በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከታሪክ ማኅደራችን

ከፒልግሪሞች ጋር እንጓዝ

ከፒልግሪሞች ጋር እንጓዝ

“ከቤት ወደ ቤት እንኳ ፈጽሞ ልሄድ አልችልም!” አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ለማያውቀው ሰው ስለ መስበክ ሲያስብ እንዲህ ቢናገር የሚያስገርም አይደለም! ይሁንና ይህን የተናገረው ፒልግሪም ተብለው ከሚጠሩት አንዱ የነበረውና ንግግር በማቅረብም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ረገድ ልምድ ያካበተ አንድ ወንድም ነበር።

ቤተ ክርስቲያናቸውን ትተው የወጡ በርካታ የጽዮን መጠበቂያ ግንብ አንባቢያን፣ እንደ እነሱ የእውነት ጥማት ካላቸው ሰዎች ጋር የመሰብሰብ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው። ይህ መጽሔት፣ አንባቢያኑ የእነሱ ዓይነት የሚደነቅ እምነት ያላቸውን ሰዎች እንዲፈልጉና በየጊዜው ከእነዚህ ሰዎች ጋር በመገናኘት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ያበረታታ ነበር። ከ1894 መባቻ ጀምሮ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር፣ ጉብኝት እንዲደረግላቸው ጥያቄ የሚያቀርቡ ቡድኖችን ያሉበት ድረስ ሄደው የሚረዷቸው ተወካዮችን መላክ ጀመረ። ከጊዜ በኋላ ፒልግሪም ተብለው መጠራት የጀመሩት እነዚህ ታታሪና ተሞክሮ ያላቸው ወንዶች ለዚህ መብት የሚመረጡት የገርነትን ባሕርይ በማዳበራቸው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታቸው፣ በንግግርና በማስተማር ችሎታቸው እንዲሁም ለቤዛው ትምህርት ታማኝ መሆናቸውን በማስመሥከራቸው ነበር። በአብዛኛው ጉብኝቱ የሚቆየው ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ሲሆን ጎብኚዎቹ ሥራ ይበዛባቸው ነበር። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አገልግሎታቸውን ሀ ብለው የጀመሩት ፒልግሪሞች ለሚያቀርቡት የሕዝብ ንግግር የመጋበዣ ወረቀቶችን በማሰራጨት ነበር። ከጊዜ በኋላ የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ሁጎ ሬመር፣ በአንድ ወቅት ምሽት ላይ ትምህርት ቤት ውስጥ ንግግር ከሰጠ በኋላ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መልስ ሲሰጥ አምሽቷል። ጉብኝቱን ሲጨርስ ድካም ቢሰማውም በጣም ደስተኛ ስለነበር ስብሰባው “ጥሩ” እንደነበር ተናግሯል።

