“ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ”
“ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ”
“ብዙዎች ወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ፤ [“እውነተኛው፣” NW] ዕውቀትም ይበዛል።”—ዳን. 12:4
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
በዘመናችን ‘እውነተኛው እውቀት’ የታወቀው እንዴት ነው?
እውነትን የሚቀበሉ ሰዎች ‘የበዙት’ እንዴት ነው?
ትክክለኛው እውቀት ‘የበዛው’ በየትኞቹ መንገዶች ነው?
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜም ሆነ ወደፊት ከተገዢዎቹ ጋር እንደሚሆን እንዴት እናውቃለን? (ለ) ዳንኤል 12:4 እንደሚናገረው ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥንቃቄ መመርመር ምን ውጤት ያስገኛል?
እስቲ ራስህን በገነት ውስጥ እንዳለህ አድርገህ አስብ። በእያንዳንዱ ቀን ከእንቅልፍህ ስትነቃ ሰውነትህና አእምሮህ እንደታደሰ ስለሚሰማህ ዕለቱን ደስ ብሎህ ትጀምራለህ። የሚሰማህ ምንም ዓይነት ሕመም ወይም ሥቃይ የለም። ከዚህ በፊት የነበሩብህ የአቅም ገደቦች በሙሉ ተወግደዋል። ሁሉም የስሜት ሕዋሶችህ ማለትም የማየት፣ የመስማት፣ የማሽተት፣ የመዳሰስና የመቅመስ ችሎታህ በትክክል ይሠራሉ። ጥሩ ጉልበት አለህ፤ በሥራህ ደስተኛ ነህ፤ ብዙ ጓደኞች አሉህ፤ እንዲሁም የሚያስጨንቅህ ነገር የለም። እነዚህ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የምታገኛቸው በረከቶች ናቸው። በአምላክ የተሾመው ክርስቶስ ኢየሱስ ተገዢዎቹን የሚባርካቸው ከመሆኑም በላይ ሁሉም ሰው ስለ ይሖዋ እንዲማር ያደርጋል።
2 ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው በዚህ የማስተማር ሥራ ሲካፈሉ ከእነሱ ጋር ይሆናል። አምላክና ልጁ ላለፉት ዘመናት ከታማኝ ክርስቲያኖች ጋር ነበሩ። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከመሄዱ በፊት፣ ከታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደሚሆን ማረጋገጫ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 28:19, 20ን አንብብ።) በዚህ ማረጋገጫ ላይ ያለንን እምነት ለማጠናከር ከዛሬ 2,500 ዓመታት በፊት በጥንቷ ባቢሎን ውስጥ በአምላክ መንፈስ መሪነት ከተጻፈ ትንቢት ላይ አንድ ዓረፍተ ነገር እንመልከት። ዳንኤል ስለምንኖርበት ‘የፍጻሜ ዘመን’ ሲጽፍ “ብዙዎች ወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ፤ [“እውነተኛው፣” NW] ዕውቀትም ይበዛል” ብሏል። (ዳን. 12:4) ከዘይቤያዊ አገላለጹ እንዲሁም በዘመናችን ካሉት እውነታዎች በመነሳት “ይራወጣሉ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ግስ በጥንቃቄ ምርምር ማድረግ የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል ብለን መናገር እንችላለን። እንዲህ ያለው መራወጥ በጣም ግሩም ውጤት እንደሚያስገኝ ጥርጥር የለውም! ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥንቃቄ የሚያጠኑ የአምላክ ሕዝቦች በቃሉ ውስጥ ያለውን እውነተኛ ወይም ትክክለኛ እውቀት በማግኘት ይባረካሉ። በተጨማሪም ትንቢቱ ‘እውነተኛው እውቀት እንደሚበዛ’ ይገልጻል። ይህም በአንድ በኩል እውነተኛውን እውቀት ያገኙ ሰዎች ለሌሎች በመንገር እውቀቱን እንደሚያስፋፉት በሌላ በኩል ደግሞ ይህ እውቀት በየትኛውም ቦታ ስለሚገኝ ሰዎች በቀላሉ ሊያገኙት እንደሚችሉ ይጠቁማል። ይህ ትንቢት እንዴት ፍጻሜውን እንዳገኘ መመርመራችን ኢየሱስ አሁንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደሆነና ይሖዋ የገባውን ቃል ሙሉ በሙሉ መፈጸም እንደሚችል እርግጠኛ እንድንሆን ያደርገናል።
‘እውነተኛው እውቀት’ ይታወቃል
3. ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ ‘እውነተኛው እውቀት’ ምን ሆነ?
