‘ለመልካም ሥራ ትቀናላችሁ?’
‘ክርስቶስ ኢየሱስ ለመልካም ሥራ የሚቀና የእሱ ብቻ የሆነ ሕዝብ ለራሱ ለማንጻት ራሱን ለእኛ ሰጥቷል።’—ቲቶ 2:13, 14
1, 2. የይሖዋ ምሥክሮች ምን ታላቅ ክብር አግኝተዋል? ይህን ክብር በማግኘትህ ምን ይሰማሃል?
ብዙ ሰዎች ላገኙት ላቅ ያለ ስኬት ሽልማት ሲሰጣቸው እንደ ትልቅ ክብር ይቆጥሩታል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች በጠላትነት በሚተያዩ ወይም በማይስማሙ ወገኖች መካከል ሰላም እንዲወርድ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ጥረት በማድረጋቸው የኖቤል ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል። ይሁንና ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር ሰላማዊ ዝምድና እንዲመሠርቱ ለመርዳት በአምላክ የተላኩ አምባሳደሮች ወይም ልዩ መልእክተኞች መሆን እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው!
2 የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ይህን ታላቅ ክብር አግኝተናል። አምላክና ክርስቶስ የሰጡንን መመሪያ በማክበር ሰዎችን “ከአምላክ ጋር ታረቁ” በማለት እንለምናለን። (2 ቆሮ. 5:20) ይሖዋ ሰዎች ወደ እሱ እንዲቀርቡ ለማድረግ በእኛ ይጠቀማል። በዚህ መንገድ፣ ከ235 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና በመመሥረት የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሊኖራቸው ችሏል። (ቲቶ 2:11) “የሚፈልግ ሁሉ የሕይወትን ውኃ በነፃ ይውሰድ” የሚለውን ግብዣ ከልብ በመነጨ ቅንዓት እናቀርባለን። (ራእይ 22:17) ይህን ክቡር ሥራ በአድናቆት ስለምንመለከትና ሥራውን በትጋት ስለምናከናውን “ለመልካም ሥራ የሚቀና” ሕዝብ ተብለን መጠራታችን ተገቢ ነው። (ቲቶ 2:14) ለመልካም ሥራ የምንቀና መሆናችን ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ የሚረዳው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ይህን ለማድረግ የሚያስችለው አንደኛው መንገድ የስብከቱ ሥራችን ነው።
ይሖዋና ኢየሱስ የተዉትን የቅንዓት ምሳሌ ተከተሉ
3. የይሖዋ “ቅናት” ስለ ምን ነገር እርግጠኞች እንድንሆን ያስችለናል?
3 የአምላክ ልጅ አገዛዝ የሚያከናውነውን ነገር በተመለከተ ኢሳይያስ 9:7 “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል” ይላል። እነዚህ ቃላት በሰማይ የሚኖረው አባታችን የሰው ልጆችን ለማዳን ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ያጎላሉ። ይሖዋ በቅንዓት ረገድ የተወው ምሳሌ፣ አምላክ መንግሥቱን እንድናውጅ የሰጠንን ሥራ በሙሉ ልብ፣ በከፍተኛ ተነሳሽነትና በቅንዓት ልናከናውነው እንደሚገባ በግልጽ ያሳያል። ሰዎች አምላክን እንዲያውቁ ለመርዳት ያለን ብርቱ ፍላጎት የይሖዋን ቅንዓት ያንጸባርቃል። ታዲያ ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ እንደመሆናችን መጠን ሁኔታችን የፈቀደልንን ያህል ምሥራቹን በማወጁ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ በግለሰብ ደረጃ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል?—1 ቆሮ. 3:9
4. ኢየሱስ በቅንዓትና በጽናት በማገልገል ረገድ ምሳሌ የተወው እንዴት ነው?
