በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ይቅር ባይነት ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

የይሖዋ ይቅር ባይነት ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

‘ይሖዋ ሩኅሩኅ፣ ቸር፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል አምላክ ነው።’—ዘፀ. 34:6, 7

1, 2. (ሀ) ይሖዋ ለእስራኤል ብሔር ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ አሳይቷል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኛውን ጥያቄ እንመረምራለን?

በነህምያ ዘመን የነበሩት አንዳንድ ሌዋውያን በሕዝብ ፊት ባቀረቡት ጸሎት ላይ አባቶቻቸው በተደጋጋሚ የይሖዋን ትእዛዛት ‘ለመስማት እንዳልፈለጉ’ ተናግረዋል። ይሁንና ይሖዋ ‘ይቅር ባይ፣ ቸርና ርኀሩኀ፣ ለቍጣ የዘገየና ምሕረቱ የበዛ አምላክ’ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል። ይሖዋ፣ በነህምያ ዘመን ከምርኮ ተመልሰው ለነበሩት አይሁዳውያን ጸጋውን ወይም ምሕረቱን ማሳየቱን ቀጥሎ ነበር።—ነህ. 9:16, 17

2 እያንዳንዳችን ‘የይሖዋ ይቅር ባይነት ለእኔ ምን ትርጉም አለው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። የዚህን በጣም አስፈላጊ ጥያቄ መልስ ለማወቅ ይሖዋ፣ ከእሱ ይቅር ባይነት ጥቅም ካገኙ ሁለት ነገሥታት ማለትም ከዳዊትና ከምናሴ ጋር የነበረውን ግንኙነት እንመርምር።

ዳዊት የፈጸማቸው ከባድ ኃጢአቶች

3-5. ዳዊት ከባድ ኃጢአት ውስጥ የተዘፈቀው እንዴት ነው?

3 ዳዊት ፈሪሃ አምላክ የነበረው ሰው ቢሆንም ከባድ ኃጢአቶችን ፈጽሟል። ከፈጸማቸው ኃጢአቶች መካከል ሁለቱ ኦሪዮንና ቤርሳቤህ ከተባሉ ባልና ሚስት ጋር የተያያዙ ናቸው። ይህ ድርጊት በዳዊትም ሆነ በእነዚህ ባልና ሚስት ላይ ከባድ ጉዳት አስከትሏል። ያም ሆኖ አምላክ ለዳዊት እርማት የሰጠበት መንገድ ስለ ይሖዋ ይቅር ባይነት ብዙ ነገሮች ያስተምረናል። እስቲ ምን እንደተከሰተ እንመልከት።

4 ዳዊት የአሞናውያንን ዋና ከተማ ረባትን ለመክበብ የእስራኤልን ሠራዊት ላከ። ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ያለችው ይህች ከተማ ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ 80 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ትገኛለች። ሠራዊቱ ለጦርነት በወጣበት ወቅት ዳዊት በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ሆኖ ባለትዳር የሆነችው ቤርሳቤህ ገላዋን ስትታጠብ ተመለከተ። በወቅቱ ባለቤቷ ወደ ሩቅ ቦታ ሄዶ ነበር። ዳዊት ቤርሳቤህን በትኩረት በመመልከቱ ስሜቱ ስለተነሳሳ ወደ ቤተ መንግሥቱ አስመጥቶ ከእሷ ጋር ምንዝር ፈጸመ።—2 ሳሙ. 11:1-4

5 ዳዊት፣ ቤርሳቤህ ማርገዟን ሲያውቅ ባለቤቷ ኦርዮን ከሚስቱ ጋር የፆታ ግንኙነት ይፈጽማል ብሎ በማሰብ ወደ ኢየሩሳሌም አስመጣው። ይሁንና ኦርዮን፣ ዳዊት በጣም ቢጎተጉተውም ወደ ቤት እንኳ ለመግባት ፈቃደኛ አልነበረም። በመሆኑም ንጉሡ፣ ኦርዮንን “ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው” ከዚያም አብረውት ያሉት ወታደሮች ‘ትተውት ይሽሹ’ የሚል ደብዳቤ ለሠራዊቱ አዛዥ በሚስጥር ጻፈለት። ዳዊት እንዳቀደው ኦርዮን በውጊያው ላይ በቀላሉ ተገደለ። (2 ሳሙ. 11:12-17) ንጉሡ ምንዝር መፈጸሙ ሳያንስ ንጹሕ ሰው በማስገደል የከፋ ኃጢአት ሠራ።