መጠበቂያ ግንብ የፒልግሪሞች ጉብኝት “ዋነኛ ዓላማ” አማኝ በሆኑ ክርስቲያኖች ቤት በመሰብሰብ “የእምነት ቤተሰቦችን ማጠናከር” እንደሆነ ገልጾ ነበር። በአካባቢው የሚኖሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ንግግሮችን እንዲሁም የጥያቄና መልስ ውይይቶችን ለማዳመጥ ይመጡ ነበር። ፕሮግራሙ ሲጠናቀቅ ደግሞ ክርስቲያናዊ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ የሚያሳዩበት አጋጣሚ ያገኛሉ። እህት ሞድ አቦት፣ ልጅ ሳለች ማለዳ በተደረገ አንድ ንግግር ላይ ተገኝታ ነበር፤ ንግግሩ ሲያበቃ ሁሉም ወደ ጓሮ ዞረው በትልቅ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው እንደነበር ታስታውሳለች። እህት ሞድ እንዲህ ብላለች፦ “በጣም ጣፋጭ የሆኑ ምግቦች ቀርበው ነበር፤ የአሳማ ሥጋ፣ የተጠበሰ ዶሮ፣ የተለያዩ የዳቦ ዓይነቶች፣ ኬኮችና ሌሎች ጣፋጭ ምግቦች ተደርድረዋል! ሁሉም ሰው የሚችለውን ያህል ሲበላ ከቆየ በኋላ ስምንት ሰዓት ላይ ሌላ ንግግር ለማዳመጥ ተሰበሰብን።” ይሁን እንጂ “ሁሉም ሰው እንቅልፍ ያዳፋው ጀመር” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። ለበርካታ ዓመታት በፒልግሪምነት ያገለገለው ቤንጃሚን ባርተን ‘የሚቀርብልኝን ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች ሁሉ በልቼ ቢሆን ኖሮ ገና ድሮ አብቅቶልኝ ነበር’ ብሏል። ከጊዜ በኋላ ብሩክሊን የሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት በላከው ደብዳቤ ላይ እህቶች ለፒልግሪሞቹ “ወትሮ የሚመገቧቸውን ቀለል ያሉ ምግቦችን ቢያቀርቡ” እንዲሁም “ጥሩ እንቅልፍ እንዲያገኙ” ቢያደርጉ የተሻለ እንደሚሆን ምክር ሰጠ።

ፒልግሪሞች በማስተማር የተካኑ ከመሆናቸውም ሌላ ትምህርቱን ሕያው በሆነ መንገድ ለማቅረብ ሥዕላዊ መግለጫዎችን፣ ሞዴሎችንና ሌሎች ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር። የሪቻርድ ባርበር ንግግሮች “ምንጊዜም የተቀመሙ ነበሩ።” አባታዊ ባሕርይ ያለው ዋልተር ቶርን ሲናገር “የጥንት አባቶችን ይመስል ነበር።” ሺልድ ቱትጂአን የተባለ ወንድም አንድ ቀን ከሌሎች ጋር በፎርድ መኪና እየሄደ ሳለ በድንገት “አቁም!” ብሎ ጮኸ። ቱትጂአን ከመኪናው ዘሎ ከወረደ በኋላ የሜዳ አበቦችን ቀጥፎ በማምጣት አብረውት ለሚጓዙት ሰዎች ስለ ይሖዋ ፍጥረት ትምህርት ሰጣቸው።

የፒልግሪሞች ሥራ በተለይ በዕድሜ ለገፉት ተፈታታኝ ነበር። ለአንዳንዶች ግን በጣም ፈታኝ የሆነባቸው በሥራቸው የትኩረት አቅጣጫ ላይ የተደረገውን ለውጥ መቀበል ነው። በዚህ ማስተካከያ መሠረት ፒልግሪሞች ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው የስብከት ሥራ በግንባር ቀደምትነት እንዲሰማሩ ይጠበቅባቸው ነበር። የመጋቢት 15, 1924 መጠበቂያ ግንብ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ከተሰጡት “ዋነኛ ተልእኮዎች” መካከል አንዱ “ስለ መንግሥቱ መመሥከር” እንደሆነ ገልጾ ነበር። አክሎም “ፒልግሪሞች የሚላኩት ለዚህ ዓላማ ነው” ብሏል።

