“ጊዜያዊ ነዋሪዎች” እንደመሆናችን መጠን አቋማችንን ጠብቀን መኖር
“መጻተኞችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች እንደመሆናችሁ መጠን . . . [ከሥጋዊ] ምኞቶች ምንጊዜም እንድትርቁ አሳስባችኋለሁ።”—1 ጴጥ. 2:11
1, 2. ጴጥሮስ “ምርጦች” ያለው እነማንን ለማመልከት ነበር? “ጊዜያዊ ነዋሪዎች” ብሎ የጠራቸውስ ለምንድን ነው?
ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ ከ30 ዓመት ገደማ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ “በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢቲኒያ ተበትነው ለሚገኙ ጊዜያዊ ነዋሪዎች ለሆኑ የአምላክ ምርጦች” ደብዳቤ ጽፎ ነበር። (1 ጴጥ. 1:1) ጴጥሮስ “ምርጦች” የሚለውን ቃል የተጠቀመው እንደ እሱ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡትንና ‘ለሕያው ተስፋ እንደ አዲስ ተወልደው’ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የመግዛት መብት የተሰጣቸውን ሰዎች ለማመልከት እንደነበር ግልጽ ነው። (1 ጴጥሮስ 1:3, 4ን አንብብ።) ይሁንና ከዚያ ቀጥሎ እነዚህን ምርጦች “መጻተኞችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች” ብሎ የጠራቸው ለምንድን ነው? (1 ጴጥ. 2:11) ደግሞስ በዓለም ዙሪያ ካሉ ንቁ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ከ650 ውስጥ 1 ክርስቲያን ብቻ በመንፈስ ተቀብቶ የተመረጠ እንደሆነ በሚነገርበት በዛሬው ጊዜ ይህ አባባል ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
2 በመጀመሪያው መቶ ዘመን “ጊዜያዊ ነዋሪዎች” የሚለውን አባባል ለቅቡዓን ክርስቲያኖች መጠቀም ተገቢ ነበር። በዛሬው ጊዜ በሕይወት እንደሚገኙት የዚህ ቡድን ቀሪ አባላት ሁሉ እነሱም በዚህ ምድር ላይ የሚኖሩት በቋሚነት አልነበረም። በመንፈስ የተቀባው ‘የታናሹ መንጋ’ ክፍል አባል የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ “እኛ ግን የሰማይ ዜጎች ነን፤ ከዚያ የሚመጣውንም አዳኝ ይኸውም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በጉጉት እንጠባበቃለን” ሲል ገልጿል። (ሉቃስ 12:32፤ ፊልጵ. 3:20) ቅቡዓን ክርስቲያኖች “የሰማይ ዜጎች” በመሆናቸው በሚሞቱበት ጊዜ ምድርን ትተው በሰማይ እጅግ የላቀና የማይሞት ሕይወት ያገኛሉ። (ፊልጵስዩስ 1:21-23ን አንብብ።) በመሆኑም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው ምድር ላይ ቃል በቃል “ጊዜያዊ ነዋሪዎች” ናቸው ሊባል ይችላል።
3. ስለ “ሌሎች በጎች” ምን ጥያቄ ይነሳል?
3 ይሁንና ‘ስለ ሌሎች በጎችስ’ ምን ማለት ይቻላል? (ዮሐ. 10:16) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በምድር ላይ ቋሚ ነዋሪዎች የመሆን የተረጋገጠ ተስፋ አላቸው። በእርግጥም ምድር ለዘላለም የሚኖሩባት ቤታቸው ትሆናለች! ያም ሆኖ በአሁኑ ጊዜ እነሱም ጊዜያዊ ነዋሪዎች ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ። እንዴት?
‘ፍጥረት ሁሉ በመቃተት ላይ ይገኛል’
4. የዓለም መሪዎች ምን ነገር የማስቀረት አቅም የላቸውም?
