በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የሚያሸብረኝ ማን ነው?”

“የሚያሸብረኝ ማን ነው?”

“የሚያሸብረኝ ማን ነው?”

“ጦርነት ቢነሣብኝ እንኳ፣ ልበ ሙሉ ነኝ።”​—መዝ. 27:3

ከታች በቀረቡት ጥቅሶች መሠረት ድፍረት ለማዳበር ምን ሊረዳህ ይችላል?

መዝሙር 27:1

መዝሙር 27:4

መዝሙር 27:11

1. መዝሙር 27 ምን ነገር ለመረዳት ያስችለናል?

የዓለም ሁኔታዎች እየከፉ ቢሄዱም በስብከቱ ሥራ የምናደርገው እንቅስቃሴ እየጨመረ የሚሄደው ለምንድን ነው? በዓለም ላይ ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም እኛ ግን ጊዜያችንንም ሆነ ጉልበታችንን በነፃ የምንሰጠው ለምንድን ነው? ብዙ ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ስጋት ቢያድርባቸውም እኛ ግን ደፋሮች መሆን የቻልነው ለምንድን ነው? ንጉሥ ዳዊት በመንፈስ መሪነት ያቀናበረው 27ኛው መዝሙር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጠናል።

2. ሽብር አንድን ሰው ምን ሊያደርገው ይችላል? ሆኖም ስለ ምን ነገር እርግጠኞች ነን?

2 ዳዊት ይህን መዝሙር የጀመረው እንዲህ በማለት ነበር፦ “ይሖዋ ብርሃኔና አዳኜ ነው። የሚያስፈራኝ ማን ነው? ይሖዋ ለሕይወቴ መከታ ነው። የሚያሸብረኝ ማን ነው?” (መዝ. 27:1 NW) ፍርሃት አንድን ሰው ሊያዳክመው ቢችልም መሸበር ግን ከዚያ የባሰ ነገር ያስከትላል። በይሖዋ የሚታመን ሰው ግን ደፋር ስለሚሆን አይሸበርም። (1 ጴጥ. 3:14) ይሖዋን መታመኛችን ስናደርግ ‘በሰላም እንኖራለን፤ እንዲሁም ክፉን ሳንፈራ ያለ ስጋት እንቀመጣለን።’ (ምሳሌ 1:33፤ 3:25) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

“ይሖዋ ብርሃኔና አዳኜ ነው”

3. ይሖዋ ብርሃናችን ነው ሲባል ምን ማለት ነው? ሆኖም ከእኛ ምን ይጠበቃል?

3 “ይሖዋ ብርሃኔ” ነው የሚለው ዘይቤያዊ አነጋገር ይሖዋ ከድንቁርና ብሎም ከመንፈሳዊ ጨለማ ነፃ እንደሚያወጣን ያሳያል። (መዝ. 27:1) ብርሃን በመንገዳችን ላይ የሚያጋጥመን አደገኛ ሁኔታ ወይም እንቅፋት ወለል ብሎ እንዲታየን ቢያደርግም ችግሩን አያስወግድልንም። ሁኔታውን ከተመለከትን በኋላ ጥበብ የተሞላበት እርምጃ መውሰድ የእኛ ድርሻ ነው። በተመሳሳይም ይሖዋ በዓለማችን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ክንውኖች ምን ትርጉም እንዳላቸው ይገልጥልናል። እንዲሁም በዚህ ሥርዓት ውስጥ ስላሉት አደጋዎች ያስጠነቅቀናል። በማንኛውም ጊዜ ልንጠቀምባቸው የምንችልባቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚሰጠን ቢሆንም የተማርነውን ተግባራዊ ማድረግ የእኛ ፋንታ ነው። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ከአስተማሪዎቻችን አሊያም ከጠላቶቻችን ይልቅ አስተዋይ ያደርገናል።​—መዝ. 119:98, 99, 130

4. (ሀ) ዳዊት ‘ይሖዋ አዳኜ ነው’ በማለት ተማምኖ ሊናገር የቻለው ለምንድን ነው? (ለ) በተለይ ይሖዋ አዳኛችን መሆኑን የሚያሳየው መቼ ነው?

