ይህ ዓለም ወደ ፍጻሜው የሚመጣው እንዴት ነው?
“በጨለማ ውስጥ ስላልሆናችሁ ሌሊቱ ድንገት እንደሚነጋበት ሌባ ያ ቀን ድንገት አይደርስባችሁም።”—1 ተሰ. 5:4
1. ምንጊዜም ነቅተን ለመጠበቅና መከራዎችን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?
ምድርን የሚያናውጡ ነገሮች በቅርቡ ይከሰታሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ይህ ነገር እውነት መሆኑን ያረጋግጣል፤ በመሆኑም ምንጊዜም ነቅተን መጠበቅ ይኖርብናል። ይሁንና ነቅተን ለመጠበቅ ምን ሊረዳን ይችላል? ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ዓይናችንን በማይታዩት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ እንዳለብን’ ማሳሰቢያ ሰጥቶናል። አዎን፣ ተስፋችን ሰማይም ይሁን ምድር ምንጊዜም የዘላለም ሕይወት ሽልማታችንን ማስታወስ ይኖርብናል። በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ጳውሎስ ከላይ ያለውን የጻፈው የእምነት ባልንጀሮቹ፣ የሚከተሉት የታማኝነት ጎዳና በሚያስገኝላቸው ሽልማት ላይ እንዲያተኩሩ ለማበረታታት ነው። እንዲህ ማድረጋቸው ደግሞ የሚደርስባቸውን መከራና ስደት እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል።—2 ቆሮ. 4:8, 9, 16-18፤ 5:7
2. (ሀ) ተስፋችንን እስከ መጨረሻው አጥብቀን ለመያዝ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?
2 ጳውሎስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ አንድ አስፈላጊ የሆነ መሠረታዊ ሥርዓት ይዟል፤ ይኸውም ተስፋችንን እስከ መጨረሻው አጥብቀን ለመያዝ ከፈለግን አሁን ከሚታዩን ነገሮች ባሻገር መመልከት ይኖርብናል። በሌላ አባባል፣ ገና ያልታዩ ወሳኝ ክንውኖች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልገናል። (ዕብ. 11:1፤ 12:1, 2) እንግዲያው በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ከዘላለም ሕይወት ተስፋችን ጋር የተያያዙ ወደፊት የሚፈጸሙ አሥር ክንውኖችን እንመለከታለን።
መጨረሻው ሊመጣ ሲል ምን ነገር ይከሰታል?
3. (ሀ) በ1 ተሰሎንቄ 5:2, 3 ላይ በቅርቡ የሚፈጸም ምን ነገር ተጠቅሷል? (ለ) የፖለቲካ መሪዎች ምን ያደርጋሉ? እነማንስ ሊተባበሯቸው ይችላሉ?
3 ወደፊት ከምንጠብቃቸው ክንውኖች መካከል አንደኛውን ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ገልጾታል። (1 ተሰሎንቄ 5:2, 3ን አንብብ።) ጳውሎስ በደብዳቤው ላይ ‘የይሖዋን ቀን’ ጠቅሷል። “የይሖዋ ቀን” የሚለው አገላለጽ በዚህ አገባቡ የሚያመለክተው በሐሰት ሃይማኖት ጥፋት ጀምሮ በአርማጌዶን ጦርነት የሚደመደመውን ጊዜ ነው። ይሁንና የይሖዋ ቀን ከመጀመሩ በፊት የዓለም መሪዎች “ሰላምና ደኅንነት ሆነ!” ይላሉ። ይህ ደግሞ በአንዴ የሚፈጸም ክንውን ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ተከታታይ በሆኑ ክንውኖች ይፈጸም ይሆናል። በዚህ ወቅት ብሔራት ለዋና ዋና ችግሮቻቸው መፍትሔ እንዳስገኙ ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል። ስለ ሃይማኖት መሪዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነሱም የዚህ ዓለም ክፍል እንደመሆናቸው መጠን ከፖለቲካ መሪዎች ጎን እንደሚሰለፉ መጠበቁ ምክንያታዊ ነው። (ራእይ 17:1, 2) በመሆኑም እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች በጥንቷ ይሁዳ የነበሩትን ሐሰተኛ ነቢያት ምሳሌ ይከተላሉ። ይሖዋ ስለ እነዚህ ሐሰተኛ ነቢያት ሲናገር “ሰላምም ሳይኖር፣ ‘ሰላም፣ ሰላም’ ይላሉ” ብሏል።—ኤር. 6:14፤ 23:16, 17
4. ከአብዛኛው የሰው ዘር በተቃራኒ ምን ነገር ማስተዋል ችለናል?
4 “ሰላምና ደኅንነት ሆነ!” የሚለው ማንም ይሁን ማን ይህ ሁኔታ መከሰቱ የይሖዋ ቀን መጀመሩን ይጠቁማል። ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት የተናገረው ለዚህ ነው፦ “ወንድሞች፣ በጨለማ ውስጥ ስላልሆናችሁ ሌሊቱ ድንገት እንደሚነጋበት ሌባ ያ ቀን ድንገት አይደርስባችሁም፤ ምክንያቱም እናንተ ሁላችሁ የብርሃን ልጆች [ናችሁ]።” (1 ተሰ. 5:4, 5) ከአብዛኛው የሰው ዘር በተቃራኒ እኛ፣ በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸሙ ያሉት ክንውኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ምን ትርጉም እንዳላቸው እናስተውላለን። ለመሆኑ “ሰላምና ደኅንነት ሆነ!” የሚለው አዋጅ በትክክል ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው? ይህ ወደፊት የምናየው ነገር ይሆናል። እንግዲያው ‘ነቅተን ለመኖርና የማመዛዘን ችሎታችንን ለመጠበቅ’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—1 ተሰ. 5:6፤ ሶፎ. 3:8
እጠፋለሁ ብላ ያላሰበችው “ንግሥት”
5. (ሀ) ‘ታላቁ መከራ’ የሚጀምረው እንዴት ነው? (ለ) እጠፋለሁ ብላ ያላሰበችው “ንግሥት” ማን ናት?
5 ቀጥሎ የሚፈጸመው ገና ያልታየ ክንውን ምንድን ነው? ጳውሎስ “‘ሰላምና ደኅንነት ሆነ!’ ሲሉ . . . ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል” ብሏል። የዚህ “ያልታሰበ ጥፋት” የመጀመሪያ ምዕራፍ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችውና “ጋለሞታይቱ” ተብላ በምትጠራው “ታላቂቱ ባቢሎን” ላይ የሚደርሰው ጥቃት ነው። (ራእይ 17:5, 6, 15) ሕዝበ ክርስትናን ጨምሮ በሁሉም የሐሰት ሃይማኖቶች ላይ የሚደርሰው ይህ ጥቃት ‘የታላቁ መከራ’ መጀመሪያ ይሆናል። (ማቴ. 24:21፤ 2 ተሰ. 2:8) ለብዙዎች ይህ ክንውን ድንገተኛ ይሆንባቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ጋለሞታይቱ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ራሷን የምትቆጥረው እንደ “ንግሥት” ከመሆኑም በላይ ‘ሐዘን ፈጽሞ እንደማይደርስባት’ አድርጋም ታስባለች። ይሁን እንጂ ልትጠፋ እንደምትችል አለማሰቧ ትልቅ ስህተት እንደሆነ መገንዘቧ አይቀርም። “በአንድ ቀን” የሆነ ያህል በፍጥነት ትጠፋለች።—ራእይ 18:7, 8
6. የሐሰት ሃይማኖትን የሚያጠፋው ማን ነው?
* (ራእይ 17:3, 5, 11, 12) ይህ ጥቃት ምን ያህል ከባድ ነው? የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት የጋለሞታይቱን ሀብት የሚዘርፉና ማንነቷን የሚያጋልጡ ከመሆኑም በላይ ይቦጫጭቋታል፤ “ሙሉ በሙሉም በእሳት ያቃጥሏታል።” በእርግጥም የሚደርስባት ጥፋት የማያዳግም ይሆናል።—ራእይ 17:16ን አንብብ።
6 ጋለሞታይቱን የሚያጠቃው “አሥር ቀንዶች” ያሉት “አውሬ” እንደሆነ የአምላክ ቃል ይናገራል። የራእይን መጽሐፍ በምንመረምርበት ጊዜ ይህ አውሬ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን እንደሚያመለክት እንገነዘባለን። ‘አሥሩ ቀንዶች’ የሚያመለክቱት ደግሞ ‘ደማቅ ቀይ የሆነውን አውሬ’ የሚደግፉ በዘመናችን የሚገኙ የፖለቲካ ኃይላትን በሙሉ ነው።7. “አውሬው” ጥቃት እንዲሰነዝር የሚያነሳሳው ምንድን ነው?
7 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት፣ ጥቃቱ እንዲሰነዘር ምክንያት የሚሆነው ነገር ምን እንደሆነም ይነግረናል። ይሖዋ ዓላማውን በሆነ መንገድ በፖለቲካ መሪዎች ልብ ውስጥ በማኖር መሪዎቹ የእሱን ሐሳብ “ዳር እንዲያደርሱ” ይኸውም ጋለሞታይቱን እንዲያጠፏት ያደርጋል። (ራእይ 17:17) ጠብ አጫሪ የሆኑ ሃይማኖቶች፣ በዓለም ላይ ብጥብጥ መፍጠራቸውን ስለሚቀጥሉ ብሔራት ጋለሞታይቱን ማጥፋት የአገራቸውን ጥቅም ከማስከበር አኳያ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አድርገው ያስባሉ። እንዲያውም መሪዎች ጋለሞታይቱ ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ “አንድ የሆነውን የራሳቸውን ሐሳብ” እየፈጸሙ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፤ አምላክ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ ለማጥፋት እንደ መሣሪያ እየተጠቀመባቸው ነው። በዚህ መንገድ ሁኔታዎች ድንገት ይለዋወጡና አንደኛው የሰይጣን ሥርዓት ክፍል ሌላኛውን ያጠፋል፤ በዚህ ወቅት ሰይጣን እጁን አጣጥፎ ከማየት ውጪ የሚያደርገው ነገር አይኖርም።—ማቴ. 12:25, 26
በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዘር ጥቃት
8. ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ ምን ጥቃት ይሰነዝራል?
8 የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላም የአምላክ አገልጋዮች “ቅጥር” ሳይኖር “ያለ ሥጋት” መኖራቸውን ይቀጥላሉ። (ሕዝ. 38:11, 14) ይሖዋን ማምለካቸውን የሚቀጥሉትና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ መስለው የሚታዩት እነዚህ ሕዝቦች ምን ያጋጥማቸዋል? ጠላቶቻቸው የሆኑ “ብዙ ሕዝቦች” ባለ በሌለ ኃይላቸው ጥቃት የሚሰነዝሩባቸው ይመስላል። የአምላክ ቃል ስለዚህ ክንውን ሲገልጽ ጥቃቱን የሚፈጽመው ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ እንደሆነ አድርጎ ይገልጻል። (ሕዝቅኤል 38:2, 15, 16ን አንብብ።) ታዲያ ስለዚህ ጥቃት ስናስብ ምን ሊሰማን ይገባል?
9. (ሀ) ክርስቲያኖች በዋነኝነት የሚያሳስባቸው ምንድን ነው? (ለ) እምነታችንን ለማጠናከር በአሁኑ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
9 በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ሕዝ. 6:7፤ ባለማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።) ‘ይሖዋ ለእሱ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት ማዳን እንዳለበት የሚያውቅ’ አምላክ ለመሆኑ አንጠራጠርም፤ በመሆኑም የሕዝቅኤል ትንቢት ወሳኝ ክፍል የሆነው ይህ ትንቢት ፍጻሜውን የሚያገኝበትን ጊዜ በከፍተኛ ጉጉት እንጠባበቃለን። (2 ጴጥ. 2:9) እስከዚያው ድረስ ግን ምንም ዓይነት ፈተና ቢደርስብንም ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ጠብቀን ለመኖር እንድንችል አሁን ያገኘነውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመን እምነታችንን ማጠናከር እንፈልጋለን። ይሁንና እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? መጸለይ፣ የአምላክን ቃል ማጥናት እንዲሁም በዚያ ላይ ማሰላሰል ብሎም የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ማካፈል ይኖርብናል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋችንን ልክ እንደ “መልሕቅ” አጽንተን መያዝ እንችላለን።—ዕብ. 6:19፤ መዝ. 25:21
አስቀድመን ማወቃችን ከልክ በላይ እንድንጨነቅ ሊያደርገን አይገባም። እንዲያውም በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው የእኛ መዳን ሳይሆን የይሖዋ ስም መቀደስና የሉዓላዊነቱ መረጋገጥ ነው። ደግሞም ይሖዋ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ ከ60 ጊዜ በላይ ‘ይሖዋ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ’ የሚል አገላለጽ ተጠቅሟል። (ብሔራት ይሖዋ ማን እንደሆነ ለማወቅ ይገደዳሉ
10, 11. አርማጌዶን እንዲጀምር ምክንያት የሚሆነው ክንውን ምንድን ነው? በዚህ ወቅት ምን ነገር ይፈጸማል?
10 በይሖዋ አገልጋዮች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት ምድርን የሚያናውጥ ምን ነገር እንዲከሰት ምክንያት ይሆናል? ይሖዋ ኢየሱስንና በሰማይ የሚገኙ ሠራዊቱን በመጠቀም ለሕዝቡ ሲል ጣልቃ ይገባል። (ራእይ 19:11-16) በሌላ አባባል ‘ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ ማለትም አርማጌዶን ይጀምራል።—ራእይ 16:14, 16
11 ይሖዋ ይህን ጦርነት አስመልክቶ በሕዝቅኤል በኩል እንዲህ ብሏል፦ “በተራሮቼም ሁሉ በጎግ ላይ ሰይፍ እጠራለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእያንዳንዱም ሰው ሰይፍ በወንድሙ ላይ ያርፋል።” ከሰይጣን ጎን የተሰለፉት ሁሉ ስለሚደነግጡ የሚያደርጉት ይጠፋቸዋል፤ በዚህም የተነሳ በገዛ ወገናቸው ላይ መሣሪያ ያነሳሉ ማለትም እርስ በርስ ይጨራረሳሉ። ጥፋቱ በዚህ ብቻ አያበቃም፤ ይሖዋ “የሚያቃጥል ድኝ፣ በእርሱና በወታደሮቹ፣ ከእርሱም ጋር ባሉት ሕዝቦች ላይ አወርዳለሁ” ብሎ መናገሩ በመላው የሰይጣን ሥርዓት ላይ መጠነ ሰፊ ጥፋት እንደሚደርስ ይጠቁማል። (ሕዝ. 38:21, 22) ይህ መለኮታዊ እርምጃ ምን ውጤት ያስገኛል?
12. ብሔራት ምን ለማድረግ ይገደዳሉ?
12 ብሔራት ጥፋት የደረሰባቸው በይሖዋ ትእዛዝ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም እስራኤላውያንን በቀይ ባሕር ላይ ሲያሳድድ እንደነበረው የጥንቱ የግብፅ ሠራዊት ሁሉ የሰይጣን ኃይላትም ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ‘ይሖዋ እየተዋጋላቸው ነው!’ በማለት መጮኻቸው አይቀርም። (ዘፀ. 14:25) በእርግጥም ብሔራት ይሖዋ ማን እንደሆነ ለማወቅ ይገደዳሉ። (ሕዝቅኤል 38:23ን አንብብ።) ለመሆኑ እነዚህ ተከታታይ ክንውኖች ሊፈጸሙ የቀረው ጊዜ ምን ያህል ነው?
ሌላ የዓለም ኃያል መንግሥት አይነሳም
13. ዳንኤል ስለገለጸው የምስሉ አምስተኛ ክፍል ምን የምናውቀው ነገር አለ?
13 በዳንኤል መጽሐፍ ላይ የሚገኝ አንድ ትንቢት፣ የምንኖረው በየትኛው ጊዜ ላይ እንደሆነ ለማወቅ ያስችለናል። ዳንኤል ከተለያዩ ማዕድናት ስለተሠራና የሰው ቅርጽ ስላለው አንድ ምስል ተናግሯል። (ዳን.2:28, 31-33) ይህ ምስል የሚያመለክተው ጥንትም ሆነ በአሁኑ ጊዜ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩ በተከታታይ የተነሱ የዓለም ኃያላን መንግሥታትን ነው። እነዚህም ባቢሎን፣ ሜዶ ፋርስ፣ ግሪክ፣ ሮምና በዘመናችን ያለው የዓለም ኃያል መንግሥት ናቸው። የዳንኤልን ትንቢት ስንመረምር ይህ የመጨረሻው የዓለም ኃያል መንግሥት በምስሉ እግሮችና ጣቶች እንደተመሰለ እንረዳለን። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ ልዩ የሆነ ጥምረት ፈጥረው ነበር። በመሆኑም የምስሉ አምስተኛው ክፍል የአንግሎ አሜሪካ
የዓለም ኃያል መንግሥት ነው። የምስሉ የመጨረሻው ክፍል እግሮቹ ስለሆኑ ከዚያ በኋላ የሚነሳ ምንም ዓይነት የዓለም ኃያል መንግሥት እንደማይኖር ይጠቁማል። እግሮቹና ጣቶቹ የብረትና የሸክላ ውህድ መሆናቸው ደግሞ የአንግሎ አሜሪካ ኃያል መንግሥት ያለበትን የተዳከመ ሁኔታ ያመለክታል።14. የአርማጌዶን ጦርነት በሚፈነዳበት ወቅት የዓለም ኃያል መንግሥት የሚሆነው ማን ነው?
14 ስለ ምስሉ የሚገልጸው ትንቢት፣ የአምላክን መንግሥት የሚያመለክት አንድ ትልቅ ድንጋይ የይሖዋን ሉዓላዊነት ከሚወክለው ተራራ በ1914 ተፈንቅሎ እንደወጣ ይናገራል። ይህ ድንጋይ በአሁኑ ጊዜ ዒላማውን ማለትም የምስሉን እግሮች ለመምታት በመገስገስ ላይ ነው። በአርማጌዶን እግሮቹን ጨምሮ መላው ምስል ይደቅቃል። (ዳንኤል 2:44, 45ን አንብብ።) በመሆኑም የአርማጌዶን ጦርነት በሚፈነዳበት ወቅት የዓለም ኃያል መንግሥት የሚሆነው አንግሎ አሜሪካ ነው። ይህ ትንቢት ሙሉ በሙሉ ሲፈጸም መመልከት በጣም አስደሳች እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም! * ይሁንና ይሖዋ በሰይጣን ላይ ምን እርምጃ ይወስድበት ይሆን?
የአምላክ ቀንደኛ ጠላት ምን ይሆናል?
15. ከአርማጌዶን በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ ምን ይሆናሉ?
15 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሰይጣን ዓይኑ እያየ በምድር ላይ ያለው ድርጅቱ በሙሉ ሙልጭ ብሎ ይጠፋል። ከዚያም ተረኛው ራሱ ሰይጣን ይሆናል። ቀጥሎ የሚከናወነውን ነገር ሐዋርያው ዮሐንስ ገልጾታል። (ራእይ 20:1-3ን አንብብ።) “የጥልቁን ቁልፍ” የያዘው መልአክ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣንንና አጋንንቱን ይዞ ወደ ጥልቁ ይወረውራቸዋል፤ በዚያም ለአንድ ሺህ ዓመት ይቆያሉ። (ሉቃስ 8:30, 31፤ 1 ዮሐ. 3:8) ይህ ክንውን የእባቡ ራስ የሚቀጠቀጥበት የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው። *—ዘፍ. 3:15
16. ሰይጣን ወደ ጥልቁ ይወረወራል ሲባል ምን ማለት ነው?
16 ሰይጣንና አጋንንቱ የተወረወሩበት “ጥልቁ” የተባለው ቦታ ምንድን ነው? ‘ጥልቅ’ ተብሎ የተተረጎመው አቢሶስ የሚለው የግሪክኛ ቃል “እጅግ በጣም ጥልቅ የሆነ” የሚል ትርጉም አለው። በተጨማሪም ቃሉ “ይህ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይችልና መቋጫ የሌለው” እንዲሁም “መጨረሻ የሌለው ባዶ ቦታ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። በመሆኑም ይህ ቦታ ከይሖዋና ‘የጥልቁን ቁልፍ በእጁ ከያዘው መልአክ’ በስተቀር ማንም የማይደርስበት ስፍራ ነው። በዚያም ሰይጣን የሞተ ያህል ስለሚሆን ምንም ነገር ማከናወን አይችልም፤ በመሆኑም ‘ብሔራትን ማሳሳት’ አይችልም። በእርግጥም ‘የሚያገሳው አንበሳ’ ጸጥ እንዲል ይደረጋል!—1 ጴጥ. 5:8
ሰላም የሰፈነበት ዘመን ከመምጣቱ በፊት የሚፈጸሙ ክንውኖች
17, 18. (ሀ) እስካሁን የተወያየንባቸው ገና ያልታዩ ክንውኖች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ከእነዚህ ክስተቶች በኋላ ምን ዓይነት አስደሳች ጊዜ ይመጣል?
17 ወሳኝ የሆኑና ምድርን የሚያናውጡ ክንውኖች ከፊታችን ይጠብቁናል። ሁላችንም “ሰላምና ደኅንነት ሆነ!” የሚለው አዋጅ የሚነገረው እንዴት እንደሆነ ለማየት እንጓጓለን። ከዚያም ታላቂቱ ባቢሎን ስትጠፋ፣ የማጎጉ ጎግ ጥቃት ሲሰነዝር፣ የአርማጌዶን ጦርነት ሲካሄድ እንዲሁም ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ጥልቁ ሲወረወሩ እንመለከታለን። እነዚህ ነገሮች ከተከሰቱና ክፋት ሁሉ ከተወገደ በኋላ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ይኸውም “ታላቅ ሰላም” የምናገኝበት የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ይጀምራል።—መዝ. 37:10, 11
18 እስካሁን ከተወያየንባቸው አምስት ክስተቶች በተጨማሪ ‘ዓይናችን ሊያተኩርባቸው’ የሚገቡ ሌሎች ‘የማይታዩ ነገሮችም’ አሉ። እነዚህን ክንውኖች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታቸዋለን።
^ አን.6 ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 251-258 ተመልከት።
^ አን.14 በዳንኤል 2:44 ላይ የሚገኘው “እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል” የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው በምስሉ የተለያዩ ክፍሎች የተመሰሉትን መንግሥታት ወይም የዓለም ኃያላን ነው። ይሁንና ስለ ተመሳሳይ ጉዳይ የሚናገር ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት፣ ‘በታላቁ የአምላክ ቀን’ ላይ ‘የዓለም ነገሥታት ሁሉ’ በይሖዋ ላይ እንደሚነሱ ይገልጻል። (ራእይ 16:14፤ 19:19-21) በመሆኑም በአርማጌዶን የሚጠፉት በምስሉ ላይ የተገለጹት መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ሰብዓዊ መንግሥታት ናቸው።
^ አን.15 የእባቡ ራስ የሚቀጠቀጥበት የመጨረሻው ምዕራፍ የሚፈጸመው በሺህ ዓመቱ ማብቂያ ላይ ሰይጣንና አጋንንቱ “ወደ እሳቱና ወደ ድኙ ሐይቅ” ሲወረወሩ ነው።—ራእይ 20:7-10፤ ማቴ. 25:41