የሕይወት ታሪክ
ይሖዋን መታዘዝ ብዙ በረከት አስገኝቶልኛል
“ከኖኅ በጣም ግሩም ትምህርት እናገኛለን! ኖኅ ይሖዋን የታዘዘ ሲሆን ቤተሰቡንም ይወድ ነበር፤ ቤተሰቡ በሙሉ ወደ መርከቡ ስለገቡ ከጥፋት ውኃው መትረፍ ችለዋል።”
ስለ አባቴ ካሉኝ የልጅነት ትዝታዎች አንዱ እንዲህ እያለ ይነግረን የነበረበት ጊዜ ነው፤ አባቴ ትሑት እና ታታሪ ሰው ነበር። የፍትሕ ጉዳይ በጣም ያሳስበው ስለነበረ በ1953 የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ሲነገረው ለመቀበል አላቅማማም። እውነትን ከሰማበት ጊዜ ጀምሮ፣ የተማረውን ነገር ለእኛ ለልጆቹ ለማስተማር አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል። እናቴ ካቶሊክ የነበረች ሲሆን መጀመሪያ አካባቢ የካቶሊክን ወግና ልማዶች ለመተው ፈቃደኛ አልነበረችም። እያደር ግን እሷም የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ተቀበለች።
እኛን ማስጠናት ለወላጆቻችን ከባድ ነበር፤ እናታችን የማንበብና የመጻፍ ችሎታዋ በጣም አነስተኛ ነው፤ አባታችን ደግሞ በእርሻው ውስጥ ሙሉ ቀን ሲለፋ ይውላል። አንዳንድ ጊዜ በጣም ስለሚደክመው በምናጠናበት ወቅት እንቅልፍ ያስቸግረው ነበር። ያም ቢሆን ግን ጥረቱ መና አልቀረም። እኔ የቤቱ የመጀመሪያ ልጅ ስለሆንኩ እህቴንና ሁለቱን ወንድሞቼን በማስተማር አግዘው ነበር። አባቴ አዘውትሮ ይጠቅሰው የነበረውን የኖኅን ታሪክ ይኸውም ኖኅ አምላክን በመታዘዝ ቤተሰቡን የሚወድ ሰው መሆኑን እንዳሳየ እነግራቸው ነበር። ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንዴት እንደምወደው ልነግራችሁ አልችልም! ብዙም ሳይቆይ ሁላችንም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርን፤ የመንግሥት አዳራሹ የሚገኘው ጣሊያን ውስጥ በአድሪያቲክ የባሕር ዳርቻ ላይ ባለች ሮዜቶ ዴልዪ አብሩትዚ በተባለች ከተማ ነው።
በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘነው በ1955 ነው፤ በወቅቱ ገና የ11 ዓመት ልጅ ስሆን ስብሰባው ላይ ለመገኘት ከእናቴ ጋር ተራሮቹን አቋርጠን በስተ ምዕራብ ወደምትገኘው ወደ ሮም ሄድን። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እነዚህን ትላልቅ ስብሰባዎች ከፍ አድርጌ እመለከታቸዋለሁ፤ ክርስቲያን በመሆናችን ካገኘናቸው እጅግ ድንቅ መብቶች መካከል እንደሚቆጠሩ ይሰማኛል።
በቀጣዩ ዓመት የተጠመቅሁ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ። በ17 ዓመቴ ላቲና በምትባል ከሮም በስተ ደቡብ የምትገኝ ከተማ ውስጥ በልዩ አቅኚነት እንዳገለግል ተመደብኩ፤ ይህች ከተማ ካደግሁበት አካባቢ 300 ኪሎ ሜትር ያህል ትርቃለች። ከተማዋ በቅርቡ የተቆረቆረች በመሆኗ ነዋሪዎቹ ‘የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ብቀበል ጎረቤቶቼ ምን ይሉኛል’ የሚል ፍርሃት አልነበራቸውም። እኔና አብራኝ እንድታገለግል የተመደበችው እህት በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማሰራጨታችን የተደሰትን ቢሆንም ልጅ በመሆኔ ቤተሰቦቼ በጣም ይናፍቁኝ ነበር! ያም ቢሆን የተሰጠኝን መመሪያ ለመታዘዝ ቆርጬ ነበር።