4 ዳዊት በ⁠መዝሙር 27:1 ላይ ያለውን ሐሳብ የጻፈው ከዚህ በፊት ይሖዋ እንዴት እንደታደገው ወይም እንዳዳነው አስታውሶ መሆን አለበት። ለምሳሌ ይሖዋ “ከአንበሳ መዳፍና ከድብ መንጋጋ [አድኖታል]።” በተጨማሪም ግዙፍ የሆነውን ጎልያድን ድል እንዲያደርግ ረድቶታል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ንጉሥ ሳኦል ሊገድለው ፈልጎ ከአንዴም ሁለቴ ጦር ቢወረውርበትም ይሖዋ አድኖታል። (1 ሳሙ. 17:37, 49, 50፤ 18:11, 12፤ 19:10) በመሆኑም ዳዊት በሙሉ ልብ ይሖዋን “አዳኜ” ማለቱ ምንም አያስገርምም! ይሖዋ ለዳዊት እንዳደረገው ሁሉ ለሌሎች አገልጋዮቹም አዳኝ ይሆናል። እንዴት? አምላኪዎቹን ከሚመጣው ‘ታላቅ መከራ’ በማዳን ነው።​—ራእይ 7:14፤ 2 ጴጥ. 2:9

ይሖዋ ያደረገላችሁን ነገሮች አስታውሱ

5, 6. (ሀ) የቀድሞውን ጊዜ ማስታወስ፣ ድፍረት በማዳበር ረገድ ምን ሚና ይጫወታል? (ለ) ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ጋር በተያያዘ ያደረጋቸውን ነገሮች ማስታወሳችን ድፍረታችንን የሚጨምርልን እንዴት ነው?

5 ድፍረትን ለማዳበር ከሚረዱን ጠቃሚ ነገሮች አንዱ በ⁠መዝሙር 27:2, 3 ላይ ተጠቅሷል። (ጥቅሱን አንብብ።) ዳዊት በተለያዩ አጋጣሚዎች ይሖዋ እንዴት እንዳዳነው አስታውሷል። (1 ሳሙ. 17:34-37) ይህን ማስታወሱ አንድ ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ይኸውም ወደፊት የከፉ ነገሮች ቢያጋጥሙትም እንኳ በይሖዋ እርዳታ እንደሚወጣቸው እንዲተማመን አድርጎታል። አንተስ ካሳለፍከው የሕይወት ተሞክሮ በመነሳት ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ መድረስ ትችላለህ? ለምሳሌ የሚያስጨንቅ ሁኔታ አጋጥሞህ ወደ ይሖዋ አጥብቀህ የጸለይክበትና ይሖዋም ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብና ጥንካሬ በመስጠት የረዳህ ጊዜ አለ? አሊያም ደግሞ ከዚህ በፊት አምላክን በደስታ እንዳታገለግል እንቅፋት የሆኑብህ ነገሮች እንዴት እንደተወገዱልህ ወይም በይሖዋ አገልግሎት ትልቅ የሥራ በር እንዴት እንደተከፈተልህ ታስታውሳለህ? (1 ቆሮ. 16:9) ታዲያ እነዚህን ነገሮች ማስታወስህ በአሁኑ ጊዜ ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድሮብሃል? በሕይወትህ ያየሃቸው እነዚህ ነገሮች ወደፊት የባሱ እንቅፋቶች ወይም መከራዎች ቢያጋጥሙህ እንኳ ይሖዋ ከጎንህ በመሆን ሊረዳህ እንደሚችል በማሰብ ምንጊዜም በእሱ ላይ እምነት እንድትጥል አላደረጉህም?​—ሮም 5:3-5

6 አንድ ኃያል መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮችን በቡድን ደረጃ ለማጥፋት ሴራ ቢጠነስስስ? በዘመናችን ብዙ ሰዎች ይህን ለማድረግ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። ይሖዋ ከዚህ በፊት ሕዝቦቹን እንዴት እንደረዳቸው ማስታወሳችን የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንድንጠባበቅ ያደርገናል።​—ዳን. 3:28

ንጹሑን አምልኮ ማድነቅ

7, 8. (ሀ) በ⁠መዝሙር 27:4 መሠረት ዳዊት ይሖዋን የጠየቀው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምንድን ነው? የአምላክ አገልጋዮች በዚህ ቦታ አምልኳቸውን የሚያቀርቡትስ እንዴት ነው?

