ይሖዋን የሚወዱ ‘ዕንቅፋት የለባቸውም’
“ሕግህን የሚወዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ ዕንቅፋትም የለባቸውም።” —መዝ. 119:165
1. አንዲት ሯጭ የነበራት አመለካከት ተስፋ ላለመቁረጥ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ሊያሳይ የሚችለው እንዴት ነው?
ሜሪ ዴከር በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ከነበረችበት ጊዜ አንስቶ በዓለም ላይ የታወቀች ሯጭ ነበረች። በ1984 በተካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር በ3,000 ሜትር የፍጻሜ ሩጫ ላይ እንደምታሸንፍ ተጠብቆ ነበር። ሆኖም ውድድሩን ሳታጠናቅቅ ቀረች። የሌላ ሯጭ እግር አደናቅፏት ባፍጢሟ ተደፋች። ጉዳት የደረሰባት ሲሆን ከመሮጫው መም አንስተው ሲወስዷት እያለቀሰች ነበር። ይሁንና ሜሪ እጅ አልሰጠችም። ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አቋሟን አስተካክላ ወደ ውድድር የተመለሰች ከመሆኑም ሌላ በ1985 በአንድ ማይል የሴቶች ውድድር አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዘገበች።
2. እውነተኛ ክርስቲያኖች በሩጫ ውድድር ላይ ናቸው ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው? ዓላማችንስ ምን መሆን አለበት?
2 እኛም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በውድድር ላይ ይኸውም በምሳሌያዊ የሩጫ ውድድር ላይ ነን። የምንሮጥበት ዓላማ ለማሸነፍ ሊሆን ይገባል። የእኛ ሩጫ ለማሸነፍ ፈጣን መሆንን ከሚጠይቀው የአጭር ርቀት ውድድር የተለየ ነው። ደግሞም በተደጋጋሚ እየቆምን የምንሮጠው የሶምሶማ ዓይነት ሩጫ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለማሸነፍ ጽናትን ከሚጠይቀው የማራቶን ሩጫ ጋር ይመሳሰላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በአትሌቲክስ ውድድር ትታወቅ በነበረችው በቆሮንቶስ ከተማ ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሩጫ ውድድርን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በሩጫ ውድድር ሁሉም እንደሚሮጡ፣ ሽልማቱን ግን የሚያገኘው አንዱ ብቻ እንደሆነ አታውቁም? እናንተም ሽልማቱን እንድታገኙ በዚሁ ሁኔታ ሩጡ።”—1 ቆሮ. 9:24
3. የዘላለም ሕይወት ለማግኘት በሚደረገው ሩጫ ሁሉም ሯጮች አሸናፊ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ምሳሌያዊ ውድድር ላይ እንድንሮጥ ያሳስበናል። (1 ቆሮንቶስ 9:25-27ን አንብብ።) ሽልማቱ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ፣ ለቀሩት የውድድሩ ተካፋዮች ደግሞ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ነው። ከሌሎች የአትሌቲክስ ውድድሮች በተለየ ሁኔታ በዚህ ውድድር የተሳተፉና እስከ ፍጻሜው የጸኑ ሁሉ ሽልማቱን ያገኛሉ። (ማቴ. 24:13) ተወዳዳሪዎቹ ተሸናፊ የሚሆኑት በደንቡ መሠረት መሮጥ ካቃታቸው ወይም ሩጫውን ሳያጠናቅቁ ከቀሩ ብቻ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የዘላለም ሕይወት ሽልማት የሚያስገኘው ይህ ውድድር ብቻ ነው።
4. የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የምናደርገውን ሩጫ ፈታኝ የሚያደርግብን ምንድን ነው?