የተወሰነ ጊዜ በልዩ አቅኚነት ካገለገልኩ በኋላ በ1963 ለተካሄደው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ የሚደረገውን ዝግጅት እንዳግዝ ተመደብኩ፤ “የዘላለም ምሥራች” የተባለው ይህ ስብሰባ የተካሄደው በሚላን ነበር። በስብሰባው ወቅት ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኜ ከበርካታ ክርስቲያኖች ጋር የሠራሁ ሲሆን ከእነሱም መካከል ፓኦሎ ፒቾሊ የተባለ ከፍሎረንስ የመጣ ወጣት ወንድም ይገኝበታል። በስብሰባው ሁለተኛ ቀን ፓኦሎ ስለ ነጠላነት ግሩም ንግግር አቀረበ። በወቅቱ ‘ይህ ወንድም ፈጽሞ አያገባም’ ብዬ አስቤ ነበር። ይሁንና ከፓኦሎ ጋር መጻጻፍ የጀመርን ሲሆን የምንመሳሰልባቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ እያደር ተገነዘብን፤ ተመሳሳይ ግቦች ነበሩን፤ እንዲሁም ሁለታችንም ይሖዋን የምንወድ ከመሆኑም ሌላ እሱን የመታዘዝ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረን። በመሆኑም በ1965 ከፓኦሎ ጋር ተጋባን።
ከቀሳውስቱ ጋር ያደረግነው ክርክር
በፍሎረንስ ለአሥር ዓመት ያህል በዘወትር አቅኚነት አገልግያለሁ። በጉባኤዎቹ ውስጥ የሚታየውን ጭማሪ በተለይ ደግሞ ወጣቶቹ የሚያደርጉትን እድገት መመልከት በጣም ያስደስታል። እኔና ፓኦሎ ከእነዚህ ወጣቶች ጋር ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መወያየትና አብረን መዝናናት ያስደስተን ነበር፤ ብዙውን ጊዜ ፓኦሎ ከእነሱ ጋር እግር ኳስ መጫወት ይወድ ነበር። ከባለቤቴ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ብፈልግም ፓኦሎ ለእነዚያ ወጣቶችና በጉባኤ ውስጥ ላሉት ቤተሰቦች ትኩረቱንና ጊዜውን መስጠቱ በጣም እንደሚጠቅማቸው እገነዘብ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስን እናስጠናቸው ስለነበሩት በርካታ ሰዎች ሳስታውስ አሁንም ልቤ በሐሴት ይሞላል። አድሪአና የተባለችው አንዷ ጥናታችን የተማረችውን ነገር ለሌሎች ሁለት ቤተሰቦች ትነግራቸው ነበር። እነሱም የሥላሴን፣ የማትሞት ነፍስ አለች የሚለውንና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሠረተ ትምህርቶችን በተመለከተ ከአንድ ቄስ ጋር እንድንወያይ ዝግጅት አደረጉ። በቀጠሮው ቀን፣ ትልቅ ቦታ ያላቸው ሦስት ቀሳውስት መጡ። ግልጽ ከሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር ሲወዳደር ቀሳውስቱ የሚናገሩት ነገር በጣም ውስብስብና እርስ በርሱ የሚጋጭ መሆኑን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በቀላሉ ማስተዋል ችለው ነበር። የዚያን ዕለት ከቀሳውስቱ ጋር ያደረግነው ውይይት ጥናቶቻችን ውሳኔ እንዲያደርጉ ረዳቸው። ከጊዜ በኋላ ከእነዚህ ቤተሰቦች መካከል 15 የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ።
እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ የምንጠቀምበት የስብከት ዘዴ የተለየ ነው። ያን ጊዜ ፓኦሎ ከቀሳውስቱ ጋር በመከራከር ረገድ “ተክኖ” የነበረ ሲሆን እንዲህ ዓይነት ክርክሮችን ብዙ ጊዜ አድርጓል። በአንድ ወቅት የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ በርካታ ሰዎች በተገኙበት እንዲህ ዓይነት ክርክር እንዳደረግን አስታውሳለሁ። በኋላ ላይ እንደተረዳነው ተቃዋሚዎች፣ ከባድ እንደሆኑ ያሰቧቸውን ጥያቄዎች የሚጠይቁ ሰዎች አስቀድመው አዘጋጅተው ነበር። ይሁንና ሁኔታዎቹ የተገላቢጦሽ ሆኑ። ከአድማጮች መካከል አንድ ሰው፣ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ስታደርገው እንደቆየችው በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባቷ ተገቢ መሆኑን በተመለከተ ጥያቄ አነሳ። ቀሳውስቱ አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡ ግልጽ ነበር። በዚህ ወቅት በድንገት መብራት የጠፋ ሲሆን ስብሰባውም ተቋረጠ። ከዓመታት በኋላ መረዳት እንደቻልነው ቀሳውስቱ ውይይቱ እንዳሰቡት ካልሄደ ኤሌክትሪክ እንዲቋረጥ አስቀድመው ዝግጅት አድርገው ነበር።
የተለያዩ የአገልግሎት ምድቦች
እኔና ፓኦሎ በተጋባን በአሥር ዓመታችን በወረዳ ሥራ እንድንካፈል ተጋበዝን። ፓኦሎ ጥሩ ሥራ ስለነበረው ይህን ውሳኔ ማድረግ ቀላል አልነበረም። ይሁንና ጉዳዩን በጸሎት ካሰብንበት በኋላ በዚህ የአገልግሎት ምድብ ለመካፈል ራሳችንን አቀረብን። በዚህ ሥራ ስንካፈል በእንግድነት ከሚቀበሉን ቤተሰቦች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስተን ነበር። ምሽት ላይ አብዛኛውን ጊዜ ከእነዚህ ቤተሰቦች ጋር አብረን እናጠና ነበር፤ ከዚያም ፓኦሎ ልጆቹን የትምህርት ቤት ሥራቸውን ያሠራቸው በተለይም በሒሳብ ትምህርት ይረዳቸው ነበር። ከዚህም ሌላ ፓኦሎ አንባቢ ስለነበረ ያገኛቸውን አስገራሚና ጠቃሚ ነጥቦች ለሌሎች ማካፈል ያስደስተዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሰኞ ሰኞ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ወደሌሉባቸው ከተሞች ሄደን በመስበክ ሰዎችን በዚያን ዕለት ምሽት በሚቀርብ ንግግር ላይ እንዲገኙ እንጋብዝ ነበር።
በወረዳ ሥራ ሁለት ዓመት ብቻ ካሳለፍን በኋላ በሮም ቤቴል እንድናገለግል ተጋበዝን። ፓኦሎ በሕግ ክፍል ውስጥ የተመደበ ሲሆን እኔ ደግሞ በመጽሔት ክፍል መሥራት ጀመርኩ። ይህን ለውጥ ማድረግ ቀላል ባይሆንልንም ምንጊዜም ታዛዥ ለመሆን ቆርጠን ነበር። ቅርንጫፍ ቢሮው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ሲሄድ ማየትና በጣሊያን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ያደረጉትን ከፍተኛ እድገት መመልከት በጣም አስደሳች ነው። በቤቴል በነበርንበት ወቅት በጣሊያን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና አገኙ፤ ይህ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ውሳኔ ነው። በእርግጥም በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ በመሰማራታችን ደስተኞች ነበርን።
