በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አኗኗራችሁ የአምላክ መንግሥት ዜጋ መሆናችሁን የሚያሳይ ይሁን!

አኗኗራችሁ የአምላክ መንግሥት ዜጋ መሆናችሁን የሚያሳይ ይሁን!

አኗኗራችሁ የአምላክ መንግሥት ዜጋ መሆናችሁን የሚያሳይ ይሁን!

‘አኗኗራችሁ ከምሥራቹ ጋር የሚስማማ ይሁን።’​—ፊልጵ. 1:27

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

የአምላክ መንግሥት ዜጋ መሆን የሚችሉት እነማን ናቸው?

ከመንግሥቱ ቋንቋ፣ ታሪክ እና ሕግ ጋር በተያያዘ ከእኛ የሚጠበቀው ምንድን ነው?

የመንግሥቱ ዜጎች የአምላክን መሥፈርቶች እንደሚወዱ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

1, 2. ጳውሎስ የሰጠው ምክር ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ልዩ ትርጉም ነበረው የምንለው ለምንድን ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ‘አኗኗራቸው ከምሥራቹ ጋር የሚስማማ እንዲሆን’ አበረታቷቸዋል። (ፊልጵስዩስ 1:27ን አንብብ።) ‘አኗኗር’ ተብሎ የተተረጎመው ጳውሎስ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል “እንደ አንድ ዜጋ መጠን መኖር” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ይህ አገላለጽ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የተለየ ትርጉም ነበረው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ነዋሪዎቻቸው የሮም ዜግነት እንዲያገኙ መብት ከተሰጣቸው የተመረጡ ከተሞች መካከል አንዷ ፊልጵስዩስ ነበረች። በፊልጵስዩስም ሆነ በመላው የሮም ግዛት የሚገኙ የሮም ዜግነት ያላቸው ሰዎች በዜግነታቸው ይኮሩ የነበረ ከመሆኑም በላይ በሮማውያን ሕግ ሥር መሆናቸው ልዩ ጥበቃ አስገኝቶላቸው ነበር።

2 ይሁንና በፊልጵስዩስ ጉባኤ የሚገኙ ክርስቲያኖች ኩራት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ከዚህ የሚበልጥ ምክንያት ነበራቸው። እነዚህ ክርስቲያኖች ቅቡዓን እንደመሆናቸው መጠን “የሰማይ ዜጎች” እንደሆኑ ጳውሎስ አስታውሷቸዋል። (ፊልጵ. 3:20) የፊልጵስዩስ ጉባኤ አባላት የአምላክ መንግሥት ዜጎች እንጂ የአንድ ሰብዓዊ መንግሥት ዜጎች አይደሉም። በመሆኑም ይህ ነው የማይባል ጥበቃና በርካታ ጥቅሞች ማግኘት ይችሉ ነበር።​—ኤፌ. 2:19-22

3. (ሀ) የአምላክ መንግሥት ዜጎች የመሆን አጋጣሚ ያላቸው እነማን ናቸው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ነገሮች እንመረምራለን?

3 ጳውሎስ “እንደ አንድ ዜጋ መጠን” እንዲኖሩ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የሰጠው ማሳሰቢያ በዋነኝነት የሚሠራው ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ለሚገዙት ነው። (ፊልጵ. 3:20) ይሁንና በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ የአምላክ መንግሥት ምድራዊ ተገዥዎች ለሆኑትም ይሠራል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች በሙሉ የሚያገለግሉት ንጉሥ አንድ ሲሆን እሱም ይሖዋ ነው፤ የሚመሩባቸው መሥፈርቶችም አንድ ዓይነት ናቸው። (ኤፌ. 4:4-6) በዛሬው ጊዜ ሰዎች፣ የአንድ የበለጸገ አገር ዜግነት ለማግኘት የማያደርጉት ጥረት የለም ማለት ይቻላል። ታዲያ እኛ የአምላክ መንግሥት ዜጋ የመሆን መብታችንን ከዚህ ይበልጥ ከፍ አድርገን ልንመለከተው አይገባም? ለዚህ መብት ያለንን አድናቆት ከፍ ለማድረግ እንድንችል የአንድ ሰብዓዊ መንግሥት ዜጋ ለመሆን በሚያስፈልጉት ብቃቶችና የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን በሚያስፈልጉት መሥፈርቶች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት እንመልከት። ከዚያም የአምላክ መንግሥት ዜጋ የመሆን መብታችንን ላለማጣት ከፈለግን ልናደርጋቸው የሚገቡ ሦስት ነገሮችን እንመረምራለን።

ዜግነት ለማግኘት የሚያስፈልጉ መሥፈርቶች

4. ንጹሑ ቋንቋ ምንድን ነው? ይህን ቋንቋ “የምንናገረውስ” እንዴት ነው?

