የአንባቢያን ጥያቄዎች
እኔና ባለቤቴ እውነትን ከማወቃችን በፊት ልጅ ለመውለድ በነበረን ፍላጎት የተነሳ ከማህፀን ውጭ በብልቃጥ ውስጥ ፅንስ እንዲፈጠር በሚያደርግ የሕክምና ዘዴ (ኢን ቪትሮ ፈርትላይዜሽን) ተጠቅመን ነበር። ሆኖም ጥቅም ላይ የዋሉት ሁሉም ሽሎች አልነበሩም፤ አንዳንዶቹ በበረዶ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርገዋል። ታዲያ እነዚህ ሽሎች በዚያው መቆየት አለባቸው ወይስ እንዲወገዱ ማድረግ ያስፈልጋል?
አንድ ባልና ሚስት ከማህፀን ውጭ በብልቃጥ ውስጥ ፅንስ እንዲፈጠር በሚያደርግ የሕክምና ዘዴ ለመጠቀም በሚመርጡበት ጊዜ ከሚደቀኑባቸው በርካታ ከባድ የሥነ ምግባር ጥያቄዎች አንዱ ይህ ነው። ሁሉም ባልና ሚስቶች ለሚያደርጉት ውሳኔ በይሖዋ ዘንድ ተጠያቂ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ በቴክኖሎጂ እገዛ ፅንስ ስለሚፈጠርበት መንገድ አጠቃላይ ግንዛቤ ማግኘት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
በ1978 በእንግሊዝ አገር የምትኖር አንዲት ሴት በዚህ ዘዴ ተጠቅማ ልጅ ለመውለድ የመጀመሪያዋ ሆነች። እንቁላል የሚፈጠርበትን የአካል ክፍል ከማህፀኗ ጋር የሚያገናኘው ፋሎፒያን ቲዩብ ተብሎ የሚጠራ ቱቦ ተዘግቶ ነበር፤ በመሆኑም የወንዴው ዘር ከእሷ እንቁላል ጋር መገናኘት ባለመቻሉ መፀነስ ተሳናት። የሕክምና ባለሙያዎች ለፅንስ የደረሰ እንቁላል በቀዶ ሕክምና ከሴቲቱ ካወጡ በኋላ በብልቃጥ ውስጥ አስቀምጠው ከባልየው ዘር ጋር እንዲገናኝና ፅንስ እንዲፈጠር አደረጉ። በዚህ መንገድ የተፈጠረው ፅንስ ምግብ በሚያገኝበት ብልቃጥ ውስጥ እንዲያድግ ከተደረገ በኋላ ማህፀኗ ውስጥ ተቀመጠ። ከጊዜ በኋላ ሴት ልጅ ወለደች። ይህ ዘዴና ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ አሠራሮች በሙሉ በብልቃጥ ውስጥ ፅንስ መፍጠር (ኢን ቪትሮ ፈርትላይዜሽን) ወይም አይ ቪ ኤፍ ተብለው መጠራት ጀመሩ።
ዝርዝር አሠራሮች ከአገር ወደ አገር ሊለያዩ ቢችሉም በጥቅሉ ሲታይ በብልቃጥ ውስጥ ፅንስ የሚፈጠረው በሚከተለው መንገድ ነው፦ ሚስትየው በርካታ እንቁላሎች ማስገኘት እንድትችል የሚረዱ መድኃኒቶች ለሳምንታት ይሰጧታል። ባልየው በማስተርቤሽን አማካኝነት ሊሆን ይችላል የወንዴ ዘር እንዲሰጥ ይጠየቃል። እንቁላሎቹና የወንዴው ዘር በላብራቶሪ ውስጥ እንዲዋሃዱ ይደረጋል። ከዚያም በርካታ እንቁላሎች ይዳብራሉ፤ በዚህ መንገድ የተፈጠሩት ሴሎች እየተከፋፈሉ ሄደው ሽሎች ይሆናሉ። ከአንድ ወይም ከሁለት ቀን በኋላ ከእነዚህ አዳዲስ ሽሎች መካከል ጉድለት ያለባቸውና ጤነኛ ሆነው ማህፀን ውስጥ ማደግ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡት በጥንቃቄ ይለያሉ። በሦስተኛው ቀን ገደማ የሴትየዋ የማርገዝ አጋጣሚ እንዲጨምር ሲባል አንድ ብቻ ሳይሆን የተሻሉ ናቸው ከሚባሉት ሽሎች መካከል ሁለቱ ወይም ሦስቱ ወደ ማህፀኗ እንዲዛወሩ ይደረጋል። አንዱ ሽል ወይም ከዚያ በላይ ቁጥር ያላቸው ሽሎች ከማህፀኗ ጋር ተላምደው ካረገዘች ጊዜው ሲደርስ ልጅ ትወልዳለች ተብሎ ይጠበቃል።