4 እስከ ውድድሩ ማብቂያ ድረስ መሮጥ ቀላል ነገር አይደለም። ሩጫው ራስን መገሠጽና የዓላማ ጽናት ይጠይቃል። አንድ ጊዜም እንኳ ሳይደናቀፍ ሩጫውን ማጠናቀቅ የቻለው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ሆኖም የእሱ ደቀ መዝሙር የሆነው ያዕቆብ፣ የክርስቶስ ተከታዮች ‘ሁሉ ብዙ ጊዜ ይሰናከላሉ’ ሲል ጽፏል። (ያዕ. 3:2) አዎ፣ የራሳችንም ሆነ የሌሎች አለፍጽምና በማናችንም ላይ እንቅፋት ሊፈጥርብን ይችላል። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ ተደናቅፈን ልንንገዳገድና ፍጥነታችንን ልንቀንስ እንችላለን። አልፎ ተርፎም ልንወድቅ እንችላለን፤ ይሁንና ተነስተን ሩጫችንን እንቀጥላለን። አንዳንዶች አወዳደቃቸው የከፋ በመሆኑ ተነስተው ሩጫቸውን እንዲቀጥሉ እርዳታ ማግኘት አስፈልጓቸዋል። በመሆኑም አንዴ ወይም በተደጋጋሚ ልንደናቀፍ አሊያም ልንወድቅ እንችላለን።—1 ነገ. 8:46
ብትደናቀፉም እንኳ ሩጫውን አታቋርጡ
5, 6. (ሀ) አንድ ክርስቲያን ‘ዕንቅፋት የለበትም’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? ‘እንዲነሳ’ የሚረዳውስ ምንድን ነው? (ለ) አንዳንዶች ከተደናቀፉ በኋላ ማንሰራራት የማይችሉት ለምንድን ነው?
5 “መደናቀፍ” ወይም “መውደቅ” የሚሉትን ቃላት አንድ ሰው ያለበትን መንፈሳዊ ሁኔታ ለመግለጽ በእኩል ደረጃ ትጠቀምባቸው ይሆናል። ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራባቸው እነዚህ ቃላት ሁልጊዜ ተመሳሳይ ትርጉም አላቸው ማለት አይደለም። ለአብነት ያህል፣ ምሳሌ 24:16 ምን እንደሚል ልብ በል፦ “ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣልና፤ ክፉዎች ግን በጥፋት ይወድቃሉ [“ይሰናከላሉ፣” NW]።”
6 ይሖዋ በእሱ የሚታመኑ ሰዎች ሊያገግሙ በማይችሉበት ሁኔታ እንዲደናቀፉ ወይም እንዲወድቁ ማለትም ማንሰራራት በማይችሉበት ሁኔታ መከራ እንዲደርስባቸው ወይም ከአምልኳቸው ወደኋላ እንዲሉ የሚያደርግ ነገር እንዲገጥማቸው አይፈቅድም። ይሖዋ እሱን በሙሉ ነፍሳችን ማምለካችንን እንቀጥል ዘንድ ከወደቅንበት ‘እንድንነሳ’ እንደሚረዳን እርግጠኞች ነን። ይሖዋን ከልብ የሚወዱ ሰዎች ሁሉ ይህን ማወቃቸው በጣም ያጽናናቸዋል! ክፉዎች ከወደቁበት ለመነሳት ተመሳሳይ ፍላጎት የላቸውም። የአምላክን ቅዱስ መንፈስና የአምላክን ሕዝቦች እርዳታ ማግኘት አይፈልጉም ወይም እንዲህ ያለ እርዳታ ሲቀርብላቸው አይቀበሉም። በአንጻሩ ግን ‘የይሖዋን ሕግ የሚወዱ’ ከሕይወት ሩጫ ለዘለቄታው እንዲወጡ ሊያደርጋቸው የሚችል ምንም ዓይነት እንቅፋት የለም።—መዝሙር 119:165ን አንብብ።
7, 8. አንድ ሰው ‘ቢወድቅም’ እንኳ የአምላክን ሞገስ ሳያጣ መኖር የሚችለው እንዴት ነው?
