የነፃነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን አገልግሉ
የነፃነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን አገልግሉ
“አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባዶች አይደሉም።”—1 ዮሐ. 5:3
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ሰይጣን፣ የአምላክ ሕጎች ከባድ እንደሆኑ እንዲሰማን የሚያደርገው እንዴት ነው?
በጓደኛ ምርጫ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
የነፃነት አምላክ ለሆነው ለይሖዋ ታማኝ እንድንሆን የሚረዳን ምንድን ነው?
1. ይሖዋ ለነፃነት ምን ዓይነት አመለካከት አለው? ለአዳምና ለሔዋን ስለሰጣቸው ነፃነት ምን ሊባል ይችላል?
በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ገደብ የለሽ ነፃነት ያለው ይሖዋ ብቻ ነው። ይሁንና ነፃነቱን አላግባብ አይጠቀምበትም፤ በተጨማሪም አገልጋዮቹ የሚያደርጉትን እያንዳንዱን ነገር በመቆጣጠር ነፃነታቸውን አይገድብባቸውም። ከዚህ ይልቅ የራሳቸውን ውሳኔ ማድረግና ተገቢ የሆኑ ፍላጎቶቻቸውን ማርካት እንዲችሉ ነፃ ምርጫ ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ አምላክ አዳምንና ሔዋንን የከለከላቸው “መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ” እንዳይበሉ ብቻ ነበር። (ዘፍ. 2:17) በእርግጥም ነፃነታቸውን ሳያጡ የፈጣሪያቸውን ፈቃድ መፈጸም ይችሉ ነበር።
2. የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አምላክ የሰጣቸውን ነፃነት ያጡት ለምንድን ነው?
2 አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ይህን ያህል ነፃነት የሰጣቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በአምሳሉ የፈጠራቸው ከመሆኑም በላይ ሕሊና ሰጥቷቸዋል፤ ይሖዋ ፈጣሪያቸው እንደመሆኑ መጠን ለእሱ ያላቸው ፍቅር በትክክለኛው መንገድ እንደሚመራቸው መጠበቁ ትክክል ነው። (ዘፍ. 1:27፤ ሮም 2:15) የሚያሳዝነው ግን አዳምና ሔዋን ሕይወት ለሰጣቸው አምላክም ሆነ ከእሱ ላገኙት ነፃነት አድናቆት ሳያሳዩ ቀርተዋል። እንዲያውም ሰይጣን ያቀረበላቸውን ተገቢ ያልሆነ ነፃነት ለማግኘት ፈለጉ፤ በሌላ አባባል ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር በራሳቸው ለመወሰን መረጡ። ይሁንና እንዳሰቡት ነፃነት አላገኙም፤ ከዚህ ይልቅ ራሳቸውንም ሆነ ዘሮቻቸውን ለኃጢአት ባርነት ሸጠዋል፤ ይህ ደግሞ አስከፊ መዘዝ አስከትሏል።—ሮም 5:12
3, 4. ሰይጣን ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር በተያያዘ ሊያታልለን የሚሞክረው እንዴት ነው?