3 ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ አስቀድሞ በተነገረው መሠረት በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ክህደት የተነሳ ከመሆኑም በላይ ክህደቱ እንደ ሰደድ እሳት ተዛመተ። (ሥራ 20:28-30፤ 2 ተሰ. 2:1-3) ከዚያ ጊዜ ወዲህ ባሉት በርካታ ዘመናት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እውቀት በሌላቸው ሰዎች ዘንድ ይቅርና ክርስቲያን እንደሆኑ በሚናገሩት ዘንድም እንኳ ‘እውነተኛ እውቀት’ ሊገኝ አልቻለም። የሕዝበ ክርስትና መሪዎች በቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚያምኑ ቢናገሩም አምላክን የሚያዋርዱ ‘አጋንንታዊ ትምህርቶችን’ በማስፋፋት ሃይማኖታዊ ውሸቶችን ሲያስተምሩ ቆይተዋል። (1 ጢሞ. 4:1) በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች በመንፈሳዊ ድንቁርና ውስጥ ነበሩ ማለት ይቻላል። ከሃዲዎቹ ከሚያስተምሯቸው ትምህርቶች መካከል አምላክ ሥላሴ ነው፣ ነፍስ አትሞትም እንዲሁም ሰዎች በገሃነመ እሳት ለዘላለም ይሠቃያሉ የሚሉት ይገኙበታል።
4. በ1870ዎቹ አንድ የክርስቲያኖች ቡድን ‘እውነተኛውን እውቀት’ መፈለግ የጀመረው እንዴት ነው?
4 ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ከመጀመራቸው ከአራት አሥርተ ዓመታት በፊት ማለትም በ1870ዎቹ በፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኝ ቅን ልብ ያላቸው ክርስቲያኖችን ያቀፈ አንድ አነስተኛ ቡድን መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ለማጥናትና ‘እውነተኛውን እውቀት’ ለማግኘት መሰብሰብ ጀመረ። (2 ጢሞ. 3:1) የዚህ ቡድን አባላት ራሳቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በማለት ይጠሩ ነበር። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ የጠቀሳቸው ‘ጥበበኞችና አዋቂዎች’ አይደሉም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ እንዲህ ካሉ ሰዎች እውቀት እንደሚሰወር ተናግሯል። (ማቴ. 11:25) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ልባዊ ፍላጎት ያላቸው ትሑት ሰዎች ነበሩ። በጸሎት ታግዘው ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥንቃቄ ያነቡ፣ በዚያ ላይ ይወያዩ እንዲሁም ያሰላስሉ ነበር። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ያመሳክሩ እንዲሁም እንደነሱ ምርምር ያደረጉ ሌሎች ሰዎች ያዘጋጇቸውን ጽሑፎች ያጠኑ ነበር። ውሎ አድሮም እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለብዙ መቶ ዓመታት ተሰውሮ የነበረውን እውነት ማስተዋል ቻሉ።
5. ጥንታዊው መንፈሳዊ ትምህርት የሚል ርዕስ ያላቸው ትራክቶች የተዘጋጁበት ዓላማ ምን ነበር?
5 እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በተማሩት ነገር ቢደሰቱም ባገኙት እውቀት አልተኩራሩም፤ ወይም አዲስ ነገር እንዳገኙ በማሰብ የተለየ ክብር እንዲሰጣቸው አልፈለጉም። (1 ቆሮ. 8:1) ከዚህ ይልቅ ጥንታዊው መንፈሳዊ ትምህርት የሚል ርዕስ ያላቸውን ትራክቶች በተከታታይ ማሳተም ጀመሩ። ዓላማቸው ሰዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት እውነቶች ጋር ማስተዋወቅ ነበር። ከእነዚህ ትራክቶች የመጀመሪያዎቹ “መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ተጨማሪ መሣሪያዎች” በመሆን ያገለገሉ ሲሆኑ ዓላማቸውም “ሐሰተኛ የሆኑ ሰብዓዊ ወጎችን በሙሉ በማስወገድ ጥንታዊ የሆነው የጌታችንና የሐዋርያት መንፈሳዊ ትምህርት ሙሉ በሙሉ እንዲያንሰራራ ማድረግ ነው።”—ጥንታዊው መንፈሳዊ ትምህርት፣ ቁ. 1 (እንግሊዝኛ) ሚያዝያ 1889፣ ገጽ 32
6, 7. (ሀ) ከ1870ዎቹ ዓመታት ወዲህ የትኞቹን እውነቶች መገንዘብ ችለናል? (ለ) አንተን ይበልጥ ያስደሰተህ የትኞቹን እውነቶች ማወቅህ ነው?
