በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዲያብሎስ ወጥመዶች ተጠንቀቁ!

ከዲያብሎስ ወጥመዶች ተጠንቀቁ!

ከዲያብሎስ ወጥመዶች ተጠንቀቁ!

‘ከዲያብሎስ ወጥመድ ውጡ።’​—2 ጢሞ. 2:26

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

ሌሎችን መተቸት የሚቀናን ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

በሰው ፍርሃትና ተጽዕኖ ላለመሸነፍ የጲላጦስና የጴጥሮስ ታሪክ ትምህርት የሚሆነን እንዴት ነው?

ከመጠን ባለፈ የጥፋተኝነት ስሜት እንዳንደቆስ ምን ሊረዳን ይችላል?

1, 2. በዚህ ርዕስ ውስጥ የምንመረምረው የትኞቹን የዲያብሎስ ወጥመዶች ነው?

ዲያብሎስ የይሖዋ አገልጋዮችን ለመያዝ አድፍጦ ይጠብቃል። የእሱ ዋነኛ ዓላማ አዳኞች እንደሚያደርጉት ሰለባዎቹን መግደል አይደለም። ከዚህ ይልቅ የዲያብሎስ ፍላጎት የአምላክ አገልጋዮችን ከነሕይወታቸው ከያዘ በኋላ የእሱን ጥቅም እንዲያራምዱ ማድረግ ነው።​—2 ጢሞቴዎስ 2:24-26ን አንብብ።

2 አዳኞች አንድን እንስሳ ለመያዝ የተለያዩ ወጥመዶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ለምሳሌ እንስሳው ከተደበቀበት እንዲወጣና እነሱ ወደፈለጉት አቅጣጫ እንዲያመራ በማድረግ ሸምቀቆ ውስጥ ያስገቡታል። አሊያም ስውር የሆኑና ሲነኩ እንስሳውን በቁጥጥር ሥር የሚያደርጉ የወጥመድ ዓይነቶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ዲያብሎስም የአምላክን አገልጋዮች ከነሕይወታቸው ለመያዝ ተመሳሳይ ዘዴዎችን ይጠቀማል። በሰይጣን ወጥመዶች ላለመያዝ የእሱ ወጥመዶች በአቅራቢያችን እንዳሉ የሚጠቁሙ የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ማስተዋልና ከዚያ መራቅ ይኖርብናል። ይህ ርዕስ ዲያብሎስ በተወሰነ መጠን ውጤታማ ሆኖ ካገኛቸው ሦስት ወጥመዶች ራሳችንን እንዴት መጠበቅ እንደምንችል ያብራራል። እነዚህም (1) ያልተገራ አንደበት፣ (2) የሰው ፍርሃትና የእኩዮች ተጽዕኖ እንዲሁም (3) ከመጠን ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ናቸው። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ደግሞ ሌሎች ሁለት የሰይጣን ወጥመዶችን እንመለከታለን።

ያልተገራ አንደበት የሚያስነሳውን እሳት ማጥፋት

3, 4. አንደበትን አለመቆጣጠር ምን ሊያስከትል ይችላል? ምሳሌ ስጥ።

3 አንዳንድ አዳኞች አንድን እንስሳ ከተደበቀበት እንዲወጣ ለማድረግ የአካባቢውን የተወሰነ ክፍል እሳት ይለቁበታል፤ ከዚያም እንስሳው ለማምለጥ ሲሞክር ይይዙታል። ዲያብሎስ በምሳሌያዊ ሁኔታ በጉባኤው ውስጥ እሳት ማስነሳት ይፈልጋል። ከተሳካለት ደግሞ የጉባኤውን አባላት ካሉበት ሰላማዊ ስፍራ እንዲወጡ በማድረግ እጁ ውስጥ ያስገባቸዋል። ታዲያ ሳይታወቀን የሰይጣን ተባባሪዎች ልንሆን ወይም በእሱ መዳፍ ውስጥ ልንገባ የምንችለው እንዴት ነው?

