በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእውነተኛው አምልኮ አንድ የሆኑ “ጊዜያዊ ነዋሪዎች”

በእውነተኛው አምልኮ አንድ የሆኑ “ጊዜያዊ ነዋሪዎች”

“ባዕዳን በዕርሻችሁና በወይን ተክል ቦታችሁ ላይ ይሠሩላችኋል። እናንተም የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ካህናት ተብላችሁ ትጠራላችሁ።”—ኢሳ. 61:5, 6

1. አንዳንድ ሰዎች ለባዕዳን ምን ዓይነት አመለካከት አላቸው? ይህ ዓይነቱ አመለካከት ትክክል ያልሆነው ለምንድን ነው?

ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ሰዎች ‘ባዕድ’ የሚለውን ቃል ሌሎችን በሚያንኳስስ መንገድ የሚጠቀሙበት ሲሆን ይህም ለሰው ያላቸውን ንቀት ይባስ ብሎም የመረረ ጥላቻ ያሳያል። በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ወደ አገራቸው የመጡ የሌላ አገር ዜጎችን ከእነሱ እንደሚያንሱ አድርገው ማየታቸው አክብሮት የጎደለው ድርጊት ነው። ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ተጨባጭ እውነታዎቹን ካለማወቅ የሚመነጭ ነው። የሰው ዘሮች (እንግሊዝኛ) የተባለው ጽሑፍ “የሰው ዘሮች በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ወንድማማቾች ናቸው” ብሏል። በወንድማማቾች መካከል በአብዛኛው ሰፊ ልዩነት ይታያል፤ ያም ሆነ ይህ ወንድማማች መሆናቸው አይቀርም።

2, 3. ይሖዋ ለባዕዳን ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

2 እርግጥ ነው፣ የትም እንኑር የት የባዕድ አገር ሰዎች በመካከላችን መኖራቸው አይቀርም። በጥንት ዘመን የነበሩት እስራኤላውያንም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር፤ እስራኤላውያን በሕጉ ቃል ኪዳን አማካኝነት ከይሖዋ አምላክ ጋር ልዩ የሆነ ዝምድና የመሠረቱ ሕዝቦች ነበሩ። በመካከላቸው የሚኖሩት እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች ያሏቸው መብቶች በተወሰነ መጠን የተገደቡ ቢሆኑም እስራኤላውያን እነሱን በአክብሮትና ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ መያዝ ይጠበቅባቸው ነበር። ይህ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ነው! እውነተኛ ክርስቲያኖች በምንም ዓይነት አድልዎ ወይም ጭፍን ጥላቻ ማሳየት የለባቸውም። ለምን? ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ እንደማያዳላ በእርግጥ አስተዋልኩ፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”—ሥራ 10:34, 35

3 በጥንቷ እስራኤል ይኖሩ የነበሩ ባዕዳን ከትውልደ እስራኤላውያን ጋር ተቀራርበው በመኖራቸው ተጠቅመዋል። ይህም ይሖዋ በጉዳዩ ላይ ያለውን አስተሳሰብ ያሳያል፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ከብዙ ዓመታት በኋላ ይሖዋን በተመለከተ ባቀረበው ጥያቄ ላይ የአምላክን  አስተሳሰብ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “አምላክ የአይሁዳውያን አምላክ ብቻ ነው? የአሕዛብስ አምላክ አይደለም? አዎ፣ የአሕዛብም አምላክ ነው።”—ሮም 3:29፤ ኢዩ. 2:32

4. “በአምላክ እስራኤል” ውስጥ ባዕዳን የሉም ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

4 በአዲሱ ቃል ኪዳን አማካኝነት ከአምላክ ጋር ልዩ ዝምድና ያለው ብሔር ሥጋዊ እስራኤል መሆኑ ቀርቶ የተቀቡ ክርስቲያኖች ጉባኤ ሆኗል። ከዚህም የተነሳ ይህ ብሔር ‘የአምላክ እስራኤል’ ተብሎ ለመጠራት በቃ። (ገላ. 6:16) ጳውሎስ በገለጸው መሠረት በዚህ አዲስ ብሔር ውስጥ “ግሪካዊ ወይም አይሁዳዊ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ ባዕድ፣ እስኩቴስ፣ ባሪያ፣ ነፃ ሰው ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነገር ነው፤ እንዲሁም በሁሉም ነው።” (ቆላ. 3:11) በመሆኑም ከዚህ አንጻር በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ባዕዳን የሉም ማለት ይቻላል።