4 ቋንቋውን መማር። አንዳንድ ሰብዓዊ መንግሥታት፣ የዜግነት መብት ለማግኘት የሚያመለክቱ ሁሉ በአገሩ ውስጥ በዋነኝነት የሚነገረውን ቋንቋ እንዲማሩ ይጠብቁባቸዋል። አንዳንዶች ዜግነት ካገኙ በኋላም ጭምር ቋንቋውን አቀላጥፈው ለመናገር ጥረት ያደርጋሉ። የቋንቋውን ሰዋስው በቀላሉ ይማሩ ይሆናል፤ ሆኖም የቃላትን ትክክለኛ አጠራር መቻል የተወሰነ ጊዜ ይወስዳል። በተመሳሳይም የአምላክ መንግሥት፣ ዜጎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ንጹሕ ልሳን’ ተብሎ የተጠራውን ቋንቋ እንዲማሩ ይጠብቅባቸዋል። (ሶፎንያስ 3:9ን በ1954 ትርጉም አንብብ።) ለመሆኑ ይህ ቋንቋ ምንድን ነው? ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ የሚገልጸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው እውነት ነው። ከአምላክ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ስንኖር ንጹሑን ቋንቋ “እየተናገርን” እንዳለ ሊቆጠር ይችላል። የአምላክ መንግሥት ዜጎች መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተምረው ሊጠመቁ ይችላሉ። ይሁንና ከተጠመቁ በኋላም ንጹሑን ቋንቋ ይበልጥ አጥርተው ለመናገር ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ አለባቸው። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ሁላችንም ብንሆን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በማወቅና ተግባራዊ በማድረግ መካከል ያለውን ክፍተት ማጥበብ ይኖርብናል።

5. ስለ ይሖዋ ድርጅት ታሪክ ለማወቅ የተቻለንን ሁሉ ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

5 ታሪኩን ማጥናት። የአንድን አገር ዜግነት ለማግኘት የሚፈልግ ሰው ስለ አገሪቱ ታሪክ በተወሰነ መጠን ማወቅ ሊኖርበት ይችላል። በተመሳሳይም የአምላክ መንግሥት ዜጋ መሆን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ስለዚህ መንግሥት የተቻለውን ያህል ለማወቅ ጥረት ማድረግ አለበት። እስቲ በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ያገለግሉ የነበሩት የቆሬ ልጆች የተዉትን ምሳሌ እንመልከት። ለኢየሩሳሌምና ለአምልኮ ስፍራው ልዩ ፍቅር የነበራቸው ከመሆኑም በላይ ስለ ከተማዋ ታሪክ መናገር ያስደስታቸው ነበር። የቆሬን ልጆች የማረካቸው ግንቡና ሕንፃው ሳይሆን ከተማዋና የአምልኮ ቦታው የሚያመለክቱት ነገር ነው። ኢየሩሳሌም የንጹሕ አምልኮ ማዕከል በመሆኗ “የታላቁ ንጉሥ” ማለትም የይሖዋ “ከተማ” ነበረች። ሰዎች የይሖዋን ሕግ የሚማሩት በዚያ ነበር። ይሖዋ ምሕረት የሚያሳየው ኢየሩሳሌም በሚኖረው ንጉሥ አማካኝነት ለሚመራቸው ሕዝቡ ነው። (መዝሙር 48:1, 2, 9, 12, 13ን አንብብ።) አንተስ የይሖዋን ድርጅት ምድራዊ ክፍል ታሪክ የማጥናትና ስለ ድርጅቱ በደስታ የመናገር ፍላጎት አለህ? ስለ አምላክ ድርጅትና ይሖዋ ሕዝቦቹን ስለሚደግፍበት መንገድ ይበልጥ ባወቅህ መጠን የአምላክ መንግሥት የበለጠ እውን ይሆንልሃል። የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ ያለህ ፍላጎትም እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለውም።​—ኤር. 9:24፤ ሉቃስ 4:43