ዳዊት ያደረገው የአመለካከት ለውጥ

6. አምላክ ዳዊት ኃጢአት ሲሠራ ምን እርምጃ ወሰደ? ይህስ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

6 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ የተከናወነውን ነገር በሙሉ ተመልክቷል፤ ያመለጠው አንድም ነገር አልነበረም። (ምሳሌ 15:3) ንጉሡ ከጊዜ በኋላ ቤርሳቤህን ያገባት ቢሆንም “ዳዊት የሠራው ሥራ እግዚአብሔርን አላስደሰተውም ነበር።” (2 ሳሙ. 11:27) ዳዊት እንዲህ ዓይነት ከባድ ኃጢአት ሲፈጽም አምላክ ምን እርምጃ ወሰደ? ነቢዩ ናታንን ወደ ዳዊት ላከው። ይሖዋ ይቅር ባይ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ምሕረት ማሳየት የሚችልበትን መንገድ እየፈለገ ነበር። ይሖዋ እንዲህ ማድረጉ በጣም የሚያበረታታ አይደለም? ይሖዋ፣ ዳዊት ኃጢአቱን እንዲናዘዝ ከማስገደድ ይልቅ የሠራው ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንዲገነዘብ የሚያደርግ ታሪክ በነቢዩ ናታን በኩል ተናገረ። (2 ሳሙኤል 12:1-4ን አንብብ።) በእርግጥም ይህ ከባድ ጉዳይ የተያዘበት መንገድ እጅግ ውጤታማ ነበር!

7. ዳዊት፣ ናታን ያቀረበውን ምሳሌ ሲሰማ ምን አደረገ?

7 ንጉሡ፣ ናታን የተናገረውን ምሳሌ ሲሰማ ፍትሕ እንደተጓደለ ተሰማው። ዳዊት በታሪኩ ላይ በተገለጸው ሀብታም ሰው ላይ እጅግ ተቆጥቶ ናታንን “ሕያው እግዚአብሔርን ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል!” አለው። በተጨማሪም እንዲህ ዓይነት በደል የተፈጸመበት ሰው ለደረሰበት ጉዳት ካሳ ሊከፈለው እንደሚገባ ገለጸ። በዚህ ጊዜ ናታን፣ ንጉሡ ጨርሶ ያልጠበቀውን ነገር ተናገረ፤ “ያ ሰው አንተ ነህ” አለው። ከዚያም ነቢዩ፣ የፈጸመው ድርጊት የሚያስከትልበት መዘዝ ይኸውም “ሰይፍ” ከቤቱ እንደማይርቅና በቤቱ ላይ ክፉ ነገር እንደሚመጣበት ለዳዊት ነገረው። በተጨማሪም በፈጸመው ኃጢአት ምክንያት በሕዝብ ፊት ውርደት እንደሚደርስበት ገለጸለት። በዚህ ጊዜ ዳዊት የፈጸመው ድርጊት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ስለተገነዘበ በጸጸት ስሜት ተውጦ “እግዚአብሔርን በጣም በድያለሁ” በማለት ተናገረ።—2 ሳሙ. 12:5-14

ዳዊት ያቀረበው ጸሎትና የአምላክ ይቅር ባይነት

8, 9. መዝሙር 51 የዳዊትን ውስጣዊ ስሜት የሚገልጸው እንዴት ነው? ይህስ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

8 ንጉሥ ዳዊት ከጊዜ በኋላ ያቀናበረው መዝሙር የተሰማውን ልባዊ ጸጸት ይገልጻል። መዝሙር 51 ዳዊት ለይሖዋ ያቀረባቸውን ልብ የሚነኩ ልመናዎችን የያዘ ከመሆኑም በተጨማሪ ስህተቶቹን ከማመን ያለፈ ነገር እንዳደረገ በግልጽ ያሳያል። ዳዊት ለፈጸማቸው ኃጢአቶች ንስሐም ገብቷል። በዋነኝነት ያሳሰበው ከአምላክ ጋር ያለው ግንኙነት ነበር። “አንተን፣ በእርግጥ አንተን ብቻ በደልሁ” በማለት ተናዟል። አክሎም “አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። . . . የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፤ በእሽታ መንፈስም ደግፈህ ያዘኝ” የሚል ልመና አቅርቧል። (መዝ. 51:1-4, 7-12) አንተስ የሠራሃቸውን ስህተቶች ልክ እንደ ዳዊት በቅንነትና በግልጽ ለይሖዋ ትነግረዋለህ?