5, 6. (ሀ) ኢሳይያስ 61:5, 6ን በተመለከተ ምን ጥያቄ ሊነሳ ይችላል? (ለ) ኢሳይያስ የጠቀሳቸው “የይሖዋ ካህናት” እና “ባዕዳን” እነማን ናቸው? (ሐ) እነዚህን ሁለት ቡድኖች የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው?

5 በአንጻሩ ግን አንድ ሰው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ፍጻሜ እያገኘ ያለ ትንቢት የያዘውን ኢሳይያስ ምዕራፍ 61ን ይጠቅስ ይሆናል። ቁጥር 6 “የይሖዋ ካህናት” ሆነው ስለሚያገለግሉ ሰዎች ይናገራል። ይሁንና ቁጥር 5 ላይ ‘ከካህናቱ’ ጋር ስለሚተባበሩና አብረዋቸው ስለሚሠሩ “ባዕዳን” ተጠቅሶ እናገኛለን። የዚህ ሐሳብ ትርጉም ምንድን ነው?

6 “የይሖዋ ካህናት” የተባሉት “በመጀመሪያው ትንሣኤ” የሚካፈሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደሆኑ እንረዳለን፤ ደግሞም “የአምላክና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር ነገሥታት ሆነው ለአንድ ሺህ ዓመት ይገዛሉ።” (ራእይ 20:6) ከዚህ በተጨማሪ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ብዙ ታማኝ ክርስቲያኖች አሉ። ይሁንና እነዚህ ሰዎች በሰማይ ከሚያገለግሉት ጋር አብረው የሚሠሩና ከእነሱ ጋር የሚቀራረቡ ሲሆን በምሳሌያዊ አነጋገር ባዕዳን ናቸው። ‘የይሖዋን ካህናት’ በደስታ በመደገፍና ከእነሱ ጋር አብረው በመሥራት ‘አራሾች’ እና ‘የወይን አትክልተኞች’ ሆነው የሚያገለግሉ ያህል ነው። አዎ፣ ሰዎችን በመንከባከብና በመሰብሰብ ለአምላክ ክብር የሚያመጣ መንፈሳዊ ፍሬ በማፍራቱ ሥራ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። በእርግጥም ቅቡዓኑም ሆኑ “ሌሎች በጎች” አምላክን ለዘላለም የማገልገል ፍላጎት ያላቸውን ቅን ግለሰቦች ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ፤ እንዲሁም በፍቅር እረኝነት ያደርጉላቸዋል።—ዮሐ. 10:16

እንደ አብርሃም ያሉ “ጊዜያዊ ነዋሪዎች”

7. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች አብርሃምንና ጥንት የኖሩ ሌሎች ታማኝ ሰዎችን የሚመስሉት በምን መንገድ ነው?

7 በፊተኛው የጥናት ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው  እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚህ የሰይጣን ክፉ ዓለም ውስጥ እንደ ባዕዳን ወይም ጊዜያዊ ነዋሪዎች ናቸው። በዚህ ረገድ አብርሃምን ጨምሮ በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ ሰዎችን ይመስላሉ፤ እነሱን በተመለከተ “በምድሩም ላይ እንግዶችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች” ነበሩ ተብሏል። (ዕብ. 11:13) ወደፊት የምናገኘው ተስፋ ምንም ይሁን ምን አብርሃም ከይሖዋ ጋር የነበረው ዓይነት ዝምድና የመመሥረት አጋጣሚ አለን። ያዕቆብ “‘አብርሃም በይሖዋ አመነ፤ እንደ ጽድቅም ተቆጠረለት’ . . . እሱም ‘የይሖዋ ወዳጅ’ ለመባል በቃ” ሲል ገልጿል።—ያዕ. 2:23

8. አብርሃም ምን ተስፋ ተሰጥቶት ነበር? ተስፋው ፍጻሜ ማግኘቱን በተመለከተ ምን እምነት ነበረው?