6. ይሖዋ የመንግሥቱን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድንማር ብሎም እንድንታዘዝ መጠበቁ ምክንያታዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

6 ሕጎቹን ማወቅ። ሰብዓዊ መንግሥታት ዜጎቻቸው የአገሪቱን ሕግ እንዲያውቁና እንዲታዘዙ ይጠብቁባቸዋል። ታዲያ ይሖዋ ሁሉም የመንግሥቱ ዜጎች የሚመሩባቸውን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድንማርና እንድንታዘዝ መጠበቁ ምክንያታዊ አይሆንም? (ኢሳ. 2:3፤ ዮሐ. 15:10፤ 1 ዮሐ. 5:3) በአብዛኛው ሰዎች የሚያወጧቸው ሕጎች ጉድለት ያለባቸው ከመሆናቸውም ሌላ ፍትሐዊ አይደሉም። ከዚህ በተቃራኒ ግን የይሖዋ “ሕግ ፍጹም” ነው። (መዝ. 19:7) ታዲያ ለአምላክ ሕግ ፍቅር አለን? ቃሉንስ በየዕለቱ እናነባለን? (መዝ. 1:1, 2) የአምላክን ሕግ መማር የምንችልበት ብቸኛው መንገድ በግለሰብ ደረጃ ሕጉን ማጥናት ነው። ይህን ኃላፊነታችንን ሌላ ሰው ሊወጣልን አይችልም።

የመንግሥቱ ዜጎች ለአምላክ መመሪያዎች ፍቅር አላቸው

7. የመንግሥቱ ዜጎች የአምላክን መመሪያዎች የሚታዘዙት ለምንድን ነው?

7 የመንግሥቱ ዜጎች ሆነን እንድንቀጥል የአምላክን መመሪያዎች ማወቅ ብቻ ሳይሆን መውደድም ይኖርብናል። ብዙ ሰዎች ከአገራቸው ሕግና መመሪያ ጋር ተስማምተው እንደሚኖሩ ይናገራሉ። ሆኖም አንድ ሕግ ካልተስማማቸው ወይም ማንም እንደማይመለከታቸው ሆኖ ከተሰማቸው ሕጉን ይጥሳሉ። ብዙ ጊዜ እነዚህ ሰዎች የሚጥሩት “ሰውን ለማስደሰት” ነው። (ቆላ. 3:22) የመንግሥቱ ዜጎች ግን የአምላክን መመሪያዎች የሚታዘዙት በዚህ መንገድ አይደለም። ሕጉን ለሰጠን አካል ማለትም ለይሖዋ ፍቅር አለን። በመሆኑም ሰው አየን አላየን ሳንል የአምላክን ሕግ በደስታ እንታዘዛለን።​—ኢሳ. 33:22፤ ሉቃስ 10:27ን አንብብ።

8, 9. የአምላክን ሕግ ከልባችን እንወድ እንደሆነና እንዳልሆነ እንዴት ማወቅ እንችላለን?

8 የአምላክን ሕግ ከልብህ ትወደው እንደሆነና እንዳልሆነ እንዴት ማወቅ ትችላለህ? የግል ምርጫ እንደሆኑ በሚሰሙህ ጉዳዮች ረገድ ለምሳሌ በአለባበስና በፀጉር አያያዝ ረገድ ምክር ቢሰጥህ ምን ምላሽ እንደምትሰጥ ራስህን መርምር። የመንግሥቱ ዜጋ ከመሆንህ በፊት የተዝረከረከና የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ አለባበስ ይኖርህ ይሆናል። ለአምላክ ያለህ ፍቅር እያደገ ሲሄድ ግን አለባበስህ ለእሱ ክብር የሚያመጣ መሆን እንዳለበት ተገነዘብክ። (1 ጢሞ. 2:9, 10፤ 1 ጴጥ. 3:3, 4) በመሆኑም አሁን ልከኛ አለባበስ እንዳለህ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም አንድ ሽማግሌ አለባበስህ በጉባኤ ውስጥ ያሉ በርካታ አስፋፊዎችን ቅር እንዳሰኘ ቢነግርህ ምን ታደርጋለህ? ሁኔታውን ለማስተባበል ወይም ለመቆጣት አሊያም በግትርነት ለመቀጠል ይቃጣሃል? ዋነኛ ከሆኑት የአምላክ መንግሥት ሕጎች አንዱ ኢየሱስን መምሰል ነው። (1 ጴጥ. 2:21) ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ ስለተወው ምሳሌ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን የሚጠቅመውን ይኸውም ሊያንጸው የሚችለውን ነገር በማድረግ እናስደስተው። ክርስቶስ እንኳ ራሱን አላስደሰተም።” (ሮም 15:2, 3) አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ለጉባኤው ሰላም ሲል፣ የሌሎችን ሕሊና የሚጎዳ ነገር ላለማድረግ ይጠነቀቃል።​—ሮም 14:19-21

9 ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ ሌሎች ሁለት ጉዳዮችን እንመልከት፤ ይህም ስለ ፆታና ስለ ጋብቻ ያለን አመለካከት ነው። የአምላክ መንግሥት ዜጎች ያልሆኑ ሰዎች ግብረ ሰዶማዊነት፣ የብልግና ምስሎችን መመልከት፣ ምንዝር መፈጸምና መፋታት ምንም ችግር የሌላቸው ነገሮች እንደሆኑ አድርገው ያስቡ ይሆናል። የመንግሥቱ ዜጎች ግን እንዲህ ያለው አመለካከት አርቆ አስተዋይነት የጎደለውና ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ተገንዝበዋል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች ቀደም ሲል ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት ይመሩ ነበር፤ አሁን ግን የፆታ ግንኙነትም ሆነ ትዳር ከአምላክ የተገኙ ስጦታዎች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች የይሖዋን መመሪያዎች ከፍ አድርገው ይመለከታሉ፤ እንዲሁም ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር መከተላቸውን የሚቀጥሉ ሰዎች የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን እንደማይበቁ ሙሉ በሙሉ አምነው ይቀበላሉ። (1 ቆሮ. 6:9-11) ያም ሆኖ ልብ ተንኮለኛ እንደሆነም ይገነዘባሉ። (ኤር. 17:9) በመሆኑም ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ጠብቀው ለመመላለስ የሚረዷቸውን ማስጠንቀቂያዎች በደስታ ይቀበላሉ።

የመንግሥቱ ዜጎች የሚሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ይሰማሉ

10, 11. የአምላክ መንግሥት የትኞቹን ጉዳዮች በተመለከተ ወቅታዊ የሆነ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል? ስለ እነዚህ ማስጠንቀቂያዎችስ ምን ይሰማሃል?

10 ሰብዓዊ መንግሥታት ለጤና አደገኛ ስለሆኑ ምግቦች ወይም መድኃኒቶች ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጡ ይሆናል። ሁሉም ምግቦች ወይም መድኃኒቶች መጥፎ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። ይሁንና አንድ ምርት ለጤና አደገኛ ከሆነ መንግሥት ዜጎቹን ከጉዳት ለመጠበቅ ሲል ሚዛናዊ የሆነ ማስጠንቀቂያ ሊሰጥ ይችላል። አለበለዚያ ቸልተኛ በመሆኑ ተጠያቂ ይሆናል። በተመሳሳይም የአምላክ መንግሥት ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ አደጋዎችን ለይቶ በመጥቀስ ወቅታዊ ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢንተርኔት ለትምህርትና ለመዝናኛ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ለመገናኘት ልንጠቀምበት የምንችል ግሩም መሣሪያ ነው። የአምላክ ድርጅት በኢንተርኔት አማካኝነት ብዙ ጠቃሚ ሥራዎችን ያከናውናል። ይሁን እንጂ በርካታ የኢንተርኔት ድረ ገጾች ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ አደጋዎችን ያስከትላሉ። የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች የሚገኙባቸው ድረ ገጾች የመንግሥቱን ዜጎች መንፈሳዊ ጤንነት አደጋ ላይ ይጥላሉ። ታማኙ ባሪያ ላለፉት አሥርተ ዓመታት እንደነዚህ ስላሉት ድረ ገጾች ማስጠንቀቂያ ሲሰጠን ቆይቷል። መንፈሳዊ ጤንነታችንን ለመጠበቅ ተብለው ለሚሰጡን ለእነዚህ ማስጠንቀቂያዎች በጣም አመስጋኞች ነን!

