በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ ፈቃዱን እንዳደርግ አስተምሮኛል

ይሖዋ ፈቃዱን እንዳደርግ አስተምሮኛል

ማክስ ሎይድ እንደተናገሩት

ጊዜው 1955 ሲሆን እኔና አብሮኝ የሚያገለግለው ሚስዮናዊ ደቡብ አሜሪካ ውስጥ በምትገኘው በፓራጓይ እያገለገልን ነበር። አንድ ቀን ምሽት ቤታችን በቁጣ በተሞሉ በርካታ ሰዎች ተከበበ፤ “አምላካችን ደም የተጠማ አምላክ ነው፤ የግሪንጎዎችን ደም ይፈልጋል” በማለት ይጮኹ ነበር። ለመሆኑ እኛ ግሪንጎዎች (የውጭ አገር ዜጎች) ወደዚህ አገር የመጣነው እንዴት ነው?

ታሪኬ የሚጀምረው በአውስትራሊያ ነው፤ ያደግኩትም ሆነ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ የተማርኩት በዚህ አገር ነው። በ1938 አንድ የይሖዋ ምሥክር ጠላቶች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ለአባቴ ሰጠው። በአካባቢው ያሉት የሃይማኖት መሪዎች፣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አፈ ታሪክ እንደሆነ ያስተምሩ ስለነበረ አባቴና እናቴ በእምነታቸው ደስተኞች አልነበሩም። በመሆኑም ወላጆቼ ከአንድ ዓመት በኋላ ራሳቸውን ለይሖዋ በመወሰን ተጠመቁ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ፣ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ በቤተሰባችን ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ሆነ። በኋላም በአምስት ዓመት የምትበልጠኝ እህቴ ሌዝሊ ተጠመቀች፤ እኔ ደግሞ በ1940 በዘጠኝ ዓመቴ ተጠመቅኩ።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ በአውስትራሊያ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማተምም ሆነ ማሰራጨት ታገዱ። በመሆኑም ገና በልጅነቴ መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ በመጠቀም ስለ እምነቴ እንዴት ማስረዳት እንዳለብኝ ተማርኩ። ለባንዲራ ሰላምታ የማልሰጠው ወይም ጦርነቱን የማልደግፈው ለምን እንደሆነ ለማስረዳት መጽሐፍ ቅዱሴን ወደ ትምህርት ቤት ይዤ መሄድ ልማድ አደረግኩ።​—ዘፀ. 20:4, 5፤ ማቴ. 4:10፤ ዮሐ. 17:16፤ 1 ዮሐ. 5:21

አብረውኝ የሚማሩ ልጆች “የጀርመን ሰላይ” እያሉ ስለሚጠሩኝ ብዙዎች ከእኔ ጋር መሆን አይፈልጉም ነበር። በወቅቱ በትምህርት ቤት ውስጥ ፊልም ይታይ ነበር። ፊልሙ ከመጀመሩ በፊት ሁሉም ተነስቶ የአገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር ይዘምራል። እኔ ግን ለመነሳት ፈቃደኛ ሳልሆን ስቀር ለሁለት ወይም ለሦስት ሆነው ፀጉሬን እየጎተቱ ከወንበሬ ለማስነሳት ይሞክራሉ። በኋላም በእምነቴ ምክንያት ከትምህርት ቤት ተባረርኩ። ይሁንና ቤቴ ሆኜ በተልእኮ ትምህርቴን ተከታተልኩ።

ግቤ ላይ ደረስኩ

አሥራ አራት ዓመት ሲሆነኝ አቅኚ በመሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ግብ አወጣሁ። ይሁንና ወላጆቼ በመጀመሪያ ሥራ መያዝ እንዳለብኝ ሲነግሩኝ በጣም አዘንኩ። ከእነሱ ጋር እስከኖርኩ ድረስ ለማደሪያና ለምግብ መክፈል እንዳለብኝ የነገሩኝ ሲሆን 18 ዓመት ሲሞላኝ ግን አቅኚ መሆን እንደምችል ቃል ገቡልኝ። በዚህም የተነሳ ከማገኘው ገንዘብ ጋር በተያያዘ ከወላጆቼ ጋር በየጊዜው እጨቃጨቅ ነበር። ገንዘቡን ወደፊት ለአቅኚነት እንዲረዳኝ ላጠራቅመው እንደምፈልግ ብናገርም እነሱ ግን ይወስዱብኝ ነበር።

