በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጥ!

ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጥ!

የትዳር ጓደኛህ አብራህ ይሖዋን የምታመልክበትን ጊዜ በመናፈቅ በርካታ ዓመታት አሳልፈሃል?

ወይም ብዙ ተስፋ የጣልክበት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ ከእውነት ጎን ጸንቶ ባለመቆሙ ተስፋ ቆርጠሃል?

 በዚህ ረገድ ፈጽሞ ተስፋ መቁረጥ የማይኖርብህ ለምን እንደሆነ የሚያሳዩ ከብሪታንያ የተገኙ ጥቂት ተሞክሮዎች በዚህ ርዕስ ውስጥ ቀርበዋል። በተጨማሪም እውነትን ያልተቀበሉ ሰዎችን መርዳት ትችል ዘንድ በምሳሌያዊ ሁኔታ “እንጀራህን በውሃ ላይ” ለመጣል ምን ማድረግ እንደምትችል የሚጠቁም ግሩም ሐሳብ ታገኛለህ።—መክ. 11:1

ጽናት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው

ከአንተ የሚጠበቀው አንዱ ወሳኝ ነገር ጽናት ነው። እውነትን የሙጥኝ ብለህ መያዝና ከይሖዋ ጋር መጣበቅ ይኖርብሃል። (ዘዳ. 10:20) ጆርጂና ያደረገችው ይህን ነበር። በ1970 መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት በጀመረች ጊዜ ባለቤቷ ኪሪያኮስ እጅግ ተቆጣ። ጥናቷን ለማስቆም ሞከረ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቱ እንዳይመጡ ከለከለ እንዲሁም ያገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎች በሙሉ አስወገደ።

ጆርጂና በጉባኤ ስብሰባዎች መገኘት ስትጀምር ኪሪያኮስ ይበልጥ ተቆጣ። አንድ ቀን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመከራከር ወደ መንግሥት አዳራሹ ሄደ። ኪሪያኮስ ከእንግሊዝኛ ይልቅ ግሪክኛ መናገር እንደሚቀለው ያስተዋለች አንዲት እህት በሌላ ጉባኤ ያለ ግሪካዊ ወንድም መጥቶ እንዲረዳቸው ስልክ ደውላ ነገረችው። ኪሪያኮስ ወንድም ያሳየው ደግነት እንዲለዝብ ያደረገው ከመሆኑም ሌላ ለጥቂት ወራት ከዚህ ወንድም ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና ቆየ። ከዚያ በኋላ ግን ኪሪያኮስ ጥናቱን አቆመ።

ጆርጂና ለተጨማሪ ሦስት ዓመታት የሚደርስባትን ተቃውሞ ችላ ለመኖር ተገደደች። ኪሪያኮስ ከተጠመቀች ጥሏት እንደሚሄድ ዛተ። ጆርጂና በምትጠመቅበት ቀን ኪሪያኮስ ጥሏት እንዳይሄድ ወደ ይሖዋ አጥብቃ ጸለየች። የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ስብሰባው ቦታ ሊወስዷት በመጡ ጊዜ ኪሪያኮስ “እናንተ ቅደሙ። እኛ በራሳችን መኪና እንከተላችኋለን” አላቸው። በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ተገኝቶ ባለቤቱ ስትጠመቅ ተመለከተ!

ጆርጂና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከተገናኘች ከ40 ዓመት ገደማ በኋላ ባሏ ሲጠመቅ ለማየት በቃች

ከዚያ በኋላ የኪሪያኮስ ተቃውሞ እየለዘበ ከመምጣቱም በላይ ቀስ በቀስ ትልቅ ለውጥ ማድረግ ጀመረ። ጆርጂና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከተገናኘች ከ40 ዓመት ገደማ በኋላ ባሏ ሲጠመቅ ለማየት በቃች! ኪሪያኮስን የረዳው ነገር ምን ነበር? “ጆርጂና ቁርጥ አቋም ይዛ በመጽናቷ ደስተኛ ነኝ” ብሏል። ጆርጂና ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ምንም ያህል ቢቃወመኝ አምላኬን ማምለኬን የመተው ሐሳብ አልነበረኝም። በዚህ ጊዜ ሁሉ ወደ ይሖዋ መጸለዬን አልተውኩም፤ ተስፋም አልቆረጥኩም።”

አዲሱ ስብዕና ያለው ጠቀሜታ

የትዳር ጓደኛህን ለመርዳት ወሳኝ የሆነው ሌላው ነገር ደግሞ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ማዳበር ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያን ሚስቶችን ሲመክር “ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ ለገዛ ባሎቻችሁ ተገዙ” ብሏል። (1 ጴጥ. 3:1) ክሪስቲን ባሏ በእውነት ቃል እንዲማረክ ለማድረግ በርካታ ዓመታት ቢፈጅባትም ይህን ምክር በሥራ ላይ አውላለች። ከ20 ዓመት በፊት የይሖዋ ምሥክር ስትሆን ባለቤቷ ጆን በአምላክ አያምንም ነበር። ጆን ከሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዲኖረው አይፈልግ እንጂ ክሪስቲን ለአዲሱ እምነቷ ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ ማስተዋል ችሏል። እንዲህ ብሏል፦ “ደስተኛ እንዳደረጋት ማስተዋል ችዬ ነበር። መንፈሰ ጠንካራና እምነት የሚጣልባት ሰው እንድትሆን ረድቷታል፤ ይህ ደግሞ የተለያዩ ከባድ ችግሮች ባጋጠሙኝ ጊዜ በእጅጉ ጠቅሞኛል።”