11 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ማኅበራዊ ድረ ገጾች በጣም ተወዳጅ እየሆኑ መጥተዋል። እነዚህ ድረ ገጾች በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁንና ጥንቃቄ ካልተደረገባቸው ከባድ ጉዳት ያስከትላሉ። ለምሳሌ፣ አንድን ሰው ለመጥፎ ጓደኝነት ሊያጋልጡት ይችላሉ። (1 ቆሮ. 15:33) የአምላክ ድርጅት እንዲህ ያሉ ድረ ገጾችን ከመጠቀም ጋር በተያያዘ ሚዛናዊ የሆነ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ የሚያስገርም አይደለም። በማኅበራዊ ድረ ገጾች አጠቃቀም ረገድ ታማኝና ልባም ባሪያ በቅርቡ ያወጣቸውን ጽሑፎች በሙሉ አንብበሃል? እነዚህን ጽሑፎች ሳያነቡ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን መጠቀም ምንኛ ሞኝነት ነው! * እንዲህ ማድረግ የሕክምና ባለሙያ ሳያማክሩ አንድን ኃይለኛ መድኃኒት እንደመውሰድ ይቆጠራል።

12. ማስጠንቀቂያዎችን ችላ ማለት ምን ጉዳት አለው?

12 በታማኙ ባሪያ በኩል የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ የሚሉ ሰዎች ራሳቸውንም ሆነ የሚወዷቸውን ሰዎች ለጉዳት መዳረጋቸው አይቀርም። አንዳንዶች የብልግና ምስሎችን የመመልከት ሱስ ተጠናውቷቸዋል፤ ወይም የብልግና ድርጊቶችን ይፈጽማሉ፤ እንዲሁም ይሖዋ የሚያደርጉትን ነገር እንደማያይ በማሰብ ራሳቸውን ያሞኛሉ። የምንፈጽመውን ድርጊት ከይሖዋ መደበቅ እንደምንችል ማሰብ ምንኛ ሞኝነት ነው! (ምሳሌ 15:3፤ ዕብራውያን 4:13ን አንብብ።) አምላክ እንዲህ ያሉ ሰዎችን መርዳት ይፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ ምድር ላይ ያሉ ወኪሎቹን ይጠቀማል። (ገላ. 6:1) በብዙ አገሮች ውስጥ፣ አንዳንድ ወንጀሎች የዜግነት መብት እንደሚያስነጥቁ ሁሉ ይሖዋም የእሱን መመሪያዎች የሚጥሱትንና ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ያልሆኑትን ሰዎች የዜግነት መብት ይነጥቃል። * (1 ቆሮ. 5:11-13) ያም ሆኖ ይሖዋ መሐሪ ነው። ንስሐ የሚገቡና መጥፎ ድርጊታቸውን እርግፍ አድርገው የሚተዉ ሰዎች በይሖዋ ፊት የነበራቸውን ጥሩ አቋም መልሰው ማግኘት የሚችሉ ከመሆኑም በላይ የመንግሥቱ ዜጎች ሆነው መቀጠል ይችላሉ። (2 ቆሮ. 2:5-8) እንዲህ ያለውን አፍቃሪ ንጉሥ ማገልገል እንዴት ያለ ትልቅ መብት ነው!

የመንግሥቱ ዜጎች ለትምህርት ቦታ ይሰጣሉ

13. የመንግሥቱ ዜጎች ለትምህርት ቦታ እንደሚሰጡ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

13 በርካታ ሰብዓዊ መንግሥታት ዜጎቻቸውን ለማስተማር ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። መሠረተ ትምህርት የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶችን ይከፍታሉ፤ እንዲሁም የሥራ ዕድል የሚያስገኙ ክህሎቶችን ያስተምራሉ። የአምላክ መንግሥት ዜጎች እንዲህ ያሉ ትምህርት ቤቶች በመኖራቸው ደስተኞች ከመሆናቸውም በላይ ማንበብና መጻፍ ለመማር ብሎም ራሳቸውን ለማስተዳደር የሚያስችላቸው እውቀት ለመቅሰም ጥረት ያደርጋሉ። ይበልጥ ቦታ የሚሰጡት ግን የአምላክ መንግሥት ዜጋ በመሆናቸው ለሚያገኙት ትምህርት ነው። ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት መሠረተ ትምህርት እንድንማር ያበረታታናል። እንዲሁም ወላጆች ለልጆቻቸው እንዲያነቡላቸው ይበረታታሉ። ታማኙ ባሪያ በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች አማካኝነት በርካታ ገጾችን የሚሸፍኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ትምህርቶችን በየወሩ ያዘጋጃል። በየቀኑ የተወሰኑ ገጾችን ብታነብ በአንድ ወር ውስጥ የሚወጡትን ሁሉንም መጽሔቶች በዚያው ወር አንብበህ መጨረስ ትችላለህ፤ በዚህ መንገድ ከመንግሥቱ የትምህርት መርሃ ግብር መጠቀም ትችላለህ።