4 የሰይጣን ክፉ ሥርዓት እንዲቀጥል እስከተፈቀደለት ድረስ ክርስቲያኖችን ጨምሮ ሁሉም ሰው፣ ሰይጣን በይሖዋ ላይ በማመፁ ምክንያት የመጣው መከራ ገፈት ቀማሽ መሆኑ አይቀርም። ሮም 8:22 “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ በአንድነት ሆኖ በመቃተትና አብሮ በመሠቃየት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን” ይላል። የዓለም መሪዎች፣ የሳይንስ ሊቃውንትና በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች በቅንነት ተነሳስተው ምንም ያህል ጥረት ቢያደርጉም ይህን ማስቀረት አይችሉም።
5. ከ1914 አንስቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምን እርምጃ ወስደዋል? ለምንስ?
5 በመሆኑም ከ1914 አንስቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክ ንጉሥ አድርጎ ለሾመው ለክርስቶስ ኢየሱስ ለመገዛት በፈቃደኝነት መርጠዋል። እነዚህ ሰዎች የሰይጣን ዓለም ክፍል መሆን አይፈልጉም። እንዲሁም የሰይጣንን ዓለም ለመደገፍ ፈቃደኞች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማራመድ ሕይወታቸውንም ሆነ ጥሪታቸውን ለዚሁ ዓላማ ያውላሉ።—ሮም 14:7, 8
6. የይሖዋ ምሥክሮች መጻተኞች ሊባሉ የሚችሉት እንዴት ነው?
6 አዎ፣ ከ200 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ሕግ አክባሪ ዜጎች ናቸው፤ ይሁንና በየትኛውም ቦታ ቢሆን መጻተኛ ሆነው ይኖራሉ። በየወቅቱ በሚነሱ አወዛጋቢ የሆኑ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ረገድ ፍጹም ገለልተኛ አቋም አላቸው። በአሁኑ ጊዜም እንኳ አምላክ የሚያመጣው አዲስ ዓለም ዜጎች እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ። በዚህ ብልሹ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ጊዜያዊ ነዋሪዎች ሆነው የሚቆዩበት ጊዜ ወደማብቂያው በፍጥነት እየተቃረበ በመሆኑ እጅግ ደስተኞች ናቸው።
7. የአምላክ አገልጋዮች ቋሚ ነዋሪዎች የሚሆኑት እንዴት ነው? የሚኖሩትስ የት ነው?
7 በቅርቡ ክርስቶስ ሥልጣኑን ተጠቅሞ የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት ይደመስሳል። የክርስቶስ ፍጹም አገዛዝ ለኃጢአትና ለሐዘን መንስኤ የሆኑትን ነገሮች በሙሉ ከምድረ ገጽ ያጠፋል። በይሖዋ ሉዓላዊ አገዛዝ ላይ የሚያምፁ፣ በዓይን የሚታዩም ሆኑ የማይታዩ ጠላቶችን በሙሉ ያስወግዳል። የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ቋሚ ነዋሪዎች የመሆን አጋጣሚ ያገኛሉ። (ራእይ 21:1-5ን አንብብ።) በዚህ ጊዜ ፍጥረት በሙሉ ቃል በቃል “ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት” ያገኛል።—ሮም 8:21
ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ይጠበቃል?
