮችን አዘጋጅቷል። አምላክ በአራተኛው የፍጥረት ቀን ላይ “ቀኑን ከሌሊት እንዲለዩ፣ የዓመት ወቅቶች፣ ቀናትና ዓመታት የሚጀምሩበትንም እንዲያመለክቱ፣ ለምድር ብርሃን የሚሰጡ ልዩ ልዩ ብርሃናት በሰማይ ይሁኑ” አለ። (ዘፍ. 1:14, 15, 19, 26) በእርግጥም ይህ የይሖዋ ፈቃድ በትክክል ተፈጽሟል።

2 ይሁንና አሁንም ቢሆን የሳይንስ ሊቃውንት ስለ ጊዜ ምንነት አንድ ዓይነት ድምዳሜ ላይ መድረስ አልቻሉም። አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ብሏል፦ “በዓለም ላይ ሚስጥራቸው ፈጽሞ ሊፈታ ካልቻሉ ነገሮች መካከል አንዱ ጊዜ ነው። ማንም ሰው ቢሆን ስለ ጊዜ ምንነት በትክክል ማብራሪያ መስጠት አይችልም።” ይሖዋ ግን ስለ ጊዜ ምንነት በሚገባ ያውቃል። ደግሞስ ‘ሰማያትን የፈጠረ፣ ምድርን ያበጃትና የሠራት’ እሱ አይደል? በተጨማሪም ይሖዋ “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ” ይናገራል። (ኢሳ. 45:18፤ 46:10) እስቲ የፍጥረት ሥራዎቹም ሆኑ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች ይሖዋ የቀጠረውን ጊዜ በመጠበቅ ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ መሆኑን የሚያሳዩት እንዴት እንደሆነ እንመልከት፤ ይህን ማወቃችን በይሖዋና በቃሉ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።

የፍጥረት ሥራዎች በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል

3. በጽንፈ ዓለም ውስጥ አስገራሚ የሆነ የጊዜ አጠባበቅ እንዳለ የሚያሳይ ምን ማስረጃ መጥቀስ እንችላለን?

3 በጽንፈ ዓለም ውስጥ፣ በዓይን በማይታዩትም ሆነ ግዙፍ በሆኑት ፍጥረታት ላይ አስገራሚ የሆነ የጊዜ አጠባበቅ ይስተዋላል። አተሞች የሚርገበገቡበት ፍጥነት ቋሚ ነው። የአተሞችን እርግብግቢት መሠረት ተደርገው የሚሠሩ ልዩ ሰዓቶች በ80 ሚሊዮን ዓመታትም እንኳ 1 ሴኮንድ ዝንፍ አይሉም። እንደ ፕላኔትና ከዋክብት ያሉ ግዙፍ የሰማይ አካላትም በሕዋ ውስጥ ጊዜያቸውንና ምሕዋራቸውን ጠብቀው ስለሚንቀሳቀሱ በምን ጊዜ የት ቦታ ላይ እንደሚገኙ አስቀድሞ በትክክል ማወቅ ይቻላል። ይህ ደግሞ ሰዎች ወቅቶችን ለመለየትና ጉዞ ሲያደርጉ አቅጣጫቸውን ለማወቅ አስችሏቸዋል። እንዲህ ያሉ ጊዜን ሳያዛንፉ የሚለኩ ነገሮችን የሠራው ይሖዋ በእርግጥም ‘በችሎታው ብርቱ’ ነው፤ በመሆኑም ውዳሴ ልናቀርብለት ይገባል።​—ኢሳይያስ 40:26ን አንብብ።

4. ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ የሚታየው የጊዜ አጠባበቅ የአምላክን ጥበብ የሚገልጸው እንዴት ነው?

