በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ቤተሰቡን ይሰበስባል

ይሖዋ ቤተሰቡን ይሰበስባል

ይሖዋ ቤተሰቡን ይሰበስባል

‘የመንፈስን አንድነት እንድትጠብቁ እለምናችኋለሁ።’​—ኤፌ. 4:1, 3

ምን ብለህ ታብራራለህ?

የአምላክ አስተዳደር የተቋቋመበት ዓላማ ምንድን ነው?

‘የመንፈስን አንድነት መጠበቅ’ የምንችለው እንዴት ነው?

‘አንዳችን ለሌላው ደግ ለመሆን’ ምን ሊረዳን ይችላል?

1, 2. ይሖዋ ለሰው ልጆችም ሆነ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

ቤተሰብ የሚለውን ቃል ስትሰማ ምን ነገር ወደ አእምሮህ ይመጣል? ፍቅርና ደስታ የሰፈነበት ቦታ? ለጋራ ግብ ተባብረው የሚሠሩ ሰዎችን ያቀፈ ተቋም? አሊያም ደግሞ ተኮትኩቶ ለማደግ፣ እውቀት ለመቅሰምና ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ የሚያስችል ምቹ ስፍራ? ጥሩ ቤተሰብ ውስጥ የምትኖር ከሆነ እነዚህ ነገሮች ወደ አእምሮህ መምጣታቸው አይቀርም። የቤተሰብ መሥራች ይሖዋ ነው። (ኤፌ. 3:14, 15) ይሖዋ በሰማይና በምድር ያሉት ፍጥረታቱ በሙሉ የደኅንነት ስሜት እንዲሰማቸው እንዲሁም በመካከላቸው የመተማመን መንፈስ እንዲሰፍንና እውነተኛ አንድነት እንዲኖራቸው ይፈልጋል።

2 አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ የሰው ልጆች በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉትን ፍጥረታት በሙሉ ካቀፈው የይሖዋ ቤተሰብ ወጥተዋል፤ ይሁንና የይሖዋ ዓላማ አልተጨናገፈም። ይሖዋ ገነት የምትሆነው ምድር በአዳም ዘሮች እንድትሞላ ያደርጋል። (ዘፍ. 1:28፤ ኢሳ. 45:18) ይህን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ አስፈላጊውን ዝግጅት በሙሉ አድርጓል። ከእነዚህ ዝግጅቶች መካከል አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በኤፌሶን መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ፤ የዚህ መጽሐፍ ዋነኛ ጭብጥ አንድነት መሆኑ ደግሞ ትኩረት የሚስብ ነው። ከዚህ መጽሐፍ ውስጥ አንዳንድ ጥቅሶችን በመመርመር ይሖዋ ፍጥረታቱን አንድ ለማድረግ ካለው ዓላማ ጋር መተባበር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

አስተዳደሩና ተግባሩ

3. በ⁠ኤፌሶን 1:10 ላይ የተጠቀሰው የአምላክ አስተዳደር ምንድን ነው? ይህ አስተዳደር የሚያከናውነው አንደኛው ምዕራፍ የጀመረውስ መቼ ነው?

3 ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው ከዓላማው ጋር በሚስማማ መልኩ ነው። በመሆኑም አምላክ “በተወሰኑት ዘመናት ማብቂያ ላይ . . . አስተዳደር” አቋቁሟል። ይህ አስተዳደር ይሖዋ፣ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡሮቹን በሙሉ አንድ ለማድረግ ያደረገውን ዝግጅት ያመለክታል። (ኤፌሶን 1:8-10ን አንብብ።) አስተዳደሩ ዓላማውን ዳር ለማድረስ በሁለት ምዕራፎች የተከፈሉ ተግባሮችን ያከናውናል። የመጀመሪያው ምዕራፍ፣ ቅቡዓኑ በኢየሱስ ክርስቶስ የራስነት ሥልጣን ሥር ሆነው ሥራቸውን ማከናወናቸውን እንዲቀጥሉ እነሱን በሰማይ ለሚኖራቸው ሕይወት ማዘጋጀት ነው። ይህ ምዕራፍ የጀመረው ይሖዋ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዙትን መምረጥ በጀመረበት ማለትም በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ዕለት ነው። (ሥራ 2:1-4) አምላክ፣ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ቅቡዓኑን ጻድቃን ብሎ የጠራቸው ከመሆኑም በላይ ሕይወት እንደሚገባቸው አድርጎ ይመለከታቸዋል፤ በዚህም የተነሳ ቅቡዓኑ “የአምላክ ልጆች” ተደርገው እንደተቆጠሩ እርግጠኞች ናቸው።​—ሮም 3:23, 24፤ 5:1፤ 8:15-17

