በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጸንታችሁ በመቆም የሰይጣንን ወጥመዶች ተቋቋሙ!

ጸንታችሁ በመቆም የሰይጣንን ወጥመዶች ተቋቋሙ!

ጸንታችሁ በመቆም የሰይጣንን ወጥመዶች ተቋቋሙ!

“የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች [ተቋቋሙ]።”​—ኤፌ. 6:11

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

አንድ የይሖዋ አገልጋይ ከፍቅረ ንዋይ ወጥመድ መራቅ የሚችለው እንዴት ነው?

አንድ ያገባ ክርስቲያን በምንዝር ጉድጓድ ውስጥ እንዳይወድቅ ምን ሊረዳው ይችላል?

ከፍቅረ ንዋይና ከሥነ ምግባር ብልግና ጋር በተያያዘ የሚቀርብልንን ፈተና መቋቋማችን ጥቅሞች አሉት ብለህ እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው?

1, 2. (ሀ) ሰይጣን ለቅቡዓኑም ሆነ ‘ለሌሎች በጎች’ የርኅራኄ ስሜት የሌለው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ የትኞቹን የሰይጣን ወጥመዶች እንመረምራለን?

ሰይጣን ዲያብሎስ ለሰው ልጆች በተለይም ለይሖዋ አገልጋዮች ምንም ዓይነት የርኅራኄ ስሜት የለውም። እንዲያውም በቅቡዓን ቀሪዎች ላይ ጦርነት አውጇል። (ራእይ 12:17) እነዚህ ቀናተኛ ክርስቲያኖች በዘመናችን የሚካሄደውን የመንግሥቱን ስብከት ሥራ በግንባር ቀደምትነት እየሠሩ ሲሆን ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ መሆኑንም እያጋለጡ ነው። ዲያብሎስ፣ ቅቡዓንን ለሚያግዙትና ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ለሚያደርጉት ‘ለሌሎች በጎችም’ ፍቅር የለውም፤ ሰይጣን ለዘላለም የመኖር ተስፋውን አጥቷል። (ዮሐ. 10:16) በመሆኑም መቆጣቱ የሚያስገርም አይደለም! ተስፋችን ሰማይም ይሁን ምድር ሰይጣን የእኛ ደኅንነት እንደማያሳስበው የተረጋገጠ ነው። ዓላማው እኛን ማጥቃት ነው።​—1 ጴጥ. 5:8

2 ሰይጣን ዓላማውን ለማሳካት የተለያዩ ወጥመዶችን ይዘረጋል። ዲያብሎስ የማያምኑትን ሰዎች ‘አእምሮ በማሳወሩ’ ብዙዎች ምሥራቹን አይቀበሉም፤ እንዲሁም የእሱን ወጥመዶች ማስተዋል አይችሉም። ዲያብሎስ የመንግሥቱን መልእክት የተቀበሉ ሰዎችንም ለመያዝ ወጥመድ ያዘጋጃል። (2 ቆሮ. 4:3, 4) ቀደም ሲል በተመለከትነው ርዕስ ላይ ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው ሦስት ወጥመዶች ራሳችንን እንዴት መጠበቅ እንደምንችል አይተናል። እነዚህም (1) ያልተገራ አንደበት፣ (2) የሰው ፍርሃትና የእኩዮች ተጽዕኖ እንዲሁም (3) ከመጠን ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ናቸው። አሁን ደግሞ ሌሎች ሁለት የሰይጣን ወጥመዶችን እንዴት መቋቋም እንደምንችል እንመረምራለን፤ የመጀመሪያው ፍቅረ ንዋይ ሲሆን ሁለተኛው ምንዝር የመፈጸም ፈተና ነው።

ፍቅረ ንዋይ​—አንቆ የሚይዝ ወጥመድ

3, 4. የዚህ ሥርዓት ጭንቀት አንዳንዶች ቁሳዊ ነገር እንዲያሳድዱ ያደረጋቸው እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ በሰጠው አንድ ምሳሌ ላይ በእሾህ መካከል ስለተዘራ ዘር ተናግሮ ነበር። አንድ ሰው ቃሉን ሊሰማ ቢችልም ‘የዚህ ሥርዓት ጭንቀት እንዲሁም ሀብት ያለው የማታለል ኃይል ቃሉን እንደሚያንቀውና የማያፈራ እንደሚያደርገው’ ተናግሯል። (ማቴ. 13:22) በእርግጥም ፍቅረ ንዋይ፣ ጠላታችን ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው ወጥመዶች አንዱ ነው።

4 ቃሉን የሚያንቁት፣ ሁለት ነገሮች በአንድነት ተጣምረው ነው። አንደኛው “የዚህ ሥርዓት ጭንቀት” ነው። የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ በሆነ’ ዘመን ውስጥ በመሆኑ በርካታ የሚያስጨንቁ ነገሮች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ። (2 ጢሞ. 3:1) ኑሮ እየተወደደ በመምጣቱና የሥራ አጦች ቁጥር በመጨመሩ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ለማሟላት ተቸግረህ ይሆናል። ስለ ወደፊቱ ጊዜ በማሰብም ተጨንቀህ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ ‘ጡረታ ከወጣሁ በኋላ ሕይወቴን ለመምራት በቂ ገንዘብ ይኖረኝ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስብህ ይሆናል። አንዳንዶች ገንዘብ አስተማማኝ የሆነ ሕይወት ለመምራት ዋስትና እንደሚሆን ስለተሰማቸው ጭንቀታቸውን ለማስወገድ ሲሉ ሀብትን ማሳደድ ጀምረዋል።

5. ‘ሀብት የማታለል ኃይል’ ሊኖረው የሚችለው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ፣ ቃሉን የሚያንቀው ሌላኛው ነገር “ሀብት ያለው የማታለል ኃይል” እንደሆነ ተናግሯል። ይህ ነገር ከጭንቀት ጋር ተዳምሮ ቃሉን ሊያንቀው ይችላል። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብ ጥላ ከለላ” እንደሆነ ይናገራል። (መክ. 7:12) ሆኖም ሀብትን ማሳደድ የጥበብ እርምጃ አይደለም። ብዙዎች ሀብታም ለመሆን ጥረት ባደረጉ መጠን ፍቅረ ንዋይ ወጥመድ እንደሆነባቸው አስተውለዋል። እንዲያውም አንዳንዶች ለሀብት ባሪያ ሆነዋል።​—ማቴ. 6:24

6, 7. (ሀ) አንድ ሰው በሥራ ቦታው በፍቅረ ንዋይ ወጥመድ የመያዝ አደጋ ሊያጋጥመው የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን ትርፍ ሰዓት እንዲሠራ ግብዣ ሲቀርብለት ምን ነገሮችን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል?

6 አንድ ሰው ሀብታም የመሆን ምኞት የሚያዳብረው ሳይታወቀው ሊሆን ይችላል። እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። አሠሪህ ወደ አንተ መጥቶ እንዲህ አለህ እንበል፦ “ዛሬ የምሥራች ይዤልህ መጥቻለሁ! ድርጅታችን አንድ ትልቅ ጨረታ አሸንፏል። ይህ ማለት እንግዲህ፣ ለተወሰኑ ወራት ምሽት ላይ ሥራ መግባት አለብህ ማለት ነው። ነገር ግን ጠቀም ያለ ክፍያ ስለምታገኝ ተጨማሪ ሰዓት ብትሠራም የሚያስቆጭ አይሆንም።” እንዲህ ያለ ግብዣ ቢቀርብልህ ምን ምላሽ ትሰጣለህ? እውነት ነው፣ ለቤተሰብህ ቁሳዊ ነገር የማቅረቡን ጉዳይ በቁም ነገር መመልከትህ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ሆኖም ያለብህ ኃላፊነት ይህ ብቻ አይደለም። (1 ጢሞ. 5:8) ግምት ውስጥ ልታስገባቸው የሚገቡ ሌሎች በርካታ ጉዳዮችም አሉ። ትርፍ ጊዜ በመሥራት የምታሳልፈው ሰዓት ምን ያህል ነው? ሰብዓዊ ሥራህ የጉባኤ ስብሰባንና የቤተሰብ አምልኮን ጨምሮ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችህን ይነካብሃል?

7 ውሳኔ በምታደርግበት ጊዜ በዋነኝነት የሚያሳስብህ ምንድን ነው? ትርፍ ሰዓት መሥራትህ ከገንዘብ አኳያ የሚያስገኝልህ ጥቅም ነው ወይስ በመንፈሳዊነትህ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ? ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ያለህ ጉጉት በሕይወትህ ውስጥ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ እንዳትሰጥ እንቅፋት ይሆንብህ ይሆን? የራስህንም ሆነ የቤተሰብህን መንፈሳዊነት ችላ የምትል ከሆነ ፍቅረ ንዋይ ወጥመድ ሊሆንብህ እንደሚችል ተገንዝበሃል? ገንዘብ ለማግኘት ስትል መንፈሳዊነትህ አደጋ ላይ ወድቆ ከሆነ የሰይጣንን መሠሪ ዘዴዎች መቋቋምና ፍቅረ ንዋይ አንቆ እንዳይዝህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?​—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ።

8. ያለንበትን ሁኔታ ለመገምገም የሚረዱን የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ናቸው?

8 ፍቅረ ንዋይ አንቆ እንዳይዝህ በየጊዜው ያለህበትን ሁኔታ ገምግም። ለመንፈሳዊ ነገሮች አክብሮት የጎደለው መሆኑን በተግባሩ እንዳስመሠከረው እንደ ዔሳው መሆን እንደማትፈልግ ግልጽ ነው። (ዘፍ. 25:34፤ ዕብ. 12:16) እንዲሁም ኢየሱስ ያለውን ሁሉ ሸጦ ለድሆች በመስጠት እሱን እንዲከተል ግብዣ እንዳቀረበለት ሰው መሆን እንደማትፈልግ የተረጋገጠ ነው። ይህ ሰው የተባለውን ከማድረግ ይልቅ “ብዙ ንብረት ስለነበረው እያዘነ ሄደ።” (ማቴ. 19:21, 22) ሀብት ወጥመድ ስለሆነበት፣ በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ ታላቅ ሰው የሆነው የኢየሱስ ተከታይ የመሆን ውድ መብት አጣ! አንተም የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የመሆን መብትህን እንዳታጣ ተጠንቀቅ።

9, 10. ቅዱሳን መጻሕፍት ቁሳዊ ነገሮችን በተመለከተ ከሚሰጡት ምክር በመነሳት ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ ትችላለህ?

9 ስለ ቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ እንዳንጨነቅ ከፈለግን ኢየሱስ የሰጠውን የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ልብ ማለት ይኖርብናል፦ “‘ምን እንበላለን?’ ወይም ‘ምን እንጠጣለን?’ ወይም ደግሞ ‘ምን እንለብሳለን?’ ብላችሁ ፈጽሞ አትጨነቁ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሕዛብ አጥብቀው የሚፈልጓቸው ናቸው። በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል።”​—ማቴ. 6:31, 32፤ ሉቃስ 21:34, 35

10 ሀብት ያለው የማታለል ኃይል ወጥመድ እንዳይሆንብህ ከፈለግክ “የሚያስፈልገኝን ያህል . . . ስጠኝ እንጂ ሀብታም ወይም ድኻ አታድርገኝ” በማለት የተናገረው የአጉር ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 30:8 የ1980 ትርጉም) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው አጉር ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደሚሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሀብት የማታለል ኃይል እንዳለው ተገንዝቦ ነበር። የዚህ ሥርዓት ጭንቀትና ሀብት ያለው የማታለል ኃይል መንፈሳዊነትህን ሊያሳጡህ እንደሚችሉ ፈጽሞ አትዘንጋ። ስለ ቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ መጨነቅ ጊዜህን ሊያባክንብህ፣ ኃይልህን ሊያሟጥጥብህ እንዲሁም ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስቀደም ያለህን ፍላጎት ቀስ በቀስ ሊያጠፋብህ ይችላል። በመሆኑም የሰይጣን ወጥመድ የሆነው ፍቅረ ንዋይ አንቆ እንዳይዝህ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ!​—ዕብራውያን 13:5ን አንብብ።

ምንዝር​—ስውር ጉድጓድ

11, 12. አንድ ክርስቲያን ከሥራ ባልደረባው ጋር ምንዝር ለመፈጸም የሚፈተነው እንዴት ሊሆን ይችላል?

11 አዳኞች፣ አንድ ትልቅ እንስሳ ለመያዝ ሲፈልጉ እንስሳው አዘውትሮ በሚመላለስበት መንገድ ላይ ጉድጓድ ይቆፍራሉ፤ አብዛኛውን ጊዜ ጉድጓዱ ላይ ቀጫጭን እንጨት ከረበረቡ በኋላ አፈር ያለብሱታል። ሰይጣን በጣም ውጤታማ ሆኖ ካገኛቸው ፈተናዎች አንዱ ከዚህ ወጥመድ ጋር ይመሳሰላል፤ ይህም የሥነ ምግባር ብልግና ነው። (ምሳሌ 22:14፤ 23:27) በርካታ ክርስቲያኖች በቀላሉ እጃቸውን እንዲሰጡ በሚያደርጋቸው ሁኔታ ውስጥ ራሳቸውን በማስገባታቸው እዚህ ጉድጓድ ውስጥ ገብተዋል። አንዳንድ ያገቡ ክርስቲያኖች ከተቃራኒ ፆታ ጋር አላስፈላጊ የሆነ ቅርርብ በመፍጠራቸው ምንዝር እስከመፈጸም ደርሰዋል።

12 በሥራ ቦታችሁ ተገቢ ያልሆነ የፍቅር ግንኙነት እንድትጀምሩ ትፈተኑ ይሆናል። አንድ ዓለማዊ ጥናት እንደጠቆመው ምንዝር ከፈጸሙት ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች እንዲሁም ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ወንዶች ይህን ያደረጉት አብረዋቸው ከሚሠሩ ሰዎች ጋር ተገቢ ያልሆነ ቅርርብ በመፍጠራቸው ነው። የሥራህ ዓይነት፣ ተቃራኒ ፆታ ካላቸው ሰዎች ጋር እንድትቀራረብ ያስገድድሃል? ከሆነ ከእነሱ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል? ከሥራ ያለፈ ግንኙነት እንዳይፈጠር ገደብ አበጅተሃል? ለምሳሌ፣ አንዲት እህት አብሯት ከሚሠራ አንድ ሰው ጋር ከሥራ ውጪ ስለሆኑ ጉዳዮች ብዙ ጊዜ የምታወራ ከሆነ ሚስጥረኛዋ ልታደርገው አልፎ ተርፎም በትዳሯ ውስጥ ስለሚያጋጥማት ችግር ልታጫውተው ትችላለች። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ወንድም አብራው ከምትሠራ ሴት ጋር ስለተግባባ እንዲህ ብሎ ሊያስብ ይችላል፦ “የእኔን አመለካከት ታከብርልኛለች፤ ደግሞም የምናገረውን በጥሞና ታዳምጣለች። እንዲሁም ለእኔ አድናቆት አላት። ምናለ ሚስቴ እንዲህ ብትሆንልኝ!” እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች ምንዝር ለመፈጸም ምን ያህል እንደተጋለጡ አስተዋላችሁ?

13. በጉባኤ ውስጥ ተገቢ ያልሆነ የፍቅር ግንኙነት ሊመሠረት የሚችለው እንዴት ነው?

13 ተገቢ ያልሆነ የፍቅር ግንኙነት በጉባኤ ውስጥም ሊጀመር ይችላል። እስቲ የሚከተለውን አንድ እውነተኛ ታሪክ እንመልከት፦ ዳንኤልና ባለቤቱ ሣራ * የዘወትር አቅኚዎች ነበሩ። ዳንኤል “እምቢ የሚል ቃል ከአፉ የማይወጣ ሽማግሌ” እንደነበር ይናገራል። የሚሰጠውን ኃላፊነት በሙሉ በደስታ የሚቀበል ሰው ነበር። ዳን⁠ኤል አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የነበሩት ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሦስቱ ተጠምቀውለታል። እነዚህ አዲስ የተጠመቁ ወንድሞች በተወሰነ መጠን እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር። በመሆኑም ዳንኤል በተለያዩ ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶች በሚወጣጠርበት ጊዜ ሣራ እነዚህን ወንድሞች ትረዳቸው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ይህ ነገር ልማድ እየሆነ መጣ፤ የዳንኤል የቀድሞ ጥናቶች ስሜታዊ እርዳታ ባስፈለጋቸው ቁጥር ወደ ሣራ ይመጣሉ። እሷ ደግሞ ትኩረት በሚያስፈልጋት ጊዜ ወደ ዳንኤል ጥናቶች ዘወር ትላለች። በዚህ መንገድ አንድ አደገኛ ወጥመድ ተዘረጋ። ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴ ከወር እስከ ወር ያላትን ኃይል ሁሉ ተጠቅማ ሌሎችን ለመርዳት ትጥር ስለነበር መንፈሳዊም ሆነ ስሜታዊ እርዳታ ያስፈልጋት ነበር። ይህ ሁኔታ እሷን ችላ ከማለቴ ጋር ተዳምሮ በጣም አሳዛኝ ነገር እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል። ባለቤቴ ከቀድሞ ጥናቶቼ ከአንዱ ጋር ምንዝር ፈጸመች። አፍንጫዬ ሥር ሆና በመንፈሳዊ ስትደክም ምንም አላስተዋልኩም፤ ምክንያቱም ትኩረት ያደረግኩት ኃላፊነቶቼን በመወጣት ላይ ብቻ ነበር።” ይህ ሁኔታ በአንተ ላይ እንዳይደርስ ምን ማድረግ ትችላለህ?