9 ይሖዋ፣ ዳዊት የፈጸመው ኃጢአት ካስከተለበት አስከፊ መዘዝ ነፃ እንዲሆን አላደረገም። ንጉሡ በቀሪው የሕይወት ዘመኑ ሁሉ ድርጊቱ ያስከተለው መዘዝ አልተለየውም። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ ዳዊት ያሳየውን የንስሐ ዝንባሌ ማለትም የነበረውን ‘የተሰበረና የተዋረደ ልብ’ በመመልከት ይቅር ብሎታል። (መዝሙር 32:5ን አንብብ፤ መዝ. 51:17) ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የአንድን ሰው ትክክለኛ ዝንባሌና ኃጢአት እንዲፈጽም ምክንያት የሆኑትን ነገሮች በሙሉ ይረዳል። ይሖዋ፣ በሙሴ ሕግ መሠረት ሰብዓዊ ዳኞች ምንዝር በፈጸሙት ግለሰቦች ላይ የሞት ቅጣት እንዲያስፈጽሙ ከማድረግ ይልቅ በምሕረት ተነሳስቶ በዳዊትና በቤርሳቤህ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ራሱ ውሳኔ ሰጥቷል። (ዘሌ. 20:10) እንዲያውም አምላክ ከእነሱ አብራክ የተገኘው ሰለሞን ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን አድርጓል።—1 ዜና 22:9, 10

10. (ሀ) ይሖዋ ዳዊትን ይቅር ያለው ምንን መሠረት በማድረግ ሊሆን ይችላል? (ለ) ይሖዋ ሰዎችን ይቅር እንዲል የሚያነሳሱት ነገሮች ምንድን ናቸው?

10 ይሖዋ ዳዊትን ይቅር እንዲለው ያነሳሳው ሌላው ምክንያት ዳዊት ለሳኦል ምሕረት ማሳየቱ ሊሆን ይችላል። (1 ሳሙ. 24:4-7) ኢየሱስ፣ ይሖዋ እኛን የሚይዘን ሌሎችን በምንይዝበት መንገድ እንደሆነ ተናግሯል። ደግሞም “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ መፍረዳችሁን ተዉ፤ በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያም ይሰፍሩላችኋል” ብሏል። (ማቴ. 7:1, 2) ይሖዋ እንደ ምንዝርና ሰው መግደል የመሳሰሉ ከባድ ኃጢአቶችን ብንፈጽም እንኳ ይቅር ሊለን እንደሚችል ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ይሁንና ይሖዋ ይህን የሚያደርገው የይቅር ባይነት መንፈስ ካለን፣ ለእሱ ኃጢአታችንን ከተናዘዝንና መጥፎ ድርጊታችንን እርግፍ አድርገን መተዋችንን ካሳየን ብቻ ነው። ኃጢአተኞች ከልባቸው ንስሐ ከገቡ ‘ከይሖዋ ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላቸዋል።’—የሐዋርያት ሥራ 3:19ን አንብብ።

ምናሴ ከባድ ኃጢአት ቢፈጽምም ንስሐ ገብቷል

11. ንጉሥ ምናሴ በአምላክ ፊት የፈጸማቸው እጅግ ክፉ ነገሮች ምንድን ናቸው?

11 ይሖዋ በጣም ከባድ የሆኑ ኃጢአቶችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነ የሚያሳይ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንመልከት። ዳዊት መግዛት ከጀመረ ከ360 ዓመታት ገደማ በኋላ ምናሴ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። ለ55 ዓመታት የዘለቀው የምናሴ የግዛት ዘመን ክፋት የነገሠበት በመሆኑ ተለይቶ ይታወቃል፤ ምናሴ በወቅቱ የፈጸማቸው አስጸያፊ ድርጊቶች ይሖዋ እንዲቀጣው ምክንያት ሆኗል። ምናሴ ከፈጸማቸው አስጸያፊ ድርጊቶች መካከል ለበአሊም መሠዊያዎችን ማቆም፣ ‘የሰማይ ከዋክብት ሰራዊትን’ ማምለክ፣ ወንዶች ልጆቹን በእሳት መሠዋትና መናፍስታዊ ድርጊቶችን ማስፋፋት ይገኙበታል። በእርግጥም ምናሴ “በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር” አድርጓል።—2 ዜና 33:1-6

12. ምናሴ ወደ ይሖዋ የተመለሰው እንዴት ነው?