4 ሕይወት ባላቸው ነገሮችም ላይ አስገራሚ የሆነ የጊዜ አጠባበቅ ይታያል። በብዙ እንስሳትም ሆነ ዕፅዋት ውስጥ የሕይወት እንቅስቃሴያቸውን የሚቆጣጠር ሰዓት አለ። አንዳንድ አእዋፍ መቼ ወደ ሌላ ቦታ መፍለስ እንዳለባቸው በደመ ነፍስ ያውቃሉ። (ኤር. 8:7) የሰው ልጆችም ቢሆኑ ቀኑንና ሌሊቱን ለመለየት የሚያስችላቸው ሰዓት በውስጣቸው አለ። አንድ ሰው ከፍተኛ የሰዓት ልዩነት ወዳለበት ቦታ በአውሮፕላን ቢጓዝ አእምሮው በአዲሱ አካባቢ ካለው ሰዓት ጋር ለመላመድ ጊዜ ይወስድበታል። በእርግጥም በፍጥረታት ላይ የጊዜ አጠባበቅ እንደሚታይ የሚጠቁሙ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፤ እነዚህ ምሳሌዎች ‘የጊዜና የወቅት’ አምላክ የሆነው ይሖዋ ጠቢብና ኃያል መሆኑን ያረጋግጣሉ። (መዝሙር 104:24ን አንብብ።) አዎን፣ የቀጠረውን ጊዜ በመጠበቅ ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ በጥበቡም ሆነ በኃይሉ አቻ የለውም። በመሆኑም ይሖዋ ዓላማውን ከግብ እንደሚያደርስ መተማመን እንችላለን!

ትንቢቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው መፈጸማቸው እምነታችንን ያጠናክርልናል

5. (ሀ) ስለ ሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ማወቅ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ የትኛው ነው? (ለ) ይሖዋ ወደፊት ስለሚከናወኑ ነገሮችና ስለሚፈጸሙበት ጊዜ በትክክል ትንቢት መናገር ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

5 ፍጥረት ‘ስለማይታዩት የይሖዋ ባሕርያት’ ብዙ የሚነግረን ነገር ቢኖርም ‘የሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው?’ እንደሚለው ላሉ አሳሳቢ ጥያቄዎች መልስ ሊሰጠን አይችልም። (ሮም 1:20) የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት የአምላክ ቃል የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስን ገጾች ማገላበጥ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስን ስንመረምር ጊዜያቸውን ጠብቀው የተፈጸሙ ትንቢቶችን እናገኛለን! ይሖዋ ወደፊት ስለሚከናወኑት ነገሮች ትንቢት መናገር የሚችለው ወደፊት የሚሆነውን ነገር በትክክል የማወቅ ችሎታ ስላለው ነው። በተጨማሪም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ትንቢቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚፈጸሙት ይሖዋ አምላክ ከዓላማውና ከእሱ የጊዜ ሰሌዳ ጋር በሚስማማ መንገድ ነገሮች እንዲከናወኑ ማድረግ ስለሚችል ነው።

6. ይሖዋ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን አፈጻጸም እንድንረዳ የሚፈልግ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?

6 ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች መረዳት እንዲችሉና ከእነሱ ጥቅም እንዲያገኙ ይፈልጋል። አምላክ ለጊዜ ያለው አመለካከት ከሰው ልጆች ፍጹም የተለየ ቢሆንም እንኳ አንድ ነገር የሚከናወንበትን ጊዜ አስቀድሞ የሚናገረው እኛ ልንረዳው በምንችለው መንገድ ነው። (መዝሙር 90:4ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ የራእይ መጽሐፍ “አራቱ መላእክት” አምላክ ለቀጠረው “ሰዓት፣ ቀን፣ ወርና ዓመት ተዘጋጅተው” እንደነበረ ይገልጻል፤ እዚህ ላይ የተገለጹት የጊዜ ክፍልፋዮች እኛ ልንረዳቸው የምንችላቸው ናቸው። (ራእይ 9:14, 15) ትንቢቶች የተቀጠረላቸውን ጊዜ ጠብቀው መፈጸማቸው ‘የጊዜና የወቅት’ አምላክ በሆነው በይሖዋና በቃሉ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። እስቲ በዚህ ረገድ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

7. ኤርምያስ ኢየሩሳሌምንና ይሁዳን አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት ይሖዋ የቀጠረውን ጊዜ እንደሚጠብቅ የሚያሳየው እንዴት ነው?