4 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ምላስን ከእሳት ጋር አመሳስሎታል። (ያዕቆብ 3:6-8ን አንብብ።) አንደበታችንን መቆጣጠር ካልቻልን በጉባኤ ውስጥ እሳት ልንለኩስ እንችላለን። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ እንመልከት፦ በጉባኤ ስብሰባ ላይ አንዲት እህት የዘወትር አቅኚ እንደሆነች ማስታወቂያ ተነግሯል። ከስብሰባው በኋላ ሁለት እህቶች ስለዚህ ማስታወቂያ እያወሩ ነው። አንደኛዋ እህት በሰማችው ማስታወቂያ እንደተደሰተችና አቅኚ ለሆነችው እህት ያላትን መልካም ምኞት ትገልጻለች። ሌላኛዋ ግን ይህች እህት አቅኚ ለመሆን የተነሳሳችበት ምክንያት ጥሩ እንዳልሆነና የሰዎችን ትኩረት መሳብ እንደምትፈልግ ትናገራለች። ከሁለቱ እህቶች ለጓደኝነት የምትመርጡት የትኛዋን ነው? ከእነዚህ ሁለት እህቶች በንግግሯ በጉባኤ ውስጥ እሳት የምትጭረው የትኛዋ እንደሆነች መለየት አዳጋች አይደለም።

5. ያልተገራ አንደበት የሚያስነሳውን እሳት ለማጥፋት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

5 ያልተገራ አንደበት የሚያስነሳውን እሳት ማጥፋት የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው” ብሏል። (ማቴ 12:34) በመሆኑም አንደበታችንን ለመግራት የመጀመሪያው እርምጃ ልባችንን መመርመር ነው። የማያንጽ ንግግር እንድንናገር የሚገፋፋንን መጥፎ ስሜት ለማስወገድ ጥረት እናደርጋለን? ለምሳሌ አንድ ወንድም አንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት ላይ ለመድረስ እየተጣጣረ እንደሆነ ስንሰማ ቶሎ የምናስበው ይህ ወንድም እንዲህ ለማድረግ የተነሳሳው በቅን ልቦና እንደሆነ ነው? ወይስ የራሱን ጥቅም ፍለጋ እንደሆነ ይሰማናል? ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር የመጠራጠር ዝንባሌ ካለን ዲያብሎስም ቢሆን ታማኝ የአምላክ አገልጋይ በሆነው በኢዮብ ውስጣዊ ግፊት ላይ ጥያቄ እንዳስነሳ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። (ኢዮብ 1:9-11) ወንድማችንን ከመጠራጠር ይልቅ እሱን ለመንቀፍ ያነሳሳንን ምክንያት መመርመራችን ተገቢ ነው። ስለ ወንድማችን እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲኖረን ያደረገን በእርግጥ በቂ ምክንያት አለን? ወይስ ልባችን በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ተስፋፍተው በሚገኙት ፍቅር የጎደላቸው ባሕርያት ተመርዟል?​—2 ጢሞ. 3:1-4

6, 7. (ሀ) ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር በመጥፎ እንድንተረጉም የሚገፋፉን አንዳንድ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ሌሎች ሲሰድቡን ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?

6 ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር በመጥፎ እንድንተረጉም ሊያነሳሱን የሚችሉ ተጨማሪ ምክንያቶችን እስቲ እንመልከት። አንዱ ምክንያት እኛ የምናከናውነው ነገር ከሌሎች ጎልቶ እንዲታይ ስለምንፈልግ ሊሆን ይችላል። በሌላ አባባል ሌሎችን ወደታች በመጫን ራሳችንን ከፍ ለማድረግ እየሞከርን ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ማድረግ የሚገባንን ነገር ሳናከናውን በመቅረታችን ከተጠያቂነት ለማምለጥ መንገድ እየፈለግን ይሆናል። ሌሎችን የሚያጥላላ ነገር እንድንናገር የሚያነሳሳን ኩራትም ይሁን ቅናት አሊያም በራስ የመተማመን መንፈስ ማጣት ውጤቱ አስከፊ ነው።