3 ሰይጣን፣ በርካታ መንፈሳዊ ፍጡራንን ማሳሳቱ እንዳለ ሆኖ ሁለት ፍጹማን ሰዎችን በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ እንዲያምፁ ማድረግ ከቻለ እኛን ማታለል የማይችልበት ምንም ምክንያት የለም። ሰይጣን የሚጠቀምበት ዘዴ አሁንም ቢሆን አልተለወጠም። የአምላክ መሥፈርቶች ከባድ አልፎ ተርፎም ደስታና እርካታ የሚያሳጡን እንደሆኑ አድርገን እንድናስብ በማድረግ ሊያታልለን ይሞክራል። 1 ዮሐ. 5:3) እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር ብዙ ጊዜ የምናሳልፍ ከሆነ ይህ ዓይነቱ አመለካከት ሊጋባብን ይችላል። የሥነ ምግባር ብልግና የፈጸመች አንዲት የ24 ዓመት ወጣት “በተለይ ከእኩዮቼ የተለየ አቋም እንዳለኝ ሆኖ መታየቱ ያስፈራኝ ስለነበር መጥፎ ጓደኝነት ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል” በማለት ተናግራለች። ምናልባት አንተም ተመሳሳይ ተጽዕኖ አጋጥሞህ ሊሆን ይችላል።
(4 የሚያሳዝነው ነገር እኩዮች የሚያሳድሩት መጥፎ ተጽዕኖ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ሊያጋጥም ይችላል። ወጣት የሆነ አንድ ክርስቲያን እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጓደኞቼ ከማያምኑ ሰዎች ጋር የፍቅር ግንኙነት መጀመራቸውን ተረዳሁ። ከእነሱ ጋር ብዙ ጊዜ ሳሳልፍ ይበልጥ እነሱን እየመሰልኩ እንደመጣሁ ተገነዘብኩ። መንፈሳዊነቴም እየቀነሰ ሄደ። በጉባኤ የሚቀርበው መንፈሳዊ ትምህርት ምንም አይማርከኝም ነበር፤ አገልግሎት የምወጣውም ከስንት አንዴ ነበር። ይህ ደግሞ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ያለኝን ግንኙነት ማቋረጥ እንዳለብኝ ጥሩ ምልክት ሆነኝ፤ እናም ወዲያውኑ ማስተካከያ አደረግኩ!” ታዲያ ጓደኛ ምን ያህል ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ተገነዘብክ? እስቲ በዚህ ረገድ ለዘመናችን የሚጠቅም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንመልከት።—ሮም 15:4
ልባቸውን ሰረቀ
5, 6. አቤሴሎም ሌሎችን ያታለለው እንዴት ነው? የጠነሰሰው ሴራስ ተሳክቶለት ነበር?
5 መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳደሩ የበርካታ ሰዎችን ታሪክ ይዟል። በዚህ ረገድ እንደ ምሳሌ ልንጠቅሳቸው ከምንችላቸው ሰዎች አንዱ የንጉሥ ዳዊት ልጅ የሆነው አቤሴሎም ነው። አቤሴሎም እጅግ ውብ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን እንደ ሰይጣን የሥልጣን ጥም ስላደረበት ለእሱ የማይገባውን የአባቱን ዙፋን ለመንጠቅ ፈለገ። * በመሆኑም አቤሴሎም ይህን ሥልጣን ለማግኘት ሲል ለወገኖቹ ከልብ የሚያስብ መስሎ ይቀርብ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ንጉሡ በትክክል እንደማይፈርድላቸው ሆኖ እንዲሰማቸው ለማድረግ በአሽሙር ይናገር ነበር። ዲያብሎስ በኤደን ገነት እንዳደረገው ሁሉ አቤሴሎምም በአንድ በኩል ተቆርቋሪ መስሎ ቢቀርብም በሌላ በኩል ግን በገዛ አባቱ ላይ የጭካኔ ድርጊት እየፈጸመ ነበር።—2 ሳሙ. 15:1-5
6 አቤሴሎም የጠነሰሰው ሴራ ተሳካለት? መጽሐፍ ቅዱስ “አቤሴሎም . . . የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ” ስለሚል በተወሰነ መጠን ተሳክቶለታል። (2 ሳሙ. 15:6) በመጨረሻ ግን ኩራቱ ለውድቀት ዳርጎታል። የሚያሳዝነው ደግሞ ከራሱ አልፎ በእሱ ለተታለሉ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሆኗል።—2 ሳሙ. 18:7, 14-17
7. ስለ አቤሴሎም ከሚናገረው ዘገባ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? (በገጽ 14 ላይ የሚገኘውን ሥዕላዊ መግለጫ ተመልከት።)
7 አቤሴሎም እነዚህን ሰዎች በቀላሉ ሊያታልላቸው የቻለው እንዴት ነው? ምናልባት እነዚህ ሰዎች አቤሴሎም ቃል የገባላቸውን ነገሮች ለማግኘት ጓጉተው ሊሆን ይችላል። አሊያም በቁመናው ተስበው ይሆናል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን፦ እነዚህ ሰዎች ለይሖዋም ሆነ እሱ ለሾመው ንጉሥ ታማኝ አልነበሩም። በዛሬው ጊዜም ቢሆን ሰይጣን የይሖዋ አገልጋዮችን ልብ ለመስረቅ ዘመናዊ አቤሴሎሞችን ይጠቀማል። እነዚህ ሰዎች እንዲህ በማለት ይናገሩ ይሆናል፦ ‘የይሖዋ መሥፈርቶች በጣም ጥብቅ ናቸው። እስቲ ይሖዋን የማያገለግሉ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚመሩ ተመልከቱ፣ በጣም ደስተኞች ናቸው!’ ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ አነጋገር መሠሪ መሆኑን በማስተዋል ምንጊዜም ለአምላክ ታማኝ ትሆናላችሁ? እውነተኛ ነፃነት የሚያስገኘው የይሖዋ “ፍጹም ሕግ” ማለትም የክርስቶስ ሕግ ብቻ መሆኑን ተገንዝባችኋል? (ያዕ. 1:25) ከሆነ ይህን ሕግ ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱት፤ እንዲሁም ክርስቲያናዊ ነፃነታችሁን አላግባብ እንዳትጠቀሙበት ተጠንቀቁ።—1 ጴጥሮስ 2:16ን አንብብ።
8. የይሖዋን መሥፈርቶች ችላ በማለት ደስታ ማግኘት እንደማይቻል የሚያሳዩ የትኞቹን ዘመናዊ ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላል?
