በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙንን መከራዎች በድፍረት መቋቋም

በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙንን መከራዎች በድፍረት መቋቋም

“አምላካችን መጠጊያችንና ኀይላችን፣ በሚደርስብን መከራ ሁሉ የቅርብ ረዳታችን ነው።”—መዝ. 46:1

1, 2. ብዙ ሰዎች ምን ዓይነት መከራዎች አጋጥመዋቸዋል? ይሁንና የአምላክ አገልጋዮች ፍላጎት ምንድን ነው?

የምንኖረው መከራ በሞላበት ዘመን ውስጥ ነው። ምድር በርካታ አደጋዎች ተፈራርቀውባታል። የምድር መናወጥ፣ ሱናሚ፣ እሳት፣ ጎርፍ፣ እሳተ ገሞራና የተለያዩ ዓይነት አውሎ ነፋሶች በሰው ልጆች ላይ ከባድ ጉዳት አድርሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ በቤተሰብ መካከል የሚከሰቱ ችግሮችና ግለሰቦች የሚያጋጥሟቸው ግራ የሚያጋቡ ሁኔታዎች ፍርሃትና ሐዘን አስከትለዋል። ሁላችንም “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” እንደሚያጋጥሙን ምንም ጥያቄ የለውም።—መክ. 9:11 NW

2 በጥቅሉ ሲታይ የአምላክ አገልጋዮች እንዲህ ያሉ አስጨናቂ ሁኔታዎችን በሚገባ ተቋቁመዋል። ይሁንና የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረበ ሲመጣ ሊያጋጥሙን የሚችሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመወጣት ከወዲሁ ዝግጁ መሆን እንፈልጋለን። በእነዚህ ፈታኝ ሁኔታዎች ሳንዋጥ ሁኔታዎቹን ተቋቁመን ማለፍ የምንችለው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ የሚደርሱብንን መከራዎች በድፍረት ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?

ድፍረት ካሳዩ ሰዎች መማር

3. በ⁠ሮም 15:4 ላይ እንደተገለጸው፣ የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ማጽናኛ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

3 በአሁኑ ወቅት ከምንጊዜውም በበለጠ በብዙ ሰዎች ላይ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እየደረሱ ቢሆንም መከራ ለሰው ልጅ አዲስ ነገር አይደለም። ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች በሕይወታቸው ውስጥ ያጋጠሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በድፍረት ተወጥተዋል፤ እስቲ ከእነሱ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እንመልከት።—ሮም 15:4

4. ዳዊት ምን ዓይነት መከራዎችን ችሎ አሳልፏል? እንዲጸና የረዳውስ ምንድን ነው?

4 ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ዳዊት በርካታ ችግሮች የደረሱበት ሲሆን በቁጣ የተሞላ ንጉሥ ስደት አድርሶበታል፣ ጠላቶቹ ጥቃት ሰንዝረውበታል፣ ሚስቶቹ ተማርከው ተወስደዋል፣ ለእሱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች አሲረውበታል እንዲሁም የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች አጋጥመውታል። (1 ሳሙ. 18:8, 9፤ 30:1-5፤ 2 ሳሙ. 17:1-3፤ 24:15, 17፤ መዝ. 38:4-8) ስለ ዳዊት ሕይወት የሚዘግቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እነዚህ መከራዎች ያደረሱበትን ሥቃይ በግልጽ ያሳያሉ። ይሁንና መንፈሳዊነቱን እንዲያጣ አላደረጉትም። ዳዊት በሙሉ እምነት “እግዚአብሔር ለሕይወቴ ዐምባዋ ነው፤ ማንን እፈራለሁ?” ብሏል።—መዝ. 27:1፤ መዝሙር 27:5, 10ን አንብብ።

5. አብርሃምና ሣራ አስቸጋሪውን ሕይወት እንዲቋቋሙ የረዳቸው ምንድን ነው?