4 ኢየሱስ ያሳየውንም ቅንዓት ተመልከት። በቅንዓትና በጽናት በማገልገል ረገድ ፍጹም ምሳሌ ትቷል። መራራ ተቃውሞ ቢደርስበትም ምድራዊ ሕይወቱ በአሰቃቂ ሁኔታ እስካበቃበት ጊዜ ድረስ የስብከቱን ሥራ በቅንዓት ማከናወኑን ቀጥሏል። (ዮሐ. 18:36, 37) ኢየሱስ መሥዋዕት ሆኖ የሚሞትበት ጊዜ እየቀረበ ሲመጣ ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ ለመርዳት የነበረው ቁርጥ አቋም ይበልጥ እየተጠናከረ ሄዷል።
5. ኢየሱስ ስለ በለስ ዛፍ ከተናገረው ምሳሌ ጋር በሚስማማ መንገድ ምን አድርጓል?
5 በ32 ዓ.ም. በበልግ ወቅት ኢየሱስ፣ በወይን እርሻው ውስጥ ለሦስት ዓመት ያህል ፍሬ ያላፈራች የበለስ ዛፍ ስለነበረችው ሰው የሚገልጽ አንድ ምሳሌ ተናግሯል። የወይን አትክልት ሠራተኛው ዛፏን እንዲቆርጣት ሲነገረው ማዳበሪያ ተደርጎባት ለተወሰነ ጊዜ እንድትታይ ጥያቄ አቀረበ። (ሉቃስ 13:6-9ን አንብብ።) በወቅቱ ኢየሱስ ያከናወነው የስብከት ሥራ ያስገኘው ፍሬ ተደርገው የሚቆጠሩት ደቀ መዛሙርት እጅግ ጥቂት ነበሩ። ሆኖም ስለ ወይን አትክልተኛው በሚናገረው ምሳሌ ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ የቀረውን ስድስት ወር ገደማ የሚሆን አጭር ጊዜ በይሁዳና በፔሪያ የስብከቱን ሥራ ለማጧጧፍ ተጠቅሞበታል። ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ቀናት በፊት ‘በጆሯቸው ሰምተው ምላሽ ላልሰጡት’ የአገሩ ሰዎች አልቅሷል።—ማቴ. 13:15፤ ሉቃስ 19:41
6. የአገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ማጧጧፍ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
6 ወደ ፍጻሜው ዘመን ዘልቀን ከመግባታችን አንጻር የስብከቱ ሥራችንን ማጧጧፋችን አንገብጋቢ አይደለም? (ዳንኤል 2:41-45ን አንብብ።) የይሖዋ ምሥክር መሆን እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው! በምድር ላይ የሰው ልጆች ለገጠሟቸው ችግሮች እውነተኛ መፍትሔ የያዘውን ተስፋ ለሰዎች የምንነግረው እኛ ብቻ ነን። በቅርቡ፣ አንዲት የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ “ጥሩ ሰዎች መጥፎ ነገር የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?” የሚለው ጥያቄ መልስ የለውም ስትል ገልጻለች። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ላሉ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ፣ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ለሆኑ ሁሉ ማካፈል ክርስቲያናዊ ግዴታችንም ሆነ መብታችን ነው። መለኮታዊ ተልእኳችንን በምንወጣበት ጊዜ ‘በመንፈስ የጋልን’ የምንሆንበት በቂ ምክንያት አለን። (ሮም 12:11) በቅንዓት በምናከናውነው የወንጌላዊነቱ ሥራ ላይ የአምላክ በረከት ሲታከልበት ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁና እንዲወዱ መርዳት እንችላለን።
የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ይሖዋን ያስከብራል
7, 8. የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ይሖዋን የሚያስከብረው እንዴት ነው?