በቤቴል እያገለገልን በነበረበት ጣሊያን ውስጥ፣ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ከደም ጋር በተያያዘ ባለን ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋም ላይ ጥያቄ ተነስቶ ነበር። በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከዚህ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት የቀረበ አንድ ክስ ከፍተኛ ውዝግብ ፈጥሮ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ አንድ ባልና ሚስት ‘ልጃቸው እንድትሞት አድርገዋል’ በሚል በሐሰት ተከሰሱ፤ በእርግጥ ልጃቸው የሞተችው በሜድትራንያን አካባቢ የተለመደና ከደም ጋር የተያያዘ በዘር የሚተላለፍ ከባድ የጤና እክል ስለነበረባት ነው። በቤቴል የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች የእነዚህን ክርስቲያን ባልና ሚስት ጉዳይ የሚከታተሉትን ጠበቆች ለመርዳት ጥረት አድርገዋል። ሰዎች እውነታውን እንዲያውቁ እንዲሁም የአምላክ ቃል ስለ ደም ምን እንደሚል በትክክል እንዲገነዘቡ ለመርዳት ሲባል በራሪ ጽሑፍና ልዩ የንቁ! እትም ተሰራጨ። በእነዚያ ወራት አብዛኛውን ጊዜ ፓኦሎ በቀን እስከ 16 ሰዓት ያህል ያለማቋረጥ ይሠራ ነበር። ይህን በጣም አስፈላጊ ሥራ ሲያከናውን እኔም እሱን ለመደገፍ የተቻለኝን ሁሉ አድርጌያለሁ።
ሌላ ለውጥ አጋጠመን
በትዳር ውስጥ 20 ዓመታት ካሳለፍን በኋላ ያልጠበቅነው ነገር አጋጠመን። እርግጠኛ ባልሆንም እንዳረገዝኩ እንደተሰማኝ ለፓኦሎ ነገርኩት፤ በወቅቱ እኔ 41 እሱ ደግሞ 49 ዓመቱ ነበር። የዚያን ዕለት በግል ማስታወሻው ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ አሰፈረ፦ “ጸሎት፦ ነገሩ እውነት ከሆነ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድንቀጥል፣ መንፈሳዊነታችንን ችላ እንዳንል እንዲሁም ጥሩ ምሳሌ የምንሆን ወላጆች እንድንሆን እርዳን። ከሁሉ በላይ ደግሞ ላለፉት 30 ዓመታት ከመድረክ ሆኜ ስናገር ከነበረው 1 በመቶ ያህሉን እንኳ ተግባራዊ ማድረግ እንድችል እርዳኝ።” ያገኘነውን ውጤት ቆም ብዬ ሳስበው ይሖዋ የእሱንም ሆነ የእኔን ጸሎት እንደመለሰልን ይሰማኛል።
ልጃችን ኢላሪያ ስትወለድ በሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አጋጠመን። እውነቱን ለመናገር አንዳንድ ጊዜ ነገሮች ተስፋ አስቆራጭ ሆነውብን ነበር፤ በምሳሌ 24:10 (NW) ላይ የተገለጸው ዓይነት ሁኔታ የገጠመን ወቅት ነበር፤ ጥቅሱ “በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል!” ይላል። ያም ቢሆን አንዳችን ሌላውን ማበረታታታችን ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው በመገንዘብ በእነዚህ ጊዜያት እርስ በርስ እንደጋገፍ ነበር።