8 በተለይ ወጣቶች የሰይጣን ዒላማ ናቸው። አሁን በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ አንድ ወንድም
በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለ ምን ይሰማው እንደነበር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የምመለከታቸው ጥበቃ እንደሚያስገኙ ሳይሆን መፈናፈኛ እንደሚያሳጡ ነገሮች አድርጌ ነበር።” በዚህም የተነሳ ይህ ወንድም የፆታ ብልግና ፈጸመ። ሆኖም የተከተለው ጎዳና ደስታ አላመጣለትም። “ለረጅም ዓመታት የጥፋተኝነትና የጸጸት ስሜት ያሠቃየኝ ነበር” ብሏል። አንዲት እህት ደግሞ በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለች ያጋጠማትን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “የፆታ ብልግና ከፈጸምኩ በኋላ በሐዘን የተዋጥኩ ከመሆኑም በላይ የባዶነት ስሜት ተሰማኝ። ይህ ከሆነ 19 ዓመታት ቢያልፉም አሁንም ድረስ መጥፎ ትዝታ ይመጣብኛል።” አንዲት ሌላ እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “በጣም የምወዳቸው ሰዎች በእኔ ምግባር ስሜታቸው እንደተጎዳ ማሰቤ አእምሯዊ፣ መንፈሳዊና ስሜታዊ ጉዳት አስከትሎብኛል። የይሖዋን ሞገስ አጥቶ መኖር በጣም ከባድ ነው።” ሰይጣን ኃጢአት የሚያስከትለውን እንዲህ ያለ ውጤት እንድታስቡ አይፈልግም።9. (ሀ) ለይሖዋ እንዲሁም ለሕጎቹና ለመሠረታዊ ሥርዓቶቹ ያለንን አመለካከት ለመመርመር የትኞቹ ጥያቄዎች ሊረዱን ይችላሉ? (ለ) አምላክን በደንብ ማወቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
9 በርካታ ትላልቅ ሰዎችን ጨምሮ በእውነት ቤት ውስጥ ያደጉ ብዙ ወጣቶች በኃጢአት የሚገኝ ደስታ በአብዛኛው ትልቅ ዋጋ እንደሚያስከፍል የተገነዘቡት ችግር ውስጥ ከገቡ በኋላ ነው። (ገላ. 6:7, 8) እንግዲያው ራስህን እንዲህ በማለት ጠይቅ፦ ‘የሰይጣን ዘዴዎች መሠሪና ጉዳት የሚያስከትሉ እንደሆኑ ተረድቻለሁ? ይሖዋን የምመለከተው ምንጊዜም እውነቱን እንደሚነግረኝና ለእኔ ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንደሚመኝልኝ የቅርብ ወዳጄ አድርጌ ነው? ለእኔ የሚበጀውንና ከፍተኛ ደስታ የሚያስገኝልኝን ነገር ፈጽሞ እንደማይከለክለኝ ሙሉ እምነት አለኝ?’ (ኢሳይያስ 48:17, 18ን አንብብ።) ለእነዚህ ጥያቄዎች ከልብህ ‘አዎ’ ብለህ ለመመለስ ስለ ይሖዋ ላይ ላዩን ሳይሆን ጥልቀት ያለው እውቀት ያስፈልግሃል። ከእሱ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት ይኖርብሃል፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች የእሱ የፍቅር መግለጫዎች እንጂ አንተን መፈናፈኛ ለማሳጣት ያስቀመጣቸው ነገሮች እንዳልሆኑ መገንዘብ ያስፈልግሃል።—መዝ. 25:14
ጥበበኛና ታዛዥ ልብ እንዲሰጣችሁ ጸልዩ
10. ወጣቱን ንጉሥ ሰለሞንን ለመምሰል ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