አቅኚነት የምጀምርበት ጊዜ ሲደርስ ወላጆቼ የምሰጣቸውን ገንዘብ በባንክ ያጠራቅሙልኝ እንደነበር ነገሩኝ። ከዚያም ልብስና ለአቅኚነት የሚያስፈልጉ ሌሎች ነገሮችን እንድገዛበት ገንዘቡን በሙሉ መለሱልኝ። ከሌሎች ከመጠበቅ ይልቅ እንዴት ራሴን ማስተዳደር እንደምችል እያስተማሩኝ ነበር። አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው የሰጡኝ ሥልጠና በጣም ጠቅሞኛል።

እኔና ሌዝሊ ትናንሾች እያለን አቅኚዎች ብዙ ጊዜ ቤታችን በእንግድነት ያርፉ ነበር፤ እኛም ከእነሱ ጋር ማገልገል ያስደስተን ነበር። ቅዳሜና እሁድ ከቤት ወደ ቤትና መንገድ ላይ በማገልገል እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በማስጠናት ጊዜያችንን እናሳልፋለን። በዚያን ወቅት አንድ አስፋፊ በወር 60 ሰዓት የማገልገል ግብ ይዞ እንዲንቀሳቀስ ይበረታታ ነበር። እናቴ፣ ሁልጊዜ ማለት ይቻላል የሰዓት ግቧን ታሳካ ነበር፤ በመሆኑም በዚህ ረገድ ለእኔና ለሌዝሊ ግሩም ምሳሌ ሆናልናለች።

በታዝሜንያ በአቅኚነት ማገልገል

አቅኚ ስሆን መጀመሪያ የተመደብኩት የአውስትራሊያ ደሴት በሆነችው በታዝሜንያ ነው፤ በዚያም ከእህቴና ከባለቤቷ ጋር አብሬ ማገልገል ጀመርኩ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ እህቴና ባለቤቷ በጊልያድ ትምህርት ቤት በ15ኛው ክፍል ገብተው እንዲሠለጥኑ ስለተጋበዙ ወደዚያ ሄዱ። በጣም ዓይናፋር የነበርኩ ከመሆኑም በላይ ከቤተሰቤ ርቄ አላውቅም። አንዳንዶች ከሦስት ወር በላይ እንደማልቆይ ተሰምቷቸው ነበር። ይሁንና እዚያ በሄድኩ በዓመቴ ማለትም በ1950 የቡድን አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ (በአሁኑ ጊዜ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ይባላል)። በኋላም ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል የተሾምኩ ሲሆን አንድ ወጣት ወንድም የአገልግሎት ጓደኛዬ ሆነ።

የአገልግሎት ምድባችን ርቃ የምትገኝና መዳብ የሚወጣባት ከተማ ስትሆን በዚያም አንድም የይሖዋ ምሥክር አልነበረም። አውቶቡስ ተሳፍረን አመሻሹ ላይ ወደዚያ አካባቢ ደረስን። የዚያን ዕለት ሌሊት አንድ የድሮ ሆቴል ውስጥ አደርን። በሚቀጥለው ቀን ከቤት ወደ ቤት ለማገልገል ስንሄድ የቤቶቹን ባለቤቶች የሚከራይ ክፍል ያውቁ እንደሆነ እንጠይቃቸው ነበር። የቀኑ መገባደጃ ላይ አንድ ሰው ከፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን አጠገብ የሚገኘው የአገልጋዩ ቤት ባዶ እንደሆነ ሆኖም ዲያቆኑን ማናገር እንዳለብን ነገረን። ይህ ሰው ወዳጃዊ በሆነ መንፈስ ያነጋገረን ከመሆኑም በላይ ቤቱን እንድንከራይ ፈቀደልን። በየዕለቱ ለስብከት የምንወጣው ከዲያቆኑ ቤት መሆኑ እንግዳ ነገር ይመስል ነበር።