7 አንድን ሰው ለመንቀፍ በቂ ምክንያት እንዳለን ሆኖ ሊሰማን ይችላል። ምናልባትም ያ ሰው አንደበቱን ባለመቆጣጠሩ የተነሳ ተጎድተን ይሆናል። ሁኔታው እንደዚህ ከሆነ አጸፋውን መመለስ መፍትሔ አይሆንም። እንዲህ ማድረግ በእሳቱ ላይ ጭድ እንደመጨመር ነው፤ አልፎ ተርፎም የአምላክን ሳይሆን የዲያብሎስን ዓላማ ማራመድ ነው። (2 ጢሞ. 2:26) በዚህ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን ተገቢ ነው። ኢየሱስ “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። . . . ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።” (1 ጴጥ. 2:21-23) ኢየሱስ ይሖዋ ነገሮችን በራሱ መንገድ እንደሚይዝና ጊዜውን ጠብቆ መፍትሔ እንደሚሰጥ እርግጠኛ ነበር። እኛም ብንሆን በአምላክ ላይ ተመሳሳይ እምነት ሊኖረን ይገባል። አንደበታችንን ፈዋሽ በሆነ መንገድ የምንጠቀምበት ከሆነ በጉባኤ ውስጥ “የመንፈስን አንድነት” መጠበቅ እንችላለን።​—ኤፌሶን 4:1-3ን አንብብ።

እንደ ሸምቀቆ ከሆኑት የሰው ፍርሃትና የእኩዮች ተጽዕኖ ተጠንቀቁ

8, 9. ጲላጦስ በኢየሱስ ላይ የፈረደው ለምንድን ነው?

8 በሸምቀቆ የተያዘ እንስሳ እንደፈለገ መሆን አይችልም። በተመሳሳይም በሰው ፍርሃትና በእኩዮች ተጽዕኖ የተሸነፈ ሰው በተወሰነ መጠን ሕይወቱን የሚቆጣጠሩት ሌሎች ናቸው። (ምሳሌ 29:25ን አንብብ።) ከዚህ በመቀጠል በሰው ፍርሃትና በሌሎች ተጽዕኖ የተሸነፉ የሁለት ሰዎችን ምሳሌ እንመለከታለን፤ እንዲሁም ከእነሱ ተሞክሮ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመረምራለን።

9 የሮማ ገዥ የሆነው ጳንጥዮስ ጲላጦስ፣ ኢየሱስ ንጹሕ ሰው መሆኑን ስለሚያውቅ ሊጎዳው አልፈለገም ነበር። እንዲያውም “ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር” እንዳልፈጸመ ተናግሯል። ያም ሆኖ ኢየሱስ እንዲገደል ፈረደበት። ለምን? ይህን ያደረገው ሕዝቡ ባሳደረበት ተጽዕኖ ስለተሸነፈ ነው። (ሉቃስ 23:15, 21-25) ሕዝቡ “ይህን ሰው ከፈታኸው አንተ የቄሳር ወዳጅ አይደለህም” በማለት ሲጮኽ የእነሱን ፍላጎት ለማርካት ተገደደ። (ዮሐ. 19:12) ጲላጦስ ለክርስቶስ ቢፈርድ ሥልጣኑን ምናልባትም ሕይወቱን ሊያሳጣው እንደሚችል በማሰብ ፈርቶ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም የዲያብሎስን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን አሳልፎ ሰጠ።

10. ጴጥሮስ ክርስቶስን እንዲክድ ያደረገው ምንድን ነው?

10 ሐዋርያው ጴጥሮስ ከኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች አንዱ ነበር። ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ በሕዝብ ፊት መሥክሯል። (ማቴ. 16:16) ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በአንድ ወቅት ኢየሱስ የተናገረው ነገር ስላልገባቸው ትተውት ቢሄዱም ጴጥሮስ ግን ለኢየሱስ ታማኝ ሆኗል። (ዮሐ. 6:66-69) ጠላቶች ኢየሱስን ለማሰር በመጡ ጊዜም ጴጥሮስ ሰይፉን በመምዘዝ ጌታውን ተከላክሏል። (ዮሐ. 18:10, 11) ብዙም ሳይቆይ ግን ጴጥሮስ በሰው ፍርሃት ስለተሸነፈ ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጽሞ እንደማያውቀው በመናገር ካደው። ይህ ሐዋርያ ለአጭር ጊዜም ቢሆን በሰው ፍርሃት ወጥመድ በመያዙ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ እንዳይወስድ ተሽመድምዷል።​—ማቴ. 26:74, 75

11. የትኞቹን መጥፎ ተጽዕኖዎች መቋቋም ይኖርብናል?