ጉድለት አለባቸው ወይም ጤናቸው የተሟላ አይደለም የተባሉትን ጨምሮ ወደ ማህፀን ሳይዛወሩ የቀሩት ሽሎችስ ምን ይሆናሉ? ትርፍ የሆኑት ሽሎች እንዲሁ ከተተዉ በሕይወት መቆየት አይችሉም። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን እነዚህ ሽሎች በፈሳሽ ናይትሮጅን ውስጥ ወደ በረዶነት ተለውጠው እንዲቆዩ ይደረጋል። ለምን? የመጀመሪያው የአይ ቪ ኤፍ ሙከራ ሳይሳካ ከቀረ ለመጠባበቂያነት ከተቀመጡት ትርፍ ሽሎች ተወስዶ ሌላ የአይ ቪ ኤፍ ሙከራ በአነስተኛ ወጪ ይካሄዳል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ድርጊት ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዘ ጥያቄ ያስነሳል። ከላይ የሰፈረውን ጥያቄ እንዳነሱት ባልና ሚስት ሁሉ ብዙ ሰዎች በበረዶ ውስጥ እንዲቆዩ የተደረጉትን ሽሎች ምን እናድርጋቸው የሚል አስቸጋሪ ጥያቄ ይደቀንባቸዋል። እነዚህ ወላጆች ተጨማሪ ልጆች እንዲኖሯቸው ላይፈልጉ ይችላሉ። በሌላ በኩል የወላጆቹ ዕድሜ ወይም የገንዘብ አቅም ሌላ ሙከራ ለማድረግ አይፈቅድላቸው ይሆናል። አሊያም ከአንድ በላይ ፅንስ መያዝ የሚያስከትለው የጤና ችግር ሊያስፈራቸው ይችላል። * ወይም ደግሞ ከባልና ሚስቱ አንዱ ወይም ሁለቱም መሞታቸው አሊያም ሌላ ሰው ማግባታቸው ሁኔታውን ሊያወሳስበው ይችላል። አዎ፣ የሚፈጠሩት አሳሳቢ ሁኔታዎች በርካታ ናቸው፤ በዚህም ምክንያት ብዙ ባልና ሚስቶች ለዓመታት የማቆያ ኪራይ ሲከፍሉ ይኖራሉ።
በ2008 አንድ የፅንስ ክትትል ከፍተኛ ባለሙያ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ ብዙ ታካሚዎች ትርፍ የሆኑትን ሽሎች ምን እንደሚያደርጉ ግራ እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ጽሑፉ እንዲህ ይላል፦ “በመላ አገሪቱ በሚገኙ ክሊኒኮች በበረዶ ውስጥ የተቀመጡ በትንሹ 400,000 የሚያህሉ ሽሎች ይገኛሉ፤ ይህ አኃዝ ደግሞ በየቀኑ ይጨምራል፤ . . . ሽሎቹ በሚገባ እንዲቀዘቅዙ ከተደረገ ለአሥር ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ዓመታት ሕያው ሆነው ሊቆዩ ይችላሉ፤ ሆኖም የቆዩበት በረዶ ቀልጦ ከወጡ በሕይወት መቆየት የሚችሉት ሁሉም አይደሉም።” ይህ ሐቅ አንዳንድ ክርስቲያኖችን ቆም ብለው እንዲያስቡ አስገድዷቸዋል። ለምን?