8, 9. ጴጥሮስ ‘ከሥጋዊ ምኞቶች ራቁ’ ሲል ምን ማለቱ እንደነበር ግለጽ።
8 ጴጥሮስ ክርስቲያኖች የሚጠበቅባቸውን ነገር እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ መጻተኞችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች እንደመሆናችሁ መጠን ከነፍስ ጋር ከሚዋጉት ሥጋዊ ምኞቶች ምንጊዜም እንድትርቁ አሳስባችኋለሁ።” (1 ጴጥ. 2:11) ይህ ማሳሰቢያ በዋነኝነት የተሰጠው ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ቢሆንም የኢየሱስ ንብረት ለሆኑት ሌሎች በጎችም በእኩል ደረጃ ይሠራል።
9 አንዳንድ ምኞቶችን ፈጣሪ ካወጣው ሕግ ጋር በሚስማማ መንገድ ማርካት በራሱ ምንም ስህተት የለውም። እንዲያውም ሕይወታችን ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ያደርጋል። ለምሳሌ በምንበላውና በምንጠጣው ነገር መደሰት፣ መንፈስ በሚያድሱ እንቅስቃሴዎች መካፈል እንዲሁም ከጥሩ ጓደኞቻችን ጋር አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ ተፈጥሯዊ የሆኑ ምኞቶች ናቸው። ሌላው ቀርቶ ከትዳር ጓደኛ ጋር የፆታ ስሜትን ማርካት ተገቢና ተፈጥሯዊ ነው። (1 ቆሮ. 7:3-5) ይሁንና ጴጥሮስ ስለ “ሥጋዊ ምኞቶች” ሲናገር እየጠቀሰ የነበረው ‘ከነፍስ ጋር የሚዋጉትን’ ምኞቶች ብቻ ነበር። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ከሥጋ ፍትወቶች” (የ1980 ትርጉም) ወይም “የኃጢአት ምኞቶች” (ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን) ብለው በመተርጎም ቃሉ የሚያስተላልፈውን ሐሳብ ግልጽ አድርገዋል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አንድ ሰው ከይሖዋ ዓላማ ጋር የሚጋጩና ከአምላክ ጋር የመሠረተውን ጥሩ ዝምድና ሊያሻክሩ የሚችሉ ሥጋዊ ምኞቶቹን በሙሉ መቆጣጠር ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ግን አንድ ክርስቲያን ነፍሱን በሕይወት ለማቆየት ያለው ተስፋ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል።
10. ክርስቲያኖች የዓለም ክፍል እንዲሆኑ ለማድረግ ሰይጣን የሚጠቀምባቸው አንዳንድ ዘዴዎች ምንድን ናቸው?
10 የሰይጣን ዓላማ እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚህ ሥርዓት ውስጥ “ጊዜያዊ ነዋሪዎች” ነን የሚል አመለካከት ይዘው ለመኖር ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ ማዳከም ነው። ቁሳዊ ሀብት ያለው ማራኪነት፣ የሥነ ምግባር ብልግና ያለው መስህብ፣ ሥልጣን ያለው አጓጊነት፣ “ከሰው ሁሉ በፊት” ለመሆን መጓጓትና ብሔራዊ ስሜት ያለው ኃይል የሰይጣን ወጥመዶች ናቸው፤ እኛም በዚህ መልኩ ልናያቸው ይገባል። ከእነዚህ መጥፎ የሥጋ ምኞቶች ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ የሰይጣን ክፉ ዓለም ክፍል መሆን እንደማንፈልግ በግልጽ እናሳያለን። በዚህ ዓለም ውስጥ የምንኖረው ለጊዜው ብቻ እንደሆነ አኗኗራችን ይመሠክራል። ከልባችን የምንፈልገውና የምንጓጓለት ነገር ጽድቅ በሚሰፍንበት የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ቋሚ መኖሪያ ማግኘት ነው።
መልካም ምግባር
11, 12. አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ለውጭ አገር ዜጎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል? ስለ ይሖዋ ምሥክሮችስ ምን ማለት ይቻላል?
