በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ከሕፃናት አፍ’ የተገኘ ማበረታቻ

‘ከሕፃናት አፍ’ የተገኘ ማበረታቻ

በታጋንሮግ፣ ሩሲያ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት እንዲፈርስ፣ የመንግሥት አዳራሻቸው እንዲወረስ እና 34 የሚያህሉ ጽሑፎቻችን ጽንፈኛ ተብለው እንዲፈረጁ በፍርድ ቤት ተበይኖ ነበር፤ ታኅሣሥ 2009 የሩሲያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይህ ብይን እንዲጸና ውሳኔ አስተላልፏል። አስደንጋጭ ስለሆነው ስለዚህ የፍርድ ውሳኔ የሚገልጽ ዘገባ በይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ድረ ገጽ ላይ ወጥቶ ነበር፤ ዘገባው ውሳኔው ተጽዕኖ ያሳደረባቸውን ወንድሞችና የሕፃናት ልጆቻቸውን ፎቶግራፍም ይዟል።

በአውስትራሊያ የሚገኙ ልጆች

ከጥቂት ወራት በኋላ በኩዊንስላንድ፣ አውስትራሊያ የሚገኝ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የሰማ አንድ ቤተሰብ በሩሲያ ላለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የተለያዩ ነገሮችን የያዘ እሽግና ደብዳቤ ላከ። ደብዳቤው እንዲህ ይላል፦ “ውድ ወንድሞች፣ ኮዲ እና ሌሪሳ የተባሉት ልጆቻችን በሩሲያ ያሉ ወንድሞች መከራ ሲደርስባቸው ባሳዩት እምነት ልባቸው በጣም ተነክቷል። በመሆኑም ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ይሖዋን በታማኝነት የሚያመልኩ ሌሎች ልጆችም በታጋንሮግ ከተማ ስላሉት ልጆች እንደሚያስቡ ለማሳየት ካርዶችና ደብዳቤዎች ልከውላቸዋል፤ ከዚህም ሌላ በዚህ ከተማ ላሉ ልጆች የሚሰጡ የተለያዩ ስጦታዎችን የያዘ እሽግ ልከናል። ኮዲ እና ሌሪሳ ሞቅ ያለ ፍቅራዊ ሰላምታቸውን ልከዋል።”

በታጋንሮግ የሚገኙት ልጆች ስጦታው ሲደርሳቸው በምላሹ በአውስትራሊያ ለሚገኘው ቤተሰብ ሥዕል ስለው ከምስጋና ደብዳቤ ጋር ላኩ። በሩሲያ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግል አንድ የይሖዋ ምሥክር ‘ከሕፃናት አፍ’ የተገኘው ይህ ማበረታቻ ስለነካው ለኮዲ እና ለሌሪሳ እንዲህ በማለት ጻፈላቸው፦ “ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች ባልሠሩት ጥፋት መቀጣታቸው ምን ያህል እንደሚያሳዝን መገመት ትችላላችሁ። በታጋንሮግ የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሠሩት ጥፋት ባይኖርም የመንግሥት አዳራሻቸው ተወስዶባቸዋል። ይህ ደግሞ በጣም አሳዝኗቸዋል። በመሆኑም በሌላ የዓለም ክፍል ስለ እነሱ የሚያስብ ሰው እንዳለ ማወቃቸው በጣም ያበረታታቸዋል። ላሳያችሁት ፍቅርና የልግስና መንፈስ እናመሰግናለን!”—መዝ. 8:2

በአውስትራሊያ ከሚገኙ ልጆች ስጦታ ያገኙት በሩሲያ ያሉ ልጆች

በእርግጥም ዓለም አቀፋዊ የሆነ የወንድማማች ማኅበር አለን፤ እንዲሁም እርስ በርስ ያለን ፍቅር በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን መከራዎችና ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሙሉ መቋቋም እንድንችል ይረዳናል። የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎች ጥላቻን የሚያስፋፉ መሆን አለመሆናቸው ፍርድ ቤቶችን እያወዛገበ ቢሆንም ልጆቻችን የብሔር እና የባሕል ልዩነት ሳይገድባቸው አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን አሳቢነት አሳይተዋል፤ ይህም “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” በማለት ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ትክክል እንደሆነ ያረጋግጣል።—ዮሐ. 13:35