7 ድፍረት እንዲኖረን የሚረዳን ሌላው ወሳኝ ነገር ደግሞ ለእውነተኛው አምልኮ ያለን ፍቅር ነው። (መዝሙር 27:4ን በNW አንብብ። *) በዳዊት ዘመን ቤተ መቅደሱ ገና አልተገነባም ነበር፤ ስለሆነም ‘የይሖዋ ቤት’ የተባለው የማደሪያው ድንኳን ነበር። ዳዊት፣ ሰለሞን በጣም ውብ የሆነውን ቤተ መቅደስ እንዲገነባ ዝግጅት አድርጎ ነበር። ከበርካታ ዘመናት በኋላ ኢየሱስ፣ ሰዎች ይሖዋን ለማምለክ ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ የማያስፈልጋቸው ጊዜ እንደሚመጣ ተናግሯል። (ዮሐ. 4:21-23) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በዕብራውያን መጽሐፍ ምዕራፍ 8 እስከ 10 ላይ እንደጠቆመው ታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ወደ ሕልውና የመጣው ኢየሱስ በተጠመቀበት ማለትም የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን ባቀረበበት በ29 ዓ.ም. ነው። (ዕብ. 10:10) ታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ የሚያመለክተው በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን ተቀባይነት ያለው አምልኮ ለይሖዋ ማቅረብ እንድንችል አምላክ ያደረገውን ዝግጅት ነው። ታዲያ በዚህ ቤተ መቅደስ አምልኳችንን ማቅረብ የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምንችለው “ከእምነት በሚመነጭ ታላቅ የመተማመን መንፈስ በእውነተኛ ልብ” በመጸለይና ተስፋችንን ያላንዳች ማወላወል በይፋ በማወጅ ነው፤ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ብሎም በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ለእምነት ባልንጀሮቻችን ትኩረት በመስጠት፣ አንዳችን ሌላውን በማነቃቃትና በማበረታታት ይህን ማድረግ እንችላለን። (ዕብ. 10:22-25) ለእውነተኛው አምልኮ አድናቆት የምናሳይ ከሆነ ለመቋቋም አስቸጋሪ በሆኑት የመጨረሻዎቹ ቀኖች እነዚህን ነገሮች በማድረግ እንጸናለን።

8 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በስብከቱ ሥራ የሚያሳልፉትን ጊዜ ከፍ በማድረግ፣ አዳዲስ ቋንቋዎችን በመማርና የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ በመሄድ በአገልግሎቱ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ጨምረዋል። ተግባራቸው ልክ እንደ መዝሙራዊው ይሖዋን አንድ ነገር እየለመኑት እንዳለ ያሳያል። ፍላጎታቸው የይሖዋን ደስታ ማግኘት ማለትም በእሱ መባረክ እንዲሁም ምንም ይምጣ ምን በቅዱስ አገልግሎት መካፈል ነው።​—መዝሙር 27:6ን አንብብ።

አምላክ በሚሰጠው እርዳታ ተማመኑ

9, 10. መዝሙር 27:10 ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?

9 ዳዊት፣ ይሖዋ እንደሚረዳው ያለውን ትምክህት በግልጽ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ይቀበለኛል።” (መዝ. 27:10) በ⁠1 ሳሙኤል ምዕራፍ 22 ላይ ከተገለጸው ዘገባ እንደምንረዳው ዳዊት ወላጆቹ አልተዉትም። ይሁንና በዛሬው ጊዜ በርካታ ክርስቲያኖች ቤተሰቦቻቸው ዓይናችሁን ለአፈር ቢሏቸውም ሞቅ ባለው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በመታቀፋቸው ጥበቃና እርዳታ አግኝተዋል።