8 አምላክ በአብርሃምና በዘሮቹ አማካኝነት አንድ ብሔር ብቻ ሳይሆን የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደሚባረኩ ቃል ገብቷል። (ዘፍጥረት 22:15-18ን አንብብ።) አምላክ የገባው ይህ የተስፋ ቃል ፍጻሜውን የሚያገኘው ገና ወደፊት ቢሆንም አብርሃም ተስፋው እንደሚፈጸም እስከ መጨረሻው ድረስ እርግጠኛ ነበር። ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ዕድሜውን ያሳለፈው ቤተሰቡን ይዞ ከቦታ ወደ ቦታ በመንከራተት ነበር። በዚህ ሁሉ ጊዜ አብርሃም ከይሖዋ ጋር የነበረውን ወዳጅነት ጠብቆ ኖሯል።

9, 10. (ሀ) አብርሃም የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) ለሰዎች የትኛውን ግብዣ ማቅረብ እንችላለን?

9 አብርሃም ተስፋው ተፈጽሞ ለማየት ምን ያህል ጊዜ መጠበቅ እንዳለበት ባያውቅም እንኳ ለይሖዋ የነበረው ፍቅርና ታማኝነት ተዳክሞ አያውቅም። ዓይኑ ተስፋው ላይ አነጣጥሮ ነበር፤ በአንድ አገር ውስጥ ቋሚ ነዋሪ ሆኖ አልተቀመጠም። (ዕብ. 11:14, 15) የአብርሃምን ምሳሌ መከተላችን ምንኛ ጥበብ ነው! እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ቀላል ሕይወት እንመራለን እንዲሁም ለቁሳዊ ንብረቶች፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ ለማግኘት ወይም ስለምንሰማራበት የሥራ ዓይነት ከልክ በላይ አንጨነቅም። በቅርቡ በሚያከትም ሥርዓት ውስጥ ሰዎች የተደላደለ ሕይወት የሚሉትን ለማግኘት ምን አደከመን? ለጊዜው ብቻ ከሚቆይ ነገር ጋር ከልክ በላይ ለምን ቁርኝት እንፈጥራለን? እንደ አብርሃም ሁሉ እኛም እጅግ የተሻለ ነገር ለማግኘት እየተጠባበቅን ነው። ተስፋችን እስኪፈጸም ድረስ በትዕግሥት የመጠባበቅ ዝንባሌ ለማሳየት ፈቃደኞች ነን።—ሮም 8:25ን አንብብ።

ልክ እንደ አብርሃም አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ፍጻሜ ላይ ምንጊዜም ትኩረት ማድረግ ትችላለህ?

10 ይሖዋ በአብርሃም ዘር አማካኝነት በረከት እንዲያገኙ በሁሉም ብሔራት ውስጥ ያሉ ሰዎችን አሁንም እየጋበዘ ነው። በመንፈስ የተቀቡት “የይሖዋ ካህናት” እና “ባዕዳን” የሆኑት ሌሎች በጎች ደግሞ ይህን ግብዣ ከ600 በሚበልጡ ቋንቋዎች በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች እያዳረሱ ነው።

ከብሔራዊ ድንበሮች ባሻገር ተመልከቱ

11. ሰለሞን እስራኤላውያን ላልሆኑ ሰዎች ምን አመለካከት ነበረው?