11 ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን አምላክን የሚያሳዝኑ ነገሮች እንድናደርግ የሚደርስብንን ጫና መቋቋም ይኖርብናል። አሠሪዎቻችን ወይም ሌሎች ሰዎች ሐቀኝነት የጎደለው ነገር እንድናደርግ አሊያም የሥነ ምግባር ብልግና እንድንፈጽም ጫና ሊያሳድሩብን ይችላሉ። ተማሪዎች ደግሞ እኩዮቻቸው ፈተና ላይ እንዲያጭበረብሩ፣ የብልግና ምስሎችን እንዲመለከቱ፣ እንዲያጨሱ፣ ዕፅ እንዲወስዱ፣ ከልክ በላይ እንዲጠጡ ወይም የሥነ ምግባር ብልግና እንዲፈጽሙ የሚያደርሱባቸውን ጫና መቋቋም ሊኖርባቸው ይችላል። ታዲያ በሰው ፍርሃትና ተጽዕኖ ተሸንፈን ይሖዋን የሚያሳዝኑ ነገሮች ከማድረግ እንድንቆጠብ ምን ሊረዳን ይችላል?

12. ከጲላጦስና ከጴጥሮስ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

12 ከጲላጦስና ከጴጥሮስ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እስቲ እንመልከት። ጲላጦስ ስለ ክርስቶስ የነበረው እውቀት ውስን ነበር። ያም ሆኖ ኢየሱስ ንጹሕ እንደነበረና ተራ ሰው እንዳልነበረ ያውቃል። ይሁንና ጲላጦስ ትሕትና ይጎድለው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ለእውነተኛው አምላክ ፍቅር አልነበረውም። በመሆኑም ዲያብሎስ ከነሕይወቱ በቀላሉ መዳፉ ውስጥ አስገባው። ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ጴጥሮስ ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት የነበረው ከመሆኑም በላይ ይወደው ነበር። ይሁን እንጂ ልኩን ማወቅ የተሳነው ብሎም በፍርሃት የተሸነፈበትና ለተጽዕኖ እጁን የሰጠበት ጊዜ ነበር። ኢየሱስ ከመያዙ ቀደም ብሎ ጴጥሮስ “ሌሎቹ ሁሉ ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ግን አልሰናከልም” በማለት በጉራ ተናግሮ ነበር። (ማር. 14:29) ይህ ሐዋርያ “እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” በማለት እንደተናገረው መዝሙራዊ ዓይነት አቋም ቢኖረው ኖሮ ፈተናውን ለመቋቋም የተሻለ ብቃት ይኖረው ነበር። (መዝ. 118:6) ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን ከማጠናቀቁ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት ላይ ጴጥሮስንና ሌሎች ሁለት ሐዋርያቱን ወደ ውስጠኛው የጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ ይዟቸው ገብቶ ነበር። ይሁንና ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ነቅተው ከመጠበቅ ይልቅ እንቅልፍ ወሰዳቸው። ኢየሱስ ከቀሰቀሳቸው በኋላ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ፣ ጸልዩም” አላቸው። (ማር. 14:38) ጴጥሮስ ግን ተመልሶ ተኛ፤ በመሆኑም በኋላ ላይ በሰው ፍርሃትና ተጽዕኖ ተሸነፈ።

13. መጥፎ ነገር እንድንፈጽም የሚደረግብንን ጫና መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

13 ከጲላጦስና ከጴጥሮስ፣ ሌላም ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን፦ ተጽዕኖን በመቋቋም ረገድ ስኬታማ መሆን ከፈለግን ትክክለኛ እውቀት፣ ትሕትና፣ ልክን ማወቅ፣ ለአምላክ ፍቅር ማዳበር እንዲሁም ሰውን ሳይሆን ይሖዋን መፍራት ያስፈልገናል። እምነታችን የተመሠረተው በትክክለኛ እውቀት ላይ ከሆነ ስለምናምንበት ነገር በድፍረትና በቆራጥነት መናገር እንችላለን። ይህ ደግሞ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋምና የሰውን ፍርሃት ለማሸነፍ ይረዳናል። እርግጥ ነው፣ ከልክ በላይ በራሳችን መመካት የለብንም። ከዚህ ይልቅ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገን በትሕትና አምነን መቀበል ይኖርብናል። መንፈሱን እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ መጸለይ ይኖርብናል፤ እንዲሁም ለስሙ ጥብቅና ለመቆምና መመሪያዎቹን ከፍ አድርገን ለመመልከት እንድንችል ለእሱ ፍቅር ማዳበር ያስፈልገናል። በተጨማሪም ፈተና ከመድረሱ በፊት ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም ራሳችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ ልጆቻችንን በጸሎት ታግዘን የምናዘጋጃቸው ከሆነ እኩዮቻቸው መጥፎ ነገር እንዲፈጽሙ ጫና በሚያሳድሩባቸው ጊዜ ጥሩ ምላሽ መስጠት ይችላሉ።​—2 ቆሮ. 13:7 *