4, 5. አስተዳደሩ የሚያከናውነው ሁለተኛ ምዕራፍ ምንድን ነው?

4 ሁለተኛው ምዕራፍ፣ በክርስቶስ መሲሐዊ መንግሥት በምትተዳደረውና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችን መሰብሰብ ነው። ለዚህ ቡድን መሠረት የሚሆኑት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ናቸው። (ራእይ 7:9, 13-17፤ 21:1-5) በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ደግሞ፣ ከሞት የሚነሱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን ቡድን ይቀላቀላሉ። (ራእይ 20:12, 13) ትንሣኤ የሚያገኙ ብዙ ሰዎች መኖራቸው በመካከላችን ምን ያህል አንድነት እንዳለ ለማሳየት ሰፊ አጋጣሚ ይፈጥርልናል! በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ ‘በምድር ያሉት ነገሮች’ የመጨረሻ ፈተና ይጠብቃቸዋል። ታማኝነታቸውን የሚያስመሠክሩ ሁሉ አምላክ በምድር ላይ እንደሚኖሩ ‘ልጆቹ’ አድርጎ ይቆጥራቸዋል።​—ሮም 8:21፤ ራእይ 20:7, 8

5 ሁለቱም ምዕራፎች ማለትም በሰማይና በምድር ያሉትን ነገሮች የመሰብሰቡ ሥራ በአሁኑ ጊዜ በመከናወን ላይ ነው። ይሁንና በግለሰብ ደረጃ ከአምላክ አስተዳደር ጋር መተባበር የምንችለው እንዴት ነው?

‘የመንፈስን አንድነት ጠብቁ’

6. ክርስቲያኖች አንድ ላይ መሰብሰብ እንዳለባቸው ቅዱሳን መጻሕፍት የሚጠቁሙት እንዴት ነው?

6 ቅዱሳን መጻሕፍት ክርስቲያኖች አንድ ላይ መሰብሰብ እንዳለባቸው ይጠቁማሉ። (1 ቆሮ. 14:23፤ ዕብ. 10:24, 25) ይህ ደግሞ እንደ ገበያ ወይም ስቴዲዮም ወዳሉ ስፍራዎች ሄዶ የተወሰነ ጊዜ ከማሳለፍ ያለፈ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። እንዲህ ባሉ ቦታዎች መሰባሰብ በራሱ እውነተኛ አንድነት አያስገኝም። እውነተኛ አንድነት ሊኖረን የሚችለው የይሖዋን መመሪያዎች ተግባራዊ ስናደርግና በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ለመቀረጽ ፈቃደኞች ስንሆን ነው።

7. ‘የመንፈስን አንድነት መጠበቅ’ ሲባል ምን ማለት ነው?