የአገልግሎት ክልሉ ፍሬያማ ነበር። ከሰዎች ጋር ግሩም ውይይቶች እናደርግ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ብዙዎቹ ጥናት ይጀምሩ ነበር። በዋና ከተማው ያሉ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች ስለምናደርገው እንቅስቃሴ ሲያውቁ እንዲሁም የት እንደምንኖር ሲሰሙ ዲያቆኑን በአስቸኳይ ከቤቱ እንዲያስወጣን አዘዙት። በዚህም ምክንያት አሁንም ማደሪያ ቦታ አጣን!

በሚቀጥለው ቀን፣ ከጠዋት ጀምሮ ስናገለግል ከቆየን በኋላ ከሰዓት በኋላ ላይ ማደሪያ ቦታ ማፈላለግ ጀመርን። ሆኖም በአንድ ስታዲየም ውስጥ ባሉ ወንበሮች ላይ ከማደር የተሻለ ቦታ ልናገኝ አልቻልንም። በዚህ ቦታ ሻንጣዎቻችንን ደብቀን ካስቀመጥን በኋላ መስበካችንን ቀጠልን። ጊዜው እየመሸ ቢሄድም የቀሩንን ትንሽ ቤቶች ለመጨረስ ተስማማን። አንድ ቤት ጋ ስንደርስ፣ የቤቱ ባለቤት በጓሮ በኩል ያለውን ባለ ሁለት ክፍል ቤት እንድንኖርበት ፈቀደልን።

የወረዳ ሥራና ጊልያድ

በዚያ አካባቢ ለስምንት ወራት ካገለገልኩ በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንድሆን ከአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ ግብዣ ቀረበልኝ። ገና 20 ዓመቴ ስለነበር ግብዣው ሲደርሰኝ በጣም ደነገጥኩ። ለተወሰኑ ሳምንታት ሥልጠና ከወሰድኩ በኋላ ጉባኤዎችን ለማበረታታት መደበኛ ጉብኝት ማድረግ ጀመርኩ። በዕድሜ የሚበልጡኝ ወንድሞች፣ ለነገሩ ከእኔ የማይበልጥ የለም ብል ይሻላል፣ ወጣትነቴን ሳይንቁ ለምሠራው ሥራ አክብሮት ያሳዩ ነበር።

ከአንድ ጉባኤ ወደ ሌላ ጉባኤ ለመሄድ የምጠቀምበት ትራንስፖርት በጣም የተለያየ ነበር። አንድ ሳምንት በአውቶቡስ፣ በሌላ ሳምንት ደግሞ በባቡር ከዚያም በመኪና አሊያም ደግሞ በሞተር ብስክሌት እጓዝ ነበር፤ ሻንጣዬንና የአገልግሎት ቦርሳዬን እንደያዝኩ ሚዛኔን ጠብቄ በሞተር ብስክሌት መጓዝ በጣም ከባድ ነበር። በወንድሞች ቤት ማረፍ በጣም አስደሳች ነገር ነበር። ለምሳሌ፣ አንድ የቡድን አገልጋይ (በአሁኑ ጊዜ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ይባላል) ቤቱ ተገንብቶ ያላለቀ ቢሆንም እንኳ እሱ ጋር እንዳርፍ በጣም ጓጉቶ ነበር። በዚያ ሳምንት የተኛሁት በመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ በተዘጋጀልኝ አልጋ ላይ ቢሆንም ከወንድም ጋር የሚያንጽ ሳምንት አሳልፈናል።