12 ከጊዜ በኋላ ምናሴ ከትውልድ አገሩ ተወስዶ ባቢሎን ውስጥ ታሰረ። በዚህ ወቅት ሙሴ ለእስራኤላውያን የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ሳያስታውስ አልቀረም፦ “ስትጨነቅና ይህ ሁሉ ነገር ሲደርስብህ ያን ጊዜ፣ በኋለኞቹ ዘመናት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ትመለሳለህ፤ ትታዘዝለታለህም።” (ዘዳ. 4:30) ደግሞም ምናሴ ወደ ይሖዋ ተመልሷል። እንዴት? (በገጽ 21 ላይ እንደሚታየው) ‘ራሱን እጅግ በማዋረድ’ እና ወደ አምላክ ‘በመጸለይ’ ነው። (2 ዜና 33:12, 13) ምናሴ ምን ብሎ እንደጸለየ የሚገልጽ ዘገባ ባይኖርም ንጉሥ ዳዊት በ⁠መዝሙር 51 ላይ ከተናገረው ሐሳብ ጋር በተወሰነ መጠን እንደሚመሳሰል መገመት እንችላለን። ምናሴ ያቀረበው ጸሎት ምንም ይሁን ምን ሙሉ በሙሉ ለውጥ አድርጎ ነበር።

13. ይሖዋ ምናሴን ይቅር ያለው ለምንድን ነው?

13 ታዲያ ይሖዋ ምናሴ ላቀረበው ጸሎት ምን ምላሽ ሰጠ? ‘በጭንቀት ልመናው ራርቶለት የምናሴን ጸሎት ሰማ።’ ምናሴ ከእሱ በፊት እንደነበረው እንደ ዳዊት፣ የሠራው ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የተገነዘበ ሲሆን ልባዊ ንስሐም ገብቷል። አምላክ ምናሴን ይቅር ያለውና በኢየሩሳሌም ወዳለው መንግሥቱ የመለሰው ለዚህ ነው። በዚህም የተነሳ ምናሴ “እግዚአብሔር [እውነተኛ] አምላክ መሆኑን ዐወቀ።” (2 ዜና 33:13) መሐሪው አምላካችን ልባዊ ንስሐ የሚገቡ ሰዎችን ይቅር እንደሚል የሚያሳይ ተጨማሪ ማረጋገጫ ማግኘታችን በጣም የሚያጽናና ነው!

ይሖዋ ይቅር ባይ በመሆኑ ምናሴን በኢየሩሳሌም ወዳለው መንግሥቱ መልሶታል

ይሖዋ ሁልጊዜ ይቅር ይላል?

14. ይሖዋ ኃጢአተኞችን ይቅር እንዲል የሚያደርገው ምንድን ነው?

14 በዛሬው ጊዜ ከሚገኙት የአምላክ ሕዝቦች መካከል እንደ ዳዊትና እንደ ምናሴ ያለ ከባድ ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት የአምላክን ይቅርታ የሚሹት በጣም ጥቂት ናቸው። ያም ሆኖ ይሖዋ እነዚህን ሁለት ነገሥታት ይቅር ማለቱ አንድ ኃጢአተኛ እውነተኛ ንስሐ እስከገባ ድረስ አምላካችን፣ ግለሰቡ የሠራቸውን ከባድ ኃጢአቶች እንኳ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል።

15. ይሖዋ ማንኛውንም ኃጢአት ምንጊዜም ይቅር ይላል እንዳንል የሚያደርገን ምንድን ነው?

15 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ኃጢአት የሠሩ ሰዎችን በሙሉ ምንጊዜም ይቅር ይላል ብለን ማሰብ አይኖርብንም። ከዚህ ጋር በተያያዘ ዳዊትና ምናሴ የነበራቸው አመለካከት ዓመፀኛ ከነበረው የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ምን ያህል የተለየ እንደሆነ እንመልከት። አምላክ ነቢዩ ናታንን በመላክ ዳዊት ንስሐ መግባት የሚችልበትን አጋጣሚ ሰጥቶታል። ዳዊት እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ በማግኘቱ አመስጋኝ ነበር። ምናሴም ቢሆን አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እንደወደቀ መገንዘቡ ልባዊ ንስሐ እንዲገባ አነሳስቶታል። የእስራኤልና የይሁዳ ነዋሪዎች ግን ንስሐ ለመግባት በተደጋጋሚ አሻፈረኝ ብለዋል። በመሆኑም ይሖዋ ይቅር አላላቸውም። ከዚህ ይልቅ የዓመፅ ድርጊታቸውን በተመለከተ ምን እንደሚሰማው በነቢያቱ አማካኝነት ብዙ ጊዜ ነግሯቸዋል። (ነህምያ 9:30ን አንብብ።) በምርኮ ከቆዩበት ከባቢሎን ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላም እንኳ እንደ ካህኑ ዕዝራና ነቢዩ ሚልክያስ ያሉ ታማኝ መልእክተኞችን አስነስቶላቸዋል። ሕዝቡ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር ተስማምተው በሚኖሩበት ጊዜ ከፍተኛ ደስታ ያገኙ ነበር።—ነህ. 12:43-47

16. (ሀ) እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ ንስሐ አለመግባታቸው ምን አስከተለባቸው? (ለ) የጥንቱ የእስራኤል ብሔር አባላት ለነበሩት ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ምን አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል?

16 ኢየሱስ ወደ ምድር ተልኮ ፍጹም ቤዛዊ መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ እስራኤላውያን የሚያቀርቡት የእንስሳ መሥዋዕት በይሖዋ ዘንድ የነበረውን ተቀባይነት አጣ። (1 ዮሐ. 4:9, 10) ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር በኖረበት ጊዜ የተናገረው የሚከተለው ልብ የሚነካ ሐሳብ አባቱ ያለውን አመለካከት ያንጸባርቃል፦ “ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም፣ ነቢያትን የምትገድል፣ ወደ እሷ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግር፤ ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ ሁሉ እኔም ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም።” በዚህም ምክንያት ኢየሱስ “እነሆ፣ ቤታችሁ ለእናንተ የተተወ ይሆናል” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 23:37, 38) በመሆኑም ኃጢአተኛና ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ያልነበረው ብሔር በመንፈሳዊ እስራኤል ተተካ። (ማቴ. 21:43፤ ገላ. 6:16) ይሁንና ሥጋዊ እስራኤላውያን በግለሰብ ደረጃ ምን አጋጣሚ ነበራቸው? በአምላክና በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት ላይ እምነት በማሳደር ከይሖዋ ይቅርታና ምሕረት ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ። ከኃጢአታቸው ንስሐ ሳይገቡ ቢሞቱም በጸዳችው ምድር ላይ ለመኖር ከሞት የሚነሱ ሰዎችም ይህን አጋጣሚ ያገኛሉ።—ዮሐ. 5:28, 29፤ ሥራ 24:15

ከይሖዋ ይቅር ባይነት ጥቅም ማግኘት

17, 18. የይሖዋን ይቅርታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

17 ይሖዋ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆኑ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል? ዳዊትና ምናሴ የተዉትን ምሳሌ መከተል እንዳለብን ግልጽ ነው። ኃጢአተኞች መሆናችንን መገንዘብ፣ ከበደላችን ንስሐ መግባት፣ ይሖዋ ይቅር እንዲለን አጥብቀን መለመንና ንጹሕ ልብ እንዲፈጥርልን መጠየቅ አለብን። (መዝ. 51:10) በተጨማሪም ከባድ ኃጢአት ሠርተን ከሆነ ከሽማግሌዎች መንፈሳዊ እርዳታ ማግኘት ይኖርብናል። (ያዕ. 5:14, 15) ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ‘ሩኅሩኅ፣ ቸር፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ ፍቅርን ለሺዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል አምላክ’ እንደሆነ ማወቃችን የሚያጽናና ነው። ይሖዋ ዛሬም ቢሆን አልተለወጠም።—ዘፀ. 34:6, 7

18 ይሖዋ ንስሐ የገቡትን እስራኤላውያን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ይቅር እንደሚል ቃል የገባው “እንደ ዐለላ” የቀላን ነገር ‘የበረዶ’ ያህል ነጭ እንደሚያደርግ በመግለጽ ነው። (ኢሳይያስ 1:18ን አንብብ።) ታዲያ የይሖዋ ይቅር ባይነት ለእኛ ምን ትርጉም አለው? አመስጋኝ ከሆንንና የንስሐ ዝንባሌ ካሳየን ኃጢአታችንና በደላችን ሙሉ በሙሉ ይቅር ይባልልናል።

19. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

19 እርስ በርስ ባለን ግንኙነት ረገድ እንደ ይሖዋ ይቅር ባይ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ከባድ ኃጢአት ሠርተው እውነተኛ ንስሐ የገቡ ሰዎችን ይቅር ማለት የምንችለውስ እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ልባችንን በመመርመር “ቸርና ይቅር ባይ” የሆነውን ይሖዋን ይበልጥ መምሰል እንድንችል ይረዳናል።—መዝ. 86:5