7 ይሖዋ፣ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ቅቡዓንን እንደ ልጆቹ፣ ሌሎች በጎችን ደግሞ እንደ ወዳጆቹ በመቁጠር ጻድቃን ብሎ ጠርቷቸዋል፤ ያም ቢሆን በዚህ ሥርዓት ውስጥ እስካለን ድረስ በመካከላችን አለመግባባት መከሰቱ አይቀርም። (ሮም 5:9፤ ያዕ. 2:23) እንዲህ ባይሆን ኖሮ “እርስ በርሳችሁ . . . በመቻቻል ኑሩ” የሚለው መለኮታዊ ምክር መሰጠት አያስፈልገውም ነበር። ታዲያ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አንድነት ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው? “ፍጹም ትሕትናና ገርነት” ማዳበር ይኖርብናል። ከዚህም ሌላ ጳውሎስ “አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ” ልባዊ ጥረት እንድናደርግ አበረታቶናል። (ኤፌሶን 4:1-3ን አንብብ።) ይህን ምክር በሥራ ላይ ማዋል የአምላክ መንፈስ እንዲመራንና ይህ መንፈስ በውስጣችን ግሩም የሆኑ ባሕርያትን እንዲያፈራ መፍቀድ ይጠይቃል። የመንፈስ ፍሬ ደግሞ ከፋፋይ ከሆኑት የሥጋ ሥራዎች በተቃራኒ በግለሰቦች መካከል ያለው ልዩነት እንዲጠፋና በመካከላቸው አንድነት እንዲኖር ያደርጋል።

8. “የሥጋ ሥራዎች” ለአንድነት ፀር የሆኑት እንዴት ነው?

8 “የሥጋ ሥራዎች” ለአንድነት ፀር የሆኑት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። (ገላትያ 5:19-21ን አንብብ።) ዝሙት፣ አንድ ሰው ከይሖዋና ከጉባኤው ጋር ያለው ዝምድና እንዲቋረጥ ያደርጋል፤ ምንዝር ደግሞ ልጆች ከወላጆች እንዲነጠሉ እንዲሁም በደል የተፈጸመበት ወገን ከትዳር ጓደኛው እንዲለያይ ሊያደርግ ይችላል። ርኩሰት አንድ ሰው ከአምላክና ከሚወዳቸው ሰዎች ጋር ያለውን አንድነት ያናጋበታል። አንድ ሰው ሁለት ነገሮችን ማጣበቅ ከፈለገ ሙጫውን ከማድረጉ በፊት ሁለቱም ነገሮች ንጹሕ መሆን ይኖርባቸዋል። የብልግና ድርጊቶችን የሚፈጽም ሰው ለአምላክ የጽድቅ ሕጎች ከፍተኛ ንቀት እንዳለው ያሳያል። ሌሎቹ የሥጋ ሥራዎችም ሰዎች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከአምላክ ጋር ያላቸውን አንድነት ያሳጣሉ። እንዲህ ያሉ ምግባሮች ከይሖዋ ባሕርያት ጋር ጨርሶ አይጣጣሙም።

9. “የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት” እያደረግን መሆን አለመሆናችንን ማረጋገጥ የምንችለው እንዴት ነው?

9 በመሆኑም እያንዳንዳችን ራሳችንን እንደሚከተለው በማለት መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘“አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት” እያደረግኩ ነው? ከአንድ የእምነት ባልንጀራዬ ጋር ችግር ቢያጋጥመኝ ምን አደርጋለሁ? ሰዎች ከእኔ ጎን እንዲቆሙ ለማድረግ ስል ብሶቴን አገር እንዲያውቀው አደርጋለሁ? ከወንድሜ ጋር የነበረኝን ሰላማዊ ግንኙነት ለማደስ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ሽማግሌዎች ጣልቃ ገብተው እንዲፈቱልኝ እጠብቃለሁ? አንድ ወንድም እንደተቀየመኝ ባውቅ ጉዳዩን አንስቶ ላለመነጋገር ስል በተቻለ መጠን ከእሱ ጋር ላለመገናኘት ጥረት አደርጋለሁ? እንዲህ ማድረጌ ይሖዋ ሁሉንም ነገር በክርስቶስ አማካኝነት በድጋሚ ለመጠቅለል ካለው ዓላማ ጋር ተስማምቼ እንደምኖር ያሳያል?’

10, 11. (ሀ) ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን ሰላም መጠበቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ሰላምና መንፈሳዊ ብልጽግና እንዲኖር አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ነገሮች ምንድን ናቸው?