7 አንዳንዶች ካለባቸው ድክመት የተነሳ አልፎ አልፎ ወይም በተደጋጋሚ ቀላል ኃጢአት ሊሠሩ ይችላሉ። ይሁንና በወደቁ ቁጥር ‘ከተነሱ’ ይኸውም ከልብ ንስሐ ከገቡና በታማኝነት ማገልገላቸውን ለመቀጠል ጥረት ካደረጉ ይሖዋ ጻድቃን አድርጎ ይመለከታቸዋል። አምላክ ከጥንት እስራኤላውያን ጋር የነበረው ግንኙነት ይህን ያሳያል። (ኢሳ. 41:9, 10) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ምሳሌ 24:16 ትኩረት የሚያደርገው አሉታዊ በሆነው ነገር ላይ ይኸውም ‘በመውደቃችን’ ላይ ሳይሆን በአዎንታዊው ነገር ላይ ማለትም መሐሪ በሆነው አምላካችን እርዳታ ‘መነሳት’ በመቻላችን ላይ ነው። (ኢሳይያስ 55:7ን አንብብ።) ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ እምነት ያላቸው በመሆኑ ‘እንድንነሳ’ በደግነት ያበረታቱናል።—መዝ. 86:5፤ ዮሐ. 5:19
8 በማራቶን ውድድር ላይ እየተሳተፈ ያለ አንድ ሯጭ ቢደናቀፍ አልፎ ተርፎም ቢወድቅ በፍጥነት ተነስቶ ሩጫውን ለመቀጠልና ውድድሩን ለማጠናቀቅ የሚያስችል ጊዜ ሊኖረው ይችላል። ለዘላለም ሕይወት በምናደርገው ሩጫ ላይ ሩጫው የሚያበቃበትን “ቀንና ሰዓት” አናውቅም። (ማቴ. 24:36) ያም ሆኖ ብዙ ጊዜ ላለመደናቀፍ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ፍጥነታችንን ጠብቀን በሩጫው መቀጠልና ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ የምንችልበት አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል። ታዲያ እንዳንደናቀፍ ምን ማድረግ እንችላለን?
እድገትን የሚያስተጓጉል እንቅፋት
9. እንቅፋት ሊሆኑብን የሚችሉ ምን ነገሮችን እንመረምራለን?
9 እንቅፋት ሊሆኑብን የሚችሉ አምስት ነገሮችን እስቲ እንመልከት፤ እነሱም የግል ድክመቶቻችን፣ የሥጋ ምኞቶች፣ የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚፈጽሙብን በደል፣ መከራ ወይም ስደት እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞች አለፍጽምና ናቸው። ይሁንና ከተደናቀፍን ይሖዋ እጅግ ታጋሽ እንደሆነ መዘንጋት አይኖርብንም። እኛን ከዳተኛ ብሎ ለመፈረጅ አይቸኩልም።
10, 11. ዳዊት ከየትኛው ድክመቱ ጋር መታገል አስፈልጎት ነበር?
10 የግል ድክመቶቻችን በመሮጫ መንገድ ላይ ከወዳደቁ ድንጋዮች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ በንጉሥ ዳዊትና በሐዋርያው ጴጥሮስ ላይ የታዩ ሁለት ድክመቶችን እንመረምራለን፤ እነሱም ራስን መግዛት አለመቻልና የሰው ፍርሃት ናቸው።
11 ንጉሥ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር የፈጸመው ድርጊት ራስን በመግዛት ረገድ ድክመት እንደነበረበት ያሳያል። ናባል የሰነዘረበትን ስድብ በሰማ ጊዜም በግብታዊነት እርምጃ ለመውሰድ ተነሳስቶ ነበር። አዎ፣ ዳዊት በወቅቱ ራሱን መግዛት አቅቶት ነበር፤ ይሁንና ይሖዋን ለማስደሰት ጥረት ማድረጉን አላቆመም። ሌሎች ባደረጉለት እርዳታ መንፈሳዊ ሚዛኑን መልሶ መጠበቅ ችሏል።—1 ሳሙ. 25:5-13, 32, 33፤ 2 ሳሙ. 12:1-13
12. ጴጥሮስ ቢደናቀፍም በሩጫው የቀጠለው እንዴት ነው?