11 ቤተ መቅደሱ በ1026 ዓ.ዓ. በተመረቀበት ወቅት ይሖዋ ለአብርሃም ከገባው የተስፋ ቃል ጋር በሚስማማ ሁኔታ ሰለሞን በሁሉም ብሔራት ውስጥ ያሉ ሰዎች ለይሖዋ ውዳሴ በማቅረብ እንደሚካፈሉ ተናግሯል። ሰለሞን ባቀረበው ከልብ የመነጨ ጸሎት ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ፣ ግን ከስምህ ታላቅነት የተነሣ ከሩቅ የመጣ የባዕድ አገር ሰው ቢኖር፣ ሰዎች ከሩቅ የሚመጡት ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ጠንካራዪቱ እጅህ፣ ስለ ተዘረጋችው ክንድህ ሰምተው ነውና፤ እንግዳው መጥቶ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢጸልይ፣ አንተ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የጠየቀህንም ሁሉ ፈጽምለት፤ ይኸውም የምድር ሕዝቦች ሁሉ ስምህን ዐውቀው፣ ሕዝብህ እስራኤል አንተን እንደሚፈሩት ሁሉ እንዲፈሩህ [ነው]።”—1 ነገ. 8:41-43

12. አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን እንደ እንግዳ ወይም እንደ ‘ባዕድ’ የሚቆጥሯቸው ለምንድን ነው?

12 አንድ ሰው ባዕድ የሚባለው፣ በሰው አገር የሚኖር ከሆነ አሊያም የአንድ ማኅበረሰብ ወይም ቡድን ክፍል ሳይሆን ከዚያ ጋር ተቀላቅሎ የሚኖር ከሆነ ነው። ይህ የይሖዋ ምሥክሮችን ሁኔታ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። ከምንም በላይ ድጋፍ የሚሰጡት በሰማይ ለተቋቋመው መስተዳድር ይኸውም በክርስቶስ ለሚመራው የአምላክ መንግሥት ነው። በመሆኑም አንዳንድ ሰዎች ዛሬ ካለው ኅብረተሰብ ጋር ፈጽሞ የማይገጥሙ አድርገው ቢመለከቷቸውም እንኳ በፖለቲካ ጉዳዮች ረገድ ፍጹም ገለልተኛ አቋም ይይዛሉ።

በይሖዋ ዓይን ማናቸውም ባዕዳን አይደሉም

13. (ሀ) ባዕድ የሚለው ቃል በአመዛኙ የአመለካከት ጉዳይ ነው ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው? (ለ) ይሖዋ መጀመሪያ በነበረው ዓላማ ውስጥ ባዕድ የሚለው ሐሳብ ተካትቶ ነበር? አብራራ።

 13 አብዛኛውን ጊዜ፣ ባዕድ የሆኑ ሰዎች እነሱ ያሉበት አናሳ ቡድን ባሉት የጋራ ባሕርያት ተለይተው ይታወቃሉ። ይህም የሚናገሩት ቋንቋ፣ ባሕላቸው፣ አካላዊ ቁመናቸው አልፎ ተርፎም አለባበሳቸው ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ እነሱን ለይተው ከሚያሳውቋቸው ከእነዚህ ባሕርያት ይልቅ የየትኛውም ብሔር አባል ቢሆኑ ከሌሎች ሰዎች ሁሉ ጋር የሚያመሳስሏቸው ነገሮች ይበልጥ ሚዛን ይደፋሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ አንድ ሰው እንደ ባዕድ የሚታየው በአንዳንድ ነገሮች ከሌሎች የተለየ ስለሆነ ብቻ ነው። ከእነዚህ በእውን ካሉ ወይም ምናባዊ ከሆኑ ልዩነቶች ባሻገር መመልከት ስንችል “ባዕድ” የሚለው ቃል ያን ያህል ትርጉም አይኖረውም። በምድር ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ወይም መንግሥት የሚመሩ ቢሆኑ ኖሮ ቃሉን ከፖለቲካ አንጻር ስናየው ባዕድ ሊባል የሚችል ሰው አይኖርም ማለት ነው። እንዲያውም ይሖዋ መጀመሪያ የነበረው ዓላማ ሰዎች በአጠቃላይ በአንድ አገዛዝ ይኸውም በእሱ አገዛዝ ሥር እንደ አንድ ቤተሰብ ኅብረት እንዲኖራቸው ነበር። ታዲያ በምድር ዙሪያ በተለያዩ ብሔራት ውስጥ ያሉ ሰዎች ሌሎችን እንደ ባዕድ ማየታቸውን ሊያቆሙ ይችላሉ?