7 የሐዋርያው ጳውሎስ ተሞክሮ እንደሚያሳየው አገልግሎታችን ‘እንቅልፍ አጥቶ ማደርና ጾም መዋል’ ሊያስከትልብን ይችላል። (2 ቆሮ. 6:5) እነዚህ አባባሎች የራስን ጥቅም መሠዋት ምን ማለት እንደሆነ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩን ከመሆኑም ሌላ ራሳቸውን ችለው እየኖሩ በሕይወታቸው ውስጥ ለአገልግሎት ቅድሚያ የሚሰጡ አቅኚዎችን ያስታውሱን ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ከአገራቸው ውጭ ለሚገኙ ሰዎች ምሥራቹን ለመስበክ ራሳቸውን ‘እንደ መጠጥ መሥዋዕት የሚያፈሱትን’ ታታሪ የሆኑ ሚስዮናውያን ወንድሞቻችንን አስቡ። (ፊልጵ. 2:17) የይሖዋን በጎች ለመንከባከብ ብለው ምግብ ሳይበሉ ወይም እንቅልፍ ሳይተኙ ስለሚቀሩ ትጉ ሽማግሌዎቻችንስ ምን ማለት ይቻላል? ደግሞም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና በመስክ አገልግሎት ለመሳተፍ የአቅማቸውን ሁሉ የሚያደርጉ በዕድሜ የገፉ ወይም የጤና ችግር ያለባቸው ወንድሞችና እህቶች በመካከላችን ይገኛሉ። የራሳቸውን ጥቅም ስለሚሠዉት ስለ እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ስናስብ ልባችን በአድናቆት ስሜት ይሞላል። እንዲህ ያለው ጥረት ሌሎች ስለ አገልግሎታችን ባላቸው አመለካከት ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።
8 ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በሊንከንሻየር ለሚታተመው ቦስተን ታርጌት ለተባለ ጋዜጣ፣ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ አንድ አንባቢ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች በሃይማኖቶች ላይ እምነት እያጡ መጥተዋል። . . . እነዚህ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ቀኑን ሙሉ ምን ሲያደርጉ ነው የሚውሉት? ክርስቶስ ያደርግ እንደነበረው ወጥተው ሰዎችን ለማግኘት ጥረት አያደርጉም። . . . ለዚህ ጉዳይ ትኩረት የሰጠው የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን አይቀርም፤ እነሱ ሰዎችን ለማግኘት ይሄዳሉ እንዲሁም እውነትን በመስበኩ ሥራ በትጋት ይካፈላሉ።” ለራስ ፍላጎት የማደር አባዜ በተጠናወተው በዚህ ዓለም ውስጥ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየታችን ይሖዋ አምላክን በእጅጉ ያስከብረዋል።—ሮም 12:1
9. ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ ለመልካም ሥራ ቀናተኞች ሆነን እንድንቀጥል ምን ሊያነሳሳን ይችላል?
9 ይሁን እንጂ ለአገልግሎት ያለን ቅንዓት እየቀነሰ እንደመጣ ከተሰማን ምን ማድረግ እንችላለን? ይሖዋ በስብከቱ ሥራ አማካኝነት እያከናወነ ባለው ነገር ላይ ማሰላሰላችን ሊጠቅመን ይችላል። (ሮም 10:13-15ን አንብብ።) ሰዎች መዳናቸው የተመካው የይሖዋን ስም በእምነት በመጥራታቸው ላይ ነው፤ ሆኖም ካልሰበክንላቸው እንዲህ ማድረግ አይችሉም። ይህን መገንዘባችን ለመልካም ሥራ ቀናተኞች ሆነን እንድንቀጥልና የመንግሥቱን ምሥራች በትጋት እንድናውጅ ሊያነሳሳን ይገባል።
መልካም ምግባር ሰዎች ወደ አምላክ እንዲሳቡ ያደርጋል
10. መልካም ምግባራችን ሰዎችን ወደ ይሖዋ ይስባል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