ከሚያደቅቀው ወጥመድ ተጠንቀቁ ​ከመጠን ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት

14. ከዚህ በፊት ከሠራነው ስህተት ጋር በተያያዘ ዲያብሎስ ምን ብለን እንድንደመድም ይፈልጋል?

14 ሌላኛው የወጥመድ ዓይነት እንስሳው አዘውትሮ በሚያልፍበት መንገድ ላይ ትልቅ ግንድ ወይም ድንጋይ ከፍ አድርጎ ማንጠልጠል ነው። ከዚያም ምንም ያልጠረጠረው እንስሳ የወጥመዱን ገመድ ሲነካው ድንጋዩ ወይም ግንዱ እንስሳው ላይ በመውደቅ ያደቅቀዋል። ከመጠን ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ከሚያደቅቅ ወጥመድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ከዚህ በፊት ስለሠራነው ስህተት ስናስብ ‘ፈጽሞ እንደደቀቅን’ ሊሰማን ይችላል። (መዝሙር 38:3-5, 8ን አንብብ።) ሰይጣን፣ የይሖዋ ምሕረት የማይገባን ሰዎች እንደሆንን ወይም አምላክ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር እንደማንችል አድርገን እንድንደመድም ይፈልጋል።

15, 16. ከመጠን ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ወጥመድ እንዳይሆንብህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

15 የሚያደቅቀው ወጥመድ ሰለባ እንዳትሆን ምን ማድረግ ትችላለህ? ከባድ ኃጢአት ፈጽመህ ከሆነ ጊዜ ሳታጠፋ ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ለማደስ የሚያስችልህን እርምጃ ውሰድ። ወደ ሽማግሌዎች በመሄድ የእነሱን እርዳታ ጠይቅ። (ያዕ. 5:14-16) ስህተትህን ለማስተካከል የተቻለህን ሁሉ አድርግ። (2 ቆሮ. 7:11) ተግሣጽ በሚሰጥህ ጊዜ ከልክ በላይ አትዘን። ምክንያቱም ተግሣጽ ይሖዋ እንደሚወድህ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ዕብ. 12:6) ወደ ኃጢአት የመራህን ድርጊት ላለመድገም ቁርጥ ውሳኔ አድርግ፤ እንዲሁም ይህን ውሳኔህን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት አድርግ። ንስሐ ከገባህና መጥፎ ድርጊት መፈጸምህን እርግፍ አድርገህ ከተውክ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሠራኸውን ኃጢአት ሊሸፍን እንደሚችል እምነት ይኑርህ።​—1 ዮሐ. 4:9, 14

16 አንዳንዶች ይቅር የተባለላቸውን ኃጢአት እያሰቡ በጥፋተኝነት ስሜት ይዋጣሉ። እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ፣ የሚወደው ልጁ ኢየሱስ በጣም ተጨንቆ በነበረበት ሰዓት ላይ ጥለውት ቢሄዱም ጴጥሮስንና ሌሎቹን ሐዋርያት ይቅር እንዳላቸው አስታውስ። በተጨማሪም አስጸያፊ የሆነ የሥነ ምግባር ብልግና በመፈጸሙ ምክንያት ከቆሮንቶስ ጉባኤ ተወግዶ የነበረ አንድ ሰው ንስሐ በመግባቱ ይሖዋ ይቅር ብሎታል። (1 ቆሮ. 5:1-5፤ 2 ቆሮ. 2:6-8) መጽሐፍ ቅዱስ ከባድ ኃጢአት ይፈጽሙ የነበሩ ሆኖም ንስሐ በመግባታቸው አምላክ ይቅር ስላላቸው ሌሎች ሰዎችም ይናገራል።​—2 ዜና 33:2, 10-13፤ 1 ቆሮ. 6:9-11