ከአይ ቪ ኤፍ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ያጋጠማቸው ክርስቲያን ባልና ሚስት ከዚህ የተለየ አንድ ሌላ የሕክምና ጉዳይ ስለሚኖረው አንድምታ ቢያስቡ ጥሩ ይሆናል። አንድ ክርስቲያን፣ እንደ መተንፈሻ መሣሪያ ባለ ሰው ሠራሽ ዘዴ ብቻ በሕይወት እንዲቆይ የተደረገና ለሞት የተቃረበ የቤተሰብ አባል ይኖረው ይሆናል፤ በመሆኑም ከዚህ የቤተሰቡ አባል ጋር በተያያዘ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ ሊደቀንበት ይችላል። እውነተኛ ክርስቲያኖች በዘፀአት 20:13 እና በመዝሙር 36:9 መሠረት ለሕይወት ከፍተኛ አክብሮት ስላላቸው የሕክምና እርዳታን ቸል ማለት ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። የግንቦት 8, 1974 ንቁ! (እንግሊዝኛ) እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዟል፦ “አኗኗራቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ለማስማማት የሚፈልጉ ሁሉ አምላክ ለሕይወት ቅድስና ያለውን አመለካከት ያከብራሉ፤ በመሆኑም ለገዛ ራሳቸው ሕሊና ሲሉ እንዲሁም መንግሥት ያወጣቸውን ሕጎች መታዘዝ ስለሚፈልጉ አንድ ሕመምተኛ ሥቃይ ከሚበዛበት በሚል ሕይወቱ ሆን ተብሎ እንዲያበቃ ለማድረግ ፈጽሞ አይስማሙም።” ይሁን እንጂ በአንዳንድ ሁኔታዎች ሕመምተኛው በሕይወት ሊቆይ የቻለው በዘመናዊ መሣሪያ እርዳታ ብቻ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ የቤተሰቡ አባሎች፣ በዚህ ሰው ሠራሽ ሕይወት ማቆያ መሣሪያ መጠቀሙን ይቀጥል ወይስ አይቀጥል የሚለውን መወሰን ይኖርባቸዋል።
እርግጥ ነው፣ ይህ ሁኔታ በአይ ቪ ኤፍ ዘዴ ከተጠቀሙ በኋላ የተቀመጠ ሽል ያላቸው ባልና ሚስት ከሚያጋጥማቸው ሁኔታ ጋር አንድ አይደለም። ይሁንና ባልና ሚስቱ ከሚኖሯቸው አማራጮች አንዱ ሽሎቹ በረዶ ከሆነው ናይትሮጅን ውስጥ እንዲወጡ ማድረግ ነው። ሽሎቹ ከማቀዝቀዣ ውስጥ ከወጡ በኋላ በሕይወት መቆየት የሚችሉት ለአጭር ጊዜ ነው። ባልና ሚስቱ እንዲህ ማድረግ ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ያስፈልጋቸዋል።—ገላ. 6:7
አንድ ባልና ሚስት ፅንስ እንዲፈጠር ለማድረግና በኋላም ልጅ ለመውለድ ተስፋ በማድረግ በአይ ቪ ኤፍ ዘዴ ለመጠቀም ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በተጨማሪም ትርፍ የሆኑትን ሽሎች በበረዶ ውስጥ ማቆየት የሚጠይቀውን ወጪ ለመክፈልና ምናልባትም ወደፊት በእነዚህ ሽሎች ተጠቅመው ሌላ ልጅ ለማግኘት ይሞክሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሌሎች ባልና ሚስቶች ሽሎቹ ሊቆዩ የቻሉት በሰው ሠራሽ ዘዴ በመሆኑ በሕይወት እንዲቆዩ ያስቻለው ይህ ሁኔታ እንዲቋረጥ ሊመርጡ ይችላሉ። እንዲህ ያለ ውሳኔ የተደቀነባቸው ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናቸውን የሚጠቀሙበት መንገድ በአምላክ ፊት ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። ፍላጎታቸው የሌሎችን ሕሊና ግምት ውስጥ ማስገባታቸውን ችላ ሳይሉ ንጹሕ ሕሊና ይዞ መኖር ሊሆን ይገባል።—1 ጢሞ. 1:19