10 ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚደርስባቸውን መገለል ተመልክቶ የሚረዳቸው ከሆነ ሌሎች ችግሮች ሲደርሱባቸው ከጎናቸው አይሆንም ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው? ለምሳሌ ያህል፣ ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ለማቅረብ ቢቸግረን ይሖዋ እንደሚረዳን እርግጠኛ መሆን አንችልም? (ዕብ. 13:5, 6) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ያሉበትን ሁኔታ ይረዳል፤ እንዲሁም ምን እንደሚያስፈልጋቸው ያውቃል።

11. በይሖዋ መታመናችን በሌሎች ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል? ምሳሌ ስጥ።

11 በላይቤሪያ የምትኖረው ቪክቶሪያ የተባለች አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያጋጠማትን ሁኔታ እስቲ እንመልከት። በጥናቷ እየገፋች ስትሄድ አብሯት የሚኖረው ሰው እሷንና ሦስት ልጆቿን ጥሎ ሄደ። ቪክቶሪያ ሥራም ሆነ መኖሪያ ቤት ባይኖራትም በመንፈሳዊ እድገት ማድረጓን ቀጠለች። ቪክቶሪያ ከተጠመቀች ብዙም ሳይቆይ የ13 ዓመት ልጇ ብዙ ገንዘብ የያዘ ቦርሳ አገኘች። ፈተና እንዳይሆንባቸው ስለፈለጉ ገንዘቡ ስንት እንደሆነ ለመቁጠር እንኳ አልፈለጉም። ከዚህ ይልቅ ወዲያውኑ የቦርሳው ባለቤት የሆነውን ወታደር ለማግኘት ጥረት አደረጉ። ወታደሩም፣ ሰው ሁሉ እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ታማኝ ቢሆን ኖሮ ዓለማችን የተሻለችና ሰላማዊ ስፍራ ትሆን እንደነበር ነገራቸው። ቪክቶሪያም ይሖዋ ቃል ስለገባው አዲስ ዓለም ለወታደሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳየችው። ወታደሩም በታማኝነቷ በጣም በመደነቁ፣ ከመለሰችው ላይ ጠቀም ያለ ገንዘብ ሰጣት። በእርግጥም የይሖዋ ምሥክሮች፣ አምላካቸው የሚያስፈልጋቸውን እንደሚሰጣቸው ያላቸው ሙሉ እምነት ሐቀኞች በመሆን ረገድ ጥሩ ስም እንዲያተርፉ አስችሏቸዋል።

12. ሥራችንን ወይም ገንዘባችንን አጥተንም እንኳ በይሖዋ አገልግሎት መቀጠላችን ምን ያሳያል? ምሳሌ ስጥ።

12 እስቲ ደግሞ በሴራ ሊዮን የሚኖር ቶማስ የተባለ አንድ ያልተጠመቀ አስፋፊ ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። ቶማስ በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በመምህርነት መሥራት ጀመረ፤ ይሁን እንጂ ትምህርት ቤቱ ሙሉ በሙሉ እስኪቀበለው ድረስ ለአንድ ዓመት ገደማ ደሞዝ አልተከፈለውም። ቶማስ ደሞዙን ለማግኘት ማሟላት የነበረበት የመጨረሻው መሥፈርት ምንድን ነው? የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ ቃለ መጠይቅ ሊያደርግለት ይገባ ነበር፤ ይህ ሰው ደግሞ ቄስ ነው። ቄሱ የይሖዋ ምሥክሮች እምነት ከትምህርት ቤቱ ደንብ ጋር አብሮ እንደማይሄድ ለቶማስ ነገረው። ከዚያም ከሥራው ወይም ከእምነቱ አንዱን መምረጡ ግድ እንደሆነ ገለጸለት። ቶማስ ግን ሊከፈለው የሚገባውን ደሞዝ በመተው ሥራውን ጥሎ ወጣ፤ ከዚያም ሬዲዮና ሞባይል የመጠገን ሥራ አገኘ። ብዙ ሰዎች፣ ሌሎች ቢያገሉኝስ የሚለው ፍርሃት ያሸብራቸዋል፤ ሆኖም ከላይ የተጠቀሰውና ተመሳሳይ የሆኑ ሌሎች በርካታ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት የሁሉ ነገር ፈጣሪ በሆነውና ሕዝቡን በመንከባከብ ረገድ ወደር በማይገኝለት አምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ያላቸው ሰዎች እንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት አያሸብራቸውም።

13. ድሃ በሆኑ አገሮች ውስጥ የስብከቱ ሥራ እየተስፋፋ ያለው ለምንድን ነው?