17. ቤዛው ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

17 እውነተኛ ንስሐ ከገባህና ይሖዋ ምሕረት እንደሚያደርግልህ አምነህ የምትቀበል ከሆነ የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ቀደም ሲል የሠራሃቸውን ኃጢአቶች ሊሸፍን እንደማይችል ሆኖ ፈጽሞ ሊሰማህ አይገባም። አለበለዚያ በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ ትገባለህ። ዲያብሎስ፣ ቤዛው የሁሉንም ሰዎች ኃጢአት ሊሸፍን አይችልም ብለህ እንድታምን ይፈልጋል። ይሁንና ሰዎች ንስሐ እስከገቡ ድረስ ኃጢአታቸው ሙሉ በሙሉ ይቅር ይባልላቸዋል። (ምሳሌ 24:16) በቤዛው ላይ ያለህ እምነት ሸክም የሆነብህ ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ከላይህ ላይ እንዲወርድ ብሎም አምላክን በሙሉ ልብህ፣ ነፍስህና አእምሮህ እንድታገለግለው ያስችልሃል።​—ማቴ. 22:37

የሰይጣንን ዕቅዶች እናውቃቸዋለን

18. ከዲያብሎስ ወጥመዶች መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

18 ሰይጣን በእጁ እንግባለት እንጂ እኛን ለማጥመድ የሚጠቀምበት የወጥመድ ዓይነት አያሳስበውም። የሰይጣንን ዕቅዶች ስለምናውቃቸው ዲያብሎስ መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ ማድረግ እንችላለን። (2 ቆሮ. 2:10, 11) የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጠን ወደ አምላክ የምንጸልይ ከሆነ በዲያብሎስ ወጥመድ አንያዝም። ያዕቆብ “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ ምክንያቱም አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣል፤ ለእሱም ይሰጠዋል” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 1:5) አዘውትረን የግል ጥናት በማድረግ እንዲሁም ከአምላክ ቃል ያገኘነውን ትምህርት በሥራ ላይ በማዋል ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት የሚዘጋጁት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎች፣ የዲያብሎስ ወጥመዶች ፍንትው ብለው እንዲታዩን በማድረግ ከእነሱ መራቅ እንድንችል ይረዱናል።

19, 20. ክፉ የሆኑ ነገሮችን መጥላት ያለብን ለምንድን ነው?

19 ጸሎትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመልካም ነገሮች ፍቅር እንድናዳብር ይረዱናል። ያም ሆኖ ክፉ የሆኑ ነገሮችን መጥላታችን የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነው። (መዝ. 97:10) የራስ ወዳድነት ምኞቶች በሚያስከትሏቸው ጎጂ ውጤቶች ላይ ማሰላሰላችን ከእነሱ ለመራቅ ያስችለናል። (ያዕ. 1:14, 15) ለመጥፎ ነገሮች ጥላቻ እንዲሁም ለመልካም ነገሮች እውነተኛ ፍቅር ስናዳብር ሰይጣን በወጥመዶቹ ላይ የሚያስቀምጣቸው ማባበያዎች አያጓጉንም፤ ከዚህ ይልቅ እንሸሻቸዋለን።

20 ሰይጣን እኛን ለማጥቃት መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ አምላክ ስለሚረዳን በጣም አመስጋኞች ነን! ይሖዋ በመንፈሱ፣ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት “ከክፉው” ያድነናል። (ማቴ. 6:13) በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ዲያብሎስ የአምላክን አገልጋዮች ከነሕይወታቸው ለመያዝ ውጤታማ ሆኖ ያገኛቸውን ሁለት ተጨማሪ ወጥመዶች እንመረምራለን፤ እንዲሁም ከእነዚህ ወጥመዶች እንዴት መራቅ እንደምንችል እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 ወላጆች ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 132-133 ላይ የሚገኘውን “የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም” የሚለውን ሣጥን ተጠቅመው ከልጆቻቸው ጋር መወያየት ይኖርባቸዋል። ይህን ክፍል በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ላይ ማካተት ይቻላል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ያልተገራ አንደበት በጉባኤ ውስጥ እንደ እሳት ያሉ ችግሮች ሊያስነሳ ይችላል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተጫነህን ከመጠን ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ከላይህ ላይ ማውረድ ትችላለህ