14, 15. የ⁠ይሖዋ ምሥክሮች በቡድን ደረጃ ሊሳካላቸው የቻለው ነገር ምንድን ነው?

14 ራስ ወዳድ በሆነና ብሔርተኝነት በሚታይበት ዓለም ውስጥ ከብሔራዊ ድንበሮች ባሻገር መመልከት የሚችሉ ደግሞም የሚመለከቱ ሰዎች ማግኘት በጣም ያስደስታል። ጭፍን ጥላቻን ማሸነፍ እንደሚከብድ የታወቀ ነው። ሲ ኤን ኤን የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ መሥራች የሆነው ቴድ ተርነር ከተለያዩ አገሮች ከመጡ ጥሩ የሙያ ብቃት ካላቸው ሰዎች ጋር በሥራ ያሳለፈውን ጊዜ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ከእነዚህ ሰዎች ጋር መገናኘት በዓይነቱ ልዩ የሆነ አጋጣሚ ነው። ከሌሎች አገሮች የመጡትን እነዚህን ሰዎች የማያቸው እንደ ‘ባዕድ’ ሳይሆን የአንድ ፕላኔት ዜጎች አድርጌ ነው። ‘ባዕድ’ የሚለው ቃል ነቀፋ አዘል ነው የሚል አመለካከት አዳበርኩ፤ ደግሞም በሲ ኤን ኤን ውስጥ ቃሉ በሚዲያ ላይም ሆነ ቢሮ ውስጥ እርስ በርስ ሲነጋገሩ እንዳይጠቀሙበት ደንብ አወጣሁ። በዚህ ቃል ፋንታ ‘ዓለም አቀፍ’ የሚለው ቃል ይሠራበታል።”

15 በዓለም ዙሪያ በሚገኙ አገሮች በቡድን ደረጃ የአምላክን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቁት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። ነገሮችን ይሖዋ በሚያይበት መንገድ ማየት በመማራቸው በአስተሳሰብም ሆነ በስሜት ብሔራዊ ድንበሮችን ማፈራረስ ችለዋል። በተለያዩ ብሔራት ውስጥ የታቀፉ ሰዎችን በተሳሳተ መንገድ፣ በጥርጣሬ ወይም ከናካቴው በጥላቻ ዓይን ከመመልከት ይልቅ እነዚህ ሰዎች ያሏቸውን ልዩ ልዩ ባሕርያትና ችሎታዎች እንደ ውበት በመቁጠር በአድናቆት መመልከትን ተምረዋል። በዚህ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ስላገኙት ስኬት አስበህ ታውቃለህ? ደግሞስ ከሌሎች ጋር ባለህ ግንኙነት ረገድ በግለሰብ ደረጃ ምን ጥቅም እንዳስገኘልህ አስተውለሃል?

 ባዕዳን የሌሉበት ዓለም

16, 17. የ⁠ራእይ 16:16 እና የ⁠ዳንኤል 2:44 ፍጻሜ ለአንተ በግለሰብ ደረጃ ምን ትርጉም ይኖረዋል?

16 በቅርቡ በአሁኑ ጊዜ ያሉ ብሔራት በሙሉ የአምላክን አገዛዝ በመቃወም በሚያደርጉት የመጨረሻ ጦርነት ከኢየሱስ ክርስቶስና በሰማይ ካለው የእሱ ሠራዊት ጋር ይፋለማሉ፤ ይህ ጦርነት “በዕብራይስጥ ሐር ማጌዶን” ተብሎ ይጠራል። (ራእይ 16:14, 16፤ 19:11-16) ከዛሬ 2,500 ዓመታት በፊት ነቢዩ ዳንኤል ከአምላክ ዓላማ ጋር የሚጋጩ ሰብዓዊ መንግሥታት ምን እንደሚደርስባቸው በመንፈስ ተመርቶ ትንቢት ተናግሯል፤ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ዳን. 2:44