10 ቅንዓት ለአገልግሎት አስፈላጊ ቢሆንም እንኳ ቅንዓት ብቻውን ሰዎችን ወደ አምላክ ለመሳብ በቂ አይደለም። በቅንዓት ከማገልገል በተጨማሪ ሰዎችን ወደ አምላክ የሚስበው ሁለተኛው ነገር መልካም ክርስቲያናዊ ምግባር ነው። ጳውሎስ “አገልግሎታችን እንከን እንዳይገኝበት በምንም መንገድ ማሰናከያ የሚሆን ነገር እንዲኖር አናደርግም” ብሎ ሲጽፍ ምግባራችን የሚኖረውን ትልቅ ድርሻ አጉልቷል። (2 ቆሮ. 6:3) ገንቢ ንግግራችንና ቀና ምግባራችን የአምላክን ትምህርት ያስውባል፤ ይህም ሰዎች የይሖዋ አምልኮ ማራኪ ሆኖ እንዲታያቸው ያደርጋል። (ቲቶ 2:10) ደግሞም ቅን ሰዎች የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል የምናሳየውን መልካም ምግባር መመልከታቸው ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ በየጊዜው እንሰማለን።
11. ምግባራችን በሌሎች ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ በጸሎት ማሰብ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
11 አድራጎታችን በሰዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል እንገነዘባለን፤ ይሁንና መጥፎ ተጽዕኖም ሊያሳድር ይችላል። ስለዚህ በሥራ ቦታም ሆን በቤት ወይም በትምህርት ቤት ማንም ሰው ከአገልግሎታችንም ሆነ ከምግባራችን ጋር በተያያዘ እንከን እንዳያገኝብን እንጠነቀቃለን። ሆን ብለን ኃጢአት የመሥራት ልማድ ካዳበርን በግለሰብ ደረጃ የሚደርስብን ጉዳት የከፋ ሊሆን ይችላል። (ዕብ. 10:26, 27) ይህ ጉዳይ ድርጊታችንም ሆነ አኗኗራችን ለሌሎች ምን መልእክት እንደሚያስተላልፍ በጸሎት እንድናስብበት ሊያነሳሳን ይገባል። የዚህ ዓለም የሥነ ምግባር አቋም እያሽቆለቆለ በሄደ መጠን ቅን ሰዎች “እግዚአብሔርን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት” ይበልጥ ማስተዋል ይችላሉ። (ሚል. 3:18) አዎ፣ መልካም የሆነው ክርስቲያናዊ ምግባራችን ሰዎች ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
12-14. የእምነት ፈተናዎችን በጽናት መቋቋማችን ሰዎች ለአገልግሎታችን በሚኖራቸው አመለካከት ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
12 ጳውሎስ በቆሮንቶስ ላሉ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ መከራ፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎች፣ ድብደባና እስራት እንደደረሰበት ጠቅሷል። (2 ቆሮንቶስ 6:4, 5ን አንብብ።) የእምነት ፈተናዎች ደርሰውብን በጽናት ማሳለፋችን ሁኔታውን የሚያዩ ሰዎች እውነትን እንዲቀበሉ ሊረዳቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አንጎላ ውስጥ በአንድ አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮችን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ጥረት ተደርጎ ነበር። ስብሰባ ላይ የነበሩ ሁለት የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮችና 30 ፍላጎት ያሳዩ ግለሰቦች ከበባ ተካሄደባቸው። ከዚያም ተቃዋሚዎች እነዚህን ንጹሐን የጥቃት ሰለባዎች ደም እስኪፈሳቸው ድረስ ሲገርፏቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተሰብስበው እንዲመለከቱ ተደረገ። ሴቶችና ልጆች እንኳ ከዚህ የጭካኔ ድርጊት ሊተርፉ አልቻሉም። ዓላማቸው ሰዎቹ በፍርሃት እንዲዋጡና አንድም ሰው የይሖዋ ምሥክሮችን እንዳይሰማ ለማድረግ ነበር። ይሁንና በአደባባይ ከገረፏቸው በኋላ በአካባቢው የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ወደ ይሖዋ ምሥክሮች መጥተው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠኗቸው ጠየቁ! ከዚህ በኋላ መንግሥቱን የመስበኩ ሥራ ወደፊት እየገፋ በመሄዱ ከፍተኛ እድገትና ብዙ በረከት ሊገኝ ችሏል።