ክሪስቲን ባለቤቷ እምነቷን እንዲቀበል አታስገድደውም ነበር፤ ጆን እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ክሪስቲን ከመጀመሪያ ጀምሮ ስለ ሃይማኖቷ እንድታነሳብኝ እንደማልፈልግ ተገንዝባ ነበር፤ በራሴ ጊዜና መንገድ እንድማር በትዕግሥት ረድታኛለች።” ክሪስቲን እሱን ሊማርኩት ይችላሉ ብላ ያሰበቻቸውን ሳይንሳዊ ወይም ተፈጥሮ ነክ የሆኑ ርዕሶች መጠበቂያ ግንብ ወይም ንቁ! ላይ ስታገኝ ታሳየውና “ይህን ርዕስ የምትወደው ይመስለኛል” ትለው ነበር።

ከጊዜ በኋላ ጆን ጡረታ ወጣና የአትክልተኝነት ሥራ ጀመረ። በዚህ ጊዜ አእምሮው ከሕይወት ጋር የተያያዙ ጥልቅ የሆኑ ጥያቄዎችን ለማሰብ ፋታ ስላገኘ ‘እዚህ ምድር ላይ የተገኘነው እንዲሁ በአጋጣሚ ነው? ወይስ የተፈጠርነው በዓላማ ነው?’ ብሎ ማሰላሰል ጀመረ። አንድ ቀን ከጆን ጋር እየተጫወተ የነበረ አንድ ወንድም “ጥናት ብንጀምርስ?” አለው። ጆን “በዚህ ጊዜ በአምላክ ማመን ጀምሬ ስለነበር ግብዣውን ተቀበልኩ” ብሏል።

ክሪስቲን ተስፋ አለመቁረጧ ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቷል። ለ20 ዓመት ያህል ከጸለየች በኋላ ጆን እውነትን ተቀብሎ ተጠመቀ። በአሁኑ ጊዜ አብረው ይሖዋን በቅንዓት እያገለገሉ ነው። ጆን እንዲህ ይላል፦ “የማረኩኝ ሁለት ነገሮች ናቸው። አንደኛው የይሖዋ ምሥክሮች ደጎችና ሰው ወዳድ መሆናቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሚስትህ የይሖዋ ምሥክር ከሆነች ታማኝ፣ እምነት የሚጣልባትና የራሷን ጥቅም መሥዋዕት የምታደርግ የትዳር ጓደኛ አገኘህ ማለት ነው።” አዎ፣ ክሪስቲን 1 ጴጥሮስ 3:1 ላይ ያለውን ምክር ሥራ ላይ አውላለች፤ ይህም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል።

 የተዘራው ዘር ከበርካታ ዓመታት በኋላ ሊያፈራ ይችላል

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመጀመሪያ ላይ የነበራቸው ፍላጎት በሆነ ምክንያት በሚጠፋበት ጊዜስ? ንጉሥ ሰለሞን “ጠዋት ላይ ዘርህን ዝራ፤ ማታም ላይ እጅህ ሥራ አይፍታ፤ ይህ ወይም ያ፣ ወይም ሁለቱ መልካም ይሁኑ፣ የቱ እንደሚያፈራ አታውቅምና” ሲል ጽፏል። (መክ. 11:6) አንዳንድ ጊዜ የእውነት ዘር ለመብቀል በርካታ ዓመታት ሊፈጅበት ይችላል። ይሁንና ግለሰቡ ወደ አምላክ መቅረብ አስፈላጊ መሆኑን የሚገነዘብበት ጊዜ ይመጣል። (ያዕ. 4:8) አዎ፣ አንድ ቀን ያላሰብከው አስደሳች ነገር ያጋጥምህ ይሆናል።

ከሕንድ ወደ እንግሊዝ የሄደችውን አሊስን እንውሰድ። በ1974 መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። የአፍ መፍቻ ቋንቋዋ ሂንዲ ቢሆንም እንግሊዝኛዋን ማሻሻል ፈለገች። ለተወሰኑ ዓመታት ማጥናቷን የቀጠለች ሲሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚካሄድ የጉባኤ ስብሰባ ላይ ለጥቂት ጊዜያት ተገኘች። የምታጠናው ነገር እውነት እንደሆነ ብትገነዘብም በቁም ነገር አልተመለከተችውም። ከዚህም በላይ ትኩረቷ ሁሉ ያረፈው ገንዘብ በማግኘት ላይ ከመሆኑም ሌላ ጭፈራ ቤት መሄድ ትወድ ነበር። ውሎ አድሮ አሊስ ጥናቷን አቆመች።