7 በመጀመሪያ፣ በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የተከናወነን አንድ ሁኔታ መለስ ብለን እንመልከት። “የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በነገሠ በአራተኛው ዓመት” የቀጠረውን ጊዜ በመጠበቅ ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ “ስለ ይሁዳ ሕዝብ ሁሉ” የተናገረው ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ። (ኤር. 25:1) ይሖዋ ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋና አይሁዳውያን ከይሁዳ ወደ ባቢሎን በግዞት እንደሚወሰዱ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። በዚያም “ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ።” ልክ እንደተባለውም የባቢሎን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን በ607 ዓ.ዓ. ያጠፋት ሲሆን አይሁዳውያንም ወደ ባቢሎን በግዞት ተወስደዋል። ሆኖም 70 ዓመቱ ሲያበቃ ምን ይከሰት ይሆን? ኤርምያስ እንዲህ የሚል ትንቢት ተናግሮ ነበር፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሰባው ዓመት የባቢሎን ቈይታችሁ በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፤ ወደዚህም ሥፍራ ልመልሳችሁ የገባሁላችሁን መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ።’” (ኤር. 25:11, 12፤ 29:10) ይህ ትንቢት በትክክለኛው ወቅት ላይ ማለትም በ537 ዓ.ዓ. ሜዶናውያንና ፋርሳውያን አይሁዳውያንን ነፃ ባወጡ ጊዜ ተፈጽሟል።

8, 9. ዳንኤል ስለ መሲሑ መገለጥና ስለ አምላክ መንግሥት መቋቋም የተናገራቸው ትንቢቶች ይሖዋ ‘የጊዜና የወቅት’ አምላክ መሆኑን የሚያሳዩት እንዴት ነው?

8 ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በተያያዘ የተፈጸመ ሌላ ትንቢት እንመልከት። አይሁዳውያን ከባቢሎን ከመውጣታቸው ከሁለት ዓመት በፊት ይሖዋ በነቢዩ ዳንኤል አማካኝነት አንድ ትንቢት አስነግሮ ነበር፤ በዚህ ትንቢት መሠረት ኢየሩሳሌምን ዳግመኛ ለመገንባት ትእዛዝ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ 483 ዓመታት ካለፉ በኋላ መሲሑ ይገለጣል። የሜዶ ፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌም እንድትገነባ ትእዛዝ የሰጠው በ455 ዓ.ዓ. ነበር። ይህ ከሆነ ከ483 ዓመታት በኋላ ማለትም በ29 ዓ.ም. የናዝሬቱ ኢየሱስ ተጠምቆ በመንፈስ ቅዱስ በተቀባ ጊዜ መሲሕ ሆነ። *​—ነህ. 2:1, 5-8፤ ዳን. 9:24, 25፤ ሉቃስ 3:1, 2, 21, 22

9 አሁን ደግሞ ቅዱሳን መጻሕፍት የአምላክን መንግሥት አስመልክተው በሚናገሩት ትንቢት ላይ ትኩረት እናድርግ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መሲሐዊው መንግሥት በ1914 በሰማይ እንደሚቋቋም ያመለክታሉ። ይህን ጊዜ ለማወቅ ከሚረዱን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት መንገዶች አንዱ የኢየሱስን መገኘት የሚጠቁመው “ምልክት” ነው፤ በዚያን ጊዜ ሰይጣን ከሰማይ ስለሚባረር በምድር ላይ ታላቅ ወዮታ እንደሚመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ማቴ. 24:3-14፤ ራእይ 12:9, 12) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “የአሕዛብ ዘመናት” የሚፈጸሙበትንና መንግሥቱ በሰማይ ላይ መግዛት የሚጀምርበትን ትክክለኛ ጊዜ አስቀድሞ ተናግሯል፤ ይህ ጊዜ ደግሞ 1914 ነው።​—ሉቃስ 21:24፤ ዳን. 4:10-17 *

10. ወደፊት የትኞቹ ነገሮች ጊዜያቸውን ጠብቀው እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

10 ኢየሱስ እንደተናገረው ከፊታችን “ታላቅ መከራ” ይጠብቀናል። ከዚያም የኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ይጀመራል። እነዚህ ነገሮች ጊዜያቸውን ጠብቀው እንደሚከናወኑ የምንጠራጠርበት ምንም ምክንያት የለም። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜም እንኳ ይሖዋ እነዚህ ነገሮች የሚከናወኑበትን “ቀንና ሰዓት” ወስኖ ነበር።​—ማቴ. 24:21, 36፤ ራእይ 20:6

“አመቺ የሆነውን ጊዜ ግዙ”

11. የምንኖረው በመጨረሻ ዘመን ውስጥ መሆኑን ማወቃችን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

11 የአምላክ መንግሥት መግዛት መጀመሩን እንዲሁም የምንኖረው ‘በፍጻሜው ዘመን’ ውስጥ መሆኑን ማወቃችን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል? (ዳን. 12:4) በርካታ ሰዎች የዓለም ሁኔታ እየተባባሰ እንደሄደ ቢመለከቱም እነዚህ ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻው ዘመን አስመልክቶ የተናገራቸው ትንቢቶች ፍጻሜ መሆናቸውን መቀበል አይፈልጉም። አንዳንዶች ይህ ሥርዓት አንድ ቀን እንደሚያከትምለት ያስባሉ፤ ሌሎች ደግሞ የሰው ልጆች የሚያደርጉት ጥረት በሆነ ወቅት ላይ “ሰላምና ደኅንነት” እንደሚያመጣ ተስፋ ያደርጋሉ። (1 ተሰ. 5:3) እኛስ ምን ይሰማናል? የምንኖረው የሰይጣን ዓለም ሊጠፋ በተቃረበበት የመጨረሻ ጊዜ ውስጥ መሆኑን እንገነዘባለን? ከሆነስ የቀረውን ጊዜ አምላክን ለማገልገልና ሌሎችም ‘የጊዜና የወቅት’ አምላክ የሆነውን ይሖዋን እንዲያውቁ ለመርዳት ልንጠቀምበት አይገባም? (2 ጢሞ. 3:1) በእርግጥም ጊዜያችንን ስለምንጠቀምበት መንገድ ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል።​—ኤፌሶን 5:15-17ን አንብብ።

12. ኢየሱስ የኖኅን ዘመን አስመልክቶ ከተናገረው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን?

12 ይህ ዓለም ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች የሞሉበት ስለሆነ “አመቺ የሆነውን ጊዜ” መግዛት ቀላል አይደለም። ኢየሱስ “በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል” ብሏል። በኖኅ ዘመን የነበረው ሁኔታ ምን ይመስላል? በዚያን ጊዜ የነበረው ዓለም እንደሚጠፋ ትንቢት ተነግሮ ነበር። በመሆኑም ክፉ ሰዎች የውኃ ጥፋት ተደቅኖባቸው ነበር። “የጽድቅ ሰባኪ የነበረው” ኖኅ በዘመኑ ለነበሩ ሰዎች የአምላክን መልእክት በታማኝነት አውጇል። (ማቴ. 24:37፤ 2 ጴጥ. 2:5) ሆኖም ሕዝቡ “ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር፤ የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም።” በመሆኑም ኢየሱስ ተከታዮቹን “የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሁኑ” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። (ማቴ. 24:38, 39, 44) እኛም እንደ ኖኅ እንጂ በዘመኑ እንደነበሩት ሰዎች መሆን አንፈልግም። ታዲያ ዝግጁ ለመሆን ምን ሊረዳን ይችላል?