10 ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲያው መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር እርቅ ፍጠር፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ። . . . ፈጥነህ እርቅ ፍጠር።” (ማቴ. 5:23-25) ያዕቆብም ቢሆን “ሰላም ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች የጽድቅን ዘር ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ይዘሩና የጽድቅ ፍሬ ያጭዳሉ” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 3:17, 18) በመሆኑም በመካከላችን ሰላም ሳይኖር ጽድቅ የሚንጸባረቅበት ምግባር እናሳያለን ማለት አይቻልም።

11 እስቲ ነገሩን በምሳሌ ለማየት እንሞክር፦ ጦርነት ባጠቃቸው አንዳንድ አገሮች ውስጥ በተቀበሩ ፈንጂዎች ምክንያት ገበሬዎች 35 በመቶ የሚሆነውን አካባቢ ማልማት አልቻሉም። የተቀበሩት ቦንቦች ሲፈነዱ ገበሬዎቹ የሚያርሱትን መሬትና መተዳደሪያቸውን የሚያጡ ሲሆን በከተማ ያሉ ሰዎች ደግሞ የሚበላ ነገር አያገኙም። በተመሳሳይም ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን ሰላም የሚያደፈርሱ ባሕርያት ካሉን መንፈሳዊ እድገታችን ይገታል። በሌላ በኩል ደግሞ ይቅር ለማለት ፈጣኖች ከሆንንና ለሌሎች መልካም ነገር የምናደርግ ከሆነ መንፈሳዊ ብልጽግና እናገኛለን።

12. ሽማግሌዎች አንድነት እንዲኖረን የሚረዱን እንዴት ነው?

12 ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችም’ ለአንድነት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። እነዚህ ወንድሞች “በእምነት . . . ወደሚገኘው አንድነት” እንድንደርስ ይረዱናል። (ኤፌ. 4:8, 13) ሽማግሌዎች በቅዱስ አገልግሎት አብረውን በመካፈልና በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ምክር በመለገስ አዲሱን ስብዕና በመልበስ ረገድ እድገት እንድናደርግ ይረዱናል። (ኤፌ. 4:22-24) ታዲያ ሽማግሌዎች የሚሰጡህን ምክር፣ ይሖዋ በልጁ ወደሚተዳደረው አዲስ ዓለም አንተን ለማስገባት ያደረገው ዝግጅት እንደሆነ አድርገህ ትመለከተዋለህ? እናንት ሽማግሌዎችስ፣ ሌሎችን በመንፈሳዊ ለማስተካከል ጥረት የምታደርጉት ይህን በአእምሯችሁ በመያዝ ነው?​—ገላ. 6:1

‘አንዳችሁ ለሌላው ደጎች ሁኑ’

13. በ⁠ኤፌሶን 4:25-32 ላይ የሚገኘውን ምክር በሥራ ላይ አለማዋል ምን ውጤት ሊያስከትል ይችላል?

13 ኤፌሶን 4:25-29 ልናስወግዳቸው የሚገቡ ባሕርያትን ለይቶ ይጠቅሳል። ውሸት፣ ቁጣ፣ ስንፍና እንዲሁም መልካምና የሚያንጽ ነገር ከመናገር ይልቅ የበሰበሰ ቃል መናገር ከእነዚህ መካከል ይፈረጃሉ። አንድ ሰው ይህን ምክር በሥራ ላይ የማያውል ከሆነ ለአንድነት አስተዋጽኦ የሚያደርገውን ኃይል ይኸውም የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ያሳዝናል። (ኤፌ. 4:30) ጳውሎስ ቀጥሎ የጠቀሳቸውን ነገሮች ተግባራዊ ማድረግ ደግሞ ሰላማችንንና አንድነታችንን ለመጠበቅ ይረዳናል፤ እንዲህ ብሏል፦ “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ መካከል ይወገድ። ይልቁንም አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ።”​—ኤፌ. 4:31, 32

14. (ሀ) ‘ደጎች ሁኑ’ የሚለው ሐረግ ምን ሐሳብ ያስተላልፋል? (ለ) ደግ ለመሆን ምን ሊረዳን ይችላል?