11 ጴጥሮስ “ጊዜያዊ ነዋሪዎች” ከሆኑት ክርስቲያኖች የሚጠበቀውን ነገር ማብራራቱን በመቀጠል ቁጥር 12 ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ምንም እንኳ ክፉ አድራጊዎች እንደሆናችሁ አድርገው ቢናገሩም አምላክ ለመመርመር በሚመጣበት ቀን እነሱ ራሳቸው በዓይናቸው ባዩት መልካም ሥራችሁ የተነሳ አምላክን እንዲያከብሩ በአሕዛብ መካከል መልካም ምግባር ይዛችሁ ኑሩ።” በሰው አገር ውስጥ ጊዜያዊ ነዋሪዎች ሆነው የሚኖሩ የውጭ ዜጎች አንዳንድ ጊዜ ትችት ይሰነዘርባቸዋል። ከጎረቤቶቻቸው የተለዩ ስለሆኑ ብቻ ክፉ ሰዎች እንደሆኑ ተደርገው ሊታዩም ይችላሉ። ንግግራቸው፣ ተግባራቸው፣ አለባበሳቸው አልፎ ተርፎም መልካቸው በተወሰነ መጠን ከሌሎች ሊለይ ይችላል። ይሁን እንጂ መልካም ነገሮችን የሚያከናውኑ ከሆነ ማለትም መልካም ምግባር ካላቸው ከሌሎች የተለዩ ናቸው ተብሎ የሚሰነዘርባቸው ትችት መሠረተ ቢስ እንደሆነ ይረጋገጣል።
12 በተመሳሳይም እውነተኛ ክርስቲያኖች አነጋገርንና የመዝናኛ ምርጫን በመሳሰሉ ነገሮች ረገድ ከብዙኃኑ የተለዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ፣ አለባበሳቸውና አጋጌጣቸው በኅብረተሰቡ ውስጥ ካሉ ከአብዛኞቹ ሰዎች ለየት ብለው እንዲታዩ ያደርጋቸዋል። እነዚህን በመሳሰሉ ጉዳዮች ከሌሎች የተለዩ መሆናቸው ትክክለኛ መረጃ የሌላቸው ግለሰቦች ‘መጥፎ ሰዎች ናቸው’ የሚል ነቀፋ በእነሱ ላይ እንዲሰነዝሩ አነሳስቷቸዋል። ሌሎች ሰዎች ደግሞ አኗኗራቸውን በመመልከት ያመሰግኗቸዋል።
13, 14. ‘ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ የተረጋገጠው’ እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
13 አዎ፣ መልካም ምግባር ማሳየት መሠረተ ቢስ የሆኑ ትችቶች እንዲከስሙ ሊረዳ ይችላል። ለአምላክ ፍጹም ታዛዥነት ያሳየው ኢየሱስ እንኳ በሐሰት ተወንጅሏል። አንዳንዶች “ሆዳምና ለወይን ጠጅ ያደረ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኃጢአተኞች ወዳጅ” ብለውት ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አምላክን እያገለገለ በጥበብ መመላለሱ ኃጢአተኛ ነው በሚል የተሰነዘረበት ክስ ውድቅ እንዲሆን አስችሏል። ኢየሱስ “ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል” ብሏል። (ማቴ. 11:19) ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ በሴልተርስ፣ ጀርመን በሚገኘው ቤቴል ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞችንና እህቶችን አንዳንድ ጎረቤቶቻቸው ከሰው የማይገጥሙ እንደሆኑ አድርገው ተመልክተዋቸው ነበር። የአካባቢው ከንቲባ ግን እንዲህ ሲሉ ለእነሱ ጥብቅና ቆመዋል፦ “በዚያ የሚያገለግሉት ምሥክሮች የራሳቸው የሆነ አኗኗር አላቸው፤ ሆኖም አኗኗራቸው በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሕይወት በምንም መልኩ አያውክም።”