5 አብርሃምና ሣራ አብዛኛውን የሕይወት ዘመናቸውን ያሳለፉት በባዕድ አገር መጻተኛ ሆነው በድንኳን ውስጥ በመኖር ነበር። ሕይወታቸው ሁልጊዜ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ይሁንና ያጋጠማቸውን የረሃብ ዘመንና በዙሪያቸው የነበሩት ብሔራት የሚሰነዝሩባቸውን ጥቃት የመሳሰሉ ችግሮችን በቆራጥነት ተቋቁመዋል። (ዘፍ. 12:10፤ 14:14-16) ይህን ማድረግ የቻሉት እንዴት ነበር? የአምላክ ቃል፣ አብርሃም “አምላክ የገነባትንና የሠራትን እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ ይጠባበቅ” እንደነበር ይነግረናል። (ዕብ. 11:8-10) አብርሃምና ሣራ በዙሪያቸው ያለው ዓለም መንፈሳቸውን እንዲያዳክምባቸው ባለመፍቀድ ትኩረታቸውን ወደፊት በሚፈጸሙት ነገሮች ላይ አድርገዋል።

6. የኢዮብን አርዓያ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

6 ኢዮብ ከባድ ችግሮች አጋጥመውታል። መላ ሕይወቱ ምስቅልቅሉ የወጣ በመሰለበት ወቅት ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል አስብ። (ኢዮብ 3:3, 11) ይህ ሁሉ የደረሰበት ለምን እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አለመረዳቱ ችግሩን የከፋ አድርጎታል። ያም ሆኖ ተስፋ አልቆረጠም። ጨዋነቱን ወይም ንጹሕ አቋሙን አላጎደፈም፤ እንዲሁም በአምላክ ላይ ያለውን እምነት ጠብቋል። (ኢዮብ 27:5ን አንብብ።) ልንከተለው የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!

7. ጳውሎስ አምላክን ሲያገለግል ምን ዓይነት ሁኔታዎች አጋጥመውታል? ሆኖም በድፍረት እንዲቀጥል የረዳው የትኛውን እውነታ መገንዘቡ ነበር?

7 የሐዋርያው ጳውሎስንም ምሳሌ እንመልከት። ‘በከተማ፣ በምድረ በዳና በባሕር ላይ አደጋ’ አጋጥሞታል። ‘ተርቤያለሁ፣ ተጠምቻለሁ፣ በብርድና በራቁትነት ተቆራምጃለሁ’ ብሎ ተናግሯል። ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ ‘ሌሊትና ቀን በጥልቅ ባሕር ውስጥ’ እንዳሳለፈ ገልጿል፤ ይህ ሁኔታ ያጋጠመው ከደረሰበት የመርከብ መሰበር አደጋዎች በአንዱ ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮ. 11:23-27) ይህ ሁሉ ቢደርስበትም አምላክን በማገልገሉ ምክንያት ሞት አፋፍ ደርሶ ከተረፈ በኋላ የነበረውን አመለካከት እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ይህም በራሳችን ሳይሆን ሙታንን በሚያስነሳው አምላክ እንድንታመን ነው። እንዲህ ካለ ለሞት የሚዳርግ ሁኔታ አድኖናል፤ ደግሞም ያድነናል።” (2 ቆሮ. 1:8-10) ብዙ ሰዎች የጳውሎስን ያህል በርካታ አስከፊ ሁኔታዎች አላጋጠሟቸውም። ይሁንና አብዛኞቻችን የእሱን ስሜት መረዳት እንችላለን፤ ደግሞም ከተወው የድፍረት ምሳሌ ማጽናኛ ማግኘት እንችላለን።

መጥፎ ሁኔታዎች ስሜታችሁን እንዲቆጣጠሩት አትፍቀዱ

8. በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሙን ችግሮች ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን የሚችሉት እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