14 “ደጎች . . . ሁኑ” የሚለው ሐረግ አንዳንድ ጊዜ ደግነት የጎደለው ነገር ልናደርግ እንደምንችልና በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብን ይጠቁማል። ከራሳችን ይልቅ የሌሎችን ስሜት ለመጠበቅ ጥረት ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! (ፊልጵ. 2:4) እርግጥ ለመናገር ያሰብነው ነገር ሌሎችን ሊያስቅ ወይም ሊያስደምም ይችል ይሆናል፤ ይሁንና ብንናገረው ደግነት ይሆናል? ከመናገራችን በፊት አስቀድመን ማሰባችን “ደጎች” እንድንሆን ይረዳናል።

ፍቅርንና አክብሮትን ከቤተሰብ መማር

15. ኤፌሶን 5:28 ባሎች ክርስቶስን ሊመስሉ የሚችሉባቸውን የትኞቹን ነገሮች ይጠቅሳል?

15 መጽሐፍ ቅዱስ በባልና በሚስት መካከል ያለውን ዝምድና ለማስረዳት ክርስቶስ ከጉባኤው ጋር ያለውን ዝምድና ምሳሌ አድርጎ ይጠቀማል። አንድ ባል የክርስቶስን ምሳሌ መከተሉ ለሚስቱ አመራር እንዲሰጥ እንዲሁም ፍቅርና አሳቢነት እንዲያሳያት ይረዳዋል፤ አንዲት ሚስትም ብትሆን የክርስቶስን አርዓያ መከተሏ ለባሏ ራስነት እንድትገዛ ይረዳታል። (ኤፌ. 5:22-33) ጳውሎስ፣ “በዚህ መንገድ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል” በማለት ጽፏል፤ ታዲያ “መንገድ” ሲል ምን ማለቱ ነው? (ኤፌ. 5:28) ጳውሎስ ቀደም ባሉት ቁጥሮች ላይ “ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደና ለእሱ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ” እንዲሁም “ጉባኤውን በቃሉ አማካኝነት በውኃ አጥቦ [እንዳነጻ]” ጽፏል፤ በመሆኑም “መንገድ” ሲል እነዚህን ነገሮች ማመልከቱ ነው። በእርግጥም አንድ ባል፣ ይሖዋ ሁሉንም ነገሮች በክርስቶስ እንደገና ለመጠቅለል ካለው ዓላማ ጋር ለመስማማት ከፈለገ ቤተሰቡን በመንፈሳዊ በመመገብ ረገድ ንቁ መሆን ይኖርበታል።

16. ወላጆች በቤት ውስጥ ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ምን ውጤት ያገኛሉ?

16 ወላጆች፣ ልጆችን ማሳደግ ከይሖዋ የተቀበሉት ኃላፊነት እንደሆነ ማስታወሳቸው ተገቢ ነው። የሚያሳዝነው ግን በምንኖርበት ዓለም ብዙዎች “ተፈጥሯዊ ፍቅር” የላቸውም። (2 ጢሞ. 3:1, 3) በርካታ አባቶች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ስለማይወጡ በልጆቻቸው ስሜት ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ይሁንና ጳውሎስ ክርስቲያን ለሆኑ አባቶች እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል፦ “ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ አሳድጓቸው።” (ኤፌ. 6:4) ልጆች ፍቅርንና ለሥልጣን አክብሮት ማሳየትን በቅድሚያ መማር ያለባቸው በቤት ውስጥ ነው። ወላጆች እነዚህን ነገሮች ለልጆቻቸው ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚያስተምሩ ከሆነ ከይሖዋ አስተዳደር ጋር የሚስማማ ተግባር እያከናወኑ ነው ሊባል ይችላል። ቁጣን፣ ንዴትንና ስድብን በማስወገድ ቤታችን ፍቅር የሰፈነበት እንዲሆን የምናደርግ ከሆነ ልጆቻችን ፍቅርንና ለሥልጣን አክብሮት ማሳየትን በተመለከተ ጠቃሚ ትምህርት ያገኛሉ። ይህ ደግሞ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለሚኖረው ሕይወት ያዘጋጃቸዋል።