17 የዚህ ትንቢት ፍጻሜ ለአንተ በግለሰብ ደረጃ ምን ትርጉም እንዳለው መገመት ትችላለህ? በአሁኑ ጊዜ በሆነ መንገድ ሰው ሁሉ እንደ ባዕድ እንዲቆጠር ያደረጉ ሰው ሠራሽ ብሔራዊ ድንበሮች ይወገዳሉ። በመልክ ወይም በሌሎች አካላዊ ሁኔታዎች ሊኖሩ የሚችሉ ልዩነቶች በሙሉ በአምላክ የፍጥረት ሥራ ውስጥ የሚታየውን ማራኪ ልዩነት ከማሳየት ያለፈ ትርጉም አይኖራቸውም። እንዲህ የመሰለው ድንቅ ተስፋ ሁላችንም ፈጣሪያችን፣ ይሖዋ አምላክን አቅማችን በፈቀደው መጠን ማወደሳችንንና ማክበራችንን እንድንቀጥል ሊያነሳሳን ይገባል።

ሰው ሠራሽ ብሔራዊ ድንበሮች በማይኖሩበትና “ባዕድ” የሚለው ቃል የተረሳ በሚሆንበት ጊዜ ለመኖር አትጓጓም?

18. እንደ “ባዕድ” መተያየት ሊቀር እንደሚችል የሚያሳይ በቅርቡ ምን የተከናወነ ነገር አለ?

18 በመላው ዓለም ላይ እንዲህ ዓይነት ለውጥ ይመጣል ብሎ ማመን የማይመስል ነገር ነው? በፍጹም። እንዲያውም ይፈጸማል ብሎ ማመን ሙሉ በሙሉ ምክንያታዊ ነው። በመካከላቸው ያሉት ሰዎች የምን አገር ዜጋ እንደሆነ ያን ያህል ትኩረት በማይሰጡት በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ “ባዕድ” የሚለው ቃል በአሁኑ ጊዜ እንኳ ትርጉም እያጣ መጥቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለሥራው አመራር የመስጠቱን ሂደት ለማቅለልና የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩን ሥራ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን ሲባል በርከት ያሉ አነስተኛ ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንዲዋሃዱ ተደርጓል። (ማቴ. 24:14) ሕግ ነክ መሥፈርቶች እስከሚፈቅዱት ድረስ ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ በተዋሃዱበት ወቅት ብሔራዊ ድንበሮች ምንም ቦታ አልተሰጣቸውም። ይህም ይሖዋ ዙፋን ላይ ያስቀመጠው ገዢ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብዓዊ ድንበሮችን እያፈራረሰ መሆኑን የሚያሳይ ሌላ ተጨባጭ ማስረጃ ነው፤ በቅርቡ ደግሞ ኢየሱስ ‘ድሉን ያጠናቅቃል!’—ራእይ 6:2

19. የእውነት ንጹሕ ቋንቋ ምን ነገር ማስገኘት ችሏል?

19 የይሖዋ ምሥክሮች ከብዙ ብሔራት የመጡ እንደመሆናቸው መጠን ቋንቋቸው የተለያየ ቢሆንም የእውነትን ንጹሕ ቋንቋ ወይም ልሳን ይናገራሉ። ይህ ደግሞ ፈጽሞ ሊንኮታኮት የማይችል ጠንካራ አንድነት አስገኝቶላቸዋል። (ሶፎንያስ 3:9ን በ1954 ትርጉም አንብብ።) የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ቢሆንም ከዚያ ተለይተው የሚኖሩ አንድ ዓለም አቀፍ ቤተሰብ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ አንድነቱን ጠብቆ የሚኖረው ይህ ቤተሰብ ለሚመጣው ዓለም ናሙና ነው፤ ያኔ ባዕድ የሚባል ነገር አይኖርም። በዚያን ጊዜ እገሌ ከእገሌ ሳይል በሕይወት ያለ ሰው ሁሉ ከላይ የተጠቀሰው ጽሑፍ ያሰፈረውን ቃል እውነተኝነት በደስታ ይቀበላል፦ “የሰው ዘሮች በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ወንድማማቾች ናቸው።”—የሰው ዘሮች (እንግሊዝኛ)