8 በአደጋ፣ በፈታኝ ሁኔታና በልዩ ልዩ ጫናዎች በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸው ነገሮች ከአቅማቸው በላይ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። አንዳንድ ክርስቲያኖች እንኳ እንደዚህ ተሰምቷቸዋል። በአውስትራሊያ ከባለቤቷ ጋር በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በደስታ ስታገለግል የቆየችው ላኒ * የጡት ካንሰር እንደያዛት በምርመራ በተረጋገጠ ጊዜ ክፉኛ ከመደናገጧም በላይ መብረቅ የመታት ያህል ሆኖ ተሰምቷት ነበር። “ሕክምናው ለከባድ ሕመም ዳረገኝ፤ ለራሴ የነበረኝንም ግምት ሙሉ በሙሉ አጣሁ” ብላለች። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ በዚህ ሁሉ ላይ የአከርካሪ አጥንት ቀዶ ሕክምና ያደረገውን ባለቤቷን መንከባከብ ነበረባት። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ምን ማድረግ እንችላለን?

9, 10. (ሀ) ሰይጣን ምን እንዲያደርግ መፍቀድ አይኖርብንም? (ለ) በየሐዋርያት ሥራ 14:22 ላይ የተገለጸው እውነታ ሲያጋጥመን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

9 ሰይጣን በሚደርሱብን መከራዎች ተጠቅሞ እምነታችንን ለማዳከም እንደሚጥር ማስታወስ ይኖርብናል። ይሁን እንጂ በዚህ መንገድ ደስታ እንዲያሳጣን መፍቀድ አይኖርብንም። ምሳሌ 24:10 “በመከራ ጊዜ ፈራ ተባ ካልህ፣ ዐቅምህ ምንኛ ደካማ ነው” ይላል። ቀደም ሲል እንደተገለጹት ባሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላችን የተለያዩ መከራዎችን በድፍረት እንድንጋፈጥ ይረዳናል።

10 በተጨማሪም ሁሉንም ዓይነት ችግሮች ማስወገድ እንደማንችል ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። እንዲያውም እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሊደርሱብን እንደሚችሉ መጠበቅ አለብን። (2 ጢሞ. 3:12) የሐዋርያት ሥራ 14:22 “ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ውስጥ ማለፍ አለብን” ይላል። መከራ ሲያጋጥምህ በሐዘን ከመዋጥ ይልቅ አምላክ አንተን ለመርዳት ባለው ችሎታ ላይ በመታመን ያጋጠመህን መከራ ድፍረት ለማሳየት እንደሚያስችል አጋጣሚ አድርገህ ለምን አትመልከተውም?

11. በሕይወታችን ውስጥ በሚያጋጥሙን መከራዎች እንዳንዋጥ ምን ማድረግ እንችላለን?

11 አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮራችን አስፈላጊ ነው። የአምላክ ቃል “ደስተኛ ልብ ፊትን ያፈካል፤ የልብ ሐዘን ግን መንፈስን ይሰብራል” ይላል። (ምሳሌ 15:13) የሕክምና ተመራማሪዎች አዎንታዊ አስተሳሰብ ጤናን የማሻሻል አቅም እንዳለው ከተገነዘቡ ቆይተዋል። ብዙ ታካሚዎች መድኃኒትነት የሌለው ኪኒን ሲሰጣቸው ኪኒኑ እንደሚያሽላቸው ስላመኑ ብቻ ከሕመማቸው እንዳገገሙ ተሰምቷቸዋል። በአንጻሩ ግን አንድ ሰው የሚወስደው ኪኒን የጤና ችግር እንደሚያመጣበት አድርጎ ስላሰበ ብቻ ሕመሙን እንዳባባሰበት ሊሰማው ይችላል። ልንለውጣቸው የማንችላቸውን ነገሮች አዘውትረን ማሰባችን ራሳችንን ከመጉዳት በቀር ምንም ጥቅም አያስገኝልንም። ደስ የሚለው ነገር ይሖዋ “የማይጠቅም ኪኒን” አይሰጠንም። ከዚህ ይልቅ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ እንኳ በቃሉ ውስጥ በሚገኝ ማበረታቻ፣ ከጎናችን በሚቆሙት ወንድሞቻችንና መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠን ብርታት አማካኝነት እውነተኛ እርዳታ እንድናገኝ ያደርጋል። በእነዚህ ነገሮች ላይ ማተኮራችን መንፈሳችንን ያነቃቃዋል። ባጋጠሙን መጥፎ ሁኔታዎች ከመብሰልሰል ይልቅ እያንዳንዱን ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ተግባራዊ እርምጃ መውሰድና ባሉን ጥሩ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል።—ምሳሌ 17:22