17. ዲያብሎስን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

17 በጽንፈ ዓለም ውስጥ የነበረውን ሰላም ያደፈረሰው ዲያብሎስ፣ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ጥረት ስናደርግ እጁን አጣጥፎ እንደማይቀመጥ እናውቃለን። የፍቺ ቁጥር ማሻቀቡ፣ ጋብቻ አብሮ መኖር በሚል ፈሊጥ መተካቱና ግብረ ሰዶም ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ ብዙዎች የሰይጣንን ዓላማ እያራመዱ እንዳለ የሚያሳይ ነው። በዚህ ዓለም ላይ የሚታየው ዘመን አመጣሽ አስተሳሰብ ወይም አመለካከት እንዲቀርጸን አንፈልግም። መከተል የምንፈልገው የክርስቶስን አርዓያ ነው። (ኤፌ. 4:17-21) በመሆኑም ሰይጣንና አጋንንቱ የሚሰነዝሩትን ጥቃት መቋቋም እንድንችል “ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ [እንድንለብስ]” ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል።​—ኤፌሶን 6:10-13ን አንብብ።

“በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ”

18. ለክርስቲያናዊ አንድነታችን ቁልፉ ምንድን ነው?

18 ለክርስቲያናዊ አንድነታችን ቁልፉ ፍቅር ነው። ልባችን ‘ለአንዱ ጌታ፣’ ‘ለአንዱ አምላክ’ እና ለወንድሞቻችን ባለን ፍቅር በመሞላቱ “አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ” ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። (ኤፌ. 4:3-6) ኢየሱስ ስለዚህ ዓይነቱ ፍቅር ሲጸልይ እንዲህ ብሏል፦ “የምለምንህ ስለ እነዚህ ብቻ ሳይሆን በእነሱ ቃል አማካኝነት በእኔ ለሚያምኑ ጭምር ነው፤ ይህን ልመና የማቀርበውም ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ ነው፤ አባት ሆይ፣ አንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለህና እኔም ከአንተ ጋር አንድነት እንዳለኝ ሁሉ እነሱም ከእኛ ጋር አንድነት እንዲኖራቸው . . . ነው። እኔን የወደድክበትን ፍቅር እነሱም እንዲያንጸባርቁ እንዲሁም እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት እንዲኖረኝ ስምህን ለእነሱ አሳውቄአለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ።”​—ዮሐ. 17:20, 21, 26

19. ምን ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል?

19 ፍጹማን ባለመሆናችን ምክንያት በውስጣችን ከአንድ ዓይነት ባሕርይ ጋር እየታገልን ከሆነ ፍቅር እንደ መዝሙራዊው “ስምህን እፈራ ዘንድ፣ ያልተከፋፈለ ልብ ስጠኝ” በማለት እንድንጸልይ ይገፋፋናል። (መዝ. 86:11) ዲያብሎስ እኛን ከአፍቃሪው አባታችንም ሆነ ከሕዝቦቹ ለማራቅ የሚያደርገውን ጥረት ለመቋቋም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንግዲያው “የተወደዳችሁ ልጆች በመሆን አምላክን” ለመምሰል ጠንክራችሁ ሥሩ፤ በተጨማሪም በቤተሰባችሁና በጉባኤ ውስጥ እንዲሁም አገልግሎታችሁን በምታከናውኑበት ወቅት “በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ።”​—ኤፌ. 5:1, 2

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መባውን በመሠዊያው ፊት ትቶ ከወንድሙ ጋር እርቅ ለመፍጠር ሲሄድ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች፣ ልጆቻችሁ አክብሮት እንዲያሳዩ አስተምሯቸው