እንዲህ ያለ ውሳኔ የተደቀነባቸው ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናቸውን የሚጠቀሙበት መንገድ በአምላክ ፊት ተጠያቂ ያደርጋቸዋል
በመራቢያ አካላት ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድሩ ሆርሞኖች የሚያጠኑ አንድ ባለሙያ ባለትዳሮች “በማቀዝቀዣ ውስጥ ያሉት ሽሎች ሁኔታ በጣም እንደሚያሳስባቸውና ይህን በተመለከተ ምን እንደሚወስኑ ግራ እንደሚገባቸው” ገልጸዋል። ከዚያም “ብዙ ባልና ሚስቶች ያሏቸው አማራጮች በሙሉ ጥሩ እንደሆኑ አይሰማቸውም” ሲሉ ደምድመዋል።
በአይ ቪ ኤፍ ዘዴ ለመጠቀም በማሰብ ላይ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም እንኳ ከዚህ አሠራር ጋር የተያያዙትን አሳሳቢ ጉዳዮች በሙሉ በጥሞና ሊያስቡባቸው እንደሚገባ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል” የሚል ምክር ይሰጣል።—ምሳሌ 22:3
መጽሐፍ ቅዱስ እያጠኑ ያሉና አብረው የሚኖሩ አንድ ወንድና ሴት ለመጠመቅ ፈለጉ፤ ይሁን እንጂ ሰውየው የመኖሪያ ፈቃድ ስለሌለው ሕጋዊ ጋብቻ መፈጸም አልቻሉም። የአገሪቱ መንግሥት ደግሞ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌለው የውጭ አገር ዜጋ ጋብቻ እንዲፈጽም አይፈቅድም። እነዚህ ሰዎች በታማኝነት አብሮ ለመኖር የሚፈጸም ውል የተባለውን ቅጽ በመጠቀም ከተፈራረሙ መጠመቅ ይችላሉ?
ይህ ጥሩ መፍትሔ ሊመስል ቢችልም እነዚህ ሰዎች ችግራቸውን መፍታት የሚችሉበት ቅዱስ ጽሑፋዊ መንገድ አይደለም። የዚህን ምክንያት ለመረዳት በመጀመሪያ በታማኝነት አብሮ ለመኖር የሚፈጸም ውል የተባለው ቅጽ የተዘጋጀበትን ዓላማ እንዲሁም ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለው እንዴትና የት እንደሆነ እንመልከት።
ይህ ቅጽ ከታች በተጠቀሰው ምክንያት በሕጋዊ መንገድ ጋብቻ መፈጸም ያልቻሉ አንድ ወንድና ሴት በምሥክሮች ፊት የሚፈርሙት ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ለመሆንና አጋጣሚውን ሲያገኙ ጋብቻቸውን ሕጋዊ ለማድረግ ቃል የሚገቡበት ቅጽ ነው። ጉባኤው እነዚህን ጥንዶች በአምላክም ሆነ በሰው ፊት አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ለመሆን ቃል እንደገቡ አድርጎ ስለሚመለከታቸው ጥምረታቸውን በመንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ እንደጸደቀ አድርጎ ይመለከተዋል።