14, 15. አንድ ያገባ ክርስቲያን በምንዝር ጉድጓድ ውስጥ ከመግባት ምን ሊጠብቀው ይችላል?

14 በምንዝር ጉድጓድ ውስጥ እንዳትወድቅ ከፈለግክ ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ማሰላሰልህ ጠቃሚ ነው። ኢየሱስ “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” ብሏል። (ማቴ. 19:6) ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነትህ ከትዳር ጓደኛህ እንደሚበልጥ አድርገህ በፍጹም ማሰብ የለብህም። በተጨማሪም እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮችን ለማከናወን ስትል ብዙ ጊዜ ከትዳር ጓደኛህ ተለይተህ ጊዜ ማሳለፍህ በትዳርህ ውስጥ ችግር እንዳለ ይጠቁማል፤ ይህ ደግሞ ወደ ፈተና አልፎ ተርፎም ከባድ ኃጢአት ወደ መሥራት ሊመራህ ይችላል።

15 ምናልባት ሽማግሌ ከሆንክ መንጋውን የመንከባከቡ ኃላፊነትህ ያሳስብህ ይሆናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክ መንጋ ጠብቁ፤ በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በመመኘት ሳይሆን ለማገልገል በመጓጓት [ጠብቁ]።” (1 ጴጥ. 5:2) በአደራ የተሰጡህን የጉባኤ አባላት ችላ ማለት እንደሌለብህ የታወቀ ነው። ሆኖም በጉባኤ ውስጥ እረኛ የመሆን ኃላፊነትህን የምትወጣው የባልነት ኃላፊነትህን አደጋ ላይ ጥለህ መሆን የለበትም። የትዳር ጓደኛህ “እየተራበች” መንጋውን ለመመገብ መሯሯጥህ ምንም ፋይዳ የለውም፤ እንዲያውም እንዲህ ማድረጉ አደገኛ ነው። ዳንኤል ‘ቤተሰብህ እስኪጎዳ ድረስ በጉባኤ ኃላፊነት መወጠር የለብህም’ ብሏል።

16, 17. (ሀ) ያገቡ ክርስቲያኖች በሥራ ቦታቸው የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር ሐሳቡም እንኳ እንደሌላቸው በግልጽ ለማሳወቅ ምን እርምጃዎችን መውሰድ ይችላሉ? (ለ) ክርስቲያኖች ምንዝር እንዳይፈጽሙ ሊረዷቸው የሚችሉ አንዳንድ ጽሑፎች የትኞቹ ናቸው?

16 ያገቡ ክርስቲያኖች በምንዝር ወጥመድ ውስጥ ከመግባት እንዲጠበቁ ሊረዷቸው የሚችሉ በርካታ ምክሮች በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ወጥተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የመስከረም 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ምክር ይዟል፦ “በሥራ ቦታም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የፍቅር ግንኙነት ወደ መመሥረት ሊያደርሱ በሚችሉ ሁኔታዎች ውስጥ ላለመግባት ተጠንቀቁ። ለምሳሌ፣ ተቃራኒ ጾታ ካለው ሰው ጋር ከሥራ ሰዓት ውጭ ተቀራርቦ መሥራት ለፈተና ሊዳርግ ይችላል። ያገባችሁ እንደመሆናችሁ መጠን ከትዳር ጓደኛችሁ ውጭ ከማንም ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት ፈቃደኛ አለመሆናችሁን በንግግራችሁም ሆነ በአኳኋናችሁ በግልጽ ማሳየት ይኖርባችኋል። ለአምላክ ያደራችሁ ሰዎች ስለሆናችሁ ሌሎችን በማሽኮርመምም ሆነ ተገቢ ባልሆነ አለባበስና አጋጌጥ አላስፈላጊ ትኩረት መሳብ እንደማትፈልጉ ጥያቄ የለውም። . . . የትዳር ጓደኛችሁንና የልጆቻችሁን ፎቶግራፍ በሥራ ቦታችሁ ማስቀመጣችሁ ከፍ ያለ ግምት የምትሰጧቸው ሰዎች መኖራቸውን እናንተም ሆናችሁ ሌሎች እንድታስታውሱ ይረዳችኋል። ሌሎች ሰዎች እናንተን በፍቅር ለመማረክ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲቀጥሉበት የሚያበረታታ አዝማሚያ ላለማሳየትና ሌላው ቀርቶ ድርጊታቸውን በዝምታ ላለማለፍም ጭምር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።”