12 ጴጥሮስ ሰውን ይፈራ ነበር፤ በዚህም የተነሳ በከፍተኛ ሁኔታ የተደናቀፈባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ያም ሆኖ ኢየሱስንና ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሉን ቀጥሏል። ለምሳሌ፣ ጌታውን ከአንዴም ሦስቴ በሰዎች ፊት ክዶታል። (ሉቃስ 22:54-62) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ጴጥሮስ የተገረዙ አይሁዳውያን ክርስቲያኖችን ከአሕዛብ ከመጡት አማኞች አስበልጦ እንደሚመለከት የሚያሳይ ክርስቲያናዊ ያልሆነ ድርጊት ፈጽሟል። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ በጉባኤው ውስጥ የመደብ ልዩነት ሊታይ እንደማይገባ በግልጽ ተገንዝቦ ነበር። የጴጥሮስ አመለካከት ትክክል አልነበረም። የጴጥሮስ አድራጎት በወንድማማች ማኅበሩ ውስጥ መቃቃር እንዲፈጠር ከማድረጉ በፊት ጳውሎስ ጴጥሮስን ፊት ለፊት ገሥጾታል። (ገላ. 2:11-14) ጴጥሮስ ስሜቱ እጅግ ከመጎዳቱ የተነሳ ለሕይወት የሚያደርገውን ሩጫ አቋርጧል? በፍጹም። ጳውሎስ የሰጠውን ምክር በቁም ነገር ያሰበበት ከመሆኑም ሌላ ምክሩን በተግባር አውሏል እንዲሁም በሩጫው ቀጥሏል።
13. የጤና መቃወስ እንቅፋት ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
13 አንዳንድ ጊዜ ያለብን ድክመት ከጤና ጋር የተያያዘ ይሆናል። ይህም ቢሆን እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴያችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ብሎም እንድንንገዳገድና እንድንዝል ሊያደርገን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ጃፓናዊት እህት ከተጠመቀች ከ17 ዓመታት በኋላ ከባድ የጤና እክል አጋጥሟት ነበር። ያለባት የጤና ችግር ስሜቷን ሙሉ በሙሉ ስለተቆጣጠረው በመንፈሳዊ ደከመች። ከጊዜ በኋላ በመንፈሳዊ ቀዘቀዘች። ሁለት ሽማግሌዎች ሄደው አነጋገሯት። በደግነት መንፈስ ያካፈሏት ሐሳብ ስላበረታታት በስብሰባዎች ላይ በድጋሚ መገኘት ጀመረች። “ወንድሞች ሞቅ ባለ መንፈስ ስለተቀበሉኝ አለቀስኩ” በማለት ታስታውሳለች። ይህች እህታችን በአሁኑ ጊዜ ሩጫዋን ቀጥላለች።
14, 15. አንድ ሰው በውስጡ መጥፎ ምኞቶች ሲያቆጠቁጡ ምን ዓይነት ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል? ምሳሌ ስጥ።
14 የሥጋ ምኞቶች ለብዙዎች እንቅፋት ሆነዋል። እንዲህ ዓይነት ፈተና ሲያጋጥመን አእምሯዊ፣ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ያስፈልገናል። ኢየሱስ ዓይናችንንም ሆነ እጃችንን ጨምሮ ሊያሰናክለን የሚችልን ማንኛውም ነገር በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘አውጥተን ወይም ቆርጠን እንድንጥል’ የሰጠውን ምክር አስታውስ። ይህም አንዳንዶች ሩጫውን አቋርጠው እንዲወጡ ምክንያት የሆኑትን የብልግና አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ማስወገድን ይጨምራል።—ማቴዎስ 5:29, 30ን አንብብ።
15 በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያደገ አንድ ወንድም ለረጅም ዓመታት ግብረ ሰዶም እንዲፈጽም ከሚገፋፋው ውስጣዊ ስሜት ጋር ይታገል እንደነበር ጽፏል። “ሁልጊዜ እሸማቀቅ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ከማንም ጋር እንደማልገጥም ሆኖ ይሰማኝ ነበር” ብሏል። የ20 ዓመት ወጣት ሳለ የዘወትር አቅኚና የጉባኤ አገልጋይ ሆነ። ከዚያ በኋላ ግን ክፉኛ የተደናቀፈ ሲሆን ቅዱስ ጽሑፋዊ ተግሣጽ ተሰጠው፤ ሽማግሌዎችም እርዳታ አደረጉለት። በመጸለይ፣ የአምላክን ቃል በማጥናትና ሌሎችን በመርዳቱ ሥራ በመጠመድ ከወደቀበት ተነስቶ መንፈሳዊ እንቅስቃሴውን መቀጠል ቻለ። ከበርካታ ዓመታት በኋላ እንዲህ ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል፦ “አሁንም ቢሆን አንዳንዴ ስሜቱ ይታገለኛል፤ ሆኖም ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠረኝ አልፈቅድም። ይሖዋ አንድ ሰው ከሚችለው በላይ እንዲፈተን እንደማይፈቅድ ተገንዝቤአለሁ። በመሆኑም አምላክ ችግሩን መቋቋም እንደምችል ይተማመንብኛል የሚል እምነት አለኝ።” በመጨረሻም ወንድም “በጽናት ያደረግኩት ተጋድሎ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ወሮታ ያስገኝልኛል። ይህ እንዲያመልጠኝ አልፈልግም! እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ትግሉን እቀጥላለሁ” ብሏል። ይህ ወንድም ሩጫውን አቋርጦ ላለመውጣት ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል።
16, 17. (ሀ) በደል እንደተፈጸመበት የተሰማው አንድ ወንድም እንዲያንሰራራ የረዳው ምንድን ነው? (ለ) ላለመደናቀፍ በምን ነገር ላይ ማተኮር ይኖርብናል?
