በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ከጥፋት ውኃ በፊት እንደነበሩ በዘፍጥረት 6:2, 4 ላይ የተጠቀሱት ‘የአምላክ ወንዶች ልጆች’ እነማን ናቸው?

ይህ አገላለጽ የአምላክን መንፈሳዊ ልጆች እንደሚያመለክት ለማመን የሚያበቃ ምክንያት አለ። ይሁንና እንዲህ ለማለት ምን ማስረጃ አለን?

ዘፍጥረት 6:2 እንዲህ ይላል፦ “የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች ውብ ሆነው አዩአቸው፤ ከመካከላቸውም የመረጧቸውን አገቡ።”

በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች” እና “የአምላክ ልጆች” የሚለው አገላለጽ በዘፍጥረት 6:2, 4፣ ኢዮብ 1:6፣ 2:1፣ 38:7 (የ1954 ትርጉም) እና መዝሙር 89:6 (NW) ላይ ይገኛል። እነዚህ ጥቅሶች “የአምላክ ልጆች” ስለተባሉት ፍጥረታት ምን ይጠቁማሉ?

በኢዮብ 1:6 (የ1954 ትርጉም) ላይ የተጠቀሱት “የአምላክ ልጆች” በይሖዋ ፊት የተሰበሰቡ መንፈሳዊ ፍጥረታት እንደሆኑ ግልጽ ነው። ከእነሱም መካከል ‘በምድር ሁሉ ሲዞር’ የነበረው ሰይጣን ይገኝበታል። (ኢዮብ 1:7፤ 2:1, 2 የ1954 ትርጉም) በተመሳሳይም በኢዮብ 38:4-7 ላይ አምላክ የምድርን ‘የማዕዘን ድንጋይ ባቆመ’ ጊዜ ‘የእግዚአብሔር ልጆች እልል እንዳሉ’ ተገልጿል። (ኢዮብ 38:4-7) በዚያ ወቅት የሰው ልጆች ስላልተፈጠሩ እዚህ ላይ የተጠቀሱት ‘የእግዚአብሔር ልጆች’ መላእክት መሆን አለባቸው። በመዝሙር 89:6 (NW) ላይ የተጠቀሱት ‘የአምላክ ልጆች’ ደግሞ በሰማይ ከአምላክ ጋር የሚኖሩ ፍጥረታት እንጂ የሰው ልጆች እንዳልሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም።

ታዲያ በዘፍጥረት 6:2, 4 ላይ የተጠቀሱት “የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች” እነማን ናቸው? ከላይ ካየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንጻር ይህ ዘገባ የሚያመለክተው ወደ ምድር የመጡ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆችን ነው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው።

አንዳንዶች፣ መላእክት የፆታ ፍላጎት ሊኖራቸው እንደሚችል መቀበል ይከብዳቸዋል። ኢየሱስ በማቴዎስ 22:30 ላይ የተናገረው ሐሳብ በሰማይ ጋብቻም ሆነ የፆታ ግንኙነት እንደሌለ ይጠቁማል። ያም ሆኖ መላእክት የሰው አካል ለብሰው ወደ ምድር የመጡባቸው ሌላው ቀርቶ ከሰው ልጆች ጋር የበሉባቸውና የጠጡባቸው ወቅቶች አሉ። (ዘፍ. 18:1-8፤ 19:1-3) በመሆኑም መላእክት የሰው አካል በሚለብሱበት ወቅት ከሴቶች ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይችላሉ ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።

አንዳንድ መላእክት እንዲህ ዓይነት ድርጊት እንደፈጸሙ እንድናምን የሚያደርጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች አሉ። በይሁዳ 6, 7 ላይ እንደምንመለከተው ከተፈጥሮ ውጭ ለሆነ የሥጋ ምኞት የተገዙት የሰዶም ሰዎች የፈጸሙት ኃጢአት ‘መጀመሪያ የነበራቸውን ቦታ ያልጠበቁትና ትክክለኛ መኖሪያቸውን የተዉት መላእክት’ ከፈጸሙት ድርጊት ጋር ተመሳስሏል። እነዚህ መላእክትና የሰዶም ሰዎች የሚመሳሰሉት ሁለቱም ወገኖች “ራሳቸውን ለሴሰኝነት አሳልፈው በመስጠታቸውና ከተፈጥሮ ውጭ ለሆነ የሥጋ ምኞት በመገዛታቸው” ነው። በ1 ጴጥሮስ 3:19, 20 ላይ ደግሞ ታዛዥ ያልሆኑት መላእክት ‘ከኖኅ ዘመን’ ጋር በተያያዘ ተገልጸዋል። (2 ጴጥ. 2:4, 5) በመሆኑም በኖኅ ዘመን የነበሩት ያልታዘዙ መላእክት የፈጸሙት ኃጢአት በሰዶምና ገሞራ የነበሩት ሰዎች ከፈጸሙት ኃጢአት ጋር ሊወዳደር ይችላል።