6 ከ100 ዓመታት በፊት ጀምሮ እጅግ አስደናቂ የሆኑ በርካታ እውነቶች ተገልጠዋል! * እነዚህ እውነቶች የሃይማኖት ምሁራን እንደሚከራከሩባቸው ያሉ እውቀትን ከማስፋት ያለፈ ፋይዳ የሌላቸው አሰልቺ ትምህርቶች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ሕይወታችን እውነተኛ ትርጉም ያለው ብሎም በደስታና በተስፋ የተሞላ እንዲሆን የሚያደርጉ ልብ የሚነኩና ነፃ የሚያወጡ ትምህርቶች ናቸው። እንዲሁም ይሖዋን እንድናውቅ ማለትም ግሩም የሆኑትን ባሕርያቱንና ዓላማውን እንድንገነዘብ ያስችሉናል። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ የሚጫወተውን ሚና ይኸውም ለምን ወደ ምድር እንደመጣና እንደሞተ እንዲሁም አሁን ምን እያከናወነ እንዳለ ያሳውቁናል። እነዚህ ውድ እውነቶች አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት፣ የምንሞተው ለምን እንደሆነ፣ እንዴት መጸለይ እንዳለብን እንዲሁም እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ገልጠውልናል።
7 ለዘመናት ‘ተዘግተው’ የነበሩ ሆኖም በዚህ የፍጻሜ ዘመን እየተፈጸሙ ያሉ ትንቢቶችን ትርጉም በአሁኑ ጊዜ መረዳት ችለናል። (ዳን. 12:9) እነዚህም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተለይም ደግሞ በወንጌሎችና በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ትንቢቶች ያካትታሉ። ይሖዋ በዓይናችን ልናያቸው የማንችላቸውን ክንውኖች ጭምር እንድናስተውል አስችሎናል፤ ለምሳሌ ኢየሱስ ሥልጣን መያዙን፣ በሰማይ ጦርነት መካሄዱን እንዲሁም ሰይጣን ወደ ምድር መወርወሩን አሳውቆናል። (ራእይ 12:7-12) በተጨማሪም በዓይናችን የምናያቸው ነገሮች ይኸውም ጦርነት፣ የምድር ነውጥ፣ ቸነፈር እና የምግብ እጥረት እየተከሰቱ ያለበትን ምክንያት እንዲሁም ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች የምንኖርበትን ጊዜ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” እንዲሆን ያደረጉት ለምን እንደሆነ እንድናስተውል አስችሎናል።—2 ጢሞ. 3:1-5፤ ሉቃስ 21:10, 11
8. በአሁኑ ጊዜ ያየናቸውንና የሰማናቸውን ነገሮች የገለጠልን ማን ነው?
8 ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ለምን እንደሆነ መገንዘብ አያዳግተንም፦ “እናንተ እያያችሁት ያላችሁትን ነገር የሚያዩ ዓይኖች ደስተኞች ናቸው። እላችኋለሁ፣ ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ እያያችሁት ያለውን ነገር ለማየት ተመኝተው ነበር፤ ግን አላዩም፤ እየሰማችሁት ያለውን ነገርም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሰሙም።” (ሉቃስ 10:23, 24) እነዚህን ነገሮች እንድናይና እንድንሰማ ያደረገን ይሖዋ አምላክ ነው። ‘ረዳት’ የተባለው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የኢየሱስን ተከታዮች “ወደ እውነት ሁሉ” የመራቸው በመሆኑ በጣም አመስጋኞች ነን! (ዮሐንስ 16:7, 13ን አንብብ።) በመሆኑም ምንጊዜም ‘እውነተኛውን እውቀት’ ከፍ አድርገን እንመልከት፤ እንዲሁም ይህን እውነት ለሌሎች ከማካፈል ወደኋላ አንበል!
‘ብዙዎች እውነተኛውን እውቀት’ ይቀበላሉ
9. የሚያዝያ 1881 መጠበቂያ ግንብ እትም ምን ጥሪ አቅርቦ ነበር?