10 ሰለሞን ወጣት ሳለ “ገና ትንሽ ልጅ ስለ ሆንሁ፣ መውጫና መግቢያዬን አላውቅም” በማለት በትሕትና ጸልዮ ነበር። ከዚያም ጥበበኛና አስተዋይ ወይም ታዛዥ ልብ ለማግኘት ጠየቀ። (1 ነገ. 3:7-9, 12) ይሖዋም ሰለሞን በቅን ልቦና ተነሳስቶ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል፤ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ብትገኝም እንዲህ ያለ ጸሎት ካቀረብክ አምላክ ለአንተም መልስ ይሰጥሃል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ማስተዋልና ጥበብ አይሰጥህም። ያም ሆኖ ቃሉን በትጋት የምታጠና፣ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጥህ የምትጸልይ እንዲሁም በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ባደረገልህ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ የምትጠቀም ከሆነ ጥበበኛ ትሆናለህ። (ያዕ. 1:5) በእርግጥም ይሖዋ በእነዚህ መንገዶች አማካኝነት ወጣት አገልጋዮቹን ሳይቀር፣ ምክሩን ችላ ከሚሉ ሰዎች ሌላው ቀርቶ ከዚህ ዓለም ‘ጥበበኞችና አዋቂዎች’ በላይ ጥበበኛ ያደርጋቸዋል።—ሉቃስ 10:21፤ መዝሙር 119:98-100ን አንብብ።
11-13. (ሀ) ከመዝሙር 26:4፣ ከምሳሌ 13:20 እና ከ1 ቆሮንቶስ 15:33 ምን ጠቃሚ ትምህርቶችን ማግኘት እንችላለን? (ለ) በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
11 መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ባጠናነው ነገር ላይ ማሰላሰል ይሖዋን በደንብ ለማወቅ እንደሚረዳ የሚያሳዩ ጥቅሶችን እስቲ እንመልከት። ሁሉም ጥቅሶች በጓደኛ ምርጫ ረገድ ጠቃሚ የሆነ መሠረታዊ ሥርዓት ይዘዋል፦ “ከማይረቡ ጋር አልተቀመጥሁም፤ ከግብዞችም ጋር አልተባበርሁም።” (መዝ. 26:4) “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል።” (ምሳሌ 13:20) “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል።”—1 ቆሮ. 15:33
12 ከእነዚህ ጥቅሶች ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን? (1) ይሖዋ በጓደኛ ምርጫ ረገድ ጠንቃቃ እንድንሆን እንዲሁም ከመንፈሳዊና ከሥነ ምግባራዊ አደጋ እንድንጠበቅ ይፈልጋል። (2) አብረናቸው የምንሆናቸው ሰዎች በጥሩ ወይም በመጥፎ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል፤ ይህ ደግሞ የሕይወት እውነታ ነው። ከጥቅሶቹ መንፈስ መረዳት እንደምንችለው ይሖዋ ደስ ብሎን እንድንታዘዘው ይፈልጋል። ይህን እንዴት እናውቃለን? ጥቅሶቹ በሙሉ በትእዛዝ መልክ እንዳልተቀመጡ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከዚህ ይልቅ ጥቅሶቹ የተቀመጡት እውነታውን ቁልጭ አድርጎ በሚያሳይ መንገድ ነው። በሌላ አባባል ይሖዋ እንዲህ እያለን ነው፦ ‘ሐቁ ይህ ነው። ታዲያ የአንተ ምርጫ ምንድን ነው? ልብህስ ምን ይላል?’