በዘፍጥረት 6:2, 4 ላይ የተጠቀሱት “የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች” የሰው አካል ለብሰው ወደ ምድር በመምጣት ከሴቶች ጋር የፆታ ብልግና የፈጸሙ መላእክት መሆናቸውን ስንገነዘብ እነዚህ መላእክት ከሰዶም ሰዎች ጋር መመሳሰላቸው ተገቢ እንደሆነ እንረዳለን።

 ኢየሱስ “በእስር ላሉት መናፍስት ሰበከላቸው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ጴጥ. 3:19) ይህ ምን ማለት ነው?

ሐዋርያው ጴጥሮስ “እነዚህ መናፍስት በኖኅ ዘመን . . . አምላክ በትዕግሥት እየጠበቀ ሳለ ሳይታዘዙ የቀሩ ናቸው” በማለት ተናግሯል። (1 ጴጥ. 3:20) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጴጥሮስ እዚህ ላይ የተናገረው በአምላክ ላይ በማመፅ ከሰይጣን ጋር ስለተባበሩት መንፈሳዊ ፍጥረታት ወይም መላእክት ነው። ይሁዳ እንደተናገረው “መጀመሪያ የነበራቸውን ቦታ ያልጠበቁትንና ትክክለኛ መኖሪያቸውን የተዉትን መላእክት” አምላክ “በታላቁ ቀን ለሚፈጸምባቸው ፍርድ በዘላለም እስራት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ አቆይቷቸዋል።”—ይሁዳ 6

በኖኅ ዘመን መንፈሳዊ ፍጥረታት ሳይታዘዙ የቀሩት እንዴት ነበር? ከጥፋት ውኃ በፊት እነዚህ ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ሥጋዊ አካል ለብሰው ምድር ላይ መኖር ጀምረው ነበር፤ ይህ ድርጊታቸው ከአምላክ ዓላማ ጋር የሚጋጭ ነው። (ዘፍ. 6:2, 4) ከዚህም በላይ እነዚህ መላእክት ከሴቶች ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸው ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ነገር ነበር። አምላክ መላእክትን ሲፈጥር ከሴቶች ጋር የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ዓላማው አልነበረም። (ዘፍ. 5:2) እነዚህ ታዛዥ ያልሆኑ ክፉ መላእክት አምላክ በወሰነው ጊዜ ይጠፋሉ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን ይሁዳ እንደተናገረው “በድቅድቅ ጨለማ” ውስጥ ናቸው፤ በሌላ አባባል በመንፈሳዊ ሁኔታ ወኅኒ ቤት ውስጥ ያሉ ያህል ነው።

ታዲያ ኢየሱስ “በእስር ላሉት መናፍስት” የሰበከላቸው መቼና እንዴት ነው? ጴጥሮስ እንደገለጸው ይህ የሆነው ኢየሱስ “መንፈስ ሆኖ ሕያው” ከሆነ በኋላ ነው። (1 ጴጥ. 3:18, 19) ጴጥሮስ “ሰበከላቸው” እንዳለ ልብ በል። እዚህ ላይ የተጠቀመው ግስ አላፊ ጊዜን የሚያመለክት መሆኑ ኢየሱስ የሰበከው ጴጥሮስ የመጀመሪያ ደብዳቤውን ከመጻፉ በፊት እንደሆነ ይጠቁማል። ከዚህ አንጻር ኢየሱስ ለእነዚህ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡራን የሰበከላቸው ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ይመስላል፤ ክርስቶስ ያወጀው መላእክቱ የተወሰነላቸውን ተገቢ የቅጣት ፍርድ ነው። የሰበከው መልእክት ተስፋ የሚሰጥ ሳይሆን ስለሚጠብቃቸው ፍርድ የሚገልጽ ነበር። (ዮናስ 1:1, 2) ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ በመሆን ትንሣኤ ማግኘቱ ዲያብሎስ በእሱ ላይ ምንም ኃይል እንደሌለው ያረጋግጣል፤ በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን የፍርድ መልእክት ለማወጅ ብቃት ይኖረዋል።—ዮሐ. 14:30፤ 16:8-11

ወደፊት ኢየሱስ፣ ሰይጣንንና እነዚያን ክፉ መላእክት አስሮ ወደ ጥልቁ ይወረውራቸዋል። (ሉቃስ 8:30, 31፤ ራእይ 20:1-3) እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን እነዚህ ያልታዘዙ መላእክት ድቅድቅ በሆነ መንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ እንዲቆዩ ተወስኖባቸዋል፤ በመጨረሻም መጥፋታቸው አይቀርም።—ራእይ 20:7-10