በ1953 ሌላ ያልጠበቅኩት ነገር አጋጠመኝ፤ በጊልያድ ትምህርት ቤት 22ኛ ክፍል ገብቼ እንድሠለጥን ማመልከቻ ደረሰኝ። በአንድ በኩል ደስ ቢለኝም በሌላ በኩል ግን ስጋት አደረብኝ። ምን መሰላችሁ፣ እህቴና ባለቤቷ ሐምሌ 30, 1950 ከጊልያድ ከተመረቁ በኋላ ፓኪስታን ተመድበው ነበር። ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሌዝሊ ታመመችና ሕይወቷ አለፈ። ‘ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ እኔ ደግሞ ሌላ ቦታ ብሄድ ወላጆቼ ምን ይሰማቸዋል?’ የሚለው ነገር አስጨነቀኝ። እነሱ ግን “ይሖዋ ወደመራህ ቦታ ሄደህ አገልግል” አሉኝ። አባቴ በ1950ዎቹ መጨረሻ ላይ ስለሞተ ከዚያ ወዲያ አላገኘሁትም።

ብዙም ሳይቆይ ከሌሎች አምስት አውስትራሊያውያን ጋር በመርከብ ተሳፍረን ወደ ኒው ዮርክ ሲቲ አመራን። ስድስት ሳምንት በፈጀው በዚህ ጉዞ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን እናነብና እናጠና እንዲሁም ለሌሎች ተሳፋሪዎች እንሰብክ ነበር። ትምህርት ቤቱ ወደሚገኝበት ሳውዝ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ ከመጓዛችን በፊት ሐምሌ 1953 በያንኪ ስታዲየም በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ተገኘን። በስብሰባው ላይ የነበረው ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር 165,829 ነበር!

በክፍላችን ውስጥ የነበሩት 120 ተማሪዎች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ናቸው። እስከ ምረቃው ቀን ድረስ የአገልግሎት ምድባችን የት እንደሆነ አልተነገረንም ነበር። ምድባችንን ስንሰማ ወዲያውኑ ስለ አገሮቹ ለማወቅ ወደ ጊልያድ ቤተ መጻሕፍት እየተጣደፍን ሄድን። እኔ የተመደብኩባት አገር ማለትም ፓራጓይ ከፍተኛ ፖለቲካዊ አብዮት እየተካሄደባት እንዳለ ተረዳሁ። እዚያ ከሄድኩ ብዙም ሳልቆይ አንድ ቀን ጠዋት ላይ ሕዝቡ “ደስታውን ሲገልጽ” የነበረው ምን ተገኝቶ እንደሆነ ሌሎቹን ሚስዮናውያን ጠየቅኳቸው። እነሱም እየሳቁ “አብዮታዊ እንቅስቃሴ ነው፤ እንግዲህ ለአንተ የመጀመሪያህ መሆኑ ነው። እስቲ በፊተኛው በር ወደ ውጪ ተመልከት” አሉኝ። ወታደሮች በየጥጉ ቆመው ነበር!

የማይረሳ ተሞክሮ

በአንድ አጋጣሚ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ርቆ የሚገኝን ጉባኤ ሲጎበኝና ዘ ኒው ወርልድ ሶሳይቲ ኢን አክሽን የተባለውን ፊልም ሲያሳይ አብሬው ነበርኩ። መጀመሪያ በባቡር ቀጥሎም በፈረስ ጋሪ ከዚያም በበሬ በሚጎተት ጋሪ ለስምንት ወይም ለዘጠኝ ሰዓት ገደማ ተጓዝን። በዚህ ላይ ደግሞ ጀነሬተርና የፊልም ማሳያ ፕሮጀክተር ይዘን ነበር። ያሰብንበት ቦታ ከደረስን በኋላ በማግስቱ በእርሻ ላይ የሚሠሩትን ሰዎች አነጋገርናቸው፤ እንዲሁም ሁሉንም ምሽት ላይ በሚታየው ፊልም ላይ እንዲገኙ ጋበዝናቸው። በዚያም ወደ 15 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተገኝተዋል።