ታዲያ በታማኝነት አብሮ ለመኖር የሚፈጸም ውል የተባለው ቅጽ ጥቅም ላይ የሚውለው ለምንና መቼ ነው? የሰው ልጆችን በጋብቻ እንዲጣመሩ ያደረገው ይሖዋ ነው፤ ዝግጅቱንም ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። ልጁ ኢየሱስም “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” ብሏል። (ማቴ. 19:5, 6፤ ዘፍ. 2:22-24) አክሎም “በዝሙት [በፆታ ብልግና] ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ምንዝር ይፈጽማል” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 19:9) በመሆኑም ትዳርን ለማፍረስ መሠረት የሚሆነው ብቸኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት “ዝሙት” ማለትም የፆታ ብልግና ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ከትዳሩ ውጭ የፆታ ግንኙነት ቢፈጽም ታማኝ የሆነችው ሚስቱ እሱን ለመፍታት ወይም ላለመፍታት ልትወስን ትችላለች። ባሏን ለመፍታት ከወሰነች ሌላ ሰው የማግባት ነፃነት ይኖራታል።
ይሁን እንጂ በአንዳንድ አገሮች ከፍተኛ ተሰሚነት ያለው አንድ ቤተ ክርስቲያን፣ በተለይም ቀደም ባሉት ዓመታት ይህን ግልጽ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ አቋም ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ከዚህ ይልቅ በምንም ምክንያት ፍቺ መፈጸም እንደማይችል ያስተምር ነበር። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኑ ከፍተኛ ተጽዕኖ በሚያሳድርባቸው አገሮች ውስጥ የመንግሥት ሕግ ፍቺን ይከለክል ነበር፤ ኢየሱስ የጠቀሰው ተቀባይነት ያለው ምክንያት እንኳ ምንም ቦታ አልተሰጠውም። በሌሎች አገሮች ደግሞ ፍቺ መፈጸም የሚቻል ቢሆንም ሂደቱ በጣም ረጅም፣ የተንዛዛና አድካሚ ነው። በመሆኑም ፍቺ መፈጸም በርካታ ዓመታት ሊወስድ ይችላል። ይህም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ነገር ቤተ ክርስቲያን ወይም መንግሥት ‘የከለከለ’ ያህል ነው።—ሥራ 11:17
ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ባልና ሚስት የሚኖሩት ፍቺ መፈጸም በማይቻልበት ወይም እጅግ አስቸጋሪ በሆነበት ምናልባትም ብዙ ዓመታት በሚፈጅበት አገር ውስጥ ሊሆን ይችላል። በሕግ ካገቡት የትዳር ጓደኛቸው ለመለያየት የሚችሉትን ሁሉ ካደረጉና መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት ለማግባት ነፃ ከሆኑ በታማኝነት አብሮ ለመኖር የሚፈጸም ውል የተባለውን ቅጽ መፈረም ይችላሉ። እንዲህ ባሉ አገሮች ውስጥ የክርስቲያን ጉባኤ አሳቢነት የሚንጸባረቅበት ይህን የመሰለ ለየት ያለ ዝግጅት አድርጓል። ይሁን እንጂ ፍቺ መፈጸም ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ወይም ሂደቱ የተወሳሰበ ቢሆንም እንኳ መፋታት በሚቻልባቸው በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ በዚህ ዝግጅት መጠቀም አይቻልም።