16 የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚፈጽሙብን በደል እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። በፈረንሳይ የሚኖር ሽማግሌ የነበረ አንድ ወንድም በደል እንደተፈጸመበት ስለተሰማው በጣም ተከፍቶ ነበር። በዚህም ምክንያት ከጉባኤው ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋረጠ፤ በኋላም ቀዘቀዘ። ሁለት ሽማግሌዎች ሄደው ያነጋገሩት ሲሆን የገጠመውን ሁኔታ እሱ በተረዳበት መንገድ በሚናገርበት ጊዜ ምንም ሳያቋርጡት በርኅራኄ ስሜት አዳመጡት። ከዚያም ሸክሙን በይሖዋ ላይ እንዲጥል ያበረታቱት ከመሆኑም ሌላ ዋናው ቁም ነገር አምላክን ማስደሰት እንደሆነ አበክረው ገለጹለት። ለተሰጠው ማበረታቻ ጥሩ ምላሽ ሰጥቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሩጫውን እንደገና በመቀጠል በጉባኤ እንቅስቃሴ ንቁ ተሳትፎ ያደርግ ጀመር።
17 ሁሉም ክርስቲያኖች ፍጽምና የጎደላቸውን ሰዎች ሳይሆን የጉባኤው ራስ ሆኖ የተሾመውን ኢየሱስ ክርስቶስን ምንጊዜም በትኩረት መመልከት ይኖርባቸዋል። “እንደ እሳት ነበልባል” የሆኑ ዓይኖች ያሉት ኢየሱስ ማንኛውንም ነገር በትክክል ስለሚመለከት እኛ ማየት ከምንችለው የበለጠ መመልከት ይችላል። (ራእይ 1:13-16) ለምሳሌ በደል እንደተፈጸመብን አድርገን ያሰብነው፣ ሁኔታውን በተሳሳተ መንገድ በማየታችን ወይም በመረዳታችን ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገነዘባል። ኢየሱስ ጉባኤው የሚያስፈልጉትን ነገሮች በትክክልና በተገቢው ጊዜ ያሟላል። በመሆኑም የእምነት ባልንጀራችን የሚያደርገው ነገር ወይም የሚወስነው ውሳኔ እንቅፋት እንዲሆንብን መፍቀድ አይኖርብንም።
18. ፈተናዎችን ወይም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
18 እንቅፋት ሊሆኑብን የሚችሉ ሌሎች ሁለት ነገሮች ደግሞ መከራ ወይም ስደት እና በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞች አለፍጽምና ናቸው። ኢየሱስ ስለ ዘሪው በተናገረው ምሳሌ ላይ አንዳንዶች በቃሉ የተነሳ የሚደርስባቸው “መከራ ወይም ስደት” እንደሚያደናቅፋቸው ገልጿል። የስደቱ ምንጭ ቤተሰብ፣ ጎረቤቶችም ሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት ‘ቃሉ በውስጡ ሥር ያልሰደደበትን’ በሌላ አባባል በመንፈሳዊ ጥልቀት የሌለውን ሰው በጣም ሊጎዳው ይችላል። (ማቴ. 13:21) ይሁንና ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ካለን የመንግሥቱ ዘር በእምነት ጸንተን መቆም እንድንችል የሚረዳ ጥልቀት ያለው ሥር እንድንሰድ ያስችለናል። ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ምስጋና በሚገባቸው ነገሮች ላይ በጸሎት ለማሰላሰል ጥረት ማድረግ አለብን። (ፊልጵስዩስ 4:6-9ን አንብብ።) አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዲያደናቅፉን ባለመፍቀድ ይሖዋ በሚሰጠን ጥንካሬ ፈተናዎችን ተቋቁመን ማለፍ እንችላለን።
19. ቅር የተሰኘንበት ነገር እንቅፋት እንዳይሆንብን ምን ማድረግ እንችላለን?