9 የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ከተዘጋጀ ሁለት ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የታተመው የሚያዝያ 1881 መጠበቂያ ግንብ 1,000 ሰባኪዎች እንደሚያስፈልጉ ጥሪ አቅርቦ ነበር። መጽሔቱ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ካላቸው ጊዜ ግማሹን ወይም ከዚያ በላይ የሚሆነውን ሙሉ በሙሉ ለጌታ ሥራ መስጠት ለሚችሉ ሁሉ አንድ ሐሳብ እናቀርብላቸዋለን። . . . ኮልፖርተር * ወይም ወንጌላውያን በመሆን በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙትን ቅን የሆኑ ክርስቲያኖች ለመፈለግ እንደ አቅማችሁ ወደ ትላልቅም ሆነ ትናንሽ ከተሞች ሂዱ፤ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ለአምላክ የሚቀኑ ቢሆኑም እውቀት የላቸውም። ለእነዚህ ሰዎች የአባታችንን የተትረፈረፈ ጸጋና ማራኪ የሆነውን ቃሉን አሳውቋቸው።”
10. የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች እንደሚያስፈልጉ ለቀረበው ጥሪ ሰዎች ምን ምላሽ ሰጡ?
10 ከዚህ ጥሪ መረዳት እንደምንችለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የእውነተኛ ክርስቲያኖች ዋነኛ ተግባር ምሥራቹን መስበክ መሆኑን ተረድተው ነበር። እርግጥ በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚያዘጋጇቸው ስብሰባዎች ላይ የሚገኙት ከጥቂት መቶዎች የማይበልጡ በመሆናቸው ያሰቡትን ያህል ሰዎች ጥሪውን አልተቀበሉም። ይሁንና ብዙ ሰዎች ትራክቶችን ወይም መጽሔቶችን ካነበቡ በኋላ እውነትን መለየትና ለጥሪው ምላሽ መስጠት ችለዋል። ለምሳሌ በለንደን፣ እንግሊዝ የሚኖር አንድ ሰው በ1882 የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት እና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚያዘጋጁትን አንድ ቡክሌት ካነበበ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አምላክ እንዲሠራ የሚፈልገውን ቅዱስ ሥራ ለማከናወን እንድችል እባካችሁ እንዴትና ምን መስበክ እንዳለብኝ አስተምሩኝ።”
11, 12. (ሀ) እኛም ሆንን ኮልፖርተሮች ምን ተመሳሳይ ዓላማ አለን? (ለ) ኮልፖርተሮች “ትምህርት ቤት” ማለትም ጉባኤ የሚያቋቁሙት እንዴት ነበር?
11 በ1885 ወደ 300 የሚጠጉ የመጽሐፍ ቅዱስ
ተማሪዎች በኮልፖርተርነት ያገለግሉ ነበር። የእነዚህ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ዓላማ ከእኛ የተለየ አልነበረም፤ ዓላማቸው ሰዎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ነው። ያም ሆኖ በወቅቱ ይጠቀሙበት የነበረው ዘዴ ከእኛ የተለየ ነው። በዛሬው ጊዜ በአብዛኛው ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናው በግለሰብ ደረጃ ነው። ከዚያም ጥናቶቻችንን ወደ ጉባኤ እንወስዳቸዋለን፤ ጉባኤው ለእነሱ ተብሎ የሚቋቋም ሳይሆን ቀድሞውኑም ቢሆን የነበረ እንደሆነ የታወቀ ነው። ቀደም ሲል ግን ኮልፖርተሮች መጀመሪያ መጻሕፍትን ያበረክታሉ፤ ከዚያም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ሰብስበው በቡድን ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠኗቸዋል። ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ ከማስጠናት ይልቅ ለእነሱ ብለው “ትምህርት ቤት” ማለትም ጉባኤ ያቋቁማሉ።