13 በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ሦስት ጥቅሶች መሠረታዊ የሆኑ እውነቶችን በውስጣቸው በመያዛቸው ጥቅሶቹ ዘመን የማይሽራቸውና በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። ይህን ለመመልከት ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ “ከግብዞች” ወይም ራሳቸውን ከሚደብቁ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ከመመሥረት መራቅ የምችለው እንዴት ነው? እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር ልገናኝ የምችልባቸው አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው? (ምሳሌ 3:32፤ 6:12) ይሖዋ ከእነሱ ጋር ወዳጅነት እንድመሠርት የሚፈልጋቸው “ጠቢብ” የተባሉት ሰዎች እነማን ናቸው? እንድርቃቸው የሚፈልጋቸው ‘ተላላ’ የተባሉት ሰዎችስ እነማን ናቸው? (መዝ. 111:10፤ 112:1፤ ምሳሌ 1:7) መጥፎ ጓደኞችን መምረጤ የትኛውን ‘መልካም አመል’ ያበላሽብኛል? መጥፎ ጓደኞች የሚያጋጥሙኝ በዓለም ውስጥ ብቻ ነው? (2 ጴጥ. 2:1-3) ለእነዚህ ጥያቄዎች ምን ምላሽ ትሰጣለህ?
14. የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁን ማሻሻል የምትችሉት እንዴት ነው?
14 ለአንተም ሆነ ለቤተሰብህ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የአምላክን አመለካከት መረዳት እንድትችል ለምን በሌሎች ጥቅሶች ላይም ከላይ በቀረበው መንገድ ምርምር አታደርግም? * ወላጆች፣ በቤተሰብ አምልኳችሁ ወቅት እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ሞክሩ። እንዲህ ስታደርጉ ዓላማችሁ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በአምላክ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ውስጥ የተንጸባረቀውን የይሖዋን ፍቅር በደንብ ማስተዋል እንዲችል መርዳት መሆን ይኖርበታል። (መዝ. 119:72) እንዲህ ያለው ጥናት ቤተሰቡን እርስ በርሱም ሆነ ከይሖዋ ጋር እንዲቀራረብ ያደርገዋል።
15. ጥበበኛና ታዛዥ ልብ እያዳበርክ መሆኑን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?
15 ጥበበኛና ታዛዥ ልብ እያዳበርክ መሆኑን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ አስተሳሰብህን በጥንት ጊዜ ከነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አስተሳሰብ ጋር ማወዳደር ነው፤ ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት “አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 40:8) የመዝሙር 119 ጸሐፊም በተመሳሳይ “ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ” ብሏል። (መዝ. 119:97) እንዲህ ያለው ፍቅር ጫር ጫር ተደርጎ ስለተዘራ ብቻ አያድግም። ከዚህ ይልቅ በጥልቀት ማጥናት፣ መጸለይ፣ ማሰላሰል እና የአምላክን መመሪያዎች መከተል ስፍር ቁጥር የሌለው በረከት እንደሚያስገኝ በሕይወታችን መቅመስን ይጠይቃል።—መዝ. 34:8
ለክርስቲያናዊ ነፃነታችሁ ተዋጉ!
16. ለእውነተኛው ነፃነት በምናደርገው ትግል ማሸነፍ እንድንችል ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል?
16 በታሪክ ዘመናት ሁሉ ብሔራት ለነፃነታቸው ሲሉ አሠቃቂ ጦርነቶችን ሲያደርጉ ኖረዋል። ታዲያ ለመንፈሳዊ ነፃነት ለመዋጋት ከዚህ ያነሰ ፍላጎት ሊኖርህ ይገባል? ጠላቶችህ ሰይጣን፣ ይህ ዓለምና መርዘኛ የሆነው የዓለም መንፈስ ብቻ እንዳልሆኑ ማስታወስ አለብህ። ተንኮለኛ የሆነውን ልብህን ጨምሮ ከራስህ አለፍጽምና ጋር መታገልም ይኖርብሃል። (ኤር. 17:9፤ ኤፌ. 2:3) ይሁንና በይሖዋ እርዳታ ውጊያውን ድል ማድረግ ትችላለህ። ትልቅም ይሁን ትንሽ እያንዳንዱ ድል ቢያንስ ሁለት ጥሩ ውጤቶች ይኖሩታል። በመጀመሪያ ደረጃ የይሖዋን ልብ ታስደስታለህ። (ምሳሌ 27:11) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ “ነፃ የሚያወጣው” የአምላክ “ፍጹም ሕግ” ያለውን ነፃ የማውጣት ኃይል በሕይወትህ ስትመለከት ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ‘ቀጭን መንገድ’ ላይ ለመጓዝ ባደረግከው ቁርጥ ውሳኔ ትጸናለህ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ወደር የሌለው ነፃነት ታጣጥማለህ።—ያዕ. 1:25፤ ማቴ. 7:13, 14
17. ፍጹማን ባለመሆናችን ምክንያት ማዘን የሌለብን ለምንድን ነው? ይሖዋስ ምን እርዳታ ያደርግልናል?