13 ይህ ምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በጽናት መደገፋችን በሌሎች ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ያሳያል። ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያት ድፍረት የተሞላበት አቋም በመያዛቸው ምን ያህል ሰዎች ከአምላክ ጋር እርቅ ፈጥረው እንደሚሆን ማሰብ እንችላለን። (ሥራ 5:17-29) በእኛ ሁኔታ ደግሞ አብረውን የሚማሩ ልጆች፣ የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም የቤተሰባችን አባላት ትክክል ለሆነው ነገር የምንወስደውን አቋም ተመልክተው በጎ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ።
14 በየትኛውም ጊዜ ቢሆን ከወንድሞቻችን መካከል አንዳንዶቹ ስደት ይደርስባቸዋል። ለአብነት ያህል፣ በአርሜንያ ወደ 40 የሚጠጉ ወንድሞች በገለልተኝነታቸው ምክንያት እስር ቤት ናቸው፤ በመጪዎቹ ወራት ደግሞ በርካታ ወንድሞች ሊታሰሩ እንደሚችሉ ይገመታል። በኤርትራ የይሖዋ አገልጋዮች የሆኑ 55 ሰዎች የታሰሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ ነው። በደቡብ ኮሪያ 700 ገደማ የሚሆኑ ምሥክሮች በእምነታቸው ምክንያት ታስረዋል። ይህ ሁኔታ ለ60 ዓመታት ያህል ዘልቋል። በተለያዩ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ስደት እየደረሰባቸው ያሉ ወንድሞች የሚያሳዩት ታማኝነት ለአምላክ ክብር እንዲያመጣና ጽድቅ ወዳድ የሆኑ ሰዎች ከእውነተኛው አምልኮ ጎን ለመቆም እንዲያነሳሳቸው እንጸልይ።—መዝ. 76:8-10
15. በሐቀኝነት መመላለስ ሰዎችን ወደ እውነት ሊስብ የሚችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
15 በተጨማሪም ሐቀኞች መሆናችን ሰዎችን ወደ እውነት ሊስብ ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 6:4, 7ን አንብብ።) በዚህ ረገድ የሚከተለው ተሞክሮ ማስረጃ ይሆነናል፦ አንዲት እህት የአውቶቡስ ቲኬት መቁረጫ ማሽን ውስጥ ገንዘብ እየከተተች ሳለ ጓደኛዋ፣ የምትሄደው አጭር ርቀት ስለሆነ ትኬት መቁረጥ እንደማያስፈልጋት ነገረቻት። ሆኖም እህት አንድ ፌርማታ ብቻ ለመጓዝም እንኳ የቲኬቱን ዋጋ መክፈል ተገቢ እንደሆነ አስረዳቻት። ከዚያም ጓደኛዋ ከአውቶቡሱ ወረደች። በዚህ ጊዜ ሹፌሩ ወደ እህት ዞሮ “የይሖዋ ምሥክር ነሽ እንዴ?” ብሎ ጠየቃት። እሷም “አዎ ነኝ፤ ግን ለምን ጠየቅከኝ?” አለችው። “የአውቶቡስ ትኬት ስለመቁረጥ ስትነጋገሩ ስለሰማኋችሁ ነው፤ የይሖዋ ምሥክሮች ከፍለው ከሚጓዙ በጣም ጥቂት ሰዎች መካከል እንደሆኑና በማንኛውም ነገር ሐቀኞች እንደሆኑ ታዝቤአለሁ።” ከጥቂት ወራት በኋላ በአንድ ስብሰባ ላይ አንድ ሰው ወደዚች እህት መጥቶ እንዲህ አላት፦ “ታስታውሽኛለሽ? የአውቶቡስ ትኬት ስለመቁረጥ አነጋግሬሽ የነበርኩት ሹፌር ነኝ። መልካም ምግባርሽን ካየሁ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ወሰንኩ።” ሐቀኝነትን በተመለከተ ያተረፍነው መልካም ስም እምነት የሚጣልብን አገልጋዮች ተደርገን እንድንታይ ያስችለናል።
ምንጊዜም አምላክን የሚያስከብሩ ባሕርያት አንጸባርቁ
16. ሰዎች እንደ ትዕግሥት፣ ፍቅርና ደግነት ያሉ ባሕርያትን ሲመለከቱ ልባቸው የሚነካው ለምንድን ነው? የሐሰት ሃይማኖት መሪዎች የሚያደርጉትን ነገር የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።
