በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ሕልሜ እውን ሆኗል”

“ሕልሜ እውን ሆኗል”

“ሕልሜ እውን ሆኗል”

ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት ኤሚልያ በዘወትር አቅኚነት ታገለግል ነበር። ይሁንና አቅኚነቷን እንድታቋርጥ የሚያስገድድ ነገር አጋጠማት። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ በነበረችበት ወቅት በሕይወቷ በጣም ደስተኛ ነበረች። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያንን ጊዜ በተደጋጋሚ ስለምታስታውስ በአገልግሎት የምታሳልፈውን ጊዜ እንደገና ከፍ ለማድረግ ተነሳሳች።

ያም ሆኖ ሰብዓዊ ሥራዋ፣ ብዙ ጊዜዋን ስለሚወስድባት ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመመለስ እንቅፋት ሆኖባት ነበር፤ ይህ ደግሞ ደስታዋን ያሳጣት ጀመር። አንድ ቀን በሥራ ባልደረቦቿ ፊት “የሥራ ሰዓቴ ቢቀነስልኝ ደስ ይለኝ ነበር!” በማለት ስሜቷን ገለጸች። አለቃዋ ይህን ስትሰማ እውነት መሆኑን ለማጣራት ኤሚልያን አነጋገረቻት። ኤሚልያም አለቃዋ የሰማችው ነገር ትክክል መሆኑን ነገረቻት። ይሁንና የኤሚሊያን ፍላጎት ለማሳካት ዋና ሥራ አስኪያጁ መፍቀድ ነበረበት፤ ምክንያቱም በድርጅቱ ፖሊሲ መሠረት ሁሉም ሠራተኞች ራሳቸውን ምንም ሳይቆጥቡ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። እህታችን ከዋናው ሥራ አስኪያጅ ጋር ለመነጋገር ጥሩ ዝግጅት ያደረገች ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ መረጋጋትና ድፍረት እንዲሰጣት ጸለየች።

ኤሚሊያ ዋናው ሥራ አስኪያጅ ፊት ስትቀርብ የሥራ ሰዓቷ እንዲቀነስላት በዘዴ ሆኖም ድፍረት በተሞላበት መንገድ ጠየቀች። ከሥራ ሰዓት ውጪ ያለውን ጊዜ ሌሎችን ለመርዳት እንደምትጠቀምበት ስትገልጽ እንዲህ አለች፦ “የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ ሰዎችን በመንፈሳዊ እረዳለሁ። በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች የሥነ ምግባር አቋማቸው እየላላ መጥቷል። እነዚህ ሰዎች ግልጽ የሆኑ የሥነ ምግባር እሴቶችንና ደንቦችን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ የማካፍላቸው ጥበብ ደግሞ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። እርግጥ ነው፣ ከሥራ ሰዓት ውጪ የማከናውናቸው ነገሮች የሥራዬን ጥራት ዝቅ እንዲያደርጉብኝ አልፈልግም፤ ሆኖም ሰዎችን ለመርዳት ተጨማሪ ጊዜ ባገኝ ደስ ይለኛል። የሥራ ሰዓቴ እንዲቀነስልኝ የፈለግኩት ለዚህ ነው።”

ዋናው ሥራ አስኪያጅ በጥሞና ካዳመጣት በኋላ በአንድ ወቅት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውስጥ መካፈል ይፈልግ እንደነበረ ገለጸላት። በመቀጠልም እንዲህ አላት፦ “ካቀረብሽው ምክንያት አንጻር የጠየቅሽውን ነገር መፍቀድ እንዳለብኝ ይሰማኛል። ነገር ግን ደሞዝሽ እንደሚቀንስ አስበሽበታል?” ኤሚሊያ ይህን እንደተገነዘበችና አስፈላጊ ከሆነም አኗኗሯን ቀላል እንደምታደርግ ነገረችው። አክላም “ዋነኛው ግቤ ለሰዎች እውነተኛ እርካታ የሚያመጣ ነገር መሥራት ነው” አለችው። ዋና ሥራ አስኪያጁ በምላሹ “ጊዜያቸውን ሳይቆጥቡ ሌሎችን የሚረዱ ሰዎችን አደንቃለሁ” አላት።

በድርጅቱ ታሪክ ውስጥ እንዲህ ያለ ልዩ መብት ያገኘ ሌላ ሠራተኛ የለም። በአሁኑ ጊዜ ኤሚሊያ በሳምንት ውስጥ አራት ቀን ብቻ እንድትሠራ ተፈቅዶላታል። የሚገርመው ደሞዝ የተጨመረላት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በፊት የምታገኘውን ያህል ይከፈላታል። “ሕልሜ እውን ሆኗል፤ እንደገና አቅኚ መሆን እችላለሁ!” ብላለች።

አንተስ ሁኔታህን አመቻችተህ ወደ አቅኚነት አገልግሎት ለመግባት ወይም ወደዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ለመመለስ አስበህ ታውቃለህ?

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዋናው ሥራ አስኪያጅ እንዲህ አላት፦ “ጊዜያቸውን ሳይቆጥቡ ሌሎችን የሚረዱ ሰዎችን አደንቃለሁ”