ፊልሙን ለ20 ደቂቃ ያህል ካሳየን በኋላ በፍጥነት ወደ ቤት እንድንገባ ተነገረን። ወዲያውኑ ፕሮጀክተሩን ይዘን ወደ ውስጥ ገባን። በርካታ ሰዎች መሣሪያ እየተኮሱ “አምላካችን ደም የተጠማ አምላክ ነው፤ የግሪንጎዎችን ደም ይፈልጋል” በማለት በተደጋጋሚ እየጮኹ የተናገሩት በዚህ ጊዜ ነበር። እዚያ የነበርነው ግሪንጎዎች ደግሞ ሁለት ነበርን። ፊልሙን ይመለከቱ የነበሩት ሰዎች፣ በቁጣ የተሞላው ሕዝብ በራችንን ሰብሮ እንዳይገባ ጥረት አድርገዋል። ይሁንና ተቃዋሚዎቹ እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ቆዩ፤ ከዚያም እየተኮሱና ወደ ቤታችን ስንሄድ እንደሚያገኙን እየዛቱ ተመለሱ።

ወንድሞች የፖሊስ አዛዡን ያነጋገሩት ሲሆን ከሰዓት በኋላ ሁለት ፈረሶችን ይዞ ወደ ከተማ ሊወስደን መጣ። ፖሊሱ በመንገዳችን ላይ ችምችም ያለ ቁጥቋጦ ወይም ዛፍ በተመለከተ ቁጥር ጠመንጃውን አቀባብሎ አካባቢውን ይቃኝ ነበር። በዚህ ወቅት ፈረስ በጣም አስፈላጊ የሆነ መጓጓዣ እንደሆነ ስላስተዋልኩ ከጊዜ በኋላ እኔም አንድ ፈረስ ገዛሁ።

ሚስዮናውያን ተጨመሩ

የሃይማኖት መሪዎች በየጊዜው ተቃውሞ ቢያስነሱም እንኳ የስብከቱ ሥራ ጥሩ ውጤት ነበረው። በ1955 አምስት አዳዲስ ሚስዮናውያን ወደዚህ ቦታ የመጡ ሲሆን ከእነሱ መካከል ከጊልያድ ትምህርት ቤት 25ኛው ክፍል የተመረቀችው ኤልሲ ስዋንሰን የተባለች ካናዳዊት እህት ትገኝበታለች። ኤልሲ ወደ ሌላ ከተማ ከመመደቧ በፊት በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ አብረን ሠርተናል። ኤልሲ ከወላጆቿ ድጋፍ ባታገኝም ይሖዋን በቅንዓት ታገለግል ነበር፤ የኤልሲ ወላጆች እስከ መጨረሻው እውነትን አልተቀበሉም። እኔና ኤልሲ ታኅሣሥ 31, 1957 ከተጋባን በኋላ በፓራጓይ ደቡባዊ ክፍል በሚገኝ አንድ የሚስዮናውያን ቤት ውስጥ ብቻችንን መኖር ጀመርን።

ቤታችን ውስጥ የቧንቧ ውኃ ስላልነበረ ውኃ የምንቀዳው ከቤታችን ጀርባ ከሚገኘው ጉድጓድ ነበር። በመሆኑም ቤት ውስጥ ሻወር፣ መታጠቢያ ቤት፣ ልብስ ማጠቢያ ማሽን ሌላው ቀርቶ ማቀዝቀዣ እንኳ አልነበረም። ቶሎ የሚበላሹ የምግብ ዓይነቶችን የምንገዛው የዕለት የዕለቱን ነበር። ያም ሆኖ አኗኗራችን ቀላል መሆኑና በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞቻንንና እህቶቻችን ያሳዩን የነበረው ፍቅር በዚያን ወቅት አስደሳች ሕይወት እንድንመራ አድርጎናል።