17 እርግጥ ነው፣ ሁላችንም አልፎ አልፎ ስህተት እንሠራለን። (መክ. 7:20) በዚህ ጊዜ የዋጋ ቢስነት ስሜት ሊሰማህ አይገባም፤ እንዲሁም ከሚገባው በላይ ማዘን አይኖርብህም። ተደናቅፈህ ብትወድቅ ማለትም ስህተት ብትሠራ ከወደቅክበት ተነስተህ ወደፊት መገስገስ ይኖርብሃል፤ የሽማግሌዎችህን እርዳታ መጠየቅ ቢያስፈልግህም እንኳ ይህን ከማድረግ ወደኋላ ማለት አይኖርብህም። ሽማግሌዎች ‘በእምነት የሚያቀርቡት ጸሎት የታመመን ሰው እንደሚፈውስና ይሖዋም እንደሚያስነሳው’ ያዕቆብ ጽፏል። አክሎም “ኃጢአት ሠርቶ ከሆነ ይቅር ይባልለታል” ብሏል። (ያዕ. 5:15) አዎን፣ አምላክ መሐሪ እንደሆነና አንተን ወደ ጉባኤው የሳበህ በውስጥህ ጥሩ ነገር ተመልክቶ እንደሆነ በፍጹም መርሳት የለብህም። (መዝሙር 103:8, 9ን አንብብ።) በመሆኑም ይሖዋ በፍጹም ልብ እስካገለገልከው ድረስ ፈጽሞ አይጥልህም።—1 ዜና 28:9
18 በዮሐንስ 17:15 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው የኢየሱስ ጸሎት ጋር ተስማምተን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ ከ11ዱ ታማኝ ሐዋርያት ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ፣ ‘ከክፉው ጠብቃቸው’ በማለት ስለ እነሱ የማይረሳ ጸሎት አቅርቦ ነበር። (ዮሐ. 17:15) ኢየሱስ እንዲህ ያለ የአሳቢነት ስሜት ያለው ለሐዋርያቱ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ተከታዮቹ ነው። በመሆኑም ይሖዋ በዚህ አስጨናቂ ዘመን ለእኛ ጥበቃ በማድረግ ለኢየሱስ ጸሎት መልስ እንደሚሰጥ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። “ያለ ነቀፋ ለሚሄዱት [ይሖዋ] ጋሻ ይሆናቸዋል፤ . . . የታማኞቹንም አካሄድ ያጸናል።” (ምሳሌ 2:7, 8) ያለ ነቀፋ ለመሄድ ወይም ንጹሕ አቋምን ጠብቆ ለመኖር የግድ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መወጣት ይኖርብናል፤ ሆኖም የዘላለም ሕይወትም ሆነ እውነተኛ ነፃነት ማግኘት የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው። (ሮም 8:21) ማንም ቢሆን ይህን መብት እንዳታገኝ እንቅፋት እንዲሆንብህ አትፍቀድ!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.5 ዳዊት ‘ዘሩ’ የእሱን ዙፋን እንደሚወርስ አምላክ የነገረው አቤሴሎም ከተወለደ በኋላ ነበር። በመሆኑም አቤሴሎም የዳዊትን ዙፋን እንዲወርስ ይሖዋ እንዳልመረጠው ተረድቶ መሆን አለበት።—2 ሳሙ. 3:3፤ 7:12
^ አን.14 ጳውሎስ ፍቅርን አስመልክቶ ስለሰጣቸው መግለጫዎች የሚናገረውን 1 ቆሮንቶስ 13:4-8ን እንዲሁም የይሖዋን ሕጎች መታዘዝ ስለሚያስገኛቸው የተለያዩ በረከቶች የሚገልጸውን መዝሙር 19:7-11ን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዘመናዊ አቤሴሎሞችን መለየትና ከእነሱ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?