14 በሞስኮ፣ ሩሲያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተም በቅርቡ ተመሳሳይ ሐሳብ ተሰንዝሯል። በርካታ መጥፎ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ የሚል የሐሰት ክስ ተሰንዝሮባቸው ነበር። ከዚያም በሰኔ 2010 በስትራዝቡርግ፣ ፈረንሳይ የሚገኘው የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ይህን ብይን አስተላልፏል፦ “ፍርድ ቤቱ፣ አመልካቹ ካለው የሃይማኖትና የመሰብሰብ ነፃነት መብት ጋር በተያያዘ [የሞስኮ ከተማ አስተዳደር] ጣልቃ ገብነት ትክክል እንዳልሆነ አረጋግጧል። በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ፍርድ ቤቶች አመልካቹ ማኅበረሰብ [በተከሰሰባቸው ይኸውም ቤተሰብን ይለያያሉ፣ የራስን ሕይወት ማጥፋትን ያበረታታሉ ወይም የሕክምና እርዳታን ያከላክላሉ እንደሚሉት ባሉ ጉዳዮች ጥፋተኝነቱን ለማረጋገጥ] ‘አግባብነት ያላቸውና በቂ የሆኑ’ ማስረጃዎችን አላቀረቡም።” በመሆኑም “የአገሪቱ ፍርድ ቤቶች የጣሉት ማዕቀብ በዚያ የሚሠራበት ሕግ የማያወላዳ ከመሆኑ አንጻር ከልክ በላይ ጥብቅ ነው፤ ከዚህም ሌላ አግባብ ያለው ዓላማ ይዘው ተነስተዋል ቢባል እንኳ ማዕቀቡ ፈጽሞ ተመጣጣኝ አይደለም።”
ለባለሥልጣናት በአግባቡ መገዛት
15. በዓለም ዙሪያ የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖች የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ይከተላሉ?
15 ጴጥሮስ፣ ክርስቲያኖች ሊያሟሉት የሚገባ አንድ ተጨማሪ ብቃት የጠቀሰ ሲሆን በሞስኮም ሆነ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ብቃት አሟልተዋል። ጴጥሮስ “ለጌታ ብላችሁ ለሰብዓዊ ባለሥልጣናት ሁሉ ተገዙ፦ ለንጉሥ ተገዙ፣ ከሁሉ በላይ ነውና፤ ለገዥዎችም ቢሆን ተገዙ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥ. 2:13, 14) እውነተኛ ክርስቲያኖች የዚህ ክፉ ዓለም ክፍል ባይሆኑም የመንግሥት ባለሥልጣናት ‘አንጻራዊ ሥልጣን እንዳላቸው’ በመገንዘብ ጳውሎስ በሰጣቸው መመሪያ መሠረት ለእነሱ በፈቃደኝነት ይገዛሉ።—ሮም 13:1, 5-7ን አንብብ።
16, 17. (ሀ) መንግሥትን እንደማንቃወም የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ? (ለ) አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎች ምን ብለዋል?
16 የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ሥርዓት ውስጥ እንደ “ጊዜያዊ ነዋሪዎች” የሚመላለሱ መሆናቸው ድምፃቸውን ሳያሰሙ ተቃውሟቸውን ከሚገልጹ ወገኖች ጋር ሊያስፈርጃቸው አይገባም፤ ከፖለቲካ ወይም ከማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሌሎች የሚያደርጉትን የግል ውሳኔ አይቃወሙም ወይም በውሳኔያቸው ጣልቃ አይገቡም። ከአንዳንድ የሃይማኖት ቡድኖች በተቃራኒ የይሖዋ ምሥክሮች ፖለቲካ ውስጥ ከመግባት ይቆጠባሉ። የመንግሥት ባለሥልጣናት በሚያወጧቸው ፖሊሲዎች ላይ ጫና ለማሳደር ጥረት አያደርጉም። ዓመፅ ለመቀስቀስ ወይም የመንግሥትን እንቅስቃሴ ለማዳከም ጥረት ያደርጋሉ ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው!