አንዳንዶች በታማኝነት አብሮ ለመኖር የሚፈጸም ውል የተባለው ቅጽ የተዘጋጀበትን ዓላማ ስላልተረዱ በሚኖሩበት አገር ፍቺ መፈጸም የሚቻል ቢሆንም የተንዛዙ አሠራሮችን ወይም ውጣ ውረዶችን ላለመጋፈጥ ሲሉ በዚህ ቅጽ ለመፈራረም ጥያቄ አቅርበዋል።
ከላይ በተነሳው ጥያቄ ላይ የተጠቀሱት ከሥነ ምግባር ውጭ በሆነ መንገድ አብረው የሚኖሩት ወንድና ሴት የመጋባት ፍላጎት አላቸው። ሁለቱም በቅዱስ ጽሑፉ መሠረት የማግባት ነፃነት አላቸው፤ ከቀድሞ የትዳር ጓደኛቸው ጋር በሕጋዊ መንገድ ተለያይተዋል። ይሁንና ሰውየው ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ስለሌለው የአገሩ መንግሥት ይህ የውጭ አገር ዜጋ ጋብቻ እንዲፈጽም አይፈቅድም። (ብዙ አገሮች አንደኛው ወይም ሁለቱም ወገኖች የመኖሪያ ፈቃድ ባይኖራቸውም እንኳ ጋብቻ እንዲፈጽሙ ይፈቅዳሉ።) አሁን እየተብራራ ካለው ጉዳይ ጋር በተያያዘ የአገሩ መንግሥት ፍቺን ለመፈጸም የሚያስችል ዝግጅት አለው። በመሆኑም በታማኝነት አብሮ ለመኖር የሚፈጸም ውል የተባለውን ቅጽ መፈረም እንደ አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም። እነዚህ ጥንዶች ፍቺ መፈጸም ፈልገው የተከለከሉ አይደሉም። ጋብቻ ለመፈጸም ሁለቱም ነፃ ናቸው። ይሁን እንጂ ሰውየው ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ስለሌለው ጋብቻ መፈጸም የሚችሉት እንዴት ነው? የመኖሪያ ፈቃድ የሌለው መሆኑ እንቅፋት ወደማይፈጥርበት አገር መሄድ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ወይም ደግሞ ሰውየው የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት የሚያስፈልጉ ተገቢ እርምጃዎችን ከወሰደ በዚያው በሚኖሩበት አገር ጋብቻቸውን ለመፈጸም ሊፈቀድላቸው ይችላል።
በእርግጥም አንድ ወንድና ሴት ሕይወታቸውን አምላክ ካወጣቸው መሥፈርቶችም ሆነ ከቄሳር ሕግ ጋር ማስማማት ይችላሉ። (ማር. 12:17፤ ሮም 13:1) እንዲህ እንደሚያደርጉም ተስፋ አለን። ይህን ካሟሉ በኋላ ለመጠመቅ ብቁ ሊሆኑ ይችላሉ።—ዕብ. 13:4
^ စာပိုဒ်၊ 6 በማደግ ላይ ያለው ሽል ጤነኛ ባይመስል ወይም በርካታ ሽሎች በማህፀን ውስጥ ማደግ ቢጀምሩስ? ሆን ብሎ ፅንስ እንዲቋረጥ ማድረግ ውርጃ መፈጸም ይሆናል። በአይ ቪ ኤፍ ዘዴ የሚጠቀሙ ሴቶች ብዙውን ጊዜ ሁለት፣ ሦስት ወይም ከዚያ የሚበልጡ መንትዮች ሊወልዱ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ እናትየው ቀኑ ያልደረሰ ሕፃን የመውለዷ ወይም በሰውነቷ ውስጥ ብዙ ደም የመፍሰሱ አጋጣሚ ከፍተኛ እንዲሆን ያደርጋል። በማህፀኗ ውስጥ ብዙ ሽሎች የያዘች እናት አንድ ወይም ከዚያ በላይ ሽሎች “ተመርጠው እንዲወገዱ” ይኸውም እንዲገደሉ እንድትፈቅድ ልትጠየቅ ትችላለች። ይህ ደግሞ ሆን ብሎ ፅንስ ማስወረድ ስለሚሆን ከነፍስ ግድያ ተለይቶ አይታይም።—ዘፀ. 21:22, 23፤ መዝ. 139:16