13 በድህነት በተጠቁ በርካታ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በአብዛኛው በስብከቱ ሥራ ከፍተኛ ተሳትፎ ያደርጋሉ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚከተለውን ጽፏል፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚጀምሩት አብዛኛዎቹ ሰዎች ሥራ የሌላቸው ስለሆኑ ቀን ላይ ለማጥናት ረጅም ጊዜ አላቸው። ወንድሞችም ቢሆኑ በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ብዙ ጊዜ አላቸው። በተለይ በከፋ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ እንደሆነ ሊነገራቸው አያስፈልግም፤ ምክንያቱም በአካባቢያቸው ካለው ሁኔታ ይህን መረዳት ይችላሉ።” እያንዳንዱ አስፋፊ በአማካይ ከሦስት በላይ ጥናቶች በሚመራበት አገር ውስጥ ከ12 ዓመታት በላይ ያገለገለ አንድ ሚስዮናዊ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አብዛኞቹ አስፋፊዎች ቀላል ሕይወት ስለሚመሩ ትኩረታቸውን የሚከፋፍሉ ብዙ ነገሮች የሉም፤ በመሆኑም በስብከቱና መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማሩ ሥራ ረጅም ጊዜ ያሳልፋሉ።”

14. እጅግ ብዙ ሕዝብ መለኮታዊ ጥበቃ ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው?

14 ይሖዋ ሕዝቡን በቡድን ደረጃ በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ብሎም እንደሚረዳቸውና እንደሚያድናቸው ቃል ገብቷል፤ እኛም ቃሉን እንደሚጠብቅ እንተማመናለን። (መዝ. 37:28፤ 91:1-3) “ከታላቁ መከራ” የሚተርፈው ሕዝብ እጅግ ብዙ እንደሚሆን የተናገረው ቃል መፈጸም ይኖርበታል። (ራእይ 7:9, 14) በመሆኑም ይህ ሕዝብ በመጨረሻዎቹ ቀኖች ከሚደርሰው ጥፋት በቡድን ደረጃ ጥበቃ ያገኛል። የሚደርስባቸውን ፈተና መቋቋም እንዲችሉና ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ጠብቀው እንዲኖሩ አስፈላጊውን እርዳታ በሙሉ ያደርግላቸዋል። በታላቁ መከራ የመደምደሚያ ምዕራፍ ላይም ይሖዋ ሕዝቦቹን ይጠብቃል።

“መንገድህን አስተምረኝ”

15, 16. መለኮታዊውን መመሪያ የምንከተል ከሆነ ምን ጥቅም እናገኛለን? ምሳሌ ስጥ።

15 ደፋሮች ሆነን ለመቀጠል ዘወትር የአምላክን መንገድ መማር ይኖርብናል። ዳዊት እንደሚከተለው ብሎ መለመኑ ይህን ያሳያል፦ “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ መንገድህን አስተምረኝ፤ ስለ ጠላቶቼም፣ በቀና መንገድ ምራኝ።” (መዝ. 27:11) ከዚህ ልመና ጋር በሚስማማ መልኩ ለመኖር በይሖዋ ድርጅት በኩል ለሚሰጠን ማንኛውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል፤ እንዲሁም የተሰጠንን መመሪያ ሥራ ላይ ለማዋል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለብን። ለምሳሌ ብዙዎች፣ አላስፈላጊ ዕዳዎችን በመቀነስና የማያስፈልጓቸውን ነገሮች በመሸጥ አኗኗራችንን ቀላል ስለማድረግ የተሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ አድርገዋል፤ ይህን በማድረጋቸው በቅርቡ በተከሰተው የኢኮኖሚ ድቀት ምክንያት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ከመግባት ድነዋል። እነዚህ ሰዎች ካሉበት ኑሮ ላለመውረድ ሲሉ መከራቸውን ከማየት ይልቅ አገልግሎታቸውን ለማስፋት የሚያስችል ጊዜ አግኝተዋል። እያንዳንዳችን ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘መሥዋዕትነት የሚያስከፍለኝ ቢሆንም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ታማኝና ልባም ባሪያ በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች ላይ የማነባቸውን ነገሮች በሙሉ ወዲያውኑ ተግባራዊ አደርጋለሁ?’​—ማቴ. 24:45