13, 14. የሰው ልጅ መምጣትን በምንጠባበቅበት በአሁኑ ጊዜ አምላክን በታማኝነት እንድናገለግል የሚረዳን ስለ ይሖዋ ምን ነገር ማስታወሳችን ነው?

13 የሰው ልጅ የሚመጣው ባላሰብነው ሰዓት ቢሆንም ይሖዋ የቀጠረውን ጊዜ በመጠበቅ ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። የዓለም ሁኔታና የሰዎች እቅድ በይሖዋ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አይችሉም። ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም ሲል አንዳንድ ነገሮች እሱ በሚፈልገው ጊዜ እንዲከናወኑ ያደርጋል፤ እንዲሁም ክንውኖቹ የእሱ ፈቃድ እንዲፈጸም የሚያደርግ ውጤት እንዲኖራቸው ማድረግ ይችላል። (ዳንኤል 2:21ን አንብብ።) እንዲያውም ምሳሌ 21:1 “የንጉሥ ልብ በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ እርሱም እንደ ቦይ ውሃ ደስ ወዳሰኘው ይመራዋል” ይላል።

14 ይሖዋ ዓላማውን በቀጠረው ጊዜ ለመፈጸም ሲል ነገሮችን እሱ በፈለገው መንገድ ማስኬድ ይችላል። በዓለም ላይ የሚታዩ ጉልህ ለውጦች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ በር ከፍተዋል፤ በተለይ የአምላክ መንግሥት በዓለም ዙሪያ እንደሚሰበክ ከሚናገረው ትንቢት ጋር በተያያዘ የዚህን እውነተኝነት ማየት ይቻላል። የኮሚኒስት አገዛዝ በሰፈኑባቸው እንዲሁም አምባገነን የሆኑ መሪዎች በነበሩባቸው አገሮች የተከሰተውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን፤ በእነዚህ አገሮች የነበረው ሥርዓት በድንገት ተቀይሯል። በዓለም ላይ እንዲህ ያሉ ትላልቅ ፖለቲካዊ ለውጦች በዚህ ፍጥነት ይከሰታሉ ብሎ ያሰበ ሰው አልነበረም። በዚህም የተነሳ ምሥራቹ፣ ሥራችን ታግዶ በነበረባቸው በርካታ አገሮች ውስጥ በመሰበክ ላይ ነው። እንግዲያው ‘የጊዜና የወቅት’ አምላክ የሆነውን ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል አመቺ የሆነውን ጊዜ እንግዛ።

ይሖዋ የቀጠረውን ጊዜ እንደሚጠብቅ ያላችሁን እምነት አሳዩ

15. ድርጅቱ ከሚያደርጋቸው ማስተካከያዎች ጋር በተያያዘ እምነት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

15 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ ለመቀጠል ከፈለግን ይሖዋ የቀጠረውን ጊዜ እንደሚጠብቅ መተማመን ይኖርብናል። የዓለም ሁኔታ እየተለዋወጠ በመሆኑ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራችንም ላይ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ሊጠይቅብን ይችላል። ድርጅቱ፣ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን የምናከናውነውን ሥራ በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት እንድንችል አልፎ አልፎ ማስተካከያዎችን ያደርግ ይሆናል። ‘የጉባኤ ራስ’ በሆነው በኢየሱስ ሥር በታማኝነት የምናገለግል እንደመሆናችን መጠን እንደዚህ ያሉ ማስተካከያዎችን ሙሉ በሙሉ በመደገፍ ‘የጊዜና የወቅት’ አምላክ በሆነው በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለን እናሳያለን።​—ኤፌ. 5:23

16. ይሖዋ እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ከጎናችን እንደሚሆን መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