14. (ሀ) ምን ዓይነት ሥልጠና እያገኘን ነው? (ለ) የቤተሰብ አምልኮን በተመለከተ ከተሰጡት ሐሳቦች መካከል እናንተ የትኛውን ሐሳብ ተግባራዊ እያደረጋችሁ ነው?

14 የመንግሥቱ ዜጎች በየሳምንቱ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለስድስት አሥርተ ዓመታት በርካታ ተማሪዎችን የተዋጣላቸው የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንዲሆኑ አሠልጥኗል። አንተስ በዚህ ትምህርት ቤት ክፍል ለማቅረብ ተመዝግበሃል? ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ታማኝና ልባም ባሪያ በየሳምንቱ የቤተሰብ አምልኮ እንድናደርግ ሲያበረታታን ቆይቷል። ይህ ዝግጅት የቤተሰብ አንድነትን ያጠናክራል። ታዲያ የቤተሰብ አምልኮን አስመልክቶ በጽሑፎቻችን ላይ የሚወጡትን ሐሳቦች ተግባራዊ እያደረጋችሁ ነው? *

15. ካገኘናቸው እጅግ ውድ የሆኑ መብቶች መካከል አንዱ ምንድን ነው?

15 በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ዜጎች፣ ለመረጡት የፖለቲካ ፓርቲ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ አደባባይ ይወጣሉ፤ እንዲያውም የሕዝቡን ድጋፍ ለማሰባሰብ ከቤት ወደ ቤት ጭምር ይሄዳሉ። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የመንግሥቱ ዜጎች መንገድ ላይም ሆነ ከቤት ወደ ቤት በመስበክ የአምላክን መንግሥት እንደሚደግፉ እያሳዩ ነው። እንዲያውም ቀደም ሲል በነበረው የጥናት ርዕስ ላይ እንደተገለጸው የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቀው መጠበቂያ ግንብ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ በብዛት በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው መጽሔት ሆኗል። ስለ መንግሥቱ ለሌሎች መናገር፣ ካገኘናቸው እጅግ ውድ የሆኑ መብቶች መካከል አንዱ ነው። አንተስ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት እየተካፈልክ ነው?​—ማቴ. 28:19, 20

16. ጥሩ የአምላክ መንግሥት ዜጋ መሆንህን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

16 በቅርቡ በምድር ላይ የሚገዛው የአምላክ መንግሥት ብቻ ይሆናል። መንፈሳዊ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚመለከቱ ነገሮችንም ይቆጣጠራል። ታዲያ በዚያን ጊዜ ጥሩ የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን ተዘጋጅተሃል? ይህን ለማሳየት ጊዜው አሁን ነው። በየዕለቱ የምታደርጋቸው ውሳኔዎች በሙሉ ለይሖዋ ክብር የሚያመጡ ሊሆኑ ይገባል፤ እንዲህ የምታደርግ ከሆነ እንደ አንድ የአምላክ መንግሥት ዜጋ መጠን እየኖርክ መሆንህን ታሳያለህ።​—1 ቆሮ. 10:31

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.14 በነሐሴ 15, 2011 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 6-7 እንዲሁም በጥር 2011 የመንግሥት አገልግሎታችን ከገጽ 3-6 ላይ የወጡትን ሐሳቦች ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ስለ ኢንተርኔት አጠቃቀም የተሰጡትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስጠንቀቂያዎች ተግባራዊ ታደርጋለህ?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ቆሬ ልጆች በንጹሑ አምልኮና ከዚያ ጋር ተያይዞ ባለው ታሪክ ትደሰታለህ?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቤተሰብ አምልኮ አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ጥሩ የመንግሥቱ ዜጎች እንድትሆኑ ሊረዳችሁ ይችላል