እርግጥ ነው፣ ይህን ለውጥ የተቀበሉት ሁሉም ፒልግሪሞች አልነበሩም፤ በመሆኑም አንዳንዶች ሥራቸውን ያቆሙ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የራሳቸውን የእምነት ቡድኖች እስከማቋቋም ደርሰው ነበር። ሮቢ አድኪንስ፣ በጣም ጥሩ ተናጋሪ የነበረ አንድ ፒልግሪም የሚከተለውን በምሬት ሲናገር እንደሰማ ያስታውሳል፦ “እኔ የማውቀው መድረክ ላይ ወጥቶ መስበክ ብቻ ነው። ከቤት ወደ ቤት እንኳ ፈጽሞ ልሄድ አልችልም!” ወንድም አድኪንስ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ወንድም ከዚያ በኋላ ያየሁት በ1924 በኮሎምቦስ፣ ኦሃዮ ተደርጎ በነበረው የአውራጃ ስብስባ ላይ ነበር። በጣም ተጎሳቁሎ የነበረ ከመሆኑም በላይ በሺዎች ከሚቆጠሩ ደስተኛ ወንድሞች ተነጥሎ ለብቻው ዛፍ ሥር ቆሞ ነበር። ከዚያ ወዲህ አይቼው አላውቅም። ብዙም ሳይቆይ ድርጅቱን ትቶ ወጣ።” በሌላ በኩል ግን “የደስታ ስሜት የሚነበብባቸው በርካታ ወንድሞች መጻሕፍትን መኪኖቻቸው ላይ ለመጫን ወዲያ ወዲህ ይራወጡ ነበር።” ይህም ከቤት ወደ ቤት ለመመሥከር እንደጓጉ ያሳያል።​—ሥራ 20:20, 21

ብዙ ፒልግሪሞች፣ እነሱ ከሚያሠለጥኗቸው ወንድሞች ያልተናነሰ ፍርሃት ቢሰማቸውም ሥራውን በቅንዓት ያከናውኑ ነበር። በፒልግሪምነት የሚያገለግለውና ጀርመንኛ ተናጋሪ የነበረው ማክስዌል ፍሬንድ (ፍረሸል) ከቤት ወደ ቤት ስለሚደረገው አገልግሎት ሲጽፍ “ፒልግሪሞች ወደተለያዩ ቦታዎች በመጓዝ ከሚሠሯቸው ሥራዎች ይሄኛው ተጨማሪ በረከቶችን አስገኝቷል” ብሏል። ፒልግሪም ጆን ቦኔት ወንድሞች በአጠቃላይ፣ ለመንግሥቱ ስብከት ሥራ ትኩረቱ መሰጠቱን ከልባቸው እንደተቀበሉት ሪፖርት አድርጓል። እሱ እንደተናገረው አብዛኞቹ ወንድሞች “በጦርነቱ ላይ ከፊት ለመሠለፍ ከፍተኛ ቅንዓት” ነበራቸው።

ባለፉት ዓመታት በሙሉ እነዚህ ታማኝ ተጓዥ ወንድሞች በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድረዋል። የይሖዋ ምሥክር ከሆነ በርካታ ዓመታት የሆነው ኖርማን ላርሰን እንዲህ ብሏል፦ “በልጅነቴ ካየሁት ነገር እንኳ በመነሳት ፒልግሪሞች ብዙ ጠቃሚ ነገር እንዳከናወኑ መናገር እችላለሁ። በትክክለኛው መንገድ እንድጓዝ ጥሩ አድርገው ቀርጸውኛል።” ዛሬም ቢሆን የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ ታማኝ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን “ከቤት ወደ ቤት መሄድ እንችላለን!” እንዲሉ እየረዷቸው ነው።

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ፒልግሪሞች የሚመጡባቸው ቀናት በጣም አስደሳች ነበሩ!

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤንጃሚን ባርተን በ1905 ያደረገው የጉብኝት ፕሮግራም 170 አካባቢዎችን ያጠቃልል ነበር

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንድም ዋልተር ቶርን የተባለው ፒልግሪም በአባታዊ ፍቅሩና የክርስቶስ ዓይነት ባሕርያት ያሉት በመሆኑ ፓፒ (አባባ) ተብሎ ይጠራ ነበር

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንድም ብራውን 14 ትናንሽ ቡድኖችን እንዲያጠናክርና እንዲያበረታታ በ1902 ፒልግሪም ሆኖ ወደ ጃማይካ ተልኮ ነበር

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፒልግሪሞች ሥራ የሌሎችን እምነት ይገነባ፣ ክርስቲያናዊ አንድነትን ያጠናክር ብሎም ወንድሞች ወደ ድርጅቱ እንዲቀርቡ ያደርግ ነበር