16 ይሖዋ “እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ” ከጎናችን እንደሚሆን ተማምነን በነፃነት ወደ እሱ በጸሎት እንድንቀርብ ይፈልጋል። (ዕብ. 4:16) ታዲያ ይህ በግለሰብ ደረጃ እንደሚወደንና እንደሚያስብልን አያሳይም? (ማቴ. 6:8፤ 10:29-31) በይሖዋ አምላክ ላይ እንደምንተማመን ለማሳየት አዘውትረን መጸለይ እንዲሁም ከጸሎታችንና እሱ ከሚሰጠን አመራር ጋር የሚስማሙ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርብናል። በተጨማሪም ለእምነት ባልንጀሮቻችን መጸለያችንን አንርሳ።

17, 18. (ሀ) ይሖዋ በቅርቡ በጠላቶቹ ላይ ምን እርምጃ ይወስዳል? (ለ) ከየትኛው ወጥመድ ራሳችንን መጠበቅ ይኖርብናል?

17 ጊዜው ‘እምነት በማጣት የምንወላውልበት’ ሳይሆን በእምነት የምንበረታበት ነው። (ሮም 4:20) የአምላክ ጠላቶች የሆኑት ሰይጣንና ተከታዮቹ፣ ኢየሱስ እኛን ጨምሮ ለሁሉም ደቀ መዛሙርቱ የሰጠውን ሥራ ለማስቆም ጥረት ያደርጋሉ። (ማቴ. 28:19, 20) ዲያብሎስ ጥቃት ቢሰነዝርም ይሖዋ “የሁሉም ዓይነት ሰዎች በተለይ ደግሞ ታማኝ የሆኑት ሰዎች አዳኝ [የሆነ] ሕያው አምላክ” እንደሆነ እናውቃለን። እሱ “ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድን” ያውቃል።​—1 ጢሞ. 4:10፤ 2 ጴጥ. 2:9

18 በቅርቡ ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት ይደመስሰዋል። ይህ የሚፈጸመው መቼና እንዴት እንደሆነ ባይነገረንም በትክክለኛው ጊዜ ላይ ክርስቶስ የአምላክን ጠላቶች እንደሚያጠፋና የይሖዋ ሉዓላዊነት እንደሚረጋገጥ እናውቃለን። በመሆኑም የምንኖርበትን ‘ጊዜና ወቅት’ አለማስተዋል ትልቅ ስህተት ነው! “ሁሉም ነገር ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ እንዳለ ይቀጥላል” የሚለው አስተሳሰብ ወጥመድ እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ።​—1 ተሰ. 5:1፤ 2 ጴጥ. 3:3, 4

ይሖዋን ‘ተስፋ አድርጉ’

19, 20. ይሖዋን ተስፋ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

19 ይሖዋ አምላክ ለሰው ልጆች የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ስለ እሱና ውብ ስለሆኑት የፍጥረት ሥራዎቹ ለዘላለም መማርን ይጨምራል። መክብብ 3:11 እንዲህ ይላል፦ “ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም።”

20 ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለውን ይህን ዓላማ ባለመቀየሩ በጣም ደስተኞች ነን! (ሚል. 3:6) አምላክ “ቦታውን እንደሚቀያይር ጥላ አይለዋወጥም።” (ያዕ. 1:17) ጥላ ቦታውን እንዲቀያየር የሚያደርገው ምድር በራሷ ዛቢያ ላይ መሽከርከሯ ነው፤ የሰው ልጆች ጊዜን ለመቁጠር የሚጠቀሙበት ይህ ሂደት በይሖዋ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር አይችልም። ይሖዋ ‘የዘላለም ንጉሥ’ ነው። (1 ጢሞ. 1:17) በመሆኑም ‘አዳኛችን የሆነውን አምላክ ተስፋ እናድርግ።’ (ሚክ. 7:7) እንዲሁም ይሖዋን “ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ፤ በርቱ፤ ልባችሁም ይጽና።”​—መዝ. 31:24

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 186-195 ተመልከት።

^ አን.9 የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 94-97 ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳንኤል፣ አምላክ የተናገረው ትንቢት እንደሚፈጸም እምነት ነበረው

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጊዜህን የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ በጥሩ ሁኔታ እየተጠቀምክበት ነው?