17 ጴጥሮስ “ንጉሥን አክብሩ” ብሎ ከሰጠው ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ ክርስቲያኖች ለሕዝብ ባለሥልጣናት ታዛዥ በመሆን ለእነሱ የሚገባውን አክብሮት ያሳያሉ። (1 ጴጥ. 2:17) የመንግሥት ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮችን በስጋት እንዲመለከቱ የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያት እንደሌለ የተናገሩባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ቀድሞ በብራንደንበርግ ግዛት የካቢኔ ሚኒስትር የነበሩትና በኋላ ደግሞ የጀርመን ፓርላማ አባል የሆኑት ጀርመናዊው የፖለቲካ ሰው ሽቴፋን ራይከ እንዲህ ብለዋል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች በማጎሪያ ካምፖችና በእስር ላይ እያሉ የነበራቸው አኗኗር ጥሩ ሥነ ምግባር እንዳላቸው ያሳየ ሲሆን እንዲህ ያለ ምግባር በዲሞክራሲ ላይ የተመሠረተ አንድ አገር በሕልውና እንዲቀጥል ከተፈለገ ምንጊዜም አስፈላጊ ነው፤ በዚህ ረገድ ኤስ ኤስን (የናዚ ወታደሮችን) በጽናት መቃወማቸውና አብረዋቸው ለታሰሩት ሰዎች ርኅራኄ ማሳየታቸው ተጠቃሽ ነው። በውጭ አገር ዜጎች ላይም ሆነ ለየት ያለ አመለካከት ወይም ፖለቲካዊ አቋም ባላቸው ሰዎች ላይ የሚፈጽመውን እየተባባሰ የመጣ የጭካኔ ድርጊት ታሳቢ በማድረግ [ምሥክሮቹ ያሏቸው] ጥሩ የሥነ ምግባር ደንቦች የአገራችን ዜጎች በሙሉ ሊያሳዩአቸው የሚገቡ ናቸው።”
ፍቅር ማሳየት
18. (ሀ) ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ማሳየታችን የሚጠበቅ ነገር የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች ምን ነገር አስተውለዋል?
18 ሐዋርያው ጴጥሮስ “ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ፤ አምላክን ፍሩ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥ. 2:17) የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት አላቸው፤ ይህም የእሱን ፈቃድ ለማድረግ ይበልጥ እንዲነሳሱ ያስችላቸዋል። በዓለም ዙሪያ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ባሉበት ማኅበር ውስጥ ታቅፈው በአንድ ዓላማ ይሖዋን በማገልገላቸው ደስተኞች ናቸው። በመሆኑም “ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር” ማሳየታቸው የሚጠበቅ ነገር ነው። የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች፣ ኅብረተሰቡ ራስ ወዳድነት በሚያንጸባርቅበት በዛሬው ጊዜ ምሥክሮቹ በሚያሳዩት የወንድማማች ፍቅር ይደነቃሉ። ለምሳሌ በአንድ የአሜሪካ የጉዞ ወኪል ውስጥ የምትሠራ አንዲት አስጎብኚ፣ በ2009 በጀርመን በተካሄደው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ከሌላ አገር ለመጡ ልዑካን ባሳዩት ፍቅርና አሳቢነት በእጅጉ ተደንቃለች። በአስጎብኚነት ባሳለፈቻቸው ዓመታት ሁሉ እንዲህ ያለ ነገር ተመልክታ እንደማታውቅ ተናግራለች። ከጊዜ በኋላ አንድ የይሖዋ ምሥክር “ስለ እኛ ትናገር የነበረው በአድናቆትና በደስታ ነበር” ሲል ገልጿል። አንተ በተገኘህበት ትልቅ ስብሰባ ላይ የይሖዋ ምሥክሮችን ሁኔታ ተመልክቶ በአድናቆት ሲናገር የሰማኸው ሰው አለ?
19. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት? ለምንስ?
19 ከላይ በተጠቀሱትም ሆነ በሌሎች መንገዶች የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ የሰይጣን ሥርዓት ውስጥ በእርግጥ “ጊዜያዊ ነዋሪዎች” መሆናቸውን አስመሥክረዋል። ደግሞም በዚህ አቋማቸው ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። በቅርቡ ጽድቅ በሰፈነበት የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ቋሚ ነዋሪዎች ለመሆን ጠንካራና እርግጠኛ የሆነ ተስፋ አላቸው። አንተስ ይህን ለማግኘት አትጓጓም?