አሊስን ታስጠና የነበረችው ስቴላ ከ30 ዓመት ገደማ በኋላ አንድ ደብዳቤ ከአሊስ ደረሳት። ደብዳቤው እንዲህ የሚል ነበር፦ “በ1974 ታስጠኛት የነበረችው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪሽ በቅርቡ በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ መጠመቋን ስትሰሚ በጣም ደስ እንደሚልሽ እርግጠኛ ነኝ። በሕይወቴ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድረሻል። የእውነትን ዘር ልቤ ውስጥ ተክለሻል፤ በጊዜው ራሴን ለአምላክ ለመወሰን ዝግጁ ያልነበርኩ ቢሆንም የእውነትን ዘር ከአእምሮዬና ከልቤ አላወጣሁትም ነበር።”

አሊስ ለስቴላ የጻፈችው ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፦ “በ1974 ታስጠኛት የነበረችው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪሽ በቅርቡ በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ መጠመቋን ስትሰሚ በጣም ደስ እንደሚልሽ እርግጠኛ ነኝ”

እንድትለወጥ ያነሳሳት ምንድን ነው? አሊስ ባሏ በ1997 ከሞተ በኋላ ከፍተኛ የሆነ የመንፈስ ስብራት ደረሰባት። በዚህ ጊዜ ወደ አምላክ ጸለየች። በአሥር ደቂቃ ውስጥ ሁለት የፑንጃቢ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቷ መጡና እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ምን ተስፋ አላቸው? የሚለውን ትራክት አበርክተውላት ሄዱ። አሊስ ጸሎቷ መልስ እንዳገኘ ስለተሰማት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመገናኘት ወሰነች። ይሁንና ከእነሱ ጋር መገናኘት የምትችለው እንዴት ይሆን? ስቴላ የሰጠቻትን በፑንጃቢ ቋንቋ የሚካሄድ ጉባኤ አድራሻ አንድ አሮጌ ማስታወሻ ላይ አገኘች። አሊስ ወደ መንግሥት አዳራሹ ስትሄድ ፑንጃቢ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች ሞቅ ባለ ስሜት ተቀበሏት። “ያሳዩኝ ሞቅ ያለ ስሜት ልቤን በጥልቅ ስለነካው ከነበረብኝ የመንፈስ ጭንቀት እፎይታ አገኘሁ” በማለት አሊስ ተናግራለች።

አዘውትራ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረች፤ በተጨማሪም እንደገና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረች ሲሆን የፑንጃቢ ቋንቋን አቀላጥፋ መናገርና ማንበብ ተማረች። ከዚያም በ2003 ተጠመቀች። ለስቴላ የጻፈችው ደብዳቤ ማጠቃለያው ላይ እንዲህ ይላል፦ “ከ29 ዓመት በፊት የእውነትን ዘር በውስጤ ስለዘራሽና ጥሩ ምሳሌ ስለሆንሽኝ በጣም አመሰግንሻለሁ።”

“ከ29 ዓመት በፊት የእውነትን ዘር በውስጤ ስለዘራሽና ጥሩ ምሳሌ ስለሆንሽኝ በጣም አመሰግንሻለሁ።”​—አሊስ

ከእነዚህ ተሞክሮዎች ምን ትማራለህ? ከጠበቅከው በላይ ብዙ ጊዜ ይወስድ ይሆናል እንጂ አንድ ሰው በመንፈሳዊ የተራበ፣ ሐቀኛና ትሑት ሰው ከሆነ ይሖዋ የእውነት ዘር ልቡ ውስጥ እንዲያድግ ማድረጉ አይቀርም። ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ የሰጠውን ሐሳብ አስታውስ፦ “[ዘሪው] እንዴት እንደሆነም ሳያውቅ ዘሩ ይበቅልና ያድጋል። መሬቱም ራሱ ቀስ በቀስ ፍሬ ያፈራል፤ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ከዚያም ዛላውን በመጨረሻም በዛላው ላይ የጎመራ ፍሬ ይሰጣል።” (ማር. 4:27, 28) ይህን የመሰለው እድገት አዝጋሚና ‘በራሱ’ የሚከናወን ነው። በመሠረቱ እያንዳንዱ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ እድገቱ እንዴት እንደሚከናወን አያውቅም። ስለሆነም አብዝተህ መዝራትህን ቀጥል። ይዋል ይደር እንጂ አብዝተህ ልታጭድ ትችላለህ።

በተጨማሪም የጸሎትን አስፈላጊነት አትዘንጋ። ጆርጂና እና ክሪስቲን አዘውትረው ይጸልዩ ነበር። ‘በጸሎት ከጸናህና’ ፈጽሞ ተስፋ ካልቆረጥክ ውኃ ላይ የጣልከውን “እንጀራ” “ከብዙ ቀን በኋላ መልሰህ ታገኘዋለህ።”—ሮም 12:12፤ መክ. 11:1