በ1963 እናቴን ለመጠየቅ ወደ አውስትራሊያ ከሄድን ብዙም ሳይቆይ ልብ ድካም ያዛት። የተገናኘነው ከአሥር ዓመት በኋላ ስለሆነ በጣም ተደስታ ነበር፤ ምናልባትም ለሕመሟ ምክንያት የሆነው ይህ ሳይሆን አይቀርም። ወደ ፓራጓይ የምንመለስበት ጊዜ ሲደርስ አንድ ከባድ ውሳኔ ከፊታችን ተደቀነ። ይኸውም በሆስፒታል የተኛችውን እናቴን አንድ ሰው እንደሚንከባከባት ተስፋ በማድረግ ትተናት ወደምንወደው የአገልግሎት ምድብ መሄድ ወይም መቅረት ነበር። እኔና ኤልሲ ነገሩን በጸሎት በደንብ ካሰብንበት በኋላ እዚያው ቀርተን እናቴን ለመንከባከብ ወሰንን። እናቴ እስከሞተችበት እስከ 1966 ድረስ የተንከባከብናት ሲሆን በዚህ ጊዜ ሁሉ የሙሉ ጊዜ አገልግሎታችንን አላቋረጥንም።

በአውስትራሊያ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በወረዳና በአውራጃ ሥራ የማገልገልና ለሽማግሌዎች በሚዘጋጀው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ የማስተማር መብት አግኝቻለሁ። ከዚህ በኋላ ደግሞ ሌላ ለውጥ መቀበል ነበረብን። በአውስትራሊያ ከመጀመሪያዎቹ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ የመሆን መብት አገኘሁ። ከዚያም አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ስንሠራ የግንባታ ኮሚቴው ሊቀ መንበር ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ተሞክሮ ባላቸውና ራሳቸውን ለማቅረብ ፈቃደኛ በሆኑ ወንድሞች ትብብር በጣም ውብ የሆነ ቅርንጫፍ ቢሮ መገንባት ችለናል።

ከዚያም በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ማገልገል የጀመርኩ ሲሆን ይህ ክፍል በአገሪቱ የሚከናወነውን የስብከት ሥራ በበላይነት ይቆጣጠራል። በኋላም የዞን የበላይ ተመልካች በመሆን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የተለያዩ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን የመጎብኘት መብት አግኝቻለሁ፤ ይህ ደግሞ በዚያ ያሉትን ወንድሞች የመርዳትና የማበረታታት አጋጣሚ ሰጥቶኛል። በተለይ ደግሞ በአንዳንድ አገሮች ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል ሲሉ ለዓመታት እንዲያውም ለአሥርተ ዓመታት በእስር ቤትና በማጎሪያ ካምፖች ያሳለፉ ወንድሞችን ማግኘቴ እምነቴን አጠናክሮልኛል።

የአሁኑ ምድባችን

በ2001 አድካሚ ከሆነው የዞን ጉብኝት ስንመለስ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ውስጥ አዲስ በተቋቋመው የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ ለማገልገል መጋበዜን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰኝ። እኔና ኤልሲ ጉዳዩን በጸሎት ካሰብንበት በኋላ ይህን ኃላፊነት በደስታ ተቀበልን። ይህ ከሆነ 11 ዓመታት ያለፉ ሲሆን አሁንም በብሩክሊን እያገለገልን ነው።

ባለቤቴ ይሖዋ የሚጠይቃትን ነገር በሙሉ ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆኗ በጣም ደስተኛ ነኝ። አሁን እኔና ኤልሲ ዕድሜያችን በ80ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲሆን በአንጻራዊ ሁኔታ ጥሩ ጤንነት አለን። ለዘላለም ከይሖዋ ለመማርና ምንጊዜም ፈቃዱን የሚያደርጉ ሰዎች የሚያገኙትን የተትረፈረፈ በረከት ለማግኘት እንናፍቃለን።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንድ ሳምንት በአውቶቡስ፣ በሌላ ሳምንት ደግሞ በባቡር ከዚያም በመኪና አሊያም ደግሞ በሞተር ብስክሌት እጓዝ ነበር፤ ሻንጣዬንና የአገልግሎት ቦርሳዬን እንደያዝኩ ሚዛኔን ጠብቄ በሞተር ብስክሌት መጓዝ በጣም ከባድ ነበር

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ለዘላለም ከይሖዋ ለመማር . . . እንናፍቃለን

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስተግራ፦ በአውስትራሊያ በወረዳ ሥራ ላይ

በስተቀኝ፦ ከወላጆቼ ጋር

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሠርጋችን ዕለት፣ ታኅሣሥ 31, 1957