በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በደንብ አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

ለሳምሶን የጥንካሬ ምንጭ የሆነለት ፀጉሩ ነበር?

ለሳምሶን የጥንካሬ ምንጭ የሆነለት ፀጉሩ በራሱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ፀጉሩ የሚወክለው ነገር ማለትም ናዝራዊ በመሆን ከይሖዋ ጋር የመሠረተው ልዩ ዝምድና ነው። ደሊላ ፀጉሩን ስትቆርጠው ይህ ዝምድና ተቋረጠ።​—4/15 ገጽ 9

እንደ ሥጋዊ ልባችን ሁሉ በምሳሌያዊው ልባችን ላይ ተጽዕኖ የሚያደርጉ ሦስት ነገሮች ምንድን ናቸው?

(1) ምግብ። የልባችን ጤንነት የተጠበቀ እንዲሆን የተመጣጠነ ምግብ መመገብ እንደሚያስፈልገን ሁሉ ጠቃሚ የሆነ መንፈሳዊ ምግብም በበቂ መጠን መመገብ ይኖርብናል። (2) እንቅስቃሴ። በአገልግሎት ላይ በቅንዓት የምንካፈል ከሆነ የምሳሌያዊው ልባችን ጤንነት የተጠበቀ ይሆናል። (3) አካባቢ። ስለ እኛ ከልብ ከሚያስቡ የእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ጊዜ የምናሳልፍ ከሆነ የሚደርስብን ውጥረት ሊቀንስ ይችላል።​—4/15 ገጽ 16

አንደኛው የትዳር ጓደኛ እምነቱን ካጎደለ በኋላ ባለትዳሮች በመካከላቸው የነበረውን የመተማመን ስሜት እንደገና ማጎልበት የሚችሉት እንዴት ነው?

ግንኙነታቸውን እንደገና ለማደስ (1) በሐቀኝነት መነጋገር፣ (2) የጋራ ጥረት ማድረግ፣ (3) መጥፎ ልማዶችን አስወግዶ ጥሩ ልማዶችን ማዳበር እንዲሁም (4) እንደ ቀድሞ ለመሆን ጊዜ እንደሚወስድ ማስታወስ ይኖርባቸዋል።​—5/1 ከገጽ 12-15

የቀብር ንግግር የሚያቀርብ ወንድም መዝሙር 116:15 በሟቹ ላይ እንደሚሠራ መናገር የማይኖርበት ለምንድን ነው?

ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “የቅዱሳኑ ሞት፣ በእግዚአብሔር ፊት የተከበረ ነው።” ይህ ጥቅስ የሚያመለክተው አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ በጅምላ እንዲጠፉ የማይፈቅድ መሆኑን ነው፤ ምክንያቱም እጅግ ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው አድርጎ ይመለከታቸዋል። በመሆኑም ይሖዋ አገልጋዮቹ በቡድን ደረጃ ከምድር ላይ እንዲወገዱ አይፈቅድም።​—5/15 ገጽ 22

ኮልፖርተሮች እነማን ነበሩ?

በአሁኑ ጊዜ አቅኚ በመባል የሚጠሩት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ከ1931 በፊት “ኮልፖርተር” ይባሉ ነበር።​—5/15 ገጽ 31

መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት የተለየ እንደሆነ የሚያሳዩት አንዳንድ ነጥቦች ምንድን ናቸው?

መጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜያቸውን ያገኙ በርካታ ትንቢቶችን ይዟል። በውስጡ ያለው ታሪክ እውነተኛ እንጂ አፈ ታሪክ አይደለም። ትክክለኛ ሳይንሳዊ ሐሳቦች የያዘ ነው። እንዲሁም እርስ በርሱ የሚስማማ ከመሆኑም በላይ በውስጡ ያሉት ምክሮች ለዘመናችን የሚጠቅሙ ናቸው።​—6/1 ከገጽ 4-8

በዳንኤል 2:44 ላይ ‘እነዚያ መንግሥታት ሁሉ’ የተባሉት እነማን ናቸው?

በዚህ ጥቅስ ላይ የተጠቀሱት መንግሥታት የሚያመለክቱት ዳንኤል በጠቀሰው ግዙፉ ምስል የተለያዩ ክፍሎች የተመሰሉትን መንግሥታት ነው።​—6/15 ገጽ 17

የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ የተገለጸው ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት የሆነው መቼ ነው?

ይህ ጥምር መንግሥት ወደ ሕልውና የመጣው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ብሪታንያና አሜሪካ ልዩ የሆነ ጥምረት በፈጠሩበት ጊዜ ነው።​—6/15 ገጽ 19

አምላክ ንስሐ የገቡ ሰዎችን ኃጢአት ይቅር ይላል እንዲሁም አያስታውስም ሲባል ምን ማለት ነው?

ይሖዋ የሚወዳቸውን ሰዎች አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ኀጢአታቸውንም መልሼ አላስብም [“አላስታውስባቸውም፣” የ1980 ትርጉም]።” (ኤርምያስ 31:34) ይሖዋ በቤዛው አማካኝነት የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ይላል። አንዴ ይቅር ካለን በኋላ፣ የሠራነውን በደል ይረሳል፤ በሌላ አባባል የፈጸምናቸውን ኃጢአቶች እንደ አዲስ እያነሳ ዳግመኛ አይቀጣንም።​—7/1 ገጽ 18

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡትን ተአምራት እምነት ልንጥልባቸው የምንችለው ለምንድን ነው?

ብዙዎቹ ተአምራት የተፈጸሙት በድብቅ ሳይሆን በአደባባይ ነው። ተአምራቱ የተፈጸሙት በማያደናግርና ግልጽ በሆነ መንገድ ነበር፤ ተአምራቱን ለመፈጸም ለየት ያሉ ቁሳቁሶችን ወይም ማታለያዎችን መጠቀም አላስፈለገም። ተአምራቱን የፈጸሙት ግለሰቦች፣ ዓላማቸው ለሰዎች ሳይሆን ለአምላክ ክብር ማምጣት ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት ተአምራት ዓይነታቸው ብዙ ከመሆኑም በላይ በወቅቱ የነበሩ ተቃዋሚዎች እንኳ ተአምራቱን አልካዱም። እነዚህ ምክንያቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰፈሩት ስለ ተአምራት የሚገልጹ ዘገባዎች ላይ እምነት እንድንጥል ያደርጉናል።​—8/1 ከገጽ 7-8