19 የሚያሳዝነው ባለፉት ዓመታት አንዳንዶች የሌሎች አለፍጽምና ከውድድሩ እንዲወጡ አድርጓቸዋል። ለሕሊና በተተዉ ጉዳዮች ረገድ ያሉት የአመለካከት ልዩነቶች እንቅፋት ሆነውባቸዋል። (1 ቆሮ. 8:12, 13) አንድ ሰው ቅር ቢያሰኘን ነገሩን በጣም አክብደን እናየዋለን? መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች በሌሎች ላይ መፍረዳቸውን እንዲተዉ፣ ይቅር ባዮች እንዲሆኑና ‘መብቴ ነው’ በሚል ስሜት ድርቅ ያለ አቋም እንዳይዙ ያሳስባል። (ሉቃስ 6:37) ሊያደናቅፍ የሚችል ድንጋይ ሲያጋጥምህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በራሴ ምርጫ ላይ ተመርኩዤ በሌሎች ላይ እፈርዳለሁ? ወንድሞቼ ፍጹማን እንዳልሆኑ ባውቅም በአንድ ሰው አለፍጽምና ተደናቅፌ ለሕይወት የማደርገውን ሩጫ አቋርጣለሁ?’ ለይሖዋ ያለን ፍቅር ሌላ ሰው በሚያደርገው ማንኛውም ነገር ተደናቅፈን ሩጫውን ከማጠናቀቅ ወደኋላ እንዳንል ይረዳናል።
እንቅፋቶችን አስወግዳችሁ በጽናት ሩጡ
20, 21. ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?
20 ‘ሩጫውን እስከ መጨረሻ ለመሮጥ’ ቆርጠሃል? (2 ጢሞ. 4:7, 8) ከሆነ የግል ጥናት ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንን ተጠቅመህ ምርምር አድርግ፣ አሰላስል እንዲሁም ሊያደናቅፉ የሚችሉ ነገሮችን ለይተህ ለማወቅ ጥረት አድርግ። የሚያስፈልግህን መንፈሳዊ ጥንካሬ ለማግኘት አምላክ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጥህ ለምነው። አንድ ሯጭ አልፎ አልፎ ስለተደናቀፈ ወይም ስለወደቀ ብቻ ለሕይወት ከሚደረገው ሩጫ ውጭ ይሆናል ማለት እንዳልሆነ አስታውስ። ከወደቀበት ተነስቶ ሩጫውን መቀጠል ይችላል። እንዲያውም እምነቱን ከሚፈታተኑ ነገሮች ጠቃሚ ትምህርቶችን በመቅሰም ሊያደናቅፉት የሚችሉ ድንጋዮችን እንደ መረማመጃ ሊጠቀምባቸው ይችላል።
21 መጽሐፍ ቅዱስ ለዘላለም ሕይወት የሚደረገው ሩጫ ንቁ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ይገልጻል። እንዲሁ አውቶቡስ ላይ ተሳፍሮ የመጨረሻው መስመር ድረስ የመሄድ ጉዳይ አይደለም። ለሕይወት የሚደረገውን ሩጫ ራሳችን መሮጥ አለብን። እንዲህ ካደረግን ከይሖዋ የምናገኘው “ብዙ ሰላም” ከጀርባችን እንደሚነፍስ ነፋስ ወደፊት ይገፋናል። (መዝ. 119:165) ሩጫውን የሚያጠናቅቁ ሁሉ አሁንም ሆነ ወደፊት ከይሖዋ ዘንድ ዘላቂ በረከት እንደሚያገኙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ያዕ. 1:12