16 ይሖዋ እንዲያስተምረንም ሆነ በቀናው መንገድ እንዲመራን የምንፈቅድ ከሆነ ፈጽሞ አንፈራም። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ አቅኚ፣ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቀጠል እንዲችሉ የሚረዳቸውን የሥራ መደብ እንዲሰጠው ጠየቀ፤ ሆኖም አለቃው የኮሌጅ ዲግሪ ከሌለው በስተቀር ሥራውን ማግኘት እንደማይችል ነገረው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አንተ ላይ ደርሶ ቢሆን ኖሮ ከፍተኛ ትምህርት ከመከታተል ይልቅ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ በመግባትህ ትቆጭ ነበር? ከሁለት ሳምንት በኋላ አለቃው ከሥራ ተባረረ፤ ከዚያም አንድ ሌላ ሥራ አስኪያጅ ወንድምን ስለ ግቡ ጠየቀው። በዚህ ጊዜ ወንድም፣ እሱም ሆነ ባለቤቱ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑና በዚህ አገልግሎት መቀጠል እንደሚፈልጉ ነገረው። ሆኖም ወንድም ተጨማሪ ነገር ከመናገሩ በፊት ሥራ አስኪያጁ ቀበል አድርጎ እንዲህ አለው፦ “አንተ የተለየህ ሰው እንደሆንክ አውቄያለሁ! አባቴ ከመሞቱ በፊት የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ሳለ የእናንተ እምነት ተከታይ የሆኑ ሁለት ሴቶች እየመጡ በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን ያነቡለት ነበር። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮችን መርዳት የምችልበት አንድ አጋጣሚ ባገኝ ይህን ከማድረግ ወደኋላ እንደማልል ለራሴ ቃል ገባሁ።” በማግስቱ ጠዋት ወንድም፣ የበፊቱ አለቃው የከለከለውን ሥራ አገኘ። በእርግጥም፣ በሕይወታችን ውስጥ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደማናጣ የገባልንን ተስፋ ይፈጽምልናል።​—ማቴ. 6:33

እምነትና ተስፋ አስፈላጊ ናቸው

17. የወደፊቱን ጊዜ በትምክህት ለመጠበቅ ምን ሊረዳን ይችላል?

17 በመቀጠል ዳዊት “የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW] ቸርነት፣ በሕያዋን ምድር እንደማይ፣ ሙሉ እምነቴ ነው” በማለት የእምነትንና የተስፋን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። (መዝ. 27:13) አምላክ ተስፋ ባይሰጠን እንዲሁም በ⁠መዝሙር 27 ላይ የተብራሩትን ነገሮች ባናውቅ ኖሮ ሕይወታችን ምን ይመስል ነበር? እንግዲያው ይህ ሥርዓት በአርማጌዶን እስኪደመደም ድረስ፣ የሚያጋጥሙንን ነገሮች ለመጋፈጥ ይሖዋ ጥንካሬ እንዲሰጠንና የእሱ ጥበቃ እንዳይለየን ምንጊዜም በትምክህት እንጸልይ።​—መዝሙር 27:14ን አንብብ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳዊት፣ ይሖዋ እሱን ያዳነባቸውን ጊዜያት ማስታወሱ ብርታት ሰጥቶታል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን አገልግሎታችንን ለማስፋት እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርገን እንመለከታቸዋለን?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 መዝሙር 27:4 (NW)፦ “ይሖዋን አንድ ነገር ለመንኩት፤ ምኞቴም ይኸው ነው፦ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በይሖዋ ቤት እኖር ዘንድ፣ ይሖዋ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን አይ ዘንድ፣ ቤተ መቅደሱንም በአድናቆት እመለከት ዘንድ ነው።”