16 እንደ ትዕግሥት፣ ፍቅርና ደግነት ያሉትን ባሕርያት በማንጸባረቅም ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን። የእኛን ሁኔታ የሚመለከቱ አንዳንድ ሰዎች ስለ ይሖዋ፣ ስለ ዓላማውና ስለ ሕዝቡ የማወቅ ፍላጎት ሊያድርባቸው ይችላል። ብዙ ሰዎች አምልኳቸውን ሲያከናውኑ የግብዝነት ጭምብል በማጥለቅ ለአምላክ ያደሩ መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፤ የእውነተኛ ክርስቲያኖች አመለካከትና ምግባር ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች መንጎቻቸውን በማጭበርበር የናጠጡ ሲሆን በዚህ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ ውድ የሆኑ ቤቶችና መኪናዎች ለመግዛት ተጠቅመውበታል፤ ይባስ ብሎ አየር ማቀዝቀዣ ያለው የውሻ ቤት የገዛም አለ። በእርግጥም የክርስቶስ ተከታዮች ነን የሚሉ አብዛኞቹ ሰዎች ‘በነፃ የመስጠት’ ዝንባሌ የላቸውም። (ማቴ. 10:8) እንዲያውም በጥንቷ እስራኤል እንደነበሩት ብልሹ ካህናት “ለዋጋ ሲሉ ያስተምራሉ”፤ ትምህርታቸው ደግሞ በአብዛኛው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጋጫል። (ሚክ. 3:11) እንዲህ ዓይነቱ የግብዝነት ምግባር ሰዎች ከአምላክ ጋር እርቅ እንዲፈጥሩ አያስችልም።
17, 18. (ሀ) በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን ባሕርያት ማንጸባረቃችን እሱን የሚያስከብረው እንዴት ነው? (ለ) መልካም ሥራ በመሥራት እንድትጸና የሚገፋፋህ ምንድን ነው?
17 በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ትክክለኛ የክርስትና ትምህርቶችን በሚማሩበትና ለሰዎች ደግነት ሲደረግ በሚያዩበት ጊዜ ልባቸው ይነካል። ለአብነት ያህል፣ አንድ አቅኚ ከቤት ወደ ቤት እያገለገለ ሳለ በዕድሜ ጠና ያሉ መበለት አጋጠሙት፤ ይሁንና ሴትየዋ ለመወያየት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ወዲያውኑ ገለጹለት። ሴትየዋ እሱ የበሩን ደወል በደወለበት ጊዜ የኩሽና አምፑላቸውን ለመቀየር መሰላል ላይ እንደነበሩ ነገሩት። ወንድም “ብቻዎትን ሆነው እንዲህ ዓይነት ሥራ መሥራትዎ አደገኛ ነው” አላቸው። ከዚያም አቅኚው አምፑሉን ቀየረላቸውና ተሰናብቶ ሄደ። የሴትየዋ ልጅ የተደረገውን ነገር ሲሰማ በጉዳዩ እጅግ ከመደነቁ የተነሳ ወንድምን ለማመስገን ይፈልገው ጀመር። ከጊዜ በኋላ የሴትየዋ ልጅ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማ።
18 መልካም ሥራ በመሥራት ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ ያደረግከው ለምንድን ነው? አገልግሎታችንን በቅንዓት ስናከናውንና ነገሮችን ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ስንሠራ ይሖዋን እንደምናስከብርና ሌሎች ለመዳን እንዲበቁ ልንረዳ እንደምንችል ስለተገነዘብክ ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 10:31-33ን አንብብ።) ምሥራቹን በመስበክ ለመልካም ሥራ ቀናተኞች መሆንና አምላካዊ በሆነ መንገድ መመላለስ፣ ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር ለማሳየት ካለን ጥልቅ ፍላጎት የሚመነጩ ናቸው። (ማቴ. 22:37-39) ለመልካም ሥራዎች የምንቀና ከሆነ በአሁኑ ጊዜ ደስታና እርካታ በማግኘት በእጅጉ እንካሳለን። በተጨማሪም የሰው ዘር በሙሉ ፈጣሪያችንን ይሖዋን በማክበር ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት የሚያሳይበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ እንችላለን።