12 ለምሳሌ በ1907፣ አንድ የኮልፖርተሮች ቡድን ቀደም ሲል ሚሌኒያል ዶውን * የተባለው መጽሐፍ ተበርክቶላቸው የነበሩ በአንዲት ከተማ የሚገኙ ሰዎችን መፈለግ ጀመረ። የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ከዚያ በኋላ የሆነውን እንዲህ በማለት ሪፖርት አድርጓል፦ “እነዚህ [ፍላጎት ያሳዩ] ሰዎች በአንዳቸው ቤት ውስጥ ትንሽ ስብሰባ ተዘጋጀላቸው። አንድ ኮልፖርተር መለኮታዊው የዘመናት ዕቅድ በሚል ጭብጥ አንድ እሁድ፣ ቀኑን ሙሉ ከእነሱ ጋር ተወያየ፤ በሚቀጥለው እሁድ ደግሞ ከዚያ በኋላ በቋሚነት ስብሰባ እንደሚኖራቸው ነገራቸው።” በ1911 ወንድሞች ሰዎችን ደቀ መዛሙርት በሚያደርጉበት መንገድ ላይ መጠነኛ ማስተካከያ አደረጉ። ሃምሳ ስምንት የተመረጡ ተጓዥ አገልጋዮች በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ የሕዝብ ንግግሮች እንዲሰጡ ዝግጅት ተደረገ። እነዚህ ወንድሞች በስብሰባው ላይ ከተገኙት መካከል ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ስምና አድራሻ ከተቀበሉ በኋላ ለእነዚህ ሰዎች በግለሰቦች ቤት “ትምህርት ቤት” ያቋቁማሉ። በ1914 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዓለም ዙሪያ 1,200 ጉባኤዎችን አቋቁመው ነበር።
13. ‘እውነተኛው እውቀት’ ከደረሰበት ደረጃ ጋር በተያያዘ አንተን የሚያስገርምህ ምንድን ነው?
13 በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ 109,400 የሚያህሉ ጉባኤዎች ያሉ ሲሆን 895,800 ገደማ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች በአቅኚነት እያገለገሉ ነው። ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ‘እውነተኛውን እውቀት’ ተቀብለው በሕይወታቸው ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። (ኢሳይያስ 60:22ን አንብብ።) * ኢየሱስ “በሰዎች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” በማለት አስቀድሞ ለደቀ መዛሙርቱ ተናግሮ ስለነበር እንዲህ ያለው ውጤት መገኘቱ በእርግጥም አስገራሚ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ ተከታዮቹ እንደሚሰደዱ፣ እንደሚታሰሩ አልፎ ተርፎም እንደሚገደሉ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:12-17) ሰይጣንና አጋንንቱ እንዲሁም ብዙ ሰዎች ተቃውሞ ቢያደርሱም የይሖዋ ሕዝቦች ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ከተሰጣቸው ተልእኮ ጋር በተያያዘ እጅግ በጣም አስደሳች ውጤት አግኝተዋል። በዛሬው ጊዜ “በመላው ምድር” ማለትም ጥቅጥቅ ካሉት ደኖች አንስቶ በበረዶ እስከተሸፈኑ አካባቢዎች ብሎም በተራሮች፣ በበረሃዎች፣ በትላልቅ ከተሞች እንዲሁም ርቀው በሚገኙ ገጠራማ ክልሎች እየሰበኩ ነው። (ማቴ. 24:14) መለኮታዊ ድጋፍ ባይኖር ኖሮ ይህ ሁሉ ሊከናወን አይችልም ነበር።
‘እውነተኛው እውቀት ይበዛል’
14. በታተሙ ጽሑፎች አማካኝነት ‘እውነተኛው እውቀት’ ሊበዛ የቻለው እንዴት ነው?
14 ብዙዎች ምሥራቹን በማወጃቸው ‘እውነተኛው እውቀት’ ሊበዛ ችሏል። ከዚህም ሌላ ይህ እውቀት ሊበዛ የቻለው በታተሙ ጽሑፎች አማካኝነት ነው። ሐምሌ 1879፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የመጀመሪያውን የመጠበቂያ ግንብ እትም ያወጡ ሲሆን በወቅቱ ይህ መጽሔት የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ ተብሎ ይጠራ ነበር። በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀው ይህ መጽሔት የታተመው በአንድ የንግድ ማተሚያ ቤት ሲሆን ብዛቱም 6,000 ነበር። የሃያ ሰባት ዓመቱ ቻርልስ ቴዝ ራስል የመጽሔቱ አዘጋጅ እንዲሆን የተመረጠ ሲሆን አምስት የጎለመሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም በቋሚነት አንዳንድ ርዕሶችን ይጽፉ ነበር። በአሁኑ ጊዜ መጠበቂያ ግንብ በ195 ቋንቋዎች ይዘጋጃል። በዓለም ላይ በብዛት በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው ይህ መጽሔት እያንዳንዱ እትም በ42,182,000 ቅጂዎች ይታተማል። ሁለተኛውን ደረጃ የያዘው የንቁ! መጽሔት ደግሞ በ84 ቋንቋዎች 41,042,000 ቅጂዎች ይታተማል። በተጨማሪም በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን በላይ መጽሐፎችና መጽሐፍ ቅዱሶች ይታተማሉ።
15. የኅትመቱን ሥራ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የምናገኘው እንዴት ነው?