12, 13. (ሀ) የአምላክ አገልጋዮች የተፈጥሮ አደጋዎች ያስከተሉትን ጉዳት እንዲቋቋሙ የረዳቸው ምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ለ) የተፈጥሮ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት በሰው ሕይወት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ በግልጽ የሚታየው እንዴት ነው?

12 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አንዳንድ አገሮች ከባድ አደጋዎች አጋጥመዋቸዋል። በእነዚህ አገሮች የሚኖሩ ብዙ ወንድሞች በአስደናቂ ሁኔታ ችግሮችን ተቋቁመዋል። እንዲህ ሲባል ግን የደረሰባቸው ነገር ቀላል ነው ማለት አይደለም። በ2010 መጀመሪያ ላይ በቺሊ የደረሰው ከባድ የመሬት መናወጥና ሱናሚ የበርካታ ወንድሞቻችንን ቤትና ንብረት ያወደመ ሲሆን አንዳንዶቹ መተዳደሪያቸውን ጭምር አጥተዋል። ወንድሞች ይህ ሁሉ ቢደርስባቸውም መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸውን አላቋረጡም። ቤቱ ሙሉ በሙሉ የወደመበት ሳሙኤል የተባለ ወንድም እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “በእነዚህ አስከፊ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ እኔና ባለቤቴ ስብሰባም ሆነ አገልግሎት አቋርጠን አናውቅም። እንዲህ ማድረጋችን ተስፋ እንዳንቆርጥ እንደረዳን አምናለሁ።” እነሱም ሆኑ ሌሎች በርካታ ወንድሞች የደረሰባቸውን አደጋ ወደኋላ በመተው በይሖዋ አገልግሎት መካፈላቸውን ቀጥለዋል።

13 በመስከረም 2009 ላይ በፊሊፒንስ በምትገኘው በማኒላ የወረደው ኃይለኛ ዝናብ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የከተማዋን ክፍል በጎርፍ አጥለቅልቆት ነበር። አብዛኛውን ሀብቱን ያጣ አንድ ባለጸጋ “ጎርፉ ሁላችንንም እኩል አድርጎናል፤ ሀብታሞችም ሆኑ ድሃዎች ልዩ ልዩ ችግሮችና መከራዎች ቀምሰዋል” ብሏል። ይህ ሁኔታ ኢየሱስ እንደሚከተለው ሲል የሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር ያስታውሰናል፦ “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ሰብሮ ገብቶ ሊሰርቀው በማይችልበት በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ።” (ማቴ. 6:20) በቅጽበት ሊጠፉ በሚችሉ ቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ሕይወት መምራት ብዙውን ጊዜ ለብስጭት ይዳርጋል። ሕይወታችን ከይሖዋ ጋር በመሠረትነው ዝምድና ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረግ ምንኛ ጥበብ ነው! እንዲህ ካደረግን ይህን ዝምድና ሊያበላሽብን የሚችል ምንም ነገር አይኖርም!—ዕብራውያን 13:5, 6ን አንብብ።

ደፋር እንድንሆን የሚያስችሉን ምክንያቶች

14. ድፍረት እንድናሳይ የሚያስችሉን ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

14 ኢየሱስ በሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚኖሩ የተናገረ ቢሆንም “አትሸበሩ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ሉቃስ 21:9) ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስና የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ስለሚደግፉን ደፋር የምንሆንበት አጥጋቢ ምክንያት አለን። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “አምላክ የኃይል፣ የፍቅርና የጤናማ አእምሮ መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንም” በማለት አበረታቶታል።—2 ጢሞ. 1:7