ኢላሪያ፣ ሁለቱም ወላጆቿ ከልጅነቷ ጀምሮ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈላቸው ደስተኛ መሆኗን ብዙ ጊዜ ትናገራለች። እንደማንወዳትና ትኩረት እንደማንሰጣት ፈጽሞ ተሰምቷት አያውቅም። ቀን ቀን ከእኔ ጋር ትውላለች። ምሽት ላይ ደግሞ ፓኦሎ ወደ ቤት ሲመለስ በአብዛኛው ሥራ ቢኖረውም ከእሷ ጋር ይጫወት እንዲሁም የትምህርት ቤት ሥራዋን ያሠራት ነበር። አንዳንድ ጊዜ የራሱን ሥራ ለመጨረስ እስከ ሌሊቱ ስምንት ወይም ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ማምሸት ቢኖርበትም እንኳ ጊዜውን ለእሷ ከመስጠት ወደኋላ አይልም። ብዙውን ጊዜ ኢላሪያ “ከማንም በላይ የምቀርበው ጓደኛዬ አባቴ ነው” ትል ነበር።
ኢላሪያ በክርስትና ጎዳና ላይ እንድትመላለስ ለመርዳት ወጥ የሆነ ሥልጠና መስጠት አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጥብቅ መሆን አስፈላጊ እንደነበረ ግልጽ ነው። በአንድ ወቅት ኢላሪያ ከጓደኛዋ ጋር ስትጫወት ተገቢ ያልሆነ ነገር አደረገች። ድርጊቷ ስህተት የሆነበትን ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አስረዳናት። ከዚህም በላይ ጓደኛዋን ፊታችን ይቅርታ እንድትጠይቃት አደረግን።
ኢላሪያ፣ ወላጆቿ ለአገልግሎት ያላቸውን ፍቅር እንደምታደንቅ ብዙ ጊዜ ትናገራለች። አሁን አድጋ የራሷን ትዳር ስለመሠረተች ይሖዋን መታዘዝና መመሪያውን መከተል ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይበልጥ ተገንዝባለች።
በሐዘን ወቅትም ታዛዥ መሆን
በ2008 ፓኦሎ ካንሰር እንዳለበት አወቀ። መጀመሪያ ላይ ፓኦሎ ከበሽታው መዳን የሚችል ይመስል ነበር፤ እኔንም በጣም አበረታትቶኝ ነበር። ከኢላሪያ ጋር ሆነን ጥሩ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኝ ጥረት ከማድረጋችን በተጨማሪ ይሖዋ ከፊታችን የሚያጋጥመንን ሁኔታ መጋፈጥ እንድንችል እንዲረዳን ረዘም ያለ ጸሎት እናቀርብ ነበር። ያም ቢሆን በአንድ ወቅት ጠንካራና ብርቱ የነበረው ባለቤቴ ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅም እያጣ ሲሄድ ማየት ፈታኝ ነበር። በ2010 በሞት ሲያንቀላፋ በከባድ ሐዘን ተዋጥኩ። ይሁንና አብረን ባሳለፍናቸው 45 ዓመታት ያከናወንናቸውን ነገሮች መለስ ብዬ ሳስብ እጽናናለሁ። ለይሖዋ ምርጣችንን ሰጥተነዋል። ያከናወንነው ሥራ ዘላቂ ጥቅም እንዳለው እገነዘባለሁ። እንዲሁም በዮሐንስ 5:28, 29 ላይ ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ፓኦሎ ትንሣኤ የሚያገኝበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።
“ትንሽ ልጅ እያለሁ ለኖኅ ታሪክ የነበረኝ ፍቅር አሁንም አልጠፋም። ያን ጊዜ የነበረኝ አቋምም አልተለወጠም”
ትንሽ ልጅ እያለሁ ለኖኅ ታሪክ የነበረኝ ፍቅር አሁንም አልጠፋም። ያን ጊዜ የነበረኝ አቋምም አልተለወጠም። ይሖዋ የሚጠብቅብኝ ነገር ምንም ሆነ ምን እሱን መታዘዝ እፈልጋለሁ። ያጋጠመን እንቅፋት፣ የከፈልነው መሥዋዕት ወይም ያጣነው ነገር ምንም ይሁን ምን አፍቃሪው አምላካችን ከሚሰጠን ድንቅ በረከቶች ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ። አምላክን መታዘዝ ፈጽሞ እንደማያስቆጭ ከራሴ የሕይወት ተሞክሮ ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ።