በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጠበቂያ ግንብ ቀለል ባለ ቋንቋ መዘጋጀት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

መጠበቂያ ግንብ ቀለል ባለ ቋንቋ መዘጋጀት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

ለብዙ አሥርተ ዓመታት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱትን በመጠበቂያ ግንብ ላይ ለሚወጡ ትምህርቶች አድናቆት ያላቸው ከመሆኑም በላይ በርካታ ጥቅም አግኝተውባቸዋል። ከሐምሌ 2011 አንስቶ ደግሞ የዚህ መጽሔት የጥናት እትም ቀለል ባለ እንግሊዝኛ መዘጋጀት ጀመረ። ይህ እትም እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ይህ አዲስ እትም ለሙከራ ያህል ለአንድ ዓመት ይታተማል፤ ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ ኅትመቱ ይቀጥላል።”

የዚህ መጽሔት ኅትመት እንዲቀጥል መወሰናችንን ስናሳውቃችሁ በጣም ደስ ይለናል! በተጨማሪም በጊዜ ሂደት ቀለል ባለ ቋንቋ የሚዘጋጀው እትም በፈረንሳይኛ፣ በፖርቱጋልኛና በስፓንኛ መውጣት ይጀምራል።

አድናቆት የተቸረው ለምንድን ነው?

በደቡብ ፓስፊክ የሚኖሩ በርካታ ወንድሞች ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጀውን እትም እንዳገኙ “አሁን ወንድሞች የመጠበቂያ ግንቡን ሙሉ ሐሳብ በሚገባ መረዳት ችለዋል” የሚል ደብዳቤ ልከዋል። አንድ ሌላ ደብዳቤ ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “የቃላትን ትርጉም በማየትና አንዳንድ አገላለጾችን በማብራራት እናጠፋ የነበረውን ጊዜ አሁን ጥቅሶቹን ለመረዳትና ከትምህርቱ ጋር እንዴት እንደሚያያዙ ለማስተዋል እንጠቀምበታለን።”

“የቃላትን ትርጉም በማየትና አንዳንድ አገላለጾችን በማብራራት እናጠፋ የነበረውን ጊዜ አሁን ጥቅሶቹን ለመረዳትና ከትምህርቱ ጋር እንዴት እንደሚያያዙ ለማስተዋል እንጠቀምበታለን”

በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ከኮሌጅ የተመረቀች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ላለፉት 18 ዓመታት ስናገርም ሆነ ጽሑፍ ሳዘጋጅ የምጠቀመው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚሠራበት ለመረዳት የሚያስቸግር ቋንቋ ነበር። ከሚገባው በላይ ውስብስብ በሆነ መንገድ የመናገርና የማሰብ ልማድ አዳብሬ ነበር። ይሁንና በምናገርበትም ሆነ በማስብበት መንገድ ላይ ትልቅ ለውጥ ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።” በአሁኑ ጊዜ ውጤታማ ወንጌላዊ የሆነችው ይህች ሴት እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጀው መጠበቂያ ግንብ  በጣም ጠቅሞኛል። መጽሔቱ የሚጠቀምበት ቋንቋ ነገሮችን ቀለል ባለ መንገድ እንዴት መግለጽ እንደሚቻል በሚገባ አስገንዝቦኛል።”

በ1972 የተጠመቀች በእንግሊዝ የምትኖር አንዲት እህት ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጀውን የመጠበቂያ ግንብ እትም አስመልክታ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “የመጀመሪያውን እትም ሳነብ ይሖዋ አጠገቤ ተቀምጦና እጁን ትከሻዬ ላይ ጣል አድርጎ አብረን ያነበብን ያህል ተሰምቶኝ ነበር። ይህም አንድ አባት ልጁ ከመተኛቱ በፊት ታሪክ እንደሚያነብለት ያህል ነው።”

ከተጠመቀች ከ40 ዓመት በላይ የሆናትና በዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል የምታገለግል አንዲት እህት ደግሞ ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጀው እትም አንዳንድ ጊዜ አዳዲስ ነገሮችን እንድታስተውል እንደረዳት ተናግራለች። ለምሳሌ ያህል በመስከረም 15, 2011 እትም ላይ ያለው “የቃላት መፍቻ” የሚለው ሣጥን ዕብራውያን 12:1 ላይ ለሚገኘው “የምሥክሮች ደመና” ለሚለው ሐረግ “እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ሊቆጠሩ የማይችሉ” የሚል ፍቺ ሰጥቷል። እህት “ይህ ፍቺ ጥቅሱ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልኝ አድርጓል” ብላለች። ሳምንታዊ ስብሰባዎችን በተመለከተ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ልጆች የሚመልሱት ቀለል ባለ ቋንቋ ከተዘጋጀው እትም ላይ እያነበቡ ቢሆንም እንኳ የሚጠቀሙበት ቃል አብዛኞቹ ተሰብሳቢዎች በሚይዙት መደበኛው የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ ካሉት ቃላት ጋር አይመሳሰልም። በመሆኑም ልጆች የሚሰጡት መልስ ለተሰብሳቢዎቹ ድግግሞሽ አይሆንባቸውም።”

በቤቴል የምታገለግል ሌላ እህት ደግሞ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “በጉባኤ ውስጥ ልጆች የሚሰጡትን ሐሳብ ለመስማት እጓጓለሁ። ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጀው መጠበቂያ ግንብ ምንም ሳይፈሩ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ አስችሏቸዋል። የሚሰጡት ሐሳብ ያበረታታኛል።”

 በ1984 የተጠመቀች አንዲት እህት ለዚህ እትም ያላትን አድናቆት እንዲህ ስትል ገልጻለች፦ “ለእኔ ተብሎ እንደተጻፈ ይሰማኛል። የማነበው ነገር በቀላሉ እንዲገባኝ አስችሎኛል። አሁን መጠበቂያ ግንብ በሚጠናበት ወቅት መልስ ለመስጠት ድፍረት አግኝቻለሁ።”

ወላጆችን የሚጠቅም መሣሪያ

የሰባት ዓመት ልጅ ያላት አንዲት እናት “ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት በምንዘጋጅበት ወቅት ለልጄ በርካታ ዓረፍተ ነገሮችን ማብራራት ስለሚኖርብኝ ዝግጅታችን ረጅም ጊዜ የሚፈጅና አድካሚ ነበር” በማለት ተናግራለች። ታዲያ ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጀው እትም የጠቀማት እንዴት ነው? እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “አንቀጾቹን በማንበብ መሳተፉና የሚያነበውን ሐሳብ በደንብ መረዳት መቻሉ በጣም አስደንቆኛል። ቃላቶቹ ከባድ አይደሉም፤ ዓረፍተ ነገሮቹም አጫጭር ናቸው። በመሆኑም ትምህርቱ የሚገባው ከመሆኑም በላይ ያስደስተዋል። ለስብሰባዎች ያለ እኔ እገዛ መዘጋጀት ጀምሯል እንዲሁም ጥናቱ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ መጽሔቱን በትኩረት ይከታተላል።”

“አንቀጾቹን በማንበብ መሳተፉና የሚያነበውን ሐሳብ በደንብ መረዳት መቻሉ በጣም አስደንቆኛል”

የዘጠኝ ዓመት ልጅ ያለቻት አንዲት እናት ደግሞ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ከዚህ በፊት ምን ብላ እንደምትመልስ የምናዘጋጃት እኛ ነበርን። አሁን ግን ራሷን ችላ ትዘጋጃለች። አብዛኛውን ጊዜ፣ ትምህርቱን እንድናብራራላት ወይም ግልጽ እንድናደርግላት የእኛን እርዳታ አትፈልግም። ሐሳቡ መረዳት ከምትችለው በላይ ስላልሆነ የመጠበቂያ ግንብ ጥናቱን ደስ ብሏት ትከታተላለች።”

ልጆች ምን ተሰምቷቸዋል?

በርካታ ልጆች ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጀው መጠበቂያ ግንብ ለእነሱ ተብሎ እንደተዘጋጀ ተሰምቷቸዋል። የአሥራ ሁለት ዓመቷ ሬቤካ “እባካችሁ አዲሱን እትም ማዘጋጀታችሁን ቀጥሉ!” የሚል ጥያቄ አቅርባለች። አክላም “‘የቃላት መፍቻ’ የሚለውን ክፍል ያዘጋጃችሁበትን መንገድ ወድጄዋለሁ። ልጆች እንኳ በቀላሉ ሊረዱት ይችላሉ” ብላለች።

የሰባት ዓመቷ ኒከሌትም ተመሳሳይ ስሜት አላት፦ “መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚወጡ ሐሳቦችን መረዳት ያስቸግረኝ ነበር። አሁን ግን ያለ ማንም እርዳታ በርከት ያሉ ሐሳቦችን መስጠት እችላለሁ።” የዘጠኝ ዓመቷ ኤመ ደግሞ “መጽሔቱ እኔንም ሆነ ስድስት ዓመት የሆነውን ወንድሜን በጣም ረድቶናል። ትምህርቱን ከበፊቱ በተሻለ መረዳት ችለናል፤ እናመሰግናችኋለን!” ብላለች።

ብዙዎች በቀላሉ የሚገቡ ቃላትና ዓረፍተ ነገሮች የያዘውን የመጠበቂያ ግንብ እትም ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ግልጽ ነው። ይህ መጽሔት የብዙዎችን ፍላጎት የሚያሟላ ሲሆን ከ1879 አንስቶ ጠቃሚ መንፈሳዊ ዝግጅት ሆኖ ከቆየው መደበኛ እትም ጋር መውጣቱን ይቀጥላል።