15. የአምላክ አገልጋዮች የነበራቸውን ጽኑ እምነት የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ። እኛም ተመሳሳይ ድፍረት ሊኖረን የሚችለው እንዴት እንደሆነ ግለጽ።

15 የአምላክ አገልጋዮች የነበራቸውን ጽኑ እምነት የሚያንጸባርቁ አንዳንድ መግለጫዎች እንመልከት። ዳዊት “እግዚአብሔር ብርታቴና ጋሻዬ ነው፤ ልቤ በእርሱ ይታመናል፤ እርሱም አግዞኛል፤ ልቤ ሐሤት አደረገ” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 28:7) ጳውሎስ ደግሞ “በወደደን በእሱ አማካኝነት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ በድል አድራጊነት እንወጣለን” በማለት ጽኑ እምነቱን ገልጿል። (ሮም 8:37) በተመሳሳይም ኢየሱስ አደጋ ተጋርጦበት በነበረ ጊዜ ከአባቱ ጋር ጠንካራ ዝምድና ያለው መሆኑን ለአድማጮቹ በግልጽ ለማስገንዘብ ሲል “አብ ከእኔ ጋር ስላለ ብቻዬን አይደለሁም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 16:32) እነዚህ መግለጫዎች ምን ያሳያሉ? ሁሉም በይሖዋ ላይ ጽኑ እምነት እንደነበራቸው እንድንገነዘብ ያስችሉናል። እኛም በአምላክ ላይ እንዲህ ያለ እምነት ማዳበራችን በዛሬው ጊዜ የሚደርስብንን ማንኛውንም ዓይነት መከራ መጋፈጥ እንድንችል ድፍረት ይሰጠናል።—መዝሙር 46:1-3ን አንብብ።

ደፋር ሆናችሁ እንድትኖሩ ከሚያስችሏችሁ ዝግጅቶች ተጠቀሙ

16. የአምላክን ቃል ማጥናታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

16 ክርስቲያናዊ ድፍረት ሲባል በራስ መተማመን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክን በማወቅና በእሱ በመታመን የምናገኘው ነገር ነው። በጽሑፍ የሰፈረውን ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ይህን ማድረግ እንችላለን። በመንፈስ ጭንቀት የምትሠቃይ አንዲት እህት “በጣም አጽናኝ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ደግሜ ደጋግሜ አነብባለሁ” በማለት የረዳትን ነገር ገልጻለች። ለቤተሰብ አምልኮ ቋሚ ጊዜ እንድንመድብ የተሰጠንን መመሪያ ተግባራዊ አድርገናል? እነዚህን ምክሮች ሥራ ላይ ማዋላችን “ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ” ሲል የተናገረው መዝሙራዊ የነበረው ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል።—መዝ. 119:97

17. (ሀ) ደፋር ሆነን መኖር እንድንችል በየትኛው ዝግጅት መጠቀም እንችላለን? (ለ) በጽሑፍ ላይ ከወጣ የሕይወት ታሪክ ያገኘኸውን ጥቅም ተናገር።

17 በተጨማሪም በይሖዋ ላይ ያለንን የመተማመን ስሜት የሚያጠናክር ትምህርት የያዙ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች አሉን። በርካታ ወንድሞች በመጽሔቶቻችን ላይ የሚወጡ የሕይወት ታሪኮችን ማንበብ በጣም ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። በእስያ የምትኖር ባይፖላር ሙድ ዲስኦርደር የተባለ የመንፈስ ጭንቀት ያለባት አንዲት እህት የአንድን ወንድም የሕይወት ታሪክ ማንበቧ አጽናንቷት ነበር፤ ይህ ወንድም ቀደም ሲል ሚስዮናዊ የነበረ ሲሆን እንዲህ ያለ የጤና እክል ቢያጋጥመውም እንኳ ችግሩን በጥሩ ሁኔታ መቋቋም ችሏል። “ተሞክሮው ችግሬን መገንዘብ እንድችልና ብሩህ ተስፋ እንዲኖረኝ ረድቶኛል” ስትል ጽፋለች።

መከራ ሲያጋጥማችሁ ይሖዋ ባደረጋቸው ዝግጅቶች ተጠቀሙ

18. አዘውትረን መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

18 ጸሎት በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ሥር ብንሆን ሊረዳን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ ዝግጅት ያለውን ጠቀሜታ ጎላ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።” (ፊልጵ. 4:6, 7) መከራ በሚያጋጥመን ጊዜ ብርታት ለማግኘት በዚህ የእርዳታ ዝግጅት በተሟላ ሁኔታ ለመጠቀም ጥረት እናደርጋለን? ለረጅም ጊዜ በመንፈስ ጭንቀት ሲሠቃይ የቆየ በብሪታንያ የሚኖር አሊክስ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋን በጸሎት ማነጋገሬና ቃሉን በማንበብ እሱን ማዳመጤ ችግሩን ተቋቁሜ እንድኖር አስችሎኛል።”

19. በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትን በተመለከተ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

19 እርዳታ የምናገኝበት ሌላው ወሳኝ ዝግጅት የጉባኤ ስብሰባ ነው። አንድ መዝሙራዊ “ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባዮች ትናፍቃለች፤ እጅግም ትጓጓለታለች” በማለት ጽፏል። (መዝ. 84:2) እኛስ እንዲህ ይሰማናል? ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ላኒ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ያላትን አመለካከት እንዲህ ስትል ገልጻለች፦ “በስብሰባዎች ላይ መገኘት ለምርጫ የተተወ ነገር አይደለም። ይሖዋ እንዲረዳኝ ከፈለግኩ የግድ ስብሰባ ላይ መገኘት እንደሚያስፈልገኝ አውቃለሁ።”

20. በስብከቱ ሥራ መካፈል የሚረዳን እንዴት ነው?

20 የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ በትጋት በመሳተፍም ማበረታቻ ማግኘት እንችላለን። (1 ጢሞ. 4:16) በርካታ ችግሮች የደረሱባት በአውስትራሊያ የምትገኝ አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “በወቅቱ በስብከቱ ሥራ የመካፈል ፍላጎቴ ጠፍቶ ነበር፤ ሆኖም አንድ ሽማግሌ አብሬው አገልግሎት እንድወጣ ጋበዘኝ። እኔም አብሬው ሄድኩ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ እየረዳኝ እንዳለ ተሰምቶኛል፤ አገልግሎት በወጣሁ ቁጥር ከፍተኛ ደስታ አገኝ ነበር።” (ምሳሌ 16:20) ብዙዎች፣ በይሖዋ ላይ እምነት እንዲገነቡ ሌሎችን በመርዳታቸው የራሳቸው እምነት እንደተጠናከረ ይናገራሉ። እንዲህ ማድረጋቸው አእምሯቸው በራሳቸው ችግሮች ከመዋጥ ይልቅ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አስችሏቸዋል።—ፊልጵ. 1:10, 11

21. የሚያጋጥሙንን ችግሮች በተመለከተ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

21 ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የሚደርሱብንን መከራዎች በድፍረት መቋቋም እንድንችል በርካታ ዝግጅቶች አድርጎልናል። በእነዚህ ዝግጅቶች ሁሉ በመጠቀም እንዲሁም ደፋር የአምላክ አገልጋዮች በተዉት ግሩም ምሳሌ ላይ በማሰላሰልና አርዓያቸውን በመከተል ችግሮችን በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንደምንችል እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ሲመጣ ብዙ ችግሮች ሊያጋጥሙን ቢችሉም ጳውሎስ “ተገፍትረን ብንወድቅም አንጠፋም፤ . . . ተስፋ አንቆርጥም” ሲል የገለጸውን ዓይነት ስሜት እንጋራለን። (2 ቆሮ. 4:9, 16) በይሖዋ እርዳታ በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙንን መከራዎች በድፍረት መቋቋም እንችላለን።—2 ቆሮንቶስ 4:17, 18ን አንብብ።

^ አን.8 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።