17 የሚያዝያ 2009 ንቁ! “ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?” በሚለው ርዕስ ላይ የትዳር ጓደኛ ካልሆነ ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት ስለ መፈጸም ማውጠንጠን አደጋ እንዳለው አስጠንቅቆ ነበር። ይህ መጽሔት አንድ ሰው ስለ ፆታ ግንኙነት ማውጠንጠኑ ምንዝር የመፈጸሙ አጋጣሚ ሰፊ እንዲሆን ሊያደርግ እንደሚችል ጠቁሟል። (ያዕ. 1:14, 15) ያገባህ ከሆንክ ከትዳር ጓደኛህ ጋር እንዲህ ያሉ ትምህርቶችን በየጊዜው መከለስህ ጥበብ ነው። የጋብቻን ዝግጅት ያቋቋመው ይሖዋ ከመሆኑም በላይ ጋብቻ ቅዱስ ነገር ነው። ከባለቤትህ ጋር ስለ ትዳራችሁ ለመወያየት ጊዜ መመደብህ ቅዱስ ነገሮችን እንደምታደንቅ ከምታሳይባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ ነው።​—ዘፍ. 2:21-24

18, 19. (ሀ) ምንዝር መፈጸም ምን መዘዝ ያስከትላል? (ለ) ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን ምን ጥቅሞችን ያስገኛል?

18 ተገቢ ያልሆነ የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት ከተፈተንክ ዝሙትም ሆነ ምንዝር መፈጸም በሚያስከትለው ጎጂ ውጤት ላይ አሰላስል። (ምሳሌ 7:22, 23፤ ገላ. 6:7) የሥነ ምግባር ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች ይሖዋን የሚያሳዝኑ ከመሆኑም በላይ ራሳቸውንም ሆነ የትዳር ጓደኛቸውን ይጎዳሉ። (ሚልክያስ 2:13, 14ን አንብብ።) ከዚህ ይልቅ ንጹሕ ሥነ ምግባር መያዝ በሚያስገኛቸው ጥቅሞች ላይ ማሰላሰሉ ጠቃሚ ነው። እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ከመሆኑም ሌላ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ንጹሕ ሕሊና ይዘው የተሻለ ሕይወት መምራት ይችላሉ።​—ምሳሌ 3:1, 2ን አንብብ።

19 መዝሙራዊው “ሕግህን የሚወዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ ዕንቅፋትም የለባቸውም” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 119:165) እንግዲያው ለእውነት ፍቅር ሊኖረን ይገባል፤ እንዲሁም በእነዚህ ክፉ ቀኖች ‘የምንመላለሰው ጥበብ እንደጎደላቸው ሰዎች ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ ማስተዋል አለብን።’ (ኤፌ. 5:15, 16) የምንጓዝበት የሕይወት መንገድ ሰይጣን እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮችን ለማጥመድ በዘረጋቸው ወጥመዶች የተሞላ ነው። ሆኖም ራሳችንን ከእነዚህ ወጥመዶች ለመጠበቅ በቂ መሣሪያዎች አሉን። ይሖዋ “የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች መቋቋም” እንዲሁም “የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ማምከን” እንድንችል የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ሰጥቶናል።​—ኤፌ. 6:11, 16

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 ስሞቹ ተቀይረዋል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍቅረ ንዋይ አንድን ክርስቲያን በመንፈሳዊ ሊያንቀው ይችላል። ይህ ሁኔታ በአንተ ላይ እንዲደርስ አትፍቀድ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማሽኮርመምም ሆነ ለዚያ ምላሽ መስጠት ወደ ምንዝር ሊመራ ይችላል