15 ይህን መጠነ ሰፊ ሥራ ለማከናወን የሚያስፈልገው ገንዘብ የሚገኘው በፈቃደኝነት ከሚደረጉ መዋጮዎች ነው። (ማቴዎስ 10:8ን አንብብ።) ከኅትመት ጋር የተያያዙ ሥራዎች ላይ የተሠማሩ ሰዎች የማተሚያ ማሽኖች፣ የወረቀት፣ የቀለም እና የሌሎች መሣሪያዎች ዋጋ ምን ያህል ውድ እንደሆነ ስለሚያውቁ ሥራው በመዋጮ ብቻ መካሄዱ በጣም ያስገርማቸዋል። በቤቴል ውስጥ በዕቃ ግዢ ክፍል የሚሠራ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ማተሚያ ማሽኖቻችንን የሚጎበኙ የንግድ ሰዎች በፈቃደኝነት በሚደረጉ መዋጮዎች ብቻ ተጠቅመን እንዲህ ባለ የተራቀቀ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሰፊ የኅትመት ሥራ ማካሄድ መቻላችን በጣም ያስደንቃቸዋል። በቤቴል የሚያገለግሉት በጣም ወጣቶች መሆናቸውና ሥራቸውን በደስታ ማከናወናቸው ያስገርማቸዋል።”
ምድር አምላክን በማወቅ ትሞላለች
16. ‘እውነተኛው እውቀት’ እንዲበዛ የተደረገበት ዓላማ ምንድን ነው?
16 ‘እውነተኛ እውቀት’ የበዛው በዓላማ ነው። የአምላክ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።” (1 ጢሞ. 2:3, 4) ይሖዋ፣ ሰዎች እውነቱን በማወቅ እሱን በተገቢው መንገድ እንዲያመልኩትና የእሱን በረከት እንዲያጭዱ ይፈልጋል። ‘እውነተኛው እውቀት’ እንዲታወቅ በማድረግ ይሖዋ ታማኝ የሆኑ ቅቡዓን ቀሪዎችን ሰብስቧል። ከዚህም ሌላ “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ” በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” በመሰብሰብ ላይ ናቸው።—ራእይ 7:9
17. እውነተኛው አምልኮ መስፋፋቱ ምን ይጠቁማል?
17 ባለፉት 130 ዓመታት እውነተኛው አምልኮ መስፋፋቱ አምላክና እሱ የሾመው ንጉሥ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ካሉ የይሖዋ አገልጋዮች ጋር አብረው እንደሆኑ ብሎም እየመሯቸው፣ እየጠበቋቸው፣ እያደራጇቸውና እያስተማሯቸው እንዳለ የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም ቁጥራቸው እያደገ መሄዱ ይሖዋ ቃል የገባቸውን ነገሮች እንደሚፈጽም ዋስትና ይሆነናል። “ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳ. 11:9) በዚያን ጊዜ የሰው ልጆች የሚያገኙት በረከት ምንኛ አስደሳች ነው!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.6 የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩት በተግባር የተደገፈ እምነት፣ ክፍል 1፦ ከጨለማ መውጣት እና የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩት በተግባር የተደገፈ እምነት፣ ክፍል 2፦ ብርሃኑ ይብራ የተባሉትን ዲቪዲዎች በመመልከት ተጨማሪ ሐሳብ ማግኘት ትችላለህ።
^ አን.9 በወቅቱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ይጠሩበት የነበረው “ኮልፖርተር” የሚለው ቃል ከ1931 ጀምሮ “አቅኚ” በሚለው ተተክቷል።
^ አን.12 ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ (የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት) ተብሎም ይጠራል።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቀድሞዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ልባዊ ፍላጎት የነበራቸው ትሑት ሰዎች ነበሩ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክን ‘እውነተኛ እውቀት’ ለማሰራጨት የምታደርገውን ጥረት ይሖዋ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል